June 12, 2022
34 mins read

አስተምህሮቶታችንን ለችግሮቻችን መፍቻነት ካልተጠቀምንባቸው በራሳቸው ፋይዳ አይኖራቸውም! – ጠገናው ጎሹ

June 12, 2022
ጠገናው ጎሹ

ለዚህ ሂሳዊ አስተያየቴ መነሻ የሆነኝ “እግዚአብሔር ሰይጣንን ውደድ ወይም ቀኝህን ሲመታህ ግራህን አዙርለት አላለም” በሚል ርዕስ በበላይነህ አባተ ተፅፎ በዘሃበሻ ድህረ ገጽ ላይ (June 11, 2022) ለንባብ የቀረበን አጭር፣ ቀጥተኛና ግልፅ መጣጥፍ ሳነብ አእምሮየን ዘልቆ የገባው ስሜት ነው። በዚህ አጋጣሚም የፀሐፊ በላይነህ አባተን ምክንያታዊ አስተያየቶች አደንቃለሁ።

ይህን ካልኩ ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልለፍ፦ ይኸኛው አባባል ቅዱስ ያኛው ደግሞ እርኩስ ነው ከሚል ደምሳሳ እና ለሰማዩም ሆነ ለምድሩ ህይወት ጨርሶ ከማይጠቅም እሰጥ ገባ ወጥተን በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ቀኙን ጉንጭህን ሲመታህ ግራህን ስጠው ሲል ለአንድ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት  በስሜት ወይም ያለምንም ማገናዘብ አፀፋዊ ምላሽ መስጠት ሊያስከትለው የሚችለው የጋራ ጉዳት ከባድ ስለሚሆን  ከማድረጋችን በፊት የምናሳየውን የትእግሥት አስፈላጊነትና ፈታኝነት ለመግለፅ እንጅ እያገላበጠ ሲጠፈጥፍህ ተጠፍጠፍ  ለማለት አለመሆኑን ለመረዳት የቲዎሎጅ ልሂቅ መሆንን ጨርሶ አይጠይቅም ።

በተፈጥሮም ሆነ በማህበራዊ መስተጋብር ሂደት ያገኘነው የሰብአዊ ፍጡርነት (ሰው የመሆን) ባህሪም ይህንን አይነት ያለምንም ምላሽ ራስን የማስጠፍጠፍ “ትእግሥት” ጨርሶ አይፈቅድልንም ። ፈጣሪም እንደ ፈጣሪነቱ ይህንን ባህሪያችንን ከማንም በላይ ስለሚያውቅ እንዲህ አይነት ፍፁማዊ ትእግሥተኝነትን ከእኛ ከፍጡሮዎቹ የሚጠብቅ አይመስለኝም። በተቻለን ሁሉ የትእሥትን ወርቃማ እና እጅግ ፈታኝ እሴትነት የእምነታችን ፅዕኑ አካል እንድናደርግ አጥብቆ መከረን (አስተማረን) እንጅ እብሪተኞች የሚያደርሱብንን መገፋትና መከራ ሁሉ ከእርሱ እንደታዘዘ ትእዛዝ በመቁጠር በትግሥት ስም እየተቀበልን መልሰን ወደ እርሱ እግዚኦ እንድንል አላስተማረንም ።

እናም በታላቁ መጽሐፍ ውስጥ ጠቅለል ባለ አኳኋን የተቀመጡ ወይም የተፃፉ አባባሎችን በደምሳሳው (በአጠቃላይ እውነትነት) እየሰበኩ የዋሁ አማኝ ህዝብ ወሰን የሌለው ትእግሥትንና መከራ ቻይነትን (መከራ ታጋሽነትን) እንደ ሰማያዊ ህይወት መውረሻ እና እንደ ምድራዊ ህይወት የስኬት መንገድ አድርጎ በመውሰድ ለሸፍጠኛ፣ ለሴረኛ፣ ለፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የተመቸ እንዲሆን ማድረግ ጨርሶ ሃላፊነት የጎደለው ነገር ነው። በእውነት ስለ እውነት እንነጋገር ካልን ማቆሚያ ለሌለው የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ሰለባዎች ካደረጉንና እያደረጉን ካሉ እጅግ አስከፊ የውድቀት አዙሪቶቻችን  አንደኛው ይኸው በእጅጉ የተንሸዋረረ አመለካከት መሆኑን ለማስተባበል የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት የለንም።

