ለአቶ አዲሱ አረጋ አድርሱልኝ – ገለታው ዘለቀ

April 5, 2023
አቶ አዲሱ አረጋ 1 1
#image_title

አቶ አዲሱ ሆይ! ይህቺን ቁጥብ መልእክት የምልክልዎ በውነት ከልቤ እያዘንኩ ነው። እርስዎ ስለ ሩዋንዳ ያነሳሉ። ሩዋንዳ ውስጥ ወደ ስምንት መቶ ሽህ ሰው ካለቀ በኋላ ሩዋንዳ ወደ ነፍሷ ተመልሳ ዛሬ ወደ ልማት አተኩራለች።

እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት አቶ አዲሱ::  እርስዎ የሚያማክሩት  አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ከመጣ በሰሜኑ ጦርነት ብቻ አንድ ሚሊዮን ወገናችን አለቀ አይደለም ወይ? በወለጋ በየወሩ የምንሰማው እልቂት ሲደመር በብዙ ሽህ አማሮች አለቁ እኮ አቶ አዲሱ! ፣ በሶማሌና ኦሮምያ ግጭት መቶ ሽህ ሰው አለቀ እኮ አቶ አዲሱ! ቤንሻንጉል ውስጥ በነበረው ፍጅት ሽህ ሰው አለቀብን እኮ! በጉጂና ቡርጂ ውጊያ ብዙ ወገን አጣን እኮ፣ በጌዲኦና በጉጂ ጦርነት ሽህ ሰው አልቆ ሚሊዮን ተፈናቅሎብናል እኮ! ደብብ ውስጥ ባሉ የብሄር ግጭቶች እልፍ መፈናቀል እልፍ ስደት አየን እኮ፣ አብይ አህመድ ስልጣን ከያዘ በብሄር ግጭት የሞተውንና የተፈናቀለውን በእርሳቸው ቋንቋ ብንደምረው የሩዋንዳውን የእልቂት መጠን አልፈን ከሄድን ውለን አድረናል እኮ! እኛ ከሩዋንዳ የተለየነው እውነት ነው በየግጭቱ ለሞቱ ወገኖቻችን አጽም ማስታወሻ አልተውንም። እንደ ባህላችን እንደደ ወጋችን አልቅሰን አልቀበርንም። ምንድን ነው የሚሉት አቶ አዲሱ?   ሩዋንዳ ላይ ያልታዬ የአገዳደል ጭካኔ የታየው በዚህ ዘመን እኮ ነው፣ እንዴት ነው የዚህ ሁሉ የወገንዎ እልቂት ልብዎን ሳይሰብር ሩዋንዳ የሄዱት። ለመሆኑ አጽሙ እንኳን ያልተሰበሰበው ወገንዎ ኢትዮጵያዊ እንዴት አላሳዘነዎትም?

አብይ ይውረድ ፖለቲካዊ ለውጥ ይምጣ የምንለው እኮ ለዚህ ነው አቶ አዲሱ። ከሩዋንዳ በላይ ወገን ስላለቀብን ነው እኮ። ሚሊዮን ወገናችን ስለተፈናቀለ በደል ስለበዛ እልቂት ስለበዛ እኮ ነው! እናንተ ሰዎች ለመሆኑ ይሄ ሁሉ የሀገራችን ህዝብ እልቂትና መፈናቀል  እንዴት አላስደነገጣችሁምና ነው ስለ ሩዋንዳ የምታወሩት? አይበቃም ወይ?

