የሰሜን ኢትዮጰያው ጦርነት ድርድርና የአደራዳሪዎቹ ማንነት ያስከተለው ተስፋና ስጋት – አክሊሉ ወንድአፈረው

ነሀሴ 1. 2014  (August 7, 2022)
አክሊሉ ወንድአፈረው (ethioandenet@bell.net)

በብልጽግና የሚመራው በኢትዮጵያ መንግስት እና ሀወሀት መሀል ለሚደረገው ድርድር  እስካሁን ሂደቱን  ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ህብረት  ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሀወሀት ድርድሩን  ይመሩ የነበርቱት ኦባሳንጆን ወደ ኢትዮጸያ መንግስት ያዘነበሉ ወገንተኛ ብቻ ሳይሆኑ ዝገምተኛም ናቸው በማለት እርሳቸው ከአደራዳሪነት እንዲነሱና  በመትካቸውም የኬንያው ፐሪዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪ እንዲሆኑ  በቃል አቀባያቸው እና በተለይዩ መግለጫዎቻቸው በኩል አሳውቀዋል፡፡፡

ይህ የሀወሀት ፐሬዚደንት  ኡሁሩ ያደራድሩን የሚለው አቋም በኢትዮጸያ መንግስት በኩል በቀጥታ አይሆንም  የሚል መልስ ባይሰጥበትም  ደግሞ ደጋግሞ ድርድሩ መካሄድ ያለበት በአፍሪካ አንድነት ሰር ነው የሚለውን  አ ቋሙን  ግን ሲያሰማ ቆይቷል ፡፡

የአውሮፓ ፣ የአሜሪካና  የተባበሩት መንግስታትም ለረዝም ጊዜ ሲነግሩን የነበረው እነርሱ  የሚደግፉት ድርድሩ በአፍሪካ ሀብረት በኩል መሆን እንደሚገባው የሚያመላከት ነበር፡፡ ያም ሆኖ የፐሪዚደንት  ኡሁሩን  ወደ አደራዳሪነት መምጣት ሲቃወሙ አልተሰማም፡

በ ሀምሌ 24፣ 2014 ወደ መቀሌ ተጉዞ የነበረው የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የምስራቅ የአፍሪካ ልዩ ልኡካን ይህን የአደራዳሪነት ሚና በተመለከት  ድርድሩ በአፍሪካ  ህብረት በኩል መሆን እንደሚገባው  እንደሚያምኑ አሳውቀው ነበር፡፡

በ ሀምሌ 30፣ 2014  (August 6, 2022)  በሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛ እትም እንደተዘገበው በአዲስ አበባና መቀሌ ተከስተው የነበሩት እነዚህ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና፣ የተባበሩት መንግስታት ልኡካንንና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ኮሚቴ አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ስብሰባ  የድርድሩ ሂደት በቀጣይነት በአፍሪካ ህብረቱ ተወካይ በኦባሳንጆ  ስብሳቢነት እንዲካሄድ አሚሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ደግሞ  በአደራዳሪው ቡድን ወስጥ እንዲካተቱ  የሚል ወሳኔ እንዳስተላለፉ ይፋ ሆኗል፡፡

AU Accommodates UN, EU To Broker Peace Between TPLF, Federal Government | The Reporter | Latest Ethiopian News Today (thereporterethiopia.com)

ይህ አዲስ ክስተት  በአጠቃላይ ፍትሀዊና ውጤታማ የድርድር  ሂደት አንጻር ሲመረመር የሚኖረው ጠቀሜታና ጉዳት በአጠቃላይም እንደምታው ምን ሊሆን ይችላል፣ ምንስ ያስከትላል ብሎ መመርመር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ይህ ጽሁፍም ይህንኑ ይቃኛል፡፡ በማስከተልም የተሻለ ወጤት ለማስገኘት የሚያግዙ ምክረ አሳቦችንም ያቀርባል፡፡

አሽማጋዮች ወይም  አደራዳሪዎች ከወገንተኘነት የራቁ ራሳቸውንም ያወቁ የመሆን አስፈላጊነት

የቅራኔ አፈታት አዋቂዎች በተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታት አሸማጋዮ ወይም አደራዳሪዎች ወጤታማ ለመሆን ከሚይስፈልጓቸው ጉዳዮች ውስጥ  አንዱና ቁልፉ ጉዳይ ራስን ማወቅ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡

አሽማጋዮች  ተጻራሪ ተደራራዲዎችን የማቴርያል የዲፐሎማሲ ወዘተ ድጋፍ በመስጠት ፣ የድርድር የሚሆን ወጪን በመሸፈን ሰለ ድርድር አካሄድ እውቀትን በማካፈል ወዘተ ሊያበረክቱት የሚችሉበት ብዙ ጉዳይ እንዳለ ሁሉ  አደራዳሪዎች የሚወክሏቸው መንግስታትና ድርጅቶች የቀደመ ወገንተኛነት፣መኖር   በድርድሩ ሂደት ነጻነትና፣ ተቀባይነት ላይ ታላቅ ተጸእኖ እንደሚኖረው ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

በመሰረቱ አሽማጋይ ወይም አደራዳሪነት  በተለይም በአለም አቀፍ ቅራኔ አፈታት ወስጥ  በከፊል የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑን በግንዛቤ ውስጥ ማሰገባት ያስፈልጋል፡፡ መንግስታት ወይም ድርጅቶች በድርድር ሂደት በአሽማጋይነት ሲሰለፉ የራሳቸውን የውጭ ጉዳይ ጥቅም  በግንዛቤ ወስጥ አስገብተው እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አንዳንዱ አሽማጋይነት ውጤታማ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስገኘትም ታላቅ አስተዋጸኦ እንደሚኖረው ሁሉ አንዳንዱ ደግሞ  በተፋላሚወች  የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ሁኔታውን አወሳስበው፣ እጅግ አስቸጋሪ  ምስቀልቀልን  በመፈጠር ይበልጥ ጥፋትን ሊጋብዝ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሀያላኑ በአደራዳሪነት የሚሰለፉት ለችግሩ ቋሚ መፍትሄን ፤ለማስገኘት ሳይሆን የሚታየው ግጭት ከሚገኛበት ደረጃ አልፎ ሰፋ ያለ ጥፋትን ሳያስከትል ባለበት ደረጃ እንዳለ እንዲቆይ ለማድረግም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌም በኮሶቮና በቦስንያ በ 1990 ወቹ መጨረሻ የሀያላኑ አላማ በከፊል ይህ ነበር፡ ለማለት ይቻላል፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአውሮፓ አቆጣጠር በ2012 ይፋ ባደረገው ዶክመንት በቅራኔ አፈታት ውስጥ  የአሽማጋይነት ሚናን ወጢታማ ለማድረግ ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው ብሎ ካቀረባቸው ስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ፣ የአሽማጋዮች ገለልተኛነት፣ (impartiality)  በተደራዳሪ ወገኖች በኩል  የአሸማጋዮች ተቀባይነት ማግኘት  (consent ) የሽምግልናው ሂደት ሀገር በቀል በሆነ  ባለቤትነት መመራቱ  (national ownership ) የሚሉት ሶስቱ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡UN Launches Guidance to Ensure Effective Conflict Mediation – Mediate.com

ተጨማሪ ያንብቡ:  የካቲት ሄደ የካቲት መጣ - አንዱ ዓለም ተፈራ

በዚህ አንጻር በሀገራችን የሰሜን ክፍል የተፈጠረውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት በአዲስ መልክ በአደራዳሪነት የተጨመሩት የአሜሪካ መንግስት፣ የአውሮፓ ህብረትንና የ ተባበሩት መንግስታት  አቋም ምን ይመስላል? ለመሆኑ በዚህ  ግጭት ውስጥ እነዚህ ክፍሎች ገለልተኛ ናቸውን ፣ ድርድሩን በገለልተኛነት መምራትና ተአማኒ ሊሆኑስ ይችላሉን ለድርድር በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ ሊያስፈጽሙት የሚፈልጉት አቋም አላቸውን  ይህን የአደራዳሪነት መድረክ ተጠቅመው የነርሱን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርጉት አካሂድስ ከሀገራችን ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል ፣ ለመሆኑ  የመራባውያኑ የአድራዳሪነት መታከል የሁሉንም ተቀባይነት አግኝቷልን፣ የድርድር ሂደቱንስ፣ ሀገር በቀል ወይም አህጉራዊ ባለቤትነት እንዲኖረው ያድርጋል ወይንስ አሳልፎ ለመራብ ሀገሮች ይስጣል የሚሉትን ቀረብ ብሎ ማየት ያስገልጋል፡፡

የአደራዳሪዎቹና እጩ አደራዳሪዎቹ  አ ቋም ሲመዘን

የአሜሪካ መንግስት

የአሜሪካ መንግስት ከስሜኑ ጦርነት እየገፋ መምጣት ጋር ተያይዞ ጦርነቱ እንዲቆምና ችግሩንም ተፋላሚዎቹ ወገኖች በስላም እንዲፈቱ የሚል  እወጃ ሲያሰማ የቆየ ቢሆንም፣ በድርድሩ ውስጥ ዋና ዋና በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ግልጽ አቋም ይዞ ይህ መደረግ አለበት የሚላቸውን ለማሰፈጸም በተለይም በኢትዮጰያ መንግስት ላይ ከፈተኛ ተጸእኖ ሲያደርግ ቅይቷል፡፡አሁንም እያደረገ  ነው፡፡  ከነዚህ ተጸኖዎች ውስጥ የተለያየ መእቀብ መጣል፣ የጸጥታ ትብብርናና  የበጀት ድጎማን መከልከል እና በተባበሩት መንግስታት ጸጥታ ምክር ቤት በአጀንዳነት አስይዞ የኢትዮጰያ መንግስት አለም አቀፍ ውግዘትና ተጸእኖ እንዲደረግበት በተደጋጋሚ ማድረጉ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰአት በድርድሩ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረትን ይፈጥራል በሚባለው የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ፣ የአማራ ልዩ ሀይል በዚህ ቦታ የመገኘት ጉዳይ በተመለከትም  የአሜሪካ መንግስት የአማራ ልዩ ሀይል ከአካባቢው መውጣት አለበት በማለት ደግሞ  ደጋግሞ  በተላያዩ ባለስልጣናቱ በኩል መግለጫ ሰጥቷል፡፡  በተጨማሪም  በአካባቢው አለ የሚሉትን የኤርትራ ሰራዊትም ከ ኢትዮጰያ  መውጣት አለበት በማለት ፣ ኢትዮጰያ  የውስጥ አስተዳደር ክልሎች ድንበርን መቀየር የለባትም  ወዘት በማለት በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ደግመው ደጋግመው በመግባት ሲናገሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይህ መጠነኛ መረጃ የሚያሳየው የአሜሪካ መንግስት የትግራይ ግጭትን በተመለከተ እጅግ ጠንካራ አቋም ወስዶ እርሱንም ለማስፈጸም ከፍተኛ እርምጃን እእደወሰድ  ነው፡፡ ይህም የአሜሪካ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ፣ (impartiality)   አለመሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡

አሜሪካ  በመላው አፍሪካና በተለይም በምስራቅ አፍሪካ  የ ቻይናን በቅርቡም የሩስያን እየተጠናከረች መምጣት አጥብቃ  የምትቃወም  ይህንንም ለማስቆም  የተለያየ እርምጃ እንደምትወስድ ይታወቃል፡፡  ከጥቂት ወራት በፊትም  የቻይና መንግስት በትግራይ በኩል የሚታየውን ግጭት በሰላም ለመፍታት እፈልጋለሁ ብሎ ለዚህ ቀጠና ልዩ መልእክተኛ  መመደቡም የሚታወቅ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የግብጸ መንግስት ፡ የሚያራምደውን አቋም  በአሜሪካ በኩል ለማስፈጸም ያደረገውንና አሁንም እያደረገ ያለውን ጥረት፣ የአሜሪካ መንግስትም ( ከፐሬዚደንት ትራምፐ እንደሰማነው)  የግብጽን አቋም ለማራመድ  ምን ያክል ሊጓዝ እንደሚችል በግልጽ የታየ ነው፡፡

በአሁኑ ሰአት የአሚሪካ መንግስት በኢትዮጰያ ጉዳይ ይዞ የሚጓዘውን ዘርፈ ብዙና የተወሳሰብ  ጉዳይ  ስናጤን የአሚሪካ  በአደርዳሪነት  መግባቱ   የሀገራችንን ችግር ከመፍታት ይልቅ እንዳያወሳስበው ያሰውጋል፡፡

