May 28, 2022
ጠገናው ጎሹ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰኙት የፖለቲካ ድርጅቶች ለዘመናት ከዘለቀው እና ግዙፍና መሪር ዋጋ ከተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ማለትም በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ (ኦህዴድ -ብልፅግና) አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ከማድረግ የትግል ሃዴድ ተንሸራተው አሁን ከተዘፈቁበት ፋይዳ ቢስ የእሮሮና የአቤቱታ ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ለምንና እንዴት እንደሚርመጠመጡ ብዙ ማለት ይቻላል ።
አዎ! የተደላደለ ኑሯቸውን ትተው ለመሠረታዊ ዴሞክራሲዊ የሥርዓት ለውጥ ኤርትራ በርሃ እንደገቡና ያው ዓላማቸው ሙሉ በሙሉ እስካልተሳካ ድረስ እረፍት እንደማይኖራቸው ድጋፉ ያስፈልገናል ያሉት ዳያስፓራ በሚኖርባቸው የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወሩ “ቃል ለምድርና ለሰማይ” ሲሉ ኖረው ቢያንስ በቅጡ አስቦ ለመወሰን የሚያስችል ጊዜና ሁኔታ ሳይወስዱ የሸፍጥ ፣ የሴራና የግፍ ሥርዓቱን በተረኝነት ለተቆጣጠረው የኢህአዴግ አንጃ ቡድን (ኦህዴድ -ብልፅግና) ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የህዝብን መከራና ውርደት እንዲራዘም ስላደረጉትና እያደረጉት ስላሉት የቀድሞ ግንቦት ሰባቶችና የአሁኑን ኢዜማ ተብየ በዋናነት ስለሚዘውሩት ፖለቲከኞች ብዙ ማለት ይቻላል።
አዎ! ከሌሎች አናሳ የፖለቲካ ድርጅቶች እና በግልም ተጠራርተው ኢዜማን በመቀላቀል የዚሁ ሸፍጠኛና ሴረኛ ሥርዓት አካል የሆኑትን ፖለቲከኞችን በተመለከተም እንዲሁ ብዙ ማለት ይቻላል ።
የዛሬው ሂሳዊ አስተያየቴ ግን ከሰሞኑ ሁለቱ የተቀዋሚ (ይቅርታ “የተፎካካሪ”) ድርጅቶች አመራር አባላት ያስነበቡንን ወይም ያስደመጡንን የእሮሮ እና የአቤቱታ ደብዳቤ የማስገባት (የማቅረብ) ፖለቲካ በሚመለከት ይሆናል።
የአገራችን ፖለቲካ አስከፊነትና አስፈሪነት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች አንደኛው የሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪ እና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ሥርዓተ ፖለቲካ የመሆኑ ጉዳይ ፈጽሞ አያጠያይቅም ። ማስረጃና መረጃ ፍለጋ ብዙ ርቆ መሄድንና የትንታኔ ጋጋታንም የግድ አይልም።
ሥርዓተ ኢህአዴግ (ኦህዴድ- ብልፅግና) በንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃና ደም የተጨመላለቀ እና ያለ ሥር ነቀል የፖለቲካ ህክምና ጨርሶ የማይድን የመሆኑ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ የሥርዓቱ እድሜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲራዘም ያደረገውና በማድረግ ላይ የሚገኘው ምሁር ወይም ልሂቅ ነኝ ባይ የህብረተሰብ ክፍልም ቢያንስ ከህሊና እና ከሞራል ተጠያቂነት ፈፅሞ ማምለጥ የማይችል የመሆኑን መሪር እውነታም ለማስተባበል የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት አልነበረም። አሁንም የለም። ይህ አስቀያሚ የፖለቲካ እውነታ እስካልተለወጠ ድረስ ወደ ፊትም አይኖርም።
እንደ ኢዜማ እና አብን የመሳሰሉ ተፎካካሪ ተብየ ድርጅቶችም እንታገልለታለን በሚሉት ህዝብ ወይም ማህበረሰብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ በተግባር የተገኙት ግን የብልግና እና የግፍ ፖለቲካ ቁማር ከሚቆመርበት የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ጋር የፖለቲካ አመንዛራነትን ሲፈፅሙ ነው። ይህ ባይሆንማ ኖሮ ለአራት ዓመታት የዘለቀውና አሁንም በተረኛ አንጃዎች በሚመራው ኢህአዴግ ሠራሽ ሥርዓት እየተካሄደ ያለውን የለየለት የአፈና፣ የእስር፣ የማሳደድ ፣ የቁም ስቃይ ፣እና የግድያ ዘመቻ ጨርሶ ማስቆም ባይቻል እንኳ ቢያንስ አደብ ማስገዛት በተቻለ ነበር ።
የኢዜማ ፣ የአብንና የሌሎች ተመሳሳይ የተቀዋሚ ተብየ ድርጅቶች ፖለቲከኞች የተዘፈቁበትን አደገኛ የፖለቲካ አረንቋ የተረዱት ዛሬ ይመስል እንደ አዲስ እያነበነቡ (እያመነዠኩ) “የረቀቀውን የፖለቲካ ስልታችን እወቁልን” ሲሉን ጨርሶ ህሊናቸውን አይኮሰኩሰውም።
ኢህአዴግ ሠራሹን የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓትን በማስወገድ ሳይሆን በእርሱ አመራር ሰጭነት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ ይቻላል በሚልና ከመሪሩ ሃቅ ጋር ጨርሶ በማይገናኝ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ የሚርመጠመጡ እንደ አንዱዓለም አይነት የኢዜማ ፖለቲከኞች ሁኔታ ባይገርምም ያሳስባል ። በዘመን ጠገቡ የአደንቆሮ ገዥ ቡድኖች ሲሰማቸው (ሲያደምጣቸው) የኖሩት አስቀያሚ ቃላት በእጅጉ ስላንገፈገፈው በውብ ቃላት የተነገረው ወይም የተፃፈው ሁሉ እውነት እየመሰለው በእጅጉ ግራ የተጋባውን መከረኛ የአገሬ ህዝብ በመስማት ሳይሆን በመኖር ተሞክሮ አሳምሮ የሚያውቀውን አስከፊ ዘመን እንደ አዲስ የፖለቲካ ግትኝ ይተርኩለታል። ይህን ሲያደርጉ እናንተስ የትና ከማን ጋር ነበራችሁ? አሁንስ የትና ከማን ጋር ናችሁ? ተብለው ቢጠየቁ ለዚህ ሁሉ መከራ ዋነኛ ምክንያት ከሆኑትና በሥልጣን ሽኩቻ አገርን የመከራ መናኸሪያ እያደረጉ ካሉ ሃይሎች ጋር ስንፋለም ነበር ለማለት እንደማይቃጣቸው እገምታለሁ።
እናንተ የፖለቲካ ሸሪካችሁ ባደረጋችሁት ተረኛ ገዥ ቡድን የገንዛ አገራችንና ቀያችን ምድረ ሲኦል ሲሆኑብን እጅግ ሰንካላ የሆነና ከሸፍጥ ፖለቲካ የሚመነጭ ምክንያት እየደረደራችሁ ከቆያችሁ በኋላ አሁን በአጋጣሚ ብቅ ብላችሁ ለዓመታት የዘለቀውን የመከራና የውርደት ትርክት መልሳችሁ ለምንድነው የምትተርኩልን? የሚለውን ፈታኝና መሪር ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የፖለቲካና የሞራል አቅም የሚኖራቸውም አይመስለኝም።
ከቶ የትም ሊደርስ እንደማይችል እያወቁ የህዝብን የመሠረታዊ ለውጥ ጥያቄ ክደው አባል ለሆኑበትና ከቤተ መንግሥት የደረሰውን ሁሉ እጅ እያወጣ ይሁን ከማለት በስተቀር ሌላ ፋይዳ ለሌለው ፖርላማ ተብየ የአቤቱታ ደብዳቤ መፃፋቸውን እንደ ትልቅ የፖለቲካ ሥራ እወቁልን የሚሉን እንደ ክርስቲያን ታደለ (የተከበሩ የኦህዴድ-ብልፅግና አጃቢ የፓርላማ አባል ) አይነት ፖለቲከኞች የፖለቲካ ጨዋታ ጨርሶ የትም አያደርስም።
ይህ አይነት ፋይዳ ቢስ ወይም እያስመሰሉ የመኖር የህዝብ ተወካይነት የሚያስታውሰኝ ከዛሬ አሥራ ሰባት ዓመት በፊት (እአአ 2005) ተመርጦ ያለ ፓርቲው ፍላጎት ፓርቲውን ወክሎ የአሻንጉሊቱ ፓርላማ ብቸኛ የተቃውሞ ፖለቲካ አሻንጉሊት በመሆን በመከረኛው ህዝብ ስም ፋይዳ ቢስ ጩኸት ይጮህ የነበረውንና አሁንም በኢዜማ አባልነቱ የአዲስ አበባ (የኦህዴድ- የአዳነች አቤቤ) ጥሩ አሻንጉሊት የሆነውን ግርማ ሰይፉን ነው።
