የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት እውነታዎች (ከታሪክ፣ ከሕግ እና ከስነ ሕዝብ ምህንድስና አንጻር)

በቴዎድሮስ ታደሰ በለይ (ጥናታዊ ጽሁፍ)

የመጨረሻ ክፍል (3)

በቀደሙት ሁለት ተከታታይ ዕትሞች በፍትሕ መጽሔት የተስተናገደው የጥናት ሐተታችን የወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት ታሪካዊ ዳራ (ከቅድመ-አክሱም እስከ 1983 ድረስ) የትግራይና የበጌምድር-ጎንደር (ዐማራ) ወሰን ተከዜ ስለመሆኑ፣ ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን ተሻግራ እንደማታውቅ፣ የግዛት ተስፋው ወያኔ በወረራ ተከዜን ከተሻገረ በኋላ በወልቃይት ስለፈፀመው የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና፣ ስለዘር ማፅዳት፣ በዐማራ መቃብር ላይ ስለተተገበረው የሰፈራ ፕሮግራም እና የወልቃይት የዐማራ ማንነት ጥያቄን በተመለከተ መረጃን መሰረት አድርገን ዳሰሳ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡

ይህ የጥናታዊ ጽሁፉ የመጨረሻ ክፍል ሲሆን፤ ሳምንት በይደር ባቆየነቸው ተጠይቆች በመንደርደር ወደማጠቃለያ ሀሳቦች እናመራለን፡-

ለተጠይቆች መነሻ ማንጸሪያ የሚሆነን፣ የወልቃይት ጥያቄ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ጥያቄው ያልሆነውን ነገሮች በአሉታዊ የትርጓሜ ዘዴ (Negetive definition mechanism) በመጠቀም “The Right to Self-Determination vis-à-vis Irredentism: A Critical Analaysis on the Nature and the Legal and Institutional Framework of the Wolkaite Case” በሚል ርዕስ በጎንደር ዩኒቨርሲቱ ሕግ ት/ቤት ‹‹የሰብአዊ መብቶች ሕግ›› ድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ስር በአበራ አበበ የተሰራ ጥናት ዋቢ በማድረግ እናብራራው፡፡

በዚህ ማዕቀፍ

 • የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የማንነት እውቅና የማግኘት ጥያቄ ነውን?
 • የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ነው?
 • የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ  የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (የመገንጠል)ጥያቄ ነው?
 • የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የግዛት መስፋፋት ጥያቄ ነው?
 • የወልቃይት ጥያቄ የደንበር/የወሰን ግጭት ነው?

የሚሉ ተጠይቆችን በሕግ መነፅር እንፈትሻለን፡፡

 1. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የማንነት እውቅና የማግኘት ጥያቄ ነውን?

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለፌደረሽን ምክርቤት ያስገባው ማመልከቻ “የአማራ ማንነት እውቅና እንዲሰጠው ጠይቋል። ይህ ግን በሕግ ቋንቋ ‹a means to another end› ሆኖ የሚያገለግል ነው። ጥያቄው የማንነት እውቅና ጥያቄ ብቻ ቢሆን ኖሮ የሚቀርበውም የሚጠየቀውም በወልቃይት ሕዝብ ብቻ ይሆን ነበር። በሌላ ሁኔታ የአማራ ብሔር ማንነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እውቅና የተሰጠው (አንድ የሆነ) የብሔር ማንነት ነው። እውቅና ያለው የብሔር ማንነት ደሞ እንደገና እውቅና እንዲሰጠው ሊጠየቅበት አይችልም። በመሆኑም የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የማንነት እውቅና የማግኘት ጥያቄ አይደለም!

 1. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ነው?

ራስን በራስ ማስተዳደር ጉዳይ የማንነት ጥያቄን በጠቅላላው በዳሰስንበት የክፍል ሁለት ሀተታችን ላይ እንደተመለከትነው በትርጓሜው መሰረት ጥያቄው ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ብቻ ቢሆን ኖሮ የሚቀርበው ሆነ የሚጠየቀው በሚመለከተው የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ሕዝብ ብቻ ይሆን ነበር። ከዚህ ባሻገር ጥያቄው ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ቢሆን ኖሮ በትግራይ ክልል ውስጥ እንዳለ ራስን በራስ የሚያስተዳድርበት መዋቅር በመፍጠር/በመስጠት (የልዩ ዞን አስተዳደር በመፍቀድ) ምላሽ መስጠት ይቻል ነበር። ስለሆነም የወልቃይት ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር አልያ ልዩ የብሄረሰብ ዞን የመፍጠር ጥያቄ አለመሆኑን እንረዳለን።

 • የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ  የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (የመገንጠል)ጥያቄ ነው?

