ከኡመር ሽፋው (August 20, 2022)
የቀድሞው ግንቦት 7 በቁጥጥሩ ሥር ያዋለው ኢዜማ ምናልባት በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ የሕዝብን አደራ በመብላት ወደር የሚገኝለት አይመስለኝም። ኢዜማ በሚመሩት ሰዎች ያለፈ መልካም ታሪክ ምክንያት ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌና የሺዋስ አሰፋ እና ሌሎችም በሕወሃት ጊዜ በመታሠር በከፈሉት መስዋዕትነት ምክንያት ማንም ዛሬ የዋሉበት ቦታ ይውላሉ ብሎ የገመተ አልነበረም። እነዚህ የትናንት ባለመልካም ታሪኮች የቆሙለትን ዓላማ አሽቀንጥረው ጥለው፣ አማራውን በሚያርድና በሚያሳርድ፣ በሚያፈናቅልና በሚያስፈናቅል፣ እንዲሁም በማንነቱ ከመንግሥት ተቋማት በሚያባርር ጥንፈኛ፣ ፋሽስታዊ፣ ተረኛና ዘረኛ መንግሥት ሥር አገልጋይ ይሆናሉ ብሎ በሕልሙም በእውኑም የጠረጠረ አልነበረም። ዛሬ እነዚህ የኢዜማ አመራሮች ከአብይ አህመድ፣ ከሽመልስ አብዲሳ፣ ከአዳነች አበቤ ባልተናነሰ መልክ አጋጣሚ ባገኙበት ጊዜ ሁሉ በመግለጫም ሆነ በቃለምልልስ በአማራውና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስቆቃ ላይ ሲያሾፉና ሲሳለቁ እየተሰሙ ነው።
በቅርብ ጊዜ አቶ የሺዋስ አሰፋ በኢትዮ 251 እንግዳ ሆኖ ቀርቦ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ በትዕቢት የተሞላና “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከደጅ ታሳድራለች” የሚለውን አባባል የሚያስታውስ ነበር። ለአቶ የሺዋስ የቀረበለት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል ወይም እየተፈጸመ ነው ብለው የሚያምኑ አሉ፤ አንተስ ታምናለህ ወይ የሚል ነበር። የሰጠው መልስ “ምን ዓይነቶች ናቸው እንደዚያ የሚያምኑት? ‘ስለዘር ማጥፋት’ ሙያው ያላቸው? ዕውቀቱ ያላቸው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ እኔ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል ወይም አልተፈጸመምም የሚሉት ሁለቱም ትክክል አይደሉም ብዬ አምናለሁ፤ ጉዳዮ ለባለሙያዎች መተው አለበት ብሎ ደመደመ። አቶ የሺዋስ አሰፋ በዚህ መልክ መልስ በመስጠት እነአብይ አህመድን ከዘር ማጥፋት ወንጀል ነፃ ለማውጣት የቱን ያህል እርቀት እንደሚሄድ ቢያሳየንም በተጨማሪ ከዘር ማጥፋት ወንጀሉ ጋር በተያያዘ ኢዜማም ሊጠየቅ እንደሚችል በውስጡ ስላመነ እራሱንና ባልደረቦቹን ለመከላከል እንደሆነ ግልጽ ነው።
