ፈጣሪ ፊቱን ወደ ሰው ይመለስ ዘንድ ፤ ሰው ሁሉ  ፤ በነገር ሁሉ ፣ እግዛብሔርን ማስቀደም አለበት – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ፈጣሪ ፊቱን ወደ ሰው ይመለስ ዘንድ ፤ ሰው ሁሉ  ፤ በነገር ሁሉ ፣ እግዛብሔርን ማስቀደም አለበት ።  ይሁን እንጂ ሰው ሁሉ በነገር ሁሉ የሥጋውን  ጥቅም  እንደሚያሥቀድም የታወቀ ነው ።  የሥጋ ጥቅም ሰውን በሽንገላ ኗሪ ያደርገዋል   ። የዓለም ተፈጥሮ ፣ የተፈጥሮ ውበት ቀልቡን ይገዛዋል ። እናም ተፈላሳፊው ሰው ልጅ  ፣ “ ሣቢ ፣ ጨምዳጅ ፣ አደዛዥ ና  አፍዛዥ የሴት ውበት   ፈጥሮ ሲያበቃ ፣ እግዜሩ ለምን አታመንዘር አለ ? “ በማለት ጥያቄ ይጠይቃል  ።

ሰው ልጅ ፣ አሁን እና ዛሬ   የሚያገኘውን ለህይወቱ ቅመም የሚሆነውን ይፈልጋል ። ማጣፈጫ ነገር ። ሴት ሆነወንድ በህይወቱ መደሠትን አጥብቆ ይሻል ። “ በዚህ ዓለም ከምግብ ፣ ከመጠለያ እና ከሠላም ቀጥሎ  የሚያሥፈልገውን ደሥታ ነው ። የተቃራኒ ፆታ ግንኙነትንም እዚህ ደሥታ ውሥጥ ይደመራል  ።

አማኙ ሰው ሁላ ፣ እግዛብሔርን አሥቀድማለሁ ” በአፊ  ይላል እንጂ የሚያሥቀድመው የየግል ደስታውን ነው ። በዓለም በህይወት ያለ ፣ የበዛው ሰው   በአፉ ብቻ ነው በነገር ሁሉ ፈጣሪውን የሚያሥቀድመው  ፡፡ በተግባር ሲፈተሽ ግን  ፤  ማሥቀደም ይቅርና በሐጢያት መፀፀት የለም ።    ፡፡ ሥለሆነም ሰው ማለት ያለበት ፦” አቤቱ የምሠራውን አላውቅም ና  ይቅር በለኝ ነው ። እንሆ ዛሬ ንሣሐ ገብቻለሁ ፡፡  ተመልሼም ለሥጋዬ ብዬ አልሸቅጥም ።  “ ። በቃ ፡፡ …

” በነገር ሁሉ እግዛብሔርን አሥቀድሙ” ቅዱሳን መፀሐፍት ቢሉንም እኛ ዓለማዊ  ሰዎች  ግን  እግዛብሔርን በነገራችን ሁሉ አላስቀደምንም ። በማሥተዋል ካያችሁት ከፈጣሪ ቃል መራቃችን  እውነት ነው ። የበዛው የእግዜር ፍጥረት የሆነው  ሰው ፥  እግዚአብሔርን አስቀድሞ አያውቅም ፡፡  ዓለማዊ ፣ ምድራዊ ሰዎች ሁላችን ፣ እግዚአብሔርን እያሥቀደምን አያደለም ። በምድር  ላይ ፈጣሪያቸውን  የሚያሥቀድሙ ሰዎች አይኖሩም ማለቴ እንዳልሆነ አሥምሩልኝ ። በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም ለፅድቅ የሚበቃ ተግባር እየፈፀሙ ያሉ ጥቂት ብፁአን እንዳሉ ይታወቃል ። መንግሥተ ሠማይ የእነሱ ናት ይላል መፀሐፍ ቅዱስ በሐዲስ ኪዳን  ።

