ሞኝ አይሙት እንዲያጫውት! – አገሬ አዲስ   

ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓመ(22-08-2022)

አብይ አህመድ በነሐሴ 15 ቀን 2014 በፈረንጆቹ ኦገስት 21 2022  የብልጽግናን የወጣት ክንፍ ሰብስቦ “የወጣቶች ሚና” በሚል መርህ ባስተላለፈው መልእክት ውስጥ  አገራችን በሦሥቱ ደካማ ምንነቶች  ማለትም በሞኝነት፣ጅልነትና ጅላጅልነት የተወረረች መሆኗን ተናግሯል።ወጣቱም ሰምቶትና አይቶት የማያውቅ እውቀት የገበዬ መስሎት እጁ እስኪላጥ ድረስ በማጨብጨብ ሞኝ፣ ጅልና   ጅላጅልነቱን ተቀብሎ አረጋግጧል።ከዘመኑ ዓለም አቀፉ የዜና እና  የእውቀት ምንጭ ከሆኑት ከዩቱብና ፌስቡክስ ተገልሎ እንዲኖር የተላለፈለትን መልእክት (ትዕዛዝ ቢባል ይሻላል) አጨብጭቦ መቀበሉን ከስብሰባው በዃላ የወጣቱ ተወካዮች በአብይ ልሳን በሆነው በፋና በኩል ሲያስተጋቡ ተሰምቷል። አዎ አብይ አህመድ ሞኝ፣ጅል፣ ጅላጅልና ጅላንፎ ያለው ከመረጃ ለመራቅ ቃል የገባን  ይህንን የወጣት መንጋ ማስረጃ አድርጎ ነው።በጣም የሚገርመው ነገር ብዙ ሚሊዮን ብር መድቦ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በፌስቡክና ዩቲዩብ የተሰማሩትን  አድርባይና  ውታፍ ነቃዮች  እራሱና የሚመራው ቡድን ብልጽግና መሆኑን የዘነጋው ይመስላል።ግን የዘነጋው ሳይሆን የራሱንም ጉድ ለማወቅ ያልቻለ፣ሰው ምን ይለኛል ብሎ የማይረዳ  ሞኝ ጅልና ጅላጅል በመሆኑ ነው። “ሞኝ አይሙት እንዲያጫውት” ይሏል የአብይ አህመድ አይነቱን ነው።

ብዙ ጊዜ ሲነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህ ነው ይባላል።የዋህነት እኮ ደግነትና ብልህነትን ሳይሆን በቀላሉ የሚታለል፣ የሚነዳ፣ያሉትን የሚያምን፣የማይጠራጠር፣ለምን ብሎ የማይጠይቅ፣ና ሲሉት የሚመጣ፣ሂድ ሲሉት የሚሄድ የሰው ረቦት  ማለት ነው።ሞኝ ወይም ጅልና ጅላጅል የሚለውን  ጠጠር ያሉ ቃላት በተለሳለሰ መንገድ ማስቀመጥ  እንጂ በየዋህነትና በሞኝነት ብሎም በጅልነት መካከል ልዩነቱ አይታይም።

አገርና ሕዝብ በጎሳ ፖለቲካና በጎሰኞች ሲተራመስ፣ሲሰቃይ፣ሲገደል፣ሲጨፈጨፍ፣ሲፈናቀል፣በኑሮ ውድነትና በድህነት፣በሥራና በሰላም ማጣት፣በቤት ችግር ብቻ ሳይሆን የአገር ባለቤትነቱን ሲነፈግ ፣በዝምታ የሚያይ ይህ በብልጽግና ሥር የሚርመሰመስ ትውልድ ከሞኝነት፣ከጅልነትና ከጅላጅልነት በላይ የሆነ ደረጃ ቢኖር የዚያ ባለቤት ነው።

