September 6, 2022
69 mins read

  የሰው ልጅና ያካሄዳቸው ጦርነቶች –  አገሬ አዲስ

Ethiopian Warriors on their way to the Northern Front scaled   የሰው ልጅ  ባለፈባቸው ታሪኮቹ በልዩ ልዩ መስኮች ተሰልፎ፣በጦርነት ሜዳም ውሎ ለመብቱና ለመረጠው ኑሮ ባለቤት ለመሆን ችሏል።ጦርነት የግዴታ እርስ በርሱ ተናንቆ ደም እያፈሰሱ አንዱ ሌላውን ለማንበርከክ የሚያስችል ግብግብ ብቻ አይደለም።የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳትና አራዊት አእዋፍም ሳይቀሩ ነፍስ ያላቸው ፍጡሮች በሙሉ ለመኖር ከተፈጥሮ ጋር ሳይቀር ትግልና ጦርነት ያደርጋሉ። ከሁሉም በላይ የሰው ልጅ በሚኖርበት ዘመኑ ለመኖር ሲል ብዙ ትግሎችን ወይም ጦርነቶችን አካሂዷል።ስለሆነም ጦርነት የአንዱ የመኖር ትግል ነው ቢባልና የሰው ልጅም ለመኖር ሲል በትግል(በጦርነት) ውስጥ መኖርና ማለፍ ያለበት የህይወት ግዳጁ ነው ለማለት ይቻላል።ከተፈጥሮ ጉዳት ለመውጣት ሲል ግብግብ ይገጥማል።ከጎርፍና ከቃጠሎ ፣ከድርቅና ከበረዶ ያንንም ተከትሎ ከሚከሰት እርሃብና በሽታ አደጋዎች ለመትረፍ ይታገላል።እነዚህና የመሳሰሉት ሁሉ ህይወቱን ለማትረፍ የሚያደርጋቸው ትግሎች ወይም ጦርነቶች ናቸው።አንዱን ትግል (ጦርነት )ሲጨርስ ትግሉ (ጦርነቱ)አበቃለት ማለት አይደለም።በሚኖርባት  በጉዞ ወይም በእንቅስቃሴና ለውጥ ውስጥ በምትኖረው ዓለም በሚከሰት አዲስ ክስተት ይዞት የሚመጣውን ለውጥ ተከትሎ ያንን ለመጋፈጥና ጉዳቱን ለመቀነስ ወይም  ለማስተካከል የእውቀትና ተመክሮ  ደረጃው በሚፈቅድለት መጠን ትግል(ጦርነት )ያደርጋል እንጂ እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም።በዬጊዜው ሌላ ክስተቶች ስለሚፈጠሩ እነዚያንም እንዳመጣጣቸው ለመፋለምና ለማሸነፍ ትግል(ጦርነት )ያደርጋል።ምንም ጊዜ ቢሆን ከኑሮ ትግል (ጦርነት)ተላቆ አያውቅም።ለዚያም ነው የሰው ልጅ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው የሚባለው።

ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገውን ትግል (ጦርነት) በጥቂቱም ቢሆን ከተረዳን እዚህ ላይ አቁመን አሁን ባለንበት ዘመን ትልቁና በጣም አውዳሚ ወደ ሆነው  የእርስ በርስ ትግል(ጦርነት)ፊታችንን አዙረን መመርመሩ አስፈላጊ ይሆናል።ከተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው ትግል(ጦርነት)ህይወቱን ለማትረፍ ሲሆን በእርስ በርስ ትግል (ጦርነት )ግን አንዱ ሌላውን ገሎና አንበርክኮ ፣አንዱ በሌላው ኪሳራ ላይ የማትረፍና የመኖር ፍላጎትና እራስ ወዳድነት የሚያመጣው ትግል(ጦርነት)ሆኖ እናገኘዋለን። ታሪክ ከመዘገባቸው ጦርነቶች መካከል የሰው ልጅ የከባቢ ኑሮ በጀመረበትና ፍላጎቱ በጨመረበት ጊዜ ያንን ፍላጎቱን ለማሟላት ከሚኖርበት አካባቢ ወጥቶ የመሄድና በሃይልም ሆነ በመግባባት (በሰላም) የሚሻውን ለማግኘት ያስቻለውን ሰላማዊ ወይም በጦርነት የታገዘ ፍልሰት(ወረራ) መኖሩን ለማወቅ ችለናል።ጎልቶ የሚታወቀው በፈረኦናውያን፣  በጥንታዊ ሮማውያን፣ በፋርስ፣ በቻይናዎች፣ በአክሱማውያን ከዚያም በቱርክ ኦቶማን ሃያላን አገዛዞች የተደረገው የጥቅም ጦርነት ያስከተለው የሕዝብ መስተጋብርና መስፋፋት ለ15ኛው ክፍለ ዘመን የወረራና የቅኝ አገዛዝ ስርዓት እርሾ ሆኗል ብንል ስህተት አይሆንም።በዚያ የመስፋፋት ሂደት የሰው ልጅ በተፈጥሮው ጉዳትና መከራን ያለመቀበል ስሜት፣እልህና እምቢ ባይነት ስላለው አንዱ ለሌላው ገብሮ ለማደር ህሊናው አይፈቅድለትምና የመጣበትን ወራሪ ለመከላከል የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ተገዷል። በጦር ሜዳ ላይ ውሏል።

የጦርነት ሃሳብ ሲነሳ ለማሸነፍ የሚያበቃ ሃይልና ዝግጅት ማድረጉ ከግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የወታደራዊ ተቋም የመገንባቱና የመሣሪያ ፈጠራው ህሳቤ አብሮ ተወለደ።እንደዘመኑ የጦር መሣሪያ ለመስራት ፉክክሩ ጀመረ።ብዙ ወታደርና መሣሪያ ያለው ለድል አድራጊነት እንደሚበቃ በጦር ሜዳዎች ተረጋገጠ።ሁሉም ለዚያ ቦታ እሽቅድድሞሽ ውስጥ ገባ።

ዘለአለማዊ ሃይለኛነትና ዘለዓለማዊ ደካማነት የለምና፣ዘለዓለማዊ ባለጸጋነትና ዘለዓለማዊ ድህነትም አይኖርምና ሁሉም ተራውን ጠብቆ ይወድቃል ይነሳል፣እነዚያም ዓለምን ለመቆጣጠር የቻሉት ሃያላን መንግሥታት ተንኮታኩተው ለተተኪው ጊዜ ላነሳው ሃይል አስረክበው አለፉ።

አገራችን ኢትዮጵያ ባሳለፈችው የረጅም ጊዜ ታሪኳ በመነሳትና በመውደቅ፣በጦርነትና በሰላም ጎዳና ተጉዛለች።በዬጊዜው የተነሱ መሪዎች ለሥልጣን የሚያበቃቸውን ዘዴና ወታደራዊ ተቋም ለመመስረት ችለዋል።ከውጭ የመጣን ወራሪ ለመመለስ በሕዝቡ አልበገሬነትና ጊዜው በፈቀደላቸው መሣሪያ  ተፋልመው መልሰዋል።