ለነገሩ በየፖለቲካ ታሪክ ምእራፉ የገጠሟት የውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነው ታላቅና ታሪካዊት የምንላት አገር የዓለም ጭራ እና መሳቂያና መሳለቂያ የሆነችው በእንደነዚህ አይነት እንጭጭና የግልና የቡድን ፍላጎት (ጥቅም) አሳዳጅ በሆኑ ፖለቲከኞች እጅ ሥር የወደቀች እለት ነው። በተለይ ከአራት ዓመታት ወዲህና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት እያየነውና እየሰማነው ያለው የገዥዎች እጅግ ጭራቃዊ የፖለቲካ እብደት የዚችን አገር ማቆሚያ ያልተገኘለት የመከራና የውርደት ዶፍ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ቀጥሏል።
ለመሆኑ ከወንጀለኛ ሥርዓት ጋር እየተሻሹ (የፖለቲካ አመንዝራነትን እየፈፀሙ) ልዑላዊትና ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ስለማድረግ አብዝቶ መደስኮር (መስበክ) አደንቋሮ ገዥ ቡድኖች ያደነቆሩትንና ግራ ያጋቡትን መከረኛ ህዝብ ይበልጥ ለማደንቆርና ግራ ለማጋባት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን አይነት ፋይዳ ሊፈይድ ይችላል? ምንም!
በእንዲህ አይነት እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ እንቆቅልሽ አዙሪት ውስጥ የሚርመጠመጡ የፖለቲከ ወይም የሲቪክ ወይም የሙያ ማህበራት መሪ ተብየዎችን ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ (አካፋን አካፋ በሚል) የፖለቲካ አቋምና ቁመና ለመሞገት የሚያስችል ወኔ ካጠረን ስለ ዴሞክራሲያዊት የጋራ አገር እውን መሆን አብዘተን መስበካችን ቅዠትነት እንጅ ራዕይነት የለውም።
ለሦስት አሥርተ ዓመታት በሁለንተናዊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከበሰበሰና ከከረፋ ሥርዓት እጅግ ወሳኝነት ያላቸውን ማለትም የህዝብ ደህንነትን የማስጠበቅ፣ ህግና ሥርዓትን የማስከበር ፣ ሰብአዊና የዜግነት መብቶችን የማረጋገጥ ፣ ከፍፁም ድህነት የመላቀቅ እና ሰላምን የመስፈን ጉዳዮች ይወለዳሉ ብሎ ከማመንና የዚሁ ሥርዓት አዳማቂ ከመሆን የባሰ የፖለቲካ ድንቁርና ወይም የአድርባይነት ደዌ ጨርሶ የለም ።
ከላይ በስም የጠቀስኳቸውን ሁለት ድርጅቶችን ጨምሮ እጅግ አብዛኛዎቹ ተቀዋሚ ተብየ ድርጅቶች አገር በማዳንና ሰላምን እውን በማድረግ ስም የመከራውንና የውርደቱን ኦህዴዳዊ -ብልፅግናዊ ሥርዓት እድሜ በማረዘም እጅግ አስነዋሪና አደገኛ የፖለቲካ መረብ ውስጥ ተጠርንፈው የመገኘታቸውን መሪር እውነት ከእነርሱ ከራሳቸውና ከጠረነፋቸው ገዥ ቡድን በስተቀር ለመረዳት የሚሳነው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
እነዚህ የኢዜማ እና የአብን ፖለቲከኞች ይህንን እጅግ አስከፊ እንቆቅልሻቸውን መፍታት ባለመቻላቸው እጅግ አስከፊው የፖለቲካ ትኩሳት እረፍት በነሳቸው ጊዜ ብቅ እያሉ አስከፊ ዘመን ላይ የመሆናችን መርዶ ዛሬ የሰሙ ይመስል ድርጊት አልባ የትንታኔ ድሪቷቸውን ለምን እንደሚደርቱልን ራሳቸውን ለምንና እንዴት ብሎ ለመጠየቅ ትእግሥቱና ፍላጎቱ ጨርሶ የላቸውም።
የአብኑ ክርስቲያን ታደለ “በእንከን የለሹ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ” አማካኝነት አባል ለሆነበት አሻንጉሊት ፓርላማ አስመስሎ የመኖር የአቤቱታ ደብዳቤ የመፃፉ ጉዳይ ብዙ የሚገርም ባይሆንም እንደ ታላቅ የፖለቲካ ተጋድሎ ይቆጠርልኝ አይነት የፖለቲካ ጨዋታ ግን ባይገርምም ጥያቄ ያጭራል። እየገጠመን ያለው አማራ ማህበረሰብ ጠል የሆነና የጋራ አገር የሚያሳጣ ፖለቲካ ወለድ ፈተና የአቤቱታ ፖለቲካ ደብዳቤ ከመፃፃፍ በላይ በእጅጉ የገዘፈና የመረረ ነው። ከሻንጉሊትነት ለማያልፍ ፓርላማ ተብየ ደብዳቤ መፃፉ በራሱ ስህተት አለመሆኑን ለመቀበል ባያስቸግርም ከማስመሰል የፖለቲካ ጨዋታ ያልፋል ብሎ እእኳን ለማመን ለመገመትም አይቻልም።
አዎ! ዘመናችን ለሚጠይቀው ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ጨርሶ የማይመጥኑ ፖለቲከኞችን ቀጥተኛ ፣ ግልፅና ገንቢ በሆነ አቀራረብ ነውር ነው ከማለት ይልቅ እንደ ወረደ ተቀበለን የምንጮህና የምናስጮህ ከሆነ አሁንም ግዙፉና መሪሩ ተሞክሯችን አላስተማረንም ማለት ነው።
ልፍስፍስና አስመሳይ የፖለቲካ ጨዋታ ተዋኔት ተዋናይ ፖለቲከኞችን የህዝብን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥያቄን ባፍ ጢሙ ደፍታችሁ የትና ከማን ጋር ነበራችሁ? አራት ዓመታት ሙሉ አገር ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል ስትሆን የተለመደውንና አሰልች የሆነውን መግለጫ አወጣን ከማለት ውጭ ምን ስታደርጉ ነበር? መቶ በመቶ እናምነዋለን ያላችሁት ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ ምን አላችሁ? ምንስ አደረጋችሁ? አሁንስ ምን የተለየ ነገር እያደረጋችሁ ነው?
በስሙና በመከራው እየማላችሁና እየተገዘታችሁ ታገልንልህ ስትሉት የነበረውን መከረኛ የአማራ ማህበረሰብ የተመኛችሁትን የፓርላማና የሌላ ሥልጣን ወንበር “ነፃና ፍትሃዊ” በተሰኘ ምርጫ እና በኦህዴድ -ብልፅግና የችሮታ ስጦታ በእጃችሁ ካስገባችሁ በኋላ ምነው ረሳችሁት? ብሎ የሚጠይቀው ወገን በቁጥርም ሆነ በአይነት እጅግ አናሳ በመሆኑ ይኸውና ሲፈልጉ ስለ የመከራው ዘመናችን እየተረኩ እና ሲያሻቸው ደግሞ መከራን ስለ መታገስ ግብረ ገብነት እየሰበኩ ግራ የተጋባውን መከረኛ ህዝብ ይበልጥ ያጋቡታል ።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን አያሌ ዘመናት ያስቆጠረውና አሁንም እጅግ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ የቀጠለው የህሊና ቢስና ባለጌ ገዥ ቡድኖች ሥርዓተ ፖለቲካ በምሁር ነኝ ባዩ የህብረተሰብ ክፍል እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ፣ የሥነ ምግባር እና የሞራል ጉስቁልና ባይታገዝ ኖሮ ወደ ታሪክ መዘክርነት ተለውጦ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ለማድረግ በተቻለ ነበር ።
በተቃራኒው አብዛኛው የተማርኩ ወይም ልሂቅ ነኝ ባዩ የህብረተሰብ ክፍል ከጨካኝ ገዥዎች አገዛዝ ቀጥተኛ ተሳታፊነት፣ ከምን አገባኝ ባይነት እጅግ ወራዳ የፖለቲካና የሞራል ሰብእና ውድቀት፣ ከአ ከፊ የፍርሃት ቆፈን ልክፍተኝነት፣ ከአድርባይነት ፍርፋሪ ተመፅዋዕችነት ፣ አብይ አህመድ “ተደመር” ሲለው ለምንና እንዴት ሳይል ከመቀበል እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ማንነትና ምንነት፣ “ተፎካካሪ ነህ እንጅ ተቀዋሚ አይደለህም” በሚል እጅግ ተራ የማጭበርበሪያ ቃላት መጫወቻ ሲያደርጉት አሜን ብሎ ከመቀበል = ወራዳነት ፣ ከትናንት ተምሮ ዛሬና ነገ የተሻለ የህብረተሰብ አካል ከመሆን ይልቅ ደጋግሞ ከመውደቅ ከፉ ልክፍተኝነት ፣ የሚደሰኩረው ንድፈ ሃሳብ መሬት ላይ ወርዶ ፍሬ ማፍራቱን ቆም ብሎና ትንፋሽ ወስዶ ለማስተዋል ያለመቻል የውድቀት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት አልሆነለትም ። አሁንም እየሆነለት (እየተቻለው) አይደለም። ከልብ አያሳዝንም?
