August 21, 2022
23 mins read

ስለአገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግር በአቶ ሚሊዮን ዘአማኑኤልና በጽዮን ዘማርያም የቀረበውን ጽሁፍ የሚመለከት ሀተታዊ ትችት!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ነሐሴ 21፣ 2022

በአቶ ሚሊዮን ዘአማኑኤልና በጽዮን ዘማሪያም ዘሃበሻ ድረ-ገጽ ላይ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያቀርቧቸውን ጽሁፎች  አልፎ አልፎ አነባለሁ። አሁን ደግሞ “የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስና የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የፕራቬታይዜሽን ሴራ” በሚል አርዕስት የጻፉትን አንብቤአለሁ።

እቶ ሚሊዮን ዘአማኑኤልና ጽዮን ዘማሪያም እንደዚህ የመሰለውን አገርን የሚመለከት ጽሁፍ ሲያቀርቡ እስካሁን ድረስ ግን የአሰራር ስልታቸውንና የኢኮኖሚ ፍልስፍናቸውን አልነገሩንም።  እንደሚታወቀው በኢኮኖሚክስ ዓለም ውስጥ የተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና ፖሊስዎች አሉ። እነዚህም በተለያየ ጊዜያት በአውሮፓ የካፒታሊስት የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት ውስጥ ተካሂደዋል። አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችም ሰፋ ካሉ አገርን ከመገንባት ጋር ከሚያያዙት፣ ለምሳሌ ከተማዎችንና መንደሮችን ከመገንባት፣ ባህላዊ የሆኑ የገበያ አዳራሾችን ከማቋቋም፣ ከተማዎችንና መንደሮችን የሚያያዙ ኢንፍራስትራክቸር ብለን የምንጠራቸውና ከተቋማት ግንባታ ጋር ተነጥለው የተካሄዱ ፖሊስዎች አልነበሩም። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ መርከንታሊዝም በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ የፖሊሲው ዋና ዓላማም በመጀመሪያ ደረጃ በተቻለ መጠን ንቁ የሆነ የባላንስ ፔይ ሜንት ፖሊሲ በመከተል(Active Balance Payment Policy) ከውጭ ወደ ውስጥ ብዙ የወርቅ ገንዘብ ወይም ወርቅና ብር ሊፈሱ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ምክንያቱም በጊዜው የአንድ አገር ሀብት የሚለካው አንድ አገር ባከማቸችው የወርቅ ክምችት  ስለሆነ ነው። ከዚህም በላይ ደግሞ በውስጥ በማደግ ላይ ያሉ ኢንፋንት ኢንዱስትሪዎችን በመከተል የውስጥ ገበያን ማስፋፋት ነው። ይሁንና ይኸኛው ፖሊሲ በራሱ የዋጋ ግሽበትን ያመጣ ስለነበር፣ ምክንያቱም ከውጭ ወደ ውስጥ የሚፈሰው የወርቅ ገንዘብ የተወሰነው በገበያ ላይ ስለሚሽከረከር የዋጋ ግሽበትን ያስከትል ስለነበር፣ የኋላ ኋላ ላይ የፍጹም ሞናርኪዎች ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማኑፋክቸሪንግ ላይ በማተኮር የውስጥ ገበያን ማሳደግና፣ በተለይም ደግሞ ንቁ ኃይሎችን መደጎም ነበር። በዚህ መልክ ነው ቀስ በቀስ ለካፒታሊዝም የሆነ የዕድገት መሰረት ሊጣል የቻለው። ይህንን ዐይነቱን አገርን በሁሉም አቅጣጫ የማሳደግና የመገንባት ፖሊሲ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች፣ በኋላ ላይ ደግሞ አሜሪካና ጃፓን፣ ቀጥሎም ደቡብ ኮሪይ ተግባራዊ አድረገውታል። ይህም የሚያረጋግጠው ዛሬ በቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛውን ቦታ የያዙ አገሮች በሙሉ እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት በመንግስት ጣልቃ-ገብነት አማካይነት ብቻ ነው።  