የተካደው የፕሪቶሪያ ስምምነት… – ሙሉዓለም ገ/መድኀን  ከሁመራ-ጎንደር

የተካደው የፕሪቶሪያ ስምምነት…
***
መቼም፣ ለሁለት ዓመት በከባድ ደም-አፋሳሽ ጦርነት ያለፈችው ኢትዮጵያ እንዲህ በአጭር ጊዜ ለዳግም እልቂት ‹ሴራ ይጎነጎንባታል› ብሎ መገመቱ ነብይ መሆንን ይጠይቃል። የሆነው ግን ይህ ነው፡፡ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የፕሪቶሪያው ስምምነት በጓሮ ተሸኝቶ፤ በምትኩ እነ ሬድዋን ሁሴን በቫዮሊን ያጅቡት፣ እነ ታደሰ ጫፎ “ጊሽጣ-ጊና” የዘፍኑለት ከስምምነቱ የተቃረነ አካሄድ ተተክቷልና። ይህ የሆነው ደግሞ፣ የኦሮሙማን ፕሮጀክት ለማስፈጽም መሆኑ ችግሩን የበለጠ አስከፊ ያደርገዋል፡፡

እዚህ ጋ “የተካደው ሰሜን ዕዝ” መጽሐፍን እያሰላሰልን፤ ክህደቱን ለማፍታታት ሦስት የተጨፈለቁ የስምምነቱን አንቀጾች ለማሳያነት እንጥቀሳቸው፦

1ኛ) ትሕነግ ፕሪቶሪያ ላይ ከፈረመው ባለ 15 አንቀፅ ሰነድ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታና ተዋጊዎቹ በሙሉ ወደ ተሃድሶ (ማሰልጠኛ) ካምፕ እንደሚገቡ፦

በአንቀፅ 6 ላይ “Disarmament, Demobilization, and Reintegration (DDR)” ተብሎ የሰፈረው ክፍል በግልፅ ያትታል። ይህንን ስምምነት ተከታትሎ የማስፈፀም ሙሉ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር የተሰጠው ለፌደራል መንግሥቱ እና በአፍሪቃ ሕብረት በኩል አሸማጋይ ሆነው በቀረቡት ሰዎች ለተቋቋመው ታዛቢ ቡድን ቢሆንም፤ “ታዛቢ” ተብየው ቡድን በአራት ኪሎ ጥቅሻ ቢሮውን ዘግቶ የሚላክለትን ሪፖርት ብቻ በመገምገም ሲታቀብ፤ የፌደራል-ኦሮሚያ ብልፅግና ደግሞ አሰላልፍ ቀየሮ ድፍን አገሪቱን ወደማያባራ ግጭት ለመክተት እያሟሟቀ ነው፡፡ በዚህም፣ በትሕነግ ካምፕ ያለው አፈጻጸም ተውኔት እንጂ፤ ትጥቅ በመፍታቱ ረገድ ወፍ የሌለ ሆኗል።

የተውኔቱን ትራጄዲ ክፍል የሚያጎላው ደግሞ ‹በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ያሰፍናል› ተብሎ የታሰበው ስምምነት ለ“እርካብና መንበር” ክፍል ሁለት መጽሐፍ መነሻ ሀሳብ ይውል ዘንድ መገደዱ ነው፡፡

የተውኔቱን ኮሜዲ ክፍል ከፈለከው ግን፣ ለይስሙላም ቢሆን በታዛቢ ቡድኑ ፊት ትሕነግ 3% የማይሞሉ ከባድ መሳሪያዎችን “አስረክቡ” ብሎ የተሳለቀበት ገቢር ላይ ታገኘዋለህ፡፡ በተቀረ፣ 97% የሚሆነው ትጥቅ እና ካለፉት ሁለት ወር ወዲህ በገፍ እየተጫነ የሚላክለት ጦር መሳሪያ ከስምምነቱ በፊት ከነበረውም በላይ አፈርጥመውት፣ የኦሕዴድን ትዕዛዝ በተጠንቀቅ እየጠበቀ መሆኑን አትጠራጠር።