ከውጭ ጠላት ጋር ከሚያደርጉት ግብግብና ጦርነት ይበልጥ ጊዜና ሃይላቸውን የበላባቸው በእርስ በርስ ውጊያ ላይ መሰለፋቸው ነበር።የአገሪቱንም ሃብት ያባከነውና ለእድገት ያላበቃው ይኸው የእርስ በርስ ጦርነትና የሥልጣን ሽኩቻ ነበር።በዚያ ጊዜ ምንም እንኳን ዘመናዊ የመከላከያ ተቋም ባይኖርም የከባቢ ገዥዎች በግዛታቸው የሚኖረውን  ሕዝብ በውድም በግድም ለሚያካሂዱት ዘመቻ እንዲሰለፍ ያደርጉት ነበር።በአገዛዛቸው ዙሪያ የተሰለፉትን ባለሙያዎችና ግብር በሌዎች የጦር መሪ በማድረግ በስራቸው ያለውን ጭሰኛ ያደረጉትን ሰፊውን ሕዝብ ፥ግዛቴን ለመቀማት የሚፈታተነኝ ጠላት መጥቶብኝ ለጦርነት ተነስቻለሁና ተከተለኝ የሚል አዋጅ በማስነገር ሁሉም ለጦርነት እንዲሰለፍ ያደርጉ ነበር።በዚህ አይነቱ የእርስ በርስ ጦርነት የአንድ አገር ዜጋ ጎራ ለይቶ ደም እንዲፋሰስ ሆኗል።ያም ለዘመነ መሳፍንት ለሚባለው ስርዓት አሳልፎ አንዱ የገነባውን ሌላው ተረኛና ጊዜ ያነሳው እያፈረሰ አገርና ሕዝብ የዃሊት እንዲጓዙ ምክንያት ሆኗል።

በእያንዳንዱ ዘመን ያልነበረና ያልተለመደ፣ሁኔታና መሪ መፈጠሩ አይቀርምና በኢትዮጵያም ውስጥ የታሪክ  ጉዞ ተከትሎ በመጣ የባለሥልጣናት ሹም ሽር፣ከባላባታዊው የመሳፍንት ስርዓት ውስጥ የአጼ ቴዎድሮስ መነሳት እርስ በርሱ እዬተዋጋ አገሪቱን በደም ያጨማለቃትን ይህንኑ ሥርዓት ለመቀዬርና በአንድ ንጉሳዊ አስተዳደር ስር ለማድረግ ቀድሞ ከነበሩት መሪዎች ሁሉ በተሻለ አገራዊ አመለካከት ያለው ወታደራዊ ቁመና በመገንባት የያዙትን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ ሞከሩ።በዬከባቢው ያሉትን  መሳፍንቶች እሺ ያለውን በሰላም እምቢ ያለውን በሃይል እያሳመኑ በሥራቸው ለማድረግ ቻሉ። አንዳንዶቹም እምቢና እሽ በማለትሁለት ጠርዝ ላይ በመቆም አልፎ ተርፎም ከባዕዳን ጋር በመመሳጠር ጉዟቸውን ለማደናቀፍ ሞከሩ።አጼ ቴዎድሮስ እቅዳቸውን ለመተግበር የግድ ቋሚ ወታደር መኖሩን ስላመኑበት ከሳቸው በፊት በግድና በውድ ከዬቦታው በአዋጅ ይሰበሰብ የነበረውን ያልተደራጀ ዘማች የሚተካ በጭሰኝነት ሳይሆን በደመወዝ የሚተዳደር ወታደር ለመጀመሪያ ጊዜ አቋቋሙ።በዚህም በደሃው ሕዝብ ላይ የነበረውን ዘማች የማብላትና የመሸከም ግዳጁን ለጊዜውም ቢሆን አቃለሉለት።ለጭሰኛው ሌላ የመተዳደሪያ ሙያ ከፈቱለት።ሆኖም ግን ለለውጥ እንግዳ የሆነው ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ስላልተቀበላቸው የጀመሩት እቅድና አገራቸውን ከፍ የማድረግ ዓላማ በእንግሊዞችና በአገር ውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸው ጥምር ሴራ ሊጨናገፍና እሳቸውም በጦር ሜዳ እራሳቸውን ለመግደል ተገደዱ።

የአጼ ቴዎድሮስ ህልምና ራዕይ ለቀጣዮቹ መሪዎች የእውቀት ፋና ወጊ ሆነላቸው።የዬራሳቸውን ወታደራዊ ተቋም እንዲገነቡ መንገድና አቅጣቻውን አመላከታቸው።ሆኖም ግን ከቀድሞው የጦርነት አሰላለፍና የሃይል ግንባታ ሙሉ ለሙሉ የተላቀቁ አልነበሩም።የዘረጉት ስርዓት ባላባታዊና ጭሰኛነት ግንኙነትን የተከተለ ስለሆነ ለዘመቻ ሲነሱም በዚያው መልክ በባላባቶች  የጦር አዛዥነት የሚመራና በጭሰኞች ተሳትፎ የተገነባ ነበር።ጦርነትና ግጭት ሲነሳ ሁሉም ከያለበት ተጠራርቶ የሚሰበሰብ የተለዬ ወታደራዊ ልብስ የሌለው፣ሸማ ለባሽ በመሆኑ ነጭ ለባሽ በሚል ስም የሚታወቅ የሕዝብ ሠራዊት ነበር።ይኸው የነጭ ለባሽ ሕዝባዊ ሰራዊት እስከ መጨረሻው ንጉስ ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ማለትም የባላባትና የጭሰኛ ግንኙነት እስከተቋረጠበት 1967 ዓመት ድረስ ሊቀጥል ችሏል።

ጦርነት ጎጂና አውዳሚ በመሆኑ የሚመርጡት ባይሆንም፣ተገደው የሚገቡበት የመጨረሻው አማራጭ ነው።የጦርነት የመጨረሻ ግቡ ጦርነትን ለማጥፋት ፤በጉልበት ሊወርና ሊገዛን ወይም ሊበታትን የመጣ ወይም የተነሳን  ሃይል በማሶገድ ሰላም፣ ብሔራዊ  ነጻነትንና አንድነትን፣የሕዝብን የተረጋጋና ስጋተቢስ ኑሮ  ለማስፈን፣ የሰው ልጆች ህይወት ከስቃይና ከስጋት ለመገላገል ህይወትን ለመገበር የሚወስዱት የመጨረሻ  እርምጃ ነው።ሕግ ያላስከበረውን መብት ሃይል ያስከብረዋልና!

የሰው ልጅ  ሊያጠቁት ከመጡ አውሬዎች ጭምር ጋር ተፋልሟል።ከራሱም መሰል ሰዎች ጋር ሳይቀር እንዲሁ ተናንቋል።በዚህ የሞት የሽረት ትግል ውስጥ ጠላቱን ሊያሸንፍበት የሚችልበትን ብልሃትና ዘዴ በማስላት መሳሪያ ከመፈልሰፍና ከመጠቀም ደረጃ ላይ ደርሷል።ተፈጥሮ ከቸረው ድንጋይ ጀምሮ እንደጊዜው የዕድገት ደረጃው እንጨት ጠርቦና ስሎ ጦር፣ደጋንና ቀስት፣የብረት ማዕድንን አቅልጦ ለጦሩ ጫፍ፣ጎራዴ፣ሳንጃ፣ለመከላከልም ከጋሻ ተነስቶ  ብረት ለበስ ተንቀሳቃሽ ካለበት የመከላከያ አቅም ላይ ለመድረስ ችሏል።የውጊያ መሣሪያውን ብቻ ሳይሆን ስልቱንም አሻሽሏል።ዘመን በመቀዬሩ የሰው ልጆች እንደ ቁጥሩ የግለኝነትና የስግብግብ መንፈስ ይበልጥ በረከተ እንጂ እዬተቀነሰ አልመጣም።መሣሪያዎቹም እንደዚያው ከጊዜው ጋር በመጠንም በጥራትም እዬተለዋወጡ መጥተዋል።

በታሪክ የታወቁ  ሁለት የዓለም ጦርነቶች ተካሂደዋል።መነሻቸው የጥቅም ምክንያት ነበር።በነዚህ ሁለት ጦርነቶች አንደኛው ከሌላው ማለትም የhl,ተኛው ከአንደኛው ጊዜ በተሻለ አደረጃጀትና መሣሪያ ብልጫ ነበረው።ያደረሰውም ውድመት እንደዚያው የባሰና የከፋ ነበር።ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ያለቀባቸው እነዚህ ጦርነቶች ግን የሰውን ልጅ ከጦርነት አውድ እንዲርቅ አላደረጉትም።ይባስ ብሎ ዓለምን ጨርሶ ሊያጠፋ በሚችል ደረጃ የጦር መሣሪያና ዝግጅት ይበልጥ እዬተጠናከረ መጣ። ከላይ እንደተጠቀሰው የጦርነት መነሻው ስግብግብነትና እራስ ወዳድነት ስለሆነ በጥቅም ደረጃ በተሰለፉ ጎራዎች የሚካሄደው ግብግብ ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጠለ።ከሁለቱም ዓለም ጦርነቶች ወዲህ እስከአሁን ድረስ ለሚካሄዱት ጦርነቶች ምክንያቱ  እራስ ወዳድነት ያመጣው ልክፍት ነው።

