በእርግጥሰ ምዕራባውያን የዓለም ህዝቦች ነፃነታችውን ቢቀዳጁና ዲሞክራሲን ቢያሰፍኑ ደስተኛ ይሆናሉ ወይ ? ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አንድ ሰሞን ዳላስ ከተማ ተጋብዞ በኢትዮጵያውያን ፊት ላደረገው ንግግር የተሰጠ ትችታዊ ሀተታ!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሚያዚያ 9፣ 2023
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከምርጫ 1997 ዓ.ም ወዲህ ታዋቂ እየሆነ የመጣና፣ በተለይም እስር ቤት ውስጥ ሆኖ መጽሀፍ ለማሳተም በመብቃቱ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህም በላይ እሱ ይቆጣጠር በነበረው ኢሳት የሚባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እየተጋበዘ ይሰጥ የነበረው የቃለ-መጠይቅ ምልልስ ብዙ ዝናን አትርፎለት ነበር። በተጨማሪም በአውሮፓው አንድነትና በአሜሪካኖች የሚታወቅ ለመሆን በቅቶ ነበር። ለመታወቅም የቻለው እንደ አማራጭ መሪ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል ነው። ከዚህም በላይ በአሜሪካን የኮርፖሬት ዲሞክራሲ የሚያምንና ከእስር ቤት ከወጣና አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባደረገው ንግግር „ለምን እንደሆን አላውቅም የኢትዮጵያ ህዝብ አሜሪካንን ከልቡ ይወዳዋል“ በማለት የራሱን ውስጣዊ ፈላጎት በግልጽ ተናግሮ ነበር። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊን ጭንቅላት ወይም ልብ ከፍቶ እንደመረመረ ይመስል። በሌላ ወግን ግን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ህዝብ ያልተማረ በመሆኑና ትችታዊ በሆነ መልክም ማሰብ ስለማይችል ከዚህ በመነሳት የአሜሪካን ናፋቂ እንደሆነ የገባው አልመሰለኝም።
ከዚህ በመነሳት የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን የትግል ስልትና የሚሰጣቸውን ትንተናዎች የተከታተለ ሁሉ፣ ትንተናዎቹ የቱን ያህል ዕውነተኛውን የነፃነት ፈለግ የሚከተል መሆኑንና አለመሆኑን፣ ዲሞከራሲያዊ አስተሳሰቡም የቱን ያህል ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕውነተኛውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ያስችል አያስችል እንደሆነ፣ እስካሁን ድረስ ለውይይት ቀርቦ ክርክር ተደርጎበት አያውቅም። እንዲያው በደፈናው ሁሉም ካለምንም ውጣ ውረድ ዝም ብሎ ዐይኑን ጨፍኖ እንዲቀበልና እንዲያምነው ሆኗል። እንደምገምተው ከሆነ ዶ/ር ብርሃኑ ዝናናን ያተረፈውና ብዙ ተከታዮችም ለማፍራት የበቃው አብዛኛዎቹ ተከታዮች የሚያራምደው ፖለቲካና የሚያምንበት ርዕዮተ-ዓለም ስለገባቸው ሳይሆን ሰውየው ደልደል ያለ ስለሆነና ከሀብታም ቤተሰብ በመወለዱ ብቻ ነው። ተከታዮቹም የየራሳቸው የፖለቲካ ዕምነት ያላቸው እንዳይደሉ የኋላ ኋላ ግልጽ እየሆነ ለመምጣት ችሏል። አብዛኛዎችም ሰለፖለቲካና ሰለ ዕውነተኛ ነፃነት ግንዛቤ ያላቸው ሳይሆኑ፣ ልክ ባለፉት አምስት ዓመታት አቢይ አህመድን በጭፍን እንደሚከተሉትና እንደሚያምኑት ኢትዮጵያውያን ዐይነቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ምንም ሳይንሳዊ የፖለቲካ ዕውቀት ሳይኖርና የዕውነተኛ ነፃነትን ትርጉም ሳይገነዘቡ አንድን ግለሰብ በጭፍን ማመን ልክ ሂትለርን አብዛኛው ህዝብ አምኖት እንደተከተለውና የኋላ ኋላ መዘዝ ውስጥ የከተታቸው ዐይነት ነው። በሌላ ወገን ግን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሂትለራዊ አመለካከት ባይኖረውም የአሜሪካን አቀንቃኝ በመሆኑ ስልጣን ላይ ቢወጣ ደግሞ የአሜሪካኑን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን ፍርክስክሷን እንደሚያውጣት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ካለው አስተሳሰብም ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባ ሳይሆን ቴክኖክራሲያዊ ስርዓት በማዋቀር ወደ አምባገነናዊ አገዛዝ እንደሚሸጋገር መገንዘቡ ይህን ያህልም ከባድ አይሆንም።
2011 ዓ.ም የቱኒዚያውን ህዝባዊ እንቅስቃሴና የቤን ዓሊን ከስልጣን መባረር አስታኮ እርስ በርሱ የሚቃረን መግለጫ ከግንቦት ሰባት ተሰጥቶ እንደነበር ይታወቃል። በመግለጫውም መሰረት፣ እስካሁን ድረስ የቤን ዓሊን አገዛዝ በምዕራቦች፣ በተለይም በአሜሪካኖች ይደገፍ እንደነበር፣ የኋላ ኋላ ግን እንደተፉት ያብራራል። ግንቦት ሰባት የሚባለው እንቅስቃሴ በነበረበት ዘመን በመሪዎቹ አስተሳሰብና ዕምነት ይህ ዐይነቱ አምባገነኖችን የመደገፉና የማስታጠቁ ጉዳይ ኖርማል እንደሆነና፣ ምዕራቦችም የአገዛዙ ፀረ-ዲሞክራሲ ተግባርና ህዝብን ማፈን ተባባሪ እንዳልሆኑ ለማብራራት ሞክረው እንደነበር በጊዜው ይሰጡ የነበረውን መግለጫ ለተከታተለ ሊረዳ ይችላል። ሰለሆነም ይላል ዋና መሪ ሆኖ እንቅስቃሴውን ይመራ የነበረው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ከኛ የሚጠበቀው ነገር ተጠናክሮ መገኘትና ምዕራቦችን ወደኛ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ነው በማለት የእቅጩን ተናግሮ እንደነበር ዳላስ ላይ ተገኝቶ በሰጠው ማብራሪያ ያለውን ዕምነት ለማስረዳት ሞክሮ ነበር። ይህ አባባሉ አሁንም በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ይህንን ወይም ያኛውን ብሄረሰብ እንወክለዋለን ብለው ምንም የፖለቲካ ግንዛቤ ሳይኖራቸው የአሜሪካንን የኮንግረስ ሰዎችንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስተርን በሮች እንደሚያንኳኩት የዋህ ኢትዮዮጵያውያን ዐይነቶች የሚመሳሰል ነው። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም ሆነ እነዚህ አዲሶቹ የዋህ ኢትዮጵያውያን አሜሪካንን በመለማመጥና የእሱ ጭራ በመሆን በአገራችን ምድር ምን ዐይነት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም የሚችልና አገራችንን ጠንካራ የሚያደርግ ኢኮኖሚያሚዊ ስርዓት እንዴት ሊገነባ እንደሚችል ሲያስረዱን አይታይም። በሌላ ወገን ግን ሌላ አማራጭ ስለሌለን የነጭ ኦሊጋርኪ የሚለንን ከመስማትና እሱ የሚፈልገውን ተግባራዊ ማድረግና ኢትዮጵያን ተገዢ ከማድረግ ብቻ ነው ብለው በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ የመርዶ ያሰሙናል።
ለማንኛውም በጊዜው ይህንን በሚመለከት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ከሚቃወሙ ወይም ደግሞ ከእንቅስቃሴው ውስጥ ትችታዊ አስተያየት ወይም ደግሞ ማብራሪያ አልተሰጠም። የሚያሳዝነው ነገር አንድ ግለሰብ በራሱ ተነሳሽነት እንደዚህ ዐይነት በተለይም ወጣቱንም ሆነ ሰፊውን ህዝባችንን የሚያሳስት ዘገባ ሲሰጥ ለመተቸት የደፈረ ባለመኖሩ ነው። በእኔ ዕምነት ለዲሞክራሲና ለነፃነት፣ እንዲሁም ለሰፊው ህዝብ የተሻለ ኑሮ እታገላለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የመሰለ ሰው የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ በደንብ ሳያነብና ሳይመረምር እንደዚህ ዐይነት ሳይንሰ-አልባ ዘገባ ሲሰጥ ዝም ብሎ መታለፍ ያለበት ጉዳይ አልነበረም። በአንድ አገር ውስጥም ዕውነተኛ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊሰፍኑ የሚችሉትና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሊገነባ የሚችለው ከማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት የሚሰጥ አስተያየትም ሆነ ሰፋ ያለ ዘገባ በሚገባ ተመርምሮ ሲተች ብቻ ነው። ለማንኛውም ይህ ጉዳይ በአገራችን ምድርም ሆነ ውጭ በሚገኝው ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ ባለመሆኑ አንድ ዝናን የተጎናጸፈ ሰው አጠቃላይ የሆነ የፖለቲካ ንግግር ሲያደርግ ዝም ብሎ አዳምጦና አጨብጭቦ ይወጣል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ ለተሟላ ዕድገትና ለዕውነተኛ ነፃነት የሚያመች አቅይደለም። ያለንበት ዘመን 21ኛ ክፍለ-ዘመን ስለሆነ በተለይም አገርንና ህዝብን በሚመለከት አንድ ሰው የተወላገደ አስተሳሰብ ሲያቀርብ ዝም ብሎ የማየት መብት የለንም። ዝም ብለን የምናልፍ ከሆነ ደግሞ የታሪክ ወንጀል ሰርተን ነው የምናልፈው ማለት ነው። በተለይም የአውሮፓን የካፒታሊዝምን ዕድገት ለተከታተለ በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ያሉት የጠለቀ ዕውቀት የነባራቸው ፈላስፋዎችም ሆነ የተፈጥሮ ሳይንስና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የሶስዮሎጂ ምሁራን በመሀከላቸው ክርክር ሳይደረግ ዝም ብሎ የታለፈበት ጊዜ አልነበረም። ስለዚህ ነው ፕሌቶ የሚባለው ታላቁ የግሪኩ ፈላስፋ አንድን ነገር ዝም ብሎ በጭፍን ከመቀበል በፊት ደጋግሞ በማንበብና በመራዳት ትክክለኛ ፍርድ ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብሎ የሚያስተምረን። አንድ አነጋገር ወይም ጽሁፍ ለመመርመር ደግሞ ዲያሌክቲክ፣ በጊዜው እየመላለሱ መጠየቅና የኋላ ኋላ ሄግል ያዳበረው የመመርመሪያ መሳሪያ በጣም ጠቃሚ ነው።
ከረጅም ዓመታት በፊት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ዳላስ ከተማ ላይ ለሁለት መቶ ያህል ኢትዮጵያውያን ባደረገው ንግግር ልክ ግንቦት ሰባት ላይ ተሰጥቶ የነበረውን ዐይነት መግልጫ የሚመስል ሀተታ አቅርቦ ነበር። በዶክተር ብርሃኑ ነጋ አገላለጽም “ምዕራባውያን የዓለም ህዝቦች ነፃነታቸውን ቢቀዳጁና ዲሞክራሲን ቢያሰፍኑ ደስተኞች ይሆናሉ“ በማለት እቅጩን ተናግሮ ነበር። በመቀጠልም፣ „ሆኖም ግን ከሌሎች አገራት ህዝቦች ነፃነት የራሳቸውን ደህንነት ያስቀድማሉ።“ በማለት ዕምነቱን ገልጾ ነበር። ይቀጥልና „ለነፃነታችን በምናደርገው ትግል የዲሞክራሲያዊ አገሮችን ድጋፍ ለማግኘት መሬት ላይ ያለው ሁኔታ መቀየር እንዳለበት ቱኒዚያም ሆነ ግብጽም አረጋግጠውልናል“ በማለት አዲስ ቲዎሪና ታሪክ ለማስተማር ሞክሮ ነበር። ከ12 ዓመታት የጥቢው አብዮት ፈነዳ ከተባለ በኋላ ዛሬ ቱኔዚያም ሆነ ግብጽ ያሉበትን ሁኔታ መመልከቱ በቂ ነው። ቱኒዜያ በኢኮኖሚ ቀውስ የምትታመስ አገር ስትሆን፣ ግብጽ ደግሞ በጃጁና ሁሉን ነገር በሚቆጣጠሩ በሲሲ ቀዳሚነት በሚሊታሪ ሰዎች የምትሰቃይ አገር ነች። በግብጽ ምድር ሲሲንም ሆነ የተቀረውን የሚሊታሪ ሰዎች መቃውም እስር ቤት ውስጥ ያስከትታል። በዚህም የተነሳ የተገለጸላቸው ግብጻዊ ምሁራን አገራቸውን ጥለው ለስደት ሲዳረጉ፣ ሌሎች ደግሞ በእስር ቤት ውስጥ የሚማቅቁ ናቸው። ታዲያ ምኑ ላይ ነው ቱኔዚያም ሆነ ግብጽ ውስጥ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ የተቀየረው? ይህንን ጥያቄ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንዲመልስልን ጥያቄ አቀርብለታለሁ።
በሌላ ወገን ደግሞ ዶክተር በርሃኑ ነጋ እንደሚለንና ሁላችንም እንደምናውቀው፣ አብዛኛዎቹ እነዚህ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት የፀረ-ሽበርተኝነት አጋዥ ስለነበሩ ከአሜሪካም ሆነ ከተቀረው የምዕራብ አውሮፓ መንግስታት ጋር በጥብቅ መስራታቸው ብቻ ሳይሆን ህዝባቸውን ለመጨቆን የሚያገለግላቸውን የጭቆና መሳሪያዎች ከአሜሪካን ያገኙ እንደነበር በግልጽ ያትታል። በገጽ አራት ላይ፣ „ እነዚህ አገሮች በፀረ-ሽብር ትግል የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት አገሮች አጋሮች የሆኑ፣ በዚህም ምክንያት የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት እንክብካቤና ጥበቃ ያልተለያቸው ናቸው ። በተለይም ሙባራክ የአሜሪካ ሁነኛ ወዳጅ መሆኑ የአሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያገኝ የነበር ከግብጽ ይልቅ ለአሜሪካ ጥቅም የቆመ ሰው ነበር።“ በማለት እቅጩን ይነግረናል። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ አሜሪካንም ሆነ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ሌሎች አገሮች ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲኖራቸውና ነፃ እንዲሆኑ ከፈለጉ ለምንስ እነዚህን ከመሳሰሉት ዲሞክራሲን ከሚያፍኑና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይኖር ህዝባችውን እረግጠው ከያዙ አምባገነናዊ አገዛዞች ጋር የፀረ-ሽብርተኛ አጋዥ ስለሆኑ ብቻ አብረው መስራት እንደተገደዱ ነው ? በነዚህ አገሮች ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ቢኖርና ህዝቦቻቸውም የተደላደለ ኑሮ ቢኖሩ ኑሮ ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ይኸኛው ቀናው መንገድ የተሻለ አይሆንም ነበር ወይ? በህብረተሰብ ሳይንስ እንደሚታወቀው አንድ ህብረተሰብ ሁሉ ነገር ከዘጋጀለት፣ የስራ መስክ በበቂው ከተከፈተለት፣ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ኖሮት ሃሳቡን መግልጽ የሚችልና በአገር ግንባታ ውስጥ በቀጥታ የሚሳተፍ ከሆነ ወደ ሌላ መጥፎ ተግባር እንደማያመራ ነው። ታዲያ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በልዩ ልዩ የምሁር ችሎታ ቀድመውና ተራቀው የሄዱት አሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በእንደዚህ ዐይነቱ ህዝብን አደንቁሮና አድኸይቶ በሚያስቀር ተግባር ውስጥ ምን አሳተፋቸው? አንድ አገርስ ደኽይቶና ተዳክሞ ቢኖር ምን ጥቅም ያገኛሉ? ከኢኮኖሚ ስሌትስ አንፃር የአንድ አገር ህዝብ የመግዛት ኃይሉ ጠንካራና የውጭን አገር ምርት ገዝቶ ለመጠቀም የሚችለው ሰፊው የህበረተሰብ ክፍል የመግዛት አቅሙ ከፍ ያለ ከሆነ አሜሪካንም ሆነ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ለዕቃዎቻቸው ሰፊ ገበያ አያገኙም ወይ? አንድ አገርስ የኛን ጥቅም ታስጠብቃለች ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? እንደዚህ ዐይነቱ የአሜሪካንም ሆነ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከአምባገነን መንግስታት ጋር እጅና ጓንቲ ሆኖ አብሮ መስራት አንድን አገር ከማዳከምና ከማደኽይት ስትራቴጂ አንፃር ተነጥሎ ሊታይ ይችላል ወይ? እነዚህን የመሳሰሉት አገሮች ጥሩ ድጋፍ ቢያገኙና ኢኮኖሚያቸውም ቢያድግ ወደ ፊት እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዛሬ ደግሞ ቻይና ሌላ ተቀናቃኝ አገሮች ሊነሱብን ይችሉ ይሆናል ብለው በመገመት አይደለም ወይ? ድርጊታቸውን ወደ ጦርነትና ወደ ሌላ የህዝቦቻቸውን አስተሳሰብ ወደሚበታትን አቅጣጫ የሚመሩት? እንደዚህ ዐይነቱንስ አሳሳች ፖለቲካ መከትል የአሜሪካንና የምዕራብ አውሮፓ ዋናው ስትራቴጂያቸው አይደለም ወይ? ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እነዚህን የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንስቶ ቢያነጋግረንና ቢያወያየን ኖሮ ለትግላችን ስልት የሚሆንን መንደርደሪያ ሊሰጠን ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ። ይሁንና አንድም ቦታ ላይ ማብራሪ አልሰጠም። በሌላ ወገን ግን ከዶ/ር ብርሃኑ የህይወት ታሪክም ሆነ ከዚሁ ዐይነቱ መግለጫ መረዳት የሚቻለው በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ተከታዮችን ያፈራው ምሁር ነኝ ባይ ሰለካፒታልዝም ዕድገትና ስለ ኢምፔሪያሊዝም ምንነት እንዳልተከታተለና እንደማያውቅም ነው መገንዘብ የሚቻለው። ስለሆነም የኢኮኖሚክስ ምሁር ነኝ ባዩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስር በተዋቀረው የኃይል አሰላለፍ መሰረት በተለይም የአፍሪካ አገሮች ለመማቀቅ እንደቻሉና ስርዓት ያለው ህብረተሰብ መገንባት እንዳልቻሉ በደንብ የተከታተለ አይመስለኝም። በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በማዕከለኛውም ሆነ በደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ በስድሳኛውን በሰባኛው ዓ..