ብዙዎቻችን ግን በአመዛኙ ዛሬ ና አሁን የምናሥቀድመው ገንዘብን እንደሆነ እሙን ነው ። ያለ ገንዘብ በዚህ ዓለም በህይወት ለመሠንበት ያሥቸግራልና ። ገንዘብን ተከትሎ ደግሞ ጥቅም የሚሉት ይመጣል ። ሰው ሁሉ ጥቅምን ሥለሚወድ ከሚጠቅመው ጋር ይጣበቃል ። በገንዘብም ፈቃድ ይኖራል ። በአቋራጭ መበልፀግ የሚመጣው በገንዘብ መጠቃቀምን ተከትሎ ነው ።…የሥጋ ደስታን ፍለጋ ።

ለሥጋ ደሥታ በእጅጉ በማሰብ ፣ በልተህ ታበላለህ ። ሌላውም እንዲሁ በተዋረድ  በልቶ ያበላል ። አንዳንዴም ለመብላት  ሲል ሊያስበላህ ሁሉ ይችላል  ። አፈር ። ( ከዛም ደቼ ብላ ! ይልሃል ። አፈር …) ለዚህ ነው በልቶ ሢተርፈው ፣ ሚጢጢ ከሚያጎርሰን አጠገብ ጭራችን ሥንቆላ አይወድቁ አወዳደቅ ሥንወድቅ የምንታየው ። አብልቶ ፣ አብልቶ ድንገት ጥግብ ሥንል  ” ደቼ ”  የሚያሥበላን ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰላማዊ ትግል በብዙሃን መጋናኛ ጭምር ታግዞ በወያኔ መቀልበሱ እና መዘዙ

በነገራችን ላይ ግለሰብ ብቻ አይደለም ደቼ የሚያሥበላው ። ህዝብም ፣ ከመሥመር የወጡ ፖለቲከኞችን እና ባለሥልጣናትን  ደቼ ያሥበላል ። ጥቂት የማንባለው ፖለቲከኞች ፣ ፈጣሪያችንን ማሥቀደም ይቅርና ፈጣሪን ሥለማናውቀው ፣ በውሸት ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጥፍራችን ሥለተሞላን  የኋላ ፣ ኋላ በትዝብት እያየን ያለው ህዝብ ደቼ እንደሚያሥበላን ከወዲሁ እንረዳ  ።   ለጊዜው ነው ፣ሆድ ሲያውቅ   ፣ በቀጣፊ አንደበት ተሞልተን ፣ ባልጀራችንን ከሥልጣኑ ለማውረድ ሥንል ብቻ ፣  ” መና ከሠማይ አወርድላቸዋለሁ ። ” እያልን የሚታዘበንን ህዝብ የምንሸነግለው  ።    ፣  ይኽ በቅጥፈት የተሞላ ድርጊታችንም        በኑሯችን ሁሉ እግዛብሄርን እንደማናስቀድም ይመሰክራል ፡፡…

ይኽ  ሁሉ ቅጥፈት ፣ ሥጋችን ከሌላው ሰው ሥጋ ይልቅ ደልቶት እንዲኖር በመፈለግ የሚከናወን ነው ።    በተለይም የአፍሪካ ፖለቲካ በመርህ ዓልባ ፣ ጀርባ ማከክና ማሳከክ የተቆላለፈ ነው ።  በአፍሪካ ያለ ፖለታከኛ እኮ ነው በአመዛኙ ፣ በጠራራ ፀሐይ እየዋሸ ፣ ከፈጣሪ ይልቅ ለሤጣን ሲያዠረግድ የሚስተዋለው ። ሰው መሆኑንን ፈፅሞ ዘንግቶ ራሱን እንደ አምላክ በመቁጠር ሰማይን በርግጫ የሚለው  ።