ዓለም ካላት ገና ያልተነካ ሃብቷ አንጻር የሰው ልጅ በሰላም እዬተረዳዳ፣አንዱ ያለውን እዬሰጠ፣የሌለውን እዬተቀበለ ተሳስቦ ለመኖር ቢሻ ኖሮ ለጦርነት የሚያወጣውን ሃብትና ጊዜ ለተሻለ የሰው ልጆች ኑሮ ለማዋል በቻለ ነበር።ዓለምን የግል ይዞታቸው ለማድረግ በሚሹ ሃብትና ሥልጣን በቃን በማይሉ ጅቦች ምክንያት ዓለም የጦርነት መስክ ሆና ቀጥላለች።

ህብረተሰብ በመንግሥታዊ ሥርዓት ተደራጅቶ፣በአገር ደረጃ መኖር ከጀመረ ወዲህ የእኔ ነው የሚለውን ከባቢ ከሌላው ወራሪ ሃይል ለመከላከል የቋሚ ወይም የመደበኛ ጦር ሃይል የማቋቋሙ አስፈላጊነት ትኩረት ተሰጥቶት እንደ አንድ ዋና ተቋም ሆኖ ለመታዬት በቅቷል።የጦር ሃይል የሌለው አገር ብቻም ሳይሆን በቅጡ ያልተደራጀና የተዝረከረከ ጦር ሃይልም ያለው አገር ለውጭ ወራሪዎችና ጥቃት የተጋለጠ መሆኑ ስለማይቀርለት ተቋሙን ለማሳደግና ለማጠናከር አገራት ብዙ ወጭ በማፍሰስ ከዘመኑ ጋር የሚመጥን አስተማማኝ የጦር ሃይል ለማቋቋም ተገደዋል።የአፍሪካ አገራትም ሕዝባቸው ጠግቦ ሳይበላ በልዩ ልዩ ዘርፍ በመሬት(በዬብስ)፣ በአዬርና በባሕር፣ጠላትን ሊቋቋም ብሎም ሊያጠቃ የሚችል አገራዊ የመከላከያ ተቋም የተፈጥሮ ሃብታቸውን እያሲያዙ በግዥና በብድር የጦር ሃይል ለመገንባት ተገደዋል።የዬአገራቱ ከፍተኛ ወጭ የሚውለው በዚሁ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ግንባታና የተመረተውን በመግዛት ላይ ነው።በብዙ  ድህነትና ምስቅልቅል ኑሮ ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ያላቸው አገሮችም ሳይቀሩ በዚሁ የመሳሪያ ገበያ ውስጥ ገብተው ሲዳክሩና ሃብታቸውን ሲያፈሱ ይታያሉ።የአገራቸውን የተፈጥሮ ማዕድንና ሃብት ለመሣሪያ ግዥ ክፍያ በማዋላቸው ሕዝባቸው የእህል ለማኝና ስደተኛ እንዲሆን አድርገውታል።ጦርነት ባይኖርባቸውም ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ሴራ ይጎነጎንባቸዋል።ከጎረቤት ወይም በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንዲማገዱ የመሣሪያ ሻጭ አገሮችና ነጋዴዎች ዘዴ ይፈeራሉ።መሳሪያ አምራች አገሮችም ይህ ሁኔታ ከተለወጠና ሕዝቡ ሰላም ካገኘ ፣ከጦርነት አሮንቃ ከወጣ ምርታቸውን ገዥ ስለሚያጡ ሁል ጊዜም በጦርነት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋሉ።እምቢ ያላቸውን እያሶገዱ ለነሱ የተመቸና ባርያ የሆነ መሪና መንግሥት እንዲኖር ያደርጋሉ።የውጭና የውስጥ ጠላቶች እንዲነሱባቸውና በነሱ የጦር መሳሪያ ገበያ ውስጥ እንዲርመጠመጡ ያደርጓቸዋል። ለምግብ፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለመገናኛ(መጓጓዣ)ለመሳሰሉት ሰላማዊና አስፈላጊ ነገሮች መሟላት ከሚደረገው ጥረት ይልቅ የጦር መሳሪያው ሸመታ ዙሪያ በሚነሳው የጥቅም ግብግብ አገራት እንዲጠመዱ ሆነዋል።አላፊነት የጎደላቸው ሆዳም መሪዎችም በዚሁ የጦር መሳሪያ ሸመታው የሚያገኙት ጥቅም ስላወራቸው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የሚጨነቁ አልሆኑም።ከፍተኛ ጥቅም ከሚያገኙበት ጋር እዬተጠጉ የአገርና የሕዝባቸውን  ጥቅም በመጻረር ለባርነትና፣ለጥገኝነት አሳልፈው ይሰጡታል፤ለማያቋርጥ ቀውስና ጦርነት ያጋልጡታል።ከረጅም ጊዜ አንስቶ ባላደጉ አገራት ኢትዮጵያንም ጨምሮ የሚታዬው የሰላም እጦት፣ የውጭና የውስጥ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ከዚሁ የከበርቴ አገሮች የጥቅም ግጭት ጋር የተያያዘ መሆኑን ማንም አይክደውም።

ዓለም በብዙ ቀውስ፣በተፈጥሮ አደጋ፣በጎርፍ፣በቃጠሎ፣በመሬት መደርመስ—ወዘተ ለመጠቃት የበቃችው በአብዛኛው በሰው ሰራሽ በዋናነት በጦር መሳሪያ ምርት የፋብሪካ ብክለት በተፈጥሮ ላይ በሚያስከትለው መዛባት ምክንያት የመጣ ለመሆኑ የተፈጥሮ ምሁራን በማስረጃ አቅርበዋል። አሁንም በነዚህ አደጋዎች በምትዳክርበት ጊዜ ቢሆን የፋብሪካ በካይ ውጤቶችን ከመጨመርና የጦር መሣሪያውን የማሻሻል ጥረቱን ከማሳደግ በቀር ውድድሩ መቆም ቀርቶ ገብ አላለም። በመሆኑም አዳዲስ መሣሪያዎችና ስልቶችን በመፍጠር  የሚወዳደሩበት መስክ ሆኗል።የተለወጠ ነገር ቢኖር ከባድ መሳሪያና ብዙ ወታደር ከማሰለፍ ይልቅ በርቀት የሚወነጨፍ ሚሳይል፣በአብራሪ ከሚዘወር አይሮፕላን በኮምፒውተር ትእዛዝና ፕሮግራም ያሰቡትን ምሽግ የሚያፈራርስ፣ ኢላማ የሚመታ ድሮን፣በጨረር የሚያወድሙበት ደረጃ ላይ ከመድረስም አልፎ ዘመኑ የኮምፒውተር  በመሆኑና ሁሉም ነገር ከኮምፒውተር ቴክኒዎሎጂ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ፣የመከላከያ ግንኙነትና የእዝ ሰንሰለት የተሳሰረበትን በመበጣጠስ፣የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚቆጣጠርና የሚያኮላሽ የሳይበር ቴክኒዎሎጂን በማሳደግ  አገራትን ለማበርከክ ከሚቻልበት የጦርነት አውድ ላይ ተደርሷል።