የእውሮፓ ህብረት

የአውሮፓ ሀበረትም ከላይ የተነሱትን ጉዳዮች  በ ተመለከት ባለፉት ሁለት አመታት ያሳዩት አቋም ከአሜሪካ መንግስት የተለየ አይደለም፡፡ይህም መሰረታዊ የሆነውን የአሸማጋዮች ገለልተኛነትን አስፈላጊነት የሚቃረን የድርድር ወጤቱንም ከማገዝ ይልቅ አስቸጋሪ ቅርቃር ውስጥ ሊጥል የሚችል  አደጋ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት

የተባበሩት መንግስታት ብዙውን ጊዜ በተመሳሳይ ቅራኔ አፈትት ሽምግልና ውስጥ ራሱን የሚያስገባው በጸጥታ ምክር ቤት ወሳኔና በቅራኔው ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች በሚያቀርቡት ጥያቄ ወይም ግብዣ ነው፡፡የተባበሩት መንግስታት በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ራሱን ለመዝፈቅ እጅግ የሚጠነቀቅ ቢሆንም በተለይም ሀያላሁ መንግስታት የነርሱን አካሄድና ፍላጎት   ድጋፍ ለማስገኘት  ተሳታፊ እንዲሆን ከፍተኛ ግፊት ያካሄዳሉ ፡፡ በሀገራችን ሁኔታ ታዲያ በዚህ የድርድር ሂደት ውስጥ እንዴት ሊገቡ አንደቻሉ፣ የኢትዮጰያ መንግስት እንዲሳተፉ ጥሪ አድርጎ ነበርን የጸጥታው ምክር ቤትስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያትቶ ወሳኔ አስተላልፎ ነበርን የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባንዲራው የ ‘ሁላችንም’ ነው!! – ታሪኩ አባዳማ

በርግጥ የህወሀቱ ዶክተር ደብረጸዮን ተከታታይ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት እንደጻፈ ቢታወቅም የኢትዮጰያ መንግስት ተመሳሳይ ግብዣ መቅረቡ ኝ አይታወቅም፡፡

በዚህ አኳያ የተባበሩት መንግስታት በድርድሩ ቀጥተኛ አደራዳሪ ሆኖ መቅረብ ምናልባት ድርድሩ ውስጥ የሚነሱ የአደራዳሪዎች ሀሳብ የኢትዮጰያ መንግስት አልቀበልም ቢል ወታደራዊ ጣልቃ ግብነትን የሚጨምር አለም አቀፍ ተጸእኖ ለማድረግ ታቅዶ የተወሰደ እስትራተጂክ እርምጃ ነው ብሎ መገመትም ይቻላል፡፡

የአሸማጋዮች ተቀባይነት ማገኘት  (consent ) የሽምግልናው ሂደት ሀገር በቀል በሆነ  ባለቤትነት መመራቱ  (national ownership )

አለመታደልሆኑ የሰሜኑን የሀገራችንን ችግሮችም ሆኑ ሌሎች  በሀገር በቀል ድርጅቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለመፍታት ኢትዮጰያውያን እልታደልንም፡፡ ትላንት ከትላንት ወዲያ  እጅግ ውስብስብ ችግሮችን በሱዳን፣ በናይጀሪያ ቢያፍራ ወዘተ ይፈቱ የነበሩ አባቶችና እናቶቻቸን ልጆች እንዳልሆንን ሁሉ እነሆ ዛሬ ቀራኔ ለመፍታት ሳይሆን ለማሽማገልም  አስቸጋሪ እየሆን መጥተናል፡፡

የሰሜኑን ግጭት ለመፍታት ለድርድር ሂደቱ በገራዊ ባለቤትነት ያስፍልጋል ሲባል ኢትዮጰያዊ አደራዳሪ ባይኖርም፣ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ በአጀንዳ አቀራረጽ ፣ በአሸማጋዩች ምርጫ፣ ወዘተ ላይ ተፋላሚዎች ሙሉ ባልቤትነት ወይም ወሳኝነት እንዲኖራቸው ማድረግ አደራዳሪውም ኢትዮጰያዊ ድርጅት ባይሆንንም  ቢያንስ  አፍሪካዊ  የማድረግን አስፈላጊነት ያሳያል፡፡በዚህ አኳያ አፍሪካ ሰውም ብቃትም እንደሌላት በሚያስመስል ደረጃ የድርድሩን ሂደት ቁልፍ ተግባር፣ ማለትም አደራደሪነትን ለአውሮፓውያንና ለአሜሪካ መስጠትም ሀገር በቀል ባለቢትነት መንፈስን የሚጻረር ነው፡፡

አስፈላጊ ከሆነ የአፍሪካ ህብረት የድርድር ኮሚቴውን በአፍሪካውያን ባለሙያዎች እንዲጠናከር ማድረግ እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በመላው አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው ጥቁር ህዝብ ዘንድ በነጻነታ ታላቅ ምሳሌ የሆነችው ኢትዮጰያ የውስጥ ችግሯን ለመፍታት ራሷ አለመቻሏ እጅግ አሳፋሪ ቢሆንም ከዚህ አልፎ ከአፍሪካዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሳይሆን የምራቡን አደራዳሪነት ማጋበዝ ታላቅ ሰነልቦናዊ ሽንፈትም ነው፡፡ አፍሪካ የደቡብ አፍሪካው የእነ ቶሞ ኢምቤኪ፣ የላይበሪያዋ ኤሊኖር ጆንሰንን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ያሉባት አህጉር መሆኗ ሊዘነጋ ከቶውንም አይገባም፡፡ በዚህ አንጻር ያለ ሁሉም ተደራዳሪዎች ምእራባውያኑን ሀገራት  በአሽማጋይነት ማካተት  የራሱ የተባባሩት መንግስታት መመሪያን ብቻ ሳይሆን የአሸማጋዮች ተቀባይነት ማገኘት  (consent)  ጽነሰ ሀሳብ የሚጻረር ነው፡፡