አብዛኛዎቹ አገሮችም ኢኮኖሚያቸውን በፓውንድ፣ በኋላ ላይ ደግሞ በዶላርና በኦይሮ ሳይሆን  መገንባት የጀመሩት፣ የየራሳቸውን ገንዘብ በማተምና ለኢንዱስትሪዎች ዕድገት በማዋል ብቻ ነው። ጀርመን እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የራሷን የባንክ ስርዓት በማቋቋምና ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በርካሽ ብድር በመደገፍ ነው። በዚህ መልክ ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣና፣ የኋላ ኋላ ላይ የከብርቴው መደብ እያደገ ሲመጣ የመንግስታትም ሚና እየቀነሰ መምጣት ቻለ። ስለሆነም የመንግስታት ሚና በሚሰበስቡት ቀረጥ አማካይነት ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ በመሰማራት፣ ለምሳሌ መንገዶችን፣ የባቡር ሃዲዶችን፣ ትምህርትቤቶችን፣ ሆስፒታሎችንና ሌሎችንም የሶሻል ፕሮጀክቶችን በመስራትና በመደገፍ አብዛኛው የምርት ክንውን በግለሰብ ካፒታሊቶች የሚካሄድ ሊሆን ችሏል። ከዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ አካሄድ ስንነሳ በጊዜው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር። የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጽንሰ-ሃሳብ ከታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ በጆን ማይራድ ኬይንስ የፈለቀ አስተሳሰብ ሲሆን፣ የእሱም አስተሳሰብ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ዕድገት ዝቅና ከፍ በማለት የሚገለጽ ስለሆነ፣ በዚህም ምክንያት የሚከሰተውን የስራ አጥ ቁጥር መጨመር ማስወገድ የሚቻለው በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስተካከል አይቻልም የሚል ነው። የኬይንስ አስተሳሰብ ንጹህ በንጹህ የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን የሚቃወም ነው።  ይህም ማለት የአይኤምፍንና የዓለም ባንክ የንጹህ ገበያ ፖሊሲን  የሚቃወም ነው። እዚህ ላይ መያዝ ያለበት ጉዳይ በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የኤይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በፍጹም አይታወቁም። የተቋም ማስተካከያ ፖሊሲ(Structural Adjustment Programs) በመባል የሚታወቀው “የኢኮኖሚ ፖሊሲ” የረቀቀው በ1980  ዓ.ም ሲሆን, የተረቀቀውም በአፍሪካውያን ኢኮኖሚስቶች የአፍሪካን ኢኮኖሚ በሌላ መልክ ለማሳደግ ተብሎ በ1980 ላይ  በሌጎስ ከተማ የቀረበውን አማራጭ ፖሊሲ ለመቃወም ነው።

