የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለስና የኀይል ሚዛን ዝዋሬ (Balance of power shifting)ይፈጠራል የሚለው ስጋት – (ጌታቸው ወልዩ)

*ግብጽና ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር ላይ ምን እያደረጉ ናቸው?

ጌታቸው ወልዩ (ከሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)

ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? ዛሬ “ኢትዮጵያ ባህር ኀይል መሥርታ ወደ ቀይ ባህር ከተመለሰችና ታላቁ የኅዳሴ ግድብን ገንብታ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ካበቃች፤ በቀጣናው የኀይል ሚዛን ዝዋሬ ወይም ሽግሽግ (Balance of power shifting) ይፈጠራል! ኢትዮጵያ ኀያል ትሆናለች!” ከሚል ስትራቴጂካዊ የክፋት ምልከታ ከቀይ ባህር ተዋሳኝ አገሮች በተለይ ግብጽ በቀይ ባህር ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ጦር ሰፈር ማጠናከር ሁኔታና ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር ላይ በተለያዩ ጊዜያት ያደረገቻቸውን የባህር ኀይል ልምምዶች አንድምታ በከፊል አስቃኛችኋለሁና የኢትዮጵያና የቀጣናው ጉዳይ ይመለከተናል የምትሉ ሁሉ ዘለግ ያለውን መጣጥፍ በአንክሮ ትከታተሉት ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።

ውድ ወገኖቼ:- በሰሜን አፍሪካ፣ በዐረቢያ ልሳነ-ምድርና በአፍሪካ ቀንድ (ምሥራቅ አፍሪካ) የሚገኙ የ22 አገሮች ጥምረት የሆነው “የዐረብ አገሮች ሊግ” ወይም በተለምዶ “የዐረብ ሊግ” አባል አገራት መካከል፦ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ሳዑዲ-ዓረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ የመን፣ ጅቡቲና ተለዋጭ አባሏን ኤርትራን ጨምሮ ዐረብ አገሮች በተደጋጋሚ እየተባበሩ ጦርነት የገጠሟትና የኀያልነት በትሯን ያሳረፈችባቸው እስራኤል፤ ኢትዮጵያ ተገፍታ የወጣችበት ቀይ ባህር ተዋሳኝ አገሮች ናቸው።

ከስምንቱ የቀይ ባህር ተዋሳኝ አገሮች መካከል እስራኤልን ሳይጨምር ሰባቱ፦በዐረቡ ዓለም ወይም በዐረቢያ ልሣነ-ምድር አሊያ በዐረቢያ ውሃ ገብ መሬትና በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ፤ በሰሜን አፍሪካ፣ ሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ፣ ምሥራቅ አፍሪካ ወይም አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያሉ ዐረብ አገሮችን እንዲያስተባብርና እንዲያስተሳስር በሚል ሽፋን በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ማርች 1945 (መጋቢት 1937 ዓመተ-ምህረት) በግብጽ መናገሻ ከተማ በካይሮ የተመሠረተው የዐረብ አገሮች ሊግ” (The League of Arab States جامعة الدول العربية Jāmiʿa ad-Duwal al-ʿArabiyya) አባል አገርነታቸው ይታወቃሉ።

በዘመናችን “በዐረቡ ዓለም ወይም በቀጣናው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማጠናከር!

በተለይም ምጣኔ ሀብታዊ ትስስርን ማጎልበት! ግጭቶችንና ውዝግቦችን ለመፍታት በወታደራዊ ጉዳዮች መተባበር እና ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ትብብር ማድረግ!” የሚሉ

ተልዕኮና ተግባራት ያሉት የዐረብ ሊግ አባላት የሆኑ የቀይ ባህር ተጎራባች አገሮችና እስራኤል፤ በቀይ ባህር ተጓዳኝ ድንበሮቻቸው ላይ ወታደራዊ ጦር ሰፈርን ማጠናከር እንደ አንድ የወታደራዊ አቅምና ብቃት መለኪያ አድርገው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።

