የሥም የለሽ ነፍስ ማን ያንሳሽ? (በላይነህ አባተ)

/

“የታወቀ” ነው የሚባለውን ወዲያኛው ዓለም ጠርቶታል ሲባሉ፣
ላብ እስቲነክራቸው ሲያደገድጉ አድረው ቢያነጉ እማይታክቱ፣
ዳሩ ድሀ ተቤተ መቅደስ ተመስጊዱ ውስጥ ታረደ ሲባሉ፣
የአስገዳይ ወንጀል ለመሸፋፈን ፕሮፓጋንዳ ምራቅ የሚተፉቱ፣
አለዚያም እንደ ክረምት አይጥ ፀጥ ብለው መአቱን የሚያሳልፉ፣
በዚህ ዘመን ውስጥ እንደ እህል ፈጅ ተምች እንደ አሸን ፈሉ፡፡

ከሥጋ ገና ሳትላቀቂ ገፍትረው ገደል ሸለቆ ቢጥሉሽ፣
አንገትሽን እንደ በግ አርደው ደምሽን በገል ቢጠጡሽ፣
ተአንጀትና ተልብ ሳትለይ በሳንጃ ካራ ወግተው ቢቀዱሽ፣
እንኳን ሌት ተቀን አሽቃባጭ የሚያስታውስም የሌለሽ፣
ምድርን በግኒደሮች ቆፍረው እንደ ቆሻሻ እንደ ኩስ የጣሉሽ፣
ብኩኗ የድሀዎቹ ነፍስ ለፍትህ ለመለኮት ሲል ማን ያንሳሽ?

ንፁሐን በአውሬ በጭራቅ ዝንጀሮ ናዳ ተወግረው ሲሞቱ፣
የዝንጀሮውን ጠባሳ ለመሸፋፈን ጣቃ ሲቀዱ ውለው የሚያድሩ፣
በነፍሰ በላ ገዥዎች ያልተወቀሱ ባለዝናዎች ይህችን ዓለም ሲለቁ፣
ድግሷ እንዳማረላት ወይዘሮ መቀመጫውን ተወዲያ ወዲህ ሲያማቱ፣
እንኳንስ በምድር ያለን ታዛቢ የሰማይ ንጉስ ዳኛንምአያፍሩ፡፡

“በሽግግር ወቅት መተላለቁ የሚጠበቅ ነው” እያሉ፣
ሆዷ በተሰነጠቀችው እርጉዝ ዓይኑ በወጣው ደጎባ ያፌዙ፣
የሰማእታት አስከሬን አፈር የሚያለብስ ግኒደር መሬትን ሲግጥ እያዩ፣
ገዳይ አስገዳዮችን ለመውቀስ ለመክሰስ ለአያሌ ዓመታት ያቅማሙ፣
ዳሩ ለባለዝናዎች አስከሬን ባንዲራ ምንጣፍ ስጋጃ የሳቡ፣
በምን መልክ ይከትባቸው ታሪኩ ምን ብሎ ይዘግባቸው ትውልዱ?

ወንበዴ ሌቦች መዝብረው ስትኖሪ መናጢ ድሀ ያረጉሽ፣
የዘረፉትን ሲጋሩ ተጣልተው ዘርሽን መንጥረው ያስፈጁሽ፣
ሥጋ አጥንትሽን እንደ ጨፈቃ ከምረው በሞተር ክሬን ያነሱሽ፣
በግኒደሮች በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ እንደ በሰበሰ ቆሻሻ የጣሉሽ፣
እንኳን ገዳይ አስገዳይ ወገኔ ያልሽው ተራ በተራ የከዳሽ፣
የእነ ሥም የለሽ እስተንፋስ የድሆች ህይወት ማን ያንሳሽ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምነው ምነው ? ( ዘ-ጌርሣም)

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ጥቅምት 29 ቀን ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share