የለዬለት አብይ አህመድ በዚህም ብቻ አልቆመም።ጫት በመቃም ጊዜያችሁን አታባክኑ ብሏል፣እርግጥ ነው ወጣቱ በዚህ ከንቱ ተግባር ላይ ጊዜውን ማባከኑ የሚካድ አይደለም።ጥያቄው ግን እነማን ናቸው ጫቱን እያመረቱ የሚሸጡት፥የብልጽግና ባለሥልጣኖችና ጀነራሎች አይደሉም ወይ ብሎ ደፍሮ የጠዬቀው የለም።የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎችንም የደመወዝ ጥያቄ አገራችን ካለባት ችግር አንጻር መጠዬቅ የሚገባው አይደለም ሲል አይ ጠ/ሚኒስትር ታዲያ በ49-9 ቢሊዮን ብር አውጥቶ  ቤተመንግሥት ለማሰራት የትኛው ያገራችን ኤኮኖሚ ይፈቅዳል? ብሎ የጠዬቀው የለም። በዚያም አስታኮ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ግል ይዞታና የንግድ ተቋም ለመለወጥ ማሰቡን “ዩኒቨርሲቲ እራሱን መቻል አለበት” በማለት ከአሜሪካና ከሌሎቹ አገሮች የግል ትምህርት ተቋም ጋር ለማመሳሰል ሞክሯል።አንድ መንግሥት ተቀዳሚ ግዳጁ የትምህርት፣የጤና፣የመገናኛ የኢንፍራስትራክቸርስ፣የመከላከያና የደህንነት ተግባራትን ማሟላት ነው።ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች(state University) ጎን ለጎን የግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ይኖራሉ፤በአገራችንም ውስጥ መኖራቸው አይካድም።የአብይ አካሄድ ግን ሁሉንም ነገር በፕራይቬታይዜሽን ስም  ሻሽጦ ገንዘብ ለመሰብሰብና የውጭ ባለሃብቶች የሚዘርፉበትን ዕድል ማመቻቸት ነው።የአብይ ሰጥቶ የመቀበሉ መርህ ማለት ይህ ነው።በዬክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እራሳቸውን ይቻሉ ቢባልስ የኦሮሚያ ክልል ውጭ ያሉት ክልሎች በራሳቸው ባጀት የመንቀሳቀስ አቅም ይኖራቸዋል ወይ?በተለይም የአማራውና የትግራዩ አካባቢ  በወያኔና ኦሕዴድ የሥልጣን ሽኩቻ ባመጣው ጦርነት ከግማሽ በላይ ንብረትና ሃብቱ ወድሞበት የነበሩትን ለመመለስ አቅም የሌለው ሕዝብና አካባቢ ወጣቱ ከፍሎ የመማር አቅም አለው ተብሎ ይገመታል ወይ?ወይስ የደሃው ልጅ ዩኒቨርሲቲ እንዳይገባ የሚያግድ መመሪያ ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የእኛ “መንግስት” - ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

ስለሰላምም አስፈላጊነት ለፍልፏል፣ግን ሰላምን ምን አደፈረሰው?የምትመራበት የጎሳ ፖለቲካና ሕገመንግሥት ብለህ የተሸከምከው ሕገጥፋት አይደለምን?ብሎ ያፋጠጠው የለም።

የጅል ብልጥ የሆነው አብይ አህመድን የፖለቲካ ጡጦ ግቶ መልምሎ ያሳደገው ጅላጅሉ ኦነግ  ስለሆነ በሱ የሚታለልና የሚደነዝዝ ወጣት ካለ እውነትም የባሰ ጅልና ጅላጅል ብቻም ሳይሆን እንከፍ ነው። አገሩ ያለችበትን የመፈራረስ አደጋ የማይገነዘብ፣እራሱንም ጨምሮ ለዚህ ሁሉ መከራ ያበቃውን አብይ አህመድ የሚወክለውን የጸረ ኢትዮጵያ ቡድን ብልጽግናን ሳይረዳ የዚያው አካል ከሆነ እውነትም ጅላጅል  ነው።  የሌቦች ስብስብ የሆነውን ብልጽግና የሚመራው አብይ አህመድ ወጣቱን ሌቦች አትሁኑ ማለቱ በሥራችን አትግቡ፣አትጫረቱን ለማለት መሆኑን ያልተረዳ ወጣት ከሞኝም ሞኝ ከጅልም ጅላጅል ነው።የአገር ሃብት የሚመዘብረውን በሥልጣን ላይ የተቀመጠ ጎሰኛ ቡድን ለመምሰል ውድድር ውስጥ የገባ ፣በሌብነት መስክ ለመሰለፍ ያሰፈሰፈ ወጣት ለሙያው ብቁ መሆኑን በዬመድረኩ ከማሰማት ባለፈ ሌብነትን ሲያወግዝና ሲቃወም አይታይም።የዘመኑ ዕውቀት ሌብነት ነው ብሎ የሚያምን ትውልድ ሌብነትን ያደንቃል እንጂ አይጠላም።ሌቦች የፎቅ ባለቤቶች ፣የውድ መኪና አሽከርካሪዎች፣በፈለጉበት አገር የሚንሸራሸሩና የሚዝናኑ መሆናቸውን ከሚያይና ከሚያደንቅ ያንንም ለማግኘት ከሚጓጓ ወጣት አገር ወዳድነት፣ሃቅና ቁም ነገር አይጠበቅም።