በእርግጥ የኢዜማ አመራሮች ገጀራ አንግበው ታይተው አያውቁም፣ የአብይ አህመድ ሪፐብሊካን ዘበኞችና ኦነግ ሸኔ የታጠቁትን ከብዙ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ግንባር የሚበትነውን ጠብመንጃ ታጥቀው አልታዩም። ነገር ግን የአማራን ዘር በማጥፋት እጁ በደም የተጨማለቀውን የኦሮሙማን መንግሥት ዕድሜ ለማራዘም በሚጫወቱት ሚናና የዘር ማጥፋቱን ወንጀል ለማድበስበስ በሚያደርጉት ሙከራ ወደዱም ጠሉም ከመጠየቅ አያመልጡም። ከኦሮሙማ ጋር ያጣበቃቸውም ይኸው ሃቅ ነው። ስለሆነም የኢዜማ ህልውና ከአብይ አህመድ በሥልጣን ላይ መቆየት ጋር የተቆራኘ ነው። የኢዜማ ዕድሜ የሚለካው በአብይ አህመድ መሰንበትና አለመሰንበት ነው። አብይ አህመድ ወይም ኦሮሙማ የሚያከትሙበት ቀን ሲመጣ አንዱዓለም አራጌ እንደተመኘው የተከዳው ሕዝብ የኢዜማን አመራሮች በአርጩሜ ብቻ ቸብቸብ በማድረግ አያልፋቸውም። የሚነርታቸው እጅግ በሚያምና ለሌሎች ትምህርት በሚሰጥ ዱላ ነው። በነገራችን ላይ አርጩሜ አባት የሚወደውን ልጁን መስመር የሚያሲዝበት እንጂ ወገን የከዱ ስብስቦች የሚቀጡበት አይደለም።
ለብዙ ዓመታት ታግለን፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለን፣ ታሥረን፣ ተገድለን፣ ተሰደን፣ ወላጆቻችንን በሃዘን እንዲገረፉ አድርገንና ጧሪ አሳጥተን፣ ተርበንና ተጠምተን፣ አካለጎዶሎ ሁነን፣ ልጆቻችንን ያለአሳዳጊ አስቀርተን በመጨረሻ አረመኔውን ሕወሃትን ከተገላገልን በኋላ እንደአብይ አህመድ ያለ የሕፃናት መታረድ ግድ የማይሰጠውና፣ ስብእና የጎደለው ሰው አራት ኪሎ መግባት እጅግ አለመታደል ነው። በዚህ ላይ ከመሃላችን የወጣ እንደኢዜማ ያለ በዜግነት ፖለቲካ የሚነግድ ከሃዲ ስብስብ ሲጨመርበት እጣ ፋንታችንን የአለመታደል ጥግ ያደርገዋል። እኛ ኢትዮጵያውያኖች በረዥሙ ታሪካችን ውስጥ ብዙ መከራ ያስተናገድን ቢሆንም ይህ አሁን ያለንበት ግን የተለየና የብቻው ነው። ቃላቶች በሕብረት አይገልጡትም። እኔ በግሌ የወደፊቱን ሳንቆጥር በአብይ አህመድ አገዛዝ ሥር ባለፈው አራት ዓመት ብቻ በወገናችን ላይ የደረሰው መከራ ከዛ በፊት ባለው መቶ ሃምሳ ዓመት ከደረሰበት መከራ ይበልጣል የሚል እምነት አለኝ። በሌላ አነጋገር ዕድሜ ለኦሮሞ ብልጽግና፣ ለአማራ ብልጽግናና ለኢዜማ፣ ወደድንም ጠላንም፣ በሕወሃት ሥር ያሳለፍነውን ሃያ ሰባት ዓመት የመከራን ዘመን እጅግ አቅልለን የምናይበት ጊዜ ላይ እንገኛለን።
አካፋን አካፋ ማለት ስላለብን፣ ኢዜማ የወገን መከራ አዋላጅ፣ የስቃይ አመቻችና የግፍ ደንገጡር ነው። ሃገሪቱን አሁን ላለችበት አስከፊ ሁኔታ ያበቃትን አብይ አህመድን ያሻግረናል፣ ሙሴያችን ነው ያለው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ዛሬም አመለካከቱ አልተለወጠም። የተወደደለት ይመስል እየገፋበት ነው። ባለፈው የኢዜማ ፓርቲ ጉባኤ ላይ እንደምንም ተሟሙቶ ሥልጣኑን ካስጠበቀ በኋላ፣ ዶ/ር ብርሃኑ የኢዜማን የኦሮሙማ ሎሌነት ከፍተኛ እርከን ላይ ሰቅሎታል ማለት ይቻላል። ዛሬ የኦሮሞ ብልጽግናና ኢዜማ ግንኙነታቸው ድንበር የለሽ ስለሆነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጨፌ ኦሮሚያ ላይ አይገኝ ይሆናል እንጂ አብይ አህመድ በሚሄድበት ቦት ሁሉ እንደማይጠፋ በመደጋገም አይተናል። ከአሁን ቀደም አንድ ወዳጄ አብይ አህመድ “ሙሴ” ከሆነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሙሴ ትልቅ ወንድም “አሮን” መሆኑ ነዋ ብሎ እንደቀልድ ነግሮኝ ነበር።