ይህንን ቀጥተኛና ግልፅ አስተያየቴን እንደ “የተሃድሶ” አራማጅነት ፣ እንደ ሃይማኖታዊ እምነት አልባነት (እግዚአብሔር አልባነት) ፣ እንደ ጨለምተኝነት፣ ወዘተ በመቁጠር  የእርግማን ናዳ ለማውረድ የሚቃጣቸው ወገኖች ቁጥር ቀላል ሊሆን እንደማይችል እገምታለሁ።

ይህ አይነት እራስን አቅመ ቢስ እያደረጉ ወደ ፈጠረ አምላክ እግዚኦ የማለት ደካማነት የሚመነጨው በዋነኛነት በመንበረ ሥልጣን ላይ ከሚፈራረቁ እኩያን አደንቁሮ ገዥ ቡድኖች ሲሆን የትክክለኛውን አስተምህሮተ ክርስቶስ ሃላፊነት መወጣት የተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች አስተዋፅኦም ከቶ ቀላል አይደለም። እርግጥ ነው እንኳንስ ኅጢአትና ነውር የሆነውን ግዙፍና መሪር እውነት መጋፈጥን እየሸሹ ኅጢአትና ነውር ያልሆነውን ግን በደምሳሳው እንደ ኅጢአትና  እንደ ነውር በመቁጠር መከረኛውን አማኝ  ህዝብ ምቹ ተከታይ (subject) እንዲሆን በሚደረግበት የእንደ እኛ አይነት ህብረተሰብ ውስጥ ይቅርና  በአንፃራዊነት በተሻለ አወንታዊ የእድገትና የሥልጣኔ ደረጃ  ላይ በሚገኝ  ህብረተሰብ ውስጥም  የምናታዘበው ድክመት ቀላል አይደለም። ጨርሶ ማስወገድም አይቻልም።

ለእንደ እኛ አይነት የነፃነት ፣የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የመከባበር ፣ የመተሳሰብ፣ የሰላምና የጋራ እድገት አገርን እውን የማድረግ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ለሚገኝ የደሃዎች ደሃ አገር  እንዲህ አይነቱ የአስተሳሰብና የአመለካከት ድህነት ሲጨመርበትየሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በእጅጉ ካባድ ነው።

እንደ ሰው በእምነትም ሆነ በሌላው የህይወታችን ዘርፍ በየጊዜው ሊያጋጥሙን የሚችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች (አጋጣሚዎች) እንደ ተጠበቁ ሆነው እንደ ዛሬው በሁሉም ዘርፍ እየሆንና እያደረግን ያለነው ነገር  በአብዛኛው መሬት ላይ  ካለው እኛነታችን ጋር እየተጣላብን በእጅጉ የተቸገርንበት ጊዜና ሁኔታ የሚኖር አይመስለኝም ። የግልና ማህበራዊ ህይወት የተሳካ ይሆን ዘንድ በምናደርገው መስተጋብራዊ ሂደት  ውስጥ የሚኖረውን መጋጨትና መፋጨት የተሻለ ነገንና  ከነገ ወዲያን ለመፍጠር በሚያስችል  ሁኔታ ልንጠቀምበት ባለመቻላችን ወደ መጠላለፊያነትና መጠፋፊያነት ተለውጦ ፈጣሪን ሳይቀር የግፍ አገዛዛቸው ተባባሪ  እንደሆነ በግልፅ በሚነግሩን ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች አገዛዝ ሥር ከወደቅን ዓመታትን አስቆጠርን።

