በፈቃዱ ሀይሉ
ባለፈው ጎበዜ ሲሳይ፣ አሁን ደግሞ ሜሮን ታደለ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ነን ባሉ አካላት ታፍነው ተለቅቀዋል። እንዲህ ዓይነቱ አፈና እና እስር በአገራችን ነባር ነው። በደርግ ጊዜ ታፍነው የተወሰዱ ሰዎች የሚሰቃዩበት ድብቅ እስር ቤት “ቤርሙዳ” ይባል ነበር። በኢሕአዴግ ጊዜም የድምፃችን ይሰማ ሰዎች፣ የመጀመሪያው ዙር የማስተር ፕላኑ ተቃውሞ ጊዜ የታሰሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በኢሕአዴጉ ቤርሙዳ ውስጥ አልፈዋል። የሜሮን ታደለን ቃለ ምልልስ ስሰማም ድርጊቱ ልክ የኢሕአዴጉ ቤርሙዳ ውስጥ የገቡ ሰዎች የተደረገባቸውን ዓይነት የነገሩኝን ይመስላል። ልዩነቱ አካላዊ ማሰቃየቱ መቅረቱ ነው። ጎበዜም፣ ሜሮንም የብልፅግና ቤርሙዳ ውስጥ ገብተው ወጥተዋል። ነገርዬው ሁሉ ወለፈንዴ የሚሆንባችሁ ይህ ድርጊት የሕግ ማስከበር ዘመቻው አካል መሆኑን ስትሰሙ ነው (ያው መንግሥት አላፈንኳቸውም ብሎ አልካደም፤ ቢክድም አፋኙን አካል ለሕግ የማቅረብ ዕዳ አለበት።)
ሕጋዊ ስርዓት እና የሕግ የበላይነት ዜጎች በወንጀል ድርጊት ተጠረጠሩ ስለሚባልበት ሁኔታ፣ የተጠረጠሩ ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲቆዩ የሚወሰንበት እና ከተወሰነ በኋላም የሚያዙበት እና የሚቆዩበት፣ አንፃራዊ ፍትሕ ሊገኝ የሚችልበት ሥነ ስርዓት አለ። የወንጀል ሥነ ስርዓቱ የተበጀው እንዲህ ዓይነቱ የማን አለብኝነት ሥራ እንዳይሠራ ነው። ገዢዎቻችን ግን ካለፉት አገዛዞች ስህተት መማር የሚፈልጉ አይመስሉም። የሜሮን አፈና ከቃለ ምልልሱ እንደገመትኩት ከሆነ ሰው ጋር ይኖራት ይሆናል ብለው የጠረጠሩትን ግንኙነት ማጣራት ላይ ያተኮረ ይመስላል። የኢንተሊጀንሱን ስንፍና ነው እንግዲህ በሕገወጥ ተግባር ለመሸፈን እየተሞከረ ያለው። ይኼ የፖለቲካ ተቃናቃኞችን የማፈንና የማሰቃየት ባሕል የሆነ ቦታ ሊቆም ይገባል። አለበለዚያ ጠንቁ ለአገርም፣ ለገዢዎቹም ይተርፋል።
https://youtu.be/V1ZH9l6Zlds