ከአንድ ወር በፊት ዶ/ር ብርሃኑ በኢሳት ሚድያ “ሞጋች” በሚሉት ፕሮግራማቸው ቀርቦ ነበር። ዶ/ር ብርሃኑ በቃለ ምልልሱ ላይ “በመግለጫ ቁጥር ከሆነ የሚበልጠን የለም” ሲል ኢዜማ በመግለጫዎቹ ላይ ስህተት ናቸው ብሎ የሚያነሳቸውን ተከታትሎ ስለማስፈጸሙ ማስረጃ አቅርቦ አይቼ አላውቅምና ፓርቲው የመግለጫ ጋጋታን እንደግብ እንደሚቆጥር ተረዳሁ። “መንግሥትን እየደገፍን ስህተቶቹን እንጠቁማለን” ሲል ሁላችንም የምናውቀውን ኢዜማ ማለት ብልጽግና ማለት እንደሆነ አረጋገጠልኝ ። ዶ/ር ብርሃኑ ቀጥሎ “የአገር ሕልውናና ፖለቲካ መለየት አለበት” ሲል የአገሪቱን ገዳይ ኦሮሙማን ለአገሪቱ ሕልውና ያስፈልገናል እያለን ነው። ቀጥሎ “አገር ከፈረሰ በኋላ ፖለቲካ የለም” ሲል እሱ “ሙሴ” የሚለው አብይ አህመድ በዘር ፖለቲካ አገር እያፈረሰ መሆኑን ሊሸፍንለት እንደሞከረ ስለገባኝ አልደነቀኝም። “መቃወም የጉብዝና ምልክት ተደርጎ ይታያል….ብዙ ሰው አበደ ብለህ አታብድም” ሲል በጣም አዘንኩ! በዶ/ር ብርሃኑ እሳቤ የወገናችንን ስቆቃ የምናሠማ ሁሉ አማኑኤል መግባት ያለብን እብድ ነን ማለት ነው። የተሟላ ጤና ያላቸው እነሽመልስ አብዲሳና እነአዳነች አበቤ መሆናቸው ነው። ዶ/ር ብርሃኑ ቀጥሎ በቃለ ምልልሱ ላይ የኢዜማ ጠላቶች የብሄር ፖለቲከኞች ናቸው፣ አዲስ አበባ ላይ መቀመጫ ያላሸነፍነው የብሄር ፖለቲከኞች ስለዘመቱብን ነው ባለ ጊዜ ለቅጽበት ተደናግሮኝ ነበር። ቢሆንም ኢዜማ የብሔር ጥንፈኛውን፣ ሰልቃጩን፣ አፋኙንና የውሸት ትርክት ባለቤቱን ኦሮሙማን አቅፎና ደግፎ እሽሩሩ እያለና አገር እያስፈረሰ በሌሎች “ብሔርተኞች” በሚላቸው ላይ ጣቱን የመቀሰር የሞራል ብቃት እንደለለው አጥብቄ አምናለሁ።
ዶ/ር ብርሃኑ የኦሮሞ ብልጽግናን ጉድ ለመሸፈን ያልወጣው አቀበትና ያልወረደው ቁልቁለት የለም። ዶ/ር ብርሃኑ የአብይ አህመድን ምርጫ አስመልክቶ “የብልጽግና ፓርቲ የተመረጠው ሕዝቡ ደህንነቴን ያስጠብቅልኛል ብሎ ስላመነ ነው” ይለናል። ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ ከምርጫው ወዲህ የታዘብነው ግን የአብይ መንግሥት ሕዝቡን ሰላም ሲነሳው ነው። ዶ/ር ብርሃኑ ቀጥሎ “በመንግሥትና በፓርቲ መጣበቅ ምክንያት” ስላለው ችግር ያወራና እራሱን በመቃረን “ከብልጽግና ሳይሆን የምንሠራው ከመንግሥት ጋር ነው… ይህ መንግሥት ከፓርቲው ይለያል” ይለናል። የሆነው ሆኖ ቀደም ሲል የግንቦት 7 መሪ በነበረበት ጊዜ ወደዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ብቅ ሲል በዕውቅ የሆቴሎች አዳራሾች ውስጥ እንደ ርእሰ መንግሥት እንቀበልው የነበረ ሰውና የሚመራው ድርጅት ጉዞ ይህን ይመስላል ብለን አልጠበቅንም ነበር። እጅግ ያማል!