ፖለቲከኛው ፖለታካ ሥላልገባው ፣ ከፖለቲካል ሣይንሥ ውጪ ሆኖ ፣ የራሱን የፖለቲካ ወንጌል ፈጥሮ በመሥበክ እያጭበረበረ ቢኖር ባይገርምም ፣ ከፖለቲካው ዋና መድረክ የሌለነው እንዴት ነው ጥቂት እንኳን በነገራችን ላይ ሁሉ ፣ ፈጣሪያችንን ማሥቀደም ያቃተን ?  ከምር ሥንቶቻችን ነን የፈጠረንን አምላክ በውል የምናቅ ? ሥንቶቻችን ነን እግዚአብሔርን እረሥተን ከሌላው ልቀን ለመታየት ፣ ለመግዘፍ ፣ ” ምናልባትም አምላክ ለመሆን ” እየጣርን ያለነው ? … በገንዘብና በጠመንጃ ቡድን ፈጥረን የምንገዳደለው ሥንቶቻችን ነን ? ። በሤራ ተቧድነን የጓዳችንን ውድቀት ማፋጠን የዘወትር ድርጊታችን አይደለም እንዴ ? ። አብዘኞቻችን ተምረናል ፣ አውቀናል ። የምንል ሰዎች ። ለሥልጣን የሚታገሉትሥ “  ጓድ “  መንግሥቱ ኃይለማርያም  እንዳሉት “ አንድ በሆነችሁ የመሪነት ወንበር ላይ ፊጥ ለማለት “ ሎቢ ( ደላላ በብዛት ) መቅጠርና በደላላ አገሩን በሐሰት ወሬ ማዳረስን  ቢያያዙት ና በነገራቸው ሁሉ ሤጣንን ቢያሥቀድሙ አይገርምም ። የሚገርመው ፣  በጥቂት ምሁራን   የሐሰት  ወሬ  ፣ ተገፋፍተን ፣  የእኛ  በመንጋነት አገር ማተራመሥ  ነው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አፍ ያለው ጤፍ ይቆላል ወይንስ ካልተናገሩ ደጃዝማችነት ይቀራል - በፓስተር ዲጎኔ ሞረቴው  

ሌላው   አሥገራማ እና ግራ የሚያጋባው ነገራችን ፣ አንዱን ጎሣ አግዝፎ አንደኛውን ማኮሰስ የዘወትር ሹክሹክታችን መሆኑ ነው ። አንዱን  ጎሣ ባለምጡቅ ጭንቅላት እና መሪ ለመሆን  የተፈጠረ አድርጎ ፤ ሌላውን ጎሣ መምራት የማይችል ጠባብና መሐይም አድርጎ መሣልና ጥላቻ መፍጠርን ደግሞ የየዕለት ሙያ ያደረግን ጥቂት አንባልም።  ይኽ የሚመሠክረው በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ያለማሥቀደማችንን  ነው ። ሰው መሆናችንን ክደን ፤ አምሳያችንን ለመግደል ቢላ መሣላችንን ነው የሚያሳብቀው ።

እንሆ ዛሬም በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እንጎሥማለን ። የዘመናት መገዳደላችን ቀጥሏል ። ዛሬም    አንዳንድ ጎሣ ለመግደል የተፈጠረ ሀኖ በህለና ቢሥ ፖለቲከኞች ያለ ሐፍረት ይፎከርባበታል ።   ይኽ ድንቁርና አይደለም እንዴ ? በእልህና በቁጭት ፣ በበቀል ሥሜት ፣” በለው ጣለው ! ውገረው ! ልኩን አሣየው ! እሠረው ! አሰቃየው ! አሩ እንዲጠማው አድርገው ! ከዛም ለሞት አሣልፈህ ሥጠው ! ወዘተ ። ” ማለትን  ? ። ባህል አደረግነው እኮ !

አናም ዛሬ ምሁር ሲታሰር ፤ ” ይኼ ጥጋበኛ ደብተራ ! ዋጋውን አገኘ ። ” የምንለው እኩይ ምግባርን ባህላችን አድርገን አይደለም እንዴ ??? አይደለም  ? ታዲያ ምኑ ላይ ነው   ” በነገር ሁሉ እግዛብሔርን ወይም ፈጣሪያችንን አስቀድመናል ” የምንለው  ? ( ኃይማኖተኛነታችንሥ መገለጫው ምንድ ነው ? “ መግደል ነው ? ማመንዘር ነው ? በሐሰት መመሥከር ነው ? ጓደኛቻችን መጥላት ነው ? ዘወትር መሳደብ ነው ? በሥኬታማ ሰዎች እርር ድብን ብሎ መጨሥ ነው ? እግዛብሔርን ትቶ ለጣዖት መሥገድ ነው ? መሥረቅ ነው ?…”

ምንድነው የዛሬ ና የአሁን መልሣችን ? ማነው እኔ አልዋሽም ባይ ከመሐላችን ? ያለ ውሸትሥ ከሰው ጋር እንዴት ይኖራል ? ሰውን የማይጎዳ “ በነጭ ውሸት “ የሚፈረጅ ውሸት እኮ አብሮ ለመሰንበት እጅግ አሥፈላጊ ነው ። ማነውሥ በነጭ ውሸት ፣ የሰውን ገንዘብ ፣ በብልጣ ብልጥነት አልወሥድም ባዩ ? “ ንግድ በኢትዮጵያ የተፈቀደ ሌብነት ነው ። “ ያለው ማነው ? ረሳሁት ።

ሰዎች ሆይ ! ከነጋ እንኳ ሥንት ና ሥንት ጊዜ ሰውን የማይጎዳ ውሸት ዋሽተናል ።  ደሞምም በወሬያችን ጣልቃ ጥቂት ሰዎችን   አምተናል ። ሐሜት አውርተናል ።  …

የሚከፈው እና ትልቅ ጉዳት የሚያሥከትለው ፣ በምንም ሁኔታ ያልደረሰብንን ሰው ፣ በቋንቋውና በጎሣው ከእኛ ያለመመሣሠል ብቻ ጥርስ በመንከስ የምንፈፅመው ደባ ነው ። …

ደሞሥ ፣ በዕውቀቱ ፣ በችሎታው እንዲሁም አንዳንዱ በሀብቱ ከእኛ በመብለጡ ቀንተን ፣ እርሱን ለማጥፋት ወደ ባለውቃቢ ፣ ጠንቆይ ፣ ደብተራ ና መፅሐፍ ገላጭ ቤት ተደብቀን ና በግላጭ ፣ የምንመላለሰውሥ ሥንቶቻችን ነን ? ለመልካም እና ለበጎ ፣ ሰውን ለማሥተማር የሚተቹ፣ እንከንን የሚያሳዩ ፣ ደፋር የሆኑ ፣ ፊት ፣ ለፊት እውነትን የሚናገሩትን የምንጠላም ጥቂቶች አይደለንም ። ነውራችን  በህየወት ሣለን እንዳይገለጥብን በብርቱ የምንጠር ብዙዎች አይደለንም እንዴ ? …

እርግጥ ነው ፣ ሰው ፣ በተፈጥሮው ጠንካራ ጎኑን እንጂ ደካማ ጎኑን በአደባባይ እንዲነሳ ያለመፈለጉ እሙን ነው ። ይኽ ግብዝነት እና የራሥን አሥጠሊታ ገፅታ ለማወቅ ያለመሻት ፣ የተጀመረው  ከአቤልና ቃየን መፈጠር ጀምሮ ነው ።( የአዳም ልጆች ። )    ቃየን አቤልን በቅናት ተነሳስቶ ከሰዋራ ሥፍራ ሸንግሎ ወስዶት ሲያበቃ ገደለው ።  ከገደለው በኋላ ፈጣሪያችን ድርጊቱን አይቶ ነበርና ፣ የቃየንን   ምላሹን እያወቀ  ሲጠይቀው ፣ ያለው ምን ነበር  ? እጠቅሳለሁ ፣ ” እግዚአብሔር  ቃየንን አለው ” ወንድምኽ አቤል ወዴት ነው ? እርሱም አለ ፣ ” አላውቅም ፤ የወድሜ ጠባቂው  እኔ ነኝን ? ” ዘፍጥረት መዕራፍ 4 ቁጥር 9 ፡፡   ? …ዛሬም እኛም የእኩዩ ቅናት ዛር ሲሰፍርብን እንደ ቃየን እያደረግን አይደለም እንዴ ? …

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔና ትግሬ | መስፍን ወልደ ማርያም

እውር በነበርነበት ሰዓት የዓለምን መንገድ ፣ ከፈጣሪ በተሰጣቸው ፀጋ  በመምራት ፣ ወደ ብርሃን ያወጡንን እንደ ጠላት የቆጠርን ፤ ፈራሽ ሥጋችንን የምናሞላቅቅ በብልህ ሰዎች ምርኩዝም ሀብታም የሆንን  በየቀበሌው የለንም እንዴ ? … በዚህ እጅግ ጠርዝ በረገጠ እራሥ ወዳድነት መንገድ ተጉዘንስ እንዴት ነው ፣ ሁለት ሆነን ብዙ የሆንበትን ፣ ቤተሰብ በመልካም ሰብዕና የምንገነባው ? …