ምን መደረግ አለበት

በሀገራችን ውስጥ የሰሜን ኢትዮጰያን ችግር ማስቀጥል ለኢትዮጰያ ሀዝብም ሆነ ለገዥው ድርጅት የሚያስገኘው ጠቀሜታ የለም፡፡ በተጻራሪው ግጭቱ እየቀጠለ ሲሄድ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስተሮች  በካቲታል ፈሰት ፣ በቱሪዝም በሰላም ከቦታ ቦታ በምዘዋወር፣ በህዝብ መፈናቀል  ወዘት የሚያስከትለው አሉታዊ ተጸእኖ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሰላምን መምረጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ይሕንም ለማደረግ የተጀመረው ወይም ይጀመራል የሚባለው ድርድር እኩልነትን ተጠያቂነተን የህዝብን መብት፣ የሀገር አንደነትንና ወንድማማችነትን መሰረት ይደረገ ወጤትን ለማሰገኘት በሚችል መልኩ ና ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ውስብስብ የሆነውን የሀገራችንን ግጭት የበልጥ ሊያወሳስቡ የሚችሉ አለም አቀፍ አጀንዳዎችን በዚህ ውስጥ እንዲታከሉ ማድረግ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም፡፡

በዚህ አንጻር  በአፍሪካ አንድነት የተጀምረው የሽምግልና ሂደት ወጤታም እንዲሆን የሚከተሉትን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የኢትዮጰያ መንግስት

በመንግስት በኩል ይህን ጉዳይ ለብቻው ሊወጣው እንደማይችል ሊገነዘብ ይገባል ፡፡ ሀገር ውስጥ ድጋፍ የሌለው የድርድር ሂደት በድርድር ጠረጰዛ  ዙሪያም ተደራራዲዎችን በሙሉ ልብ እንዳይሰሩ ተጋላጭ ያደርጋል፡፡ በዚህ አንጻር የኢትዮጰያ መንግስት / ብልጽግና / ህዝብን በተመለከተ የተሰበረውን መተማመን ለመጠገን የሚያስችለው መሰረታዊ እርምጃዎችን በአስቸኳይ ሊወስድ ይገባል፡፡ የኢትዮጰያ መንግስት አባይን በተመለከት በተደረገው ድርድር በትራምፐ አስተዳደር የተሰነዘረበትን ተጸእኖ ተወጥቶ የሀገርን ጥቅም የሚያስከብር የድርድር አቋም የያዘው በጊዜው መሉ የህዝብ ድጋፍ አብሮት ሰለነበረ እንደሆነ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

አሁንም  በየቦታው ከሚገኘው ማህበረስብ ጋር ግጭት ውስጥ የሚያስገቡትን ጉዳዮች  (ለምሳሌ በአማራ ክልል፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ ) ለመፍታት አዲስ ጥረት በመጀመር መተማመንን መገንባት መጀመር ይኖርበታል፡፡

ከዳያስፖራ ኮሚኒቲውም ጋር አስቸኳይ ምክክርን በማድረግ ቅሬታዎችን ለምፍታት አስቸኳይ እና ልባዊ ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማነው“እርስት(መሬት) አስመልሳለሁ”በሚል እየዶለተ ያለው? እነ ወልቃይትና አዲስ አበባ እንደ አስረጅ - ከፍትህ ይንገስ

ከውስጥም ከውጭም የሚኖረውን ተጸእኖ ለመቋቋም ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ በአስቸኳይ መማካከር እና የጋራ አቋም በመያዝ  በቀጣይም የተቃዋሚው ድምጽ በድርድሩ ሂደት የሚደመጥበትን ሜካኒዝም ጊዜ ሳይፈጅ ከድርድሩ በፊት ሊያስተካክል ይገባል፡፡

ድርድሩ በአፍሪካ ድርጅት እና በአፍሪካውያን ብቻ መካሄድ እንደሚገባው የምእራባውያኑ ሚና በሚጠየቁበት ጉዳይ ላይ  ድጋፍ ከመስጠት ያለፈ ሊሆን እንደማይገባው  ይህም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ በይፋ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

በኢትዮጰያ  ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች

የተቃዋሚ ድርጅቶች መንግስትን መቃወምና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት መሀል ያለውን ልዩነት እንደሚረዱ በመገንዘብ አሁን የመራባውያን  መንግስታት በድርድሩ ውስጥ በአስታራቂ ወይም የሽምጋይነት ለመግባት የቀረበው ሀሳብ ለሀገራችንና ህዝባችን ዘላቂ ጥቅም ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን  እንደምታ በመገንዘብ ይህ ሽምግልና የአድራዳሪነት ተግባር ገለልተኛነትን በሁሉም ተቀባይነትን መሰረት አድርጎ ባአፍሪካ ህብረት ስር በሚዋቀር አፍሪካዊ አደራዳሪዎች ብቻ እንዲመራ መታገል ተጸእኖም ማድረግ ጊዜው የሚጠብቀው ተግባር ነው፡፡

ይህ ጉዳይ የሁለት ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ ሰለሆን ተቃዋሚው በዚህ ሂደት በቀጣይነት ተሳታፊ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዲመቻች ለማድረግ ግፊት ያስፈልጋል፡

የአፍሪቃ ህብረት

የአፍሪካ ህብረት በአደራደሪነት ወይም አሽማጋይነት ሊቀርቡ የሚገባቸው ገለልተኛ ድርጅቶች፣ የመንግስታት ተወካዮች እና  ገለልተኛ ግለሰቦች ብቻ መሆን እንደሚገባቸው፣ በእጅ መጠምዘዝና በድብቅ በማስገደድ የሚገኝ መፍትሄ ዘለቄታ ያለው ሰላምን ሊያስከትል እንደማይችል ተረድቶ  በአስቸኳይ አሜሪካን እና የአውሮፓ ህብረትን የአደራዳሪነት ሚና በሌሎች አፍሪካዊያን ሊተካ ይገባል፡፡

የአሜሪካ መንግስት እና የአውሮፓ ማህበር

የምእራቡ መንግስታትም ሆኑ የቀጠናው ጥቅም ሊጠበቅ የሚችለው በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ተቀባይነት ባለው የእርቅ ወይም ሽምግልና ሂደት ውስጥ አልፎ እውን በሚሆን የድርድር የሰጥቶ መቀበል እናም ፍትህና ባካተተ ሂደት ኢትዮጰያ ሰላም ስትሆን ነው፡፡  ይህንንም እውን ለማድረግ የመጀመሪያው ተግባር የአደራዳሪዎችን ገለልተኛ መሆን በሁሉም ተደርዳሪዎች ተቀባይነት ማግኘትን እናም ሂደቱ በተደራዳሪዎች ባለቤትነት ሊካሂድ እንደሚገባው  መቀበል፣ነው፡፡  ባለፉት ሁለት  አመታት የኢትዮጰያ ግጭት ወስጥ አሜሪካንም ሆነ አውሮፓ ህብረት ግጭቱን በተመለከተ ይዘዋቸው የቆዩትን ግልጽና ወገንተኛ አቋም በግምት ውስጥ በማስገባት ራሳቸውን ካደራዳሪነት ሊያገልሉ እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ ይህ ማለት የድርድሩ ሂደት የሁለቱንም ሀያላን ድጋፍ አይፈልግም ማለት አይደለም፡፡