እጅግ ብዙዎቹ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎቻችንና ሰባኪዎቻችንም ሃይማኖትን ጨምሮ ለዘመናት ህዝብን ያስተሳሰሩ ገመዶችን ወይም ክሮችን (social fabrics or values) እየበጣጠሰ የመከራና የውርደት ዶፍ የሚያወርደውን የእኩያን ገዥዎች ሥርዓተ ፖለቲካ ከምር በሆነ የሃይማኖታዊ አርበኝነት ከመገሰፅ እና መከረኛው ህዝብ ከሁለንተናዊ በተለይም ከሞራልና ከመንፈሳዊ  ቀውስ ሰብሮ እንዲወጣ ከማገዝ ይልቅ ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር በሚለዋወጥ ትእይንተ ጉባኤ፣ መግለጫና እግዚታ የተጠመዱ ናቸው። ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችንና ግብረበላዎቻቸውን “አገርን (ህዝብን) እንዳልነበር የማድረግ እኩይ ድርጊታችሁን አቁሙና በጋራ ምክክር የጋራ የሆነች ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን አድርጉ” ብሎ ከምር ለመገሰፅና ለመምከር ወኔው የሚገደው የሃይማኖት መሪና አስተማሪ አእምሮውን ሰብሰብ አድርጎ የሚፀልይበት ቦታና ሁኔታ የሌለውን የዋህ አማኝ ስለ ምን አይነት ፅድቅና ኩነኔ እንደሚሰብከው ለመረዳት ይቸግራል ።

የሃይማኖት ተቋማት መሪዎቻችን ውድቀት በዚህ ብቻ የሚገለፅ አይደለም።  የሩብ ምእተ ዓመት ህወሃት መር ግንባራቸውን (ኢህአዴግን) በሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ ምክንያት  በሁለት አንጃ ከፍለው በመወዛገብ እጅግ ስሜት የማይሰጥ ግን አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት በማካሄድ ከባድ ወንጀል የፈፀሙትን እኩያን ፖለቲከኞች ትርጉም ያለው የፍትህ ሂደትና ውሳኝነት በሌለበት “ይቅር ተባባሉና አገርን ከመፍረስና ህዝብን ከመከራ ታደጉ“ በሚል እጅግ የተድበሰበሰ  የእርቀ ሰላም አዋላጅነት ሚና ለመጫወት ለመንግሥት ተብየው ማመልከቻ ማስገባታቸውን በቅርቡ ሰምተናል።

እጅግ አያሌ ንፁሃን ዜጎች በተገኙበት ማህበረሰብና በእምነታቸው ምንነት ምክንያት እየተለዩ ማቆሚያ ላልተበጀለት አሰቃቂ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰለባነት እንዲዳረጉ ያደረገው ገዥ ቡድን ለሸፍጥና ለሴራ ፖለቲካው ሽፋን ለመሥጠት ፣ ከተጠያቂነት ለማምለጥ እና ሥልጣንን ይበልጥ ለማጠንከር ያስችለው ዘንድ ባዋቀረው  የሰላምና እርቅ ኮሚሽን ተብየው የአመራር አባልነት ውስጥ ገብተው በመርመጥመጥ ላይ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች በየትኛው የእውነተኛ የሰላምና የፍቅር አርበኝነት ተምሳሌትነት እንደሆነ ከምር መጠየቅ ሃይማኖታዊ እውቀትንና ማእረግን መዳፈር ተደርጎ ሊታይ አይገባም።

ተረኞች የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች እጅግ ታላቅ ዋጋ ያለውን የሰላም ምንነትና እንዴትነት ምን ያህል እንዳረከሱትና እያረከሱት እንደሆነ ለመረዳት አብይ አህመድ ሥልጣኑን ሲረከብ የደሰኮረው “ድንቅ” ዲስኩር ብዙም ርቀት ሳይሄድ በንፁሃን ዜጎች ላይ የወረደውንና እየወረደ ያለውን ታይቶና ተስምቶ የማይታወቅ የመከራ ዶፍ ከምር ልብ ማለት በቂ ነበር።