ከቤተሰብ ፣ ማህበረ ሰብ ፣ ከዛም ህብረተሰብ ፣ የማህበረሰቡ ሥብሥብ ደግሞ ህዝብ ይባላል ። ከዛም ይኽ ህዝብ መንግሥት ይመሠርታል ። ታዲያ ራሱን በመልካም ዲሢፕሊን ያላነፀ ፣ ሰው መሆኑንን እንዲረሣ ፣ እግዛብሔርንም በቅጡ እንዳያውቅ የተደረገ ፤  ትውልድ ፣ እንዴት ነው ፣ አገርን በማበልፀግ ና መጪውን ትውልድ ለማኩራት የሚችለው ? …

እንደ ህዝብ ፣በዚህ ዓይነት ከፈጣሪ በራቀ “  በጠልፎ መጣል “ መንገድ ተጉዘን  ና በጥላቻ ተሞልተን የምናልፍ ከሆነ እኮ ፣ ተተኪ ትውልድ ብሎ ነገር አይኖረንም ። የማን ዘር ጎመን ዘር ። የዘሬን ብተው ይዘርዝረኝ ይሆናል ነገራችን ። …” ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሣም ” እንዲሉም ማንኛውም ሰው ፣ ያደገበት ቤተሰብ ና ማህበረሰብ ግልባጭ በመሆኑ ከጥፋት አዙሪት ከቶም ለመውጣት አንችልም ፡፡

ሰው ውጥ የሆነ ቀና አመለካከቱም ሆነ እኩይ የሆነ መሰሪ ተግባሩ የሚመነጨው ካደገበትና ከኖረበት ማህበረሰብ ነው ፡፡ ….  ይኽንን እውነት በአንክሮ እናጢነው ። ለአፍታ በጭፍን መጓዛችንን አቁመን ራሳችንን ፣ ሰውነታችንን በብርሃን አእምሮ እንጠይቅ ፡፡ ሁላችንም ሰው ነንና ! እናም ይኽንን ሰውነታችንን ከተገነዘብን ፤ ዛሬ ላይ ሆነን ” አቤቱ ! የምንሠራውን አናውቅም እና ይቅር በለን ። ” በማለት በንሥሐ ወደ ቀልባችን እንመለስ ።   ወደ ቀልባችን ሥንመለሥ ነው ፣   በነገሬ ሁሉ  ፈጣሪዬን አሥቀድማለሁ ። “ በማለት አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችለው ።

 