ለአብነት ያህል፦ ከቀይ ባህር ጋር በድንበር ከሚጋሩ የዐረብ ሊግ አገሮች መካከል በተለይ ግብጽና ሳዑዲ-ዓረቢያ በቀይ ባህር ላይ ጫና ለመፍጠርና የጎላ ሚና ለመጫወት ወታደራዊ ኀይልን ማጠናከር እንደ አንድ ትልቅ የአቅማቸው ማሳያ አድርገው ይቆጥራሉ። እነዚህ አገሮች ከቀይ ባህር ጋር የማይዋሰኑ ግን በብዙ ጎኖች ቅርበትና ተጠቃሚነት ያላቸው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በምሥራቅ አፍሪካና አፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸው የገዘፉ፤ በዘርፈ-ብዙ አቅማቸው ከፊት የሚሰለፉ የቀጣናው አገሮች፤ በቀይ ባህር ላይ ባህር ኀይል ከመሠረቱ፤ አሊያ በቀይ ባህር ላይ ጂኦ-ፖለቲካዊ ወይም ጂኦ-ወታደራዊና ጂኦ-ዲፕሎማሲያዊ አቅማቸውን ጨምሮ ጂኦ-ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቷቸውን ካጎለበቱ፤ “በቀጣናው የኀይል ዝዋሬ ሚዛን ዝዋሬ ወይም ሽግሽግ (Balance of power shifting) ይፈጠራል!” የሚል ስጋትና ፍራቻ ይዘው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ሚና እንዳይኖሯት በልዩ ልዩ መልኮች እየገፏት ይገኛሉ።

ለምሳሌ:- ራሷን የመካከለኛው ምሥራቅና የዐረቡ ዓለም ጠበቃ አድርጋ የምትቆጥረውና ከአሜሪካ ከእስራኤል ቀጥሎ በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ያላነሰ ወታደራዊ ድጋፍ የምታገኘው የግብጽ ዓረብ ሪፑብሊክ፤ እነሆ ሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች በብዙ መልክ እየተገዳደሯትና በል ሲላቸው አኪሯን እየቀሟት ባሉበት ወቅታዊ ሁኔታ፤ ከሌሎች የቀይ ባህር ተዋሳኝና እንደ እስራኤል ካሉ የቀድሞ ባላንጣዎቿ አገሮች በበለጠ፤ በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የተጠናከሩ በርካታ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን በመመሥረት በቀዳሚነት የምትጠቀስ አገር ነች።

ለመጥቀስ ያህል:- ግብጽ በቀይ ባህር ወደቧ ዘመናዊቷ ከተማ ሻርም አልሼክ “Multinational Force and Observers” የሚሰኘውን “የሻርም ኤልሼክ የደቡብ ካምፕ” ወታደራዊ ጦር ሰፈር ከመሠረተች ዓመታት አስቆጥራለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወድቃ አትቀርም የኛ እናት!

ግብጽ በተለይ ከሱዳን ጋር በሀይላይብ ሦስትዮሽ ማዕዘን ላይ ባላትን የድንበር ውዝግብ ሱዳንን ለማስፈራራት፤ ከሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች ጋር ሆና በየመን እርስ በርስ ጦርነት እያደረገች ያለውን የጣልቃ ገብነት ጦርነት ለማገዝ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎልና ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት ላይ ማነቆ ለመሆን የመሠረተችውንና ከቀይ ባህር ዳርቻ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮቿ እጅግ ግዙፉ የሆነውን የቀይ ባህር ዳርቻ ጦር ሰፈር በሬናይስ (ቤርኒስ) ጨምሮ “ሀርግሃዳ” እና “ሣፋጋ” የተሰኙ የተጠናከሩ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችንም በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ገንብታለች።

በጥቂቱ ለመመልከት ያህል፦ “የግብጽን ደቡባዊ ድንበር፣ የኢንቨስትመንት (መዋዕለ-ነዋይ)፣ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴና የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠበቅ፤ በቀይ ባህር ዙሪያ የደኅንነትና ፀጥታ ስጋቶች እንዳይገጥሙ ለመከላከል እና ወደ ስዊዝ ቦይ መተላለፊያ የሆነውን ዓለም አቀፍ የውሃ ትራፊክ መስመር ሰላም ለማረጋገጥ!” የሚሉ የግንባታ ማጣፈጫ የዳቦ ስሞች የተሰጡት በሬናይስ (ቤርኒስ) ጦር ሰፈር ፤ አየርና ባህር ኀይሎችን ይዞ በደቡባዊ ግብጽ ቀይ ባህር ግዛት ለሱዳን በሚቀርብ ስፍራ፤ ከአስዋን ግድብ ምሥራቅ አቅጣጫ ላይ በ150 ሺ ፌዳንስ ( 63, 000 ሄክታር) የቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ነው የተመሠረተው።

ከሁለቱ ኀይሎች ማለትም አየርና ባህር ኀይሎች መካከል፦ የአየር ኀይሉ መደብ (ክፍል) 3ሺ ሜትር (ሦስት ኪሎ ሜትር) ርዝመትና ከ30 እስከ 40 ሜትሮች ስፋት ያለው የጦር አውሮፕላኖች ማቆሚያና ጥገና ክፍሎችን ጨምሮ የአስተዳደር ክፍሎች ያሉበት 51 ያህል ህንጻዎች አሉት።

የባህር ኀይል መደቡም ቢሆን፦ አውሮፕላን ተሸካሚ፤ ባህር ጠላቂና ፍሪጌትስ የጦር መርከቦችን ጨምሮ ለልምምድና ውጊያ የሚያገለግሉ ቁሳቁስና የሎጅስቲክ አቅርቦትና መኖሪያ ሕንጻዎች ተገንብተውለታል።

ወታደራዊ ጦር ሰፈሩ በቀን 3ሺ 4 መቶ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ማጣራት የሚችል፣ ዘመናዊ ሆስፒታልና ከዋና ዋና መንገዶች የሚገናኝበት 40 ኪሎ ሜትር መንገድ ተሠርቶለታል።

እንዲሁም በቀን ስድስት መቶ (600) ተሳፋሪዎችን ማሳፈር የሚችል፣ 3ሺህ 650 ሜትር ርዝመትና ስድሳ (60) ሜትር ስፋት ያለው የሲቪል አውሮፕላን ማረፊያ አለው።

በሬኒስ (በሬናይስ) ጦር ሰፈር ከመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ትልቁን ባህር ኀይል የያዘ ሲሆን፤ ከግብጽ ደግሞ በዓይነቱ ሁለተኛነት ደረጃን ይዟል።

ይህ የጦር ሰፈር ግንባታው ተጠናቅቆ በፕሬዚዳንት አብድል ፈታህ ኤል ሲሲ የተመረቀው፤ እንደ አውሮፓውያኑ ቀመር ጃንዋሪ 15 ቀን 2020 (ጥር 7 ቀን 2012 ዓመተ-ምህረት) ሲሆን በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፦ በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች የአቡዳቢ ልዑል ሞሐመድ ቢን ዛይድ፤ የሳዑዲ ዐረቢያ መከላከያ ሚኒስትር ካህሊድ ቢን ሳልማን፤ የአርሜንያ ፕሬዚዳንት አርሜን ሣርኬዚያን እና የቡልጋሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦይኮ ቦሪሶቭ ተገኝተዋል።

ግብጽ ቀደም ሲል እንደ አውሮፓውያኑ ቀመር በ2017 ከመካከለኛው ምሥራቅ በትልቅነቱ የታወቀውን “ሞሐመድ ነጂብ” የተሰኘ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ማቋቋሟ ይታወሳል።

የዓረብ ሊግ መሥራች አገሯን የግብጽ አረብ ሪፑብሊክ፤ ከቅኝ ግዛት ነጻ እንደ ወጣች የዓረብ ሊግን የተቀላቀለችውን የሱዳን ሪፑብሊክ፤ “በመረብ ወንዝና ቀይ ባህር መካከል ያለች አገር” የምትሰኘውን ኤርትራና ዓረብ ሳትሆን በግብጽ መንገድ ተመርታ የአረብ ሊግ አባል አገር የሆነችው የሶማሌያ ሪፑብሊክ አመታዊ የአገር ውስጥ ምርት በጋራ ተደምሮ ቢቀርብ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) መጠን የምትበልጣቸው ሳዑዲ ዓረቢያ በበኩሏ፤ በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ካላቸውና ሌሎች ሎሌዎቿን አስተባብራ በቀይ ባህር ላይ ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ የምትታወቅ የዓረብ ሊግ አባል አገር ነች።