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (የመገንጠል) ጥያቄ የማንነት ጥያቄን በጠቅላላው በተመለከትነው ክፍል ትርጓሜ መሰረት ጥያቄው አንድ የሆነ ብሔር የራሱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች በራሱ የመወሰን አገር ወይም ክልል የመሆን መብትን የሚመለከት ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ ጥያቄ ነው። በርግጥ የወልቃይት ጥያቄ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ይዘትን በከፊል ይዞ እናገኘዋለን። ይህም የጥያቄው ይዘት በብሔር፣ በማንነት፣ በታሪክ፣ በስነ ልቦና ወዘተ ከማይመስለው የትግራይ አስተዳደራዊ ክልል ወጥቶ ወደ ሚመስለው እና ፍቃዱ ወደ ሆነው የአማራ ክልል አስተዳደር መጠቃለልን ስለሚመለከት ነው።  ይህም የጥያቄው ይዘት ራሱን የቻለ ክልል ወይም አገር የመሆን ሳይሆን ወደነበረበት የቀድሞው በጌምድር (ጎንደር ክፍለ-ሃገር) ክፍል የሆኑ አካባቢዎች ወደ ተካለሉበት የአማራ ክልል መካለል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

 1. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የግዛት መስፋፋት ጥያቄ ነው?

የወያኔ ፖለቲከኞች የወልቃይትን ጥያቄ ለማጠልሸት እና የአማራ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻከር ጥያቄውን “የግዛት መስፋፋት” ጥያቄ አድርገው በተደጋጋሚ ሲገልጹት ይስተዋላል። ለዚህ ምላሽ ለመስጠት የግዛት መስፋፋት ምንነትን ተርጉመን መነሳት ይኖርብናል።

‹‹State expansion is a mere annexation of extra-territorial areas irrespective of the interest and ethnic status of the trans-border peoples. It aims to territorial expansion of the state against a neighboring state which is mainly devised using economic, political or military superiority of the expansionist state against a relative less positioned adjacent state.››

በዚህም የግዛት መስፋፋት ማለት፡- አንድ የወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የበላይነት ያለው አገር/ክልል ይህን የበላይነቱን ተጠቅሞ የሌላ አገር/ክልል ግዛትን ያለ ሕዝቡ እና አስተዳደሩ ፍቃድ በኃይል ወሮ መያዝ ማለት ነው።

በዚህ ትርጓሜ መሰረት ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ከላይ በተመለከትነው አግባብ በወቅቱ የነበረውን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ የበላይነት በመጠቀም ሕዝቡ በወራሪዎች አልገዛም “ከፋኝ” ብሎ እያመጸ በወረራ የያዘው የወያኔ ኃይል ነው።

በመሆኑም ጥያቄው በትግራይ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን ውስጥ ያለፍቃዳቸው በግዳጅ ተካለው የሚኖሩ አማራዎች ያነሱት ጥያቄ በመሆኑ እና ይህኑ ጥያቄም የተቀረው የአማራ ሕዝብ እና የአማራ ክልል መንግሥት የራሱ ጥያቄ ያደረገው ሁለት በአንድ ለመዋሀድ በሚፈልጉ አንድ የሆነ የብሔር ማንነት ያላቸው ሕዝብ ጥያቄ በመሆኑ ምክኒያት የግዛት መስፋፋት ጥያቄ አያደርገውም።

 1. የወልቃይት ጥያቄ የደንበር/የወሰን ግጭት ነው?

የደንበር ግጭት በሁለት እና ከዚያ በላይ አገራት መካከል አንድ የተወሰነ የመሬት ክፍል ወይም አዋሳኝ ደንበር ‹የኔ ነው› በሚል የሚፈጠር አለመግባባት ነው። በዚህ ሂደትም የጉዳዮ ወሳኝ ሁነው የሚወጡት ለኔ ይገባኛል የሚሉ አገራት እንጅ በአወዛጋቢው ደንበር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች አይደሉም። በተመሳሳይ ሁኔታ የደንበር ግጭት በአንድ አገር ውስጥ ባሉ አስተዳደራዊ ክልሎች መካከል የወሰን ግጭት ሆኖ ሊነሳ ይችላል። የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ጥያቄ ከትግራይ ክልል ወጥቶ (ተገንጥሎ) ወደ አማራ ክልል መካለልን የሚመለከት ስለሆነ የወሰን ግጭት ነው ለማለት አያስችልም። ነገር ግን ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ሰቲት ሁመራ በጥቅሉ ተከዜ ምላሽ ወደ አማራ ክልል በሚካለሉበት ጊዜ በአማራ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን መቀየሩና ወደነበረበት የተከዜ ወንዝ ተፍጥሯዊ ወሰን መመለሱ አይቀርም። በመሆኑም በመርህ ደረጃ የወልቃይት ጥያቄ የወሰን ግጭት ባይሆንም በልዩ ሁኔታ ቀደምት አስተዳደራዊ ወሰኑን መልሶ የማካለል ይዘት እንደሚኖረው መረዳት ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጲያ ገዳማት እና የግብፅ ሴራ የመነኮሳቱ ገድል እንዳይረሳ!

የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ መፍታት የሚያስችለው የሕግ ሥነ ሥርዓት

 

በክፍል ሁለት ላይ እንደተመለከትነው የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ሕዝብ ጥያቄ በይዘቱ “የሕዝቡ ማንነት፣ ታርክ፣ ሥነ ልቦና፣ ባህል እና ሌሎች የአንድ ሕዝብ መገለጫ በሆኑ መስፈርቶች ሁሉ ሲመዘን የጎንደር አማራ ሕዝብ በመሆኑ፤ በፖለቲካ ውሳኔ ግልጽ የሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ ወደ ትግራይ ክልል በ‹ዲፋክቶ› ከተካለለበት አስተዳደር ወጥቶ ወደ አማራ ክልል መካለልን” የሚመለከት ነው። ይህኑ ጥያቄ የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በቀን 28/05/2008 ዓ/ም፤ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በቀን 28/07/2014 ዓ/ም ለኢፌድሪ መንግሥት የፌደሬሽን ምክር ቤት በጽሁፍ አስገብተዋል።

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ እና የአማራ ክልል መንግሥት ጥያቄ ጠቅላላ ይዘት ሲጠቃለል “የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ራያ ሕዝብ በማንነቱ እና በታሪኩ የአማራ ማንነት ያለው ሕዝብ ሆኖ እያለ በወቅቱ ክልሎችን ያዋቀረው የብሄራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 7/1984 በአንቀፅ ቁጥር 4 “የብሔር፣ ብሄረሰብ እና ሕዝብ ኩታ ገጠም አሰፋፈር ለብሄራዊ መስተዳደር ወሰን አከላለል መሰረት ይሆናል” በማለት በግልጽ የደነገገውን ሕግ በተቃረነ ሁኔታ በፖለቲካ ውሳኔ አካባቢዎቹ ወደ ትግራይ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን ስለተካለሉ ከዚህ ሕግን ያላገናዘበ አስተዳደራዊ ወሰን ወጥተው ወደ አማራ ክልል ይካለሉ።” የሚል ነው። ይህም የጥያቄውን ይዘት በመርህ እና በልዩ ሁኔታ ደረጃ የአስተዳደራዊ ወሰን ጥያቄ ያደርገዋል።

ይህን አስተዳደራዊ ወሰን ጥያቄ በሕግ ማዕቀፍ ደረጃ ምላሽ ለመስጠት ደግሞ አዋጅ ቁጥር 7/1984 እና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን መመልከት ይገባል። አዋጅ ቁጥር 7/1984 በአንቀጽ ቁጥር 4 የተቀመጠውን መስፈርት መሰረት በማድረግ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ ቁጥር 3 ንዑስ 1 እና 2 በኢትዮጵያ ያሉ 64 ብሔር፣ ብሄረሰብ እና ሕዝብ በ14 ብሄራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን እንደተቋቋሙ ደንግጓል። በአንፃሩ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀፅ ቁጥር 46 “ክልሎች የሚዋቀሩት “የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍቃድ” ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ይሆናል” በማለት ከደነገገ በኋላ በአንቀጽ ቁጥር 47 የፌደራል መንግሥት አባላት ዘጠኝ ክልሎች መሆናቸውን እና በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የተካለሉ ብሔር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል ሊመሰርቱ እንደሚችሉ መብት በመስጠት ደንግጓል።

ይህም አዋጅ ቁጥር 7/1984 በአንቀጽ ቁጥር 3 ያቋቋማቸው 14 ክልሎች እንደተሻሩ እና በዘጠኝ ክልሎች እንደገና እንደተዋቀሩ ያስረዳል። ከዚህ ባሻገር ሕገ መንግስቱ በአንቀፅ ቁጥር 48 “የክልሎችን ወሰን በተመለከተ ጥያቄ ከተነሳ ጉዳዮ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል፤ የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈር እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ጥያቄው በቀረበ በሁለት ዓመት ውስጥ ይወስናል” በማለት ደንግጓል። ይህም አዋጅ ቁጥር 7/1983 ሆነ ሕገ መንግስቱ የፌደራል መንግሥት አባል ክልሎች አዋቅሮ እንዳላጠናቀቀ፤ በክልሎች መካከል የወሰን እና የአስተዳደር ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እና በሚነሳበት ወቅትም በዚህ ድንጋጌ አግባብ እንደሚታይ ያመላክታል። በዚህ አግባብም በቅርቡ የሲዳማ ክልል እና የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል እንደተቋቋሙ፣ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎችም እየቀረቡ እንዳለ እና ሂደቱ እንዳልተጠናቀቀ መገንዘብ ይቻላል።

በመሆኑም ወደ ተናሳንበት ጥያቄ ስንመለስ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ራያ ጥያቄ መሰረት የሚያደርገው እና ምላሽ የሚሰጠው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 48 ድንጋጌ መሆኑን እንረዳለን። ሕገ-መንግሥቱም በአንቀጽ ቁጥር 48 የአከላለል ለውጦችን በተመለከተ ክልሎች መስማማት በማይችሉ ጊዜ የፌደሬሽን ምክር ቤት “የሕዝብን አሰፋፈር እና ፍላጎት” መሰረት በማድረግ እንደሚወስን ድንግጓል።