1 Comment

  1. ለጻሃፊው ያለኝን አክብሮት በመግለጽ በሃሳቡ ግን ጭራሽ አልስማማም። ፈጣሪ ብሎ ነገር የለም። ችግሩ እኛው በእኛው ነን። የሰው አራዊቶች። ፈጣሪማ የምናስብበት የምናሰላስልበት ጭንቅላት ሃሳብን ከመግለጽ ጋር ሰጥቶናል። የነ ዳርዊን ትምህርት ሰው የመጣው ጦጣ መስል ከሆነ ምንጭ ነው በማለት አመጣጣችን ሂደታዊና ጅራታዊ ያረገዋል። እኔ በዚሁ ፍልስፍና እምብዛም አረካም። ግን አሁን ላይ ሰው ከሰውነት ወደ አውሬነት እየተለወጠ እንደሆነ በዓለም ዙሪያ ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመውን ግፍና ገመና ተመልክቶ የራሱን እይታ መውሰድ ይችላል። በቅርቡ በሁለት ክፍል የቀረበው የኢትዮጵያ ወታደሮች ሚስቶች በትግራይ የደረሰባቸውን ገመና ላዳመጠ ሰው የሆነ በሰው ላይ እንዲያ ያለ ግፍ ይፈጽማል ብሎ መገመት ይከብዳል። ግን ጉዳዪ ዛሬ አይደለም የተበላሽው በፊትም እንደዛሬው በዘርና በቋንቋ ተከፋፍለን አንዣለጥ እንጂ ግፍ በምድሪቱ ተለይቶ አያውቅም። የታቦትና የመስጊድ መብዛት እንደ አሸን የፕሮቴስታንት ቤ/ክ በዚህ በዚያም ብቅ ብቅ ማለት ለህዝባችን ያመጣው ሰላምና እፎይታ የለም። ከዚህም በላይ በየጊዜው የህዝቡ ልመናና ጸሎት ሰሚ የለውም። ወደ ላይ አንጋጠን፤ መሬት ላይ ተደፍተን ጸልየናል። ቀናቶች ሲከፉ እንጂ ሲሻላቸው አላየንም። ለዚህ ችግሩ እኛውና እንደ አረም በየስፍራው በፓለቲካ ድርጅት ስም ብሄርንና ቋንቋን ተገን አርገው ህዝባችን መነገጃና የስልጣን መወጣጫ ያደረጉት ስመ ምሁራኖች ናቸው።
    አሁን በትግራይ የሚሆነውን ዘርና ቋንቋውን ተገን ሳያረግ ለፈተሸ አስለቃሹ ሲያለቅስ፤ በዳዪ ተበደልኩ ሲል፤ የጠገበው ተራብኩ፤ ማንም ያልከበበውን ተከበብኩ እያለ ኡኡታ ሲያሰማ እንሰማለን። በዚህ ሁሉ ግን ምርጫ የተነፈገው የትግራይ ህዝብ በደሙ ዋጋ እየከፈለ ነው። አሁን ማን ይሙት ጌታቸው ረዳ የትግራይን ህዝብ ይወክላል? ውፋሬውን እዪት። እሱ በልቶ እያደረ ስንቱ ተሰዷል፤ ሞቷል፤ ተርቧል ታርዟል። ምድሪቱ ትቁጠረው። አሁን ይባስ ብሎ የትግራይ መሬት ነው ብሎ ወያኔ የሚያምነውን ምድር በጉልበትም ሆነ በሌላ መንገድ እናስመልሳለን ሲል የአማራው መሪ ደግሞ ይህ አባባል ቀይ መስመር ማለፍ ነው ይሉናል። እኛ ስንገዳደል እነርሱ ሊኖሩ። ምድሪቱ ለሁሉም የምትበቃ ምድር ናት። ከትግራይ የበቀሉ አረሞዎች ኢትዮጵያን ማጫ ካለበሷት በህዋላ ሰው ሁሉ ለእኛ ማለቱን ትቶ ለእኔ በክልሌ በማለት በራሱ በራፉ ላይ ቆሞ የክልል ባንዲራ ማውለብለብን እንደመሰልጠን ቆጥሮት ሰው ሲያባርርና ሲገድል ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራ እስከ ምዕራብ እያየን ነው። ይህ የአራዊት አስተሳሰብ ሁሉ በፈለገበት፤ በሃገሩና በምድሩ እንደ ፈለገ የሚኖርባት የጋራ የሆነች ምድር እስካልፈጠርን ድረስ ዛሬም ስንዴ ልመና ነገም ያው ነው የሚሆነው። ይህንም የሚያደርገው የሚያስብ የሰከነ አዕምሮ እንጂ ፈጣሪ ከሰማይ ወርዶ እኛን አያስታርቅም።