ለማንኛውም በዶ/ር እዮብ ተስፋዬም ሆነ በአቶ ሚሊዮን ዘአማኑኤልና በጽዮን ዘማርያም የቀረቡትን ተከታታይ ጽሁፎች ስመለከት በመጀመሪያ ደረጃ የአይኤምኤፍንና የዓለም ባንክን የተቋም ማስተካከያ ፖሊሲ(Structural Adjustment Programs)   እንዳለ በመውሰድ ሳይሆን የሚተቹት ፕራይቬታይዜሽንን ብቻ ነው። የዋጋ ግሽበትንም ሁኔታ ስንመለከት ጸሀፊዎቹ የትችታቸው መሰረተ-ሃሳብ የገንዘብን በብዛት መታተምና በኢኮኖሚው ውስጥ መፍሰሱን ብቻ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በየጊዜው እንዲቀነስ መደረጉ በዋጋ ግሽበት ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለማሳየት አልቻሉም። ይህ ዐይነቱ ተከታታይ የገንዘብ ቅነሳ በማምረቻ ዋጋ (Production Cost) ላይ ያለውን ተፅዕኖ ግንዛቤ ወስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በየጊዜው እንዲቀንስ የሚደረግ ከሆነ የማምረቻ መሳሪያዎችን፣ ጥሬ ሀብቶችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን በዶላር እየገዙ ወደ አገር ቤት የሚያስገቡ አምራቾችና ነጋዴዎች፣ ቀድሞ አንድ ዶላር ለመግዛት 2, 05 የኢትዮጵያ ብር የሚያቀርቡ ከሆነ፣ ገንዘባችን እንዲቀነስ ከተደረገ በኋላ በዛሬው ምንዛሪ አንድ ዶላር ለመግዛት እስከ 50 የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ አለባቸው ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ የሚችለው ሲለውጥ፣ ለመግዛት የማይችለው ደግሞ የማምረት ኃይሉን እንዲቀንስ ይገደዳል ማለት ነው። በዚህ መልክ የማምረቻ ዋጋ ሲጨምር፣ ምርት ወደ ገበያ ላይ ወጥቶ በሚሸጥበት ጊዜ ዋጋውም ይወደዳል ማለት ነው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ጸሀፊዎቹ ይህንን መሰረታዊ ለዋጋ ግሽበት ዋናው ምክንያት የሆነውን ጉዳይ በፍጹም አያሳዩም። እንደዚህ ዐይነት የገነዘብ ቅነሳም ከአገራችን በስተቀር በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ተስምቶም ታይቶም አይታወቅም።  ለማንኛውም የተቋም ማስተካከያ ተብሎ የሚጠራውን የአንድን አገር ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ እንዲገነባ የማያደርገውን ፖሊስ ስንመለከት ፖሊሲው በፕራይቬታይዜሽን ላይ ብቻ የሚያበቃ አይደለም።  የተቋም ማስተካከያው  ቢያንስ አራት መሰረታዊ ነገሮችን የያዘ መሆኑን እንመለከታለን። እነዚህም፣ 1ኛ) የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር መቀነስ (Devalutaion)፣ 2ኛ) የአገሪቱን ገበያ ለውጭው ንግድ ክፍት ማድረግ(liberalaization) 3ኛ) ድጎማን ማስወገድና ገበያው በአቅራቢና በጠያቂ መሰረት እንዲደነገግ ማድረግ፣ 4ኛ) የመንግስት ሀብትን ለግለሰብ ሃብታሞች መሽጥ (Privatization) …ወዘተ. የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ ነገሮች ተነስተው ያመጡት ውጤቶችና ያስከተሉት አሉታዊ ተጽዕኖዎች አንድ በአንድ አልተዘረዘሩም። በተለይም የእይምኤምፍን ፖሊሲ ስንመለከት ዋናው ዓላማቸው የአንድ አገር የኢኮኖሚ ችግር በመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚፈታ ሳይሆን ንጹህ በንጹህ በገበያ ኢኮኖሚ ክንዋኔ አማካይነት ነው የሚል ነው። በኢኮኖሚ ፖሊሲው አማካይነት አንድ አገር ወደ ገበያነት መለወጥ ያለባት እንጂ ማህበራዊና ባህላዊ፣ እንዲሁም ህብረተሰቡን የሚያያዙ ልዩ ልዩ እሴቶች የሚፈጠሩባቸውና  የሚከናወኑባቸው አይደሉም። ሁሉም ነገር ገንዘብ በማግኘት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ሁሉም ነጋዴዎች መሆን አለባቸው የሚል ነው። ከዚህም በላይ በፖሊሲው መሰረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ማኑፋክቸሪንግ ቦታ የላቸውም። ዋናው ነገር የንግድ እንቅስቃሴ መኖር ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ዕምነትና አካሄድ ደግሞ በጣም አደገኛ ሲሆን፣ በተለይም እንደነ አርስቲቶለስ በመሳሰሉት ፈላስፋዎች የተተቸ ነው። ምክንያቱም በገንዘብ ላይ የተመሰረተ ማንኛውም ዐይነት ግኑኝነት የአንድን አገር ሞራልና ባህላዊ ግኑኘነቶ እንዳለ ስለሚያናጋና ወንጀለኞች እንዲፈለፈሉ ሰለሚያደርግ ነው። ይህም አካሄድ በአገራችን ምድር ባለፉት 30 ዓመታት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በገንዘብ አማካይነት ሰውና የሰው ኦርጋኖች የሚገዙበት አገር ለመሆን በቅቷል።

ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ስንመጣ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የኬይንስን የመጀመሪያውን አስተሳሰብ፣ የመንግስትን ጣልቃ-ገብነት በማስወገድ ሁሉንም ነገር ወደ ፊስካልና ወደ ሞኔተሪ ፖሊሲ ለውጠውታል። በእነሱ አስተሳሰብም መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ምንም የሚያገባው ነገር የለም የሚል ነው። ሀቁን ስንመለከት ግን በማንኛውም የካፒታሊስት አገር የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ካለመንግስት ጣልቃ-ገብነት የሚንቀሳቀስ ነገር በፍጹም የለም። በተለይም እንደ 2008 ዓ.ም የፋይናንስ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ የመንግስታት ሚና በግልጽ ይጠየቃል፣ ይታያልም።

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመጣ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚለው አከራካሪና ተጨባጩንም የአገራችንን የኢኮኖሚና የማህብራዊ ሁኔታ እንድንመለከትና እንድናነብ የሚረዳን አይደለም። ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይንስ ነው ብለን የምንቀበል ከሆነ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንድናነብ የሚረዳ መሆን አለበት። ስለሆነም ችግሮችን በሚገባ እንድናውቅና  ፍቱን መፍትሄም ለመፈለግና ለማቅረብ የሚረዳን መሆን አለበት። እነ ኤይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ፖሊሲ ግን የሁሉም አገር ኢኮኖሚና የዓለም ህዝብ ፍላጎቶች በሙሉ ተመሳሳይ ስለሆኑ በሁሉም አገሮች ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ፖሊሲ አንድ ዐይነት ብቻ ነው ከሚለው የሚነሳ ነው። ይህም ማለት  የሁሉም ሰው በሽታ ተመሳሳይ ስለሆነ ምንም ዐይነት ምርምር ሳይካሄድ አንድ ዐይነት መድሃኒት ብቻ ይታዘዝለት እንደማለት ነው።

ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ አካሄድ ፀረ-ሳይንስ ነው። ሁሉም አገሮች ተመሳሳይ በሽታ ሊኖራቸው አይችልም። ለምሳሌ የአገራችን ዋናው ችግር ድህነትና ረሃብ ናቸው።  ይህ ደግሞ በየጊዜው የሚከሰተው አገራችን የተትረፈረፈ ሀብት እያላት ነው። ይህ ዐይነቱ ቀውስም የሚከሰተውምና አብዛኛው ህዝባችንም በድህነት ዓለም ውስጥ የሚኖረው ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ሳይንሳዊ ስላልሆኑ ብቻ ነው። ስለሆነም ነው የእነ አይኤምኤፍ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ  ጀምሮ የደህነቱ መጠን እየጨመረ የመጣው። በአዲስ አበባ የሚኖረው የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ከቆሻሻ ቦታዎች እየለቀመ እንደሚመገብና እንደሚኖር የተረጋገጠ ነው። ባለፉት ስለሳ ዓመታት ቁጥራቸው የማይታወቁ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች እንደ አሸን ፈልቀዋል። ይህ በአንድ በኩል እያለ፣ በጣም ጥቂት የሆነው የህብረተሰብ ክፍል የናጠጠ ሀብታም ለመሆን በቅቷል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ደግሞ በፈጠራና በአምራጭ ኢዱስትሪዎች ውስጥ የሚሳተፍ ሳይሆን ሆቴልቤቶችን በመስራትና በንዱ ዓለም ነው። እንደሚታወቀው የአንድ አገር የኢኮኖሚ መስረት ደግሞ በማምረት ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በማኑፋክቸሪን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚመካ መሆን አለበት። እነዚህም ደግሞ ዋና ዓላማቸው የውስጥ ገበያና በአስተማማኝ መልክ ማስፋፋትና ማዳበር መሆን አለበት። ከዚህም በላይ የከታማዎች ግንባታ፣ የባቡር ሃዲድ ግንባታና የተቀላጠፉ የተቋማት ግንባታ የግዴታ ለአገር ውስጥ ገበያ መዳበር አስተማማኝ ይኖሉ። ምክንያቱም የአንድ አገር ኢኮኖሚ በቦታባ በጊዜ (Space and Time) ብቻ ተግባራዊ ስለሚሆንብቻ ነው። ስለቦታ ስናወራ በደንብ ወይም በስርዓተ የተገነባ ከተማ ሲሆን፣ ጊዜ ደግሞ ዕቃዎችንንም ሆነ ሰውን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ለማመላለስ የሚጠቅም መለኪያ ነው። በሌላ አነገጋገር አንድ አገር በኢኮኖሚ ማደግ የምትችለው የተቀላጠፈ የትራንስፖርቴሽን ሲይስተም ሲኖራት ነው። ከዚህ ስንነሳ ዶ/ር ኢዮቭም ሆነ አቶ ሚሊዮን ዘአማኑኤልና ጽዮንን ያሳሰባቸው የህዝባችን የኑሮ ሁኔታ ሳይሆን፣ ለምሳሌ የተሟላ ዴየት ማግኘት፣ የንጹህ ውሃ ጉዳይ፣ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ፣ የትምህርት ቤት ጉዳይ፣ የህክምና ጉዳይ፣ የስራ መስክ ጉዳይና፣ ከዚህ ጋር የተያያዘው የአገር ግንባታ ጉዳይ ሳይሆን፣ አበስትራክት የሆኑ ከህዝባችን ኑሮ ጋር በምንም መልክ የማይገናኙ የማይክሮ ኢኮኖሚ ነገሮች ናቸው።