ሁለቱም ሀያላን ለድርድሩ ሲጠየቁ ቴክኒካል ድጋፍን በመስጠት፣  የድርድሩን ሂደት በፋይናንስ በመደገፍ፣  በተደራዳሪዎቹ የጋራ ፍላጎትና ውሳኔ ሊቀርቡ የሚችሉትን የተለያዩ የድጋፍ ጥያቄዎች  በመመርመርና በመደገፍ ሊተባበሩ የሚችሉበት ሰፊ እድል አለ፡፡እነዚህ ሀያላን ከአሁን በፊት በኢትዮጵጸያ የውስጥ አስተዳደር በሰራዊት አሰፋፈር፣ ወዘተ ላይ ያንጸባረቋቸው አቋሞች ግልጽ ቢሆኑም ከዚህ ወዲህ ግ ን በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመሰጠት ሙሉ በሙሉ በመቆጠብ የአደራዳሪዎቹን ነጻነት በማክበር  ይህ ሂደት የራሱህ  ይዞ እንዲጓዝ በማድረግ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም በኩል የሚገኘው የአትዮጰያ ህዝብ በጦርነቱ የደረሰበትን ጊዜያዊም ሆነ የረጅም ጊዜ ድጋፍ በሚሹ የስብአዊና የልማት  ተግባሮች ላይ ታላቅ ጋፍን በመስጠት እጅግ ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላል፡፡

የትግራይ ክልል እና አጣቃላዩ  የኢትዮጰያ ህዝብ

የትግራይ ክልል እና ቀሪው የኢትዮጰያ ህዝብም  ( በተለይም የአማራና የአፋር ክልል ነዋሪዎች)  መንግስትና ሀወሀት ራሳቸውን ችለው በውስጣቸው የተፈጠረውን ቅራኔ በሰላም ለመፍታት እንደማይችሉ ወደ ጦርነት የገቡበት እስካሁንም የቆዩበት ሂደት ራሱ በቂ ማስረጃ እንደሆነ ግልጸ ነውው፡፡ አሁንም ሁለቱ ድርጅቶች ለብቻቸው በሚያደርጉት ድርድር የህዝብን ችግር ከሰር ከመሰረቱ  ዘላቂ ሰላምን ሊያስከትል በሚችል መልኩ  ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ እጅግ ይከብዳል፡፡

ሰለዚህም ህዝባችን ወደ ሌላ አስቃቂ የግጭት መእራፍ የሚያሸጋግረውን ሂደት ለማምከን የሚካሄደውን ድርድር በቅርብ በመከታተል ችግር  ፈጣሪ ወይም አደናቃፊ የሆኑ አካሄዶችንም በየደረጃው በመታገል ህዝባችን በአንድነት፣ በሰላም በወንድንማማችና እህትማማችነት ሊኖርበት የሚችል ድባብን  እውን ለማድረግ ግፊት ሊያደርገ ይገባል፡፡የኢትዮጰያ ህዝብ ሊጠቀም የሚችለው ከሰላም እንጂ ከጦርነት እንዳልሆነ ታሪካችን በተደጋጋሚ አሳይቶናል፡፡ ከዚህ ተምሮ ዳግም እንዳይከሰት መታገል ደግሞ የሁሉም ዜጋ ሀላፊነት ነው፡፡

ሰላም ለኢትዮጰያ

3 Comments

  1. የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ሽምግልና ገዳዳና ወያኔን ወደ ስልጣን ለመመለስ ያቀደ ነው። ለዚህም ነው ወያኔ የቀድሞውን የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት አደራዳሪነት አልቀበልም ያለው። ግራም ነፈሰ ቀኝ ድርድሩ አይሳካም። ለምን? እንዴት? ለሚለው ጥያቄ የሚከተሉትን ሃሳቦች ልሰንዝር።
    ሀ. ወያኔ መሰረቱ በሸፍጥ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ እውነትን አሽቷት አያውቅም። በትግራይ ህዝብ ስም ለዘመናት እንደሚቀልድትና እንደሚነግድበት ሁሉ ዛሬም በዚሁ የውሸት ፓለቲካቸው ተጠቅልለው እልፍ የሃገር ሃብትና ንብረት አስጨርሰው ዛሬም ለሌላ ጦርነት ቡራ ከረዪ ይላሉ። ከዘመናት በፊት ከTPLF ቀድመው በረሃ ገብተው ይታገሉ የነበሩ የትግራይ ልጆችን (TLF) ለእርቅ ጠርተው ከተበላ ከተጠጣ በህዋላ በተኙበት ነው የፈጇቸው። ከዚያ በህዋላ ራሳቸውን አጎልብተው ዛሬ ላሉበት አቋም ደረሱ። ያው የተኙ ታጣቂዎችን መግደል አመል ሆኖባቸው ከ 20 ዓመታት በላይ ያገለገለውን የሰሜን እዝ በተኛበት በሴራ የጨፈጨፉት። እንዴት ባለ ሂሳብ ነው ከእነዚህ ጋር የሰላም ድርድር የሚደረገው? የትግራይን ህዝብ የሚወክሉትስ ወያኔዎች ብቻ ናቸው? በተመሳሳይ መልኩ ኢዲዪን፤ ኢህአፓን አልፎ ተርፎ ሻቢያንም እየተነኮሉ ሲያልቁና ሲተላለቁ የኖሩ ሰላምን የማያውቁ የዘመናችን ናዚዎች ናቸው።
    ለ. ድርድሩ ለወያኔ ራሱ ቆፍሮ ራሱ ከገባበት ጉድጓድ መውጫና ጊዜ መግዣ እንጂ በጭራሽ እነዚህ ሰዎች ለትግራይ ህዝብና ለሰላም የቆሙ ሃይሎች አይደሉም። አደራዳሪ ቢቀየር፤ ቢለመኑ፤ መብራትና ሌላ አገልግሎትም ቢለቀቅ በጭራሽ አይለወጡም። ባጭሩ ወያኔ ካልጠፋ የትግራይ ህዝብም ሆነ ሌላው የሃገሪቱ ክፍል ሰላምን አያገኝም። አሁን በዚህም በዚያም የሚቀጣጠለውን እሳትና የአማራ ህዝብ እልቂት የሚመሩትና የሚያቀነባብሩት ወያኔዎች ናቸው። የክፋታቸውን ጥግ የሚያሳይ አንድ የመለስ ጠባቂ (ልጅን የሚጠብቅ) ከነገረኝ አስገራሚ ነገር ልጥቀስ።
    ጊዜው ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ ዘብጥያ የወረደበት ጊዜ ነው። ሁለተኛ ልጇን ወልዳ አራስ የነበረችው ወ/ሮ ሙሉ ግርማይ ደግሞ የሆነው ሁሉ ግር ብሏት ከቤቷና ከሥራዋ ተባራ ከወንድሟ ጋር ሆናለች። በዚህ መካከል ከብዙ ውጣ ውረድ በህዋላ የኢትዮጵያ ፓስፓርት አግኝታ ወደ ጋና ለመብረር ቦሌ ከዘመዶቿ ጋር ተኮልኩላለች። ሁሉም ተላቅሶና ተሰነባብቶ እሷም 2 ልጆችና አንዲት እህቷን አስከትላ አውሮፕላን ላይ ትሳፈራለች። ይህ ታሪኩን የሚነግረኝም ሰው አብሮ ተሳፍሯል። አክራ እንደ ደረሱ ሁለት የአየር መንገድ አስተናጋጆች ተጠግተው በህዋላ በር እንድትወጡ ይሁን በማለት ይጠይቋታል። ጠርጣራዋና የሜዳ ታጋይ የነበረችው ወ/ሮ ሙሉም ምን ሲደረግ ፊት ለፊት ባለው በር ከሰው ጋር ነው የምወጣ ትላለች። የወያኔ እቅድ እነርሱን አፍኖ ወደ ሃገር ይዞ በመመለስ ደብዛቸውን ማጥፋት ነበር። ሲጠየቁ ያው ዘመድ ሁሉ ሸኝቷት ወደ ጋና ሂዳለች በማለት ነገሩ በዚያው ይዘጋ ነበር። ወያኔዎች ከሰው ያልተፈጠሩ እርኩሶች ናቸው። ያን የኋላ በር መውጫ ግብዣ ተቀብላ ቢሆን ኑሮ እሷም ልጆቿም እህቷም በህይወት ዛሬ አይኖሩም ነበር። ሳስበው እኔ ራሴን ይሰቀጥጠኛል በማለት ነበር ያወራኝ። ያ ሰው ዛሬ በህይወት ይኑር አይኑር አላውቅም። እንግዲህ የዶ/ር አብይ መንግስት የሚደራደረው ከእነዚህ አራዊቶች ጋር ነው።
    ሐ. ወያኔ በቅጀት ዓለም የሚኖር ድርጅት ነው። ጫት፤ ዝሙት፤ መጠጥና የሰው ደም ያደነዘዛቸው እብዶች የሚመሩት ድርጅት ነው። እስቲ በየጊዜው የሚሰጡትን መግለጫዎች አዳምጡ። እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው። ይታያችሁ የሰሜን እዝ ተሰባስቦ ወደ መቀሌ ሲጠጋ ጄ/ባጫን ገለነዋል እሱን ልናይ ልንሄድ ነው በማለት ነበር ከከተማ ተሰባስበው ወደ ጫካ የፈረጠጡት። ዛሬም ነገም ለግላቸው ጥቅም ብቻ የቆሙ እነዚህ የዘር ልክፍተኞች ለትግራይ ህዝብ አይበጅም። አሁን መጠራቅቅ ውስጥ ገብተው አንዴ ምዕራብ ትግራይ፤ ሌላ ጊዜ ተከበናል እያሉ የሚያወናብድት የራሳቸውን እድሜ ለማራዘም እንጂ ለትግራይ ህዝብ አስበው አይደለም። ወያኔ ኢትዮጵያን በዘርና በጎሳ ክልል የአፓርታይድ ሃገር ሳያረጋት ማንም በተለይም የትግራይ ልጆች በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል እንደ ፈለጉ ሰርተው የሚኖሩባት ነበረች። ክልል ግጭትን እንደሚያስከትል ቀድመው ስለሚያውቁ እኛ ስንገዳደል እነርሱ ምድሪቱንና የሃገሪቷን አንጡራ ሃብት ሳይቀር ለ 27 ዓመት ዘረፉ፤ አከፋፈሉ፤ ወደ ውጭ አሻገሩ። አሁንም የናፈቃቸው ያው የዘረፋ ዘመናቸውና ስልጣን እንጂ የትግራይ ህዝብ በልቶ ማደር አይደለም። ስለሆነም የአሜሪካና የምዕራባዊያን (Fox in the Chicken Coop) አይነት ነው። ነጩ ዓለም በጥቁሩ ዓለም ላይ ሲጫወት መኖሩና አሁንም እየተጫወተብን እንደሆነ አይንና ጀሮ ላለው ለመረዳት አይከብድም። ማንም ያደራድር ምንም ውጤቱ ባዶ ነው። ይህ ሁሉ ጥፋት ሳይሆን የእናቶችን እንባ ከሰላም ሚኒስቴርዋ ልመና እና እንባ ጋር ረግጦ እልፍ ህዝብ የጨረሰና ያስጨረሰ ድርጅት የሚታረቀው ከራሱ ጋር ነው ወይስ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር? የሰላም የመጀመሪያ መሰረቱ ከራስ ጋር ራስን ማስታረቅ ነው። ወያኔ ከራሱ ጋር የተጣላ እብድ ድርጅት ነው። ለራሱም ለማንም አይሆንምና የሰላሙ ድርድር አይሳካም። በቃኝ!