አነዚህ የሁለቱ ድርጅቶች ፖለቲከኞችም የዚሁ አስቀያሚ የፖለቲካ ተውኔት ልክፍተኞች አለመሆናቸውን ለማስተባበል የሚያስችል አሳማኝ የመከራከሪያ ሃሳብ የሚኖር አይመስለኝም።
እያወራሁ ያለሁት ስለ ግለሰቦች የግል ሰብእና እና የግል እምነት አለመሆኑ ግልፅ ይሁንልኝ። እያልኩ ያለሁት የአጠቃላይ ማለትም የፖለቲካዊ ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የማህበራዊ፣ የሞራላዊና የመንፈሳዊ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት (root cause) የሆነውን እና በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓት በሰላማዊ ህዝባዊ አንገዛም ባይነት አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ከማድረግ ይልቅ በየዋህነትም ሆነ በፖለቲካ አመንዝራነት የመተሻሸት አስቀያሚ ፖለቲካ ለሦስት ዓሥርተ ዓመታት ተሞክሮ የወደቀ እና ይበልጥ አስከፊ መከራና ውርደት እያስከተለ ያለ ክፉ አዙሪት ነውና ቆም ብለን በማሰብ ወደ ትክክለኛው መንገድ እንሰባሰብ ነው። ይህን የማድረጉ ሥራ መጀመር ያለበት ደግሞ ግልፅና ግልፅ ስለሆነው የመከራና የአፈና ፖለቲካ ሥርዓት የመነጋገሩ አስፈላጊነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ከዚሁ እኩይ ሥርዓት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየተሻሹ ሃቀኛ የህዝብ ተቆርቋሪ ወይም ወኪል የመምሰል አስቀያሚ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የተዘፈቁትን ወገኖች ቀጥተኛ፣ ግልፅና ገንቢ በሆነ ቁጣ በቃችሁ ለማለት ከሚያስችል የፖለቲካና የሞራል አርበኝነት ነው።
ሥርዓቱን እና ሥርዓቱን የሚቆጣጠሩትን እኩይ ግለሰቦች እየነጣጣጠለ እገሌ ወይም እገሊት የተናገረው/የተናገረቸው ዲስኩር ወይም የሰጠው/የሰጠቸው መግለጫ ጠንካራ ስለሆነ ሊደነቅ/ልትደነቅ ይገባዋል/ይገባታል በሚል እጅግ የወረደ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የሚርመጠመጥ ልሂቅ ነኝ ባይ ፖለቲከኛ በበዛበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ምን አይነት ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ለማድረግ እንደሚቻል ለመረዳትም ሆነ ለማስረዳት ይከብዳል።
አርበኝነትን ከሚጠይቀው የዘመናችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሃዲድን በመሳት እጅግ እኩይና አደገኛ በሆነው በተረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ወጥመድ ውስጥ ገብቶ የሚንደፋደፍ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ምሁር እጅግ ከወረደ የእሮሮ እና የአቤቱታ ፖለቲካ አዙሪት ፈፅሞ መውጫ መንገድ የለውም። እንዲህ አይነቱ ፖለቲከኛ ትክክለኛውን መንገድ ፈልጎ የማግኘትና ከገንቢ ፀፀት ጋር የእርምት እርምጃ የመውሰዱ ወኔ ስለሚያጥረው የሚመርጠው በዚያው በተዘፈቀበት አዙሪት ውስጥ ሆኖ ፋይዳ ቢስ የእሮሮ ዲስኩር መደስኮር እና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖች ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫታቸው የሚወረውሩትን የአቤቱታ ደብዳቤ እንደ ታላቅ የፖለቲካ ሥራ እየቆጠረ ለወንበሩ የተመደበችለትን ምንዳዕ (ደመወዝ) ማስቆጠር ነው የሚሆነው።
