አልወለድም – አቤ ጉበኛ (የመፃሕፍት ማዕድ)

እውነት በሌለበት በዚህ ውሸት አለም፣
እኔ አልወለድም ይቅርብኝ ግዴለም፣
ሠው በሰውነቱ እኩል ካልተዳኘ፣
ወፍራም በውፍረቱ ዳኝነት ካገኘ፣
ድህነት እርሀብን ችግርና ስቃይን ፣
ለማየት አልሻም ቅጡ ያጣ ፍርድን፣

አልወለድም፣

እቢ አልወለድም እኔ በዚህ ዓለም፣
ለህይወት የሚያጓጓ አንድ ነገር የለም፣
ለኗሪ አኗኗሪ ሆኘ ከምገፋው፣
ህይወት ተብሎ ስቃይን ከምጎናፀፈው፣
ሳልወለድ ልሙት እዚሁ ግደሉኝ፣
ከእናቴ ማህፀን ቀጥታ ቅበሩኝ፣

አልወለድም

ሳልፈልግ በወላጆች ስራ ፈጥራችሁኝ ሳለ፣
ብየ ስጠይቃችሁ በዓለም ምንድን አለ?
ለእኔ መኖሪያ ሚሆን ፣
ሀብት አለ?……….የለም፣
ነፃነት አለ?……….የለም፣
ፍትህ?……….የለም፣
ታዲያ ይሁ ነገር ከሌለ በምድር፣
ኧረ አልወለድም ውሀ ሁኘ ልቅር፣

አልወለድም፣

በዳይ እና ተበዳይ ገዢና ተገዢ፣
የሚል መደብ ካለ ስበብ ሳታበዢ፣
ዐለም አልሻሽም አትሽኝ እኔንም፣
ከአንቺጋ ለመኖር እኔ አልወለድም፣

አልወለድም፣

የዋሁ ደሀ ህዝብ ጉልበቱን በዝብዞ፣
ሀብታሙ ካለልክ ሁሉን አግበስብሶ
የሚወስድበት ዓለም፣
ባለስልጣን እንደጌታ እራሡን ኮፍሶ፣
ሁሉን የሚያሸክም የሚቀማም ነክሶ፣
በሆነበት ዓለም ለመኖር አልመጣም፣
እንዲህ ያለ ህይወት ልኖር እኔ አልወጣም፣

አልወለድም፣

ተወለድ ካላችሁ
ሠው በሠውነቱ እኩል ከተዳኘ፣
በሚሠራው ስራ ፍትህን ካገኘ፣
ጥቅምም ሆነ ጉዳት እንደሠራው ሁሉ
እኩል ክፍፍልን ካደረግን እዉን
የዛኔ ልወለድ ዐለም እኩል ስታይ
ሠውን ላይ ታች አድርጋ ከፍላ ሳትለያይ፡፡

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮሽታ (ዘ-ጌርሣም)

