ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])
ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን በወጣው የሐበሻ ወግ ሳምንታዊ መጽሔት ላይ አቶ መስፍን አረጋ “የኤፍሬም ማዴቦ ሸፍጥ” በሚል የጻፉትን ጽሁፍ አነበብኩና እንደማህበረሰብ ለገባንበት ቀውስ አንዱ ምክንያት የነ አቶ መስፍን አረጋ አይነቶቹ ቆርጦ ቀጥሎች መብዛታቸው መሆኑን አረጋገጥኩ። አቶ መስፍን ግዜ ወስደው እኔ “ኦ – ብልፅግና. . . . አ – ብልፅግና” በሚል አርዕስት የጻፍኩትን ጽሁፍና፣ እሳቸው እኔን ለመተቸት በደመ ነብስ የጫሩትን ጽሁፍ ጎን ለጎን አስቀምጠው ተራ በተራ ደጋግመው ቢያነቡ፣ የሚቀጥለው ጽሁፋቸው አርዕስት “የመስፍን አረጋ ሸፍጥ” እንደሚሆን አልጠራጠርም። ችግሩ የአቶ መስፍን ትልቁ ችሎታ ያልተጻፈ ማንበብና ቆርጦ መቀጠል ነው እንጂ ለቁም ነገርና እራስን ለመውቀስ ድፍረቱ አላቸው ብዬ አላምንም! እንዲህ አይነት ድፍረትና ችሎታ ቢኖራቸውማ ኖሮ መጀመሪያውኑ ያልተጻፈ አያነቡም፣ የሌላ ሰው ጽሁፍ ላይም የራሳቸውን ድሪቶ አይደርቱም ነበር!
የአቶ መስፍን አረጋ ጽሁፍ የሚጀምረው እኔ “ኦ – ብልፅግና. . . . አ – ብልፅግና” በሚል አርዕስት ከጻፍኩት ጽሁፍ ውስጥ፣ አንድ አንቀጽ (Paragraph) ወስደውና ከአንቀጹ ውስጥ እሳቸው ላሰቡት የሸፍጥ ስራ አልሆን ያላቸውን ሃረግ ቆርጠው አስቀርተውና፣ በቆረጡት ሃረግ ቦታ ጽሁፌ ውስጥ የሌላ አንቀጽ መክፈቻ የሆነ ዓረፍተ ነገር ቀጥለውበት ነው (እሱንም ቆራርጠው)። አንባቢ በግልጽ እንዲገባው አቶ መስፍን አረጋ በጽሁፋቸው መጀመሪያ ላይ አቶ ኤፍሬም አሉ ብለው ያስቀመጡት ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ነው-
“በዛሬዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ግልጽ የሆነ ልዩነት ያላቸው ሁለት ትልልቅ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች በአቋማቸውም በፖለቲካ አሰላለፋቸውም “አማራ ብልፅግና” እና ”ኦሮሞ ብልፅግና” ዉስጥ ካሉ ኃይሎች ጋር በቅርብ የተሳሰሩ ናቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው የፖለቲካ ምስቅልቅል እነዚህ ሁለት ኃይሎች . . . . የሚያደርጉት ትግል ውጤት ነው” ኤፍሬም ማዴቦ
እኔ በራሴ እጅ የጻፍኩትና ዛሬ በተለያዩ ሜዲያዎች ላይ የሚገኘው ጽሁፍ የሚከተለውን ይመስላል-
በዛሬዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ግልጽ የሆነ ልዩነት ያላቸው ሁለት ትልልቅ ቡድኖች አሉ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች በአቋማቸውም በፖለቲካ አሰላለፋቸውም “አማራ ብልፅግና” እና ”ኦሮሞ ብልፅግና” ዉስጥ ካሉ ኃይሎች ጋር በቅርብ የተሳሰሩ ናቸው። አንደኛው ቡድን እራሱን “ፌዴራሊስት ኃይሎች” እያለ የሚጠራው የብሔር ፖለቲካ አራማጆች ስብስብ ሲሆን፣ የዚህ ቡድን መንፈሳዊ መሪ ኦሮሚያ ክልል ነው፣ ሌላው የአንድነት ኃይል የሚባለው ስብስብ ሲሆን የዚህ ቡድን መሪ ደሞ አማራ ክልል ነው።
መስመር የተሰመረበት የመጨረሻው አራት ረድፍ አቶ መስፍን አረጋ ቆርጠው ያስቀሩት ክፍል ነው። የአቶ መስፍን ሸፍጥ ይህንን ክፍል ቆርጠው ማውጣታቸው ብቻ አይደለም፣ቆርጠው ባወጡት ክፍል ምትክ ለቅጥፍታቸውና ለሸፍጥ ስራቸው ያመቸኛል ያሉትን የጽሁፌን ሌላ ክፍል እንደ ክትፎ ከታትፈው የአቶ ኤፍሬም አባባል ነው ብለው ማቅረባቸው ጭምር ነው። አቶ መስፍን አረጋ ኤፍሬም ማዴቦን ብቻ ሳይሆን ማንንም ሰው የመተቸትና በየትኛውም ጽሁፍ ላይ አስተያየት ማቅረብ መብታቸው ነውና እሱ ላይ ምንም ችግር የለኝም። ነገር ግን የሌላ ሰውን ጽሁፍ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ አድረገው ሲያቀርቡ፣ የሰውየውን ጽሁፍ እንዳለ ነው ማቅረብ ያለባቸው እንጂ፣ አንድ ሰው ከጻፈው ጽሁፍ ዉስጥ አረፍተ ነገሮችን የራስን አላማ በሚያሳካ መልኩ ከየቦታው ሰብስበው ጸሐፊው ያላለውን ነገር አለ ብለው ማቅረብ ከነውርም ነውር መሆኑን አቶ መስፍን ሊያውቁ ይገባል።
አቶ መስፍን የሚያነቡት ከቀኝ ወደግራ ይሁን ወይም ከግራ ወደ ቀኝ እኔ ብዙም የማውቀው ነገር የለም፣ የኔን ጽሁፉ ግን ከቀኝ ወደግራም ከግራ ወደቀኝም እንዳላነበቡት እርግጠኛ ነኝ። እኔ በጻፍኩት ጽሁፍ ውስጥ ሁለት ቡድኖች ብዬ ያስቀመጥኩት እራሳቸውን ፌዴራሊስት ኃይሎች እና የአንድነት ኃይል እያሉ የሚጠሩትን ስብስቦች ነው እንጂ አማራ ብልፅግና እና ኦሮሞ ብልፅግናን አይደለም።
አቶ መስፍን “አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የአማራ ህዝብ የሚጨፈጨፈው በኦሮሞ ብልጽግና እና በአማራ ብልፅግና ሽኩቻ ሳቢያ ነው ሲል እየሸፈጠ ነው” በሚል በፍጹም ያላልኩትን ነገር አለ ብለው ከሰውኛል። የኔን ጽሁፍ ቅዳሜ መስከረም 14 ቀን በወጣው ፍትህ መጽሔት ላይ ወይም ዘሐበሻና (You searched for ኦ – ብልፅግና. . . . አ – ብልፅግና – ዘ-ሐበሻ (Zehabesha) የዕለቱ አብይ ዜና | ሰበር ዜና | አስተያየትና ትንታኔ | ዜና የኢትዮጵያ (amharic-zehabesha.com)) ቦርከና ድረገጾች ላይ ማንም ሰው ሄዶ ማንበብ ይችላል። እኔ በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ በተመለከተ የሚከተሉት ሦስት ዓረፍተ ነገሮች ናቸው ያሉበት፣
“ብዙዎቻችን አማራ ዘረኛ ሆነ፣ አማራ ከኢትዮጵያዊነት ሸሸ እያልን አማራን እንከሳለን። የአማራ ብሔረተኝነት እየገነነ የመጣው በአንድ በኩል ደደቢት በረሃ ዉስጥ በህወሓት የተሸረበና በተደጋጋሚ በተግባር የታየ በአማራው ላይ ያነጣጠረ የጥፋት ዘመቻ በመኖሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ በተገለጸው መልኩ የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች አማራ ላይ በመተባበራቸውና የተከበሩ ዶር ሃንጋሳ ኢብራሂም በቅርቡ እንደተናገሩት ኦሮሚያ ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ መንግስታዊ ድጋፍ ያለው መሆኑ ነው”
“መከራ፣ግፍ፣ስደት፣መፈናቀልና ሞት አማራው ላይ የበረከተው አማራው የሚገኝበት ጎራ የማይናበብ፣የማይግባባ አንድ ላይ ቆሞ እራሱን መከላከል የማይችል ሳይሆን ያልቻለ በመሆኑ ነው”
“የአማራ ክልል እንደ ክልልም እንደ ፖለቲካ ማህበረሰብም ይህ ነው ተብሎ የሚነገር መሪም አመራርም የሌለው በአክቲቪስቶች፣ በባለኃብቶች፣ በዩቲዩብ አርበኞችና በተለያዩ የጎበዝ አለቆች የሚመራና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መጫወት የሚገባውን ትልቅ ሚና የዘነጋ ክልል ነው። የህወሓት ኃይሎች ወሎ፣ጎንደርና ሰሜን ሸዋ ድረስ ያለማንም ከልካይ እየዛቱ መጥተው ይህንን ህዝብ የዘረፉት፣ያፈናቀሉትና የጨፈጨፉት አማራው ባለፉት ሰላሳ አመታት በፖሊሲ ደረጃ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ መጫወት ያለበትን ሚና እንዳይጫወት ስለተደረገ ነው”
አቶ መስፍን እስኪ ያሳዩኝ በየትኛው የጽሁፌ ክፍል ውስጥ ነው የአማራ ህዝብ የሚጨፈጨፈው በኦሮሞ ብልጽግና እና በአማራ ብልፅግና ሽኩቻ ሳቢያ ነው ያልኩት?
“በኤፍሬም ማዴቦ ምክር መሰረት የአማራ ህዝብ ከመጨፍጨፍ የሚድነው የአማራ ብልፅግናን (ማለትም ብአዴንን) ካዳነ ብቻ ነው” በሚል ክስም ተከስሻለሁ። አቶ መስፍን የት ቦታ ነው ይህንን ያልኩት? ለመሆኑ እርሶ ማንበብ ይችላሉ? ያነበቡትንስ ይረዳሉ? ወይስ ምንም ይባል ምን እርስዎ የፈለጉት ኤፍሬምን በሸፍጥ መክሰስ ነው? እሱ ከሆነ ለምን ጽሁፌን መጥቀስ አስፈለጎት? የእርስዎ ብጤ ጥራዝ ነጠቅ እየተነሳ አንቱ የተባሉ ምሁራንን እንዳሰኘው መቦጨቅ በሚችልበት የማህበራዊ ሜዲያ አለም ለምን እርስዎም እንደ ስራ ጓደኞችዎ ያለማስረጃ አይከሱኝም? እኔም ማስረጃ ከማያስፈልገው የማህበራዊ ሜዲያ ቆርጦ ቀጥል አርበኛ ጋር በመመላለስ ግዜዬን አላጠፋም ነበርኮ!