የፌደረሽን ምክር ቤትም ይህን ውሳኔ እንዴት ሊወስን እንደሚችል ስንመለከት ደሞ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን እና ተግባር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1261/2013 ምላሽ ይሰጠናል። አዋጅ ቁጥር 1261/2013 በአንቀጽ ቁጥር 37 የአስተዳደር ወሰን ውዝግብን ስለ መፍታት ባስቀመጠው ድንጋጌ “የቀረበው ጥያቄ የአስተዳደር ወሰን ውዝግብን የሚመለከት ከሆነ ምክር ቤቱ የሕዝብን አሰፋፈር እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ” እንደሚወስን ደንግጓል።

ይህ አዋጅ በአንቀጽ ቁጥር 38 የሕዝብ ፍላጎት እና አሰፋፈር በተመለከተ ምክር ቤቱ መከተል ስላለበት የቅደም ተከተል ሥነ-ሥርዓት ሲያስቀምጥ በንዑስ አንድ፤ “ምክር ቤቱ የሕዝቡን አሰፋፈር በማጥናት አካባቢው ወደየትኛው ክልል መካለል እንዳለበት ለመወሰን የሚያስችል በቂ መረጃ እንዳለው ካመነ በዚያው መሰረት ይወስናል።” በማለት ቀዳሚውን ቅደም ተከተል ሲደነግግ በንዑስ ሁለት ደግሞ፤ “ምክር ቤቱ የሕዝቡን አሰፋፈር በማጥናት አከራካሪ አካባቢ ወዴት መካለል እንዳለበት ለመወሰን የማይቻል መሆኑን ካመነ የሕዝቡን ፍላጎት መጠየቅ ይኖርበታል።” በማለት ደንግጓል።

በተጨማሪ አዋጅ ቁጥር 1261/2013 የሕዝብን ፍላጎት ስለማረጋገጥ ባስቀመጠው ድንጋጌ ጥያቄው “በሕገ መንግስቱ አንቀጽ ቁጥር 39/5 የብሔር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት ለብሔር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የተሰጠውን ትርጓሜ የሚያሟላ ከሆነ የሕዝቡን ፍላጎት በህዝበ ውሳኔ እንዲረጋገጥ ያደርጋል።” በማለት ደንግጓል።

በመሆኑም ከላይ የተቀመጡትን የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት አድርገን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ራያ የወሰን እና የአከላለል ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው የሕግ ድንጋጌ እና ሥነ-ሥርዓት የኢፊድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ቁጥር 48 እና የፌደሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን እና ተግባር ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀጽ ቁጥር 37 እና 38 መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ አሰፋፈር በጥናት በማረጋገጥ በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት መሆኑን እንረዳለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግራኝ አህመድ

1ኛ. ጥያቄው የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ቁጥር 39 የብሔር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት መሰረት በማድረግ የቀረበ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (የመገንጠል፣ ክልል የመሆን ሆነ ልዩ የብሄረሰብ አስተዳደር መሆን) የሚመለከት የማንነት ጥያቄ ባለመሆኑ፤ ቢሆን ኖሮ የልዩ ብሔር ማንነት ጥያቄ የሕዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ፍላጎት ለማወቅ በሚደረግ የህዝበ ውሳኔ የሚወሰን መሆኑ እና፤

2ኛ. ጥያቄው የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ቁጥር 48 መሰረት በማድረግ የቀረበ የወሰን እና የአከላለል ጥያቄ በመሆኑ፤ ይህ አይነት ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ደሞ የሕዝብን አሰፋፈር መሰረት በማድረግ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈር በጥናት በማረጋገጥ በሚሰጠው ሕገ መንግስታዊ ውሳኔ በመሆኑ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ራያ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው የሕግ ድንጋጌ እና ሥነ ሥርዓት የሕዝብ አሰፋፈር በጥናት በማረጋገጥ በሚሰጥ ውሳኔ እንጅ ፍላጎትን ለማወቅ በሚደረግ የህዝበ ውሳኔ አለመሆኑን እንረዳለን።

ማጠቃለያ

በክፍል አንድ የቀደመ ታሪክ ድርሳናት ሀተታ በዝርዝር የተመለከትናቸው የተለያዩ ዋቢ መጽሐፍት (ጥናቶች፣ የጉዞ ማስታወሻዎች፣ ዜና መዋዕላት፣…) እና ስለወልቃይት ታሪካዊ ሁኔታ የሚያውቁ ሰዎች እንዳስረዱት የወልቃይት ሕዝብ የዐማራ ማንነት ያለው ሆኖ አስተዳደራዊ ወሰኑ በጌምድር ይባል በነበረው የጎንደር ክፍለ-ሃገር አስተዳደር ውስጥ ነበር፡፡ ነገር በ1983 ዓ.ም. የትጥቅ ትግልን መሰረት አድርጎ የተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ መሰረት በማድረግ የወያኔ ኃይል የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ሰቲት ሁመራ አካባቢወችን በወረራ ከያዘ በኋላ አገዛዙ ራሱ የደነገጋቸውን ሕጎች በግልጽ በተቃረነ ሁኔታ ሲተዳደሩበት ከነበረው የቀድሞው በጌምድር ጎንደር ክፍለ-ሃገር ከተካለሉበት የአማራ ክልል አውጥቶ ቀጠናዎች በየትኛውም የመመዘኛ መስፈርት ወደማይመስላቸው የትግራይ ክልል ሊያካልላቸው ችሏል።

