ትልቁን ቃል (ፅንሰ ሃሳብ) አረከሱት! (ጠገናው ጎሹ)

November 6, 2022

ጠገናው ጎሹ

የዚህ ሂሳዊ አስተያየቴ ዋነኛ ትኩረት ጥልቅና ሰፊ ይዘት ያላቸውን ፅንሰ ሃሳቦች ትርጉምና ጠቀሜታ መተንተን አይደለም።  ይልቁንም እኩያን ገዥ ቡድኖች እነዚህን ፅንሰ ሃሳቦች ለማታለያነት ባሰለጠኑት ብዕራቸውና አንደበታቸው እያስተጋቡ ለእኩይ ዓላማቸው ማሳለጫነት እየተጠቀሙባቸው የመሆኑ መሪር እውነታ እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ አጠቃላይ የውድቀት ቁልቁለት ይዞን እየወረደ ነውና ከምር ከሆነና ገንቢነት ካለው የህሊና ፀፀት የሚነሳ የእርምት እርምጃ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ግድ ይለናል ለማለት ነው።

እጅግ ብዙዎቻችን ብልፅግና (prosperity) ሲባል ብዙውን ጊዜ ቀድሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው የቁስ ወይም የማተሪያል (የገንዘብና የሌላ ንብረት) መትረፍረፍ ነው። ምንም እንኳ የገንዘብና የሌላ ንብረት መኖር ለፅንሰ ሃሳቡ ትርጉም የተሟላ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ቢሆንም ብቻውን ግን በፍፁም አተረጓጎም አይደለም ። በእውን  እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ (የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ እድገት የሚረጋገጥበት ሥርዓተ ፖለቲካ)  የምንሻ ከሆነ  ባለጌና ጨካኝ  ገዥ ቡድኖችና  ህሊናቸውን እንደ ማነኛውም ተራ ሸቀጥ የሚቸበችቡ ሸሪኮቻቸው በበጎ ነገር ገላጭነታቸው ሰፊና ጥልቅ  ትርጉም ያላቸውን ቃላት (ፅንሰ ሃሳቦች) የመከራና የውርደት አገዛዛቸው መገለጫ እያደረጉ ሲነግሩን ለምንና እንዴት ሳንል እየተቀበልን እንደ በቀቀን ከማስተጋባት እጅግ ወራዳ ልማድ ሰብረን መውጣት አለብን።

ብልፅግና (PROSPERITYፍፁም ወይም እንከን የለሽ ህይወት ወይም አኗኗር ማለት ሳይሆን (በገሃዱ ዓለም ህይወት ፍፁምነት የለምና) አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ በንብረት፣ በአካል፣ በአእምሮ፣ በሞራል፣ በሥነ ምግባር ፣ በመንፈስ፣ ወዘተ  ስኬታማ የሆነ ህይወት ወይም አኗኗር ለመኖር የመቻልን መልካምነት የሚገልፅ ጥልቅና ሰፊ ቃል ( ፅንሰ ሃሳብ ነው) ።  ሰው ከመሆን ባህሪ ጋር የተጣበቁና ጨርሶ ለማስወገድ የሚያስቸግሩ የግል ባህሪያት ፣ የቤተሰብ እና የማህበረሰብ መስተጋብሮች ተፅዕኖ የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ብልፅግና የማያቋርጥ የአስተሳሰብ ፣ የእውቀት፣ የክህሎት፣ የሥራ ሥነ ምግባር፣ የግልና የወል ጥረት አስፈላጊነትንና በአጠቃላይ የማያቋርጥ የተሻለ የህይወት አድማስን ቅን በሆነና በተቀደሰ ህሊና ወይም ሰብዕና አሻግሮ የማየት ችሎታንና የሚደረስበት አመንገድ ሁሉ የማመቻቸትን  አቅምና ችሎታን የተሸከመ  ፅንሰ ሃሳብ ነው። ይህ አይነት ሰፊና ጥልቅ ግንዛቤ ሊኖር ሲችል ብቻ ነው በማያቋርጥና ሁለንተናዊ በሆነ የሥልጣኔ ግሥጋሴ ንቁ ተሳትፎ የሚኖረውና የዚሁ በጎ ውጤት ተጠቃሚ የሚሆን  ግለሰብ ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ብሎም አገር ለመፍጠር  የሚቻለው።  በእውነተኛ የብልፅግና ህይወት ሰንሰለት የሚተሳሰር ትውልድ መፍጠር ማለት ይኸው ነው።  በዚህ አይነት አስተሳሰብና አካሄድ ብቻ ነው ለገሃዱ ዓለምም ሆነ ከሞት በኋላ ተስፋ ለምናደርገው ዓለም የሚበጅ ብልፅግናን ሰፊና ጥልቅ ትርጉም የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ የምንችለው።

በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ብልፅግና የተጠቀሰው (የተፃፈው) መሠረታዊ ትርጉምም እንዲሁ በአየር ላይ የሚንሳፈፍ መንፈስ ሳይሆን ከሞት በኋላ ተስፋ ለምናደርገው ህይወት ስንቅ የሚሆነንን ሥራ በዚሁ በገሃዱ ዓለም በምንኖርበት ዘመናችን ሠርተን ለመገኘት በምናደርገው እልህ አስጨራሽ ጥረት የሚገገኝ መሆኑን ለመረዳት የቲዎሎጅ ልሂቅ መሆንን ወይም የተለየ ቅዱስነትን አይጠይቅም ።

ክርስቶስ የመጨረሻውን መስእትነት ይከፍል ዘንድ መሰቀያውን (መስቀሉን) እራሱ ተሸክሞ ወደ መሰቀያው ሥፍራ እንዲሄድ ሲያደርጉትና ሲሰቅሉት በፀጋ የተቀበለው በፈጣሪ አምሳል ተእንደተፈጠረ የምናምንለት የሰው ልጅ  ለምድሩም ሆነ ለሰማያዊው  ህይወቱ የሚበጅ ቁም ነገር መሥራት ካለበት ሊከፍል የሚገባው ዋጋ እስከ የትና እስከምን ሊያደርስ እንደሚችል ለማስተማር እንጅ ተሰቅሎ መነሳቱን አምናለሁና አምናለሁ በሚል ተግባር አልባ  መነባንብ ወይም ፀሎት ወይ ኤሉሄ ወይ እግዚኦታ ወይም ንስሃ ፣ ወዘተ ብቻ አለመሆኑን ለመረዳት የነገረ መለኮት  (ቲዎሎጅ) ልሂቅነት ጨርሶ አይጠይቅም። የብልፅግና ጥልቅና ሰፊ የሆነ ምንነትና እንዴትነት እስከዚህ ድረስ የሚሄድ ነው።

የእኛዎቹ ተረኛ የኢህአዴግ አንጃ ገዥ ቡድኖች ጠርናፊ የሆነው አብይ አህመድና መሰሎቹ ግን እንኳን መስዋእትነት ሊከፍሉ የሩብ ምእተ ዓመቱ አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል  አልበቃ ብሎ አገር አራት ዓመታት ሙሉ  በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ስትቃትት ቢያንስ አዝናለሁ ለማለት ለምን ተሳናችሁ? ሲባሉ የብልፅግና ወንጌል አማኝነታችን ምንም ቢፈጠር ማዘንና መተከዝን ወይም እናዝናለን ማለትን አይፈቅድም ወይም ይህንን ማድረግ ከብልፅግና መንገዳችን ያስወጣናል  በማለት ሊያሳምኑን ሲሞክሩ መስማት በአገራችን የሆነውንና እየሆነ ያለውን እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ምክንያታዊና ሚዛናዊ በሆነ ህሊና ለታዘበና ለሚታዘብ ወገን ፈታኝነቱበእጅጉ ከባድ ነው። አዎ! አብይ አህመድና ባልደረቦቹ  ከዚህ አልፈው ፈጣሪን ሳይቀር በደም የጨቀየ የቤተ መንግሥት ፖለቲካቸው ተባባሪ ሲያደርጉት መታዘብ የሚያስከትለውን የህሊና ቁስለት ቃላት በተሟላ ሁኔታ የሚገልፁት አይመስለኝም። በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለዘመናት የበሰበሰውን ፣የከረፋውን እና ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ አገርን እጅግ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ምድረ ሲኦል በማድረግ ላይ የሚገኘውን ገዥ ፓርቲ  ብልፅግና የሚል ስያሜ በመስጠት በታላቁ መፅሐፍ ቅዱስ ወይም በወንጌል ላይ የሚሳለቀውን የፖለቲከኞች ጨዋታ ከምር ልብ ለሚል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የደረስንበትን ሁለንተናዊ ዝቅጠት ለመረዳት በፍፁም አይቸገርም።

 ባለጌና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ጥልቅና ሰፊ ትርጉም ያለውን የብልፅግና ፅንሰ ሃሳብ ሲያረክሱትና ሲያራክሱት ሲሆን በግልፅና በቀጥታ ነውር መሆኑን ለመናገርና ቢያንስ ግን እንደ በቀቀን እየተቀበሉ ላለማስተጋባት መወሰን አቅምና ወኔ ማጣት አሳዛኝና አስፈሪ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውድቀትና የሞራል ዝቅጠት ነው። አዎ! ሸፍጠኛ ፣ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ይህ ትውልድ በእራሳቸው የሚዘወረው ሥርዓት ያደረሰውንና እያደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያና የቁም ሰቆቃ የብልፅግና መንገድ  ነውና ከመቃወም ይልቅ እየመጣችሁ ተደመሩ የሚለውን  ጨካኝ የፖለቲካ ኦርኬስትሬሽን ለምንና እንዴት  በቃ ለማለት እንደተሳነው እንኳን ለመረዳት ለማሰብም በእጅጉ ከባድና አስፈሪ ነው።

አዎ! ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ንፁሃን ወገኖች የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ በሚያዩበት እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ ባለሙያ የጠፋ እስኪመስል ድረስ “ለድንቅ አገዛዛቸው” አሻራ የሚሆን መናፈሻ እያዘጋጁና እየመረቁ ስለ ብልፅግና ለማታለያነት ባሰለጠኑት አንደበታቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳቸውን ሲያስታውኩበት (ሲያቀረሹበት)  ትርጉም ያለው ተቃውሞ ለማድረግ አለመቻሉ አልበቃ ብሎ እንደ በቀቀን  እየተቀበለ የሚያስተጋባ ወይም የእራሱን አጀንዳ ትቶ የሚወረወርለትን አጀንዳ እየተቀበለ የሚያላዝን ትውልድ እንዴትና መቼ ከዚህ ክፉ የአዙሪት እንቆቅልሽ ለመውጣት እንደሚቻለው ለመገመት በእጅጉ አስቸጋሪና አስፈሪ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሳማ አንሁን! የሆንም ከአሳማነት ባህሪ እንላቀቅ!

በእውነት ከተበደሉት ጋር ከመቆም ፣ ገዳይና አስገዳይ ገዥዎችን በግልፅና በቀጥታ ከመገሰፅና ከመቃወም ፣ ሸፍጥኝነትንና ከንቱ ሰባኪነትን ከመፀየፍ ፣ ከግል ፍላጎት አልፎ ለጋራ ፍላጎትና ጥቅም እውን መሆን ከመታገል፣ በግልብ ስሜት ሳይሆን በሰከነና ዘላቂነት ባለው ሰብዕና ከመራመድ፣ የትናንቱን መልካም ነገር ለዛሬው እና የዛሬውን ደግሞ ለነገው ግብዓት እያደረጉ ወደ ፊት ማራመድን ድምጥማጡን ከሚያጠፋ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት የበላይነትን በመቀበልና በማስታመም የእውነተኛ ብልፅግና ትርጉምን ወደ ተግባር መተርጎም ይቻላል ብሎ ለማመን ከመከጀል (ከማሰብ) የከፋ የፖለቲካ አስተሳሰብ ጉስቁልና እና የሞራል ዝቅጠት ከቶ የለም።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የህወሃት እኩይ ገዥ ቡድን የፍፁም አፈና እና የፍፁም ጭካኔ ፖለቲካ መሳሪያ ሆነው ያገለገሉ ሸፍጠኛ ፣ ሴረኛና ጨካኝ ኦህዴድ (አብይ) መራሽ የኢህአዴግ አንጃዎች የህዝብን በተለይም በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የግድ ባይነት የትግል መርህና ዓላማ ላይ ሳይሆን እጅግ ግልብ በሆነና አገርን መልሶ የውድቀት ሰለባ በሚያደርግ  የጅምላ ተቃውሞ (mob) አቅሉን ያጣውን ወጣት ትውልድ ተጠቅመው ፍፁም እርጉም የሆነ የተረኝነት ሥልጣነ መንበርን በመቆጣጠር  በመከረኛው ህዝብ ላይ  የጭቃ ጅራፋቸውንና የፍፁም ጭካኔ ሰይፋቸውን እያወረዱበት ቀጥለዋል።

እናም እነዚህ ኦህዴድ (አብይ አህመድ)  መራሽ ኢህአዴጋዊያን ጥልቅና የተቀደሰ ትርጉም ያለውን ብልፅግናን በእጅጉ ሲያረክሱትና ሲያራክሱት በተለይ የተማርኩና ልሂቅ ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል በግልፅና በቀጥታ ነውር ነው አለማለቱ አልበቃ ብሎት ይህንኑ ፀያፍና አደገኛ የሆነ አጀንዳ እየተቀባበለ እንደ በቀቀን ሲያስተጋባ  መታዘብ በእጅጉ አስጨናቂና አስፈሪ ነው።

በዓለማዊውም ህይወትም ሆነ በሃይማኖታዊ እምነት እጅግ ሰፊና ጥልቅ ትርጉም ያለውን የብልፅግና ፅንሰ ሃሳብ በእጅጉ ሲያጎሳቁሉት (ሲያረክሱት) ሲሆን ከምር በሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ  ቢያንስ ግን በግልፅና በቀጥታ ከነውርነት አልፎ ወንጀል ነው ለማለት ወኔው የሚከዳው  ትውልድ የትኛውን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እያለመ (እየናፈቀ) እንደሆነ ለመገመት በእጅጉ ያስቸግራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከራሳችን አልፎ በአምሳሉ የፈጠረንን እውነተኛ አምላክ ለምን ለመሸንገል እንሞክራለን?

ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላወቻቸው የእያንዳንዱን መከረኛ ኢትዮጵያዊ ህይወት በቀላሉ ሊያገግም በማይችልበት አኳኋን እያመሰቃቀሉ ጉዟቸውና ግባቸው ዴሞክራሲንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደሆን ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ህሊናቸውን ጨርሶ አይጎረብጣቸውም።  እነዚህ እኩያን ገዥ ቡድኖች ዴሞክራሲ ፣ ፍትህ፣ ነፃነት፣መብት ፣ ግዴታ ፣ እኩልነት፣ መቻቻል፣ አብሮነት፣ መከባበር፣ መተሳሰብ ፣ መረጋጋት፣ ሰላም እና  የጋራ እድገት/ብልፅግና የሚሰኙትን እጅግ ሰፊና ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ቃላት (ፅንሰ ሃሳቦች)  ለዘመናት በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ ተዘፍቀው የኖሩበትንና አሁንም ከመቸውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ ተዘፍቀው የሚገኙበት ሥርዓታቸውን  ቆንጆ አስመስለው ለማሳየት በኮስሞቲክነት  (as cosmotics) እንደሚጠቀሙባቸው ለመረዳት  በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር እውነት በላይ መረጃና ማስረጃ ፈፅሞ የለም። አለ የሚል ሰው ወይም አካል  ካለ ወይ ህሊናው ጨርሶ የበከተ የሥርዓቱ ሰው ነው ወይም የሥርዓቱ ፍርፋሪ ለቃሚ ግብረ በላ ነው ወይም እንደ ደመ ነፍስ እንስሳ ሆዱ ከሞላ ምን አገባኝ  ባይ ፍጡር ነው ወይም ራሱን ለባርነት አሳልፎ የሰጠ ሰው መሳይ ደመ ነፍስ እንስሳ  ነው ወይንም የፍፁም ድንቁርና ሰለባ ነው። ወደድነውም ጠላነው እንኳንስ ማስቆሚያ ማስታገሻም ያላገኘንለት ግዙፍና መሪር እውነት ይኸው ነው።

