ልጆቿን እዬበላች የማትጠግብ ሀገር – አገሬ አዲስ

ግንቦት 21 ቀን2014 ዓም(29-05-2022)

በተለምዶ አባባል የራባት ድመት ልጇን ትበላለች ሲባል እንጂ ሃገር ልጇን ትበላለች ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም።እርሃብ ክፉ ነው፤ክፉ ነገርም ያሠራል።ምሳሌው በድመት ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሰው ልጆችም በተግባር የሚፈጸም መሆኑን በቅርቡ በአገራችን ውስጥ የልጅ ኩላሊት ወጥቶ ሲበላ አይተናል።በዚችው አገራችን የሚኖር ትኩስ ሬሳም የሚበላ ማህበረሰብም መኖሩ ምንም እንኳን በይፋ ባይወጣም የሚያውቁ ይናገራሉ።ይህ ሁሉ የሚፈልጉትን ጤነኛና ተገቢ ምግብ ከማጣትና ከመራብ፣በችግር አስገዳጅነት የተነሳ የሚፈጸም ዘግናኝ ድርጊት ነው።አድራጊው ግን ስለለመደውና ምርጫም ስለሌለው እንደ በጎ ሥራ ይመለከተዋል፤እንደ መልካም ባህልም ይቆጥረዋል። ከዚህ የአውሬ ድርጊት ለመመለስ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ጤነኛና መልካም ምግብ እንዲመገብ እንደሰው እንዲኖርና እንዲያስብ ማብቃት ተገቢ ነው።ፍላጎቱና ጥያቄው ካልተመለሰ ሰው ሰውን መብላቱ ሊቆም አይችልም።

Kidnaper Abiyድርጊቱ ሰለጠነ በተባለው ዓለም የሚኖሩትንም ሰዎች ያካተተ ሆኗል።ከሃምሳ ዓመት በፊት በኦክቶበር 13 ዐን 1972 ዓም የኡራጉዋይ የረግቢ ቡድን ተጫዋቾች ለውድድር ወደ ቺሊ  የሚጓዙበት አውሮፕላን ተከስክሶ በተራራማና በበረዷማ ቦታ ሲወድቅ ብዙዎቹ ሲሞቱ ጥቂቶቹ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው ከሞት ለመትረፍ ችለው ነበር።በዚህ ከግንኙነት መረብ በራቀ አስቸጋሪ ከባቢ ለተወሰነ ቀናት የቆዩት ቁስለኞች ምንም እንኳን ነፍሳቸው ባትወጣም በሞትና በመኖር መካከል ላይ ነበሩ።ሁኔታቸውን የከፋ ያደረገው ደግሞ ለቀናት ምግብ ሳይበሉ መቆየታቸው ነበር።በዚህ አስከፊ hሁኔታ ላይ እርሃብ ሲጨመርበት የገጠማቸው ፈተና  የለመዱትንና የነበራቸውን ሰብአዊ ሞራልና ስነምግባር እንዲሁም የአመጋገብ ልምድና የምግብ ምርጫ እንዲረሱትና በሚፈሩትና በሚጠዬፉት ድርጊት ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል።ያም ከሞቱት ጓደኞቻቸው የሰውነት ክፍል ቆርጠው መብላት ነበር።እርሃብን አሸንፎ ለመቆዬት ሲሉ ያደረጉት ለሰሚው የሚከብድ ድርጊት የቁስለኞቹን ህይወት አትርፎ ለመኖር እረድቷቸዋል።እንዲህ አይነቱ ድርጊት የሰውን ልጅ ገድሎ ከመብላት ከካኒባሊዝም የተለዬ ቢሆንም ለመቀበል ይከብዳል።ታሪኩን ያነሳሁት  እርሃብ ምን ያህል የሰውን ልጅ ወደ ማይፈልገው ድርጊት ሊመራው እንደሚችል  ለማሳዬት ነው።በማጣትና በመራብ የተነሳ ሰው ገሎ የመብላቱ ነገር ግን ወንጀል ከመሆኑም በላይ ማጣት የሰውን ልጅ ህሊና ነስቶ   ወደ አውሬነት ሊለውጠው እንደሚችል ያሳዬናል።

