April 9, 2023
72 mins read

በኢትዮጵያ “የብሄር ፖለቲካ” እና “የዘረኝነት ስርአት”፤ ያስከተለው መዘዝና መፍትሄዉ (ክፍል-3) – ዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)

ክፍል-3

Abiyu Birele 1 1 1
#image_title

መግቢያ፤

ባለፈው ጽሁፌ (በክፍል-2) አሁን ባለው የኢትዮጵያ ህገመንግሥት በዉስጡ ያሉትን ዋና ዋና ችግሮችና፤ ለማሻሻልም ምን ያክል አዳጋች እንደሆነ በመጥቀስ መፍትሄወችን ለመጠቆምም ሞክሬአልሁ፡፡ ለእዚህ ከባድ ጥያቄ አጭር መልስ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው፤ እኔም በቂ መልስ አለኝ ብየ እራሴን አላሞካሽም፤ ሆኖም፤ በእዚህ ቀጣይ ጽሁፌ፤ በተለይ መዋቅራዊ በሆኑት ዋና ዋና የህገመንግስቱ ችግሮች ላይ በማተኮር፤ ቢሻሻሉ መፍትሄ ይገኛል ብየ የምገምታቸዉን ሀሳቦች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በዋነኝነት ህገመንግሥቱን የማሻሻያ ወይም የመቀየሪያዉ ቀና መንገድ ግን የሕዝብን ፍላጎት፤ ፍቃድና አመኔታ በማገናዘብ ስኬታማ የሆነ ሁለገብ “ሀገራዊ ምክክር” ማድረጉ የግድ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ፤ በቅድሚያ ባለፉት ሰላሳ አመታት በህገመንግሥቱ ምክንያት ስር የሰደደው የብሄር ፖለቲካና እሱ የወለደው ዘረኛ ስርአት ያስከተለዉንና፤ እራሱን ህገመንግሥቱንም ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ትልቅ እንቅፋት የሆነዉን ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል በመጠኑ ዳስሸ ለማለፍ እወዳለሁ፡፡

 

  1. የብሄር ፖለቲካው የወለደው “የአስተሳሰብ ድህነት የተካነው የፖለቲካ ባህል”

 

ከሰላሳ ዓመት በፊት በሀገራችን በህወሐትና በአጋሩ ኦነግ ተተክሎ ስር በመስደድ እስከዛሬ እያደገ የቀጠለውና፤ በብሄር ፖለቲካ ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ባህልና የዘረኝነት ሥርአት ከወለዱት ዋና ዋና ችግሮች አንዱ፤ በቀላሉ ሊፋቅ የማይችል “የአስተሳሰብ ድህነትን” በዜጎች፤ በተለይም በወጣቱና ታዳጊው ትዉልድ አእምሮ መቅረጹ ነው፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ወይም “የአእምሮ ድህነት”፤ ሀገራችንን በኢኮኖሚ ድህነት በዐለም ከታወቁትና በእድገት የመጨረሻወቹ አንዷ ናት የሚል የመታወቂያ ስም ለዘመናት ካሰጣት በባሰ ነው በህብረተሰቡ ጉዳት ያስከተለ፡፡ በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ወይም ብልጽግና ሊመጣ የሚችለው በዋነኝነት፤ የመሪወችና ዜጎች አስተሳሰብ በእወቀት የዳበረና በሀገራዊ ፍቅር የታነጸ ሲሆንና፤ ድህነትን ከሀገራችን እናጥፋ በሚል ቁጭት በጋራ ቆርጠው ሲነሱ ነው፡፡ ያንን የፖለቲካ ባህል ግን ዛሬ ዓለም በስልጣኔ በመጠቀበት ዘመን በሀገራችን ማዳበር አልቻልንም፡፡ ለእዚህም የብሄር ፖለቲካውና እሱ የወለደው ጠባብ የዘረኝነት አስተሳሰብ ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡

 

በርካታ የሰለጠኑና በእድገት የመጠቁ ሀገራት በታሪካቸው ልክ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ አንዳንዶችም ከእኛ በባሰ ብዙ ዉጣ ውረድና ፈተና፤ እረሀብ፤ የእርስበርስ ጦርነትና ግጭት እያሳለፉ ነው እዚያ ደረጃ የደረሱት፡፡ ለስኬታቸው ዋናዉ ምስጢር ደግሞ እኛን እስከዛሬ ለመማር ያቃተን፤ አእምሮአቸዉን ክፍት አድርገው ካለፈው ታሪካቸውና ተሞክሮአቸው መማር መቻላቸው ነው፡፡ እንደእኛ ሀገር ጠባብ የብሄር ፖለቲከኞች በገነኑበት፤ ባሉበት ቆመው እያደከደኩ፤ አባቶቻቸው ባሳለፉት የፈተና ታሪካቸው ከመናቆርና ከመነታረክ ይልቅ፤ በሀገራቸው የወደፊት ዕድል ላይ በማተኮር፤ ለችግሮቻቸው መፍትሄወችን በጋራ እያፈላለጉ በማግኘታቸው ነው ዜጎቻቸዉን በፍጥነት ከድህነት የጨለማ ዓለም እያወጡ፤ የተስፋ ብርሀን በመዘርጋት ማደግ የቻሉት፡፡

 

ለአንድ ሀገር እድገት የዉስጥ ሰላምና መረጋጋት፤ አንድነትና፤ ከሀገራዊ ፍቅር የሚመነጭ ቁጭት ወሳኝ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከብዙ የዓለም ሀገራት በፊት ሀገረ መንግሥት ገንብታ፤ በተለይም በአፍሪካ አህጉር በብቸኝነት በነጻነቷ ኮርታ፤ በዉስጧም ሰላም ፈጥራና ተረጋግታ በተለይም ከ50 ዓመት በፊት በስልጣኔ ዓለም በማዝገም ላይ እያለች፤ አርቆ አሳቢና አስተዋይ መሪወችን በማጣቷ፤ ግፍ የበዛበት ሕዝብ በአመጽ ሲነሳ መዉጫው ወደጠፋ የፖለቲካ ቀውስ ልታመራ ቻለች፡፡ ከዚያም የተነሳ ባለፉት አምሳ አመታት በተለይ ወደፊት ለመራመድና ለማደግ ተስኗት በቀውስ አዙሪት ላይ ትገኛለች፤ ዜጎቿም በእረሀብ፤ በድርቅ፤ በእርስበርስ ጦርነትና በግጭት፣ በሰቆቃና በመከራ የሚማቅቁባት ምሳሌ ሆናለች፡፡ ለእዚህ ዋና ምክንያት በተለይም የፖለቲካ “ልሂቃንና” መሪ ነን የሚሉት በአስተሳሰብ ድህነት በሽታ በመበከላቸው ነው፡፡

 

እርግጥ እኔ ያለፍኩበት ትዉልድም ቢሆን ከእዚህ የአስተሳሰብ ድህነት ወላፈን ነጻ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህን ስል ግን በሽ የሚቆጠሩ ሀገራቸዉን አፍቃሪ ወጣቶች ዘር፤ ብሄርና ቋንቋ አጥር ሆኖ ሳይገድባቸው ለሕዝባቸው ነጻነት፤ ፍትህና እኩልነት ለማምጣት በአንድነት ሲታገሉ በህይወታቸው ሳይቀር መስዋእትነት የከፈሉትን በመርሳት አይደለም፡፡ ሆኖም፤ በተለይም “የብሄሮች እኩልነት” እያሉ በቅንነት የታገሉለት የተቀደሰ ዓላማ በጠባብ ብሄረተኞች ተጠልፎ፤ የሕዝብ ሰቆቃ ሊያስከትልና የሀገራቸዉን ህልዉና አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ግምት አልነበራቸዉም፡፡

 

የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነቱ ኋላ ቀር ባህል ስር የሰደደዉና እየባሰበት የመጣዉም በተለይ ባለፉት ሰላሳ ዓመት ዉስጥ ነው፡፡ አዕሞሮአቸው በጠባብ ብሄረተኛና የዘር አስተሳሰብ ተበክሎ፤ በሀገርና በሕዝብ ጥላቻ ተመርዞ፤ በቂም በቀል ታጥሮ፤ የግል ፍላጎታቸውን እያሳደዱ፤ በመንግሥት ስልጣን ሽሚያና፤ በሀገር ሀብት ዝርፊያ በየተራ ተሰማርተው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን እንደሌሎች ሀገራት በሰላምና በጋራ እንዳታድግ ትልቅ እንቅፋት ነው የሆኑባት፡፡ ምንም የማያልፍላት፤ መልካም ዕድሏንና የተፈጥሮ ሀብቷን፤ ግሩም ታሪኳንም ያባከነች አሳፋሪ ሀገር እየተባለች፤ በተለይም በአፍሪካ አህጉር መሳቂያና መሳለቂያ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ በተለይም ወጣቱና ታዳጊው ትዉልድ የድህነት ሀፍረቱን ለመሸፈን እንኳን ማካካሻ ቢሆነው፤ የጀግኖች አባቶቹን ግሩም ታሪክ እያስታወሰ፤ እነሱ ያወረሱትን የአፍሪካና የጥቁር ሕዝብ መኩሪያ የሆነዉን ሰንደቅ ዓላማዉንም ከፍ አድርጎ ይዞ በኩራት ቀና ብሎ ወደፊት እንዳይጓዝ፤ እሱንም ሊያሳጡትና አንገቱን አስደፍተው እንደእነሱ ህሊና ቢስ፤ ጠባብና ዘረኛ እንዲሆን፤ በአስተሳሰቡ መቶ ዓመት ወደኋላ እንዲሄድ አድርገዉታል፡፡ ይህ ነው ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል!

 

ጠባብ የብሄር ፖለቲከኞች ባለፉት ሰላሳ አመታት በእራሳቸውና በትዉልዱ ላይ የተከሉት የአስተሳሰብ ድህነት የጀመረውም የኢትዮጵያን ታሪክ ሆነ ብለው በመበረዝ ነው፡፡ አዲሱ ትዉልድ ኢትዮጵያዊ (ሀገራዊ) ማንነቱን እንዲስትና፤ በጠባብ አእምሮው በዘሩ፤ በብሄሩ በመንደሩና በጎጡ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ብዙ ነው የሠሩት፡፡ ካለፈው የሀገራችን ታሪክ በቅንነት መማርና ሀገሪቱን ማሳደግ ሲያቅታቸው፤ የሆነ ያልሆነ ሰበብ እየፈጠሩ፤ ሕዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛትና እንደነእነሱ ለማደንቆር እዉነተኛዉን ታሪክ ለመበረዝ በሀሰት ትርክት መተካትን መረጡ፡፡ ስንትና ስንት መስዋእትነት ከፍለው ምን የመሰለች ሀገር ያወረሱንን አባቶቻችንና እናቶቻችንን እንደጠላት እያዩ በማዉገዝ፤ ሀገራዊ ግዴታቸዉን ፈጽመው ታሪክን ለመማሪያ ያወረሷቸው ሳይሆን፤ የጣሉባቸው ትልቅ “እዳ” ወይም ሸክም እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የእዚያ አይነት አመለካከት እራሱ የአስተሳሰብ ድህነት አንዱ ምንጭ ነው፤ አቅም ማጣትንና ደካማነትን ያመላክታል፡፡

 

ታሪክ የሀገር እዳ ወይም ሸክም ሆኖ አያውቅም፡፡ ላወቀበት መማሪያና የዕዉቀት ምንጭ እንጅ! ታሪክን “ዕዳ” ነው ብሎ ማሰብ እራሱ በተለይም ለአዲሱ ትዉልድ መጥፎ ትምህርትን ይሰጣል፡፡ አዕምሮዉን ክፍት አድርጎ፤ ሀገራችን ዛሬ ላጋጠሟት ዉስብስብ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ኃላፊነት እንዲሰማዉና በእራሱ አነሳሽነት እንዲበረታ ማነቃቃት ትቶ፤ ያለፈዉን ትዉልድ (ዕዳ ያሸከመዉን) በሰበብ አስባቡ እየረገመ፤ ህሊናዉን ዘግቶ በቂምና በቀል ኑሮውን እያማረረ፤ ተስፋ በመቁረጥ በመጥፎ ባህል ተዉጦ መዉጫው ጠፍቶት እንዲዳክር ያደርገዋል፡፡ ሲጨንቀው “ይህን ሁሉ እዳ ያሸከመን ያለፈው የ60 ወቹ ትዉልድ ነው” ወይም “ምኒልክ ነው” እያለ በማማረር፤ ጊዜውን በስንፍና፤ ተስፋ በመቁረጥና በጨለምተኝነት እንዲያሳልፍ አድርገዉታል፡፡ እሱ እራሱ ታሪክ ሰሪ መሆኑን እርስቶ፤ ሀገሩን እንዲጠላና፤ ህይወቱን ለመቀየር ከመጣር ይልቅ እየጣላት ወደባእድ ሀገር መሰደድን እንዲመርጥ ይገፉታል፡፡

 

ይህ ሁሉ ሲሆን የጠባብ ብሄር ፖለቲከኞች ግን በሌብነትና ዝርፊያ ላይ ተሰማርተው ምስኪኑን ደሀ ሕዝብ እያራቆቱና፤ እያፈናቀሉ የሀገሪቱን መሬትና ሀብት በቃን ሳይሉ ያግበሰብሳሉ፡፡ ያ አልበቃ ብሎአቸው ሕዝቡን እያስጨፈጨፉና እርስበርስ እያጋጩ፤ ሰላም ፍቅርና ዉበት የሰፈነባት የነበረች ሀገራችንን ወደሲኦልነት ቀይረዋታል፡፡ በእዚህ አይነት፤ ለማደግ ስንት ተስፋ የነበራትን፤ ከሁሉም ቀድማ በፊት ልትሆን ትችል የነበረች ስመ ጥር ሀገር ኢትዮጵያችን፤ በኢኮኖሚ ማደጓስ ቀርቶ፤ በስነልቦና በባህልና አስተሳሰብ፤ ቢያንስ መቶ ዓመት ወደኋላ ሄዳለች፡፡ እንባዋን አብሶ፤ ፊቷን አድሶ ለመመለስና ትክክለኛዉን የእድገት አቅጣጫ ለማስያዝ ገና ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡

 

  1. የብሄር ፖለቲካ ዘረኝነትና ኋላ ቀሩ አስተሳሰብ፤ በማህበራዊ ኑሮ ላይ ያስከተለው ከፍተኛ ጉዳት፤

 

ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስቶትል “የሰው ልጅ በተፈጥሮው የፖለቲካ እንስሳ” (“Man by nature is a Political Animal”) ነው አለ ይባላል፡፡ በርካታ የፍልስፍና አዋቂወች ይህን አባባሉን ሲተረጉሙት፤ አሪስቶትል የሰው ልጅ ያለማህበራዊ ኑሮ የብቻዉን ሊኖር አይችልም፤ ወደ ፖለቲካ የሚገባዉና መንግሥት የሚመሰርትበት ዋና ምክንያትም በጋራ ተስማምቶ በሰላም ለመኖር ሲል ነው፤ ያንን ማድረግ ካልቻለ ግን ከእንስሳ ወይም ከአዉሬ ምንም ያክል አይሻልም፤ እርስበርሱም ሊጨራረስ ይችላል ማለቱ ነው ይላሉ፡፡ የሚያሳዝነው ሀገራችን በተለይም ባለፉት 50 አመታት በመጥፎ የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ያጋጠማት ችግር ከእዚያ አሪስቶትል ጥንት ከሰጋበት “የሰው ልጅ ጥሩ የፖለቲካ ባህልና ማህበራዊ ኑሮ ካጣ፤ ወደ አውሬነት ይቀየራል” ካለው ምንም ያክል አይርቅም፡፡ ጠባብ የብሄር ፖለቲከኞች የህብረተሰቡን የዘመናት መልካም እሴቶች እያጠፉ፤ ሀቅን በዉሸት፤ ሥራን በቅጥፈት፤ ርህራሄን በጭካኔ፤ ማህበራዊ ኑሮን በግለኝነት እንዲተኩ አድርገው ዉጥንቅጡን አውጥተዉታል፡፡