  2. በመሰረቱ በወያኔና በአቢይ አገዛዝ መሀከለ የሚደረገው ድርድር በአገራችን ምድር ያለውን የተወሳሰበ ችግር የሚያራዝመው እንጂ በፍጹም መፍትሄ ሊሆን አይችልም። በመጀመሪያ ደረጃ ለድርድር የዲሞክራሲያዊ ስብዕና ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ጸሀፊው እንዳስቀመጠው ራስን ማወቅ ያስፈልጋል። በሶስተኛ ደረጃ ሰፋ ያለ ዕውቀት ያስፈልጋል። የዕውቀት አስፈላጊነት ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ በብዙ መልክ የሚታየውን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት ነው። ከእነዚህ ሶስት መሰረተ-ሃሳቦች ስንነሳ ወያኔም ሆነ የኦሮሞን ጥቅም አስጠብቃለሁ የሚለውና ስልጣንን የተቆናጠጠው የአቢይ አገዛዝ አንዳቸውንም መሳፍርት የሚያሟሉ አይደሉም። ወያኔ የዲሞክራሲ ስብዕና ቢኖረው ኖሮ ከመጀመሪያውኑ ወደ በረሃ ባልገባና ስንትና ስንት ወጣቶችን ባላስጨረሰ ነበር። ከዚያም በማለፍ ከሻቢያ ጋር በመሆን የአገራችንን ሁኔታ እንዲወሳሰብ ያደረገ ህሊና-ቢስ የሽፍቶች ድርጅት ነው። ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ደግሞ ምን እንዳደረገ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። የመንግስቱን መኪና፣ ማለትም በተለይም የወታደሩንና የፀጥታውን፣ እንዲሁም የፖሊስ ተቋማትን በራሱ ቁጥጥር ስር በመጠቅለል ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት ለመለወጥ የቻለ ነው። በጉልበት የጨበጠውን የመንግስት መኪና በመጠቀም ወደ ዘራፊ መንግስትነት(Predatory State) የተለወጠ ነው። የአገሪቱን ሀብት ለመዝረፍ ደግሞ እነ አይ ኤም ኤፍና(IMF) የዓለም ባንክ(WB) ያቀረቡለትንና በማስገደድ ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመጠቀም ቀስ በቀስ የአገሪቱን ስትራቴጂክ ኢንዱስትሪዎች፣ ትላልቅ የንግድ መደብሮችና ባንኮችን፣ እንዲሁም የጥሬ ሀብቶችን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ራሱን ያደለበና፣ በዚያው መጠንም በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ያሸሸ ነው። ባጭሩ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮች የበላይነትና ትዕዛዝ ተግባራዊ ያደገረው የተቋም መሰተካከያ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት(Structural Adjustment Program) የመንግስትን ሀብት በግዥ ወደ ግል ማዘዋወር፣ የአገራችንን ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር መቀነስ፣ ለሶሻል መስኮች የተመደበ በጀትን መቀነስ፣ የአገሪቱን ገበያ ለውጭ ክፍት ማድረግ…ወዘተ. እነዚህ ሁሉ በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ የተደረጉና የአገራችንን ኢኮኖሚና ህብረተሰብ ያዘበራረቁ ናቸው። ወያኔና የበላይ ተጠባባቂዎቹ በፈጠሩት የተወሳሰበ ሁኔታና በተፈጠረው ህብረተሰብአዊ ቅራኔ የተነሳ የወያኔ አገዛዝ በዚያው ሊቀጥል አልቻለም። እየተደራረቡ የመጡት ኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ቅራኔዎችን መፍታት ባለመቻሉና፣ አዲስ አበባን ለማስፋፋት በሚል ያወጣው ማስተር ፕላን ጋር ተደምሮ የተከሰተው ተቃውሞ የወያኔን ስልጣን እየሸረሸረው ለመምጣት በመቻሉ በድሮው የአገዛዝ ስልቱ ሊቀጥል አልቻለም። ስለሆነም ሳይወድ በግድ ስልጣኑን ለአቢይና ለግብረአበሮቹ ለመልቀቅ ተገደደደ። ወያኔ ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ከእንግዲህ በኋላ ስልጣን በቃኝ፣ ያግበሰበስኩትን ሀብት ተቀመጬ ብበላ ይሻላል ብሎ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ግዜን አድብቶ እንደገና ስልጣን ላይ ለመወጣት ስልት ያወጣና ይዘጋጅ ነበር። በጊዜው የደረሰበት ስልትም በትግራይ ውስጥ የሰፈረውን ወታደር የሰሜን ዕዝ ተብሎ የሚጠራውን አድብቶ በተኛበት ማረድ ነበር። ይህን የሰሜን ዕዝ ለመግደል አሜሪካኖችንም በተዘዋዋሪ ተባብረዋል የሚል ጭምጭምታ ይወራል። ለማንኛውም ይህ ዐይነቱ አሰቃቂ ግፍ ከተፈጸመ በኋላ የቀረው ወታደር በፋኖኖና በአማራ ልዩ ኃይል በመታገዝ የወያኔን የሽፍታ ታጣቂ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ሊያዳካመው ችሎ ነበር።
    ይሁንና ግን በዚያ መቀጠል ሲገባና ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ወያኔን እንዳያንሰራራ ከመደምሰስ ይልቅ አቢይ አዲስ አበባ ሆኖ ቀጪን ትዕዛዝ በማስተላለፍ ወታደሩ እንዲያፈገፍግ ያደርጋል። ወታደሩም ትግሬን፣ በተለይም እንደመቀሌ የመሳሰሉ ከተማዎችን ለቆ ሲወጣ ብዙ መሳሪያዎችን ጥሎ እንደወጣ ይታወቃል። ይህ ጉዳይ ሆን ብሎ የተደረገ ለመሆኑ ሁኔታውን በደንብ የተከታተለ ሊገነዘበው ይችላል። ወያኔ በጊዜው ያገኘውን ዕድል በመጠቀምና ራሱን እንደገና በማደራጀትና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማሳመራት በተለይም በወሎና በአፋር ግዛቶች ላይ ወራር በማድረግ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እንዲያልቁ ተደርገዋል። ህጻናትና ባልቴቶች ተደፍረዋል። ከተማዎችና መደበሮች ፈራሰዋል። በአጭሩ የአቢይ አገዛዝ ሆን ብሎ በሰራው ስትራቲጂያዊ ወንጀል የተነሳ ወያኔ በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ወንጀል እንዲፈጽም ለማድረግ በቅቷል።
    ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ ብቻ ሳይሆን ስልጣን ከለቀቀም በኋላ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ጦርነትን ካወጀና አገራችንን ምስቅልቅሏን እንድትወጣ ካደረገ ኃይል ጋር በምን ዐይነት የሞራል መለኪያ ነው ድርድር ማካሄድ የሚቻለው? ምንስ ለማምጣት ነው? በሌላ ወገን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቿ ጥቅም ሳይሆን ዋና ፍላጎታቸው እንደዚህ ዐይነቱን ዘራፊ ኃይል እንደገና ስልጣን ላይ ቁጥጥ እንዲል በማድረግ የአገሪቱን ሀብት ለመዝረፍና በከፍተኛ ደረጃ የብልግና ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ብቻ ነው። በዚያውም መጠንም በራሱ የማይተማመን የሽርሙጥና ባህርይ ያለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሚሊታሪና የፀጥታ ኤሊት በማፍራት ከዘጠና በመቶ በላይ የሚቆጠረውን ህዝባችንን ማድኸየትና አደንቆር ማስቀረት ነው። የአሜሪካኖችና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ኤሊት በዚህ መልክ ብቻ ነው የአንድን አገር ህልውና የሚያዳክመው፤ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባ የሚያደርገው። በዚያው መጠንም በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ለማድረግ የሚችለው። ስለሆነም የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ዋና ዓላማ እንደኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች በሁሉም አቅጣጫ የተስተካከለ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግና ሰፊውን ህዝብ የሚያስተሳስረው ባህላዊ እንቅስቃሴ እንዳይካሄድና እንዳይዳብር ማድረግ ነው። በአጭሩ ሰፊው ህዝብ ብዥ ብሎበት እንዲኖር ማድረግና፣ በዚያው መጠንም የሃይማኖትና የጎሳ ግጭቶች እንዲፋፋሙ በማድረግ ጠቅላላው አገራችን የጦር አውድማ የምትሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
    ወደ አቢይ አገዛዝ ስንመጣ የአቢይ አገዛዝም በራሱ የሞራል ብቃትነት ያለው አይደለም። ማንነቱን በአለፉት አራት ዓመታት ተኩል አሳይቷል። ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ዕድገት፣ ፀረ-ሰላምና በራሱ አሸባሪ የሆነ ኃይል መሆኑን አረጋግጧል። የአገራችንን ሁኔታ የባሰውኑ ምስቅልቅሉ እንዲወጣ አድርጓል። ሰላማዊ ዜጎችንና ለነፃነት የሚታገሉትን ያፍናል; አንዳንዶችን ደግሞ ይገድላል፤ እንደፋኖ የመሳሰሉ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችን ለመደምሰስ የማይፈነቅለው ዲንጋይ የለም። ራሱ በአደራጀው ኦነግ ሸኔ በሚባለው ኃይል አማካይነት በተለይም ኦሮሚያ ክልል በሚባለው ቦታ የሚኖሩ አማራው ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ይገደላሉ። ከተማዎች ይፈራርሳሉ። በአጭሩ በዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ሰፍኗል፤ ሰላም ጠፍቷል። ሰፊው ህዝባችን እፎይ ብሎ በምርት ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፍ ከፍተኛ እንቅፋት ተደቅኖበታል። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ በምን ዕውቅና ነው የአቢይ አገዛዝ ከወያኔ ጋር የሚደራደረው? ማንስ ኃላፊነት ሰጠው? ሃሳቡስ በፓርሊያሜንት ደረጃ ውይይትና ክርክር ተካሂዶበታል ወይ? የሰፊው ህዝብስ፣ በተለይም ደግሞ ከፍተኛ ወንጀል የተፈጸመበት የወሎ፣ የአፋርና የጎንደር ህዝብ ተጠይቋል ወይ? እነዚህ ነገሮች ግልጽ ሳይሆኑ ነው እንደራደራለን የሚባለው። አንድ አገዛዝ ዲሞክራት ነኝ የሚል ከሆነ በመሰረቱ ከወንበዴና አገር አፍራሽ ከሆነ ድርጅት ጋር በፍጹም ሊደራደር አይገባውም። እንደዚህ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ በሌብነትና በግድያ ተከሰው እስር ቤት ውስጥ ከተወረወሩት ጋር ሁሉ ድርድር በማድረግ በሰላም መልቀቅ አለበት። በወያኔና በሌሎች ያልተደራጁ ገዳዮችና ሌቦች መሀከል በመሰረቱ ይህን ያህልም ልዩነት የለም። ሌባና ገዳይ ፍርዱን ሳያገኝ እንደማይለቀቅ ሁሉ ወያኔና ግብረአበሮቹ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ባደረሱት ከፍተኛ ወንጀል መከሰስና እሰከመሞት የሚያደርስ ቅጣት መቀጣት ያለባቸው ናቸው። ስረ-መሰረታቸው ከኢትዮጵያ ምድር መወገድ አለበት። እነሱና ግብረአበሮች ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ ሲወገዱ ብቻ ነው በአገራችን ምድር ሰላም ሊሰፍን የሚችለው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ አቢይና ግብረአበሮች ከኢትዮጵያ ምድር ሲነቀሉ ብቻ ነው ህዝባችን እፎይ ብሎ መተኛትና ጥሩ ህልም ማለም የሚችለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ሰላምና የተሟላ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው።
    ከዚህ ሀተታይ ስነሳ አክሊሉ ወንድአፈረው ያቀረበው ሀተታ በሳይንስ መነፅር ሲገመገም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታዎች በደንብ ያላገናዘበ፣ በሳይንሱ አጠራር ዲስክሪፕቲቭ ብለን የምንጠራው ተራ ገለጻ ነው። ጸሀፊው በአቀራረቡ ሳይንሳዊ ግንዛቤ የሌላቸውን ብዙ የዋህ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳስት ነው። እንደሰማሁት ከሆነ አቶ አክሊሉ ድሮ የኢህአፓ አባል የነበረ እንደነበር ነው። በጊዜው ኢህአፓ ማርክሲስት ነኝ ይል የነበረ ድርጅት ነበር። ታዲያ የማርክሲስት ድርጅት አባል ከነበረ ግለሰብ እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ ሊቀርብ ይችላል? መልካም ግንዛቤ! ለሰፊ ሀተታና ግንዛቤ፣ እንዲሁም ጥናት ይህንን ድረ-ገጽ ተመልከቱ፤ http://www.fekadubekele.com

    ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share