ማሳያ ማቅረብ ካስፈለገ፤ ሳዑዲ ዐረቢያ፦ “ያንቡ”፣ ንጉሥ ፋህድና “ራቢህ” (Rabigh) ከተሰኙ የቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ከተገነቡ የንግድ ወደቦቿ፤ በታችና “ጃዛን” ከተሰኘው ወደቧ በላይ ሽቅብ ወጥታ፤ በአመቺ ሥፍራ የገነባችውን “ምዕራባዊ የባህር ኀይል ፍሊት” የምትለውን “የጂዳ ንጉሥ አብዱላዚዝ ባህር ኀይል ጦር ቤዝን” ጨምሮ ለሰፊው የቀይ ባህር ክልሏ በቀረቡ ቦታዎች ወታደራዊ የጦር ሰፈሮችን ገንብታ ትገኛለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢሬቻው ማን ተጠቀመ? ማንስ ተጎዳ? - አሊጋዝ ይመር

በሌላ በኩል ወታደራዊ አቅሟን ለማሳየት ራሷን ጨምራ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ሱዳንና ጅቡቲን አስጠርታ፤ ሶማሌያን በተመልካችነት ጠርታ፤ “ወታደራዊ ትብብርን ለማጠናከር!” የሚል የወታደራዊ ብልጠት ቁልምጫ ስም አሰጥታ፤ “የአምስቱ ቀይ ሞገድ” ( Red Wave 5) የባህር ኀይል ወታደራዊ ልምምድ በጅዳ የቀይ ባህር ተዋሳኝ የውሃ አካሏ ዳርቻ ላይ በተደጋጋሚ እንዲካሄድ አስደርጋለች።

ለአብነት ያህል፦ በቅርቡ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ከሜይ 29 ቀን እስከ ጁን 4 ቀን 2022 ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከግንቦት 21 ቀን እስከ ግንቦት 27 ዓመተ-ምህረት፤ ቀይ ባህርንና የኤደን ባህረ-ሰላጤ የሚዋሰኑ አገሮች (Countries Bordering the Red Sea and Gulf of Aden) በሚል አድማሰ-ሰፊ ሽፋ፤ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ከሆኑት ጅቡቲና ሱዳን እስከ ግብጽና ዮርዳኖስ በተሳተፉበት፤ ሶማሌያ በተመልካችነት በተጋበዘችበት፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ወዳጅ እየሆነች በመምጣቷ እንዳትሳተፍ በተደረገችበት፤ የቀይ ባህር ውሃ መድረክ፤ ሳዑዲ ዐረቢያ ራሷ በበላይነት የመራችው “የአምስቱ ቀይ ሞገድ” ( Red Wave 5) የባህር ኀይል ወታደራዊ ልምምድ በጅዳ የቀይ ባህር አካሏ ላይ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ ፈጥራ በአውራ አስፈጻሚነት ዓላማዋን አሳክታለች።

ቀደም ሲልም በጃንዋሪ 2019 ማለትም በጥር 2011 ዓመተ-ምህረት፤ በተመሳሳይ ስም ተመሳሳይ የባህር ኀይል ወታደራዊ ልምምድ በቀይ ባህር ተዋሳኝ የውሃ ድንበሯ ላይ ማካሄዷን አል-ሞኒተርን ጨምሮ በርካታ የዓረቡ ዓለም፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ የምዕራባውያንና የአፍሪካ አገሮች ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይም ኢትዮጵያ የባህር በር በነበራት ዘመን፤ የቀይ ባህር ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ላይ ያተኩሩ የነበሩ ተደጋጋሚ ዘገባዎች እንዳመለከቱት፤ ሳዑዲ ዐረቢያ በደኅንነትና ጥንቃቄ የተነሳ፤ የነዳጅ ሀብቷን በባህር ጉዞ እንደምትልክ ካሳወቀች ወዲህ፤ ቀይ ባህር፦ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በኤደን ባህረ-ሰላጤ (በዐረቢያ ባህር)ና በህንድ ውቅያኖስ ጭምር ቁልፍ የነዳጅና የንግድ መስመር ለመሆን የበቃ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው አዋጭ ባህር ሊሆን በመቻሉ፤ “ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በተንኮልና ሴራ ተገፍትራ በመባረሯ፤ በቀይ ባህር ላይ የነበራትን የጎላ ሚና ከነጠቋት የዐረብ አገሮች አንዷ ሳውዲ ዓረቢያ ነች!” በማለት የሚናገሩ ዲፕሎማቶችና ወታደራዊ ባለሙያዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

በይበልጥም እነሆ “ቀይ ባህር ለአሸባሪነት ድጋፍ ከሚሰጡ አገሮችና ቡድኖች ኮሪደርነት እስከ አጸፋ-አሸባሪነት ዘመቻዎች (counterterrorism operations) ማጠንጠኛነትና ማከናወኛነት የሚያገለግል የፍጥጫና የፍልሚያ ባህር!” ለመሰኘት የበቃው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የነበራት ባህር ኀይል በመፍረሱ ነው ይላሉ የዘርፉ አጥኚ ባለሙያዎች።