 

ለሀገር ጥሩ ባህልና ሞራል ግንባታ ዋልታ የነበሩትን የሀይማኖት ተቋማት ሳይቀር በክለዋቸዋል፡፡ በሀገራችን ፍቅርና ሰላም ሳይሆን፤ ቂምና በቀል፤ ጥላቻና ጥርጣሬ እየተስፋፋ ማህበራዊ ኑሮም እየጠፋ፤ እሱም እንደፖለቲካ ባህሉ ሴራና መበላላት የሰፈነበት ከሆነ አመታትን አስቆጥሯል፡፡ የብሄር ፖለቲካ ባለፉት 30 አመታት የተከለው የዘረኝነት ስርአት፤ ሀገራችን ለዘመናት ያዘለቀቻቸዉን ግሩም የሆኑ ማህበራዊ ግንኙነታችን፤ አብሮ የመኖርና የሀገራዊ ፍቅራችንን እሴቶች እያከሰመ፤ በሕዝቡ መሀል መከፋፈልንና እርስበርስ መበላላትን እያጠናከረ፤ ህብረተሰቡን ከሰው ልጅነት ወደክፉ አዉሬነት እንዳወረደው ምንም አያጠራጥርም፡፡

 

አንዳንድ የዱር አዉሬስ ከእኛ በተሻለ ሰላማዊ ማህበራዊ ኑሮ ይኖራል፡፡ የሚያሳዝነው፤ በእዚህ መርዘኛና ኋላ ቀር የብሄር ፖለቲካ ዘረኛ ስርአት፤ ከባዱን ዋጋ እየከፈለ ያለዉ፤ ምንም ፖለቲካ የማያዉቀው ምስኪኑ ሕዝብ ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትዉልድ ትልቁን ድርሻ እየከፈለ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ህወሐት በቆሰቆሰው ጦርነት በትግራይ ብቻ እንኳን በወጣቱ ላይ የደረሰው እልቂት ለመገመት ያዳግታል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማፋጀት በሚል እርኩስ ዓላማ ቀልቡን ወርሰው፤ በአማራና አፋር ክልሎች ዘምቶ የገዛ ወንድሞቹንና እህቶቹን ህጻናትን፤ ልጃገረዶችን፤ አሮጊቶችን፤ እናቶችንና አባቶችን ሳይቀር በአሰቃቂ ሁኔታ እንደክፉ አውሬ የበላቸውና እሱም በጦርነት የተበላዉ በእዚህ ጠባብ የብሄርና ዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ ህሊናዉን መርዘዉ አዉሬ ስላደረጉት ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገሪቱ ዙሪያ፤ በወለጋ፤ በቤኒሻንጉል፤ በኣጣየ፤ በጉጅ፤ በጋምቤላና በሌሎችም አካባቢወች የደረሰው አስከፊ የሕዝብ ጭፍጨፋም ይኸው የጠባብና ጽንፈኛ የብሄር ፖለቲካ የዘራዉ፤ አዕምሮን የሚበክል የዘረኝነት መርዝ ዉጤት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

 

የጠባብ ብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብ ዋናው ጉዳቱ ደግሞ ለሀገር ግንባታ ትልቅ ጸር መሆኑ ነው፤ ባለፉት ሰላሳ አመታት፤ ለእዚህ መርዘኛ አስተሳሰብ በሀገራችን በቅሎ ማቆጥቆጥና ማደግ በዋነኝነት ህወሐትና ኦነግ ተጠያቂወች ናቸው፡፡ እነሱ በጋራ የተከሉት ህገመንግሥት ነው በሀገራችን የግንባታ ጉዞ ላይ ትልቅ ጋሬጣ የተከለው፡፡ ሌላዉ ቢቀር “ለብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች” በፈለጉበት ጊዜ “የመገንጠልንና ክልል የመመስረትን” መብት ያለገደብ በህገመንግስቱ አንቀጾች (39 እና 47)ን የሰጧቸዉን ብቻ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ሀገር በጋራ ለመገንባት የሚመኝ መንግሥት ይህን አያደርግም፡፡ የአንድ ሀገር ሕዝብ ቋንቋዉን፤ ባህሉንና ታሪኩን በእኩል የመንከባከብና የማሰደግ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ድህነትን ለማጥፋትና ለማደግ ግን በጋራ ካልታገለ የትም አይደርስም፡፡ ሕዝብን በክልልና በብሄር በቋንቋ በማለያየት፤ በቂምና በቀል፤ በድንበርና በሀብት ዝርፊያ እርስበርስ በማጋጨት፤ በጠባብ አእምሮ የሌላዉን ባህልና ቋንቋ በማሰጠላትና፤ የሀገርን የጋራ ታሪክ በማፈራረስ፤ ሲፈልጉም ለመገንጠል በቋፍ ላይ ቆሞ በማሰላሰል ሀገር በአንድ ልብ ለመገንባትና ለማበልጸግ ምንም ጊዜ ቢሆን አይቻልም፡፡ የህልም እሩጫ ነው!

 

በእዚህ ረገድ ሀገራችንን በተለይ ባለፉት አመታት በብዙ እርቀት ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ያስቀራት የብሄር ፖለቲካዉ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡ የሚያሳዝነው በተከታታይ የሚመጡት የሀገር መሪወች፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በእዚህ የብሄር ፖለቲካ በመመረዛቸው፤ ይህን ሀቅ በሚገባ ለመረዳት አለመቻላቸዉ ነው፡፡ እስከዛሬ መፍትሄ ሊገኝለት ያልቻለዉና፤ ሀገራችንን ለእድገቷ ብቻ ሳይሆን ለህልዉናዋም ጸር የሆነው ዋናዉ ኋላ ቀሩ ህገመንግሥት እንደሆነም አምነው መቀበል ያዳግታቸዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ የብዘሀነት መገለጫ የሆነችና፤ ከ80 በላይ “ብሄር ብሄረሰቦች” የተለያየ ባህልና ቋንቋ ቢኖራቸዉም፤ እንደዛሬው በብሄር ፖለቲከኞች ዘረኛ አጥር ሳይራራቁ፤ ለዘመናት ተከባብረውና ተፋቅረው፤ ተጋብተዉና ተዋልደው፤ በሰላም የኖሩባት የምታስቀና ሀገር እንደነበረች ዓለም ይመሰክርላታል፡፡ አልፎ አልፎ እንደቤተሰብ የእርስበርስ ግጭት በመሀላቸው ቢፈጠርና፤ የእድገት እንከኖች ቢኖርባትም እንኳን፤ ሕዝቦቿ ይህን ግሩም እሴታቸዉን ለዘመናት ጨርሰው አልተዉም ነበር፡፡

 

በዚህ ግሩም የሀገር ቅርስና እሴት ላይ በመገንባት፤ የተለያዩ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን ታሪክ፤ ቋንቋና ባህል እኩል ትኩረት እየሰጡ በማዳበር፤ የጋራ ሀገራቸዉን ኢትዮጵያን በማፍቀር በአንድነት እንዲያድጉና እንዲበለጽጉ፤ ሚዛናዊና ዘመናዊ የሆነ ህብረ ብሄራዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ሲገባ፤ በመከፋፈልና በመለያየት ተጠምደው ሀገራችንን ከሁሉም ወደኋላ በማስቀረት ለዜጎቿም ሰቆቃ እንድትሆን አደረጓት፡፡ ስለዚህ ዛሬ ዋናዉ አንገብጋቢ ጥያቄ እንዴት አድርጎ ነው ይህን ስር የሰደደ በጠባብ ብሄር አስተሳሰብ ላይ የቆመ የዘረኝነት ስርአትና ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል መቀየርና፤ ሀገራችንን ትክክለኛ አቅጣጫ ማስያዝ የሚቻለው የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ለእዚህ ዋና መፍትሄ፤ ከፋፋዩንና ኋላ ቀሩን የዘረኝነት ስርአት ስር እንዲሰድ በማድረግ ቀጥ አድርጎ ያቆመዉን ህገመንግሥት ማሻሻሉ ወይም መቀየሩ ምንም አማራጭ የለዉም፡፡

 

*********

 

  1. በብሄር ፖለቲካ የቆመው የኢትዮጵያ ህገመንግሥት እንዴት ቢሻሻል ይሻላል?