ቁጥራቸውን አንድና  ሁለት ለማለት ከማያልፈፉት በስተቀር  ትክክለኛውን ፍኖተ ፀፀት፣ ፍኖተ ይቅርታ፣ እና ፍኖተ ዘላቂ ሰላም የሚያሳይና ለተግባራዊነቱም በሃይማኖታዊ መሪነት አግባብና የተግባር አርበኝነት ፀንቶ መቆም የሚችል ባለመገኘቱ እኩያን ገዥ ቡድኖች የህዝብን ደህንነትና የአገርን ልዑላዊነት ለማስጠበቅ ሳይሆን ልክ ለሌለው ሥልጣናቸው ያሰጋናል የሚሉትን ንፁህ ዜጋ ሁሉ ያፍኑላቸውና ያሳድዱላቸው ዘንድ ልዩ ልዩ ክፍሎችን በአንድ ላይ ጠርንፈው ታሪካዊውን የሰላም ሚኒስቴር አምጠን ወለድን ያሉን እለት ነበር የሰላም ትርጉምና እሴት ባአፍ ጢሙ የተደፋው። አለመታደል ወይም የፈጣሪ ቁጣ ሆኖብን ሳይሆን “ከፖለቲካ ወለድ የግፍ አሟሟትና የቁም ሰቆቃ እንገላገል ዘንድ ለማገዝ ወኔው ቢያጥራችሁ እንኳ ቢያንስ ሃይማኖታዊ እምነታችንን የርሽካና የወንጀል ፖለቲካ ጨዋታ አካል አታድርጉብን” ብሎ የሚቆጣ አማኝ ባለመገኘቱ አብይ አህመድ  የዚሁ የማታለያ ኮሚሽን የአመራር አባል አድርጎ የሾማቸው የሃይማኖት መሪን ከአንድ መያዣና መጨበጫ ካልነበረው ቃለ መጠየቅ በኋላ  ምን እያደረጉ እንደሆነ አይቸም ሆነ ሰምቼ  አላውቅም ።

ከታላቁ መጽሐፍ የምንጠቅሳቸው አጠቃላይ እውነትን የሚገልፁ ሃይለ ቃሎችንና አገላለፆችን ተስፋ ለምናደርገው የሰማያዊው ህይወት ወሳኝ የሆነውን ሃላፊነት ከምንወጣበት የገሃዱ (ምድራዊው) ዓለም ህይወታችን ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር እያገናዘብን ፣ የሚቆራኘውን እያቆራኘን እና የማይቆራኘውን ደግሞ ተገቢውን ቦታ እያስያዝን ወደ ፊት ለመራመድ ካልቻልን ከጠቀሜታቸው ይልቅ አሳሳችነታቸውና ጉዳታቸው በእጅጉ ያመዝናል።

ይህን ለብዙ የዋህ አማኝ ወገኖች ሊከብድ የሚችል ቀጥተኛና ግልጽ አስተያየቴን ለግልብ ስሜት በሚመች አገላለፅ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነበር። ለዘመናት ከተዘፈቅንበት አጠቃላይ የውድቀት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት እንዳንችል ካደረጉን ምክንያቶች መካከል አንዱ በሃይማኖት መሪዎቻችንና አስተማሪዎቻችን ላይ ሂሳዊ አስተያየት (ትችት) መሠንዘር የሰማያዊውን ቤታችንን በር የሚያስከረችም አድርገን የማሰባችን ድክመት መሆኑን ባለኝ የመረዳት አቅም መጠን ስለምረዳ አላደረግሁትም። ወደ ፊትም አላደርገውም።

የግልና ማህበራዊ ህይወቶቻችንን ምስቅልቅሉን የሚያወጡ እኩያን ገዥ ቡድኖችንና የግፍ ሥርዓታቸውን ከደምሳሳ (ከጅምላ) “የእባካችሁ ተው (አደብ ግዙ)” መግለጫና ስብከት አልፎ የሚፈለገውን አወንታዊ ውጤት ለማስመዝገብ ወኔው የሚጎለው የሃይማኖታዊ እምነት መሪነትና መምህርነት ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊው ህይወታችን የምትበጅ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ አይጠቅመንምና ቆም ብለን በማሰብና ከአስቀያሚ ተሞክሯችን በመማር የተሻለ ዛሬ ላይ ሆነን እጅግ በጣም የተሻለ ነገን ለመፍጠር ተጨማሪ ጊዜ ባንወስድ መልካም ነው።

የሰው ልጆችን ከሌላው ፍጥረተ ዓለም ሁሉ ለይቶ የፈጠረበትን ታላቅና የተቀደሰ ዓላማ ማዛባት ብቻ ሳይሆን ዘቅዝቀን እያነበብነው ነውና ቆም ብለንና ትንፋሽ ወስደን ልናስብበት ይገባል። ምንም እንኳ ፖለቲካና ሃይማኖት ለየራሳቸው የተሰጠ ተልእኮና ተግባር ያላቸው በመሆኑ ልብ እያሉ መራመድን ቢጠይቀንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያገናኟቸውን ነፃነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣ ሰብአዊ መብት፣ እኩልነት ፣ መከባበር፣ መተሳሰብ ፣ ውሸትንና ሙስናን መፀየፍ ፣ የግልና የጋራ ደህንነት ፣ ፍቅር፣ ሰላምና የጋራ ህይወት ስኬት ፣ ወዘተ የመሳሰሉ እጅግ ወርቃማ እሴቶች ሲያስፈልገን የምንናነሳቸው እና ሳንፈልግ ደግሞ የምንጥላቸው ከሆነ የሚበላሸው ተስፋ የምናደርገውና የምድራዊው ህይወታችን በአንድ ላይ መሆኑን ለመረዳት ልዩ እውቀትን የሚጠይቅ አይመስለኝም። ሃይማኖታዊ አስተምህሯችን ከዚህና ከዚያ የንባብ ምንጭ ከምንጠቅሳቸው አጠቃላይ እውነትን ከሚገልፁ ሃይለ ቃላነት አልፈው የሁለቱንም (ሰማያዊውንና ምድራዊውን) ህይወታችን በሚፈትሽና የተሻለ በሚያደርግ አኳኌን ካልተጠቀምንባቸው ለዘመናት ከተዘፈቅንበት አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ፣ሞራላዊ እና መንፈሳዊ ቀውስ መውጫ አይኖረንም ።

በሌላ አገላለፅ አሁንም ስለ መከራና ውርደት አብዝተን ከማውራት (ከመተረክ) አልፈን ትርጉም ወይም ውጤት ያለው ሥራ ላይ ባለመሆናችን ቀጣይ የመከራ ዓመታትን ከመቁጠር ክፉ  አዙሪት ለመውጣት ከባዶ ተስፋ አልፎ በተግባር የሚገለፅ ዋስትና   የለንምና ከምር ልብ እንበል ። በአግባቡ አንቅቶ (የፖለቲካና የሰብአዊ መብት ሀሁ አስቆጥሮ) እና አደራጅቶ በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ አደንቁሮረው ከሚገዙት እኩያን ገዥ ፖለቲከኞች ነፃ እንዲወጣ የሚያችሉ የፖለቲካ ሃይሎችን ለማፍራት ያልተሳካለትን መከረኛ የአገሬ ህዝብ በሚገባ አውቀዋለሁና ጅምላዊ ወይም ደምሳሳ ሂሳዊ ትችት ጨርሶ አይቃጣኝም።

አቅጣጫቸውንና መንገዳቸውን የሳቱ አስተሳሰቦቻችንና አካሄዶቻችን ሁሉ ተመልሰው ትክክለኛውን አቅጣጫና መንገድ አይዙም የሚል ደምሳሳ (ጭፍን) እምነትና አስተያየትም የለኝም። ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም ከምንገኝበት እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ አንፃር እንዴትና መቼ ነው ተስፋን  ወይም ምኞትን ወደ የሚጨበጥ ስኬት የመተርጎሙ ተልእኮ የሚሳካልን?  እስከ መቼና እስከ የትስ ድረስ ነው ሲያሻን ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው በሚል ቁንስል ምክንያት ፖለቲከኞች ስለሚፈፅሙት ግፍና መከራ አያገባንም እያልን እና ሲያስፈልገን ደግሞ ሃይማኖትንና ፖለቲካን ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ እየቀላቀልን የህዝብን መከራና ወርደት የምናራዝመው? ለሚሉና በርካታ ተያያዥ    ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ እስከምናገኝላቸው ድረስ ህሊናችን ሲሞግተን ይኖራሉ።

ለሩብ ምእተ ዓመት በህወሃት የበላይነት ይመራ የነበረው ወንጀለኛ ገዥ ግምባር (ኢህአዴግ) በውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት በሁለት ክፉ አንጃዎች ተከፍሎ የአራት ኪሎውን ቤተ መንግሥት ኦህዴድ ከታማኝ አሽከርነት መላቀቅ በማይችለው የብአዴን ስብስብ ረዳትነት ሲቆጣጠር እና የህወሃት እኩይ ሃይል ደግሞ መቀሌ ቤተ መንግሥት በመግባት የበለጠ አስከፊ ወይም አደገኛ በሆነ የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ሲዘፈቅ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ሰባኪዎች ከምር የሆነ ምክርና ተግሳፅ ለመሰንዘርና ተግባራዊነቱንም እየተከታተሉ ለማሳወቅ የሚያስችል የሞራልና የመንፈሳዊነት ብርታት (ደፋርነት) አላሳዩም።