የሆኖ ሆኖ ከእስራኤል ጋር በቅርበት የምትዋሰነውና በአካባ (አቃባ) ባህረ-ሰላጤ በኩል ከቀይ ባህር ዳርቻ በ26 ኪሎ ሜትር (16 ማይል) ብቻ በመዋሰን፤ ለጥቂት እንደ ኢትዮጵያ ባህር አልባ ከመሆን የዳነችው ዮርዳኖስ (ጆርዳን) በበኩሏ፤ በሳዑዲ ዓረቢያ እየተጋበዘች የአምስቱ ቀይ ሞገድ” ( Red Wave 5) የባህር ኀይል ወታደራዊ ልምምድ የመሳተፏን ያህል፤ ሰባ ዓመታት ዕድሜን ባስቆጠረው በሮያል የዮርዳኖስ ባህር ኀይል የሚመራ፤ የባህር ኀይል ቀምራ፤ አቅሙን አጠናክራ፤ በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ በእስራኤል አፍንጫ ሥር “የአካባ ወታደራዊ ጦር ሰፈርን” አደራጅታ፤ ግዛቷን በንቃት እየጠበቀች ትገኛለች።

እስራኤል በበኩሏ፤ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የመጨረሻ ጠርዝ (ግርጌ) በምትገኘው “ዒላት” ወይም “ዒይላት” የቀይ ባህር ወደብ ከተማ ዳርቻ ላይ፤ “ድፍረት ያለው ይጠጋና እንተያይ?” በሚል ዓይነት ስሜት፤ “የዒላት” ወታደራዊ ጦር ሰፈርን ገንብታ፤ ደረቷን ነፍታ፤ ቀጣናውን አፍጥጣ መከታተል ከጀመረች ዓመታት አስቆጥራለች።

ይህ የእስራኤል የጦር ሰፈር፤ በኔጌቭ በረሃ ደቡባዊ ጫፍ እና በዕብራይስጥ “ሚፍራዝ ዒላት” በሚሰኘው የአካባ (የአቃባ) ባህረ-ሰላጤ አናት ወይም የቀይ ባህር ምሥራቃዊ ክንድ (the eastern arm of the Red Sea) ላይ የተቋቋመ፤ በወሳኝ ወታደራዊ ቤዝነቱ ስሙን ከፍ አድርጎ ያቆመ፤ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢትዮጵያ የህዝብ ቆጠራ የማይደረግበት ዋና ምስጢር (እውነቱ ቢሆን)

ኤርትራም ብትሆን በቀይ ባህር ላይ በምጽዋ በኩል የራሷ ባህር ኀይል ቢኖራትም፤ በቀይ ባህር ላይ ካሏት የምጽዋና አሰብ ወደቦቿ መካከል፤ ከሳዑዲ ዐረቢያና ግብጽ ጋር አብራ፤ በየመንን ዕርስ በርስ ጦርነት እጇን ላስገባችው የተባበሩት ዐረብ ኢሜሬቶች፤ በአሰብ ወደብ ላይ ወታደራዊ ጦር ሰፈር እንድትመሠርት ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች! ተብሎ ይነገርላታል።

በቀይ ባህር ደቡባዊ መግቢያ ላይ በመገኘቷ የተነሳ በአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ መካከል እንደ ድልድይ ሆና በማገልገል ላይ ያለችው ስትራቴጂካዊ አገር ጅቡቲን በተመለከተ፤ እንኳን የቀይ ባር ድንበሯን የውሃ ዳር ዳርቻዎቿን (ባህር በሯን) እና የመሬት ክፍሏን በሊዝ በማከራየት ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችል የኪራይ ስትራቴጂ አመቻችታ፤ ጦር ሰፈር ከመሠረቱት:-ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ጣልያንና ሌሎች ኀያላን አገሮች ገንዘብ የምትሰበስብባቸው ስትራቴጂዎችና ስልታዊ መንገዶችን ቀደም ሲል በትንታኔ ያቀረብኳቸው በመሆኑ ለዛሬው ሳልጠቅሳቸው ለማለፍ ፈልጌያለሁ።