እኔ በጽሁፌ ውስጥ የአማራ ህዝብ ከመጨፍጨፍ የሚድነው የአማራ ብልፅግናን ካዳነ ብቻ ነው በፍጹም አላልኩም። እኔ ያልኩት የአማራ ህዝብ መሪ የለውም፣- የአማራን ክልል ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ነው፣ ነገር ግን የአማራን ህዝብና የአማራ ብልፅግና ፓርቲን የሚያገናኛቸው እጅግ በጣም ቀጭን ክር ነው። ይህ ምን ግዜም ሊበጠስ የሚችል ክር እንደየሁኔታው ሊጠነክርና ጥንካሬው ለሌሎች “ኢትዮጵያ” ከሚባል ትልቅ የፖለቲካ ማህበረሰብ ዉጭ ሌላ አማራጭ ለሌላቸው አካባቢዎችም ተስፋ ሊሆን ይችላል። ይህ እንዲሆን የአማራ ክልል መሪዎች የአማራን ህዝብ መፈናቀል ማስቆም አለባቸው፣የአማራን ህዝብ ስደት ማስቆም አለባቸው፣የአማራን ህዝብ ሞትና መከራ በድፍረት በቃ ማለት አለባቸው፣ ከሁሉም በላይ ግን የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መጫወት ያለበትን ሚና ማወቅና አማራ ይህንን ሚናዉን እንዲጫወት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው። የአማራ መሪዎች ይህንን ማድረግ የሚችሉትና ማድረግ ያለባቸውም “አማራ ብልፅግና” ፓርቲ ሆነው ሳይሆን የአማራ ህዝብ ትክክለኛ መሪ ሆነው ነው። የአማራ መሪዎች ታማኝነት ለአማራ ህዝብ ነው እንጂ ለብልፅግና ፓርቲ አይደለም። እውነትን ማወቅ የፈለገ ሰው እነዚህን ቃላት ዛሬም ጽሁፌን ፈልጎ ማንበብ ይችላል፣ የ”ኤፍሬም ማዴቦ ሸፈጥ” ያሰኘኝ ይህ ከሆነ፣ አዎ ሸፍጠኛ ነኝ!
ሌላው የአቶ መስፍን አረጋ ትልቅ ነውር እኔ በጽሁፌ ውስጥ በፍጹም ያልዳሰስኳቸውን ሃሳቦችና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልጠቀስኳቸውን ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች ስም ጠቅሰው ጭራሽ የኔን ጽሁፍ ከአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ጋር ማያያዛቸው ነው። እኔ ቤቴ ውስጥ ቁጭ ብዬ በጻፍኩት ጽሁፍ የሌሎች ግለሰቦች ስም የሚጠራበትና የፖለቲካ ፓርቲ ስም የሚጎድፍበት ምክንያት ምንድነው? ለማሞገስም ለመውቀስም እኔ የጽሁፉ ባለቤት አለሁኮ፣ ወይስ ለዚህ ማንም ላይ እንዳሰኘው ለሚሰነዘር የጭቃ ጅራፍዎ እኔ ኤፍሬም አልበቃ አልኮት?
አቶ መስፍን ይቺን የመጨረሻ ውኃዬን የማፈሰው ድንጋይ ላይ እንደሆነ አውቃለሁ፣ ግን ድንጋይም ቢሆን አንዳንዴ ይርሳልና ማፍሰሴን ልቀጠል። በመጽሐፍ፣በጦማር ወይም በሌላ በተለያየ መልኩ ጽሁፍ እየጻፍን ሃሳባችንን ለማህበረሰብ የምናጋራው ለማሳወቅና ለማወቅ ወይም ለመማርና ለማስተማር ነው። እራስንም ማህበረሰብንም የማያስተምር ጽሁፍ መጻፍ የማህበረሰብን የእውቀት መሰረት ይንዳል፣ቆርጦ መቀጠልና ያልተጻፈ ማንበብ የፈጠራ ችሎታን የገድላል፣የእርስዎን ግዜ በከንቱ ያባክናል፣ ከሁሉም በላይ ደሞ አቶ መስፍን ምንኛ የቀለሉ ሰው ናቸው ያሰኞታል። ስለዚህ እባክዎ ካሁን በኋላ ማህበረሰብን የሚጎዳ፣ ግዜዎን የሚያጠፋና እርሶነትዎን የሚያቀል ጽሁፍ አይጻፉ!
http://amharic-zehabesha.com/archives/177301