    በትግራይ የሰሜን ጦር ሲመታ አሻፈረኝ ብለው የሚታኮሱትን እናስታርቅ በማለት ገብተው የገላገሉ አስመስለው ራቁታቸውን እንዲረሽኑ ያረጉት የሃይማኖት አባቶች ናቸው። ቄስ በለው ጳጳስ በእኛ ላይ ይቀልዳሉ እንጂ ለሰማይ አምልክ መኖር ከቀረ ቆይቷል። ሁሉም አሸንክታቡን አብዝቶ የአቡሻክሩ አዋቂ እኔ ነኝ እኔን ስሙኝ ቢልም የሚበዙት የውሸት ክምርና የዘር ፓለቲካ ትርምስ ፈጣሪዎች ናቸው። ጊዜው ረዘመ እንጂ እውቁ ኢትዮጵያዊ ይልማ ዴሬሳ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በነጮች 1958 -1960) እንዲህ ብለው ነበር። ” ዘረኝነት በሽታ ነው። ኢትዮጵያ በሃገርም ሆነ በውጭ የቆመቸው ለሰው ልጆች መብትና ለህዝቦች አንድነት ነው” ዛሬ በህይወት ኑረው ያለንበትን ሁኔታ ቢመለከቱ ምን ይሉን ይሆን? የተጣመረን ህዝብ ለመከፋፈልና ለመበታተን የሚሻው የውስጥና የውጭ ሃይል ኢትዮጵያን እንደ ሶማሊያ፤ ሶሪያ፤ ሊቢያና ኢራቅ ለማድረግ እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም። ሙት ሰው ሌላውን ይዞ ይሞታል። ወያኔ በረጅም ታሪኩ አሁን እንደ ገባበት ያለ መጠራቅቅ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። እልፍ ገብሮ እልፍ አስገብሮ እዪን ሁለታችንም ጉንድሽ ቢል ማን ተጠቅሞ ማን ተጎዳ? ከአማራና ከአፋር ክልል ዘርፎ የወሰደውን በትግራይ በመካዝን ውስጥ ደብቆ ያስቀመጠው ምንም ሳይሰራበት ያው ከጊዜ ጋር የሸረሪት ድር አድሮበት ወያኔ ነፍሱን ለማትረፍ ይራወጣል። ከወያኔ ጋር እንዴት ያለ ድርድር ነው መንግስት ተብየው የሚያረገው? የራሱን ወገን በተኙበት ከረሸነ ሃይል ጋር እንዴት ነው ለሰላም ቁጭ የሚባለው? ወደ ኋላ የወያኔን ታሪክ ለሚረዳ የራሳቸውን ታጋዪችም አብልተው፤ አጠጥተው በተኙበት ነው የረሸኗቸው። ያ ያልተገራ ልምድ ነው የሰሜን ሰራዊትን በተኙበት ለማረድ ወያኔን ያነሳሳው። የወያኔ አረመኔነት የቆየና ሥር የሰደደ ነው። ከሰው ስብዕና ውጭ ናቸው። እጃቸው በሰው ደም የተጨማለቀ፤ ሂሊናቸው ያደፈ፤ የራሳቸውን ወገን አሳልፈው ለሱዳን ወንዶች ሰጥተው እህታችን ስትሰቃይ ቁጭ ብለው የሚስቁ ጉዶች ናቸው። ያቺ እህት ዛሬ በስዊድን ትኖራለች። ወያኔ አውሬ ነው። ይበላል፤ ይበላል።
    በማጠቃለያው ፈጣሪን በዚህም በዚያም እየነካካን ኡ ኡ ከማለት ይልቅ፤ የሰው አንገት የሚቀላውን፤ ሰውን አህያ ከአህያ ወልዳችሁ ተጋብታችሁ እያለ ራሱን የሚሰድበውን ያን ጭንቅላት ለመሞረድ መጣር ነው። ህጻናትን በጥይት ነው የምላቸው እናንተ ከአማራ ተወልዳችሁ ገለ መሌ የሚል እይታ እንዴት ባለ መልኩ ነው ለትግራይ ህዝብ እፎይታ የሚያመጣው? የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር። የትግራይ ህዝብ መፍትሄ በራሱ እጅ ነው። መታገልና ወያኔ እንደ ሞሶሎኒ ዘቅዝቆ መስቀል ያለበት ራሱ መጠለያና መጠጊያ የሆናቸው የትግራይ ህዝብ ነው። ለዚህም ነው ለውጥ የሚመጣው ለትግራይ ህዝብ በራሱ በትግራይ ህዝብ እንጂ በሌላ ሃይል አይደለም የምለው። ይህ እስካክልሆነ ድረስ ብንጾም፤ ብንጸልይ፤ ብናነባ፤ ብንስቅ (ወደው አይስቁ ዓይነት) ከሰማይ ጠብ የሚል ነገር አንድ አይኖርም። ሶስት ጊዜ በቀን በልቶ የማያድርን ህዝብ እግዚኦ በሉ እያሉ በባዶ ሆድ ማሰገድም ወንጀል እንጂ ጽድቅ አይደለም። በክራራይሶ ቢሆን ኑሮ ድሮ ችግራችን ይቋጭ ነበር። የችግሩ ምንጭ እኛው፤ የመፍትሄውም ምንጭ እኛው ነን። ሌላው ሁሉ ቅራቅንቦ ሃሳብ ነው። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share