 

የኢትዮጵያ ህገ መንግሥትን ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር በአንደኛ ደረጃ ህገመንግሥቱ በ1987 ዓም (1994) ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ (ለ29 ዓመት ያክል) ያጋጠሙትን ትላልቅ ፈተናወችን በመመርመርና፤ የሌሎችን ሀገሮች ተሞክሮንም በማገናዘብ፤ በእዉቀት ላይ የተመሠረቱና ለሀገራችን ይበጃሉ የሚባሉ ሀሳቦችን ለምክክር ለሕዝብ በማቅረብ ዉሳኔ ለመድረስ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግሥቱ በመሠረቱ በርካታ ችግሮች ያሉት ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም እዚህ ላይ ለመዘርዘር ቦታ አይበቃኝም፤ በቂ ሙያና አቅሙም የለኝም፡፡ ይሁን እንጅ፤ የህገ መንግሥቱ አንዱ ዋነኛ ችግር፤ በሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች ማለትም በህግ አውጭው፤ ህግ አስፈጻሚዉና ህግ ተርጓሚው መሀል ያሉት ኃላፊነቶችና የስልጣን እርከኖች፤ ወይም የሥልጣን ክፍፍሉ (Separation of Powers) በሚገባ አለመገለጻቸዉና መደብዘዛቸው፤ በመሀላቸዉም በቂ ቁጥጥርና ሚዛናዊ አስተዳደር (Check and Balance) አለመኖሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

 

በእዚህ ረገድ ከየትም ሀገር በተሻለ ከአሜሪካን መንግሥት አወቃቀር ትልቅ ትምህርት ለማግኘት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ከ230 አመት በላይ በማስቆጠር ጸንቶ፤ ለረዥም እድሜ የቆየው የአሜሪካ ፌደራል ስርአት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ሊቃዉንት እንደሚሉትም፤ ይህን ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ስርአት ስኬታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተውጽኦ ካበረከቱት ባህሪወቹ፤ በዋነኝነት የሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች (ህግ አዉጭ፤ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ) ኃላፊነቶችና ስልጣኖቻቸው በህገመንግሥቱ በሚገባ መለየታቸዉና፤ በመሀላቸውም የእርስበርስ ቁጥጥሩና ሚዛናዊ አስተዳደሩ በሚገርም ሁኔታ በጥንቃቄ የታነጸ መሆኑ ሁልጊዜ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ሶስት የመንግሥት ቅርንጫፎች፤ ምንም እንኳን የተለያየ ስልጣን ቢኖራቸዉና በመሀላቸው ቁጥጥር ቢኖርም፤ በአንጻሩ ሶስቱም እርስበርሳቸው እንዲደጋገፉና በጋራ (በቲም) እንዲሠሩ ሆነው ነው በህገ መንግሥቱ የተዋቀሩት፡፡ ይህ የመንግሥት አወቃቀር፤ ሀገሪቱ በየጊዜው ሊያጋጥሟት የሚችሉትን ፈተናወች እየተቋቋመች በአንድነቷ ጸንታ እንድትቀጥል እየረዳ በስኬት በማሳለፍ፤ ህገመንግሥቱንም ትዉልድና ታሪክ ተሻጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

 

የአሜሪካንን ህገመንግሥት ያነጹት የመጀመሪያወቹ አባቶች (“The Founders”) ብዙ ተጨንቀዉና በሀሳብ ተፋጭተው ነው ይህን የመሰለ ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር ሊዘረጉ የቻሉት፡፡ ይህም የሚያሳየው ለእራሳቸው ሳይሆን ምን ያክል ለመጭዉ ትዉልድና ለሀገራቸው ዜጎች መብትና ነጻነት የሚጨነቁ፤ የሚቆረቆሩና አርቆ አሳቢ እንደነበሩ ነው፡፡ ለዚህ የህገመንግሥቱና የፌደሬሽኑ ከ230 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ረዥም እድሜ እራሱ በቂ ምስክር ነው፡፡ እርግጥ በእዚህ ረዥም እድሜው፤ መሠረቱን ሳይለቅ 27 ጊዜ መሻሻያ (Amendment) ተደርጎለታል፡፡

 

ይህን እድሜ ጠገብና የረቀቀ የአሜሪካን ህገመንግስት ለመረዳት ቢያግዝ በሚል አንድ ምሳሌ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፤ የህግ አውጭዉ አካል (Congress) በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጡ አባላት ያሉበት ሁለት ምክር ቤቶች አሉት፡፡ እነዚህም የሕዝብ ተወካዮችና የህግ መወሰኛ (“ሴኔት”) ምክር ቤት ይባላሉ፡፡ አንድ ህግ (Bill) ሲረቀቅ፤ ሁለቱም ምክር ቤቶች በየግላቸው መድረክ ተወያይተዉና ተመካክረው፤ ልዩነቶቻቸዉን ካጠበቡና በስምምነት ካጸደቁት በኋላ፤ ቀጥሎ ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛዉ ህግ አስፈጻሚ አካል ማለትም ወደ ፕሬዘዳንቱ እንዲጸድቅ ይልኩታል፡፡ ፕሬዘዳንቱ ከተስማማበት ያጸድቅና ይፈርምበታል፤ ከዚያም የሀገሪቱ ህግ ይሆናል፡፡

 

ካልተስማማበት ግን ከፈለገ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣኑ (Veto Power) ይሽርና እረቂቁን ወደምክር ቤቱ (Congress) ይመልሰዋል፡፡ ከእዚያ በኋላ ምክር ቤቱ ከፈለገ የፕሬዘዳንቱን ስጋት ለማቃለል ህጉን ያሻሽልና፤ እንዲያጸድቀው እንደገና ወደ ፕሬዛዳንቱ መልሶ ይልከዋል፡፡ አለዚያ ግን የፕሬዛዳንቱን ሀሳብ በመቀበል ህጉን ማሻሻል ካልፈለገ፤ እሱም በህገ መንግሥቱ ደንብ መሠረት፤ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቱን ተጠቅሞ 2/3 ኛ ድምጽ ካገኘ ሊያሳልፈው ይችላል፡፡ ያ ከሆነ፤ ፕሬዘዳንቱ ህጉን አልቀበልም ሊል አይችልም፤ እረቂቁም የሀገሪቱ ህግ ይሆናል፡፡ 2/3 ኛ ድምጽ ካላገኘ ግን ፕሬዘዳንቱ እንደሻረው ይቀራል፡፡

 

ሁለቱ የመንግሥት ቅርንጣፎች ተስማምተውበት የሀገሪቱ ህግ ከሆነ በኋላ፤ ቀጥሎ ሶስተኛዉ የመንግሥት ቅርንጫፍ፤ ማለትም የሀገሪቱ ፌደራል ፍ/ቤትም ህጉን በመመርመር ካልመሰለው ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት ዕድል አለው፡፡ ፍ/ቤቱ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት ስልጣን፤ አንድ የሆነ የመንግሥት አካል (ለምሳሌ ከህግ አስፈጻሚው) ወይም የዜጎች መብት ጠባቂ የሆነ የስቪክ ማህበር፤ ይህ አዲስ ህግ ህገመንግሥቱን ይጻረራል ካለና በፌደራል ፍ/ቤት ክስ ከመሰረተበት ብቻ ነው፡፡ ክሱም ካስፈለገ በይግባኝ እስከ ከፍተኛዉ የሀገሪቱ ፍ/ቤት (Supreme Court) ድረስ ሊሄድ ይችላል፤ ይህ አካል ያሳለፈዉን ህግ ማንም ሊሽርው አይችልም፡፡ የእዚህ ሶስተኛዉ የመንግሥት ቅርንጫፍ፤ የፍ/ቤቱ ኃላፊነት በዋነኝነት በሀገሪቱ የሚወጡት ህጎች ህገመንግሥቱን የሚጻረሩ እንዳይሆኑ ነቅቶ መጠበቅ ነው፡፡ ዜጎችም ይህን ስለሚያዉቁ ማናቸዉም በሀገሪቱ የሚወጣ ወይም የሚጣስ ህግ፤ ህገመንግሥቱን ወይም የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጻረር ከመሰላቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት በፍ/ቤት የመክሰስ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

 

በእዚህ አይነት ሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች ህገመንግሥቱ የሰጣቸዉን ስልጣን በሚገባና በትክክል በመጠቀም፤ እርስበርሳቸውም በቂ ቁጥጥር በማድረግና ተደጋግፎ በመሥራት፤ በህገ መንግሥቱ የተጻፉትን የዜጎች ስብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ፤ ፍትህ የሰፈነበት የፌደራል ዴሞክራቲክ ስርአት በሀገራቸው እንዲያድግ ተግተው ይሠራሉ፡፡ በነገራችን ላይ በክልሎች (States) ወይም ክልሎችና የፌደራል መንግሥቱ መሀል ችግር ካለም ፍ/ቤቱ በህገመንግሥቱ መሠረት ክሱን የማየትና በጉዳዩ የመወሰን መብት አለው፡፡ በዚህ አይነት፤ ሀገሪቱ በየጊዜው ያልጠበቀችው ትልቅ የዉስጥ ወይም የፖለቲካ ቀውስና ፈተና ሲያጋጥማትም፤ ህገመንግሥቱን በመመርኮዝና መፍትሄ በመፈለግ፤ ችግሩን በመፍታት ለበርካታ ጊዜአቶች ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ ስኬታማ ዉጤትን ለማግኘት ችላለች፡፡ ለምሳሌ ፕሬዘዳንት ኒክሰን ትልቅ ጥፋት ስላጠፋ በህገመንግሥቱ መሠረት ከኃላፊነቱ እንዲለቅ ተገዷል፤ ፕሬዘዳንት ክሊንተንም በስልጣን ላይ እያለ የስነምግባር ጉድለት በማሳየቱ በህግ አውጭዉ አካል ተከሶ፤ በህጉ መሠረት ክሱ (Impeachment) በሴኒት ታይቶ በድምጽ ብልጫ በነጻ እንዲወጣ ተደርጓል፤ ዛሬ ደግሞ ፕሬዘዳንት ትራማፕ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ትልቅ ጥፋት አጥፍተሀል ተብሎ በፌደራል ፍ/ቤት ተከሶ ጉዳዩ እየታየ ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ማለት እንዲህ ነው!

 

እንግዲህ ይህን ከላይ ያቀረብኩትን የአሜሪካን ህገመንግሥት ተሞክሮ እንደትምህርት ለመውሰድ ብንሞክር፤ የኢትዮጵያ ህገመንግሥትስ ችግሮቹን ለመፍታት በተለይም በሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መሀል በቂና ግልጽ የሆነ የስልጣን ክፍፍል፤ ቁጥጥርና ሚዛናዊ የሆነ አወቃቀር አለው ወይስ የለውም? የሚለዉን ጥያቄ መርምሮ ለመመለስ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ፤ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህገመንግሥት በሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎቹ መሀል በቂና ግልጽ የሆነ የስልጣን ክፍፍል፤ የቁጥጥርና ሚዛናዊ አስተዳደር አለው ብየ አላምንም፡፡ ስለዚህ ህገመንግሥቱ ሊሻሻል ከተፈተሸ ይህን አብሮ ማየቱ መልካም ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ አንዱም በሀገሪቱ ብዙ ችግር እየፈጠረ ያለውም እሱ ይመስለኛል፡፡

 

በተለይም በህግ አስፈጻሚው ገደብ የለሽ ስልጣንና፤ በሁለቱ፤ ህግ አዉጭዉና ህግ ተርጓሚው ደካማነት ወይንም በህገመንግሥቱ የተሰጣቸዉን ስልጣን፤ ኃላፊነትና ግዴታቸዉን በሚገባ ባለመጠቀማቸው የተነሳ፤ በህገመንግሥቱ የተጻፉት የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩና እየተረገጡ ነው፡፡ ነጻነት፤ ፍትህና እኩልነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ስርአት ሊገነባ ቀርቶ፤ ሀገራችን ጭራሽ ዛሬም ዕድል ብሎላት ወደ ተላመደችው የአምባ ገነንነት ስርአት ተመልሳ ለመግባት በፍጥነት ወደኋላ እየሄደች ይመስለኛል፡፡

 

ዛሬ ያለዉን የኢትዮጵያ ህገመንግሥት የመዋቅር ችግር ለማሳየት፤ ለምሳሌ ያክል ጥቂቶቹን እንድገልጽ ይፈቀድልኝ፤ በአንቀጽ 72 (ቁ 2) ህገመንግሥቱ “ጠቅላይ ሚንስትሩና የሚንስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪወች ናቸው ይላል፤ እንዲሁም በአንቀጽ 53 (ቁ 4) “የምክር ቤቱ አባላት የመላዉ ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፤ ተገዥነታቸዉም ሀ) ለህገመንግሥቱ ለ) ለሕዝቡ ሐ) ለህሊናቸው ብቻ ይሆናል” ይላል፡፡ ህገመንግሥቱ ይህን ይበል እንጅ በተግባር እንደሚታየው ግን፤ የምክር ቤቱ አባላት አንዳንዴ ተገዥነታቸው (ተጠሪነታቸው) ለህገመንግሥቱና ለሕዝቡ ሳይሆን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ይመስላል፡፡ ለእዚህ በርካታ ምሳሌወችን ማቅረብ ይቻላል፤ ቦታ ስለማይበቃን ግን በቅርቡ የሆነ አንድ አስገራሚ ክስተት ብቻ ልጥቀስ፡፡

 

ምክር ቤቱ ከአመት በፊት ህወሐትን “አሸባሪ” ነው ብሎ ወስኖ እንደነበር ሁላችንም እናስታዉሳለን፤ ይሁን እንጅ ከፕሪቶሪያዉ ስምምነት በኋላ (ለፓርላማውና ለሕዝብ በሚገባ ያልተብራራዉ) ጠ/ሚንስትሩ የፓርላማዉን አፈጉባኤ የካቢኔ ሚንስቶሮቻቸዉን መርተው መቀሌ እንዲሄዱና “የአሸባሪዉን” የህወሐት ቡድን መሪወች እንዲያነጋግሩ አዘዟቸው! አፈጉባኤዉም በምክር ቤታቸው ያስወሰኑትን ዉሳኔ ወደጎን ትተው፤ ምንም ሳይሳቀቁ፤ መቀሌ ሚንስትሮችን እየመሩ ሄደው ገና ስያሜው በፓርላማ ላልተሻረለት “ከሽብርተኛዉ ህወሐት” መሪወች ጋር አንገት ለአንገት እየተቃቀፉ፤ ፊታቸው በፈገግታ ፈክቶ፤ ናፍቆታቸዉን ሲወጡና ሲወያዩ ዉለው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ለጠ/ሚንስትሩ ሪፖርት አቀረቡ! የኢትዮጵያ ሕዝብም ጉዱን በመገረም ተመለከተ! አፈጉባኤዉን ወይም ጠ/ሚንስትሩን “ነዉር ነው ተው” ያላቸው ወይም የጠየቃቸው አካል ማንም አልነበረም፤ ሕዝቡም ምንም አቅም ስለሌለው በዝምታ በመገረምና በሀፍረት አለፈው!