ለነገሩ እነዚህ የህወሃት/ኢህአዴግ ውላጆች የተጠናወታቸውን የሸፍጥ፣ የሴራ ፣ የዝርፊያና የግፍ ፖለቲካ ሥርዓት በተረኝነት ለማስቀጠል እስካስቻላቸው ድረስ ልክ በሌለው የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ የተጎሳቆለውንና የተመሰቃቀለውን የህዝብ ህይወት የብልፅግና መንገድ እንደሆነ ሊያሳምኑት ሲቃጣቸው ከምር የሚቆጣና “ብልፅግናን ያህል ሰፊና ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ የማርከሳችሁና የማራከሳችሁ እብደት በቃ!” ለማለት ተስኖት በውድቀት ድግግሞሽ አረንቋ ውስጥ የሚጓጉጥን ትውልድ እንቆቅልሽነት ለመረዳትና ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካና የሞራል ወኔ የማጣት ጉዳይ በእጅጉ ሊያስበን ካልቻለና የሚበጀውን ለማድረግ ካላነሳሳን ፊታችን ያለው እጣ ፈንታ በእጅጉ አስፈሪ ነው።

አዎ! ይህ ትውልድ በራሱ አምሳል ፈጥሮ ታማኝ አገልጋዩ በማድረግ የፖለቲካ ወለድ ወንጀሉን ሲያስፈፅምባቸው የነበረውን ህወሃትን ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ አስወግደው በንፁሃን ደም የተጨመላለቀውን የፖለቲካና የሞራል ሰብእናቸውን ወይም ማንነታቸውን በእውነተኛ ፀፀት፣ ይቅርታ፣ እና ሁሉንም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ አካል በሚያሳትፍ አካሄድ በማደስ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ለማድረግ የድርሻቸውን ከመወጣት ይልቅ ተሃድሶ በሚል እጅግ የለየለት የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታ በማስቀጠል የገንዛ አገሩን ለእነርሱ ምድረ ብልፅግና ፣ለእርሱ ግን ምድረ ሲኦል ሲያደርጉበት “የመከራውና የውርደቱ ፅዋ ሞልቶ ከፈሰሰ አያሌ ዓመታት ተቆጥራዋልና በቃችሁ” ለማለት ወኔና አቅም ያጣበትን እንቆቅልሽ መፍታት ይኖርበታል።

እስካሁን የመጣንበትና አሁንም እየሄድንበት ያለው ግዙፍና መሪር እውነት ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና ሸሪኮቻቸው ሰፊና ጥልቅ የሆነ ትርጉም ያላቸውን ፅንሰ ሃሳቦች ለእኩይ ዓላማቸው ሽፋን ሰጭነት ሲጠቀሙባቸው እያየንና እየሰማን እንዳላየንና እንዳልሰማን የማለፋችንን ፣ ለምንና እንዴት ብለን ሳንጠይቅ እንደ በቀቀን እየተቀበልን የማስተጋባታችንን እና ለአድርባይነት (ለከርስ አዳሪነት) የማዋላችንን እጅጉ አስቀያሚ የፖለቲካ አስተሳሰብና የሞራል ዝቅጠት ከምር የማያሳስበንና ውጤታማ ለሆነና ዘላቂነት ላለው የጋራ ትግል ከምር የማያነሳሳን ከሆነ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ናፋቂነታችን ባዶ  ቅዠት ነው።

እርግጥ ነው ትልልቅ እና ጥልቅ ትርጉም ያላቸውን ቃላት (ፅንሰ ሃሳቦች) በማስተጋባት ለሚፈልጉት ዓላማ የመጠቀም ጉዳይ እንኳንስ እኩያን ፖለቲከኞች በሚገዙት እንደኛ ባለ ማህበረሰብ በአንፃራዊነት አድጓል ወይም ሠልጥኗል በሚባል ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥም ፍፁምነት ባለው ሁኔታ ማስቀረት አይቻልም። ማድረግ የሚቻለው በጠንካራና ዘላቂ በሆነ መሠረት ላይ በተመሠረተ ሥርዓተ ፖለቲካና አስተዳደራዊ እርምጃ በመቆጣጠር ጤናማ  የሆነውን ማህበረሰባዊ መስተጋብርና  የማያቋርጥ የእድገት ወይም የብልፅግና ግሥጋሴን ማስቀጠል ነው። ለዘመን ጠገቡና አሁንም በተረኛ ኦህዴድ (አብይ መሃመድ) መር እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ለቀጠለው የመከራና የውርደት ሥርዓት ሰለባዎች ካደረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይህንኑ ለማድረግ ያለመቻላችን ውድቀት ነውና ከዛሬ በኋላ ይበቃናል ።

