ድርድር እስከ ምን? – ከቴዎድሮስ ሃይሌ

ድርድር ዘመኑን የዋጀ የቅራኔ መፍቻ ጥበብ ነው:: የግጭትን በር ዘግቶ የስምምነትን ምዕራፍ ለመጀምር ከድርድርና ከውይይት የተሻለ አማራጭ የለም::  በድርድር ጦርነትን የማስቀረት የመቻሉን ያህል አንዳንዴም በተገቢው መንገድ ካልተያዘ ከሚቀድመው ይልቅ የሚብስ ጥፉትን ስለማምጣቱ ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል::  በተለይም ሽብርተኛና የማይገባውን ለማግኘት ግጭት ውስጥ ከገባ ሃይል ጋር የሚደረግ የሰላም ድርድር ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው::

ድርድር በሃገሮች መካከል ይደረጋል ::  በፖለቲካና በትጥቅ ሃይሎችም ጋር መደራደር የተለመደ ነው:: በመንግስትና በአንድ የጎጥ ቡድን መካከል የሚደረግ ድርድር ብዙም የተለመደም አይደለም:: ሃገር የሚያስተዳድር ታንክም ባንክም ሕዝብም ያለው መንግስት ከሽፍታ ጋር ለድርድር መቀመጡ ክብሩን ዝቅና ደረጃውን የሚያወርደውለመሆኑ እርግጥ ነው::

ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት የውድቀት አረንቋ የዳረጋት ሕወሃት አቧራ ልሶ ለድርድር የሚያበቃ ቁመና ላይ መገኘቱ የብልጽግና መንግስትና ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ከሽፈን ለመገኘታችን ማሳያ ነው::  በመረን የለሽ ዘረፉው በጭካኔው ክፉት በዘረኝነቱ ጥልቀትና በወንጀሉ ብዛት ፍርድ ማግኘት እና መደምሰስ የሚገባው ቡድን ለድርድር መብቃቱ የዚህ ትውልድ ኪሳራ ነው::

መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አነቃንቆ ማናቸውንም በሃገርና በሕዝብ ላይ የተቃጣን አደጋ መቀልበስ የሚያስችል አቅም እያለ ይህንን በቅጡ አስተባብሮ መምራት ያልቻለው የብልጽግና ልፍስፍስ መንግስት የጦር ሜዳውን ስህተት በድርድር መድረኩም እንዳይደግመው መላው ሕዝብ ሁኔታውን በጥንቃቄና በንቃት ሊክትተለው ይገባል::

የሃገር ሕልውና የሕዝብ ደህንነት ለአንድ ቡድንና ግለሰብ የሚተው አይደለም:: የሚካሄደው ድርድር እንደ አስፈላጊነቱ ሕዝብ የማወቅ መብት አለው:: ታክቲካል ከሆነ የመደራደሪያ አጀንዳዎች ባሻገር

መንግስት ግልጽ መረጃና ማብራሪና ለሕዝቡ እንዲሰጥ ተጽዕኖ መፍጠር የፖለቲካ ቡድኖች የጋዜጠኞችና የማህበረሰብ አንቂውች ድርሻ ይሆናል:: መንግስት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለድርድር መዘጋጀቱ ሕዝቡን ግራ ቢያጋባም በዲፕሎማሲው መስክ ግን ነጥብ ማስቆጠሩ ይነገርለታል::  ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ሁኔታ አንጻር በመርሕ ደርጃ ለድርድር መንግስት በጎ ፈቃድ ማሳየቱ መልካም ነው:: ሕዝባችን ያሳለፈው መከራ አንሶ ሌላ የባሰ ጥፉት እንዳይደርስ የሰላም አማራጭን መመልከት ይገባናል::  መንግስት ለመደራደርድ ዝግጁነቱን ቢያሳይም  በአንጻሩ ሕወሃት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን ከማስፈራሪያ ጋር እያቀረበ ይገኛል::  ይህም በድርድር ችግሩን ለመፍታት ፍላጎትም ዝግጁነትም ከሕወሃት በኩል እንደሌለ ማሳያ አድርጎታል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሱሰኛ አማራ ሆይ! ተሱስህ ተላቀህ ወደ ጎበዝ አለቃህ! - በላይነህ አባተ

ዳግም ጦርነቱ ሊያገረሽ እንደሚችል ሕወሃት ቀይ መስመር በሚል የሚያራግበው የወልቃይት አጀንዳ በውይይትና በድርድር ሊፈታ የሚችል አለመሆኑ ነው:;  ሕወሃት በተፈጥሮው በንግግር የማያምን ድርድርን ለተንኮል ሲጠቀምበት የኖረ ጨለምተኛ ድርጅት ነው::  ሕወሃት ድርድርን በራሱ ሜዳ ካልሆነ ይፈራዋል:: ይህውም የፖለቲካ ርዕዮቱ ወንዝ የማያሻግር የብሄር ትንተናው ለሴራ እንጂ ለራሱ እንደማያዋጣው ስለሚያውቅ ነው::  ታሪክን አስመልክቶ ለሚያነሳው ጥያቄ በድፍረት ለመከራከር የሚያስችል መረጃም የለውም::  መሪዎቹም በወንጀል ያደፉ በዘረፉ የነቀዙ አታላይ ሕዝበኞች በመሆናቸው በእራሳችው ተማምነው በውይይት ጠረጼዛ ላይ ለመገኘት ድፍረቱም ቁመናውም የላቸውም:: ይህንን ውስጣዊ ባዶነታቸውን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ግዜ ለመግዛትና አድብተው ለመጣል እስኪያመቻቸው ለውይይት ይሁን ለድርድር ዝግጁ መስለው መቅረብ ባህላቸው ነው::  ሕወሃቶች በትግራይ አማጺ በመሆን ይታወቅ ከነበረ ሌላ ትግራዋይ ድርጅት ጋር ተደራድረውና እርቅ ፈጽመው ለሊቱን በተኙበት የገዛ ወንድሞቻቸውን ስለማረዳቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው:: ሕወሃት ዛሬም ያው ነው::  ትላንት ላይ ቆሞ የቀረ ዘመኑን የማይዋጅ ግጭት ጠማቂ የሽብር ቡድን ነው:: ለዚህ ነው ዛሬም ለከትየለሽ ትዕቢቱን የሚያንጸባርቀው ::

ሕወሃት ዛሬም ከጦርነት የዘለለ እሳቤ ያለው አይደለም:: ለዚህም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አይዞህ ባይነት :  የምዕራባውያን አጋሮቹ  ድጋፍ ልቦናውን ደፍኖት ቆይቷል: ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሕወሃትን እንደልቡ አጉራ ዘለል ያደረገው ዋናው ነጥብ ለዘመናት በጥላቻ አውሮ በስጋትና ጭንቀት ፕሮጋንዳ አስሮ የፖለቲካ ፍላጎቱ ማስፈጸሚያ ያደረገው የትግራይን ሕዝብ ከጀርባው በማሰለፉ ነው::   አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ሕወሃትን እንደ አዳኝና መተኪያ የለሽ ተቋም አድርጎ የማየት የተዛነፈ አመለካከት ተሸካሚ ሆኖ ቆይቷል::  ለዚህ ነው ሕግ ለማስከበር የተሰማራውን የመከላከያ ሃይል ከጀርባ የወጋው ኢትዮጵያዊነትን እረግሞ ትግራዋይነትን ያነገበው::  በሌሎች ጎረቤቶቹ ላይ በቀል ሲታወጅ ተው ያላለው እንዲያውም እንደ ሕዝብ ዘምቶ በዘረፉና ወንጀል የተሰማራው:: የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ ነጋዴዎች መጫወቻ የሃገር ሻጮች መደበቂያ እና የወንጀለኞች ሰብዐዊ ጋሻ በመሆኑ የደረስበት መከራ እንዲዘነጋ ያለበትም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳይታይ ግርዶሽ ሆኖበታል::  ይህ ሕዝብ ሰላም ሰፍኖ የተቋረጠው የሕዝብና የልማት ግንኙነት እንዳይቀጥል ተቀባይነት ፈጽሞ ሊኖረው የማይችል ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ወያኔ የትግራይ ሕዝብን ለዳግም ሰቆቃ ሲጋብዝ ተው የሚለው እንኳ ድምጽ ብዙ አይሰማም ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማለቂያ የሌለው ጉዳችን - አንዱዓለም ተፈራ

የትግራይ ሕዝብ በታሪክም በባህልም በብዙ ማህበራዊ ሁኔታዎች ተጋምዶና ተቀላቅሎ ለብዙ ሺ አመታት አብሮት ከኖረው የአማራ ሕዝብ ጋር የደረሰበት የግንኙነት ደረጃ እስከ መጨረሻው እንዳይበጠስ ወደ ሰላምና እርቅ መቅረቡ ጊዜው አሁን ነው:: አማራው የሕወሃት ሂሳብ ማወራረጃ ተደርጎ በይፉ በተፈጸመበት በቀል ስሜቱ ተጎድቷል:: ሆኖም አማራው የትግራይ ሕዝብንና ሕወሃትን ለይቶ የማየት ግንዛቤ እንዳለው ይታያል:: ለዚህ አንዱ ማሳያ በአማራ ክልል የሚኖሩ ትግራውያንን ነጥሎ በማንነታቸው ብቻ አላጠቃም :: ሌላው ከሕወሃት አምልጠው የመጡ ትግራውያንን ተቀብሎ ከማስተናገድ ውጪ ብቀላ አልፈጸመም::

የትግራይ ሕዝብ ከአፋርና ከኤርትራ ወገኑም ጋር ያለው ትስስር ከአማራው ጋር ካለው ብዙም አይለይም:: ሕወሃት በተከተለው አጥፊ የክፉት ፖለቲካ ዙሪያውን ካሉ ሕዝቦች የትግራይ ሕዝብ ተቆራርጦ ለከፉ ስቃይ እንዳይዳረግ ከሕወሃት ድርጅታዊ ማነቆ ውጪ ያለው በዲያስፖራና በመሃል አገር የሚገኘው የትግራይ ኤሊት በግዜ ሕዝብን መዐከል ያደረገ የሰላም አማራጭ እንዲቀላጠፍ ፈጥኖ መንቀሳቀስና ድምጹን ማሰማት ይኖርበታል:: የትግራይ ሕዝብ ከሕወሃት ድርጅታዊ ምርኮኝነት ተላቆ በእራሱ ደህንነትና ዘለቄታዊ ጥቅም ላይ አቋም እንዲዝ አማራጭ መንገድ ማሳየት የተጋሩ ልሂቅ ግዴታ ነው:: የሕወሃትን አዝግ የጦረኝነት ድንፉታ የትም እንደማያደርሰው ሊያውቁትና ለሕዝቡ ሊያሳውቁት  ይገባል::  ሕወሃት የብልጽግና መንግስት ድክመትንና የኢትዮጵያ ጠላቶች በዙሪያው ማሰፍሰፍን ተመልክቶ ዳግም ወደ ጦርነት የትግራይ ሕዝብን ከጨመረው ፍጻሜው አያምርም :: ሌላው ቢቀር በአማራ በአፉርና በኤርትራ ላይ ሕወሃት የፈጸመው ሰቆቃ ከስልሳ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እራሱን ለመከላከል እንዲገደድ ያደርገዋል::

ለማጠቃለል ከሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለም:: ከድርድርም የተሻለ አማራጭ ለማንም አይበጅም:: ለሕዝብ አብሮነት ለዘለቄታዊ ጥቅሙ ከጦርነት ባሻገር ያሉ እድሎችን ለመጠቀም ሁሉም ወገን ሆደ ሰፊ መሆኑ ለሁላችን ይበጃል:: የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የትግራይ ሕዝብ ከገባበት አጣብቂኝ እንዲላቀቅ የሕዝቡን ሰቆቃ እስካቃለለ ድረስ አፍንጫችንን ይዘንም ቢሆን ከሕወሃት ጋር መነጋገሩ ተገቢም አስፈላጊም ይሆናል:: ነገርግን በክፉትና ተንኮሉ ሰይጣንን እንኳ ከሚበልጠው ሕወሃት ጋር ለሰላም የሚደረገው ድርድር እንዳለ ሆኖ የሃይል አሰላለፉን የሚመጥን ዝግጅት ማድረጉ ላይ ለሰከንድም መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው ይገባል:: ሁኔታው በአንድ እጅ ዘንባባ በሌላው እጅ ሰይፍ ትይዝ ዘንድ ግድ ይላል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንደእናቴ ሣይሆን እንደሚስቴ አውለኝ! ብሥራት ደረሰ

 

ሰላም ለሃገራችንና ለመላው ሕዝባችን!

ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ!!! አሜን!!

 

3 Comments

  1. The struggle of the Ethiopian people should focus on ridding themselves of the entire Stalinist bunch. A truce between terrorists in Addis Ababa and Mekele would have no bearing on the freedom of their captives.

  2. ግራ የገባ ነገር ነው የሆነብን እራሱ ተዋርዶ አገር የሚያዋርድ መንግስት ትግሬዎች ገንዘብ ካልተላከልን ያፈረስነው መሰረት ልማት ካልተስተካክለ ወደ ድርድር አንመጣም ብለው መንግስትም እናንት ብቻ ጠይቁ ችግር የለም እያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያን መከላከያ አርደው የአማራን ክልል መሰረት ልማት አውድመው ይህን ሁሉ ጥያቄ ደፍረው ሲጠይቁ በመሪነት የተቀመጡት ምን ያህል እንኩቶ እንደሆኑ ያሳያል፡፡ በኦሮሙማው ተስፋ ቆርጠናል ኢሳይያስ ብርታቱን ይስጠው፡፡

  3. ድርድር ከሸፈ አልከሸፈ እና እስከመቼ ? ብሎ ከመጠየቅ በፊት ማንና ማን ናቸው ስለምንና በምን የሚደራደሩት? ብሎ መጠየቅ ነው ወደ ትክክለኛው የነፃነትና የፍትህ መንገድ የሚወስደን።
    ለአገር እና በአገር ጉዳይ ሳይሆን በሥልጣንና ለሥልጣን ሽኩቻ የሚገድሉትንና የሚያጋድሉትን ሁለት የአንድ እጅግ ወንጀለኛ ሥርዓት ውላጆች (አንጃዎች) ለአገር የሚበጅ ድርድር ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ የመከራንና የውርደትን ዘመን ከማራዘም ወይም ተቀብሎ ለመኖር ካልሆነ በስተቀር ፈፅሞ መፍትሄ አይደለም። ለመሆኑ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ምን ያህል የንፁሃን ደም ነው መፍሰስ ያለበት? የፖለቲካና የሞራ ዝቅጠቱ ማብቂያ የትና መቼ ነው?ይህን ያህል እየተምዘገዘግን ቁልቁል የምንፈጠፈጠው እስከመቼና እስከምን ድረስ ነው? እንዴት ሰው የአንድ ትልቅ እባብ እንቁላል ከተገኙ ሁለት መርዘኛ እባቦች ( ህወሃትና ብልፅግና) ፈዋሽ መድሃኔትን ይጠብቃል? ምን ያህል ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች እየወረድን እንደሆነ ጨርሶ አይሰማንም እንዴ?

    እናም ብቸኛው መፍትሄ ሁለቱም የንፁሃንን ደም የሥልጣን ማስጠበቂያ ያደረጉትን እጅግ ጨካኝ ጦርነት አቁመው ወደ ሁሉን አቀፍ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ምክክርና ተግባር እንዲገቡ በህዝባዊ አልገዛምባይነት ማስገደድ ነው! የእባካችሁ እጅግ ወራዳና አዋራጅ ተማፅኖ ከቶ የትም አያደርስም! ከእራሳችን መከራና ውርደት በላይ የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ የመሆናችን ክፉ ልክፍት ምነውህሊናችን አላስጨንቀው አለ?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share