ዶክተር በቀለ ዓለሙ ይባላል። በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ከቀኑ 9:30 ልጆቹን ከትምህርት ቤት ለማውጣት በሄደበት በመንግሥት ኃይሎች አፈና ተፈጽሞበታል።
ዶክተር በቀለ ልጆቹን ከትምህርት ቤት ተቀብሎ መኪናው ውስጥ እንደገባ ነው እነዚህ የመንግሥት አፋኞች ልጆቹን መኪናው ውስጥ ቆልፈውባቸው እሱን የሰሌዳ ቁጥር በሌለው ተሽከርካሪ አፍነው የወሰዱት።
ዶክተው በቀለ ዓለሙ በሙያው የህክምና ባለሙያ ሲሆን፤ በአዲስ ዘመን፣ ወረታና በአዲስ አበባ በህክምና ሙያ ችሎታው ‘አንቱ’ የተባለ፤ እጆቹ ፈዋሽ የሆኑ የህሙማን አገልጋይ ነው። በተለይም አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎችን የነፃ ህክምና ከመስጠት አልፎ መድሐኒት በመግዛት እገዛ በማድረግ የሚታወቅ የድሆች አባት ነው።
ሰብዓዊነቱ የገዘፈ የህክምና ሙያ ባለቤት የሆነው፣ ዶክተር በቀለ ዓለሙ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፈተው የጦር ወረራ ሀገር አቀፍ የህልውና ትግል ሲታወጅ ወዳጆቹን በማስተባበር በገንዘብ፣ በሞራልና በሙያው ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተ አገር ወዳድ የሙያ ሰው ነው።
በተለይም በአማራ ክልል በወራሪው ኃይል የተዘረፉና የወደሙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን መልሶ ለማቋቋም ሰፊ ሙያዊ፣ አስተዳደራዊና ረጅ ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማነጋገር (ወደአማራ ክልል በመውሰድ) ሰፊ አበርክቶ የተወጣ የተግባር ሰው ነው።
ዶክተር በቀለ፣ በጦርነቱ ወቅት ካደረገው ሰፊ እገዛ በተጨማሪ በአማራ ክልል “የጀግኖች አምባ” እንዲቋቋም ሀሳብ ጠንስሶ ለክልሉ መንግሥት አቅርቦ ነበር።
ይህ በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች በአዳሪ ትምህርት ቤት የሚማሩበት ሰፊ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ሀሳብ ከማቅረብ አልፎ የቅርብ ወዳጆቹን በማስተባበር በትግሉ ለተሰው ሰማዕታት ዘላቂ ወገናዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ነሳሽነት ያለውን ሰው በጠራራ ፀሐይ ያፈነው መንግሥታዊ ኃይል፤ ያፈነው አንድ ግለሰብን ሳይሆ ኢትዮጵያዊ ቅንነትን፣ ትልቅ ሙያዊ አቅምን ነው።
የታሰረው በጎነት ነው። የታሰረው መልካምነት ነው። የታሰረው የድሆች አባት የሆነ የህክምና ሙያ ባለቤት ነው።
መንግሥት ይህን ንፁህ ሰው በማሰር የሚያገኘው አንዳችም ትርፍ የለም። ይልቁንም ከሕዝብ ልብ ውስጥ ጨርሶ እንዲወጣ ያደርገዋል። ምክንያቱም የታሰረው አንድ ግለሰብ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ቅንነትና ትልቅ የሙያ አቅም ነውና።
መንግሥታዊው አፈና ራሱን መንግሥትን ኪሳራ ላይ የሚጥል እንጅ በንፁሃን አፈና አንዳችም ፖለቲካዊ ጥቅም ሊያኝበት አይችልም።
ዶክተር በቀለ ንፁህ የህክምና ሙያ ሰው ነው።
ዶክተር በቀለ የልጆች አባት ብቻ ሳይሆን የድሆች አባትም ነው።
እናም ይህን ንፁህ ሰው ፍቱት። የታሰረው ወገንና ሀገሩን የሚወድ የህክምና ዶክተር ነው። የታሰረው አገሩን በሙያውና በገንዘቡ የሚያገለግል ቅን ኢትዮጵያዊ ነው።
#ዶክተር #በቀለአለሙን #ፍቱት #Free #Doctor #BekeleAlemu
በ-ሳሙኤል መልካምሰው