አዎ አገራችን የጅሎችና የፈሪዎች መናኸሪያ ሆናለች።ላለፉት 50 ዓመታት ለሰፈኑት ጨካኝ ሥርዓቶች በሥልጣን ላይ እንዲቀመጡ የረዳቸው ጅልነትና መጃጃል በመኖሩ ነው።አለማወቅና አለመረዳት ጅልነት ነው።ሲነግሩት አለመስማት መጃጃል ነው።ከእባብ እንቁላል እርግብ ይቀፈቀፋል ብሎ እባብን እሹሩሩ እያሉ ተሸክሞ መኖር አዎ ጅልነት ነው።አገር የመፍረስ አደጋ ላይ ሆና ፎቅ ቤትና ንብረት እይዛለሁ ብሎ ደፋ ቀና ማለት ከጅልነት የመነጨ ድንቁርናም ነው።አገር ሳይኖር፣ሰላም ሳይሰፍን፣የሕዝብ እኩልነትና መብት ሳይረጋገጥ ንብረት ሊኖር አይችልም። በተረኞች የተነጠቁትን እያዩ ያልተማረ ከሞኝም ያለፈ ጅልና ጅላጅል ነው።አብይ አህመድ በዚህ ላይ እውነቱን ተናግሯል።ጅል ባይኖር ጅሎች ሥልጣን ላይ ወጥተው ሊገዙ አይችሉም።እያጃጃሉ የሚገዙት ሞኝ ሕዝብ ባይኖር ዕድሉን አያገኙም፤ሞኝ መሪ ከሞኝ ሕዝብ ይቀዳል፤መንግሥት ወይም መሪ ከሕዝቡ ይወጣል የሚባለውም ለዚያ ነው።

የተሰበሰበው ወጣት ሞኝ፣ ጅልና ጅላጅል ባይሆንማ ኖሮ ከማጨብጨብ ይልቅ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በመሬት ላይ በገሃድ በሚታዬው በራሱ  ጉዳይ ላይ አብይ አህመድን  ወጥሮ በያዘው ነበር። ሥራ ማጣቱ፣የአገር ባለቤትነቱ፣ሰላሙን፣ተስፋና ህይወቱን በማን እንደተነጠቀ ያላወቀ ወጣት ከጅልና ጅላጅልም ባለፈ ነሆለል ቢባል ተገቢ ነው። ለመብትና ለሃቅ መቆም ከነቁና  ካወቁ ወጣቶች  እንጂ ለሆድና ለጥቅም ከአገር አጥፊው ብልጽግና ድንኳን ውስጥ ከተሰገሰጉት ሞኞች፣ጅሎችና ጅላጅሎች አይጠበቅም። ጅል ያልሆኑትማ፣የሥርዓቱን ምንነትና አካሄድ በመረዳት እምቢ ብለው የህይወት ዋጋ እዬከፈሉ ነው።የመከራ ጽዋ እዬተጋቱ ነው።ከተሟላና ከተመቼ ኑሮዋቸው ይልቅ ያገር ደህንነት፣ የሕዝብ እኩልነትና መብት መከበር በልጦባቸው በሚችሉት የትግል መስክ ተሰልፈዋል። ለአደጋ ተጋልጠዋል።በዬእስር ቤቱ እዬማቀቁና እዬተሳደዱ ነው።ለሆዳቸውና ለግል ጥቅማቸውማ ቢያስቡ ኖሮ ሞኞች፣ጅሎችና ጅላጅሎች የተጠቀጠቁበትን የብልጽግና አዳራሽና መድረክ ባጨናነቁት ነበር።ተመስገን ደሳለኝም ወጣት ነው፣መአዛ ሞሃመድም ወጣት ነች፣መስከረም አበራም ወጣት ነች።ግን ሞኞች፣ጅሎችና ጅላጅሎች አይደሉም።በአብይ አህመድ እይታ ግን ነቅተው የሚያነቁ ጅሎች ናቸው።እነሱንም የሚሰማና ለእውነት የሚቆም ጅላጅል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰማይ ተቀደደ ቢሉት ሽማግሌ ይሰፋዋል ይላሉ አበው - አማኑኤል ታደሰ (ከድሬዳዋ)