የዓለም ሕዝብ  የጦርነትን አውዳሚነትና ጉዳቱን ተገንዝቦ፣ሁሉም እንደእምነቱ ተከባብሮ የሚኖርበትን ሁኔታ ካልፈጠረ፣ የተያዘው የጦር መሳሪያ ውድድርና የአገራትን የበላይነት እብሪታዊ መንገድ ካላሶገደ የሚገጥመው አደጋ ካለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች ይበልጥ የከፋ ይሆናል።የሰው ልጅ በሰላም ኑሮ ማለፍን እንጂ በጦርነት ሳቢያ ተጨፋጭፎ ማለቅን አይመርጥም።ለዚህ መፍትሔው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ነው።ጦርነት ጦርነትን ያጠፋል ቢባልም ጦርነት እንዳይመጣ ማድረግ ግን ቀላሉና እርካሹ መንገድ ነው።የያገራቱ ሕዝብ በስሙ የሚነግዱትንና ለጥቅማቸው ሲሉ ጦርነት የሚቀሰቅሱትን ሥልጣን ይዘው በመንግሥት ስም የሚንቀሳቀሱትን ወራሪዎችና እራስ ወዳዶች ከትከሻው ላይ አውርዶ ቢጥላቸው በሚኖራት አጭር ዕድሜው የሰላምና የደስታ ጌታ በሆነ ነበር።

አገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ረጅም የታሪክ ጉዞ ስንመረምረው፣ከላይ እንደተገለጸው ታሪኳ የጦርነት ታሪክ ነው።አገራዊ መልክ ይዛ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በውስጥና በውጭ ሃይሎች የተነሳ  እልህ አስጨራሽ ጦርነቶች ተደርገዋል።አሁን ላለችበት ደረጃ የዳረጋትም በዬወቅቱ በተካሄዱት ጦርነቶች ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። ከውጭ የመጡ ወራሪዎችን ለመከላከል ከተደረገው ጦርነት ይልቅ በእርስ በርስ በተካሄደው ውጊያ የወደመው ንብረትና የጠፋው የሰውና የእንስሳት ህይወት ለቁጥር ያዳግታል።በዘመነ መሳፍንት ጊዜ እንኳን የነበረውን ብናነሳ አንዱ የሌላውን ከባቢ በመውረርና የበላይ ሆኖ ለመግዛት ባደረገው ጦርነት ዙፋኑን ለመንጠቅ ብቻ ሳይሆን በግዛቱ ውስጥ የሚኖረውን ሕዝብ በመጨፍጨፍ፣የተገነቡም ካሉ በመዝረፍና በማውደም አቅም ማሳጣት ነበር።

በዚያን ጊዜ የነበረው መከላከያ እንደ አሁኑ ዘመን  በአገር አቀፍ፣በቋሚ ደረጃ በቅጡ የተደራጀ ባለመሆኑና ክተት ሲባል ከያቅጣጫው በውድም ሆነ በግድ ተሰባስቦ የራሱን፣ ስንቅ፣ የጦርመሳሪያ ማለትም፣ጎራዴ፣ሰይፍና ጋሻ፣የሌለውም ማጭድና ዱላ ሳይቀር ያነገበ ነበር።በንጉሱ ዙሪያ የነበሩ ባለሟሎችና የጦር ሹማምንት የሚመሩትም ነጭ ለባሽ ወይም ጭሰኛ የሚሳተፍበት ጦር ሜዳም ላይ  ዘራፍ እኔ የገሌ አሽከር! እያለ በፉከራ ታማኝነቱንና ወኔውን የሚገልጽ ተዋጊ ነበር።

ከዚያም በተረፈ በራሱ ፍላጎት የሚንቀሳቀስ ለመብቱና ለአገሩ ነጻነት  በሕዝባዊ እምቢተኝነት የሚዘምት ፋኖ ወይም አርበኛ በሚል ስያሜ የሚታወቅ ሕዝባዊ ጦር አንዱ ነው።የታሪክን ጉዞ ተከትሎ እያንዳንዱ አሰላለፍ ቅርጽና ይዘቱን እዬለወጠ ለመሄድ ችሏል።

የአገር መከላከያ ቋሚ ሠራዊት

ይህ የጦር አደረጃጀት መንግሥታዊ ስርዓት በሰፈነበት አገር የሚፈጠርና የሚደራጅ፣ለትጥቅና ለስንቁ መንግሥት ባጀት መድቦለት በቅደም ተከተል የሹመት ሰንሰለት የሚመራና  የሚንቀሳቀስ የጦር ሃይል ወይም ተቋም ነው።በዚህ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ የሚሰማራው ምልመላውን ተከትሎ መስፈርቶችን አልፎ የሰለጠነ፣ በሙያው የተካነ አባል ነው።ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ በመሆኑ አገራዊ አደጋና ጥቃት ለመከላከል ብሎም ጦርነትን ለማሸነፍ አስተማማኝ ብቃት ያለው፣የማይገረሰስ ብሔራዊ  አጥር ወይም ግምብ ነው።ይህ ብሔራዊ የመከላከያ ተቋም በመሬት፣በአዬርና በባሕር ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማክሸፍ እንደ አገሩ አቀማመጥና የተፈጥሮ ገጽታ ሊደራጅ ይችላል።በመልክዓምድር አቀማመጥ  በበረሃማ፣በአሸዋማ፣በበሮዳማ፣በሜዳ፣በተራራና ሸለቋማ፣በጫካና ወጣ ገባ ቦታዎች፣ብርድና ቃጠሎን፣ እርሃብና ጥምን፣የአውሬ ጥቃትንና በሽታን ተቋቁሞ ፣ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ አልፎ የጠላትን ግንባርና ምሽግ ለመስበር የሚያስችል አካላዊ ና ስነልቦናዊ ብቃት ያለው ተዋጊ ሃይል ሆኖ ይደራጃል።

በዘመናችን እንደምናዬው ይህ ተቋም ጠንካራነቱ የሚለካው ገዝቶ በታጠቀው የውጭ አገሮች የጦር መሣሪያ  ለመዋጋት መቻሉ ብቻ ሳይሆን እራሱ የጦር መሣሪያ አምራች የመሆኑን ችሎታና አቅም መገንባቱ ነው። ከዘመኑ ሳይንስና እውቀት ጋር የተቆራኘ ከሆነ ለዃላቀር አስተሳሰቦች የተመቼ አይሆንም።ከአገሩ አልፎ ዓለም አቀፋዊ እይታ ላይ ሆኖ ለሌሎቹም አገራት ይተርፋል።እራሱ የሚዋጋበትን መሣሪያ ፈጣሪና አምራች መሆኑ ለአገራዊ ኤኮኖሚያዊ ግብአት ከሚሰጠው አበርክቶ በላይ በራስ የመተማመን ስነልቦና ያላብሳል።ጠላትን በማያውቀው መሣሪያና ጥበብ ለማጥቃትና ድል ለማድረግ ይረዳል።የዚህ አይነቱ የፍልስፍናና የፈጠራ ችሎታ  በጦርነት ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በሰላም ጊዜም ለአገርና ለሕዝቡ ኑሮና እድገት በሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የድርሻውን ያበረክታል።የማውደም ብቻ ሳይሆን የግንባታም ሠራዊት ይሆናል።