ይህንን አባባሌን ስለ ተለመደ የፖለቲካ እንከን (normal political challenges) እንደሚያወራ ሰው ዲፕሎማቲክ በሆነ ወይም እጅግ በማይጎረብጡ የፖለቲካ ቃላት መግለፅ ብችል ደስ ባለኝ ነበር። ይህ አይነቱ አቀራረብ ግን ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ከምንገኝበት መሪር እውነታ አንፃር ራስን ማታለል ነውና አላደረግሁትም ። የገንዛ ራሳችንን መሪር ሃቅ እየሸሸን ወይም እያስታመምን የሚበጀንን የሃቀኞች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እናደርጋለን ብሎ ማሰብ የክፉ አዙሪታችንን ዙር ያበዘዋል እንጅ ጨርሶ አያሳጥረውም።
ይህንን አስተያየቴን እንኳን በጥሞና ለመረዳትና ለመቀበል ለማንበብም የሞራል አቅሙ የሚገደው ወገን እንደሚኖር በሚገባ እገነዘባለሁ። ከምር እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን ማየት የምንፈልግ ከሆነ ግን ስለ ገንዛ ራሳችን ግዙፍና መሪር እውነት በዚህ ልክ ነው መነጋገር ያለብን። በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ከለየለላቸው ግፈኛ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ይልቅ እንዲህ አይነት ዥዋ ዥዌ የሚጫወቱ ፖለቲከኞች ናቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች ደጋግመው ወደ ጭንጋፍነት (ወደ ውድቀት) እንዲለወጡ የማድረጉን አሳዛኝ ሚና የሚጫወቱት። እናም ጨርሶ ሳይመሽ ከተንጠለጠላችሁበት አደገኛ የፖለቲካ የዥዋ ዥዌ ገመድ ላይ ውረዱና እውነተኛውን የሥርዓት ለውጥ መንገድ ተቀላቀሉ ማለት በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
አዎ! እንደ አንዱዓለም አራጌ እና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደ ክርስቲያ ታደለ አይነት ግለሰቦች ቀደም ሲል ለከፈሉት ዋጋ እውቅና መንሳት ትክክል አይደለም። ይህ ግን በዜሮ ከተባዛ ወይም በክፍልፋይ የሂሳብ ስሌት (fraction) እርስ በርሱ የሚጠፋፋ ከሆነ ጨርሶ ትርጉሙን ማጣት ብቻ ሳይሆን የብልሹና የባለጌ ሥርዓት ሽፋን ሰጭ ሆኖት ያርፋል። ለዚህ እውነትነት ደግሞ ከእኛው ከራሳችን ቀደምት የፖለቲካ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እና በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት እየሆነ ካለው ማቆሚያ ያጣ ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ በላይ ዋቢ (አስረጅ) የለም።
ቀደም ሲል ያገኙትን የፖለቲና የሞራል ክሬዲት ወደ ኪሳራ ወይም አክሳሪ ክሬዴት እየመነዘሩ መቀጠል ፈፅሞ ስሜትየሚሰጥ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ለነፃነትና ለፍትህ ፍለጋ ትግሉም አደገኛ ነው።
ከእሥር ሲፈታ “ኢትዮጵያ ያለ መሠረታዊ (ሥር ነቀል) የሥርዓት ለውጥ መዳኛ እንደሌላት” የነገረንን ፖለቲከኛው አንዷለም አራጌ ገጠመን ለሚለው አስከፊ መከራ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን በአራት ዓመታት ውስጥ ያስመሰከረውን ኢህአዴጋዊ (ብልፅግናዊ) ሥርዓት በሚመሩት እኩያን ፖለቲከኞች እና ኢዜማን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ራሳቸውን ችለው መቆም የማይችሉ የፖለቲካ አካላት በአጃቢነት በሚሳተፉበት የሽግግር ሂደት እና የምርጫ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ እንደሚቻል እና በፓርቲው መሪነት ቢመረጥም ለዚሁ ዓላማ ተግቶ እንደሚሠራ ሲነግረን ከማን ጋርና እንዴት? ብለን ካልጠየቅን ተመልሰን ከተዘፈቅንበት ክፉ የፖለቲካ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ፈፅሞ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች አይደለንም ማለት ነው።
አፍቃሪ አብይ በሆነ የፓርቲ ዲስፕሊን እና አገር ይፈርሳል በሚል የተሸናፊነት ፖለቲካ አስተሳሰብ አዙሪት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ራሱን ከህዝብ ደብቆ በመቆየት አሁን ለፓርቲው መሪነት እራሱን ባስተዋወቀበት አጋጣሚ የነገረን ነገር አዲስና ቁርጠኛ የእርምት እርምጃ ከማብሰር ይልቅ ያንኑ የምናውቀውን የመከራ ዘመን መርዶ እና የአብይን ሸዋጅነት (ርካሽ ግን አደገኛ አታላይነት) ነው።
አንዱዓለም እርሱና ፓርቲው ከገቡበት የተለጣፊነት ቅርቃር ወጥተው እኩይ በሆነ የሸፍጥና የሴራ ፓለቲካ የተካኑ አብይና ካድሬዎቹን በምን አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ጥብብና የሞራል ልእልና መታገል እንዳለባቸውና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንደሚቻላቸው አልነገረንም። እነ አብይን መቶ በመቶ አምናቸዋለሁ ብሎ ፍፁም ታማኝ ተለጣፊነቱን (አሽከርነቱን) ላረጋገጠበት ውለታ የሚኒስተርነት ሹመት ከተቸረው ፕሮፌሰር ብርሃቡኑ ነጋ ጋር ለፓርቲው መሪነት እንደሚወዳደርና ከተሸነፍም የማያፈናፍነውን የፓርቲ የማእከላዊነት ዲሲፕሊንን አክብሮ እንደሚቀጥል ነገረን እንጅ ፓርቲው በለመደው የአድርባይነት ባህሪና ተግባር ቢቀጥል ምን ማድረግ እንደሚችል የተነፈሰው ቃል የለም። ምናልባት በተአምር ተሳክቶለት እርሱም ቢያሸንፍ ፓርቲውን ከገባበት ወራዳ ተለጣፊነት በማላቀቅ እንዴት የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ መሣሪያ ሊያደርገው እንደሚያስብ ጨርሶ የተነፈሰው ቁም ነገር የለም።
ከሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድን ለተገኘውና ሊገኝ ለሚችለው የሥልጣን ጥቅም ፍርፉሪ በገፀ በረከትነት በተሰጠ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ እየተርመጠመጡ ስለ ልዑላዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የእሮሮ ፖለቲካ ማመንዥክ (ማላዘን) ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።
ለፓርላማ ተብየው የአቤቱታ ደድብዳቤ መፃፍን እንደ ትልቅ የፖለቲካ ሥራ ክንዋኔ መቁጠርም ከምንገኝበት እጅግ አስከፊ ሁለንተናዊ ውድቅት አንፃር ብዙም ስሜት አይሰጥም ።
አንዱዓለም “በህዝብ ዘንድ ከሃዲዎች ተባልን” በሚል አጥብቆ ያማርራል። ለመሆኑ አራት ዓመታት ሙሉ በመከረኛው ህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ በወረደባት እና አሁንም የለየለት የአፈና እና የሰቆቃ ማእበል እያጥለቀለቃት በምትገኝ አገር ውስጥ ኢዜማነታችሁ ምን ትርጉም ያለው የፖለቲካ ሥራ ሠራ? ኢትዮጵያን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል እንድትሆን ካደረጓትና እያደረጓት ካሉ ተረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ቤተ መንግሥት ዙሪያ ለምን ትልከሰከሳላችሁ? የአስከፊውን የመከራ ዘመን እሮሮ እየነገርከን ባለህበት በዚች እለት የእናንተ የፖለቲካ ሸሪክ በሆነው ጭራቃዊው ኦህዴዳዊ (ብልፅግናዊ) ሥርዓት ዓመት ያልሞላቸው ህፃናት ያሏቸውን እናቶች ሳይቀር ስለ ኢትዮጵያ በጮሁና ህዝብ ባሳወቁ እየታፈኑ ያሉበትን ሁኔታ የማውገዙ ሞራል ቢያጥርህ እንኳ ምነው ቢያንስ እንደ አንድ ተራ ዜጋ አዝናለሁ ለማለት ተሳነህ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብለት አሳማኝ ምክንያት የሚኖው አይመስለኝም።
መንግሥት (እንደ እኔ መንግሥት ሳይሆን በመንግሥት ስም የተደራጀ የፖለቲካ ጋንግስተሮች ስብስብ ነው) “አታሎናል” ይለናል ልጅ አንዱዓለም ። በዚህ እጅግ ግልፅና ቀጥተኛ በሆነ የመከራና የውርደት ሥርዓት ለዓመታት ከተታለላችሁማ ወይ የፖለቲካ እንጭጮች ናችሁ ወይም በለየለት ርካሽ የፖለቲካ አመንዝራነት ውስጥ የተዘፈቃችሁ ናችሁ ማለት ነው።
ታዲያ ይህንን የታዘበ ህዝብ ተላጣፊና ከሃዲዎች ቢላችሁ ምኑ ላይ ስህተቱ?
“ነገ ምን እንደሚፈጠር የማይታወቅበት ዘመን ነው” ይለናል ልጅ አንዷለም። ለአራት ዓመታት አገር በፖለቲካ ወለድ ሰደድ እሳት ስትጠበስ ምነው ዝም አላችሁ? ስትባሉ “አይ እኛ እኮ ከመንግሥት ጋር ውስጥ ለውስጥ እየተመካከርንና እየተከራከርን የሽሽግሩን ሂደት ማሳለጥ እንጅ እዚሀም እዚያም ኮሽ ባለ ቁጥር አንጮህም ወይም እወቁልን አንልም” የሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ ምክንያት ስትደረድሩ ቆይታችሁ አሁን በየአጋጣሚው ብቅ እያላችሁ ግልፅና ግልፅ የሆነውን አጠቃላይ ቀውስ ለምን እንደ መርዶ ትነግሩናላችሁ ? የተረኛ ገዥ ቡድኖች የፖለቲካ ሸሪኮች የሆናችሁት እናንተ ይህ አስከፊና አስፈሪ ሁኔታ እንዲፈጠር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንደኛው አካል ከመሆን ነፃ ያደርጋችኋል እንዴ? ለሚሉና መሰል ፈታኝ ጥያቄዎች አሳማኝ ምክንያት ለመስጠት ከቶ የሚቻለው አይመስለኝም።
እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ላልሆነ ሰው ይህን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን እንኳን ለመቀበል ለማየትም እንደሚቸገር እገምታለሁ ። ግን ለዘመናት በመጣንበት እጅግ ልፍስፍስና ጎጅ የፖለቲካ ልማድ ለመቀጠል ካልፈለግን በስተቀር ግዙፉና መሪሩ እውነት ይኸው ነው ። እስካሁን የባከነው ጊዜ ፣ እውቀት፣ ጉልበት፣ ሃብት መብቃት ካለበት ፧ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የአያሌ ንፁሃን ዜጎች ህይወት በግፍ የሚቀጠፍበት እና ብዙ ሚሊዮኖች ለቁም ሰቆቃ እየተዳረጉ ያሉበት እጅግ አስከፊው የውደቀት አዙሪታችን መሰበር ካለበት አካፋን አካፋ ብሎ በመጥራት ወደ ትክክለኛው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ጎራ መሰባሰብ ብቻ ነው እውነተኛውና ዘላውቂ መፍትሄ ።
በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ ዘመን ጠገብ የሆነ የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓትን ካስቀጠሉትና እያስቀጠሉት ካሉት እኩይ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ጋር በመተሻሸት የሚመጣ አንዳችም በጎ ውጤት የለምና ልብ ያለው ልብ ይበል!