1 Comment

  1. የዚህችን ዓለምን ማዘንበል ሲፋለሙ ያለፉ ብዙ ናቸው። ጥቂቶችን ወፈፌ፤ እብድ፤ ሥራ ፈትና ሌላም ስም እያወጣንላቸው እያለ የማይታለፍ ሥራ ጥለው አልፈዋል። ከእነዚህም መካከል አንድና የጊዜው ግዞተኛ አቤ ጉበኛ ነው። በግዞት ከሚኖርበት የአሜሪካ ምድር ሃገሬ ውስጥ ለውጥ መጣ በማለት እቃውን ጠቅሎ የገባው ደራሲ አቤ ጉበኛ በመንግስት እጅ እንደተገደለ የሚያመላክቱ ነገሮች ነበሩ። ከተጎዳበት ቦታ ደርሰው ያነሱት እንዳሉት የመጨረሻ ቃሉ “ተጠቃሁ” ነበር። ለህዝባቸው ፍትህ ፍለጋ ዘብጥያ የወረድ፤ በፓሊስ ቆመጥ የተቀጠቀጡ፤ ያለምንም ጥፋት በጨለማ ውስጥ በግዞት ዘመናትን የቆጠሩ እልፍ ናቸው። አቤ አልወለድም፤ የጉድጓድ ሚስጢር የመሳሰሉትን በመጻፍ ጥሎልን አልፏል። አቤ መጽሃፍ ጸሃፊ ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኛም፤ ገጣሚም ሌላም ነበር ግን ምን ይደረግ እውነትን ፍለጋ እንደቃተተ አለፈ። እውቁ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) በባለ ቅኔ ምህላ ላይ የሚያስተምረን በግጥሞቹ የፍትህን መጥፋት፤ የፈጣሪን ዝምታ፤ የሰውን ድንዛዜ አጥንት ዘልቆ በሚገባ ግጥሙ ነካክቶንና ቀስቅሶን ነው ያለጊዜው ቦግ ብሎ የደበዘዘው። ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ሌላው ዓለምንና ዙሪያውን እንደፈተለ ያለፈ ወገናችን ነው። ገጣሚዎች፤ ዘፋኞች፤ የመድረክ ሰዎች ኸረ ስንቱ ይቆጠራል ለምን? እንዴት? በማን? ስለማን? ከነማን ወዘተ የሆኑትን ቁልፍ ጥያቄዎች እየጠየቁ ቀድመውን ሰው ሂዶ ወደ ማይመለስበት ዓለም ተሻግረዋል።
    አሁን ደግሞ እንደ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የመሰሉ ጸሃፊዎች ህሊናችን እየጎነተሉ መቼ ነው የምትነቁት። የዛሬ መቶ ዓመት በታረሰበት ማረሻ ዛሬስ ለምን እናርሳለን። መሬት ላራሹ ብለው በተፋለሙበት መሬት ላይ እንዴት ነው መሬት ለባለሃብት የሆነው በማለትና ተጨማሪ ጭንቅላት አዟሪ ነጥቦችን በማንሳት የአንቀላፋውን ህብረተሰብ ለመቀስቀስ ይታገላል። ግን የፈጠራ ችሎታ ያላቸውንና ሩቅ ሃሳቢ ልጆቿን አንገት የምትቆርጥ ምድር፤ ሰማሁ እንጂ አየሁ ብሎ በማይመሰክርበት መሬት ላይ ፍትህ እንዴት ሊሰፍን ይችላል? ቢንቢ ነደፈኝ ብሎ መዶሻ ከሚያነሳ ህብረተሰብ ጋር እንዴት ነው ጭካኔና ዘረኝነቱን ሃይ በማለት ማስቀረት የሚቻለው? የፍጥረት መቃተት እውነትን ፍለጋ ነው። ሌላው ሁሉ ትርፍ አተካራ ነው። ምንም የብር መቆለል ለሰው ልጅ ጣፋጭ እንቅልፍን አያመጣም። ዛሬ በደርግ ጊዜ፤ በወያኔና በሻቢያ ዘመን በዚህም በዚያም ደም ሲያፈሱ የነበሩ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የህሊና ዲወላቸው ሁሌ እያቃጨለ አንዳንዶች ራሳቸውን ሲያጠፉ፤ ሌሎች ደግም የዝንተ ዓለም የጨለማ ጭጋግ ውስጥ ሆነው ሁሌ ጥላቸው ሲያስበረግጋቸው ይኖራል። የሰው ልጅ ግፍ ሰርቶ ሰላምን ሊያገኝ አይችልም። በዚህም በዚያም የተበዳይና የሟች ጩኸት ዝንተ ዓለም ይጣራል። ከመቃብር ማዶ ፍትህን ይጠይቃል። አቤ ጉበኛን ለግዞት ያበቁት፤ በህዋላም የገደሉት ለሃገር ቁመናል የሚሉ ተውሳኮች ናቸው።
    ደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር” በሚለው ግጥሙ ላይ ከብቸኝነት ግርጌ ያሰፈረውን ልዋስና ሃሳቤን ላጠቃል። እንዲህ ይለናል።
    ከተማው ተይዞ ሲጣል ምድረበዳ
    ሰው ከራሱ በቀር ለሌላው እንግዳ
    ሆኖ ሲውል ሲያድር በብቸኝነቱ
    ሞተች ይላል ዓለም ውስጣዊ ፍጥረቱ።
    ያለቅጥ የተንጋደደችውን ዓለም ደግፎ የሚያቆማት ምሰሶ የለም። የሚያለቅሰው ያለቅሳል። ጠግቦ የሚገሳው ያገሳል፤ ግፈኛው በግፉ ይቀጥላል፤ የድሃ አድግ ልጆች ለግፈኞች ሴራ ማስፈጸሚያ ለሃገርህ ነው፤ ለህዝብህ ነው፤ ተከበህ ነው ወዘተ እየተባሉ በየሜዳው ወድቀው ይቀራሉ። ሌላውም አካለ ጎደሎና የጭንቅላት በሽታ ይዞት ቃብዞ ያልፋል። መቼ ይሆን የከሸፈና የሻገተ ሃሳብ ይዘን ወገናችን ለመከራና ለስቃይ መማገድ የምናቆመው? ለተጠቁ፤ በግፍ ለተገፈተሩ ብሄርና ሃይማኖትን ከለላ ሳናረግ አለንላችሁ። አይዞአችሁ። ቀን ይለወጣል የምንላቸው? ሰው ሰውን አህያ ብሎ የሚሰድብበትና ሲኖ ትራክ ነድቶ የሚገልበት ሃገር ላይ ፍትህ ይመጣ ይሆን? ጠብቀን እንይ። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share