ሕዝባዊ ጦር ፣ነጭ ለባሽ፣አርበኛ ወይም ፋኖ

አገር በውጭ ወራሪዎች በተወረረችበት ወቅት ወይም የአገርን አንድነትና ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል የውስጥ ሃይል በተነሳ ጊዜ ፣ እንዲሁም አንዱ በሌላው ጉልበተኛ በእምነቱ፣በማንነቱ፣ በቋንቋው ተለይቶ ሲጠቃና ከሚኖርበት ቦታ ሲፈናቀል ፍትህና ሰላምን ለማስፈን በራሱ ተነሳሽነት ተጠራርቶ ከያቅጣጫው ተሰባስቦ  የራሱን ስንቅ ቋጥሮ የራሱን መሣሪያ ታጥቆ የሚዘምት አገር ወዳድ ዘማች ነው።እምነት፣ጎሳና የፖለቲካ መስመር የማይለዬው በአገር ፍቅር ስሜት የተሰበሰበ፣ለሰዎች ክብርና መብት የሚቆም የክፉ ቀን መከታ የሆነ ከሕዝብ አብራክ ወጥቶ ለሕዝቡ ጥቅም የሚቆም ዜጋ ነው።ከቋሚው ሠራዊት የሚለዬው ሙያተኛ ሆኖ ደመወዝ የሚቆረጥለት አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የወጣበትን ዓላማ ካጠናቀቀ በዃላ ወደ ነበረበት ተግባሩ፣ገበሬም ወደ እርሻው፣ነጋዴም ወደ ንግዱ፣ቄሱም ወደ መቅደሱ፣…ወዘተ የሚመለስ መሆኑ ነው።

ሕዝባዊ ጦር እንደ አገሩ ባሕልና ወግ፣እንደሕዝቡ ንቃትና የዕድገት ደረጃ የራሱን አመራር መርጦ የሚከተል፣መለያ ምልክትና ስምም ሊይዝ ይችላል።በአገራችን ከታወቁት ስያሜዎች መካከል አርበኛና ፋኖ የሚሉት ስያሜዎች ዋናዎቹ ናቸው።ሕዝባዊ ጦር፣አርበኛ ወይም ፋኖ የጋራ አገራዊ ዓላማ ያነገበ እንጂ በአንድ የፖለቲካ መስመርና ርዩተዓለም የሚመራ፣በአንድ የእምነት ጎራ፣ወይም ለአንድ የማህበረሰብ ክፍል ጥቅምና ፍላጎት ብቻ ላይ የሚያተኩር ጦረኛ አይደለም።

በአንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚመራና የሚታዘዝ ወይም የዚያ አካል ከሆነ ሕዝባዊ ጦርነቱ ያበቃና የፖለቲካው ድርጅት ወታደራዊ ክንፍ ይሆናል።የሚከተለው ወታደራዊ ስትራቴጂ ወይም ግብ የፖለቲካ ክንፉ በሚነድፈው ዕቅድ ረገድ የመጨረሻ ግቡም ለሆነው የሥልጣን እርከን መወጣጫ ሃይል ወይም ተሸካሚ ካሮሳ  ይሆናል ማለት ነው።ይህ ደግሞ ከሚመራው የፖለቲካ ድርጅት ህሳቤ ውጭ ያለውን የሚሰበስብ ሳይሆን በተቃራኝነት ፈርጆ ለማጥቃት፣ለእርስ በርስ ክፍፍሎሽና ፍጅትም የሚዳርግ ሊሆን ይችላል፤በታሪክም ተደጋግሞ ታይቷል።

ሕዝባዊ ጦር  ወይም ፋኖ በዓላማ ከሚመሳሰለው፣የፖለቲካ ድርጅት ወይም ፓርቲ ጋር ጨርሶ ግንኙነት አያድርግ ማለትም አይደለም፣የራሱን ነጻነትና አደረጃጀት ጠብቆ ለጋራ ጥያቄና ግብ አብሮ የመሥራት ግንኙነት መፍጠሩ ለሚያደርገው ትግል መሳካት ጉልበት ይሆነዋል።በጋራ አገራዊ ጥያቄ ላይ በሚያመሳስላቸው አቋም ሊተባበሩ ይችላሉ።ይህ ሲባል ግን በአንድ ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው ፣አንዱ በሌላው ውስጥ ይኖራል ማለት አይደለም።የጋራ ግንባር አባላት በመሆን ይንቀሳቀሳሉ ለማለት ነው።

ተናቦ በመሥራት ሃይልና ጊዜያቸው በከንቱ እንዳይባክን፣ በመመካከር ከስህተትም ለመዳን  ይረዳቸዋል፣አንዱ ለሌላው ያለውን ተመክሮ፣ መረጃም ሆነ ቁስ በመቀባበል፣የትግላቸውን አቅም ሊያጎለብቱ ይችላሉ።ግንኙነታቸው በቅጡ የተብራራ(defined) መሆን ይኖርበታል።የሚኖራቸው ድርሻና እስከዬት ድረስ አብረው ሊጓዙ እንደሚችሉ በግልጽ ሊቀመጥ ይገባዋል።የጠላቴ ጠላት በሚለው ህሳቤ ብቻ ማዬትና መቅረብ ላልጠበቁትና ላላሰቡት የእርስ በርስ ግጭት ይዳርጋል።

አብዛኛውን ጊዜ ተደጋግሞ እንደታዬው የፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝባዊ ጦሩን በአጋርነት ይጠጉና በደካማ ጎኑ ገብተው ውስጡን በመሸርሸር የራሳቸው ታዛዥና ሥልጣን ላይ የሚወጡበት ሰረገላ ያደርጉታል።የዚህ አይነቱ ሁኔታ ከተከሰተ በአንድ ዓላማ በተሰለፉ ፋኖዎች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ይነሳና ሃይላቸው ይዳከማል። በዋናነት የሚጠቀመው የጋራ ጠላታቸው ይሆናል። በፖለቲካ ድርጅቱ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ቢባል እንኳን ለአምባገነንነት ስርዓት በር የሚከፍት ይሆናል።

አሁን በአገራችን በኢትዮጵያ በሚካሄደው የመብት ማስከበር ትግል ላይ የተሰለፉትን ቡድኖች በተለይም ሚሊሽያ፣ልዩ ሃይልና  ፋኖ የተባለውን ስብስብ በሚመለከት ግንዛቤ እንዲኖር ማድረጉ አስፈላጊ ነው።ስለሆነም ከአነሳሱና ከዓላማው ምንነት ጀምሮ አሁን ያለበትን ደረጃ ገምግሞ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ማዬቱ አስፈላጊ ነው።

ሚሊሽያ

ሌላው የሕዝባዊ ጦር አካል ሚሊሽያ የሚባለው ሲሆን ፣የዚህ ስያሜ የተጀመረው በወታደራዊ አምባገነኑ በደርግ ሥርዓት ጊዜ ነው።ይህ ጦር ከሕዝቡ የተውጣጣ መሆኑ ባይካድም በመንግሥት ጥሪና ምልመላ የሚደራጅ ተዋጊ ነው።ቋሚ ደመወዝ ባይኖረውም በመንግሥት መሬት ላይ የሠፈረና የሚያርስ በመሆኑ መንግሥት የሚጠይቀውን ተቀብሎ የመፈጸም ግዴታ አለበት።በጦር ሜዳ መዋል ካለበት ይውላል።ከራሱ መሣሪያም በተጨማሪ በመንግሥት ሊታጠቅ ይችላል።በ17ቱ የወታደር አምባገነን አገዛዝ በዬቦታው በተለይም የሰኢድ ባሬ  ሶማሊያ ድንበር ጥሳ በገባች ጊዜ፣ከዚያም በሰሜኑ የተገንጣዮች ሃይል እያደገና እዬጠነከረ ሲመጣ ለመከላከል  በገበሬ ማህበራት በኩል ተመልምሎ በለብ ለብ ሥልጠና ቢወድም ባይወድም  ለዘመቻ የተሰለፈው ይህ የገበሬ ጦር ነበር።ስሙም ከዚያ  ወዲህ የተለመደ ሆነ።ይህ ጦር ለመዋጋት የተገደደ በመሆኑ ሞራሉ ደካማ ነው።መሣሪያ ጥሎ የመኮብለልም ፍላጎት እንዳለው በተግባር ታይቷል።በውጊያ ማግኘት የሚችለውን ውጤት በመዋጋት ሳይሆን በፈጣሪው ፈቃድ የሚያገኝ ይመስለዋል።በጦርነቱ ጊዜ ታዲያ የሰለቸውና ፍርሃት ያደረበት የሚሊሽያ አባል እጁን ወደ ሰማይ ሰቅሎ ፈጣሪውን ቢማጸን ምንም ዱብ ስላላለለት እንዲህ አለ ይባላል።