 

ያስ ይሁን እሽ፤ ምናልባት ቀላል ነው ሊባልና በመገረም ሊታለፍ ይችላል፡፡ ከእዚያ በባሰ የሚያሳዝነው፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕዝብ የተመረጡ ሆነው እያለ፤ የህግ አዉጭዉ የጸጥታና የደህነነት አካላት በሕዝብ ላይ ብዙ ግፍ ሲሰሩና፤ መንግሥት የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ አቅቶት ምስኪኑ ሕዝብ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል እያዩ፤ ለአመታት ምንም ስቅጥጥ ሳይላቸው መቅረቱ ያሳዝናል፡፡ ለምሳሌ በወለጋ በተደጋጋሚ በሽ የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ሲታረዱና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ፤ ሌላዉ ቀርቶ በፓርላማ ስብሰባ ላይ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ይደረግ ተብሎ ሲጠየቁ እንኳን አልፈቀዱም! ለሕዝቡስ ይቅር እሽ፤ ህገመንግሥቱ እንደሚለው ምኑ ላይ ነው ታዲያ “ለህሊናቸው ተገዥ” የሆኑት?

 

ይህን ጉድ እየታዘበ በማዘን፤ የመረጣቸውና ስልጣን የሰጣቸው ሕዝብ ቢያንስ በሆዱ “ህሊና የላቸዉም” ቢላቸው ምንም አያስገርምም፡፡ እሽ ያም ይቅር በዙሪያቸው በአዲስ አበባ፤ ዜጎች በዘራቸው እየተመረጡ ቤታቸው በላያላቸው ላይ እየፈረሰባቸው በረሀ ሲጣሉ፤ ለአዉሬ ሲዳረጉ፤ ሲደበደቡና ሲገደሉ፤ እነሱም ሆነ የአዲስ አበባ ምክር ቤት፤ የፍትሕ ስርአቱም ምንም ደንታ አልሰጣቸዉም፡፡ ለጊዜዉም ቢሆን የመንግሥትን ስብአዊ መብት ጥሰት አስቁሞ ሁኔታዉን መመርመር አልፈለጉም፡፡ የህግ አስፈጻሚው አካልም ተዉ ሚለው ስለሌለ ግፍ መፈጸሙን ቀጥሏል፡፡

 

በአንቀጽ 55 ተራ ቁጥር 16 ህገ መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በማንኛዉም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማስቆም ሳይችል ሲቀር፤ በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፍቃድ ተገቢዉን እርምጃ እንዲወስድ ለፌደሬሽን ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፤ በተደረሰበት ዉሳኔ መሰረትም ለክልሉ ምክር ቤት ዉሳኔ ይሰጣል” ይላል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ ምክር ቤቱ ይህን ኃላፊነቱንም እስከዛሬ አልተወጣም! በተጨማሪ በእዚህ አንቀጽ (55) ቁጥር 18 ላይ ህገመንግሥቱ እንዲህ ይላል፤ “ለህግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛዉም ሥልጣን ላይ የምክር ቤቱ አባላት በ1/3ኛ ድምጽ ሲጠየቁ ምክር ቤቱ ይወያያል፤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየዉን እርምጃ የመዉሰድ ስልጣን አለው” ይላል፤ እርግጥ ምን አይነት “እርምጃ” ነው የሚወስደው የሚለው ባይብራራም፤ ምክር ቤቱ ግን ይህን ስልጣኑንም እስከዛሬ አልተጠቀመበትም፡፡ ይህም ለአስፈጻሚ አካሉ ህገመንግሥቱን ያለገደብ መጣሱንና በሕዝብ ላይ ግፍ መሥራቱን እንዲቀጥልበት የልብ ልብ የሰጠው ይመስላል፡፡

 

በነገራችን ላይ በአንቀጽ 50 ተራ ቁጥር 3 “የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ የስልጣን አካል የፊደራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው” ይላል ህገመንግሥቱ፤ ምስኪኑ ሕዝብ ፈርዶበት! በምን ስልጣኑ ነው ምክር ቤቱን ሊቆጣጠረው የሚችለው? አምስት አመት ቆይቶ በምርጫ? ወይስ በሶስተኛው ከፍትሕ ስርአቱ መዋቅር ጋር በተገናኘው፤ ሌላ የመንግሥት ቅርንጫፍ በ”ፌደራል ምክር ቤቱ”? በእሱማ እንዳይቆጣጠረው አይችልም፡፡

 

የፌደራል ምክር ቤቱ በህገመንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤትንም ሆነ ህግ አስፈጻሚዉን አካል የመቆጣጠር ስልጣን አልተሰጠዉም፡፡ አባላቱ የሚመረጡትም በሕዝቡ ሳይሆን በክልል ምክር ቤቶች ነው፤ እርግጥ “የክልሉ ምክር ቤት ከፈለገ በሕዝብ ሊያስመርጣቸው” ይችላል ይላል ህገመንግሥቱ፤ (ከፈለገ!) እስኪ እግዜር ያሳያችሁ፤ አሁን እዉነት እንደዚህ የብሄር ፖለቲካ አምባገነንነት በገነነበት ሀገር የክልል ምክር ቤቱ የፌደራል ምክር ቤቱን ተወካዮች በሕዝብ የሚያስመርጥ ይመስላችኋል? ከዚያስ ይልቅ ምናለበት የፌደራል ምክር ቤቱ ወኪሎች በቀጥታ በሕዝብ ይመረጣሉ ቢል ኖሮ ህገመንግሥቱ፤ እሱ ትንሽ ይሻል ነበር፡፡

 

በነገራችን ላይ የክልሎች ህገመንግሥት ደግሞ እራሱን የቻለ ሌላ የሀገሪቱ አንድነት ጠንቅ ነው ቢባል ከእዉነት የራቀ አይሆንም፡፡ እሱን እዚህ ላይ ለመዘርዘር ያዳግታል፡፡ ሌላዉ የሚገርመው፤ የተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣዉን ህግ ለቁጥጥር እንዲያመች የሚመረምርና ድምጽ የሚሰጥበት ሌላ የመንግሥት አካል አለመኖሩ ነው፤ የፌደራል ምክር ቤቱም አይችልም፡፡ እረቂቁ በተወካዮች ምክር ቤት በድምጽ ብልጫ ከጸደቀ በኋላ በቀጥታ ለፕሬዘዳንቱ ለፊርማ ይላክና ከእዚያ በኋላ የሀገሪቱ ህግ ይሆናል፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች በጣምራ የሚሰሩትም ኃላፊነት በሚገባ አልተብራራም፡፡

 