ሌላው የእነ አይኤምፍ  ፖሊሲ ፀረ-ሳይንስነቱ ሴተሪስ ፓሪቡስ፣ ወይንም ሁሉም ነገሮች እንዳሉ ሆነው ወይም ሳይነኩ፣ መለወጥ ወይም መሻሻል ያለበት ነገር የኢኮኖሚው ሁኔታ ብቻ ነው የሚል ነው። ይህንን አካሄድ ፈላስፋዎች ፖዘቲቭ ሳይንስ ብለው የሚጠሩት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ከዚህ ስንነሳ የመንግስትን ምንነትና ሚና፣ ጨቋኝና በዝባዥ መንግስት ይኑር አይኑር፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጉዳይና ሌሎችም የማህበራዊ ጥያቄዎችን አይኤምኤፍንና የዓለም ባንክን በምንም አያሳስባቸውም ወይም አያውቋቸውም። የዶ/ር እዮብና የእነ አቶ ሚሊዮን ዘአማኑኤልም አካሄድ እየፈራሁ ይህንን የሚመሰል ነው። ስዚህ ነው የአይኤምኤፍንና የዓለም ባንክን ፕሮግራም እንዳለ በመውሰድ አንድ በአንድ ለመተቸት የማይቃጡት። መልካም ግንዛቤ

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ሰፋ ላለ ጥናት በድረ.ገጼ ላይ የወጡትን የኢኮኖሚ ጽሁፎች ተመልከቱ

www.fekadubekele.com

https://zehabesha.com/the-greatest-confusion-and-deception-of-all-time-duty-free-or-free-trade-policy-cannot-solve-the-complicated-problems-of-african-countries/

https://zehabesha.com/i-cant-eat-gdp-why-numbers-dont-matter-fekadu-bekele-ph-d/

የኢኮኖሚን ዕድገት በደንብ ለመረዳት እነዚህን ከታች የተጠቀሱትን መጻህፍት አንብቡ፡

1ኛ) የማርክስ ዳስ ካፒታል ሶስቱም ቅጾች ሊታለፉ የሚገባቸው አይደሉም፣

2ኛ)Reinert S. Erik; How Rich Countries Got Rich… Why Poor

Countries Stay Poor, London, 2007

3)  Raworth, Kate;  DOUGHUNT Economics: Seven Ways to Think Like

a 21 st-Century Economist, London 2017

4ኛ) Keen, Steve; Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned? London, 2011

5ኛ) Sedlacek, Thomas; Economics of Good and Evil, New York, 201

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop