የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዚህ ቀደም በሕዝብ ፊት የሚካሄዱ ግልጽ የምርመራ መድረኮችን በሃዋሳ ከተማ ከሰኔ 27 ቀን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. እና በጅግጅጋ ከተማ ከታኅሣሥ 11 ቀን እስከ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ማካሄዱ የሚታወስ ነው። በባሕር ዳር ከተማ ከመጋቢት 19 ቀን እስከ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የተዘጋጀው መድረክም የዚህ መርኃ ግብር ቀጣይ አካል ነው።
የግልጽ ምርመራ መድረክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ስልት ነው። በዚህም መሠረት አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ መድረክ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን የሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባሕርይ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ለግልጽ ምርመራ ኮሚሽኑ ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም ያካትታል።
የግልጽ ምርመራ መድረክ በተለይ ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚለዩበት፤ እንዲሁም በአንድ ተቋም ወይም በበርካታ አካባቢዎች ለመመርመር አዳጋች የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር እና ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት የሚያስችል ስልት ነው። በተጨማሪም በቂ ትኩረት ያላገኙ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚያስችል ነው።
በባሕር ዳር ከተማ በተከናወነው የግልጽ ምርመራ መድረክ ለአብነት የተመረጡ 20 ተጎጂዎች እና ምስክሮች ያቀረቧቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የተመለከቱ አቤቱታዎች ኮሚሽኑ አዳምጧል። ከእነዚህም መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ እና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት ታሳሪን ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ እንዲሁም የዋስትና መብትን፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጸዳጃ እና ሕክምና የማግኘት መብትን አለማክበር እና ጭካኔ የተሞላበት የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በአቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል ናቸው። በግልጽ ምርመራ መድረኩ የተሳተፉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ኃላፊዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የሰጡትን ምላሽና አስተያየት መሠረት በማድረግ ጉዳዮቹ ተጣርተው በኮሚሽኑ የማጠቃለያ ሪፖርት ምክረ ሐሳብ ይሰጣል። ከዚህ በፊት ከነበሩት ልምዶች እንደታየውም የግልጽ ምርመራ ሂደቱ በራሱ የሚያስገኛቸው ውጤቶች ለሰብአዊ መብቶች መሻሻል ዓይነተኛ አስተዋጽዖ አለው።
የግልጽ ምርመራ መድረኩን የመሩት የኢሰመኮ መርማሪ ኮሚሽነሮች፤ የሲቪል፣ የፖለቲካ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል፣ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እና የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ ሲሆኑ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። ዶ/ር ዳንኤል የዚህ ዓይነቱ በብዙ ሀገሮች ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የተለመደውና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የግልጽ ምርመራ መድረክ ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ ያለውን ጠቀሜታ አስታውሰዋል። አክለውም በዚህ መድረክ ላይ የቀረቡ ሰዎች በመድረኩ ላይ በሚሰጡት ምስክርነት ወይም ማስረጃ የተነሳ በተለይ ከመንግሥት አካላት ምንም ዓይነት አፀፋዊ እርምጃ እንዳይወሰድ አበክረው በማሳሰብ የክልሉ ኃላፊዎች አስቀድመው ቃል በገቡት መሠረት ይህን ቃላቸውን እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተው የደረሱባቸውን መረጃዎች በመድረኩ ያቀረቡ ሲሆን የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እያዋሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በክልሉ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎችም በበኩላቸው ያስተዋሏቸውን ችግሮች አስረድተው ለክልሉ ሰላምና የሰብአዊ መብቶች መከበር የየራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ እንዳለና ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በክልል እና በተለያዩ ዞኖች ደረጃ ያሉ የፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች በበኩላቸው ኢሰመኮ ተበዳይ ነን ያሉ ሰዎችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችን በአንድ መድረክ አገናኝቶ ማወያየቱ አበረታች ጅማሮ ነው ብለዋል። ተፈጽመዋል ለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ለቀረቡ አቤቱታዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የፍትሕ እና የጸጥታ ተቋማቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታም አስረድተዋል።
የመርማሪ ኮሚሽነሮች ሰብሳቢ ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በግልጽ የምርመራ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ የቀረቡ አቤቱታዎችን እና ምስክርነቶችን ኮሚሽኑ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ሪፖርት እንደሚያዘጋጅ፣ በሪፖርቱ ላይ ግብረ መልሶች የሚቀበልበት መንገድ እንደሚኖር እና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በዘላቂነት ለማሻሻል የሚስችሉ ምክረ ሐሳቦችና የድጋፍ ሥራዎችም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።