ም በ20ኛው ክፍለ-ዘመን የተነሱት አምባገነን አገዛዞች በሙሉ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተደገፉና፣ የሚሊታሪ ሰዎችም በአሜሪካን የሚሊታሪ ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑና ለብዙ መቶ ሺሆች ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች መገድል ተጠያቂ ለመሆናቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በደንብ የተከታተለ አይመስለኝም። ታዲያ ይህን ጉዳይ በደንብ ያልተከታተለ ከሆነና፣ ይህንን አስመልክቶ ምርምራዊ ጽሁፍ ካላወጣ ለምን ዐይነት ዲሞክራሲ ነው የሚታገለው? ይህንን ያላደረገ ምሁር ነኝ ባይስ እንዴት ተደርጎ ነው ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮችን በጊዜው ሊያፈራ የቻለው? ጉዳዩ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳስብም ነው። ምክንያቱም በዚህ ዐይነቱ የተወላገደና ምሁረ-አልባ አስተሳሰብ ነው እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ከድጡ ወደ ማጡ በመሽ´ጋገር ነው ህዝቦቻቸው ደኽይተውና አቅጣጫው ጠፍቶባቸው ድረግ እንደወሰደ ሰው ወዲህና ወዲያ እያሉ የህይወትን ጣዕም ሳይረዱ የሚያልፉት።
ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ስንመጣ የካፒታሊስት አገሮች የዓለም ህዝብ ዲሞክራሲን ቢጎናጸፉና ነጻነትን ቢቀዳጁ ደስታውን አይችሉትም የሚለው፣ ምን ዐይነት ዲሞክራሲን እንደሚመኙልን ግልጽ አድርጎ አላስቀመጠም። የነሱን ዐይነት ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ነው የሚለን ከሆነ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደራቸው እንዲሁ በፎርማል ደረጃ የሚገለጽ ቢሆንም የምዕራቡ ዲሞክራሲ የተወሰነ የህብረተሰብን ግኑኝነትና የኃይሎችን አሰላለፍ የሚገልጽ ነው። ዲሞክራሲውም ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌለበት የውክልና ዲሞክራሲ ነው። ልክ አስራስምንት ዐመት ዕድሜ ያልሞላው ወጣት በምርጫ ጊዜ ድምጽ በመስጠት መሳተፍ እንዳማይችል ሁሉ የውክልና ዲሞክራሲ ተመርጠናል፣ የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን በሚሉ ተመራጮች እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ማንኛውም ነገር በመራጩ ህዝብ ላይ የሚጫንበትና እንዲቀበለው የሚደረግ ነው። እንደሚታወቀው ይህ ዐይነቱ የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ በታሪክ ውስጥ ሌሎች አማራጭ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቶችን እየተቀናቀነ በመውጣት የከበርቴውን መደብ የበላይነት ለማረጋገጥ የታቸለበትና በመሰረቱ እንደ ግል ሀብት የመሳስሉትን ህጋዊ በማድረግ ህብረተሰቡ ይህንን አምኖ እንዲቀበል የተደረገበት ነው። እንደሚታወቀው በአብዛኛዎች የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የግል ሀብት ወይም መሬት የለውም። አብዛኛው መሬትና ቤቶችም ጭምር በጥቂት ግለሰቦችና ኩባንያዎች የተያዙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ባንኮችና በመዋዕለ-ነዋይ ስም ገንዘብ ከሀብታሞች በመሰብሰብ ገንዘብን በሚያስተዳድሩ እንደነ ብላክ ሮክስ በመሳስሉ የአሜሪካ ትላልቅ ኩባንያዎች ነው። በሌላ ወገን ግን የምዕራቡ ካፒታሊስት ዲሞክራሲ የዛሬው የዕደገት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው እየወደቀና እየተነሳ፣ በተለያዩ ኃይሎች መሀከል በሃሳብም ሆነ በጉልበት ግብግብ ከተፈጠረና ቀስ በቀስ ህብረተስብአዊ መረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ ነው። ለዚህ ደግሞ ከ13ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ጭንቅላትን ለአዳዲስ አስተሳስቦች ክፍት ያደረገ አስተሳሰብ፣ በተለይም በሰው ልጅ ሚና ላይ ያተኮረና በሰው ልጅና በተፈጥሮ መሀከል ያለውን ግኑኝነት የሚመረምር ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በመካሄዱም ጭምር ነው። በተለይም በሬናሳንስ አማካይነት የተፈጠረው ከተማዎችን መገንባት፣ የንግድ ተግባር ከዕደ-ጥበብ ጋር በመያያዝ የህብረተሰቡን አትኮሮ መሰብሰብና ጥልቀት እንዲኖረው ማድረግ፣ ይህንን ከጥንታዊ ሙዚቃና ስዕል ጋር በማገናኘት ወደ ህብረ-ብሄር ግንባታ ለመሽጋገር የተቻለበት ነው። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የውጣ ውረድ ጉዞ ዕውነተኛውን በስብአዊነት ላይ የተመረኮዘውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓትም እየተቀናቀነ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። በተለይም የኢምፕሪሲስቶች የነፃ ገበያና የነፃ ንግድ እንደ ዋና የኢኮኖሚ ግንባታ መርሆች ሆነው ተቀባይነት እንዲኖራቸው ከተደረጉ ወዲህ የፎርማል ዲሞክራሲ በብዙ የአውሮፓ አገሮች ተቀባይነትን እያገኘና ብዙ ነገሮችን እያጣመመ ለመምጣት እንደቻለ መረዳትም ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ የዛሬው የከብርቴው ዲሞክራሲ በአንድ ኃይል በችሮታ የተገኘ ሳይሆን የትግል ውጤት ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን ባህርዩን ሊለውጥ ችሏል። በመጀመሪያ ግን መሰረቱ በራሱ በከበርቴው መደብና በመንግስት የተነጠፈ ሳይሆን፣ ለለውጥ በሚታገሉ በተለያዩ ምሁራን አማካይነት ነው። የከበርቴው መደብ ግን የፊዩዳሉን መደብና አሪስቶክራሲውን ለመዋጋት ሲል የግንባር ቀደምትነትን ሚና በመውሰድ ኢንስቲቱሽናዊ ሪፎርሞች ማድረግ ጀመረ። ይህ ዐይነቱ ዲሞክራሲ ተቀባይነትን ካገኘም በኋላ በተለይም የኢኮኖሚ ኤጀንቶች ርስ በራሳቸው በሚያደርጉት ትግልና በመንግስቱም መኪና ላይ በሚያካሄድት ተፅዕኖ ባህርዩን እየለወጠ ሊመጣ ችሏል። ህግን የሚያረቀውና ህግን ተግባራዊ የሚያደርጉት ሙሉ በሙሉ በሎቢስቶች የተገሰገሱና ለራሳቸው በሚስማማ መልክ ህግንም ለማውጣት የደረሱበት ደረጃ እንዳለ ሁኔታዎችን ለሚከታተል ግልጽ ነው። በዘመነ ኒዎ-ሊበራሊዝምና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመንም የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ ውስንነቱን እያረጋገጠ ለመምጣት ችሏል። በተለይም ይህ ጉዳይ በአሜሪካን ምድር ግልጽ ነው። ይህም ማለት የሰው ልጅ ነጻነት በከፍተኛ ደረጃ በጥያቄ ውስጥ እየገባና የተለያዩ ምክንያቶችን እያሳበቡ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየተሽረሸሩ በመምጣት ላይ ናችው።