አቶ አዲሱ ሆይ ስለዚህ አሁን የሚሻለው  አብይን ገለል አድርጉና የፖለቲካ ለውጥ አድርጋችሁ ለሁሉን አቀፍ የሽግግር ስርአት ሥሩ። ይህን ብታደርጉ ይሻላል። ይበቃል። በእርስ በርስ እልቂት ከሩዋንዳ የቀለጠ ኪሳራ አስመዝግበናል። በቃ።  ደግሞ በቃ ስንል እያስፈራራችሁ ሀገር አታፍርሱ። ውጥረት ላይ አትቆዩ ውጥረት አይቀጥልም። እባካችሁን እባካችሁን እባካችሁን…

—————–

ሩዋንዳ የሆነችውን ሁሉ ከመሆኗ በፊት የሩዋንዳ ጽንፈኛ ሚድያዎች የኛዎቹን ግጭት ጠማቂ ጽንፈኛ ሚዲያዎች ይመስሉ ነበር!

(አዲሱ አረጋ)

በነፃነትና በልቅነት፤ በግልጽነትና በክፍትነት መሀከል ያለውን ግልጽ ድምበር ለመለየት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርትን ወይም መሰል ሙያዎችን መማር የግድ አይልም! ምክንያቱም ይህን ለመገንዘብ፣ ለመለየት እና ለመረዳት ሰው መሆን ከበቂ በላይ በመሆኑ፡፡
እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለ በስርዓት በተገራ ፤በስርዓት በሚመራ ማህበረሰብ ውስጥ ተወልዶ ያደገ የትኛውም ሰው የቱን መቼ ፤ምንን እንዴት ማለት እንዳለበት፤ ማለት የፈለገውንም ለምን ፋይዳ ማለት እንደሚኖርበት ጠንቅቆ ይረዳል! የማህበረሰቡ ፣ የስርዓቱ እና የእሳቤው ውጤት ነውና ይህንን በዚያው አግባብ ይጠቀማል ተብሎ ይታመናል፡፡
የሀገራችንን የዲጂታል ሚዲያውንም ሆነ የሜንስትሪም ሚዲያውን ሚና ፣ ባህል እና ሚድያው የተቃኘበትን ተፈርጥሮ ስንመለከተው በዚህ ማዕቀፍ ወይም ደግሞ በዚህ መርህ የሚመራ እንዳልሆነ ለመመልከት ብዙ ልፋት የማይጠይቅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የትኛውም እውነት ለእውነትነቱ ብቻ ሲባል፤ የትኛውም ዜና እና መረጃ ለዜናና መረጃነቱ ፋይዳ ብቻ ሲባል ወደ ህዝብ አይለቀቅም ወደ ህዝብ እንዲደርስም አይደረግም!
መረጃን ከህዝብ እና ከሀገር ጥቅም ፣ ከዓለም አቀፍ አሁናዊ አተያይ እና ፋይዳ አንጻር ተገንዝቦ እና ተንብዮ ፤ መርምሮ እና አመዛዝኖ ለህዝብ ማቅረብ የሚድያ ባለሞያ ሁነኛ ተግባር እና የሙያ መለኪያ ነው! ከዚህ አንፃር አንዳንዶቹን የጽንፈኛ ሚዲያ “ተንታኞች” ከታጠቁት የጥላቻ መርዝ ውጭ በትምህር ቤት ደጃፍም ያለፉ አይመስለኝም።
አንድ መረጃ ህዝብ ጋ ከደረሰ በኋላ ለሀገር ልማትና እድገት ፤ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ፤ አብሮነትና የጋራ እሴት የሚፈይደው አንዳች ቁምነገር እስከሌለው ድረስ ከመቅረቡ ይልቅ ባለመቅረቡ ብዙ ማትረፍ ይቻላል፡፡
ለመጠፋፋትና ለመተላለቅ ፤ አንደኛውን በሌላኛው ላይ ለማነሳሳትና የሌላኛውን ሀሳብ በአንደኛው ላይ ለመጫን የሚደረግን ‹‹ የእኔን ጭነት ተሸከም›› አይነት ያረጀ ያፈጀ እና የምንኖርበትን ዘመን ያልዋጀ ከንቱ ህልምን ለማንጸባረቅ እና ለማስተጋባት የሚደረግ የበቀቀን አይነት ከንቱ ልፈፋ ከሚድያ መርህ እና ስነ ምግባር በተጻራሪ የቆመ ነው፡፡ ህዝብን እና ሀገርንም የካደ ነው፡፡
ለዛሬ ብሎም ለነገና ከነገ ወዲያችን ምንም ዋጋ ካላማበርከቱ ባለፈ ምን ያህል አስከፊ ፣ አክሳሪ ፣ አጥፊና እና የሰውን ልጅ ባህሪ በተጻረረ መልኩ ዋጋ እንደሚያስከፍል ከዚህ ቀደም ‹‹ይህቺ ኪጋሊ ናት›› በሚል ጽሁፍ ባሰፈርኩት መጣጥፍ ላይ ለመግለጽ ሞክሪያለሁና በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ እና ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቤ ወደ ጀመርኩት የመረጃ እና የመረጃ ሰጪ ባለሞያዎች እና ተቋማት ርዕሰ ጉዳይ ላምራ…
ዜናዎች ወይም ደግሞ መረጃዎችም መድረስ በሚገባቸው ግዜና መጠን ለህዝብ መድረስ አለባቸው! የመረጃ ወይም ዜና ተቀባዮች ከነዚያ ዜናዎች እና መረጃዎች ትምህርትን፣ እውቀትን አሊያም ሌላ የተዝናኖት መልክን ወይንም ውጤትን ያገኛሉ ፤ ይማራሉ፣ ያውቃሉ ይጠነቀቃሉ ፣ይዝናናሉ ውዘተ … ነገር ግን አንድ ጋዜጠኛ ወይንም የሚድያ ተቋም ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት ፣ ለዘመናት አብሮ የዘለቀ የህዝቦችን አብሮነት ለመናድ ፤ የአገርን ሰላም ለማናጋት ብሎም ደህንነቷን እና ክብሯን አደጋ ላይ ለመጣል ከሚደረጉ ርብርቦሾች ጋር ሲያብር … አብሮም ዘመኑ እና ግዜው የሰጠውን የብዙሀን መገናኛ መንገድን ለዚህ አፍራሽ ተግባር ሲጠቀም ፣ ሲያውል እና የርብርቦሹ ልሳን ሆኖ ሲታይ እጅጉን ያሳዝናል፡፡
በተለይም በኢትዮጵያዊያን በሚመሩ ሚድያዎች እና ኢትዮጵያዊያን ከሆኑ የሚድያ ባለሞያዎች አንደበት ሲሆን እጅጉን ያማል! ይሰቃልም! “ይህቺ ኪጋሊ ናት” በሚለው ጽሁፍ ዉስጥ ካሰፈርኳቸው ቁም ነገሮች አንጻር በሚዲያ ስም የተደራጁ ግጭት ጠማቂዎች፣ በበሉበት የሚጮሁ እና የጮሁባችውን የሚያስተጋቡ በቀቀኖች የተቀበሏቸውን፤ ተቀብለውም ለበሉበት የመጮህ አባዜ መርጠው ያስተጋቧቸውን አንዳንድ አፍራሽ ከጽሁፌ እንድምታ በተቃራኒ ነገሮችን ፍሬም ለማድረግ የተደረጉ የግጭት ጠማቂዎችን ሙከራ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡
በጽሁፌ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ ያነሳሁት የአንደኛውን ገዢ ትርክት በሌላኛው ላይ ለመጫንና ያንንም በግድ ለማድረግ የሚደረጉ መውተርተሮችን ወይም ደግሞ የራስን ገዢ ትርክት ሌላውን እንዲገዛ የማስገደድን፣ በዛ ላይ የመስራት፣ ደጋግሞ እንደ ቁራ ጮሆ ሰዎች ዕውነት ያልሆነውን እውነት እውነት ብለው እንዲቀበሉት ለማስገደድ የመሞከር ፅንፈኝነት የተጠናወታቸውና የተጋባባቸው በርካታ ሚድያዎች (የዲጂታልና ሜይንስትሪም ሚዲያዎችን ማለቴ ነው) እዚህም እዚያም ለመመልከት ብዙ ልፋት የሚጠይቅ አይደለም፡፡
ይህ አካሄድ ከዚህ በፊት ሰርቶ ነበረ ቢባል እንኳን አሁን መስራት በሚችልበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ለቅርብም ለሩቅም ለወዳጅም ለጠላትም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጓት ወይም ደግሞ የሚገባት በጋራ ተነጋግረው፣ ተወያይተው የጋራ ታሪክ የጋራ እሴት እና የጋራ አገር ለመገንባት የሚደረግ ርብርቦሽ እንጂ የአንደኛውን ታሪክ ፣የአንደኛውን ባህል ፣የአንደኛውን እምነትና የአንደኛውን የማህበረሰብ ፍልስፍና በሌላኛው ላይ ለመጫን የሚደረጉ አካሄዶችና የሚታዩ መጋጋጦች አይደሉም፡፡