ይህን ብለን፤ እስኪ አሁን ደግሞ፤ ወደሶስተኛዉ የመንግሥት ቅርንጫፍ ወደፍትሕ ስርአቱ ትኩረት እናድርግ፤ ይህማ በእኔ እምነት ጭራሽ የተጠላለፈና የተወሳሰበ፤ ለመረዳትም የሚያስቸግር ነው፡፡ በህገመንግሥቱ መሠረት የፍትህ ስርአቱን ከሚያስከብሩት ከላይ የተጠቀሰው የመንግሥት ቅርንጫፍ የፌደራል ምክር ቤቱ አንዱ ሲሆን በዋነኝነት ግን ዳኞች ናቸው፤ ዳኞች በፊደራልና በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ሲሆኑ፤ “የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት በፌደራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ ዳኝነት ስልጣን ይኖረዋል” ይላል ህገመንግሥቱ (አንቀጽ 80 ቁ 1)። ይሁን እንጅ የፌደራል ምክር ቤቱ ደግሞ ህገመንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን አለው ይላል (አንቀጽ 62 ቁ 1)፤ የህገመንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳም በፌደሬሽኑ ምክር ቤት ዉሳኔ ያገኛል ይላል ህገ መንግሥቱ (አንቀጽ 83 ቁ 1)። እዚህ ላይ በሁለቱ አካልት መሀከል (በፌደራል ምክር ቤቱና በዳኞች ወይም በፌደራል ጠ/ፍ/ቤት መሀል) የኃላፊነት “ግጭት” አያስነሳም ወይ የሚል ጥያቄ ቢያስነሳ ምንም አያስገርምም፡፡

 

ይህ ብቻ አይደለም፤ ለፌደራል ምክር ቤቱ ተጠሪ የሆነ (ለጠ/ፍ/ቤቱ ሳይሆን) ሌላ ተጨማሪ ወይም ደጋፊ ስልጣን ያለው አካልም አለ፤ ይህ አካል “የህገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ” ይባላል፡፡ ችግሩ የፌደራል ምክር ቤቱ ህገመንግሥቱን በሚመለከት ጉዳይ ዉሳኔ የሚሰጠው፤ በቅድሚያ በዚህ በስሩ ባለው አካል ተጣርቶ ከቀረበለት በኋላ ነው (አንቀጽ 84 ን ይመልከቱ)፤ ይህ “ህገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ” ከፈለገ ጉዳዩን (ክሱን) መርምሮ “ህገመንግሥትን አይመለከትም” ብሎ ወደ ፌደራል ምክር ቤቱ ሳይልክ ሊጥለውም ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ፤ ጠ/ፍ/ቤቱ 11 አባላት ያሉት የዚህ “የሀገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ” ሰብሳቢ ነው እንጅ በግሉ (ወይም ከሌሎች ዳኞች ጋር ሆኖ) የመወሰን ስልጣን የለዉም፤ እንግዲህ ዜጎች ፍትሕ ለማግኘት መሄድ ያለባቸዉን ዉጣ ዉረድ በእዚህ “ቢሮክራሲ” ብቻ ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

 

በእኔ እምነት፤ እነዚህ የአንድ የመንግሥት ቅርንጫፍ (የፍትህ) አካል የሆኑት ሁለቱ (ማለትም የፊደራል ምክር ቤቱ፤ ጠ/ፍ/ቤቱና/ዳኞች) በስልጣን ሊጋጩ የሚችሉበትና፤ በመሀሉ ሕዝቡ ቀልጣፋ ፍትሕ በማጣት ሊንገላታና ሊሰቃይ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ይመስለኛል፡፡ በእዚህ አወቃቀር፤ በተለይም ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ወይም ዳኞች የሚወስኗቸዉን ዉሳኔወች በተግባር ለማዋል የሚያስፈጽመውን አካል ማለትም፤ ህግ አስፈጻሚውን ለመቆጣጠርም ቀላል አይሆንም፡፡ ምናልባት ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ብየ የምገምትው፤ በተደጋጋሚ ፍ/ቤቶች የሚወስኗቸዉን ዉሳኔወች እየጣሱ ፖሊሶች ዜጎችን በእስር ቤት በማቆየት የሚያሰቃዩበት አንዱ ዘዴ ነው፡፡

 

ይህ መጥፎ ልምድ በግልጽ ህገ መንግሥቱን የሚጻረር ቢሆንም፤ አሁን ባለው የፍትሕ ስርአት፤ “ለፌደራል ምክር ቤቱ ጉባኤ” ቀርቦና ተጣርቶ፤ ለዚያዉም ካለፈ “ለፌደራል ምክር ቤት” ቀርቦ ከተሳካ፤ ህገ አስፈጻሚዉን በህጉ መሠረት ይህን “በስልጣን የመባለግ” ልምዱን (Power Abuse) ለአንዴም ለመጨረሻም ለማስቆም ምን ያክል አዳጋች አቀበት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በእኔ እምነት ምናልባት በየእርከኑ ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ የተዘረጋ “የህገ መንግሥት ፍ/ቤቶች” (Constitutional Courts) መዋቅር ቢኖር፤ ይህ ችግር ሊቃለልና ዜጎችም ቀልጣፋ ፍትሕ ሊያገኙ ይችሉ ነበር፡፡

 

በእዚህ ሁሉ የህገመንግሥት እንከን መሀል የህግ አስፈጻሚው አካል (መከላከያን ደህንነትንና ፖሊስን የሚቆጣጠረው) መረን የለቀቀ ስልጣን ተሰጥቶት፤ በማን አለብኝነትና በእብሪት ተሞልቶ፤ የሕዝብ ተውካዮች ምክር ቤቱም አሁን ባለው ህገመንግሥት የተሰጠዉን ዉሱን የመቆጣጠር ስልጣን እንኳን ለመጠቀም ወኔና አቅም ስለተሳነው፤ በሀገሪቱና በሕዝብ ላይ ብዙ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ እግዜርን ካልፈራ በቀር ገና ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ለጭቁኑ ሕዝብ ድምጽ ሊሆኑ የሚችሉትን እንደነጻ ሚድያ ያሉትንም እያፈነ፤ የስቪክ ማህበራትን፤ ለምሳሌ “የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና” “እንባ ጠባቂ” የሚባሉትን በህገ መንግሥቱ የተፈቀዱትንም ተቋሞች እያኮላሸ የአምባገነንነት ስርአት በመገንባት ላይ ያለ ይመስላል፡፡

 

ይህ አካሄዱ በሀገሪቱ በብሄር ፖለቲካና በዘረኝነት የተደገፈዉን ስርአትም እንኳን ለመግታት ይቅርና ይበልጥ እንዲያድግና እንዲጠናከር እያደረገው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስተሩ በየጊዜው “ተቋም እየገነባን ነው” ይበሉ እንጅ፤ ህግ አስፈጻሚው አካል “ሕዝባዊ፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋሞችን” እየቦረቦረና እየናደ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፤ ከጠባብ ብሄረተኞች ጋር በመተጋገዝ፤ ህገ መንግሥቱም እንዳይሻሻል ወይም እንዳይቀየር በግልጽ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡

 

ያም ሆነ ይህ፤ ከላይ እንደተጠቀሰው፤ ከተቻለ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ህገመንግሥት ለማሻሻል ወይም ለመቀየር መፈተሽ ካለባቸው ዋና ዋና ባህሪወች አንዱ የመንግሥቱ አወቃቀር ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በሶስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መሀል ግልጽ የሆነ የስልጣን ክፍፍልና (Separation of Powers) ጠንካራ የቁጥጥርና ሚዛናዊ አስተዳደር (Check and Balance) ስርአት እንዲኖረው ቢደረግ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብዙ ይረዳል ብየ እገምታለሁ፡፡ በእዚህ ረገድ የአሜሪካንን ህገመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሀገሮች ተሞክሮ፤ ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካንና የናይጀሪያን ማየቱም ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከእነሱና ከሌሎችም ተሞክሮ በመቅሰም ለሀገራችን የሚበጅ ትክክለኛ ህገመንግሥት መቅረጽ ይቻል ይሆናል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 