የፓርቲዎችን አደረጃጀትና የፖለቲካ መስመር ስንመለከት ደግሞ፣ በተለይ የሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎችና የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች እንደስማቸው ሳይሆን በአማዛኙ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠረውን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ነው የሚያስጠብቁት። ለምሳሌ የሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ሜዳው ነፃ ነው፣ ማንም ሰው እንደችሎታው መታገል ይቸላል፣ እንደአስትዋጽዖውም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያገኛል ቢሉና ቢሰብኩም፣ የኢኮኖሚው ሜዳ እነሱ እንደሚሉት ክፍት አይደለም። አንድ ሰው ሊሰራ የሚችለው ስራ ሲያገኝ ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ በሚያወጡት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዛኛውን ጊዜ የኢንዱስትሪና የፊናንስ ኦሊጋርኪዎችን ጥቅም አጉልቶ የሚያሳይና ተግባራዊ የሚያደርግ ነው። ለምሳሌ በቀረጥ ቅነሳ ፖሊሲ አማካይነትና በድጎማ መቀነስ ሀብት ከታች ወደ ላይ እንዲሽጋሽግ በማድረግ ሰፊውን ህዝብ ወደ ድህነት ይገፈትራሉ። እንደዚሁም የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲዎች እንደስማቸው እኩልነትና ሰብአዊነትን የሚያራምዱ ሳይሆን በስሙ በመነገድ እኩልነት እንዳይኖር እገዳ የሚያደርጉ ናችው። እነሱም ልክ እንደ ሊበራል ዲሞክራቶች በቀረጥና በተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የሀብት ክፍፍል እንዲዛባ በማድረግ የሰፊውን ህዝብ ሞራል እያዳከሙ ነው። በተለይም በትምህርት ፖሊሲ ላይ የሚያካሂዱት ግልጽና አድልዎ የተሞላበት ፖሊሲ የታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ጥሩ ቦታ እንዳይኖረው እያደረጉ ነው። ለምሳሌ ወጣቶች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከስድስተኛ ወይም እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነው የመማር ዕድል ያላቸው። በተለይም ከሰራተኛው የህብረተስብ ክፍል የመጡ ስድስተኛ ክፍል ከደረሱ በኋላ በመጣራት ወደ ታች ቀጭጨው እንዲቀሩ ይገደዳሉ። እንክብካቤ ማግኘት የሚችሉ ህጻናትና ወላጆቻችወ ሀብታም የሆኑ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የመማር ዕድል አላቸው። የስራ ዕድልና የማኔጀር ፖስት ማግኘት የሚችሉት ከሰራተኛው ህብረተስብ የፈለቁ ሳይሆኑ፣ ከላይኛው ህብረተስብ ክፍል የመጡ ናቸው። በቅርቡ በሰፊ ተመርምሮ በወጣ መጽሀፍ ህብረተስቡ በጠበቀ ሂራርኪ የተደራጀ ስለሆነ ከፍተኛ ትምህርት ተምሮ ጥሩ ስራ ሊያገኝ የሚችለው ከከብርቴው፣ ከጠበቃና ጥሩ ገቢ አላቸው ከሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ነው። በሌላ ጥናት ደግሞ፣ ፓርቲዎች ከውጭ ሆነው በተደራጁ ጠበቃዎችና የኢኮኖሚክስ አማካሪዎች የተተበተቡ ሲሆን፣ አማካሪዎቹም የተወሳሰበ ሞዴል በማውጣት የቱን ያህል ሀብት ያለውን እንደገና ሀብታም እንደሚያደርጉት ነው። አሜሪካ ደግሞ ከዚህ የባሰ ነው። የኮርፖሬቶች ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግበትና ሁለቱም ፓርቲዎች ካለኮርፖሬቶች ፍላጎት አንድም ሜትር ፈቀቅ ማለት አይችሉም። ሰሞኑን በቀረበ ስፊ የሬዲዮ ሀተታ እያንዳንዱ ፓርሊሜንቴሪያን ለምሳ ወደ ምግብ ቤት በሚሄድበት ጊዜ ለምግብና ለመጠጥ መክፈል እንደሌለበትና፣ ቢሉም ቀድሞ ተከፍሎ እንደሚጠብቀው ነው። በሀተታውም መሰረት ጋባዦቹ ሄጅ ፈንድስ፣ ኢንቬስትሜንት ባንኮችና የዎል ስትሪት ማኔጀሮች ናችው። ለእያንዳንዱ ፓርሊሜንቴሪያን እስከ ዘጠና ዶላር ድረስ ወጪ ይደረግለታል። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ሊነግሩን እንደሚፈልጉት ፓርቲዎቹ ከአድልዎ ነጻ የሆኑ አይደሉም። እንደዚህ ዐይነቱ የሎቢስቶች ስራ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ይዞ በመምጣትና የሶስተኛውን ዓለም አገሮች ኤሊትን እየተበተበ በመምጣት ለዕድገትና ለዲሞክራሲ ማበብ እንቀፋት በመሆን ላይ ይገኛል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የፊናንስ ካፒታል እጅግ በጠናከረበት ጊዜና ከሚሊታሪና ከኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ጋር በተሳሰረበት ወቅት የሶስተኛ ዓለም መንግስታት መሪዎች በልዩ ልዩ ጥቅሞች በመታሰር የዚህ ዐይነቱ የአገዛዝ ሰንሰለት አካል በመሆንና ጦርነትን ፈልፋይ እንዲሆኑ በመገደድ ለሰላምና ለዕድገት ዕንቅፋት ሆነዋል። ከዚህ ስንነሳ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ምን ዐይነት የሊበራል ዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማራመድ እንደሚፈልግና ምን ዐይነትስ ዕርዳታ ከምዕራቦች ማግኘት እንደሚችልና እንደሚጠብቅ ግልጽ አድርጎ አላስቀመጠልንም።
በአገሮች መሀከል የተደረገውን ፍክክርና ተንኮል ስንመለከትም በመሀከላቸው መደጋገፍና መረዳዳት እንዳልነበረ መገንዝብ እንችላለን። በምዕራቡ ካፒታሊስት የትግል ታሪክ ውስጥ ቀድሞ የሄደው አንደኛው አገር በሌላው ላይ የራሱን የበላይነት ለማስፈን ትግልም ያካሄድ ነበር። በተለይም በሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብና በኢንዱስትሪ ግንባታ ቀድማ የሄደችው እንግሊዝ ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የሷን ፈለግ እንዳይከተሉ አሻጥሮች ትሰራ ነበር። በተለይም የነፃ ንግድን ቲዎሪንና ዓለም አቀፋዊ የስራ-ክፍፍልን በማዳበርና ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ ሌሎች አገሮች በእርሻ ምርትና በሌሎች ጥሬ ሀብቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የዕድገታቸውን አቅጣጫ ለማዛነፍ የማታደርገው ጥረት አልነበረም። በተለይም በጀርመን በኩል የፍልስፍና እንቅስቃሴ እያየለ በመምጣቱ የእንግሊዙን የኢምፕሪሲስቶች መንገድ እስከተወሰነም ደረጃ መቋቋም ተችሏል። እነላይብኒዝና በኋላ ደግሞ ፍሪድሪሽ ሊስት የእንግሊዙ የኢምፕሪሲስቶችን ቲዎሪና የነፃ ንግድ ፍልስፍና እንዳይገባ አጥብቀው የታገሉና ለጀርመን ሳይንስና የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ናቸው። ይህም ማለት በየአገሮች ውስጥ የተነጠፈው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከውስጥ የመጣና በትግል የተደረሰበት እንጂ አንድ በዕድገት ቀድሞ የሄደ አገር በሌሎችም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር ሰለፈለገና ለማገዝም ፈቃደኛ ስለሆነ አይደለም። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የካፒታዝምን ዕድገትና በተለያዩ ምሁራን ዘድን ይደረግ የነበረውን ክርክር በደንብ የተከታተለና ያጠና ቢሆን ኖሮ ሰለ ምዕራቡ የካፒታሊስት ዲሞክራሲ የተሻለ ግንዛቤ ባገኘ ነበር።
ወደ ኢትዮጵያና ወደተቀረው ሌላው የአፍሪቃ አገሮች ስንመጣ፣ የምዕራብ አውሮፓ የዲሞክራሲያዊ አጋዥነት በቀጥታ የራስን ጥቅም ከማስጠበቅና እነዚህን አገሮች ተቀጥያና ደካማ ሆነው እንዲቀሩ ከማድረግ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። ይህም ማለት በምዕራብ አውሮፓ የሚደገፈው የዲሞክራሲ ስርዓት አገነባብ ውስንነት ያለውና ወደ ዕውነተኛው ነፃነትም በፍጹም ሊያመራን አይችልም። ምክንያቱም በተለይም ባለፉት አርባ ዓመታት እንደተከታተልነው ከሆነ የካፒታሊስት አገሮች ሰለ ዲሞክራሲ ሲያውሩ ከኒዎ-ሊበራል አጀንዳ ጋር ስለሚያያይዝና በተወሰነ ኤሊት አማካይነት እነሱ የሚፈልገትን ዲሞክራሲ ከበላይ ለመጫን ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ዕውነተኛና መሰረታዊ ለውጥ ሳይመጣ የተግማማው ስርዓት በዚያው የሚቀጥልበትን ሁኔታ ነው ነው የሚፈልጉት። ጥቅማቸውንም ለማስጠበቅ የሚችሉት አምባገነናዊና ያልተገለጸለት አገዛዝ ብቻ ስልጣንን ሲቆናጠጥ ብቻ ነው። አንገቱን ደፍቶ እሺ የሚላቸውንንባ ሰፊውን ህዝቡን ተዳክሞ እንዲቀር የሚያደርግላቸውን አገዛዝ ነው የሚፈልጉት። ይህ ዐይነቱ ዲሞክራሲ ደግሞ ሰፊውን ህዝብ የሚያገልና የሳይንስና የቴክኖክሎጂን ተግባራዊነት የሚቀናቀን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም የበላይነትን ለማስፍን የሚደረግ ትግል ስለሚካሄድ አሜሪካም ሆነ ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊት አገሮች በአፍሪካ ምድር ውስጥ ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይመሰረት የፈለጉትን ነገር ከማድረግ አይቆጠቡም። በተለይም በአገራችን ምድር ህወሃት ስልጣን ላይ እንዴት ለመውጣት እንደቻለና ከዚያስ በኋላ የተከተለውን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ፖሊኢ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። ህወሃት ከስልጣን ላይ ከተወገደ በኋላ ስልጣንን የያዘው የአቢይ አህመድ ቡድን የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምን ጥቅም የሚያስጠብቅና አገርን የሚበታትን ነው። ለዚህም ነው ዶላር በየጊዜው የሚጎርፍለትና የአሜሪካኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አንቶኒ ብሊንከን አዲስ አበባ በመምጣትና ቤተ-መንግስት ውስጥ በመጋበዝ ትዕዛዝ የሚሰጠው። ሰለዚህም የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮችና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአገራችን ምድር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ቢሰፍን ደስታውን አይችሉትም የሚለው አባባል ከታሪክና ከህብረተስብ ዕድገት ጋር፣ እንዲሁም ከዓለም የፖለቲካ አወቃቀር ጋር እየተነፃፀረ የቀረበ አይደለም። የቀረውን ትተን፣ በተግባርም እንደታየውና በተለይም የስድሳ ዐመቱን የምዕራቡን ካፒታሊስት ዓለም፣ ´ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ ስንመለከት በአፍ ልፍፋና በተግባር መሀከል የምድርንና የስማይን ያህል ልዩነት እንዳለ መገንዝብ ይቻላል።
ከ1945 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረው አዲስ የኃይል አሰላለፍና የኢኮኖሚ አወቃቀር በተለይም አፍሪካውያንና ሌሎች የሶስተኛውን ዓለም አገሮች በኢንዱስትሪ እንዳያድጉና የሳይንስና የቴኮኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆኑ ቆልፎ ይዟቸዋል። በተለይም ኢኮኖሚክስ ቲዎሪ ከአዲሱ የኃይል አሰላለፍ ጋር በማቀናጅት ብዙ የሶስተኛውን ዓለም ኤሊት ለማሳሳት ችለዋል። በቲዎሪዉም መሰረት የነፃ ንግድ የታሪክና የኃይል አሰላለፍ ለውጥ ውጤት ሳይሆን ተፈጥሮአዊና ማንኛውም አገር ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ነው። የሰው ልጅ ዕድል ሁሉ በነፃ ንግድና በነፃ ገበያ አማካይነት ብቻ ነው የሚወሰነው። በተጨማሪም እያንዳንዱ አገር ባለው የጥሬ-ሀብት አማካይነት ብቻ ነው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ሊጎናጸፍ የሚችለው። ስለሆነም በዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍል መሰረት፣ ለምሳሌ አፍሪካ ለዓለም ገበያ የጥሬ-ሀብት ብቻ ነው ማቅረብ ያለባት። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ዕድገትን ልትጎናጸፍ የምትችለው። ይህንን ርዕዮተ-ዓለም ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ እንደ አይ ኤም ኤፍ፣ እንደ ዓለም ባንክና እንደ ዓለም የንግድ ድርጅት ተቋቋመዋል። በእነሱ አማካሪነትና ገፋፊነት አፍሪካና ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው። ይህ ዐይነቱ ምክር እያደገ መጥቶ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ብዙ የአፍሪካ አገሮች የተቅዋም ማስተካከያ ወይም የኒዎ-የኒዎ ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ፣ በአንድ በኩል በዕዳ ሲተበተቡ፣ የውጭ ዕቃ ማረጋፊያ ሲሆኑና በተወሰነ ምርት ላይ ሲረባረቡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ወደ ውስጥ ኢኮኖሚያቸው የባሰውን እንዲደቅ፣ ድህነት እንዲስፋፋና በዚያው መጠንም በደሀና በሀብታም መሀከል ያለው ለዩነት የባሰውን እንዲስፋ ለመሆን በቅቷል። ብዙ ጥናቶችም እንደሚያመለክቱት እንደዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ ሆን ብሎ እንደተዘጋጀና መሪዎችና የተቀረውንም ኤሊት ዐይኑን ጨፍኖ እንዲቀበለው ለመሆን የበቃ ነው። ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው ምሁራን እንደሚሉን ከሆነ ብዙዎች የአፍሪካ ኤሊቶች የተወሳሰበውን የካፒታሊስቱን ሞዴል ያልገባቸው ብቻ ሳይሆን፣ በኔዎ-ሊበራሊዝም ሽፋን ስር የሚተበተበውን ተንኮል ለመረዳት አልቻሉም ነው የሚሉን። እነዚህ ምሁራንም በትክክል እንደሚነግሩን፣ በአፍሪካ ምድር ውስጥ ዕውነተኛና ሰፋ ያለ የምሁር እንቅስቃሴ ሊዳብር አልቻልም፤ በዚህም ምክንያት ዕውነትን ከውሽት በዲያሌክቲክ መነጽር መለየት አይችሉም የሚል ነው። ስለሆነም የአፍሪካን ኤሊት ለማወናበድና የአፍሪካን ህዝብ ኑሮ በየጊዜው በሚወጡ ሞዴሎችና ፖሊሲዎች ህይወታቸው ትርጉም እንዳይኖረው ማድረግ ይቻላል። እንግዲህ አንድ አገር በኢኮኖሚ ራሷን ካልቻለች፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂም ባለቤት መሆን ዕድል ከሌላት እንዴት ነው ዲሞክራሲያዊን ስርዓት ልትገነባ የምትችለው? የምዕራቡስ ዓለም በሆነው ባልሆነው አሻጥር የሚሰራ ከሆነ እንዴትስ የዲሞክራሲ ስርዓት አጋዥ ሊሆን ይችላል? የማይገባኝ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሎጂክ!
የስድሳ ዓመቱን የአሜሪካንንም ሆነ የምዕራብ አውሮፓን የውጭ ፖለቲካ ለተከታተለ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ምድር በኮሙኒዝም ስም እያሳበቡ ጣልቃ መግባትና በኩዴታ አማካይነት ለነሱ የሚስማማ ሰው ስልጣን ላይ በማውጣት ዲሞክራሲያዊና ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማገድ ነው። ከኮንጎ ዛየር ሞቡቱ እስከ ዩጋንዳው ኢዲያሚን ድረስ የተደረገው የመንግስት ግልበጣ የሚያረጋግጠው በነዚህ አምባገነኖች አማካይነት ከውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳያብብና ራሱን ያወቀና በራሱ የሚተማመን ከበርቴያዊ መደብ ብቅ እንዳይል ለማድረግ የተካሄደ አሻጥር ነው። በተለይም በመንግስት የስለላ አፓራተስ ውስጥ ሰላዮችን በማስቀመጥና በቢሮክራሲው ውስጥ ለነሱ የሚስማማ ፖሊሲ አውጭ በማፍራት ወይም እንዲገባ በማድረግ አጠቃላዩ የመንግስት ፖሊሲ እንዲኮላሽ ያደርጋሉ። የማይሆን ምከር በመስጠትም ሆነ በማስገደድ ወደ ውስጥ ያተኮረ ዕድገት እንዳይካሄድ ያደርጋሉ። በራሱ በሲ አይ ኤ ሰው በጆን ፐሪኪን የተደረሰው Confession of an Economic Hit Men የሚባለው መጽሀፍ ይህንን የምዕራቡን ተንኮል ነው የሚያጋልጠው። ሌሎችም አያሌ መጽሀፎችና ማረጋገጫዎች አሉ። ከብራዚልና እስከቺሌ፣ እንዲያም ሲል እስከ አርጀንቲና ድረስ በስድሳኛውና በሰባኛው ዓ.ም ኮሙኒዝምን ለመዋጋት በሚል የተካሂደው ዘመቻና የመንግስት ግልበጣ በእርግጥም ኩሙኒዝምን ለመዋጋት ሳይሆን በአነዚህ አገሮች ውስጥ የኢንዱስትሪ አብዮት እንዳይካሄድና የከበርቴ መደብ ብቅ እንዳይል ለማድረግ ነው። ሰለሆነም በአሜሪካን የሚሊታሪ ሳይንስና በሚልተን ፍሪድማን ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ የሰለጠኑ ሰዎች ስልጣንን እንዲቀዳጁ በማድረግ ህብረተስቡን ማከረባበት ገቡ። ፋሺስታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የአሜሪካንን የፊናንስ ኦሊጋርኪ ጥቅም ተግባራዊ ማድረግ ቻሉ። እነዚህን አገሮች በዕዳ በመተብተብና አንጀት አጥብቅ የሞኔተሪ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ፣ በአንድ በኩል በወለድና የወለድ ወለድ ክፍያ አማካይነት ሀብት ወደውጭ እንዲወጣ አደረጉ፤ በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪዎች መዳከም የተነሳ የአገር ውስጥ ገበያ እንዳያድግ ሆነ። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በላቲን አሜሪካ የፈጸመውን ወንጀል በሚመለከት ብዙ የአሜሪካ ምሁራን በሰፊው ጽፈዋል። የእነሱን መጽሀፍ ላገላበጠና ሁኔታውን በጥብቅ ለተከታተለ በቂ ማስርጃ ሊያገኝ ይችላል። ከሃምሳኛው ዓ.ም ጀምሮ ሲአይ ኤ ለአሜሪካን የማይስማሙ ስዎችን በመግደልና ውሽት በማውራት የሚያደርገውን ወረራ በዶኩሜንተሪ ፊልም ተዘጋጅቶ ታይቷል። በአገራችንም በአፄ ሃይለ ስላሴ ዘመን የተካሄደው ትግል ከላይኛው ጋር ሲመዛዘን የሚያንስ ቢመስልም ዋናው ዓላማው ኢትዮጵያን አቀጭጮ ማስቀረት ነው። በደርግ ላይም የተካሂደው ዘመቻ የምዕራቡ ዓለም ሊያሳምነን እንደሚሞከረው ኮሙኒዝምን በእንጭጩ ለመቅጨት ሳይሆን፣ ብሄራዊና የአንድነት ስሜት እንዳይዳብር ለማድረግ ነው። እኛ የምዕራቡን የካፒታሊስት አገሮች ተንኮል አለመገንዘብና በትናንሽ ነገሮች መደለል፣ በተለይም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያ እንድንሆን አድርጎናል። ጠለቅ ያለና የሾለ ምሁራዊ አስተሳሰብ ለማዳበር ባለመቻላችን ርስ በራሳችን እንድንጨራረስና የአሜሪካን መሳሪያ ለመሆን በቅተናል። በተለይም በርዕዮተ-ዓለም ሽፋን ስም የተካሄደብን ዘመቻ ርስ በርስ እንድንጠራጠርና ለመጠቋቆም በቅተናል።
የሃያ ሰባት ዐመቱን የኢህአዴግ ፖለቲካ እንመልከት። አሜሪካንም ሆነ የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በአገራችን ምድር በእርግጥም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ቢፈልጉ ኖሮ እንደዚያ ፀረ-ዲሞክራሲውያዊ ስራ ሲሰራና ህዝብን ሲከፋፍል ሲያዩ ዕርዳታ አንሰጥህም ማለት በቻሉ ነበር። በእነሱ ዕምነት ግን ወጣትና ተስፋ በሚጣልበት መሪ አማካይነት አገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያመራች ነው በሚል ያልተቆጠበ የገንዝብ፣ የማቲሪያልና የፖለቲካ ድጋፍ መስጠት ነውበር ሙያዬ ብለው የተያያዙት። ፀረ-ሳይንሰና ፀረ-ህዝብ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲም ከላይኛው ዕርዳታ ጋር በጥብቅ የተያያዝና በእከክልኝ ልከክልህ ፖለቲካ አማካይነት ብሄራዊ ስሜትን ለማዳከምና የተኮላሽ የህብረተስብ ክፍል በመፍጠር በአካባቢው አገሮች የጦርነት ፖለቲካ ከማካሄድ ስሌት ጋር የተያያዘ ነው። ከአንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተዋንያን የሚሰጠው አስተያየት፣ ኢትዮጵያ ብትዳከምና ብትፈርስ አሜሪካ ምን ጥቅም ያገኛል? የሚለው አባባል የዓለም አቀፍ ፖለቲካን አወቃቀርና ወደ ውስጥ ደግሞ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በምን መልክ እንደተዋቀረ በቅጡ ካለመገንዘብ የተነሳ ነው። በተለይም ከምርጫ 1997 ዓ.ም ወዲህ አሜሪካንንም ሆነ የአውሮፓውን አንድነት ተቃዋሚው ያደረገው መለማምጥና „የዲፕሎማሲ ትግል“ ፋይዳ ሊያገኝ ያልቻለው የምንፈልገውን ነገር የሚያደርግልን ውሻ ስላለን እናንተ ከሱ ስለማትሻሉ ለስልጣን አትገቡም በማለትም ነው። ስለዚህም አንዳንድ የቅንጅት መሪዎች እኛ የምንሰጣቸውን ምክር ትተው ከነቲም ክላርክ ጋር በመታሸት የምርጭ 97 ዓ.ም ውጤት ሊከሽፍ በቃ። በተለይም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እዚህ እኛ የምኖርበት አገርና ዋና ከታማ ከመጣ በኋላ ስናስተናግደው ይህንን ሀቅ ነው ለመገንዘብ የቻልነው። ከእኛ ጋር ከመነጋገርና ምክር ከመፈለግ ይልቅ በእኛ ፊት በቀጥታ ከቲም ክላርክ ጋር የእንግሊዝ የስለላ ሰው ጋር ነበር ስልክ ይደውልለት የነበረው። በጊዜው ሊጠራ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍና የቤት ውስጥ አድማ እንዲቀር የተገደደው በፈረንጆች ላይ ጭፍን ያለ ዕምነት ስለተጣለ ነበር። ምርጫ 97ን ያከሸፉት እነ አቶ መለስ ሳይሆኑ ራሳቸው የቅንጅት መሪዎች ናቸው። የኢትዮጵያም ህዝብ የሚለው ቅንጅት ሳይቸግረው ምርጫ ብሎ አስጨረሶን አለፍ ነው ብለው ይነግሩን የነበረው። በእርግጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ወጣት ሊሸሽ ሲል ታርዷል። ሀቁ ይህ ነው። ይሁንና የተቃዋሚው ኃይል ይህ የምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ አገርን የማዳከምና የማፈራረስ ፖለቲካ ስላልገባው በሚያሳፍር መልክ አስር ጊዜ አቤቱታውን ከማሰማት አላቋረጠም። ይህ የተቃዋሚው ፖለቲካ ዘይቤ ራሱንም ምዕራቡን አስገርሞታል። እኛ አገራችሁን እያፈራረስ ነው፤ ከኛ ምንድነው የምተጠብቁት? እስኪሉና በግልጽ እስኪናገሩ ድረስ ነው ተቃዋሚው ኃይል የሚጠባበቀው። በግልጽ አውጥተው ባይናገሩም እንኳ የተቃዋሚው ኃይል ልናምናችሁ አንችልም ብሎ በየዋህነቱ እንደገፋበት በጊዜው ሁኔታውን ለተከታተለ ሊገነዘበው ይችላል። ከአንዳንዶቹ የዋሆች የሚሰነዘረው አነጋገር ደግሞ አቶ መለስ የማይሆን ኢንፎርሜሽንና ስታቲስቲክስ እየሰጣቸው ያታልላቸዋል የሚል ነው። አቶ መለስ እንኳን አሜሪካኖችንና አውሮፓውያንን ቀርቶ ያልተማረ ሰውንም ሊያታልል አይችልም። ምከንያቱም የሚሰራው ስራ ስለሚታይና ራሱ የኢትዮጵያ ተጨባጩ ሁኔታ ብዙም ማረጋገጫ ስለማይሻ ነው።
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ በምን ተዓምር ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ልክ እንደ ግብፅና ቱኒዚያ የመስለ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ቢፈጠርና እነ አቶ መለስ ከስልጣን ቢባረሩ ኖሮ የምዕራቡ ዓለም ፊቱን ወደ አዲሱ ኃይል ሊያዞር ይችል የነበረው? አዲሱን ኃይል እደግፋለሁ ቢልስ በምን መልክ ነው የሚደግፈው? ካለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ያግዛል ወይ? ዕርዳታስ ይሰጣል ወይ? ይህንን ካላደረጋችሁ ዕርዳታ አልሰጥም ካለስ እንደ ወትሮው የኒዎ-ሊበራሊዝምን የኢኮኖሚክ ፖሊስን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ናችሁ ወይ? አሜሪካ ከኢትዮጵያ እየተነሳ ሌሎች አገሮችን ላምስ ቢልስ ፈቃደኛ ሊኮን ነው ወይ? ይህ ከሆነ ደግሞ አልሽሹም ዞር እንደሚሉት አነጋገር ነው። በጊዜው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ብዙ ነገሮችን ለማብራራት አልቻለም ነበር። ለስልጣን የቋመጠም ስለነበር ብዙ ነገሮችም አይታይቱም ነበር። ከዚህም በላይ በኢምፔሪሲዝም የአካዳሚ ዕውቀት ስለሰለጠነ ጠለቅ ብሎ ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ የመርመር ችሎታ አልነበረውም። ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ ባህርይ ስለሌለው በራሶ ኤጎ ብቻ ነበር በመመራት ነበር እንደኛ ያሉ ደካማ ፍጡርችን እየደፈጠጠ ወደፊት ይጓዝ የነበረው።
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የቱኒዚያውን ህዝባዊ እንቅስቃሴና የቤን ዓሊንና እንዲሁም የሙባራክን መባረር አስመልክቶ፣ „ለነጻነታችን በምናደርገው ትግል የዲሞክራሲያዊ አገሮች ድጋፍ ለማግኘት መሬት ላይ ያለው ሁኔታ መቀየር እንዳለበት ቱኒዚያም ግብጽም አረጋግጠውልናል። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ሲቀየር ደግሞ ትላንት እሹሩሩ ያሉትን አምባገነን አንስቶ ከማፍረጥ እንደማይመለሱ በመጀመሪያ ክቱኒዚያው ቤን ዓሊን ከዚያም ከግብጹ ሙባራክ የተማርነው ትልቅ ነገር ነው“ በማለት የቅጩን ይነግረናል። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ተቀይሯል ሲልስ ምን ማለቱ ነው? አንድ መሪስ ስለተባረረ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ተቀይሯል የሚያስብልስ ነገር ምንድነው