በመሆኑም በወያኔ አማጽያን በወረራ የተያዘው የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አማራ ሕዝብ የአማራን ሕዝብ በብሔራዊ ጠላትነን በፈረጀ የጥላቻ አስተዳደር በመተዳደሩ በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ግፍ፣ በደል እና ዓለም አቀፍ ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡

ይህን ግፍና በደል በመቃወም ሕዝቡ በትግራይ ክልል ከተካለለበት ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ስለ አማራዊ ማንነቱ እና ወደ አማራ ክልል መካለልም እንደሚፈልግ ሲጠይቅ እና ሲታገል ቆጥቷል፡፡ ይህኑ ጥያቄም በተደራጀና ሕጋዊ ሥነ-ሥርዓትን በተከተለ መልኩ የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 251/2001 መሰረት እና ለፌደሬሽን ምክር ቤት በኢፊድሪ ሕገ መንግሥት አ/ቁ 46 መሰረት አቅርቧል። ነገር ግን ጥያቄው በቀረበበት የሕግ አግባብ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የትግራይ ክልል መንግሥት በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት በመጠቀም ጥያቄውን ያቀረቡ የኮሚቴ አባላትን በሽብርተኝነት ፈርጆ ክስ ከመስረት ጀምሮ የኮሚቴው አባላትን በኃይል በመሰወር እና በማሳደድና በመግደል ጥቃቄውን ለማዳፈን ሞክሯል። ምንም እንኳን የወያኔ አገዛዝ የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ የማንነት ጥቃቄ በማፈን በፈሽሽታዊ አገዛዝ በኃይል ማስተዳደርን ቢመርጥም ጥያቄው በሕዝብ ልብ ውስጥ በጥልቁ የሰረፅና በየትኛውም ፋሽሽታዊ ጭካኔ ሊዳፈን የማይችል በመሆኑ ምክኒያት ግፍና በደል ያንገበገበው ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ  ጋር በመሆን ባደረገው የህዝባዊ እንቢተኝነት ትግል የአገዛዝ ሥርዓቱ በማክተም አዲስ የለውጥ ጎዳና ሂደት ሊከፍት ችሏል።

በዚህ የወያኔ የበላይነት አገዛዝ ባከተመበት እና በምትኩ አዲስ የስርዓት እየተካሄደ ባለበት ሂደት የወልቃይት ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ ሳያላገኝ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ ወያኔ የሀገር ክህደት ወንጀል ከፈጸመበት ከጥቅምት 24/2013 ምሽት ጀምሮ እንደሀገር በተጀመረው  ሕግ የማስከበር  እና የህልውና ዘመቻ ተከዜ ምላሽ በወረራ ተይዞ የኖረው ሕዝብ ከፌዴራልና ከአማራ የጸጥታ ኃይል ጋር ተሰልፎ ራሱን ከወራሪ፤ ሀገሩን ደግሞ ከከዳተኛና ባንዳ ነጻ ለማውጣት ተፋልሟል፡፡ በዚህም ነጻነቱን መጎናጸፍ ችሏል፡፡ ሕዝቡ ትርጉም የሚሰጥ መስዋዕትነት ከፍሎ ያገኘውን ነፃነት፣ ዛሬ ማንም ኃይል ጣልቃ ገብቶ ‹በማንነታችሁ እኔ ልወስን› እንዲለን የማይፈቅድ ስለመሆኑ መሬት ላይ ባደረግነው የደሰሳ ጥናት አረጋግጠናል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ነጻነቱን ባገኘ ማግስት ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ የተጣራ መረጃ የሌላቸውና የአካባቢውን ሕዝብ የዘመናት መከራና በደል በውል ያልተረዱ ኃይሎች በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የተዛቡ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ይታያል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግሥትም አሁን ድረስ ጉዳዮን ጠረጴዛው ላይ አድርጎት ቀጥሏል። የግዛት ተስፋፊው ወያኔም ለሦስት አስርታት በወረራ ይዞት የኖረውን የተከዜ ምላሽ መሬት ‹‹ምዕራብ ትግራይ›› በሚል ሐሳዊ ትርክት የሰላም ድርድሩ አካል አደርገዋለሁ በሚል ዓይን ያወጣ የተስፋነት ስሜት፣ ፍላጎቱን በማሳየት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ወያኔ ይህን ቀጠና ዳግም መርገጥ ከቻለ አንድም ለዘመናት ዋጋ የተከፈለበት የአማራ ሕዝብ ጥያቄን መካድ ይሆናል፤ አንድም ደግሞ ወያኔ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ፣ ኢትዮጵያ እንደሀገር እንዳትቀጥል ለማድረግ የሚያስችል ግብጽን ከመሰሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በየብስ የሚገናኝበት ምቹ ኮሪደር እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ በጥቅሉ የወልቃይት ጉዳይ በሚታየውም ሆነ በማይታየው መልኩ በዛሬይቷ ኢትዮጵያ በርካታ የሰውና የሀገር ሀብት ዋጋዎችን እያስከፈለ በመሆኑ፣ በቀጣይም የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና በከፍተኛ ደረጃ የሚፈትኑ አደጋዎች ምንጭ በመሆኑ የፌደራሉ መንግሥት ጥያቄውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መርምሮ ሕጋዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ጥናት በቡድን የሰራውና የዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ አዘጋጅ ተሳታፊ የሆነበት ‹‹የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የታፈኑ እውነታዎች›› በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው መጽሐፍ አዘጋጆች በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምክረ-ሀሳብ ለመጽሔቱ አንባቢያን በሚያመች መልኩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ምክረ-ሀሳቦች