እነዚህን እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ  ጅሎች ሆነው በአብይና በመሰሎቹ ለመታለል ያልቻሉት ቁጥራቸው ብዙ ነው።አንታለልም ያሉ፣ በዬክፍለሃገሩ፣በዬመንደሩና በየገጠሩ፣በዱር በገደሉ እምቢ ላገሬ ብለው ከመዋረድ የሞትን ጽዋ የመረጡ ወጣቶች ብቻም ሳይሆኑ ጎልማሳና አዛውንቶች የጅሎችን አገዛዝ እዬተፋለሙት ይገኛሉ።ታዲያ የጅልነትን መስፈርት የሚያሟላው በዬትኛው ጎራ የተሰለፈው ነው? በጅሎቹ ወያኔና ኦነግ በተሠራው ቤት ውስጥ ገብቶ አንድ ጊዜ ኢሕአዴግ ሌላ ጊዜ ብልጽግና እያለ በአስራስድስተኛው ክፍለዘመን የዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብ ተጠምቆ የሚጃጃለው አድርባይ ወጣትም ይሁን ጎልማሳ ወይስ የጅሎችን ፖለቲካ ተጠይፎ ለሃያ አንደኛው ክፍለዘመን የሚመጥን ዘመናዊና ሳይንሳዊ  የፖለቲካ ራእይ ሰንቆ  የሚንቀሳቀሰው  ታጋይ?

ወጣት የዕድሜን ጣራ የሚገልጽ እንጂ የአስተሳሰብንና የእውቀትን መጠንና ደረጃ የሚገልጽ አይደለም።ወጣት አገር ወዳድ እንዳለ ሁሉ ወጣት ሆድ አደርና ባንዳ አለ።በወጣትነት ዕድሜ አንድ ቢሆኑም በአሰላለፍ ጎራ የተለያዩ ናቸው።የሌላውም ዕድሜ ተካፋይ እንዲሁ ነው።በአዛውንቱ ዳውድ ኢብሳና በታድዮስ ታንቱ መካከልም የዕድሜ ልዩነት ባይኖርም በአጥፊና ጠፊነት በጸረ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ጎራ የቆሙ ናቸው።ዳውድና መሰሎቹ በቤተመንግሥት ፣ታዲዎስና መሰሎቹ በእስርቤት የሚገኙ ናቸው።ሌላው ቀርቶ ከአንድ ማህጸን የወጡ ልጆችም ቢሆኑ በተለያዬ ጎራ ተሰልፈው የታገሉ በታሪካችን አይተናል፣እያዬንም ነው።ታዲያ ሞኝነትንም ሆነ፣ጅልነትን እንዲሁም  ጅላጅልነትንና የነዚያንም ተቀናቃኝ የሆነውን ብልህነትን የዕድሜ ተዋረድ ሳይሆን የአስተሳሰብና የንቃተ ህሊና ደረጃ የሚወስነው ነው።

ሥራ አትምረጡም ብሏል፤አዎ ሥራ አይመረጥም።አቅምና ችሎታ በሚፈቅደው መሠረት ያገኙትን መሥራት ተገቢ ነው።ጥያቄው ግን እኮ ሁሉም ሥራ በጎሳ ማንነት የሚሰጥና የሚነሳ ከሆነ፣ያንን የሚያራምድ ስርዓት ከሰፈነ እንዴት ዜጋ በችሎታውና በሚፈልገው ሙያ ሊሰማራ ይችላል?

አዎ አብይ አህመድ ትክክል ነው ፣የሚያጭበረብረውና የሚያወናብደው፣በጥቅም የሚገዛው እርካሽ ወጣትም ሆነ ጎልማሳ ሴትም ሆነች ወንድ ከቦት በሚሰማው እያጨበጨበ የሚነዳለት እስከካለ ድረስ በቅርቡ የሚያዬውና የተከበበው በነዚህ አይነቶቹ ሞኞች፣ጅሎችና ጅላጅሎች ነውና  ኢትዮጵያ በሞኞች፣ጅሎችና ጅላጅሎች ተጨናንቃለች ብሎ ቢናገር አይፈረድበትም።ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከኦነግ ብልጽግና መነጽር የእይታ ክልል ውጭ አያውቃትም።ደፋሮቹን ደፍሮ ለማዬት ወኔም ብቃትም የለውም።የሱ ብቃትና ችሎታ የኦነግን ጸረ ኢትዮጵያ ፍልስፍና በተሞናሞነ ቃላት ሸክኖ፣ልብ በሚያማልል አቀራረብ  ማራመድና በዚያ ዙሪያ ወጥመድ የተጠለፉትን አድርባዮች ማድነቅና ማሞካሸት፣መሾምና መሸለም ነው። ለዚያ ያልተመቹትን ማሳደድ፣መግደልና ማስገደል ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኤርምያስ ለገሠና በዲ/ን ዳንኤል ክብረት በኩል እኛን ማዋራት አሰኘኝ

የሞኞቹ፣የጅሎቹና የጅላጅሎቹ ጎራና አስተሳሰብ የወለደው የወያኔ ኢሕአዴግና የኦነግ ብልጽግና ሥርዓት ይደርመስ! የጎሰኞች በረት የሆነው ክልል ይፍረስ

የአዋቂዎቹና የጀግኖቹ ጎራ የሆነው ኢትዮጵያዊነት ይጠንክር፣ይታደስ!!

አገሬ አዲስ

3 Comments

 1. አብይ ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለበሻሻ አይመጥንም፡፤
  የአብይ አህመድ አባትና እናት ከብቶቻቸውን ሸጠው እርሱን ማለትም አብይን “ከብቱን” ከሚያስተምሩ ይልቅ ከብቶቹ ባይሸጡ ይሻል ነበር፡፡ ይህ ልክ መሆን ስላለመሆኑ ሆዳሞቹና ተረኞቹ ሳይሆኑ በተረናውና በዘረናው የኦሮሙማ ስርአት የተጎሳቆለውና በአብይ ድንቁርና ቁም ስቅሉን ያየው የኢትዮጵያ ህዝብ ይመስክር፡፡
  አማራ በኦሮሙማ ፖለቲከኞች ጥጋብና እብሪት በህይወት መኖር፣ መተንፈስና መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጎ ተጠርንፎ ባለበት በዚህ ሰአት “ጅል፣ ጅላጅልና ጅላንፎ ብሎ ምጡቁን ኢትዮጵያዊ ወጣት እንድያጨበጭቡ ብቻ መራርጦ ለሰበሰባቸው “” ወጥ ጠራጊወች” መናገሩ የከብት አስተሳሰብ ነው፡፤ ማንም ሊስትው የማይገባው ነገር የኢትዮጵያ ወጣት የታሪክ ባለቤት እንጅ ለገዥው መደብ አጎብዳጅ አለመሆኑን ነው ታሪክ የሚመሰክረው፡፡ አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንደዚህ የሚሳለቀውና በተለዬ ሁኔታም በአማራው ላይ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ውርደት እልቂትና ስደት እንድንደርስበት ያደረገው የአማራ ሆዳም ሹመኞች ታማኝ አሽከሩ ሆነው ሁሉንም እንድያደርግ ስላስቻሉት ብቻ ነው፡፡
  አብይ አህመድና ተረናው የጅቦቹ ቡድን በታማኝ የአማራ አስከሮቹ ትከሻ ላይ ተመቻችተው ተቀምጠው እንጅ ተረኞቹ ኦሮሙማውች (የኦነግ ክፍልፋዮቹ) ጎበዝና ተዋጊ ሆነው አማራውን አሸንፈውት አይደለም፡፤ በበደሉና ግፉ ልክ ፋኖ አፈር ልሶ እየተነሳ ስለሆነና በተለይም አብይ አማራን በማዋከቡ ከምንጊዜውም በላይ አማራ በአማራነቱ ስር የሰደደ ጥላቻን ስላስከተለ አማራው እንደ አዲስ እየተዳራጀ ስለሆነ በቅርቡ ውጤቱን ህዝቡ ያየዋል፡፡ እድሜ ለአብይ አህመድ ጥጋብ፡፤ ይህ ጥጋቡ ነው አማራን ነቅንቆ ጸረ አብይ አህመድ ሆኖ የማይታጠፍ ግንባሩን እያደራጀ ያለው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ አማራ ኢትዮጵያ እኢትዮጵያ ሲል ተዘናግቶ ስሩ ተነቅሎ ይቀር ነበር፡፡
  አዲስ አበባ ላይ የሚሰራውንም ግፍ በሚመለከት ቀበሮዋ አዳነች አበቤና በጡንቻው የሚያስበው ሽመልስ አብዲሳ ህዝቡን ይህንን ያህል ቁም ስቅሉን እንዳበሉት አይዘልቁም፡፤ ህዝቡ በቅርቡ የሚግባቸውን መልስ ይስጣቸዋል፡፡ ክንዱንም ያሳያቸዋል፡፡

 2. ደግ ብለሃል። የሆነው ያው የአገዛዝ ለውጥ እንጂ ዲሞክራሲን ለህዝብ የሰጠ ለውጥ አይደለም። የጠገበው ወርዶ ሌላ የተራበና ጨካኝ የተተካበት የዘር ሰልፍ ፓለቲካ። አባታችን ተው ተው ብሎ ይመክረንና የተመከርንበትን ጉዳይ ሳንሰማ ቀርተን ሲሆን በሉ ተውት ብዪ ነበር በማለት ነገሩን ያልፈዋል። አሁን እየሆነ ያለውም ይህ ነው። ወያኔ በትግራይ መሬት ህዝብን እያስጨነቀና ከውጭና ከውስጥ ሴረኞች ጋር ነገር እየፈተለ የአዲስ አበባው መንግስት ክልል አካላይና አልፎ ተርፎም በየጎራው ላይ ተሳዳቢዎችንና ቀልደኞችን አሰባስቧል። ዘረኝነት የጭንቅላት በሽታ ለመሆኑ በወለጋ መከራ የደረሰባቸውን ወገኖች ጠይቆ መረዳት ነው። አይ ወለጋ እንዲህ ትሆኝ?
  የዛሬው የዜና አውታር ደግሞ ያው የተጠበቀውን የማይቀር ጦርነት ይዞ ብቅ ብሏል። ራሱን በሌሊትና ቀን ተጉዞ በገባለት መሳሪያ ያዘመነው ወያኔ ዳግመኛ ጦርነት ከፈተብኝ በማለት የአብይ መንግስት ሲያላዝን ወያኔ ደግሞ ከቀናት በፊት ተተኮሰብኝ በማለት እውነትን ለማወቅ ያንቀላፋውን ዓለም ሲያምታታ ቆይቷል። እውነቱ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ወድቋል። ሲጀመር ለምን ወያኔን ይህን ያህል መለማመጥ እንዳስፈለገ ጭራሽ አይረዳኝም። ህዝቡን በር ዘግቶ ከመቅጣት ወያኔን ከገባበት ገብቶ ማሳደድ ተገቢ በሆነ ነበር። ግን የወያኔን የክፋት ቁንጮ ስብሃት ነጋን ፈቶ ጦማሪዎችንና ጋዜጠኞችን እንዲሁም ለሃገራቸው ደማቸውን ያፈሰሱትን ፋኖዎች ከሚያሳድድ አፉ ብቻ ከቀረ መንግስት ምን ይጠበቃል?
  ሞኝ ይኑር እንዲያጫውት ያሉት አበውም በላያቸው ላይ ያለውን ግፍና መከራ የሚያስረሳ በመሆኑ ነው። ላፍታም ቢሆን ፈገግ ያሰኛልና! ለመሆኑ ጅልና ጅላጅሎቹ እንዲሁም ሞኞቹ እነማን ይሆኑ? ፍትህ የሚጠይቁት በእስር ቤት ያሉት አዛውንቶች ይሆኑ? ወይስ ጊዜው የእኔ ነው በማለት ከየሥርቻው እየተጠራራ ጥቅማ ጥቅም የሚያሳድደው የኦሮሞ ስብስብ? አሁን አሁን ላይ ጠ/ሚሩ የሃገር መሪ ሳይሆኑ የኦሮሞ ሰልፈኞች አሳላፊ ይመስላሉ። ከንግግራቸው እንጥቀስ። በአዲስ አበባ ኦሮሞ ጠሎች በዝተዋል፤ ጥቁር ክላሽን እየቀሙ ነው ራሳቸውን ፋኖዎች ያስታጠቁት፤ ጉቦኛ የሞላው በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ ነው ወዘተ የሚሉ መረጃ የለሽ ንግግሮች ሃገር የሚያስተዳድር አንድ ሰው የሚናገረው ጉዳይ አይደለም። ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ጉዳዪች እውነትነት ሊኖራቸው ይችላል። ግን ከአንድ ተደመሩ እያለ ከሚለፈልፍ መሪ እንዲህ ያለ ከፋፋይና ተናዳፊ ንግግር አስፈላጊ አይደለም።
  ያው በየዘመናቱ እንዳየነው ሁሉ አንድ የአንድን ሥጋ ሲግጥ ፈጥኖ በጊዜው የጋለበው ወድቆ ሲከሰከስ፤ ትሻልን ትተን ትብስን ስናፈራርቅ ኑረናል። የአሁኑም የወያኔና የድህነት (ብልጽግና) ግብግብ የሚያስከትለው ሞትንና ውድመትን ነው። ሲጀመር ሰራዊቱ ትግራይ በር ላይ ቆሞ አሁን እንዲጠቃ ያደረገው ያ የሞኝ ብልሃት እንደገና ደብረ ብርሃን ቢደርሱ ቆሞ የሚመክት አይሆንም። የአሜሪካው መሪ በቅርቡ የትግራይን ጉዳይ አንስተው ወያኔ በአማራና በአፋር ላይ ያደረሰውን እንዲሁም በአማራ ህዝብ ላይ የኦሮሞ ታጣቂዎች ያደረሱትንና የሚያደርሱትን አለመጠቀሳቸው ሆን ተብሎ የተደረገ ስልፍ የማመቻቻ ብልሃት እንጂ ሌላ ጉዳይ አይደለም። ስንጋደል ደስ ይላቸዋል። ይኸው እንሆ ዛሬ ለዪክሬን እልፍ መሳሪያ የሚያጋግዙት አውሮፓውያንና አሜሪካኖች ሳያውቁት ዓለምን ልክ እንደ ቀድሞው በሁለት ካምፕ እየፈረጇት ይገኛሉ። የወያኔው የበፊት ጦርነትም ሆነ የአሁኑ የአሁኑ ፊልሚያም ከአሜሪካ በሚሰጣቸው ድጋፍና አይዞህ ባይነት የተፈጸመና የሚፈጸም ጥቃት ነው። ነጩ ዓለም ስንሞት ደስ ይለዋል። ስንራብ የራሱን የሻገተ ሞራል ማደሻ ይመጸውተናል። በእጅ አዙር ያለንን አንጡራ ሃብት ይዘርፋል። የኢትዪጵያ ችግር ተጀመረ እንጂ ገና አላለቀም። ወያኔን የማጎልበቱ ሥራ ደግሞ ሻቢያንም ከሥልጣን ለማውረድና የራሳቸውን ሰው በሥፍራው ለመገተር ታልሞ የሚሰራ እንጂ በደመ ነፍስ የሚደረግ እንቅስቃሴ አይደለም።
  ባጭሩ ለጠ/ሚ አብይ ያለኝ ምክር ወያኔ ሰላምን አያውቅም። ይህ ጦርነት ዳግም እንደሚያገረሽ ብዙዎች ተናግረዋል። የሰላም ድርድር የሚባለውም ዝም ብሎ መወላገድ ነው። የዓለም ካርታ የተሰመረው በጉልበተኞች ነው። ሌላው ሁሉ የፓለቲካ አሸንክታብ የከፋ ውስልትና እንጂ የጠብታ እውነት የለበትም። አሁን የኢትዮጵያ ጦር መቀሌ እንዳይገባ የሚያግደው ምን ይሆን? እሰይ ሞኝ አይሙት ቀሪን እንዲያጫውት.. በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share