አሻቅቤ ባዬው ሰማዩ ቀለለኝ፣

እሱንም ዘመቻ ወሰዱት መሰለኝ ።አለ ይባላል።ተገዶ ዘማች ሚሊሽያና ወዶ ዘማች ፋኖ ልዩነቱ ከዚህ ይጀምራል።

ነጭ ለባሽ ወይም ብሔራዊ ጦር

በዘውዳዊ ሥርዓት ጊዜ መሬቱ እንደ ደሞዝ የሚቆጠርለት በግብርና ሙያ የሚተዳር ዜጋ ነጭ ለባሽ የሚል ስያሜ የነበረው ሲሆን ባስፈለገ ጊዜ ለግዳጅ ይጠራል።በሰላምም ጊዜ የመንግሥት ተቋማትን ዘብ እዬቆመ ለአንድ ወር የመጠበቅ ግዴታ ነበረበት።ይህ የሰላም ጊዜ ገበሬ የክፉ ቀን ጊዜ ወታደር የሆነ ሕዝባዊ ጦር ከጊዜ በዃላ ብሔራዊ ጦር የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ጥቂት ከቆዬ በዃላ በመከላከያ ሥር እንደ አንድ እግረኛ ክፍለጦር ሊቆጠር ቻለ።ለዚያም ነው በየካቲቱ የወታደራዊ እንቅስቃሴ ጊዜ ለደርግ መመሥረት አንዱ አካል በመሆን  የጦር ሃይሎች፣የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ ለሚለው መጠሪያ ምክንያት ሊሆን የቻለው።

ልዩ ሃይል

ይህ ጦር በአለፉት 32 ዓመታት ወዲህ በሰፈነው የጎሰኞች ስርዓት በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት እያደገና እዬሰፋ የመጣ የክልል ጦር ሃይል ነው።ጦሩ የተቋቋመው በጎሳ እይታ ሲሆን በክሎች መካከል ልዩነትና ግጭት ቢነሳ የተቋቋበትን ክልል ለመጠበቅና ጥቅሙን ለማስከበር ሲሆን የመሪዎችም የሥልጣን መደላድል እንዲሆን ታስቦ የተደራጀ ነው።ከአገራዊ ስሜት ይልቅ ክልላዊ ስሜት የሚነዳው ጦር ነው።ይህ ጦር ቢቻል ተበትኖ በሌላ ሙያ እንዲሰማራ ቢደረግ አለያም በአገራዊ ስሜት ታንጾ  ከክልል እይታ ተላቆ በአገር መከላከያ ውስጥ እንዲጠቃለል ካልተደረገ የሚያደርሰው ውድመት ቀላል አይሆንም። በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ የተዘጋጀ የባለሥልጣናት የእጅ ቦምብ ማለት ነው።በከባቢ ጥበቃ ስም  ያሻውን የሚያደርግ፣ የኔ ነው ያላለውን ዜጋ የሚያንገላታ፣የሚዘርፍና የሚቀማ ሕጋዊ ሌባ ማለት ነው።ያንንም በተግባር እያዬነው ነው።

ፋኖ

በአሁኑ ጊዜ  ፋኖ የሚለው ቃል በቅጡ ግንዛቤ አላገኘም። በሥልጣን ላይ ባሉትና በደጋፊዎቻቸው በኩል የአማራው ጎሳ ብቻ የሆነ፣ አንድ ጠባብ ዓላማና ግብ ያለው፣ የታጠቀ አሸባሪ ወይም ዘራፊ ቡድን  እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል፣ ይቆጠራል። ያንንም ተቀብሎ የሚያስተጋባ የህብረተሰብ ክፍል አልጠፋም። ከላይ ክፍ ብለን በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት ግን  ፋኖ በነዚህ እኩይ ተግባራት ላይ የማይሰማራ መሆኑን ከሞላ ጎደል ለማብራራት ተሞክሯል።በዘረፋና ባሸባሪነት የተሰማራ ከሆነ ፋኖ ሳይሆን አሸባሪ፣ዘራፊ፣ወንበዴ የሚል መጠሪያ ይሰጠዋል እንጂ ፋኖ አይባልም።

እውነተኛው የፋኖ ትርጉም ግን  የላቀ ክብርና ዓላማ ያለው፣የብዙሃኑን ዓላማ ይዞ የተነሳ፣ ብዙሃኑን የሚያሳትፍ  የትግል አሰላለፍ ማለት ነው።አብዛኛውን ጊዜ በትጥቅ ትግል የሚንጸባረቅ ሲሆን በሌሎቹም የትግል መስኮች የሚሰለፉት ሁሉ የዚሁ የፋኖ ትግል ውስጥ የሚካተቱ የጀርባ አጥንቶች ናቸው።የትጥቅ ትግል የፖለቲካ ትግሉ ተቀጥያ እንጂ ተጻራሪ አይደለም።የፖለቲካ ችግር በሰላም መፈታት ቢችል  የሰው ልጅ ወዶ ለመሞትና ለመግደል ወደ ጦር ሜዳ አይሰማራም።በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ሲጠፋና ከገዳዮች ለመዳን ሌላ መውጫ መንገድ ሲገድ፣በሕግና በስርዓት መብቱን ማስከበር ሲያቅተው፣ ብሎም ግፈኛ ስርዓትን ከጫንቃው ለማውረድ፣ያገሩ ብሔራዊ ነጻነትና አንድነት አደጋ ውስጥ ሲገባ፣አገር በጠላት ሲወረር አማራጭ አድርጎ የሚወስደው በዱር በገደል መሣሪያ አንግቦ የሞት የሽረት ትግል ማድረግ ይሆናል።በዚያ ትግል ውስጥ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ባህል፣ሃይማኖት ፣ዕድሜና ጾታ፣ የቦታ እርቀት፣የመደብ ልዩነት ሳይነጣጥለው በአንድ የጋራ ዓላማ ሃይሉን አስተባብሮ ይሰለፋል።ይህ ነው እውነተኛው የፋኖ ትርጉም።

ላለፉት 30 ዓመታት የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ እንዲወገድ ልዩ ልዩ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል።እኔም በቅርቡ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋም ከገባንበት መቀመቅ ውስጥ እንደምንወጣ ሃሳብ አቅርቤ ነበር።ከዚያ ጎን ለጎንም የአገር ልዑላዊነት አደጋ ውስጥ ስላለ፣ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘር ዛቻ እዬጎላ በመምጣቱ ያንን ሊቋቋም የሚችል ሃይል ማዘጋጀቱ አስፈላጊ እንደሆነ ካቀረብኩት የሽግግር መንግሥት ጎን ለጎን መታዬት ያለበት መሆኑን ጠቁሜ ነበር።

“ሕግ ያላስከበረውን ሃይል ያስከብረዋል”

የሕዝባዊ ጦርና ፋኖ የመሣሪያ ትግል  አገራት ሲመሠረቱና ከተመሠረቱም በዃላ የህልውና አደጋ ሲገጥማቸው፣ በውጭ ሃይሎች ሲወረሩ፣የሕዝብ መብት ሲጣስ፣አምባ ገነኖች ሲነሱ በእምቢ ባይነት የሚሰለፉበት የትግል አይነት መሆኑ አይካድም።የሩቁን ትተን የቅርቡን ብናይ፣የአገራችን ሕዝብ  በጣልያን ወረራ ጊዜ ያደረገው ተጋድሎ፣ የቬትናም፣የደቡብ አፍሪካ፣ የዚምባብዌ፣ የፍልስጤማውያን፣ የላቲን አሜሪካ፣የእስያ ሕዝቦች ያደረጉት  የነፍጥ(የመሣሪያ)ትግል የፋኖ መርሆና አሰላለፍን የተከተለ ነው። ፋኖ ማለት በአጭሩ የነጻነት አርበኛ፣አገር ወዳድ፣የሽምቅ ተዋጊ፣ ሕዝባዊ የጦር ሃይል ማለት ነው።