አንደኛ፡- ለኢፌዴሪ መንግሥት

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከፌዴራሉ መንግሥት ሦስት ቁልፍ ተግባራት ይጠበቁበታል፡-

1ኛ) የወልቃይትም የአማራ ማንነት ጉዳይ ታውቆ ያደረ አጀንዳ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡ ለዘመናት ሲያቀርበው የኖረው ወደአማራ ክልል የመጠቃለል አስተዳደራዊ ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕግ ሊጸናለት ይገባል፡፡

2ኛ) በግዛት ተስፋፊው ወያኔ አገዛዝ ስር በነበሩት በእነዚህ አካባቢዎች አማራ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ከባድ የሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አስተናግዷል፡፡ አያሌ ወገኖቹ በጅምላ ተገድለውበታል፡፡ በማንነቱ ሞትን የማስተናገድ መራር ዕጣ ፈንታ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ገብቷል፡፡ እንዲሳደድና እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡ ሀብትና ንብረቱንም ተዘርፏል፡፡ ለዚህም በዓለማቀፍ ተሞክሮዎች መሰረት ሕዝቡ ለደረሰበት ግፍና በደል ካሣ ያስፈልገዋል፡፡ የሚጠየቀው ካሣ ለሰላሳ ዓመታት በዘለቀው የወያኔ የአፓርታይድ የአፈና አገዛዝ ያጣናቸውን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሕይወት ባይመልስም፣ ለደረሰው ግፍና በደል እውቅና መሰጠቱ የሕዝቡን ቁስል ያሽረዋልና፣ የፍትሕና የካሳ ጥያቄው በፌዴራሉ መንግሥት በኩል ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡

3ኛ) በወያኔ የግፍ አገዛዝ ተማርረውና በእርሱ አስገዳጅነት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ አምስት መቶ ሺህ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ወደቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ስራ የፌዴራሉ መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ሊሰራው የሚገባ ቁልፍ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡

ሁለተኛ፡- ለመላ ኢትዮጵያዊያን

ከጅምሩ የኢትዮጵያን የጋራ ማንነት ክዶ ለ‹‹ታላቋ ትግራይ›› የአገር ምስረታ የተነሳው ወያኔ፣ በዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሚጠላውን ሀገርና ሕዝብ የመራ ብቸኛው ድርጅት ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የተሰወረ  አይደለም፡፡ በወያኔ የጥፋት ሴራ ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም፡፡ ‹ለብሔር ብሄረሰቦች መብት ታገልኩ› ቢልም በገቢር የኢትዮጵያን ልጆች ለሥልጣኑ የበላይነት ሲል እርስ በርስ ሲያጋጭና በመካከላችን በሚፈጠረው ቅራኔ የፖለቲካ ትርፍ ሲሰራ የኖረ የጥፋት ቡድን ነው፡፡

ከ‹ትግራይ ሪፐብሊክ› ወደ ትግራይ የበላይነት የተሸጋገረው ወያኔ፣ በአገዛዛ ዘመኑ አማራውን ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያዊያን ለመነጠል፣ ባይተዋር አድርጎ ለመግዛት ሰፊና አፍራሽ የፕሮፖጋንዳ ስልት ተከትሏል፡፡ አማራው በማንነቱ የደረሰበት ግፍና መከራ እንዲሁም ያጣቸው ብሔራዊ ጥቅሞች መነሻ መሰረቱ በአማራ ጥላቻ የተዋቀረው የደደቢት ትርክት ነው፡፡ የወያኔ የፖለቲካ ግብ በአማራ ቁልቁለት እንዲሁም ሕብረትና አንድነቷን ባጣች የተዳከመች ኢትዮጵያ ስር የትግራይ የበላይነትን ማረጋገጥ ስለመሆኑ ከፈጠራቸው ሃሳዊ ትርክቶች፣ ከጥላቻ ፖለቲካው፣ ከአገዛዝ ባህሪው እና ከግዛት ተስፋፊነቱ መረዳት ይቻላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  መስከረም 26 ቀን 1928 ዓ.ም - እንደ ወጣ የቀረው ደራሲ የልደት ቀን ሲታወስ

