ዶክተሩን ፍቱት!! – በ-ሙሉዓለም ገ/መድኀን 

የፌዴራል “መንግሥቱ” የአሮጌው ዘመን ቁማርተኝነቱን ካላቆመ ሕዝባዊ አመጽ ገዛ እጁ እንደጠራ ይቆጠራል። አገዛዙ በዚህ የእውር ድንብር ጉዞው ኢትዮጵያን ከድጡ ወደማጡ እየወሰዳት ነው። ይህ አደጋ ለራሱም ለሀገርም ለዜጎችም አይበጅም።
ወያኔ በአገዛዝ ዘመኑ ንፁሃንን ከቤታቸው እያፈሰ በማሰር የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም ቢጥርም በዜጎች የጅምላ እስርም ሆነ ግድያ ሥልጣኑን አስጠብቆ መቀጠል አልቻለም።
ጊዜው ደርሶ በሕዝብ ትግል ከቤተመንግሥት ተጠርጎ ለመውጣት ተገድዷል። በኦሕዴድ የበላይነት የሚዘወረው የፌዴራል መንግሥቱ ከፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ የሌላቸውን ንፁሃን ዜጎችን ሳይቀር እያፈሰ በማሰር ላይ ይገኛል።
ሲጀመር የፖለቲካ አመለካከት የእስር መነሻ ሊሆን አይገባም። ሲቀጥል ከፖለቲካ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሀገር ጭንቅ ውስጥ በወደቀች ጊዜ የህልውና ትግሉን ጥሪ ተቀብለው በሙያቸው፣ በገንዘባቸውና በሕዝብ ሞብላይዜሽን  (ማህበራዊ ተፅዕኖ) አቅማቸው ወገንና አገራቸውን ያገለገሉ ቅን ሰዎችን ከጦርነቱ በኋላ በየቤታቸው እየለቀመ ማሰሩን ተያይዞታል።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት ክዶ የሐላላ ኬላውን ገቢር በማድረግ ላይ ያለው የፌዴራል-ኦሮሚያ አገዛዝ ይህ ንፁሃንን አፍኖ የመውሰድ ተግባር መንግሥታዊ የሀገር ክህደት እንጅ ሕግ ማስከበር ሊባል አይችልም።
ዶክተር በቀለ ኃይሌ ዓለሙ፣ በትላንትናው ዕለት ልጆቹን ከትምህርት ቤት ለመቀበል በወጣበት ታፍኖ ተወስዷል። በታዳጊ ልጆቹ ፊት የታፈነው ይህ ንፁህ ኢትዮጵያዊ በሙያው የህክምና ዶክተር ነው። ከሙያው ባሻገር በተለያዩ ማህበራዊ በጎ አድራጎት ተግባራት በመሳተፍ ይታወቃል።
ጎንደር አዲስ ዘመን፣ ወረታና አዲስ አበባ ፍጡነ ረድዔት በሆነው የህክምና ሙያ ችሎታው ይታወቃል።
በእርሱ ክሊኒክ በነፃ ከታከሙ ህልቆ መሳፍርት ህሙማን ጀምሮ የሰዎችን እጅ የሚያዩ ምስኪኖች ከነፃ ህክምና ድጋፉ በተጨማሪ የህክምና መድሃኒት ግዥ አልፎም በኑሯቸው የደገፋቸው ሁሉ  የሚመሰክሩለት የድሆች አባት ነው።
ዶክተር በቀለ፣ በህልውና ጦርነቱ ወቅት በወረራ ውስጥ የወደቁት የአማራ ክልል አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ ከሙያና አብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር ሰፊ እገዛ ያደረገ፤ ከክምር ድንጋይ እስከ መቄት፤ ከጋሸና እስከ ወልድያ፤ ከጭና እስከ ደባርቅና አድርቃይ-ጠለምት ድረስ የተጫኑ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ያስተባበረ፣ የወደሙ የህክምና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ረገድ የፕሮጀክት ሀሳቦችን በማቅረብ በእውቀቱ አገርና ወገኑን ሲደግፍ የኖረ መልካም ሰው ነው ዛሬ በመንግሥታዊ ኃይሎች አፈና የተፈፀመበት።
የሁመራ ሆስፒታል በቁስለኞች ተጨናንቆ በህክምና ቁሳቁስ እጦት በተቸገረበት ወቅት፣ ውጭ ሀገር የሚኖሩ የሙያ አጋሮቹንና ሀገር ወዳድ ዲያስፖራዎችን በማነጋገር የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ወደአገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ በሁመራ ሆስፒታል ይታከሙ የነበሩ የጥምር ጦሩ ቁስለኞች በአግባቡ እንዲታከሙ የበኩሉን እገዛ አድርጓል።
በዛ የጭንቅ ሰዓት በወሎም፣ በሸዋም በጎንደርም ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማቃለል የሙያ፣ የሀሳብና የፋይናንስ እገዛ በማድረግ የሚያኮራ ወገናዊ እገዛ ያደረገው ዶክተር በቀለ እስር ሳይሆን ሽልማት ነበር የሚገባው!!
የሆነው ግን በተቃራኒው ነው የድሆችን አባት በእጆቹ ፈዋሽነት የተመሰከረለትን የህክምና ዶክተር እጁ ላይ ካቴና አጥልቀውበታል።
ይህን  ወገኑንና ሀገሩን የሚወድ ንፁህ ሰው እንዴትም አድርገው ቢመረምሩት ወንጀል ሊያገኙበት አይችሉም። ምናልባት ወያኔን መጥላት ወንጀል ከሆነ አዎ ዶክተር በቀለ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነውን ወያኔን አብዝቶ ይፀየፋል።
የፌዴራል-ኦሮሚያ አገዛዝ ከያዘው የአሮጌው ዘመን ቁማርተኝነት በፍጥነት ካልወጣ አደጋው በራሱ ላይ ይብስበታል። የንፁሃን ግፍና እንግልት ሕዝብ በራሱ ጊዜ እንዲቀጣው ያደርገዋል።
አዎ ዶክተሩን ፍቱት!!
#ዶክተር #በቀለኃይሌአለሙን #ፍቱት
#Free #Doctor #BekeleHaileAlemu
ተጨማሪ ያንብቡ:  በመርካቶ የ32 ቀበሌ ወጣቶች በብዛት ታሰሩ፣ ሰፈራቸውን ለቀው እየጠፉ ናቸው

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share