መታወቅ ያለበት ግን የግብጽም ሆነ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋምና ፀረ-ኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ አቋም የያዙ ኀያላን ሆኑ እርጥባን ጠባቂ ጭፍራዎቻቸው (ሎሌ አገሮች) ፍራቻዎችና ጥላቻዎች አንዱ ስትራቴጂያቸው (የክፋትና ተንኮል አቋማቸው) ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ተባብራ በቀይ ባህር ላይ ባህር ኀይል እንዳይኖራት “ስቦ ካመጣት ቀይ ባህር ቀጣና ድጋሚ ማባረር” (The new expulsion of Ethiopia from the magnet Red Sea) የሚል ነው።

ሌላው “ኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታን አጠናቅቃ ተጠቃሚ መሆን ከጀመረችና ወደ ቀይ ባህር ከተመለሰች፤ በቀጣናው የኀይል ዝዋሬ /ሽግሽግ (Balance of power shifting) ይፈጠራል! ግብጽ አደጋ ውስጥ ገብታ ሚናዋ ይቀጭጫል! ሌሎች የቀይ ባህር፣ የኤደን ባህረ-ሰላጤና በቀጣናው የሕንድ ውቅያኖስ ተዋሳኝ አገሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ትገዳደራለች አሊያ ትቀናቀናለች! እናም! ኢትዮጵያ እንደውም እንደውነች፤ በምጣኔ ሀብት ከተመነደገች ደግሞ እንደ ግብጽ እሺ እያለች ሎሌ ሆና አትታዘዝም!” የሚሉ የምዕራባውያንና የአንዳንድ ዐረቡ ዓለም መንግሥታት ዕይታዎች ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ቀጣና እንዳትመጣ ጫና አሳድረዋል።

በመሆኑም የዐረብ ሊግ አገሮች ከሆኑት መካከል በተለይ ግብጽና ሳዑዲ-ዓረቢያ በቀይ ባህር ላይ ከፍ ያለ ሚና ለመጫወትና ወታደራዊ ጫና ለማሳደር ወታደራዊ አቋማቸውን ማጠናከር አንዱ ትልቁ ስትራቴጂያቸው ካደረጉ ከራርመዋል።

ኢትዮጵያ ተገፍታ የወጣችበት ቀይ ባህር:- በጂኦ-ፖለቲካዊ

ጠቀሜታ አንጻር ከስትራቴጂካዊ ምርጫዎች (strategic choice)፣ ስታራቴጂካዊ አቅም (strategic efficiency) እስከ ወሳኝና ጠቀሜታቸው ላቅ ያሉ ስታራቴጂካዊ ጉዳዮች፤ በወታደራዊ የኀይል ምንጭ (source of military power) ረገድ ደግሞ፦ በአገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች (global affairs) ፍጥጫና ፍልሚያ የበዛበት ቁልፍ ባህር መሆኑ ይታወቃል።

ቀይ ባህር ደግሞ:- ከአፍሪካ:-ግብጽ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያን የተካችው ኤርትራና ጅቡቲ፤ ከእስያ ደግሞ፦ የመን፣ ሳዑዲ ዐረቢያ፣ እስራኤልና ዮርዳኖስ የሚዋሰኑት፣ 1 ሺ 398 ማይል ርዝመትና 221 ማይል ስፋት እንዳለው የሚነገርለት፤ በአጠቃላይ 169ሺ 1መቶ ካሬ ማይል የሚሸፍን፤ አፍሪካና እስያ በበጎሞ ሆነ በመጥፎ የሚያስተሳስር ባህር ነው።

እናም! ኢትዮጵያም የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ከመትጋት፣ ሰላሟንና ደኅንነቷን አረጋግጣ ምጣኔ ሀብቷን በማሳደግ፤ በተባበረ ክንድ ወደ ቀይ ባህር ቀጣና ለመመለስ የምታደርገው ጥረትና ጉዞ፤ በከባድ የውስጥና የውጭ ጫናዎች እየተፈተነ የሚገኝ ቢሆንም፤ በፈተናው እሳት እየተፈተነች ወደ ፊት መግፋት የግድና የግድ ይላታል በማለት የዛሬ ቀይ ባህር ተኮር የወታደራዊ ጉዳዮች ትንታኔዬን እቋጫለሁ።

በመጨረሻም ቸሩ እግዚአብሔር አገራችንን ይጠበቅልን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

(ጌታቸው ወልዩ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share