ኢዜማ ከኦሮሙማ ጋር በሞጋሳ መጠቃለሉ የሚያከራክር አይደለም። ሰሞኑን ኦሮሙማ በአዲስ አበባ ላይ የሚፈጸመውን ሸራርፎ የመሰልቀጥ እርምጃም ሆነ በደብረብርሃን በኩል ከአማራ ክልል የሚመጡ አማሮችን አዲስ አበባ እንዳይገቡ የመከልከልን ጉዳይ አስመልክቶ የኢዜማ አሻራ አይታየኝም የሚል ካለ በደምብ ቢመለከት ጥሩ ነው። የደቡብ ክልል ርእሰ ብሔር አቶ እርስቱ ይርዳው በቅርቡ ዋሺንግተን ዲሲ መጥቶ በነበር ጊዜ ከኦሮሞዎች ጋር ካልተደመርን አያዋጣንም፤ መንገዱን ሁሉ ይዘጉብናል አለ የተባለው ላይ የኢዜማ አሻራ የለበትም የሚል ካለ እራሱን ከማታለል አባዜ ይውጣ። ኢዜማ እስከአሁን የሚከተለው አቅጣጫ ቁሜለታለሁ ከሚለው የዜግነት ፖለቲካ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ዛሬ ላይ ስንገመግመው የዜግነት ፖለቲካንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም ሌሎች ስሙን ሳይይዙበት ቀድሞ ያስመዘገበና አመሠራረቱ ላይ የእነሌንጮ ለታ እጅ ያለበት አቀባባይ ተረኛ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል።
የኢዜማ አመራሮች የኦሮሙማ አገልጋይና አይዞህ ባዮች በመሆናቸው በወገናችን ላይ የሚደርሰው ግፍ ወገቡን እያጎበጠውና ጉልበቱን እያዛለው ነው። ስለሆነም በኢዜማ ምክንያት ወደፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ እኩልነትና ፍትህ ለማስፈን የሚከፈለው መስዋዕትነት ሕወሃትን ለማውረድ ከከፈልነው መስዋዕትነት በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ልንገነዘብ ይገባል። የኢዜማ አመራሮች ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዱዓልመ አራጌ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ እንዲሁም ከነሱ ጀርባ 24 ሰዓት የሚሠሩት እነአቶ ነአምን ዘለቀና አንዳርጋቸው ጽጌ የመሳሰሉት ሃገራችን ለምትገኝበት ውጥንቅጥ በተለይም ለአማራው ስቆቃ ተጠያቂዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም አማራውና አዲስ አበቤ ኢዜማን የህልውናው ጠላቶች ከሆኑት ኦሮሙማ፣ የአማራ ብልጽግናና ሕወሃት ተርታ ሊያሰልፈው እንደሚገባ መጠቆም ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል። የወገናችን መከራ አዋላጅና የግፍ ደንገጡር የሆነውን ኢዜማን በየመድረኩ ልንረባረብበት ይገባል። ኢዜማን መታገል የአብይ አህመድን ሥርዓት መታገል ማለት ነውና!