የወልቃት፣ ጠገዴና ጠለምት ጉዳይም የሚታየው ከዚሁ አውዳሚ የፖለቲካ ባህሪው በመነሳት ነው፡፡ በታሪክ፣ በሕግና በሞራል አግባብ ከታየ እነዚህ አካባቢዎች የአማራ ናቸው፡፡ ይሁንና በግዛት ተስፋፊው ወያኔ ለሠላሳ ዓመታት በጉልበት ተነጥቀው ያለማንነታቸው የትግሬ ማንነት ለመጫን በአፓርታይድ የሚመሰል አገዛዝ ስር አይነተ ብዙ የሆነ ግፍና መከራ ሲደርስባቸው ቆይቷል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እንዲያውቁት የሚፈለገው እውነት ወያኔ ለሠላሳ ዓመታት በጉልበት ይዟቸው በነበሩ በእነዚህ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን ነው፡፡ ለዚህም የሰውና የጅምላ መቃብር ምስክሮች አስረጅ ምሳሌ ሆነው ይቀርባሉ፡፡

አሁን ላይ እነዚህ አካባቢዎች ነጻ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ይገኛል፡፡ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራ እየጠየቀ ያለው፣ ‹ማንነቴ አማራ ነው፤ ማንነቴና አስተዳደራዊ ፍላጎቴ ተከብሮልኝ በአማራ ክልል ስር ልተዳደር› የሚል ነው፡፡ ስለሆነም ፍትሕና ነጻነት ወዳድ የሆኑ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለጥያቄው ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ይጠየቃሉ፡፡

ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍቶት በኖረው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የተነሳ የአማራ ጥያቄ  የሌሎችን መብት የሚጋፋና የሚጨፈልቅ እንዲመስል ለማድረግ ሞክሯል፡፡ እውነታው ግን አማራ የሚፈልጋት ኢትዮጵያ ከማንም በላይ አልያም ከማንም በታች መሆን ሳይሆን፡- ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ እና በሕግ-ገዥነት የተመሠረተ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላት አገር ተገንብታ ማየት ነው፡፡

በዚህ መሻቱ ውስጥ በመሰረታዊነት የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ከታሪክ፣ ከሕግ፣ ከሞራል የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ የወልቃይት ጉዳይም በዚሁ አግባብ የሚታይ ነው፡፡

ሦስተኛ፡- ለትግራይ ሕዝብ (በይበልጥ ለልሂቃኑ)

ስለአማራ እና የትግራይ ሕዝብ የሺህ ዓመታት ትስስር አለም የሚያቀው እውነት ነው፡፡ ሁለቱም ሕዝብ የማህበረ-ባህል ተቃርኖ የሌለባቸው ስለመሆኑና ‹ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ፤አንድ ቤተሰብ› ሁነው ለሺህ ዓመታት በጋራ ስለመኖራቸው ነጋሪ አያሻቸውም፡፡ ስለእውነት ነጋሪ የሚያሻው፣ አኗኗሪ ምክረ-ሀሳብ የሚያስፈልገው፣ ደደቢት በረሃ ላይ ስለተጸነው ጸረ-አማራ የጥላቻ ትርክትና ድኀረ-1983 ጀምሮ በመዋቅር ገቢር ስለተደረገው የጥላቻ ፖለቲካ ባለቤትነት፣ የግዛት ተስፋፊነት እና ውጤቱ ነው፡፡

 

‹ወያኔ በትርክትና በተግባር በአማራ ሕዝብ ላይ ለሠላሳ ዓመታት የፈጠረው የወል ሰቆቃ እና የታሪክ ቁስል እንዴት ይታከም?› በሚለው ላይ መምከር፣ በጥፋቱ ልክ ለበደሉ እውቅና መስጠት እና በደባባይ ይቅርታ መጠየቅ የዘመኑ አሰገዳጅ እውነት ሆኖ ከፊት ለፊት ቀርቧል፡፡

 

ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ በተለይም ልሂቃኑ

 

 • ከምስረታውጀምሮ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ፣ በትርክት፣ በተቋምና በሥርዓት አማራን ሲያጠቃ እና በሌሎች እንዲጠቃ ሲያደርግ፤

 

 • በግዛት ተስፋፊነቱ ተከዜን ተሻግሮ የበጌምድር (ጎንደር ክፍለ-ሃገር) አካል የሆኑትን ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም የወሎ ክፍለ-ሀገር አካል የሆነውን ራያን በወረራ ወደትግራይ ሲያጠቃልል፤

 

 • በእነዚህ አካባቢዎች ባለርስት ሁነው ይኖሩ በነበሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም፣ በጅምላ ወደእስራት ሲያግዛቸው፣ ከቀያቸው በገፍ ሲያፈናቀላቸው፣… ነበር፡፡

 

