ግጥም አጉሊ መነፀር ነው ፡፡ የማታየውን ያሳይኻል ፡፡
ሥማኝ ወዳጄ
ስማኝ ወዳጄ ምነው ?
ዛሬ በ21 ኛው ክ/ዘመን
የጥንቱን ሰው በመኮነን
የዛሬውን ትውልድ መክሰሱ.
ምን ይረባል መዋቀሱ ?
ሥማኝ ወዳጄ ምነው ?
ሰው የልብ ወደጁን ሲጠላ
እሳት ይሆናል የሚባላ
አለሁ፣አለሁ እያለው
ሥንቱ ጓዱን በለው ?
ስማኝ ወዳጄ ፣ ምነው ?
ዛሬ ጋኖች አልቀዋል
ምንቸቶች ጋን ሆነዋል
አያችሁ አይደል በጥበብ ልብስ
ድንቁርና አገር ሲያፈርስ ።
ስማኝ ወዳጄ ምነው ?!
በገንዘብ ገዝቶ ያንን ካባ
ወንበር ሲሰጠው በደባ
ይኸው ከላይ ተቀምጦ
መግዛት ጀመረ ደፍጥጦ ።
ስማኝ ወዳጄ ፣ ምነው ?
ዴሞክራሲ ሆኖ ለበጣ
ከሆነ ሂስ የሚያሥቀጣ
ቀና ምክራችን ሰሚ ካጣ
ወይኔ ! ወይኔ ! ነው ፤ ኋላ ፣ የሚመጣ ።
ስማኝ ወዳጄ ፣ ምነው ?
የእውነት አንደበት ተዘግቶ
ኃቅ አውሪ ሰው ተፈንክቶ
ውሸታም ሰው ከበረታ
አገር በወሬ ነው የሚፈታ ።
ሥማኝ ወዳጄ ምነው ?
በዝተዋል ጥላቻን ሰባኪዎች
በቋንቋ ጎሣ አጋጪዎች
በምለስ ጉልበት ብር ሊያፍሱ
እዩት ጥላቻን ሲያነግሱ ።
ስማኝ ወደጄ ፣ ምነው ?
በሬ አዋለጅ ሲበዛ
ይከተለናል ድንዘዛ
ተፈጥሮው ሳይሆን እርግዝና
ለምን ትላለህ ?
በሬዬ ወለደ አማጠኔ ! ፣ ።
( ይኽንን ግጥም መጋቢት 2013 ዓ/ም ነው ፣ የፃፍኩት ግንቦት 23 /2014 ዓ /ም አድቸዋለሁ ። – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ )
ሁላችንም አልጎምጓሚ ነን ፡፡
የእኔ ማንነኝ ጥያቄን በወጉ ያልመለስነው ፤ ሁላችንም አልጎምጓሚ በመሆናችን ፤ መደማመጥ አቅቶን ነውን ? ማልጎምጎም ፣ በውስጥህ የሆነ ነገር ማለትህን የሚያሳብቅ ውስጣዊ ንግግር ነው ፡፡ ቅሬታን አመልካች ፡፡ቅሬታ ያሳደረብኽ ሰው ኃይለኛ ከሆነ ቅሬታህን በማልጎምጎም እንጂ በግልፅ አውጥተህ አትናገርም ፡፡ በውስጥህ እራስህ ለራስህ የምታኝከው ፤የምትብሰለሰልበት ድምጽ አለ ፡፡ እንደ ልሳን ንግግር ዓይነት ፡፡ እንደ ግዕዝ ቅዳሴ ዓይነት ፡፡ እንደ ቁራን መቅራት ዓይነት … ላልተማረ ሰው እንግዳ የሆነ ፡፡…
እና ፣ ይኽንን ይዘህ ፣ ” ፈጣሪዬ ሆይ ! እኔ እንደ እነሱ ማልጓምጎም አልችልምና አንተው ራሥህ አልጎምጉምልኝ። ” ወይም ፤ ” እኔ እንደ ፓስተሩ ፤ እንደ ሼኪው ፤ እንደ ቄሱ በእውቀት መፀለይ አልችልም ፡፡ አንተ የጥበብ ዓምላክ ነህና አንተው ለእኔ የሚበጀውን አልጎምጉልኝ ፡፡ ” ያሉትን የዋኽ ዓባት ፀሎሎትን የላይኛው ሃሰብ ላይ ደምርና የማልጎምጎምን ፍቺ ቡሁለት መልኩ ተረዳ ፡፡ ቋንቋዎች በበዙና በሞኖፖል በተያዙ ቁጥር ፤ ቋንቋዎቹን የማያውቅ ሁሉ ፤ የቋንቋ ተናጋሪዎቹን ንግግር እንደማልጎምጎም እንደሚወስዱትም ተገንዘብ ፡፡ ለዚህ ነው የዋሁ አርሶ አደር ፣ በጠዋት በቤተክርስቴን ቅጥር ውስጥ ተገኝተው ፤ የማይገባቸውን የግዕዝ ቅዳሴ እያዳመጡ ፤ ” እኔ እነደእነሱ ማልጎምጎም አልችልምና ራስህ አልጎምጉምልኝ ፡፡ … ” በማለት ለፈጣሪ ፀሎታቸውን በፍፁም የዋህነት ያሰሙት ፡፡ …
የየዋሁ በለአገር ፀሎት የፈጣሪን ሁሉን ቻይነት በቅጡ የተገነዘበ ነው ፡፡ በእርግጥም ፤ ሰው ልጅ ራሱን ፤ ለራሱ ከማልጎምጎሙ በፊት እኮ ፈጣሪው ነበር ፤ከኤደን ገነት እንደ ተባረረ በየዋህነቱ ዘመን ፤ ገና ከፍጥረቱ የሚያልጎመጉምለት ፡፡ ” ጥረህ ግረህ ብላ !” ተብሎ፣ ወደ ምድር መጥቶ ፤ በዘመናት ብዛት ፤ ምድርን እንደ አሸዋ ከመሙላቱ በፊት ፤ ስለ ኑሮና ህይወት የሚያውቀው ባለመኖሩ ማልጎምጎም እንኳ አይችልም ነበር ፡፡
ቅዳሴ ፤ መቅራት ፤ መስበክ እና መዘመር አይችልም ነበር ፡፡ ጥንቆላ ፣ አስማት ፣ አንደ ዕርቢ ፣ ኮኮብ ቆጠራ ፣ መተት ፤ ደንቃራ ፤ ቦረንትቻ ፤ አቴቴ ወዘተ ፡፡ ፈፅሞ አያውቅም ነበር ፡፡ በቅሬታ ማልጎምጎም ካለመቻሉ የተነሳም ፈጣሪው ራሱ ነበር ለፍጥረቱ የሚያልጎመጉምለት ፡፡ ሁሉን ቻዩ ፈጣሪ ነበር እንዳሻው እና እንደፍቃዱ በፀጥታ እያልጎመጎመ የሚያኖረው ፡፡…ዛሬ እንዲህ ምድር እንደ ሸማ እያለቀች ፤ በርሃው እየተስፋፋ ፤ የሰው ክፋት እየተንሰራፋ ፣ ከመምጣቱ አስቀድሞ ፤ ሰው ያለብዙ ድካም ፤ የሚያሻውን ምግብ ከየትም በቀላሉ ያገኝም ነበር ፡፡ መጠለያውም በየዋሻው ፣ ነበር ፡፡ ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ለካ ! …
ሰው ልጅ በጊዜ ብዛት ፤ ከነበር ባሻገር ፤ ጥንተ ፍጥረቱን የሚያሥረዳ መታወቂያ ለማግኘት ብዙ ርቀት ተጉዞ ምርምር አድርጓል ። አፋዊ ምርመራ ና ትንተና በመሥጠት “ሀ” ብሎ በመጀመር ። ለጠየቀውም ጥያቄ አከራካሪ ና ዛሬም የሚጠየቅ ምላሽ የሚፈልግ የቀድሞውን ጥያቄ ግን አለዛቢ መልሥ አግኝቷል ።
ይህ የመጠየቅ እና በተመሥጦ አሥቦ የመመለሥ ብቃት ሃሳቢውን ግለሰብ ፈላስፋ ሲያሰኘው፣ክዋኔውንም ፍልሥፍና አሰኝቶታል ። ፍልስፍና የመጠየቅ ና ጥያቄውንም በአሳማኝ መንገድ “በሎጂክ” የመመለሥ እና መልሱንም እንደገና የመጠየቅ ሳይንሥ ነው ።
ሌላው ከፍልሥፍና በተፃራሪ ያለ ሣይንሥ ” ማየት ማመነው” የተባለ ሣይንሥ ነው ። አንድ እና አንድ ሁለት መሆናቸው ብቻ ሣይሆን አንድ ራሷ ቢሊዮን ቦታ ተቆራርጣ ያላትን መጠን በተጨባጭ የሚገልፅ ሣይንሥ ነው።
ይህንን በሂሣብ ፣በፊዚክስ፣ በባዮሎጂ፣ በኬሚሥትሪ፣ወዘተ በተባሉ ፣አይቶ በማመን የዕውቀት ዘርፎች አማካኝነት የሚገለፀውን ሣይንሥ፣ ሰው ተጠቅሞ ማንነቱን ለመረዳት እየጣረ ፣እግረ መንገዱን ኋላ ቀር አኗኗሩን አዘምኗል።
ይህቺ ዓለም በታላቁ ፍንዳታ “a great big bang ” ነው የተፈጠረችው ፣ ብሎ የሚያምነው ሣይንሥ በሥልጣኔ በደመቀው ሀገር ፤ የዚህን እውነት ለማሥረዳት የሚችል ግዙፍ የምርምር ተቋም በስለጠነው ዓለም ገንብቶ ያለእረፍት በመመራመር ላይ ይገኛል።
ሰው የራሱን አፈጣጠር ለማወቅ ዛሬም በምርምር ላይ ነው ። በሣይንሣዊ መንገድ ሰው ሥለራሱ አፈጣጠር እስከዛሬ ቁርጥ ያለ መልስ አላገኘም ። ከዳርዊን ጀምሮ ብዙ ሣይንቲሥቶች የራሳቸውን መላምት በማቅረብ በመላምታቸው መሰረት ሥለ ሰው አፈጣጠር በተጨባጭ ለማወቅ ጥረት አድርገዋል ። በሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለውን ዐፅም ከከርሰ ምድር ቆፍረው በማውጣት ፣ሰው ከሚሊዮን ዓመታት በፊት በምድር ላይ ሲኖር እንደነበር መሥክረዋል ። ሆኖም ተገኘች የተባለችውን አንዷን “ሉሲን” ወይም የኛዋን በአፋር ከርሰ ምድር በአርኪዮሎጂስቶች የተገኘችውን ” ድንቅነሽን ” ብቻ ለምሳሌ ብንወሥዳት ሰውን የመሰለ ቅርፅ አላት እንጂ ፍፁም የዛሬውን ሰው እንደማትመስል መገንዘብ ከፈጣሪ ጋር ከመጣላት ያድነናል ።
ለዚህም ነው ፣ ሰው እኔ ማን ነኝ የሚለውን መልሥ ለማግኘት ዛሬም በሣይንሣዊ መንገድ በመጣር ላይ የሚገኘው።
እርግጥ ነው ፣ሣይንሥ በየጊዜው መላምቶችን የሚያሥቀምጥና የመላምቶቹን እውነትነት ለማጣራት ያላሠለሰ ምርምር የሚያደርግ ነውና ነገም በምርምሩ ሌላ ለጆሮ እንግዳ ነገር እንደሚያሰማን እንረዳለን ። እኔ ማነኝ ? ኬትስ መጣው? ማን ፈጠረኝ ? የሚለውን ጥያቄ በተጨባጭ ለመመለስ ለሳይንሥ ከባድ ነው።
ይሁን እንጂ ሰው፣ሳይንሥን በመጠቀም ሰለሰውና ሥለምድር ውሥጣዊና ውጫዊ ተፈጥሮ በጥልቀት አጥንቷል ። በጥናቱ፣በምርምሩ ና በፈጠራው፣ይኽቺ ምድር ጠፊ መሆኗን ተገንዝቧል ። እናም ማምለጫውን እየፈለገ ነው ። በጠፈር ላይ ባሰማራቸው ሳተላይቶች አማካኝነትም የአሁኗን ምድር የመሰለች ፣ ፕላኔት በጠፈር ውሥጥ ትኖራለች ብሎ ፣ፍተሻውን አጠናክሮ ቀጥሏል ። በጠፈር ላይ እየተገነባ ያለውንም የሰዎች መስፈርዬን አትዘንጋ ፡፡ ምክንያቱም ከኒኩሌር ቦንብ መደበቂያ ዋሻ ቱጃሮቹ መንግስታት ቢያዘጋጁም ፤ የኒኩለር አረሩ በየጊዜው ዘምኖ ፣ በየተራራዎቹ ስር ቢሊዮነሩ ሁሉ የሰራውን ከመሬት በታች ከ300 ሜ በላይ ምሽጎ ወይም (Nuclear Bomb Shelter ) የማጥፋት አቅም እንዳለው ከወደ ቻይና እየተነገረ ስላለ ነው ፡፡ …
ለዚኽም ይመስላል ፣ በ2050 ይህንኑ እውነት ማረጋገጥ እንደሚችል ተስፋ አድርገው ቱጃሮቹ ያለመታከት ግሩም የፈጠራ ሃሰባቸውን በተግበር ለመተርጎም በብርቱ እየተቀሳቀሱ ያሉት ። ሩሲያ ኒኩለር ቦንብን ካልተጠቀመች ፣ በ2050 እጅግ በጣም የሚደንቁ በአየር ና በምድር የሚንቀሳቀሱ በኤሌትሪክ የሚሰሩ አውሮፕላኖችና መኪናዎች እፈጥራለሁ ብለዋል እነ አማዞን ። ከዚህም በላይ ሰው እጅግ የተራቀቁ የጠፈር መንኮራኩሮች በ2050 ይኖሩታል። እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጣራ ይነካል ፡፡ አጀኢብ ያሰኛል ፡፡ ( የዘሪቱ አርቴፊሻል ዘፈን እውን ይሆናል ፡፡ )
የበለጸጉት አገራት ፤ ኑሮን ከማዘመን እና የህይወትን ስቃይ ከመቀነስ አንፃር የሚሄዱበትን እና የሄዱበትን እርቀት እስቲ ለአፍታ አስቡት ? እኛ እዚህ በሀገራችን በቋንቋ በዘር፣በጎሣ በመንደር ተደራጅተን እርስ በእርሥ እንናቆራለን ። ከመናቆርም ባሻገር ሰው መሆናችንንም ክደን፣በቋንቋ አማካኝነት ላገኘነው ሥልጣን ሥንል “በታላቅ ግብዝነት” እንደ ባቢሎን ግንበኞች ባለመደማመጥ እርስ በእርሳችን እንባላለን ፡፡ በዕውቀት የበለፀጉት አገሮች ግን ፤ ይህቺ ምድር እንደጨርቅ ከመጠቅለሎ በፊት ፣ሌላ መጠጊያና ፣ህይወትን ማሥቀጠያ ዓለም ለማግኘት ያለእረፍት እየጣሩ ነው ።
እንደእነሱ ፣ እጅግ በመጠቀ ቴክኖሎጂ ታግዞ ሥለጠፈር መመራመርና ሌላ ምድርን ለመፈለግ መጣርን ባንታደል፣” በጠበቀ እምነታችን ” እንዴት ፣ የፈጣሪያችን ናት የምንላትን ምድር ፣በኃይማኖታችን አግባብ በመረዳት፣ ሁላችንም በፈጣሪ የተገኘን የአንድ እናት ና የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን ለመገንዘብ ያቅተናል ???
እኔ ማን ነኝ ? ማን ነው በመጀመሪያ የፈጠረኝ ? የሚለውን ጥያቄ በሃይማኖታዊ መንገድ መመለስ ከባድ አይደለም ፡፡ እንደው በኃይማኖት ሰበብ ፣ ቤተ ክርሥቲያን ፣መሥጂድ ና ሌሎች ቤተ እምነቶች እየሄድን እንጂ የሁላችንም ፈጣሪ አንድ መሆኑን ማመን ከቶ እንዴት ይሳነናል???
ሰው የማንነቱ ጥያቄ በዓለማዊና በፍልሥፍናዊ መንገድ ሲታይ የመክበዱን ያህል በሃይማኖት መነፅር ሲታይ ፣ እጅግ ቀላል ሆኖ ሣለ፣ ለምን እምነተ ቢሥ እና ፣ በአሳዛኝ መልኩ የሚታይ አስገራሚነት ያለው ፣ በማሥመሰል የተካነ ኃይማኖተኛ ሊሆን ቻለ ???
እንደሚታወቀው የሃይማኖት እውነት ማመን ብቻ ነው። ያለአንዳች ማንገራገር የዕምነቱን የተፃፈና ያልተፃፈ የህልውና መልስ መቀበል ና በጥቅሉ “ሰው የፈጣሪ ፍጥረት መሆኑን ማመን ነው።
ሰው ፈጣሪ የሰራው ሸክላ ነው።” ብሎ ማመን ነው ። እናም ሸክላ ነህና ፈጣሪህን እግዜር ወይም አላህን መጠየቅ አትችልም ። ያአንተ ሰው የፈጠረው ኮፒዊተር ለምን እንዲህ አርገህ ሰራኸኝ ብሎ እንደማይጠይቅ ሁሉ አንተም የፈጣሪ እጅግ ውስብስብ ኮፒዊተር ነህና ፈጣሪህን ለምን እንዲኽ አድረገህ ሰራኸኝ ብለህ የመጠየቅ ችሎታ የለህም ። ፍጥረተህን ፈጣሪህ ብቻ ና ብቻ ነው የሚያውቀው ። ይህንን የእምነት እውነት በምርምር እደርስበታለሁ ማለትም ከንቱ ድካም ነው ።
ከቶም የፈጠረህን ና የምታመልከውን ፈጣሪህን ልትመረምረው አትችልም ። ኃይማኖታዊ መፅሐፍቶችም ይህንን ይመሰክራሉ ። የአንተ እና የእኔ፤የእሷ ና የእነሱ ግዴታ ሃይማኖታችን ስለሰውነታችን የሚገልፅልንን በፍፁም ልባችን እውነት እንደሆነ ማመን ብቻ ነው ። ካላመንን ሃይማኖቴ ነው ማለት አንችልም ። ከተከራከርን እና ሃይማኖታችንን ከተጠራጠርን ደግሞ እምነታችን ከንቱ ነው።
መስጂድ፣ቤተክርስቲያን፣ሙክራብ፣ እንዲሁም የተለያየ ማምለኪያ ሥፍራ መመላለሳችንም ለታይታ ነው። ለታይታ ተመላላሽ ሰዎች፣ የፈጣሪን መኖር ክደው፣በውስጣቸው ምንም እምነት ሳይኖር፣ ለድብቅ አላማቸው ስኬት ሲሉ በየሃይማኖት ተቋማቱ ነጋ ጠባ የሚመላለሱ ናቸው። ፈጣሪ የሐጥያት ድርጊታቸውን እያየ ብቻ ሳይሆን ፤ ሃሳባቸውን እያወቀ ዝም የሚላቸው፣ ለምንድነው ? የሚሉ ጠያቂዎች ቢኖሩም ፣ “ፍጥረቱን እንደፍጥርጥሩ የማኖር መብት ያለው እርሱ ነውና ዕድሜ ሥጠን እያላችሁ የሱን እንከን አልባ ሥራ ለመመልከት ናፍቁ ሁኑ እንጂ ፤ በሐጢያተኞች አትቅኑ ። እላችኋለሁ። “የሐጥያት ደሞዙ ሞት ነውና !” ይላል ቅዱስ መፅሐፍም ፡፡
ደሞም በዕምነት ተቋማቱ እንደሚያምኑ ለማስመሰል ዘወትር መመላለስ፣ ቀድሞ የነበረን የሃይማኖተኝነት መታወቂያ ላለማጣት የሚከወን አሳዛኝ የማሥመሰል ድራማ ከሆነ የቁም ሞትን ማስከተሉ አይቀርምና እንጠንቀቅ ።
አንዳንዶች ፈጣሪያቸውን በሚያመልኩበት የሃይማኖት ተቋም እንደነሱ የሚመላለሱ፣በሥራ የተተረጎመ እምነት ያላቸው፣ የሃይማኖቱ ቤተሰቦች ” ምን ይሉኛል ? ከዕድር፣ከሰንበቴ፣ከማህበር፣ከጥዋቸው ፣ባሥ ሢልም ከጉርብትናቸው ቢያገሉኝስ???” በማለት ነው፣በትወናው የሚገፉበት ና — ድራማውን ዛሬ ቢያቆሙት ለስጋም ሆነ ለነፍሳቸው ይበጃቸዋል ፡፡ ሳል ይዞ ስርቆት እንደማያወጣ ሁሉ ሐጥያትን ፣ ዘረኝነትን ፣ ክፋትን እና ምቀኝነትን ተሸክሞ እምነትም አያጸድቅም ፡፡
ዛሬ ዛሬ እልም ያሉ የቋንቋ አምላኪዎች ፣ በየዕለት ኑሯቸው፣ ስለማይኖሩበት የፅድቅ መንገድ ያለመታከት ሲያወሩ ና የሃይማኖት ተቆርቋሪ መሥለው ለመታየት የሚጥሩ ሆነው እናገኛቸዋለን ። ይህ ድርጊታቸው ፣ ምን ያህል የስነ ልቡና ችግር እንዳለባቸው ይመሰክራል እንጂ ” ጻድቅ ” አያሰኛቸውም ። ጥቂት የማይባሉትም ጨርቃቸውን ያልጣሉ እብዶች መሆናቸውን ድርጊታቸው ይመሰክራልናል ።
እንደነዚህ አይነቶቹ ሰዎች እንዲሁ ፤ በነጻ ከፈጣሪ የመቀበልን የየዕለት በዕለት ክስተት እና የየሃይማኖታቸውን ቀኖና እና ዶግማ ተከትሎ በእምነት ፈጣሪያቸውን እያመለኩ መጓዝን በውስጣቸው ገድለውታል ። በዓለም ና በመንፈሳዊ ህይወት መካከልም በከንቱ የሚዳክሩ አሳዛኝ ፍጡር ሆነዋል ። “እኔ ማነኝ?” የሚለውን መልሥ ከኃይማኖታቸው ለማግኘት እንዳልቻሉ መንቀዠቀዣቸው፣ ለውሸት፣ ለሌብነት፣ ለማወናበድ፣ለመሥረቅ፣ለመዝረፍ ና ለመግደል ያለማመንታታቸው ይመሰክራል ።
የእኛ ሰው፣እጅግ የቀለለውን የኃይማኖት እውነት እንኳን ያልተገነዘብ ምሁር ነኝ ባይ ይበዛበታል። ያልተማረውማ እምነቱ ጠንካራ ነው ። በግእዝ ባያሥቀድሥ እና ከቅዳሴው ጋር ህብረት ባይኖረው ” እኔ እንደቄሶቹና እንደ አንዳንድ የተማሩ መዕመናን ማልጎምጎም ሥለማልችል አንተው አልጎምጉምልኝ ” በማለት የእምነቱን ጥንካሬ ለፈጣሪው ይገልፃል ። የፈጣሪን እውነት በየዋህነት በመመስከሩም ብፅእናውን ያገኛል ። …