እርግጥ ዛሬ በሀገራችን የተዘረጋዉ የፖለቲካና የመንግሥት ስርአት ፓርላሜንታዊ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ከህገመንግሥቱ መሻሻል ጋር አያይዞ የትኛዉ ስርአት ለሀገራችን ይበጃል? ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዘዳንታዊ? የሚለውንም ጥያቄ አብሮ ማየቱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱም ስርአቶች የራሳቸው የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሏቸው፤ ሆኖም በእኔ እምነት በተለይም በብሄር ፖለቲካ ሰበብ ዛሬ በሀገራችን ስር ሰዶና ተንሰራፍቶ የሚገኘዉን የዘረኝነት ስርአት ለማስቆም፤ ፕሬዛዳንታዊ ስርአት የተሻለ አማራጭ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በሽግግሩ ጉዞ መንገራገጭ ሊኖር ይችላል፤ እሱ ያለ ነው፤ በመጨረሻ ግን ህገመንግሥቱ ቢሻሻል ወይም ቢቀየርና ፕሬዜዳንታዊ ስርአት ቢገነባ፤ ዘንቦ ተባርቆ ለሀገራችን የፖለቲካ ህይወት ጥሩ ቀን ይወጣል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 

የፕሬዘዳንትነት ስርአት ይሻላል የምልበትን ምክንያቶች በሚቀጥለው ጽሁፌ (በክፍል-4) ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በዚያዉም እግር መንገዴን በብሄር ላይ የቆመውንና ዉስብስቡን “የፌደራል አወቃቀር” እንዲሁም “የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቱን” ስርአትም እንዴት አብሮ ከህገ መንግሥቱ ጋር ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አማራጭ ሀሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፤እስከዚያ ግን ዋናዉ ማሳሰብ የምወደው ህገመንግሥቱን ለማሻሻል አሁንም የሀገራዊ ምክክሩ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡

 

  1. ብሄራዊ ምክክሩ ለምን ያስፈልጋል? እንዲሳካስ ምን መደረግ አለበት?

 

ባለፉት 50 ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ቀውሶችንና ችግሮችን አሳልፋለች፤ ለእዚህም አንዱ ዋና መንስኤ በተለይም “የፖለቲካ ልሂቃኑ” ልዩነታቸዉን በሰላም በመፍታት ፋንታ፤ በሁለቱም ወገን ያሉት፤ የመንግሥት ስልጣን የያዙትም ሆነ ሊይዙ የሚፈልጉት በጉልበት ለማቸነፍ ሲሞክሩ፤ ሕዝቡን በተለይም ወጣቱን በየጊዜው በጦርነት እየማገዱ ሀገራችን ወድማለች፡፡ ስለዚህ ካለፈው ታሪካችን ተምረን፤ የሀገራችንን ዉስብስብ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት በሰላማዊ መንገድ “ሀገራዊ ምክክር” ማድረጉ አማራጭ የለዉም ብየ አምናለሁ፡፡

 

ችግሩ ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ አሁን ያለው የሀገራችን ሁኔታ አመች ይሆናል ወይ የሚለው ነው፤ ይህ ጥያቄ ደጋግሞ ቢመጣ አያስገርምም፤ ግን ሁለተኛዉ ከባድ ጥያቄ ደግሞ ሌላ ምን አማራጭ አለን ታዲያ የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ሁለቱንም ለመመለስ በቅድሚያ ወደድንም ጠላንም ያለውን መንግሥት ተባባሪነት፤ ቅንነትና ቆራጥነት ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪ ግን ኢትዮጵያን አፍቃሪ የሆኑ ዜጎች በሙሉ ሀገራቸዉን ለማዳን በጋራ መነሳት አለባቸው ብየ አምናለሁ፡፡ ብሄራዊ ምክክሩ እንዲካሄድና እንዲሳካም በቁርጠኝነት ተደራጅተው በሰላማዊ ትግል መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ መረዳት ያለብን በርካቶች ጽንፈኛና ጠባብ የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች፤ ሀገራዊ ምክክሩን ከልባቸው አይፈልጉትም፤ ህገ መንግሥቱም እንዲሻሻል ወይም እንዲቀየር አይፈልጉም፤ ለምን ቢሉ ጥቅማቸው ይነካልና!

 

ስለዚህ ሀገራቸዉን ማዳን የሚፈልጉ ኢትዮጵያዉያን በትግላቸዉ ማተኮር ያለባቸው ህገመንግሥቱን ለመቀየር እንዲተባበር፤ በመንግሥት ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ለማሳደር መሆን አለበት ብየ አምናለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን አሁን ባለው ህገመንግሥትም ኃላፊነቱንና ግዴታዉን ተቀብሎ በማክበር፤ በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉን ግፍ፤ የዴሞክራሲና ስብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲያቆምና፤ ህግንም ማክበርና ማስከበር እንዳለበት ደጋግመው ማሳሰብና ማስገደድ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች በነጻነት የመናገር፤ የመጻፍና የመሰብሰብ መብታቸው ሳይከበር፤ የሕዝብ ድምጽ የሆኑትን ጋዘጠኞችም እያፈኑ በመዉሰድ መደብደብና ማሰቃየት ሳይቆም፤ በህግ የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲወች ያለስጋት መሰብሰብና፤ እንደልባቸው በየትኞቹም የሀገሪቱ ክልሎች እየተዘዋወሩ ሀሳባቸዉንና ፕሮግራማቸዉን ለሕዝብ ማስረዳት ካልቻሉ፤ ስኬታማና እዉነተኛ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ አይቻልም፡፡

 

በተጨማሪ ሀገሪቱ ሰላም አጥታ በዉጥረት ላይ እያለች ስኬታማ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ በርካቶች መንግሥት የዜጎችን መብት ለመጠበቅና፤ የሀገራችንንም ጸጥታ፤ ሰላምና አንድነት ለማስከበር ከልቡ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ስለሌለው፤ ሀገራዊ ምክክሩ አይደረግም ወይም አይሰራም፤ ቢደረግም ለይስሙላ እንጅ ስኬታማ አይሆንም ብለው ያምናሉ፡፡ እርግጥ ይህ አደጋ እንዳለ ይሰማኛል፤ ሆኖም ሁኔታወች እንዲቀየሩ በጋራ ተባብሮ ኃይልን አሰባስቦ በሰላማዊ ትግል መታገል እንጅ ተስፋ መቁረጡ ለዉጥ አያመጣም፡፡

 

ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድም የለንም፤ ደም መፋሰሱ ይበቃናል! ሰላም ሲጠፋ ዋና የሚጎዳዉ ምስኪኑ ሕዝብ ነው! ኋላ ቀሩ ህገመንግሥትና በዘረኝነት ላይ የቆመው “የፌደራል ስርአት” በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ በሕዝብ ምክክር፤ ፍላጎትና ድምጽ ካልተሻሻለ ወይም ካልተቀየረም፤ ሀገራችን ምንጊዜም ቢሆን ዘላቂ ሰላም አታገኝም፡፡ ሕዝባችንም ነጻነትና ፍትህ ሊያገኝና ከድህነት ሊላቀቅ አይችልም፡፡ ያ ብቻ አይደለም ሀገራችን ለህልዉናዋ ያሰጋታል፡፡ ለእዚህ ነው ተባብሮ በሰላማዊ ትግል መታገል የሚያስፈልገው! መደራጀት ነው የሚጎድለው እንጅ ኢትዮጵያን አፍቃሪ የሆነው ሕዝባዊ ኃይል ከዘረኞች፤ ጽንፈኞችና ጠባብ ብሄረተኞች እጅግ አድርጎ ይበልጣል፡፡

 

በሚቀጥለው ጽሁፌ (በክፍል 4) ዉስብስቡ “በብሄር ላይ የቆመው ዘረኛዉ ስርአት፤ የፓርቲና የክልል ፌደራል መዋቅሩ” እንዴት ሊሻሻል ይችላል? በሚለው ሀሳቤን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያ በሰላም ያገናኘን!

 

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ! ለሀገራችን ሰላም ያዉርድልን!

 

ዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)

በሀገር ፍቅር ጉዞ መጽሐፍ ደራሲ

መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓም (April 8, 2023)

 

http://amharic-zehabesha.com/archives/180532

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ “ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና

ጀልባዋ አትሰምጥም፤ የሚሰምጥ ግን አለ!

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] (https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/) ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

Go toTop