ይህን ስል የሃይማኖታዊ እምነት መሪነታችን ተልእኮ ተወጣን ለማለት የተደረጉ (misleading) እንቅስቃሴዎች አልነበሩም እያልኩ አይደለሁም። እያልኩ ያለሁት በሃይማኖታዊ እምነት መሪነትና ሰባኪነት ስም የተደረጉ ሙከራዎች ከደምሳሳ (ከጅምላ) የሰበካ ዲስኩሮችና እግዚኦ በሉ ከሚል ተግባር አልባ ጥሪ አልፈው የሄዱ አልነበሩም ነው። በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና መምህራን (ሰባኪያን) እንኳንስ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖችንና ግብረ በላዎቻቸውን ከምር ሊመክሩና ሊገስፁ ከፖለቲከኞች ባልተሻለ ሁኔታ በየራሳቸው የዘውግ ማንነት ውስጥ እየተወሸቁ ከመተራመስ እና በግል ወይም በቡድን ጥቅም እየተጠላለፉ ከመሽመድመድ አላለፉም ፈጣሪ የሚያጋጥመንን እጅግ ፈታኝ ሁኔ በትእግሥት ለማስተናገድ የሚያስችል ረቂቅ አእሞሮን በመስጠት በትግሥት እንድንጠቀምበት አስተማረንና  መከረን እንጅ እንኳን የሰው ልጅ  የደመ ነፍስ እንስሳት ተፈጥሯዊ ባህሪ የሆነውን  ራስን ከአሳዳጅና ከአጥፊ ሃይል የመከላከል  ባህሪ  እርግፍ አድርገን በመተው  ራሳችንን ለማያቋርጥ ጥፊ ወይም ከዚያ በላይ ለሚደርስ ጥቃት ፈቃደኞች እንድናደርግ በፍፁም አላስተማረንም።

እንኳን እኛ የሰው ልጆች መላእክታንስ ከልክ በላይ ሲሆንባቸውና ሲቆጡ እርምጃ ይወስዳሉ እያልን አይደለ እንዴ የምንሰብከው ።  ዓለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ የፅሁፍ ወይም የቃል አስተምህሮቶችን እኛ በምንፈልገው እና በተለይም እኩያን የገዥ ቡድኖች በሚመቻቸው አኳኋን እየተረጎምንና እያስተረጎምን ከፈጣሪ የተሰጠንን ልዩ የማሰብና የማከናወን ሥጦታ በቅጡ ያለመጠቀማችን ውድቀት ያስከተለብንና እያስከተለብን ያለው የአቅመ ቢስነት ክፉ ልማድ መቸና እንዴት ትክክለኛውን መንገድ እንደሚይዝ ለማወቅ ይቸግራል።

ክርስቶስ በአንድ ቤተ እምነትና ቦታ ሳይሆን ግፉዓን በሚገኙበት ሁሉ እየተገኘ ግፈኛ ገዥዎችን  ህዝቤን ልቀቁ እና ለሰማዩ የአባቴ ቤትም ሆነ ለምድሩ ህይወት የሚበጅ ሥራ ሥሩ – ፍትህንና ርትዕን ስፍኑ “  እያለ በማስተማሩ የመጨረሻ መስዋእትነት የከፈለበትን ታላቅ መንፈሳዊ ሥራ ከየምእራፉና ከየቁጥሩ በመቀነጫጨብ ሃይማኖትን ከክፉ አገዛዛቸው  ጋር  እያመሰቃቀሉ (እያምታቱ) የመከራና የውርደት  ዘመንን በማራዘም ላይ ለሚገኙ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ሰለባነት አሳልፎ ከመስጠት የከፋ ኀጢአት (ክፉ ሥራ)  የሚኖር አይመስለኝም። በየአደባባዩ ብቅ በማለት ድርጊት አልባ ስብከት የሚሰብክ፣ ራሱን በየጓዳው በመወሸቅ  በሃይማኖት ስም ሟርት የሚያሟርት፣ እድሜ ለዘመኑ ሥልጣኔ በየ ሶሻል ሚዲያው መስኮት ብቅ በማለት ሸር/ላይክ/ ሰብስክራይብ ካላደረጋችሁ ገሃነመ እሳት ትገባላችሁ እያለ ሳንቲም የሚለቅም ፣ በየገዳማቱ ግቢ የዋህና መከረኛ አማኝን በፈጣሪ ስም እየጠረነፈ እና ለማታለያነት ባሰለጠነው አንደበቱ እየሰበከ ከየመቀነቱና ከየቦርሳው ሳንቲም የሚመነትፍ (የሚለቅም)  እና የመፈወስ ሥልጣን ተሰጥቶኛል በሚል የለየለት ማጭበርበር የተካነና የእራሱ የተደራጀና የተቀናጀ ቅጥረኛ ምስክርነት ሰጭ ያለው ወገን ቁጥሩ እየበዛ በሄደበት ሃይማኖት መሰል አውድ ውስጥ ትክክለኛውን ክርስቶሳዊ አስተምህሮት ፈልጎ ማግኘት በእጅጉ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።