ወያኔ እነዚህን ወንጀሎች የፈጸመው በ ‘ትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭነት’ ስም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይሁንና ልሂቃኑ ለሠላሳና ከዚያ ለሚበልጡ ዓመታት ‹‹በስሜ ይህ አይደረግም» («Not in My Name») አለማለታቸው፣ ወደ ጋራ ጥፋተኝነት ያስጠጋቸዋል። የጋራ ጥፋተኝነት ጽንሰ ሃሳብ ከግል ጥፋተኝነት በተቃርኖ ምንም ማለት አይደለም፤ ይልቁኑም ዕውነቱን በመደበቅ ከበስተጀርባ ለጥፋተኛ ግለሰቦች/ቡድኖች ለብቻ በመሸሸጊያነት የሚያገለግል ነው። የጋራ ጥፋተኝነት የአንድ ቡድን አባላት የሚጋሩት አስነዋሪ ሆነው የሚታዩ ድርጊት ወይም ድርጊቶች ናቸው። ያልተነገረ ነገርግን በድርጊት የሚገለጥ እንደማለት ነው።

 

የትግራይ ልሂቃን ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ በተለይም ደግሞ በወልቃይትና ራያ ያደረሰውን ግፍና ደበል እያዩ እየሰሙ ‹‹በስሜ ይህ አይደረግም» በማለት ፈንታ፤ ቁጥሩ በቀላሉ የማይገለጽ ልሂቃን የዘር ማጥፋቱን በሀሳብና በድርጊት ሲደግፉ ታይቷል፡፡ በዚህም በአማራና በትግራይ ሕዝብ መካከል በቀላሉ የማይሽር የታሪክ ጠባሳ እንዲፈጠር ዋና ተጨማሪ ምክንያት ሆነዋል፡፡

 

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሁለቱ ሕዝቦች ቅራኔ እንዲለዘብ በትንሹ የሚከተሉት ኃላፊነቶች ከትግራይ ሕዝብ በተለይም ከልሂቃኑ ይጠበቃሉ፡-

 

 • ወያኔ በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የአማራ ተወላጆች ላይ ለፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እውቅና መስጠት፤
 • ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በእነዚህ አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ ልዩ ልዩ ግፍና በደሎች ለተፈጸመበት የአማራ ሕዝብ የፍትሕና የካሳ ጥያቄው እንዲመለስለት አጋርነትን ማሳየት፤
 • በትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ የተሸሽጉም ሆኑ በስደት ዓለም ያሉ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን በሃሳብ የደገፉ፣ በተግባር ያስፈጸሙ የወያኔ አመራሮች፣ አባላትና አጋሮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ አሳልፎ መስጠት፤
 • ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት በታሪክ የአማራ ግዛት መሆናቸውን፣ ድኀረ-1983 በጉልበት ተነጥቀው ተወስደው እንደነበሩ አምኖ መቀበል፤ …

 

በትንሹ ከትግራይ ሕዝብ በተለይም ከልሂቃኑ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡

 

በግልጽ እንደሚታወቀው የወልቃይት አማራ አስተዳደራዊ ፍላጎቱን በተመለከተ ትላንትም ሆነ ዛሬ ቃሉ አንድ ነው፡፡ ‹ማንነታችን አማራ ነው፤  አስተዳደራዊ ፍላጎታችን በአማራ ክልል ስር መተዳደር ነው› የሚለው ሕዝባዊ መሰረት ያለው ጥያቄ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ‹ከትግራይ የሚመጣ ጥሩ ጎረቤት እንጅ፤ አስተዳደር ፈጽሞ አንቀበልም!› እያለ ያለው ሕዝቡ ‹ዛሬ ወደኋላ ላንመለስ ነጻ ወጥተናል› የሚል አቋሙን በአደባባይ ደጋግሞ አሰምቷል፡፡ ስለሕዝቡ ማንነት ከራሱ በላይ ምስክር ሊሰጥ የሚችል ሌላ አካል የለም፡፡ ከእንግዲህ ከትግራይ ሊመጣ የሚያስብ የትኛውም አስተዳደራዊ ኃይል ከአሸባሪው ወያኔ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡

ስለሆነም ተፈጥሯዊ ወሰን የሆነውን ተከዜ ወንዝን በጋራ የሚጋራው የትግራይ ወንድም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ምድር በሠላምና በነጻነት መኖር ይችላሉ፡፡

ዛሬም ‹ሥርዓት ይመጣል፣ ሥርዓት ይሄዳል፤ የሕዝብ ግንኙነት ግን ቋሚና ዘላቂ ነው› ብለው ያመኑ የትግራይ፣ የኩናማ፣ የኢሮብ፣… ተወላጆች በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ይኖራሉ፡፡ ሕግና ሥርዓትን አክብረው ለሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ክፍት ናቸው፡፡

ከዚህ ውጭ ከታሪክ፣ ከሕግና ሞራል ሁኔታዎች በሚቃረን መልኩ ወልቃይትን እንደ1983ቱ በጉልበት ልጠቅልል ብሎ ለሚመጣ ኃይል ተከዜን የጎላን ኮረብታዎች አምሳያ ከማድረግ ውጭ ፋይዳ የለውም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share