ከአርባ  ዓመታት በፊት በአገራችን የተከሰተውን የፖለቲካ ውዝግብና ኢፍትሃዊነት ተከትሎ በተቀሰቀሰው የለውጥ ማዕበል የተማሪው ትግል ከፍ ወዳለው የትግል መስክ ለመግባት የሌሎቹን አገራት የግራ ዘመም  የትግል ዘዴ እንደ አማራጭ  በመውሰድና የፋኖን ድርሻና ወሳኝነት በማጤን ፣የታወቁትን የፋኖ ትግል መሪዎች ስም እያነሳና እያወደሰ ወጣቱን ለትግል ቀስቅሶበታል።

ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼኩቬራ! በማለት እዬዘመረ ወጣቱን ለሽምቅ ትግል እንዲሰለፍ አድርጎታል።ወጣቱም ያንን ተከትሎ በከተማና በገጠር የመሳሪያ ትግል ለማካሄድ ተሰልፎ ብዙ መስዋእትነት ከፍሏል።ምንም እንኳን ብዙ መስዋእትነት ቢከፈልም ውጤቱ ለባሰ ወታደራዊ አምባገነን ሥርዓትና ከዚያም ባለፈ የዘረኞች ቡድን ስርዓት መስፈን ሆነና አሁን ላለንበት ቀውስ ዳርጎናል።መታወቅ ያለበት ጥፋቱ የፋኖ ትግል ማድረጉ ሳይሆን የፋኖ ትግሉ በተገቢው ቦታና ጊዜ መካሄድ የሚገባው፣የሃይል ሚዛንን የተገነዘበ ስልት የተከተለ እንዲሁም ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ ተገንጣይ ዓላማ ባላቸው መጠለፉና ለእኩይ ዓላማ መሣሪያ ለመሆን መመቸቱ ነው።

ይህ የአሁኑ አገር አፍራሽ የጎሰኞች  ስርዓት የዚያው የጠላፊው ቡድን ውጤት ነው።ይህ  የጎሰኞች ቡድን ሥልጣኑን ከጨበጠ በዃላ ብዙ አገራዊ ስብራቶችን አድርሷል።ወደፊት ሊያደርስ የሚችለውን አገር የማፈራረስ አደጋ ለመከላከል፣ በሕግ ሊወገድ ያልቻለውን ግፍና መከራ  ለማሶገድና ፍትሕ ለማስፈን  ሲባል አገር ወዳዱ ለዳግመኛ የሽምቅ ውጊያ፣ለዳግመኛ ፋኖ፣ለዳግመኛ አርበኝነት ፣ያለውን መሣሪያ፣ዱላ፣ጦርና ጋሻ አንግቦ፣ ጨርቄን ማቄን ፣ሃብት ንብረት፣ሚስቴን  ልጄን ሳይል ዱር ቤቴ ብሎ የህይወት ዋጋ በመክፈል ላይ ይገኛል።ይህንን ቆራጥ አገር ወዳድ የአንድ ጎሳ ፣ዘራፊና አሸባሪ አድርጎ በማቅረብ ሕዝብ እንዳይከተለው፣ትግሉ እንዲዳከምና በሰርጎ ገቦችም አቅጣጫውን እንዲቀይር የማድረጉ ሴራ በስልጣን ላይ ባለውና ጸረ ኢትዮጵያ በሆኑት አክራሪና ጠባብ ጎሰኞች በኩል ያልተደረገ ሴራ ያልደረሰበት  ጥቃት የለም።አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።አባላቱን ማሳደድና ለመግደል ሙከራ ማድረግ አልቆመም።ግለሰቦችን በመግደል የተሰበሰበው ፋኖ ይበተናል የሚል gmeት አላቸው።ግምታቸው እውን እንዳይሆን የፋኖ ስብስብ በአንድ ማዕከላዊ ዕዝ ተቋም  ሥር መሰለፍ አለበት።አደጋ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ለትግሉ መልክና ሂደት ወሳኝ ነው።ሁል ጊzm በድርጅት የሚመራ እንቅስቃሴ ለአደጋና ለችንፈት አይጋለጥም።

እንደ አገር ወዳዱ ፋኖ መሣሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ  በጥቅም የተገዙ ከሃዲያን በልዩ ልዮ መጠሪያ ስም  በወለጋ፣በኢሉባቦር፣በመተከል(ቤኒሻንጉል) በሕዝቡ ላይ ጉዳት፣ዘረፋና ጥቃት የሚያደርሱት  ቡድኖች ከተራ ሽፍትነት ተለይተው የሚታዩ አይደሉም።እነዚህ ፋኖ ሳይሆኑ አሸባሪዎች፣አፉኞች፣ ጨፍጫፊና ዘራፊዎች ናቸው።እነዚህ ወንጀለኞች በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥትና መቀሌ በመሸገው የወያኔ ቡድን እርዳታና ከለላ፣በምዕራባውያንም ቸልታና ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።ለሕግ ሊቀርቡና ቅጣታቸውን ሊያገኙ ይገባል።እነዚህ በያቅጣጫው የተሰማሩት አጥፊ ቡድኖች በከባቢው ሕዝብ መብት በማስከበር ስም የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ ከዛም በተጨማሪ የውጭ ሃይሎች የሚገለገሉባቸው  መሳሪያዎች ስለሆኑ የገንዘብና የማሳሪያ ተፋሰስ በቀላሉ የሚያገኙ ስለሆነ ጡንቻቸው እዬፈረጠመ በመሄድ ላይ ነው።ዓላማቸውም ኢትዮጵያን የማፈራረስና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የቆመውን ማህበረሰብ በተለይም አማራውን መጨፍጨፍና ማፈናቀል ነው።የኢትዮጵያዊነት አቋም ካለው የራሳቸውም ጎሳ ተወላጅ ቢሆን አይምሩትም፣ጨፍጭፈውታል ፣ወደፊትም ይጨፈጭፉታል።ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አገር ወዳድ በሙሉ እነዚህን እኩይ ስብስቦች ለመፋለምና የአገሩና የመብቱ ጌታ ለመሆን በፋኖነት መሰለፍ ይኖርበታል።

ምን መደረግ አለበት?

በፖለቲካው በኩል የፖለቲካ መልስ መስጠት የሚችል አገር ወዳድ ስብስብ ማደራጀት አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ  አገር ወዳዱ የሚያደርገው የሞት የሽረት የትጥቅ ትግል መኖሩን በአጭሩ ተረድተናል።ይህ በፋኖ ስም የሚጠራው፣የአገር ወዳዶች፣የሽምቅ ተዋጊ፣የአርበኞች ትግል የሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ትግል መሆኑን ተረድተን የሚችል አብሮ እንዲሰለፍ ያልቻለ ደግሞ በሚችለው መንገድ መርዳት እንዳለበት ሁኔታው ያመላክታል።አሁን በትግሉ ሜዳ የተሰማሩት ቁጥራቸው ጥቂት ባይባልም ይበልጥ መጎልበት ይኖርበታል።የፋኖ ጥረት ብቻውን በቂ ስላልሆነ ሕዝባዊው ደጀን በውትድርናው መስክ ለተሰለፉት ፋኖዎች የስንቅና ትጥቅ አቅርቦት እንዲሟላ፣የመረጃና ከለላ ድጋፍ፣ የአርበኞቹ ቤተሰቦች እንዳይቸገሩ የገንዘብ(የኤኮኖሚ)እገዛ ማድረግ፣ የተፈናቀሉት መልሰው እንዲቋቋሙ፣በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክም እንዲሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች ከሆኑት በኩል እርዳታ የሚገኝበትን መንገድ መሻት ይጠበቃል። አገር በምኞትና በስለት የሚመሰረት ሳይሆን በደም፣ በሥጋና በአጥንት ዋጋ ተከፍሎበት የሚመሠረት የጋራ ይዞታ ነው።ለአገር አንድነትና ልዑላዊነት የሚከፈለው ዋጋ ቀላልና ትንሽ አይደለም፣ኢትዮጵያዊነት ሊረጋገጥም የቻለው በአንድነትና በጸረ አንድነት ሃይሎች መካከል ፍልሚያ ተደርጎ የብዙሃኑ የሆነው የአንድነት ሃይሉ ጎራ በተቀዳጀው  ድል ነው።የአገራችንም ሆነ የሌሎች አገሮችም ታሪክ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው።

የሰይጣንን ጆሮ ይድፈነው እንበልና ተወደደም ተጠላም፣አደጋ ቢኖርም ባይኖርም መዘጋጀቱ የግድ ይላል።በመሬት ላይ ያለው ሃቅ ሲታይም አገራችን ለቅርጫ የቀረበች እንስሳ ትመስላለች።በየክልል ተብዬው የጎሰኞች ጎራ ልዩ ሃይል በሚል ስያሜ የወታደር ስልጠናና ዝግጅት ለዚያ ግብ የሚዳርግ መሰናዶ መሆኑን መካድ አይኖርብንም።ያ ካልሆነ ለምን አስፈለገ?ብሎ መጠዬቅ የመልሱ ግማሽ ይሆናል።በፌዴራል ስም የተዋቀረውም የጦር ሃይል በጎሳ ተዋረድ የተውጣጣ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።በጎሳው ብዛት መጠን የተመለመለ ወታደር መሆኑንም ተደጋግሞ ሰምተናል።የመሪዎቹም ሹመትና የሥልጣን እርከን እንዲሁ ጎሳ ተኮር ነው።ይህ በጎሳ አውጫጭኝ የተዋቀረ ወታደር የማታ ማታ በየጎሳው ተለያዬቶ እርስ በርሱ የሚጨራረስ ላለመሆኑ ዋስትና የለም።በጥቂቱም ቢሆን በአንዳንድ ቦታዎች በሕዝብ መካከል በተፈጠረ ግጭት ማን ለማን እንደቆመ በአንዳንድ ቦታዎች በፖሊሶች በኩል የታዘብነው ሃቅ ነው።ከሁለት ዓመት በፊት  በትግራይ የጦር ሠፈር የተፈጸመው ሌላውን ለይቶ የማጥቃትና  የመጨፍጨፍጨፍ ወንጀል ከዚያ ድክመት የመነጨ መሆኑን መካድ አይገባም። እውነቱን መናገር ለተመሳሳይ ድርጊት ተዘናግቶ ላለመቀመጥ ትምህርት ይሰጣል።

ታሞ ከመሟቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ወይም ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንዳይሆን የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ የተሰለፈ የሚያስተማምን ፋኖ፣ሕዝባዊ ጦር መፍጠር ወይም ካለ መርዳትና ማጠናከር፣ ለዘላቂው ብሔራዊ ሠራዊት ተቋም ምስረታ መንደርደሪያ ይሆናል።ይህንን አገርና ሕዝብን ሊያድን የሚችል ሃይል ይፈጠር ማለት የጦርነት ነጋሪት መጎሸም አይደለም፣የማስጠንቀቂያ ደወል ማሰማት እንጂ!

የፋኖ ትግል እንዲሳካና ውጤታማ እንዲሆን የግድ በተደራጀ መልኩ የሚመራ አካል መኖር አለበት።ወታደራዊ ዕውቀትና ልምድ እንዲሁም ብቃት ባላቸው የሚመራ ከሆነ የግለኝነትና የጎጠኝነት መንፈስን ያሶግዳል።የአምባ ገነን  ግለሰብ የሥልጣን መረማመጃና መጠቀሚያም እንዳይሆን ይረዳል።ግለሰብ አስተዋጽኦ እንዳለው ባይካድም  መላው ፋኖ በሱ ጥላና ስም የሚሰበሰብና የሚታወቅ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።ለግለሰቦች የሥልጣን ሽኩቻ መነሻና ምክንያት ይሆናል።ከብሔራዊ ፋኖነት ወጥቶ የገሌ ጭፍራ የመሆን አደጋ ይከሰታል።በዘመነ መሳፍንት ወይም ባላባት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱ ጭፍራ ስለነበረው ጭፍራውም እኔ የገሌ አሽከር እያለ የሚኩራራ በመሆኑ አገራዊ ማንነቱ የላላ ነበር።ከጌታው ሌላ አይታዬውም ነበር።አሁንም የዚያ መንፈስ እንዳያንሰራራ መቆጣጠር ተገቢና አስፈላጊ ነው።በግለሰብ ዙሪያ የተሰበሰበ ከሆነ ግለሰቡ ላይ የሚደርስን ለውጥ ተከትሎ መበታተን ይከሰታል።በታሪካችንም በመተማ ጦርነት ጊዜ የአጼ ዩሃንስ ጦር ሊበተንና የተሸነፉት የሱዳን ደርቡሾች ጦር ከተበተነበት ተሰብስቦ ለዳግመኛ ጥቃት የበቃው በአንድ ግለሰብ፣በንጉሱ ጥላ ስር በመሰለፉና ንጉሱ በጥይት ተመተው በመውደቃቸው ነበር።

ጎን ለጎንም አገራችንን ወደ ተሻለ ስርዓት የሚመራ ለፖለቲካ ቀውስና ችግር የፖለቲካ ምላሽ መስጠት የሚችል የፖለቲካ ድርጅት መፍጠር መዘንጋት የሌለበት ተግባር ነው።እስከ አሁን ድረስ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች በንትርክና በራስ ወዳድነት የተጠመዱ፣ቆራጥነትና በራስ መተማመን የሌላቸው፣ከመተባበር ይልቅ መጠላለፍን ሙያ አድርገው የያዙ፣ያለውን ሥርዓትና ሕገመንግሥት የተቀበሉ አማራጭ ሳይሆኑ አንቋላጭ ከዛም አልፈው ካለው ጎሰኛ ስርዓት ጋር የሥልጣን ቦታ የተቃረጡ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ስለሆኑ ብሄራዊ  አደራ ይወጣሉ ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው።ሰላም ከማያውቅ ከወያኔ ቡድን  ጋር ሰላማዊ ድርድር አድርጌ ችግር አሶግዳለሁ ማለትም ሆነ በሥልጣን ላይ ያለውን ማመን እራስንም ሕዝብንም ማታለል ነው። ከወያኔና ከፈጠራቸው የጎሳ ስብስቦች ፣ተገንጣይ ፣ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የባዕዳን መሣሪያ ከሆኑት ቡድኖች  ጋር ተደራድሮ ሰላምና አንድነት ሊረጋገጥ አይቻልም።እኩልነትና የአገር ልዑላዊነት የሚከበረው በእነሱ መቃብር ላይ ብቻ ነው።

የፖለቲካውና ወታደራዊው ክንፍ በመቀራረብና በመመካከር የአገርን እጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችሉ መሣሪያዎች ናቸው።አንዱ በጉልበት ሌላው በእውቀትና ብልሃት የሚከሰቱ ችግሮችን ለማሶገድ የሚያስችል አቅም ይፈጥራሉ።

አስተማማኝ ከሆነ  ከአገር መከላከያ ሃይል ጎን ለጎንም የአገርን የፖለቲካ ጎዳና የሚቀይስ ድርጅታዊ ቁመና ያለው ፣ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከብር፣የሰፈነው የጎሰኞች ስርዓት ተወግዶ በምትኩ  ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሁሉም አገር ወዳድ የድርሻውን ሊያበርክት ይገባል።ከዚህ የተሻለ ምርጫ የለም።

አገሬ አዲስ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

Go toTop