2ኛ) “Transitional Measures” በተመለከተው የስምምነቱ ክፍል አንቀፅ 10 ላይ፦ “በትግራይ ዐዲስ የጊዜዊ አስተዳደር ይቋቋማል” ይላል።

መሬት የረገጠው እውነታ ጮኾ የሚነግረን ግን፣ መከላከያ ሠራዊቱን ከጀርባ ወግቶ ያንን ሁሉ ምስቅልቅሎሽ የፈጠረው የትሕነግ ታጣቂ (a.k.a TDF) የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል እንዲሆን ተደርጎ፤ በሺሕ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰማዕትነት ደመ ከልብ መሆኑ ነው።

3ኛ) በፕሪቶሪያው ስምምነት ከፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመተማመን መልሶ ግንባታን በተመለከተ ደግሞ በአንቀፅ 7 ላይ ስለ Confidence-building measures በግልፅ ተደንግጓል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የራያን ሕዝብ ትግል የሁሉም አማራ የማድረግ ተልዕኮ! - ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

ይሁንና፣ ከዚህ ስምምነት ውጭ፣ ያውም ያለአንዳች አሳማኝ አመክንዮ ትግራይ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ክልሉን እጁ በደም ለጨቀየውና በጥላቻ ለሰከረው ትሕነግ አስረክቦ ወጥቷል። መጪውን ጊዜ በእጅጉ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ፣ ሠራዊቱ ትግራይን ሲለቅቅ ከባድ መሳሪያዎቹን ይዞ ይሁን ወይም እዛው ትቶ በግልፅ አለመታወቁ ነው። ነገሩን፣ ወደ መሀል አገር የተመለሰው ሠራዊት የነፍስ-ወከፍ መሳሪያ ብቻ የታጠቀ ከመሆኑ አኳያ ካየነው፣ ‹ትሕነግ በቀጣይ ከዐማራ እና አፋርም አልፎ፤ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ላይ አደጋ እስከመጣል የሚደርስ ወታደራዊ ቁመና እየያዘ መጥቷል› ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።

ማን ነው የሚፈርሰው?

አገር አፍራሹ ኃይል በዐውደ-ውጊያም በፕሪቶሪያው መድረክም በክቡድ መስዋትነት ተሸንፎ የጥፋት እጁን የሚሰበስብበትን የሰላም ሰነድ ለመፈረም መገደዱ የታሪክ ፍርድ ቢሆንም፤ ኦሕዴድ-ብልጽግና በዐማራ ክልል ላይ ለመተግበር ላቀደው የኦነግ ፕሮጀክት ሲባል የስምምነቱ ዋና ዋና ጭብጦቹ ተጥሰዋል፡፡

የዐማራ ልዩ ኃይልን መበተንን በጠቅላዩ በተሾሙት ሬድዋን ሁሴን እና ተሾመ ቶጋ በኩል ለማስፈጸም መጣደፉቸውን ስታይ፣ ወትሮም የ confuse and convince ደራሲ ማንነት ይገለጥልሃል፡፡

ትንሽ ነገሩን ከአቢሲኒያውን ሥነ-ልቦና አፈንግጦ የምታገኘው፣ ለሃያ ሰባት ዓመታት በተላላኪ ድርጅቶቹ በኩል ኢትዮጵያን ጠርንፎ የገዛው ትሕነግ፣ ዛሬ ደግሞ ለቀድሞ ሎሌዎቹ  ደስተኛ መላክተኛ ለመሆን አላማቅማማቱ ነው፡፡

መቼም፣ ይህንን የሥነ-ልቦና ንቅለት ‹ለዘርፉ ተመራማሪዎች እንተወው› ብንል እንኳ፤ እነርሱው ራሳቸው “ፈጠርናት” በሚሏት ኢትዮጵያ የተገነቡ ተቋሟትን፣ ኦሕዴድ ቀለም ቀብቶ አንድ ሁለት ተጨማሪ ሕንፃ ገንብቶ ሲያስጎበኛቸው በአግራሞት ሲደነቁ ተመልክቼ መደንገጤን አልሸሽግም፡፡

የደብረዘይትና ናዝሬት ቆይታቸውም ስለዘመነኛው ውርዳታቸውና የፖለቲካ ግልሙትናቸው የሚናገረው ሀቅ አለ፡፡ ከአዲስ አበባ ወደደብረዘይት ሲጓዙ በአንዲት ነጭ ኮስትር-ባስ ያጓጓዟቸው ሲሆን፤ ይህ ክስተት የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤት የቀብር ሽኝት ላይ የተናቁ የአፍሪቃ መሪዎች በአንድ ባስ እንዲጓዙ የተደረገበትን ሁነት ያስታውሳል፡፡ ሌላኛው ገራሚው ነገር ሽመልስ አብዲሳ ቁሞ ማብራሪያ በሚሰጥበት ወቅት የትሕነግ ሰዎች (የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኒዎች ላለማለት ነው) ይጠበቁ የነበሩት በተወሰኑ ሪፐብሊካን ጋርድ እና በኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት ነበር፡፡ የእነሱን ጠባቂዎች በአንድ ክፍል ውስጥ አስገብተው አስቀምጠዋቸው ነበር የዋሉት፡፡

ይህን ጉድ የተመለከቱ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ነገሩን በትግረኛ ‹ሸዋ ቓላይ ውሒጣቶም ንመኳንንቲ ትግራይ› (የሸዋ ሀይቅ የትግራይ መኳንንት ዋጠ) ማለታቸውን ስንሰማ የትዝብታቸውን ጥልቀት ለማድነቅ እንገደዳለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነገረ ህወሓት: ህወሓትና ‹‹ወያኔ›› ምንና ምን ናቸው? - ጌታቸው ሺፈራው (ጋዜጠኛ)

በርግጥ፣ በዚህ ደረጃ ይገብሩ ዘንድ እስካሁን እየተሰፈረላቸው ካለው መቁንን በተጨማሪ፤ የዐማራ መሬቶችን በኃይል የመውረር እና ዐማራን እንደ ሕዝብ የማጥፋት ‹ሊቼንሳ ተሰጥቶታናል› ባይ መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡

ይህን ተከትሎም፣ “ቲም በሻሻ-ጀልዱ” ሰሜናውያኑን እያፈራረቁ በማጋደል በኦሮሙማ የምትበየን “ዐዲስ ኢትዮጵያን” ለመፍጠር፣ በዐማራ እና ትግራይ ተራራዎች ተደቁሶ የተበተነውን ትሕነግ በአገሪቱ ወጪ ዳግም እያጠናከረው ነው።

እንግዲህ፣ ስሌትም ስልትም የነጠፈበት ትሕነግ ለፌዴራል-ኦሮሚያ መንግሥት ገብሮ ባገኘው ድጋፍ ለ4ኛ ዙር ጦርነት በግላጭ እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ፣ የዐማራን እና የአፋርን ልዩ ኃይል የማፍረሱ ታሪካዊ ስህተት ወደ መድረክ መጥቷል፡፡ ውሳኔውን የሚያስፈጽም ቡድን ተቋቁሞም ሥራ ለመጀመር አኩብኩቧል፡፡ ጎን ለጎንም፣ ከጠቅላዩ ጀምሮ ሁሉም የኦሮሞ ፖለቲከኞች በዐማራ ሕዝብ ላይ በግላጭ ‹ምታ ነጋሪት› እያሉ ነው፡፡