መደበኛ በሆነው ሃይማኖታዊ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ መሪዎችና አስተማሪዎችም እንዲህ አይነቱን እውነተኛ እምነትን የሚፈታተን አካሄድ ቢያንስ ከሚሰብኩት ስብከት ጋር እያያዙ ከምር ነውር ነው ለማለት የማይደፍሩበትን ምክንያት በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም መገመት ግን የሚያስቸግር አይመስለኝም። ጉዳዩን መስሎና አስመስሎ ለማለፍ ምክንያት የመኖሩን መሪር እውነት ግን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ከፖለቲከኞች ጋር የሚያተሻሸቱ ባህሪ ምክንያትም ከዚሁ አስቀያሚ ባህሪ የሚለይ አይደለም።

እንኳንስ የራሱ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች በፈጣሪ ስም የነገሩትን እንደ አብይ አህመድ አይነት እጅግ ሸፍጠኛና ሴረኛ  ፖለቲከኛን  ስሜት ኮርኳሪ ዲስኩሩን ብቻ በመስማት “ያለ እርሱ አገር ትፈርሳለች” ብሎ እንዲያምን የተደረገ ህዝብ መቼና እንዴት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንደሚቻለው እንኳን ለማመን ለማሰብም ይከብዳል።

አዎ! እንደ አብይ አህመድ አይነነቶች ፈጣሪን የሸፍጥና የሴራ ተባባሪያቸው የሚያደርጉ ፖለቲከኞችን “እግዚአብሔር የሾማቸው ስለሆኑ ያለ እርሱ (ያለ ፈጣሪ) ፈቃድ የሚሆን የለምና ከመተቸትና ከመቃወም መደመር ነው የሚበጀው” የሚል አክቲቪስት አይሉት ትንቢተኛ በቅጡ ለመለየት የሚያስቸግረው ወገን ቁጥር ቀላል ባልሆነበት  መሪር እውነታ ውስጥ ለምድሩም ሆነ ለሰማዩ ህይወት የምትበጅ አገርን እውን ማድረግ በእጅጉ ከባድ ነው።

“ፈጣሪ ከአብይ አህመድ ጋር ቤተ መንግሥት ገብቷልና አብይም እንኳን በጥፊ መጠፍጠፍ ቢገድልህና ቢያስገድልህም  አሜን ብለህ ተቀበል “ የሚል አይነት የለየለት  ደንቆሮና  ጨካኝ ነብይ ነኝ ባይ   መፅሀፍ ቅዱስን ለምስክርነት ሲጠቅስልን  እንዲህ አይነት አምላክ የአንተ ጨካኝ ልብ ወለድ ገፀ ባህሪ እንጅ እውነተኛው አምላክ አይደለምና ከገባህበት ክፉ ሰብእና ወጣ “ ማለት ቢያንስ የሞራል ግዴታ  መሆን ነበረበት። ለዚህ አይነት የመከራና የውርደት አዙሪት ፍፃሜ ማጣት ተጠያቂዎች እኛው እራሳችን እንጅ በፍፁም ፈጣሪ ሊሆን አይችልም። እናም ከገንዛ ራሳችን ዘመን  ጠገብ የሞራልና የመንፈስ  ድህነት ሰብረን መውጣት ካለብን አስተምህሮቶቻችንን ለይምሰል ወይም ተለምዶን ላለማስተጓጎል   ሳይሆን ተስፋ ለምናደርገው ሰማያዊ ህይወት ስንቅ ለምናዘጋጅበት ለዚህ እየኖርንበት ላለው ዓለም ችግር መፍቻነት እንጠቀምባቸው።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop