የአለም የሰብአዊነት ቀንን አስመልክተው የፕሬዝዳንት ባይደን መግለጫ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግጭት አስመልክቶ ትግራይ ክልልን ብቻ መጠቀሱ ተገቢነት የጎደለው ነው ሲሉ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ገለፁ።
መግለጫው በሰሜኑ ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ትግራይን ብቻ የጠቀሰ መሆኑ አሳዛኝ ነው። ከትግራይ ውጭ በሌሎች አካባቢዎች የደረሰውን ሰቆቃ የረሳ መግለጫ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት ለተፈጸመው ግፍና ሰብዓዊ ቀውስ ግድ እንደሌላቸው ባስተላለፉት መልዕክት አሳይተዋል።
በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ብቻ በማንሳት አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልል ላደረሰው ሰብአዊ ቀውስና ግፍ ግድ እንደሌላቸው በመልዕክታቸው አመላክተዋል።
ቲቦር ናዥ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን እና የሚወሰዱ አቋሞችን በተደጋጋሚ በግልጽ በመቃወምና እውነቱን በመጋፈጥ የሚታወቁ አሜሪካዊ የቀድሞ ዲፕሎማት ናቸው።
ለአብነት ያህልም ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ያዘችውን ፍትሃዊነት የጎደለውን አቋም፤ “ለዓባይ ውኃ አንዲት ጠብታ የማታበረክተው ግብፅ በወንዙ ላይ መቶ በመቶ የመወሰን መብት መጠየቅ አትችልም” ሲሉ መቃወማቸው ይታወሳል።
በሌላ ጊዜ ደግሞ፤ የህወሃት ቡድንን ለአመታት እንደተከታተለ ሰው ቡድኑ አመጽን ወደ ስልጣን መመለሻ አድርጎ እየተጠቀመ ነው ሲሉ የቡድኑን ትክክለኛ ባህሪ ለዓለም አሳውቀዋል።
ከሁለት አመት በፊት እአአ በ2020 በቢቢሲ ሬድዮ አገልግሎት ላይ ቀርበው በሰጡት ገለጻ፤ መንግስት ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን መግለጹ፤የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ቶሎ ለመድረስ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እያደረገ ያለው ጥረትም አበረታች ነው፤ የህወሃት ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን ለማውረድ ያለመ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር ለቢቢሲ ሬድዮ ተናግረዋል።
እአአ በኦገስት 2021 ደግሞ ቲቦር ናዥ፤ ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ ትበተናለች የሚሉ አካላት ተሳሥተዋል ይልቁንም የገጠማትን ፈተና በድል ትወጣዋለች ሲሉም የኢትዮጵያዊያንን ጥንካሬ በአደባባይ መስክረዋል።
በወቅቱ ዩጎዝላቪያ የመጀመርያው የዓለም ጦርነትን ባሸነፉ አገራት የተፈጠረች መሆኗን ያስታወሱት ቲቦር ናዥ፤ ኢትዮጵያ ግን ከሁለት ሺህ ዓመት በላይ የኖረች አገር እንደሆነች በመግለጽ እዚህ የደረሰችውም በርካታ ቀውሶችን ፈትታ አልፋ ነው፤ አሁን ላይ የገጠማትን ፈተና አልፋ ሰላሟን እንደምታረጋግጥና ወድቀድሞ እድገቷ እንደምትመለስም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።
ዛሬም ከነጩ ቤተመንግስት በተዛባ መንገድ የቀረበውን የአንድ ወገን እይታ ብቻ የተንጸባረቀበትን መግለጫ ትክክል አይደለም ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አሳውቀዋል።
(ኢ ፕ ድ)