መቼም፣ መሬት ያለው እውነታ ይህ ሆኖ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ የታጠቀው ኃይል “ይበትናል” ብሎ ማሰብ የክፍል ዘመኑ ቧልት ነው፡፡ ቧልቱን ለማስፈጽም ገፍቶ መሄድ ደግሞ መዘዙ አደገኛ ነው፡፡

ውሳኔውን የዐማራ ብልጽግና ቢቀበለው እንኳ፣ ለመተግባር ስትሞክረው የላዩ ወደታች፣ የታቹ ወደላይ ሲገላበጥ ታገኘዋለህ፡፡ “ዐማራ” ሲባልም አጠገብህ ያሉት ‹ሥራ-አስፈጻሚዎች› ወይም ‹የባህር ዳር አለቆች› ከመሰለህም፣ ይህም አደገኛ ስህተት ነው፡፡ ራሱን ለመከላከል አንድም አርባ ሚሊዮንም ሆኖ የሚወጣ፣ በክብሩ ፈጽሞ የማይደራደር ሕዝብ፣ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተለ ነውና፡፡

በአጭሩ፣ ትሕነግ ትጥቅ ካለመፍታቱ በተጨማሪ፤ የፖለቲካ አሰላለፉ በተቀየረበት ሁኔታ የዐማራ ልዩ ኃይልን አፍርሶ ሕዝቡን ለዳግም ወረራና እልቂት የሚዳርግ ውሳኔ እንኳንስ ከአራት ኪሎ፣ ከሰማይም ቢመጣም ዐማራ መስሚያው ጥጥ ነው። ከዚህ ባለፈ፣ ልዩ ኃይል የሚፈርስበት ዘመን ምናልባት ወደፊት የሚመጣ ከሆነ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

የፕሪቶሪያን ስምምነት ኦዲት ስለማድረግ

የፌደራል መንግሥቱ፣ ፕሪቶሪያ ላይ በፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብ የተጣለበትን ሕግን የማስከበር መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በተግባር መወጣቱን እና አለመወጣቱን አደጋው በቀጥታ በሚመለከተው የዐማራ ሕዝብ እና የክልሉ መንግሥት በሚሰይመው (በኔ ዕይታ በክልሉ ምክር ቤት ቃለ-መሃላ የሚፈጽም) ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ በኮሚቴው በኩል ኦዲት ሊያደርግ ይገባል።

ይህ በችሮታ የተሰጠ መብት ሳይሆን፤ ሺህዎችን ገብረን  በተከፈለ ዋጋ የተገኘ ራስን መከላከል ነውና፡፡ እየታየ ያለው ግን፣ ትግራይ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተጥሶ ዳግም ማንሰራራት እድል እንዲያገኝ በተመቻቸለት ትሕነግ ሙሉ ቁጥጥር ስር መሆኗ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ በወሳኝ የሽግግርና የታሪክ መታጠፊያ ምእራፍ ላይ: የአብይ አህመድ ስልጣን መልቀቅ አስፈላጊነት - ገለታው ዘለቀ

ይህ ቡድን ደግሞ፣ ለዐማራም ሆነ ለኢትዮጵያ ጥፋት ስለመሆኑ ያሳለፍናቸው ሁለት በጋና ክረምቶች ተጨባጭ ምስክሮች ናቸው፡፡

‹የልዩ ኃይሉን ሥራ መከላከያ ይረከበዋል› የሚለዋን ቀልድ ደግሞ በተከታዮቹ ምክንያቶች ዱቄት መሆኑን አሳይተን እንለፍ፡-

አንደኛ፣ መከላከያ ሠራዊት ጦርነቱን ብቻውን የሚችለው ባለመሆኑ ነው የዐማራ ኃይል ቤተሰቡን በትኖ የማይተካ አንድያ ሕይወቱን ሰጥቶ ለግዳጅ የተሰለፈው፡፡

ሁለተኛ፣ የመከለከያው የብሔር ተዋጽኦ ገና እንደተድበሰበሰ ነው፡፡ በደንብ ለቅሞና አበጥሮ ወደፍትሐዊነት ሚዛን መመለስ ይጠይቃል፡፡

ሦስተኛ፣ መከለከያ ከአደረጃጀቱ አኳያም ቅድሚያ ለውጪ ወራሪ የመስጠት ግዴታ ስላለበት የሱዳን ጦር በኃይል ከያዘው መሬት አስለቅቆ ይረከብ፤ (መቼም አብረውት በአንድ ምሽግ የወደቁ የዐማራ ልጆች አጋሩ እንጂ፣ ጠላቱ ስላልሆነ፤ ግዳጁን የሱዳን ወታደሮችን በማባረር ቢጀምር ‹ይከፋዋል› ተብሎ አይታሰብም፡፡)

አራተኛ፣ መከላከያ ትግራይን ከትሕነግ ታጣቂዎች ነፃ በማድረግ እና ትጥቅ በማስፈታት የተጣለበትን የሰላም ስምምነቱን የማስፈጸም ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡

(ለጊዜው አምስተኛ፣ ስድስተኛ… መከራከሪያዎች ባሉበት ይቆዩን፡፡)

በተረፈ፣ የዐማራ ክልል የፕሪቶሪያው ሰነድ በስምምነቱ መሠረት ተግባራዊ መሆን አለመሆኑን የሚያጣራ አንድ ዐቢይ ኮሚቴ በምክር ቤት ደረጃ አቋቁሙ አፈጻጸሙን በቅርበት መከታተል አለበት የሚለው ምክረ-ሀሳቤ በጥንቃቄ እንዲደመጥ እጠይቃለሁ፡፡

ይህ ኮሚቴ ሥራውን በምልዓት ከገመገመ በኋላ በሚያመጣው ሪፖርት መሠረትም ልዩ ኃይሉ የመፍረስ፣ አደረጃጀትን የማስተካከል፣ የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ተዋፅዖን ማመጣጠን እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የዐማራ ሕዝብን በሚያሳምን መልኩ ውሳኔ መስጠት ይቻላል።

የተደገመ ምክር፡-

የዐማራ ሕዝብ ዕጣ-ፈንታ የአማራ ብልጽግና የሥራ አስፈፃሚ አባል በሆኑ ‹በስምንት ሰዎች እጅ ማውጣትና አለማውጣት የሚወሰን ነው› ብሎ ማሰብ ለማይታረም ስህተት ያጋልጣል፡፡

ሺህዎች ሕይወታቸውን የገበሩለት፣ ቤተሰባቸውን ጎዳና ላይ የበተኑበት፣ ኧረ እንዴውም አፅማቸው ተለቅሞ በክብር ባላረፈበት፣ ቤተሰቦቻቸውም እርማቸውን ባላወጡበት ሁኔታ፣ ሰማዕታቱ አጥንታቸውን ከስክሰው የገነቡትን ተቋም እንዲሁ በዋዛ ይፍረስ ማለት ባለሥልጣናቱ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በአሳፋሪ የታሪክ መዝገብ ውስጥ እንዲገቡ ማህበራዊ መገለልና መሸማቀቅ እንዲደርስባቸው በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው እንደፈረዱ ይቆጠራል።

በጣሊያን የወረራ ዘመን የኖሩ ባንዳዎች ቤተሰቦቻቸው እንዴት ይሸማቀቁ እንደነበር 90 ዓመት ያልሞላው የታሪክ እውነታ ነው። ጣሊያን ግን በአርበኞች ቆራጥ ተጋድሎ ተዋርዶ መልቀቁ ይታወሳል።

ዛሬ ለጥቁር ጣሊያኖች አሳልፋችሁ ሰጥታችሁን በድሎት ልትኖሩ አትችሉም!! ታሪክ ምስክር ይሁነን!!! እናም የማይሳካውን ተልዕኮ እንዳትሞክሩት!!

ሙሉዓለም ገ/መድኀን
ከሁመራ-ጎንደር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share