ቀደምት ትውልዶች በነበሩበት  አገራዊና ዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ ሠርተውት ያለፉትን እጅግ ድንቅ ታሪክና የሠሩትን ስህተት በቅጡ ለይቶ በትምህርት ሰጭነቱ በመጠቀም የእራስን ሁለገብ ብልፅግና ታሪክ ሠርቶ ከመገኘት ይልቅ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያነትን ድራሹን የማጥፋት የፖለቲካ ሸፍጣቸውንና እብደታቸውን እንደ ፍኖተ ብልፅግና እየተረኩ ሊያሳምኑን ሲቃጣቸው ከምር በቃችሁ ለማለት በፍፁም ተጨማሪ ጊዜ ልንጠብቅ አይገባንም።

 አሳዛኝ የሆነው ጉዳይ ግን እንኳንስ ከረጅሙ አሁን ከምንገኝበት መከራና ውርደትም  ከምር እየተማርን ያለመሆናችን መሪር እውነታ ነው።

የዛሬ አራት ዓመት እነ አብይ አህመድ በህወሃት/ኢህአዴግ እቅፍ ውስጥ ሲያድጉና ሲያገለግሉ ባካባቱት እኩይ ተሞክሮና  ከዚሁ አኳያ ባሰለጠኑት አንደበታቸው ለግልብ ስሜት በሚስማሙ (በሚጥሙ) ዲስኩሮችና ትርክቶች ሲያነሆልሉን ለምንና እንዴት ብለን ለማሰብ ጊዜና ትእግሥት ሳንወስድ “የዘመናችን ሙሴዎች” የሚል አሳፋሪ ውዳሴ ያቀረብንበትን የውድቀት መንገድ ዛሬም እየደገምነው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተራ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን አንናቀው ! ግርማ ካሳ

ለዘመናት በዘለቀ የንፁሃን ደም ፣ የደም እንባ እና የቁም ሰቆቃ እጆቻቸው የጨቀዩና ህሊናዎቻቸው የበሰበሱ የአንድ ሥርዓት (የኢህአዴግ) ውላጆች በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ያጠፉት ነፍስ ፣ ለቁም ሰቆቃ አጋልጠው የሰጡት ህይወት እና ለውድመት የዳረጉት ንብረትና ሃብት በእጅጉ አሳዛኝነት የመሆኑ ጉዳይ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሁለቱ አንጃዎች (ኦህዴድ/ብልፅግናእና ህወሃት) በመርህ ደረጃ መግደላቸውንና ማገዳደላቸውን ለማቆም መስማማታቸውን የሚቃወም ባለ ጤናማ አእምሮ ሰው ያለ አይመስለኝም።