በመጀመሪያ መሬት ላይ ያለው ነገር መቀየር አለበት ሲባል አንድ መሪ የመባረሩ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመጨቆኛ መሳሪያዎች፣ በተለይም የስለላ መዋቅሩ እንዳለ መደምሰስ አለበት። እንደሚታወቀው የስለላ መዋቅሮች፣ በአገራችን ደግሞ የደህንነት ጥበቃ የሚባሉት ከምዕራቡ ዓለም ካለምንም ማሰብ የተወሰዱና ስልጣን ላይ ያሉትን ለመጠብቅና ከህዝብ የሚመጣውንም ብሶት በእንጭጩ ለመቅጨት የተዘጋጁ ናቸው። በተጨማሪም ክሪቲካል አመለካከት ያላቸውን ምሁራን ለማጥፋት ነው። ስለሆነም እነ ሙባራክ ቢባረሩም የስለላ መዋቅሩ እንዳለ ነው። በሲአይ ኤና በሙባራክ የስለላ መዋቅር መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት እንዳለ የታወቀ ሲሆን፣ ሁኔታውም በዚያው እንደሚቀጥል ግልጽ ነው፤ ቀጥሏልም። በሁለቱም አገሮች በጊዜው የሚታየው ሰላማዊ ሰልፍና ግብግብ የሚያረጋግጠው ሰፊው ህዝብ፣ በተለይም ወጣቱ በሁኔታው እንዳልተደሰተ ነበር። አንዳንድ የግብጽ ምሁራንም እንደሚሉት አብዮት ከሰራን ከጥቂት ቀናት በኋላ ፀረ-አብዮት እየተካሄደብን ነበር ይሉ የነበረው። እንግዲህ ምኑ ላይ ነውቭ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ የተቀየረው? ምናልባት ለዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሚታየው ነገር ለኛ ላይታየን ይችል ይሆናል። ከዚህ በተረፈ በተለይም በግብፅ ሚሊታሪው ራሱ ብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎችንም ይቆጣጠራል። ከዚህም ሌላ ጠቅላላው ሁኔታ ለአሜሪካኖችና ለምዕራብ አውሮፓ በሚስማማ መልክ እንዲደራጅ በመጣደፍ ላይ ነበር። አሜሪካንም ሆነ ምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊሲት አገሮች እነሱ በሚፈልጉት መንገድ በቻ እንዲሄድ የማታለል ስራቸውን እየሰሩ ነበር። በህግ የበላይነትና በነፃ ንግድና ገበያ አሳበው እንቅስቃሴውን ለማኮላሸት ደፋና ቀና ይሉ እንደነበር ሁኔታውን የተከታተለ ሊገነዘብ ይችላል። በተለይም ከቱኒዚያ ምሁራን የሚሰማው ሮሮ ይህ የምዕራቡ ዲሞክራሲ ተንኮል በማለት ነበር። በሁለቱም አገሮች ከኛ በተሻለ መልክ የዳበረ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ቢኖርም ወደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲመጣ ትልቅ ውዥንብር እንዳለ መገንዘብ ይቻል ነበር። በጊዜው ቀናና ክሪቲካል አመለካከት ካላቸው የጀርመን ምሁራን ጋር ባደረግነው የሃሳብ መለዋወጥ የደረስንበት ድምደማ፣ እነ አይ ኤም ኤፍ እንደግና የኒዎ-ሊበራል አጀንዳቸውን ይዘው በመምጣት ድህነቱ እንዲራዘም እንደሚያደርጉት ነበር። ስለሆነም ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም፣ በተለይም ደግሞ ለወጣቱ የሙያ ማስልጠኛ ተቋማት መስርቶ ተስፋ እንዲኖረው ለማድረግ ግብፅም ሆነ ቱኒዚያ ብዙ ዐመታት መጠበቅ አለባቸው ማለት ነው። በተጨማሪም ኢኮኖሚው በሰፊው ሪፎርም መደረግና ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲኖረው ለማድረግ ውስብስብ ሁኔታዎች ከበፊቱ ተደቅነዋል። የሁለቱን አገሮች ሁኔታን ትተን፣ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለው ልክ እሱ በሚፈልገው መልክ ብቻ የኢኮኖሚክ ሪፎርም ተጠቃሚ ይሆናል። ይህም ማለት አዳዲስ ኃይሎች በመፈጠርና በመኮትኮት የግብፅንም ሆነ የቱኒዚያን ህዝቦች ህልም ዕውን ከማድረግ ይልቅ የዓለም አቀፍን የፊናንስ ኦሊጋርኪ ጥቅም ተግባራዊ ያደርጋሉ ማለት ነው። በዚያው ወቅት እንኳ ባይሆን ልክ በጊዜው በግሪክ ላይ የሚደረገው ማዕቀብና አንጀት አጥብቅ የቁጠባ ፖሊሲ በሁለቱ አገሮች ተግባራዊ በመሆን የውስጥ ገበያ እንዳያድግ ይደርጋሉ ማለት ነው። ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ቀለል አድርጎ ለማየትና ሊያዘናጋን እንደሚሞክረው ነገሩ ቀለል ተብሎ መታየት የለበትም። ምናልባትም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የተለየ ግምት አላቸው ብሎ አስቦ ይሆናል። እናንተ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ሳናውቀው ነው እስከዛሬ ድረስ ዲሞክራሲን ከሚጠላና ጭቆናን ከሚያስፋፋ አገዛዝ ጋር አብረን ስንሰራ የነበርነው፤ አገዛዛችሁ ለካስ ሲያታልለን ነበር ማየት የሚቻለውን ነገር ሁሉ እንዳናይ ተጋርደን ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከእናንተ ጎን በመቆም ሳይንስና ቴክኖሎጂን እናፈስላችኋለን፤ ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችንም እንገነባላችኋለን፤ የባቡር ሃዲድም በመዘርጋት ስፋ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲዳብር እናደርጋለን፤ በዚያውም የተከበረችና ጠንካራ ኢትዮጵያን እንገነባላችኋለን፣ ብሎ ታስቦ እንደሆን በጣም የዋህነት ነው።
ለማንኛውም ነገሩ እጅግ በጣም ውስብስብና በኛ መሀከልም የሚደረገው ትግል ውጣ ውረድ የበዛበት እንደሚሆን በጊዜውን የዶ/ር ብርሃኑንም ገለጻ ሆነ አስተሳሰቡንና የሌሎችንም በተቃዋሚ ስም የሚንቀሳቀሱትን አስተሳሰብ ለተረዳ ግልጽ ነበር። ከዚያ በኋላ የተፈጠረው ሁኔታና እሁንም በግልጽ በምሁሩ ዘንድ የሚታየው የቲዎሪና የሳይንስ ድክመት አዲስና ጠንካራን ኢትዮጵያን ለመገንባት አንድ ሺህ ዓመት ያህል መጠበቅ ይኖርብናል ማለት ነው። ለመሆኑ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በጊዜው ይህንን ዐይነቱን ዕምነት እንዴት ሊያዳብር ቻለ? ዛሬም በዚያ በድሮው ዐምነቱ በመቀጠል ነው የአቢይ አህመድ ተለጣፊ በመሆን በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚካሄደውን ዘረፋና ጭቆና፣ እንዲሁም ግድያ እንደትክክልና ዲሞክራሲያዊ አካሄድ አድርጎ በመቁጠር ዝም ብሎ የሚመለከተው። እንደተከታተልኩት ከሆነ በተለይም የነፃ ገበያንና የሊበራል ዲሞክራሲን ርዕዮተ-ዓለምን እናራምዳለን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ዓለምን በጥቁርና በነጭ ስለው ነው የሚመለከቱት። ሳናውቀው በብዙዎቻችንም ጭንቅላት ውስጥ አንድ የተቀረጸ ነገር አለ። ፈረንጅን እንደ አምላክ ማየት። ሊሳሳቱ ቢችሉም እንኳ መጨረሻ ላይ ወደ ቀናው መንገድ ይመጣሉ የሚል አስተሳስብ በሁላችንም ዘንድ ያለ ይመስላል። እዚህ ላይ እንዲያው በደፈናው በነጭ ላይ ዘመቻ ለማካሄድ ሳይሆን፣ በተለይም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኤሊቱ የሚያካሂደው ፖሊሲ ራሱን ለመጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችንንም ለማዳከም ነው። ቢያንስ ያለፈው የሁለት መቶ ዐመት ፖለቲካ፣ በተለይም ደግሞ ባለፈው ስድሳ ዐመታት የተካሂደው ፖለቲካ የሚያረጋግጠው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም ፖለቲካ ከተንኮልና አገሮችን ከማዳከም ጋር የተያያዘ ነው። በታሪክ ውስጥ ታላላቅ ጦርነቶችን አስነስቶ ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ተጠያቂ ሊሆን የቻለው የጥቁር፣ የላቲንና የአሲያ ህዝብ ሳይሆን አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ ኤሊቶች ናቸው። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላም ቀላልና ትላልቅ ጦርነቶች ቀስቅሶ ህዝቦችን ማስጨረስና ማፈናቀል የአሜሪካና የአውሮፓ የነጭ ኦሊጋርኪው ተግባር ነው። እጅግ በረቀቀ መንገድ ዓለምን የሚያስሰውና የሚያተረማምሰው ሰለጠንኩኝ የሚለው የነጩ ኦሊጋርኪ ነው። ትላንትናና ዛሬ በብዙ የሶስተኛው ዓለም የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ የውክልና ጦርነቶች ናቸው። በአገራችንም ምድር ወያኔና አቢይ አህመድ በመናበብ በህዝባችንና በአገራችን ላይ የሚያካሄዱት ጦርነት የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ጦርነት ነው። ህወሃትና አቢይ አህመድ የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ተወካዮች በመሆን ነው ብሄረሶቦቻቸውን እንወክላለን በማለት በታሪካችን፣ በባህላችን፣ በህዝባችንንባ በአገራችን ላይ የማያቋርጥ ጦርነት የከፈቱብን። ከዚህ ውጭ ማሰብ አደገኛ አካሄድ ነው።