መሰል መጋጋጦች ተቀባይነት የሌላቸው ያለፈባቸው፣ ያረጁና ያፈጁ የትላንት ተረት- ተረቶ ናቸው፡፡
ጽንፈኛ ሚዲያዎች በሃገሪቱ ብሎም በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ህጎች ፣ አዋጆች እና በሌሎች ህግጋት ለመመራት ፍቃደኝነቱ፣ ብቃቱና መረዳቱ የሌላቸው በሚድያ ሰሌዳ የሚንቀሳቀሱ የስልጣን ጥመኞች እዚህም እዚያም በሚያናፍሷቸው ህዝብን በህዝብ ላይ በሚያነሳሱ ፤በከተማ ውስጥ ሁከትን እና ብጥብጥን በሚፈጥሩ ፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ለመግደልና ለማፈን በሚያሴሩ ብሎም ጦርነት እና ስርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር በሚለፍፉ እና በሚለፉ ጋዜጠኛ ነን ባይ እኩያን ሀገርም ሆነ ህዝብ ሊጠቅሙ እንደማይችሉ ግልጽ ነው፡፡
የሀገር እና የህዝብን ጥቅም ወደ ጎን ብለው ለአፍራሽ ተልዕኮዎች እንደበቀቀን መጮህ ምናልባት ከላኪዎቻቸው የሚወረወርላቸው ሳንቲም ያስገኝላቸው እንደሆን እንጂ በሀገር ግንባታ እና በህዝቦች አንድነት ላይ የሚያበረክተው ፋይዳ አይኖረውም፡፡
እነዚህ የዲጅታል ሚዲያው የፈጠረውን አጋጣሚ ወይም የሰጠውን በረከት ለዕኩይ አላማቸው ማስፈጸሚያ እንደ መልካም እድል በመጠቀም ሃገር ላይ ጦርነት የሚያውጁ ፤መንግስትን ለመገልበጥ የሚቀሰቀሱ፤ ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት፤ ለውጭና ለውስጥ ፍርፋሪ ጣዮቹ ተመችተው የነሱን ፍርፋሪ የሚጠብቁና የሚናፍቁ እራሳቸውን እንደ ጋዜጠኛ እና እንደ ሚዲያ ሰው የሚቆጥሩ ሰዎች የጋዜጠኝነትን እና የሚድያን ሀሁ ያልቆጠሩ በዘርፉም ትምህርትም ቤት ሄደው የወጡ የማይመስሉ መሆናቸው በሀገር ላይ የደቀነውን አደጋ በግልጽ ያሳያል ፡፡
መንግስት በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በዲጂታል ሚድያውም ሆነ በሜይን ስትሪም ሚዲያው የሚሰሩ ጋዜጠኞችን እውቀት የመገንባት የማጎልበት የሚሠሩበትን ምህዳር የማመቻቸት ህግና ስርኣትን አክብረው የሚሰሩትን በሙሉ የማስተባበር የመምራት የመደገፍ ግዴታው እንዳለ ሆኖ አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብና እና እንዲቀጡ የማድረግ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ይወጣልም፡፡ እንጀራው ላይ የሚሻሙና መሶባቸው አደጋ ላይ የወደቀባቸው እነዚያ ጋዜጠኞች ወይም ደግሞ ጋዜጠኞች ነን ባዮች ቆም ብለው የሚያስቡበት ጊዜ አልረፈደምና ይህን እንዲያደርጉ በጽኑ እመክራለሁ።
ወደድንም ጠላንም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ለውጥ ሲመጣ አብሮ የሚመጣው ስክነት እና መደማመጥ ሀገሪቱን የሁሉም ቤት እንድትሆን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የተሳካ እና ጎዳናውንም ቀሊል እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በበላበት ጓዳ የሚጮሀውን ሁሉ የምናዳምጥ እና እሱን የምንከተል ከሆነ ግን መጨረሻው እና መዳረሻው እንደማያምር ከሌሎች ልንማር ይገባናል፡፡በሀገር ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞችን ፣ የሚድያ ሀውሶችን፣ የመገናኛ ብዙሃን  ባለሞያዎችን እና ሌሎች ከሚድያ እና ኮምንኬሽን ጋር በተገናኘ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ተዋንያን በሙሉ በዓለም አቀፍ የሚድያ ድንጋጌዎች እና በሌሎች ሀገራዊ ህጎች የመዳኘቱ ወይም ደግሞ በትክክለኛው መስመር እንዲጓዙ የማድረጉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ አጥፊዎችን ግን ተገቢ እርምት፣ ማስተካካያ እና እርምጃ መውሰድ የሚመለከተው አካል የሚሰራው አስቸኳይ የቤት ስራ ሆኖ ከፊታችን አለ!
የሆነው ሆኖ እነዚህ ባቀጣጠሉት ልክ ያልነደደላቸው ፤ በናዱት ልክ ያልፈረሰላቸው ፤ እዚህም እዚያም በበሉበት የሚጮሁ በቀቀኖች የሚነዟቸው ፕሮፖጋንዳዎች እና የጠቅላይነት አባዜ የተጸናወተው አካሄድ ዛሬ ላይ ያከተመለት፣ ያበቃለትና ያፈጀለት ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ማህበረሰባችንም ብስሉን ከጥሬው ፤የሚጠቅመውን ከሚጎዳው ፤ ብርሃኑን ከጨለማው፤ ለሀገር እና ለህዝብ የሚበጀውን ከማይበጀው የመለየት የባህል ፣የሃይማኖት እና የታሪክ ልዕልና አለውና ይህን እንደሚያውቅ እና እንደሚረዳ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ጽንፈኝነትን የሚያራግቡ ግጭት ጠማቂ ሚዲያዎች እነሱ ለማፍረስ በሰሩት፤ እነሱ ለማበላሸት በጣሩት፤ እነሱ ለማቃቃር እና ለማጨራረስ አቅደው በተንቀሳቀሱት ልክ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባለው ታላቅ ሀገር አሁን እየሄደችበት ባለው የስኬት እና የድል ጎዳና መጓዟ ቀርቶ ድሮ ገና ታሪክ-ተረት ሆና በቀረች ነበር፡፡
ነገር ግን ያ አልሆነም!
እንዲሆንም አንፈቅድም!
ዛሬ ላይ መንግስትና ፓርቲያችን እንዲሁም ህዝባችን በአስደናቂ የድል ግስጋሴ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ወደ ከፍታዋ እና ክብሯ ለመመለስ የሚያደርጉት ርብርቦሽ እና ጥረት ለወዳጅም ለጠላትም ለቅርቦችም ለሩቆችም ህልው በሆነ መልኩ እየታየ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ላይ በድል ጎዳና እየተጓዘች ትገኛለች፡፡ መንግስት በማህበረሰባችን የሚድያ ሊትሬሲ ወይንም ደግሞ ሚድያን የመምረጥን፣ የመረዳትትን እና የማዳመጥን እውቀት ለማዳበር ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን በሀገር ውስጥ ለሀገር ሰላም፣ እድገት፣ ልማት ፣ ለብልጽግናችን እና ለመዳረሻችንም ስኬት ጥረት የሚደርጉ ጋዜጠኞችን ፣ የሚድያ ባለቤቶችን እና የሚድያ ሀውስን መሪዎችን የማበረታታት እና በትክክለኛው መም ላይ እንዲጓዙ የማፈድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ይህ ቢሆንም በሟርተኞች ጩሀት እና በበለው በለው ዛቻና እና ድርቅት የሚፈርስ ሀገር የሚወርድ መንግስት እንደሌለ ወዳጆቻችንም ጠላቶቻችንም በውል ሊገነዘቡት የሚገባ አንኳር አብይ ጉዳይ ነው፡፡ መሶቡ ላይ ላለው እንጀራ ሲባሉ መሶቡን የሚያስበሉ ሆዳም ጋዜጠኞች ለመብላት እና ሆድን ለመሙላትም ሀገር እንደምታስፈልጋቸው ቆም ብለው የማሰቢያ ሰከን ብሎ የማንሰላሰያ ግዚያቸው አሁን እና አሁን ብቻ እንደሆነ በውል ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
ከጅብ ቆዳ የተሰራ ከበሮ ቅኝቱ ‹‹እንብላው እንብላው›› ከመሆን የዘለለ ወይም የተሻገረ እንደማይሆን እሙን ነው፡፡በበሉበት ጓዳ የሚጮሁ፤ ለሰፈሩላቸው ቀለብ የሚለፉና የሚጥሩ በቀቀቦችን የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ተፈጥሯውን እና ባህሪያቸውን በመረዳት እና በመታገል ለልማት እና ስኬታችን ፤ ለእድገት እና ስምረታችን በጋራ ይሰራሉ ፡፡
እስካሁን እንደሆነውም በስኬት ጎዳና ጉዟቸውን ወደፊት ያደርጋሉ፡፡ ሚድያ እና ጋዜጠኝነት ህዝብን እና ሀገርን የማገልገያ እንጂ የህዝብን ሰላም እና አንድነት የሀገርን ህልውናና ጽናት የመንጠቂያ መሳሪያ አይደለም!
ሩዋንዳ የሆነችውን ሁሉ ከመሆኗ በፊት የሩዋንዳ ጽንፈኛ ሚድያዎች እና አጋሮቻቸው የኛዎቹን ግጭት ጠማቂ ጽንፈኛ ሚዲያዎች ይመስሉ ነበር!

1 Comment

  1. OPDO is a copy-paste organization lacking any originality. At every turn, they look for what TPLF did do at a similar moment in its past and do a poorly executed copy=paste.
    The copied Hawzen successfully, even taking their creators by surprise. They staged the Irrecha Massacre and catapulted themselves to power.
    At the lowest point in his public acceptance, following his election defeat in 2005 (1997 E.C), Meles Zenawi started crying Interhamewe! Rwanda! Genocide! He forgot that genocide is planned and implemented by those holding state power. Addisu, as an Abiy Ahmed mouthpiece, is just copying this grand blunder of Meles Zenawi.

    If there is any upcoming genocide (as the west has planned and waited too eagerly), it would be carried out by the government and forces allied to it. The loud crack of the whip is not going to disguise that the injured victim is not the whip itself.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

IMG 20230405 004413 878 Copy 1 1 1
Previous Story

ዶክተሩን ፍቱት!! – በ-ሙሉዓለም ገ/መድኀን 

Killer abiy 1 1 1 1
Next Story

መዝቀጥ እንደ አብይ አህመድ – እውነቱ ቢሆን

Go toTop