ችግሩ ያለው ግን ፈፅሞ እዚህ ላይ አይደለም።

በተካሄደው ድርድር ተገኘ የተባለው ውጤት የአገራችን የፖለቲካ ብልሹነት ካስከተለውና እያስከተለ ካለው አጠቃላይ ቀውስ አንፃር ሲታይ ከስኬታማነት ይልቅ የውድቀት መንገድ ሊቀርበው እንደሚችል ለመተንበይ አያስቸግርም።  አዎ!  የዚህ ድርድር ሂደትና ተገኘ የተባለው ውጤት ሁለቱም አንጃዎች (ኦህዴድ/ብልፅግና እና ህወሃት) እጅግ ግዙፍና አስከፊ  በሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቁ ከመሆናቸው አኳያ ሲገመገም ፣የሁለቱም አንጃዎች ምንነትና ማንነት  እጅግ አስከፊ በሆነ የሸፍጥ፣ የሴራ፣ የሙስና፣ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ፣ የክህደትና የጭካኔ ፖለቲካ ክፉኛ የተበከለ ከመሆኑ መሪር እውነታ አንፃር ሲታይ፣  የጦርነቱ ቀጥታ ተጎጅ (ሰለባ) የሆኑ ማህበረሰቦች ቢያንስ ስለ ድርድሩ ሂደትና  ውጤት  ወቅታዊና ተገቢ የሆነ ግንዛቤ ወይም እውቀት እንዲኖራቸው  ባለመደረጉ ከፈጠረው ያለመተማመን  ሁኔታ አኳያ ሲቃኝ ፣ የኢትዮጵያን ልዑላዊነት በመድፈር በህዝብ ላይ ጉዳት እንዲያደርስ ስለተፈቀደለት የኤርትራ (የሻእቢያ) መንግሥትን  በተመለከተ የተባለ ነገር ካለመኖሩ አንፃር ሲገመገም ፣ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪዎች እራሳቸው ከእውነተኛና ዘላቂ ህዝባዊ መፍትሄ አፈላላጊነት ይልቅ የአምባ ገነንነት ልምድን  ለማካፈል የሚመጥኑ ከመሆናቸው አስቀያሚ እውነታ አንፃር ሲታይ ፣ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ትርጉም ባለው ቁመና እና አቋም የወንጀለኛ ተደራዳሪዎችን የሃይል ሚዛን የሚገዳደር የፖለቲካ ሃይል ጨርሶ ካለመኖሩ  መሪር የፖለቲካ እውነታ አንፃር ገሲገመገም ገንቢነትና ዘላቂነት ያለው የፖለቲካ መፍትሄ ይፈጠራል ብሎ ለማመን በእጅጉ አስቸጋሪ ነው። እናም ትልቁ ችግር ያለው በዚህ ሁሉ ግዙፍና ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ሰላም ሆነ በሚል የድል ነጋሪት በመጎሰም ከተደጋጋሚ ውድቀት ያለመማር እጅግ አስቀያሚና አስፈሪ የፖለቲካ አባዜ ከመሆኑ ላይ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በእጅጉ የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ ስለ ድርድሩ ምንነትና እንዴትነት ትንሽ ጌዜና ትዕግሥት ወስደው ሳያዩና ሳይገነዘቡ “የሁላችንም የድል ህልም እውን ሆነ” የሚል አይነት የደስታ መግለጫ ያስነበቡንና ያስደመጡን የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው የመሆናቸው ጉዳይ ነው። እያልኩ ያለሁት መግለጫ ማውጣታቸው ትክክል አይደለም የሚል አይደለም ። እያልኩ ያለሁት ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና መሰሎቻቸው የሚደሰኩሩልንንና የሚያስነብቡንን ለግልብ ስሜት የሚስማማ (የሚመች) ዲስኩርና ድርሰት ጊዜና ትግሥት ወስደን ለመረዳት ሳንሞክር የምናቀርበው ውዳሴ ምን ያህል የመከራና የውርደት ዘመንን እንደራዘመብንና እያራዘመብን እንደሆነ ተገንዝበን ተገቢውን እርምት እናድርግ ነው። ይህን አድርጎ ለመገኘት  በተለይ ለሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች የሚከብዳቸው ከሆነ በእውነትም ሥር የሰደደና አደገኛ ችግር አለብን ማለት ነው።

ብልፅግና ፣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ መግባባት፣ መቻቻል፣ መብት፣ እኩልነት፣ ፍቅር እና መሰል እጅግ ጥልቅና ሰፊ ትርጉም ያላቸውን ፅንሰ ሃሳቦች ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ለርካሽ የፖለቲካ ቁማራቸው በሽፋንነት እየተጠቀሙ ሲያረክሷቸው ጊዜና ትእግሥት ወስደንና ከግልብ ስሜት ወጥተን ገንቢነትና ዘላቂነት ለሚኖረው አስተሳሰብና አካሄድ ይበጃል የምንለውን ሂሳዊ አስተያየትና ምክረ ሃሳብ ለመሰንዘር ካልቻልን  የችግሩ እንጅ የትክክለኛው መፍትሄ አካላት ልንሆን ፈፅሞ አይቻለንም።

እናም ልብ ያለው ልብ ይበል! ልብ የሌለው ልብ ይግዛ!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share