አንዳንዶች ሊያሳምኑን እንደሚሞክሩት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩት ውዝግቦች በሙሉ ኮሙኒስቶች የፈጠሩት ሳይሆን አሚሪካኖች በሚሰሩት ተንኮል ነው። የዓለምም ኢኮኖሚ የተዋቀረው ለእነሱ በሚስማማ መልክ ነው። በኒዎ-ሊበራሊዝምና በግሎባላዜሽን ስም የሚካሄደው መስፋፋት ጥሬ-ሀብቶችን ለመቆጣጠርና የየአገሮችን ኢኮኖሚዎች አዳክሞ የራስን ሸቀጥ ለማራገፍ ነው። በግሎባላይዜሽን አማካይነት ዓለም ወደ መንደርነት የተቀየርች ሳትሆን፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ማራገፊያና ህዝብን ማመሺያ ነው የሆነችው። ምናልባት ለአንዳንዶቻችን ሞባይል ስልክና ሌፕቶፕ ይዘን ጉድ ጉድ ስላልን የተቀረው የዓለም ህዝብ ያለፈለት ይመስለን ይሆናል። ሜርሴዲስና ቤኤም ደብልዩ ስለነዳን ሌላውም ያለፈለት ይመስለን ይሆናል። በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በድህነትና በረሃብ እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በማጣቱ እንዲሰቃይ የመሆኑ ጉዳይ፣ አይ የተፈጥሮ ህግ፣ ወይም ደግሞ የደሀው ህዝብ ጥፋትና ድክመት ተደርጎ ተወስዶ ሊሆን ይችላል ። የሰብአዊ መብቱም መገፈፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀነባበረ መልክ ከሚካሂደው ሁኔታ ጋር ተሳስሮ ሊታይ አይችም ይሆናል። ህዝቦች በየአገሮቻቸው እንዳይኖሩና ቆንጆ ቆንጆ ነገሮች እንዳይሰሩ መታገዳቸውም የየአገሩ ኤሊት ተግባር ብቻ ተደርጎም ተውስዶም ሊሆን ይችላል። የሶስተኛው ዓለም መንግስታትና ኢንስቲቱሽኖች የካፒታሊስቱን የምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ የሚያግዙና የሚያጠናክሩ እንጂ ወደ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዲሰሩ ለማድረግ አይደለም የተዋቀሩት። ይህን የመሰለውን እጅግ በተሰበጣጠረ መልክ የሚካሄደውን ጭቆናና ደሀ አገሮችን ማዳከምን ነው ዶከተር ብርሃኑም ሆነ ሌሎች የሊበራል ዲሞክራቲክ አራማጆች ነው ብለው የሚያወናብዱ ሊገነዘቡ የማይችሉት። ምክንያቱም ቀላል ነው። አስተሳሰባቸው ኢምፕሬሲስታዊ ስለሆነ ብቻ። እነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋና ሌሎች የነፃ ገበያና የሊበራል ዲሞክራሲ አራማጆች ይህንን ነው ለማየት የማፈልጉትና የማይችሉት። ፕላቶን እንደሚያስተምረን መታየት የማይችለውን ነገር ማየት የማይችሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጠለቅ ብለው በመሄድ የነገሮችን አነሳስ፣ ዕድገትና አቅጣጫ ለመመርመር የማይፈልጉም ናቸው። በተሰበጣጠረው በሚከሮና በማክሮ ኮስሞስ መሀከል ያለውን የተዋሰሰበ ግኑኝነት ለመረዳት በፍጹም አይችሉም። ብዙዎችም በመሳፍንቶች ዘንድ ከሚካሄድ ውይይት አልፈው ህዝባዊ ብሶቶች በሚነሱባቸው ትላልቅ ሰሚናሮች ጋ በመካፈል ትችታዊ ውይይትንና አመለካከትን ለማዳበር ዝግጁ ስላይደሉና ብቃትም ስለሌቸው የተወላገደ አስተሳሰብ ይዘው ሌላውን በማሳሳትና ትላልቅ ሰዎች ሆነው በመቅረብ አንድ አገርና ህዝብ ታሪክ እንዳይሰራ እንቅፋት ይሆናሉ። የብዞዎቹ የሊበራል ዲሞክራሲ አራማጅ ነን ባዮች ችግር ከዚህ የካፒታሊስት የኒዎ-ሊበራል አቀንቃኞች ካዋቀሩት ቲዎሪ ባሻገር ርቀው ሂደው ለማየት አለመቻል ነው። በተለይም የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስንና የዕድገት ኢኮኖሚክስን አስመልክቶ የታወቁት ስዊዲናዊ ኢኮኖሚስትና በሰላሳኛው ክፍለ-ዘመንም ሆነ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የስዊድንን ኢኮኖሚ መስመር እንዲይዝ ያደረጉት ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ጉናር ምርያልድ ማስጠንቀቂያ ሰጠተው ነበር። አሳሳች መሆኑን በዝርዝር አረጋግጠዋል። ሌሎችም እንደ ፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርት እጅግ ግሩም በሆነ መጽሀፋቸው፣ „ለምን ደሀ አገሮች ደሀ ሆነው ቀሩ፣ እንዴትስ ሀብታም ሀገሮች ሀብታም ሊሆኑ በቁ“ በሚለው መጽፋቸው በየትምህርት ቤት የሚሰጠውን የኢኮኖሚክስ ትምህርት አጥብቀው ያወግዛሉ። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢኮኖሚስቶች በዚህ መልክ ተኮትክተው አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለዓለም ድህነት አስተዋፅዖ እንዳደረጉ ያመለክታሉ። ሌሎችም ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው ምሁራን ይህንን የፕሮፌሰር ምይራልድንና ፕሮፌሰር ራይነርትን ትንተናና ሳይንሳዊ ማስረጃ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ። ለንደን የሚገኘው ስኩል ኦፍ ኦሪዬንታል ስተዲስ(School of oriental studies)የኒዎ-ሊበራልን ፖሊሲም ሆነ ቲዎሪ፣ በቲዎሪና በኢምፔሪካል ደረጃ በማሳየት አሳሳችነቱን ያረጋግጣል። ብዙ ፕሮፌሰሮችም በግልጽ ትግል በማድረግ አዲሱ ትውልድ ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዝ ጥረት እያደረጉ ነው። በእኛ ምሁራን ጋ ያለው ትልቁ ችግር ግን ይህንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ትግል እንዳላዩ አድርጎ ማለፍና ካለ ኒዎ-ሊበራል ፖሊሲና ከነፃ ገበያ ሌላ መፍትሄ የለም ብሎ ቁጭ ማለትና ሌላውን ደግሞ እንደ ዕብድ ማየት ነው። ይህ አጉል ትልቅ ሰዎች ነን ብለው አንዳንድ ስዎች የማያካሂዱት ትግል ለንቃተ-ህሊና ማደግና ለስለጣኔ እንቅፋት ሆኗል ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ የሚካሄድ ትግል እጅግ የመረረና የድህነቱንም ዘመን የሚያራዝም ነው። ስለሆነም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተሳስተዋል። ይህንን ሁኔታ የመግታቱና ቀናውን መንገድ የማሳያዙ ጉዳይ በብዙ ስዎች ትከሻ ላይ መውደቅ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ትግሉ ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው። ካለበለዚያ ግን የሰለጠነችና የተከበረች ኢትዮጵያን ማየት ሳንችል እናልፋለን ማለት ነው። መልካም ግንዛቤ!!
ማሳሰቢያ፤ ከምርጫ 1997 ዓ.ም በኋላ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋንም ሆነ ልደቱ አያሌውን እዚህ በርሊን በመጡ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ውስጥ በመውሰድ ካስተረጎምኩላቸው ሰዎች ውስጥ አንደኛው እኔ ነበርኩ። የሁለቱንም ዕውቀትና ባህርይ በጊዜው ለመረዳት ችያለው። ለስልጣን የታጩ የሚመስሉ እንጁ በትክክለኛ ዕውቀት መንፈሳቸውን በማነጽ ህዝብን ለማገልገል የተዘጋጁ እንዳልሆነ ለመረዳት ችያለሁ። በተለይም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ዛሬ ያለበትን ሁኔታ መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው። ሰውየው የህዛብችን ጠበቃ ከመሆን ይልቅ ከአቢይ አህመድ ጋር በመለጠፍ በህዛባችን ላይ ጭፍጨፋ ሲካሄድና አገር ልተበታተን ስትቀርብ ዝብ ብሎ ይመለከታል። እሱ የሚያዘው ኢዜማ የሚባለው ፓርቲም ምንም ሲሰራ አይታይም። ፓርቲው በአንድ ግለሰብ ብቻ እንደሚመራ ዝም ብሎ የሚመለከት ነው። በአገራችን ምድር የሚካሄደው ጭፍጨፋ ከአገዛዙ ከአቢይ አህመድ ፈቃድና ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ነው ኤዜማና ብርሃኑ ነጋ ለማሳመን የሚሞክሩት። ታዲያ ከዚህ ዐይነቱ ድርጅትና ሰዎች ዘንድ ምን ዐይነት ዲሞክራሲ ነው የሚጠበቀው?