ይህንን እንደ ዋቢ አድርገን ወደተነሳሁበት ርዕስ ስመለስ አገርም ተገቢውን አገራዊ ቁመና ስታጣና የነዋሪዎቿ መብት ሲረገጥ፣የዴሞክራሲ እርሃቧ ሲጠና ለለውጥ የሚሰለፉ ልጆቿን እንክት አድርጋ እንደምትበላ ያለፉት ሃምሳ ዓመት ታሪኳና ታሪካችን ያሳያል።አገር አፍ አውጥታ የልጆቿን ሥጋ ባትበላም ብዙ ልጆቿን በመቃብር ሆድቃዋ/ዋሻዋ መዋጧን ታዝበናል። በእሷ መንፈስና ስም የራሷ ልጆች የሆኑት ሌላውን ልጆቿን ሲገሉ፣ሲያሳድዱና መከራ ሲያሳዩ በአርምሞ ተቀብላለች።ለዴሞክራሲና ለለውጥ እርሃቧ ማስታገሻ የሚሆን በብዙ አማራጮች የታጀበ የተሻለ ሥርዓት አቅርቦ ማስፈን ተስኗት በአንድ ነጠላ ፈላጭ ቆራጭ በሆነ አመለካከት ብቻ እዬተሽከረከረች ብዙዎቹ ሲሞቱባትና ሲቀበሩባት  ሃገርእንደ ድመቷ ተርባ  ልጆቿን እዬበላች መኖሯን የሚያሳይ ነው። ሃገር ስንልም ሕዝቧ ስለሆነ በሕዝቧ መካከል የሚከናወነው መልካምም ሆነ መጥፎ፣አኩሪም ሆነ አሳፋሪ ድርጊት ሃገርን ያሶድሳል ወይም ያሶቅሳል።

ለአለፉት ሃምሳ ዓመታት ተራ በተራ በትረመንግሥቱን በጨበጡ ጉልበተኞች በሰፈነ ሥርዓት ሥር ስትንከባለል የኖረችው ኢትዮጵያ የሚፈጸመው ሁሉ በስሟ ስለሆነ የምትታወቀው ስርዓቶቹ በፈጸሙት ተግባርና በደረሰባት ስብራት ወይም በሕዝቧ ኑሮና ግንኙነት ላይ በደረሰው ቀውስ ና ልዩነቶች ነው።አገር ሕዝቧንና መሪዎቿን ትመስላለችና!

የአገሪቷን ፍላጎትና እርሃብ የተረዱት ልጆቿ የሚያነሱት ጥያቄና የሚሰጡት መልስ በተግባር ካልተተረጎመ አገር ልጆቿን እዬበላችና እያባለች መኖሯ ይቀጥላል፤በይና ተበይም ይኖራል።በመጨረሻም እራሷን በልታ ማለትም ፈራርሳ ትወድቃለች።ለዚያ መንደርደሪያ የሚሆነው ላለፉት 31 ዓመታት እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ የሰፈነባት የጎሳ ስርዓት ነው።ይህንን  ስርዓት መለወጥና ማሶገድ ተገቢ ነው።አገር በህይወትና በጤና አቋም እንድትኖር የሚያስቡላት ልጆቿ የሚያቀርቡላትን የዲሞክራሲ  ምግብ መመገብ አለባት።

የምግቡ ዓይነቱና ዝርዝርም ከሃምሳ ዓመት በፊትና በዃላ ይቀርቡ የነበሩት ጥያቄዎች ናቸው።እነሱም

ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣

የዴሞክራሲ መብቶች ማለትም፣ የመጻፍና የመናገር፣የመሰብሰብ፣የመንቀፍና የመደገፍ ፣የመምረጥና የመመረጥ መብቶች ይከበሩ

መሬት ላራሹ ማለትም መሬት ለሚጠቀምባት ዜጋ ሁሉ ትሁን፣

መንግሥት በምርጫ እንጂ በጠበንጃ የሚወጣና የሚወርድበት መንገድ በሕግ ይታገድ፣

ሕገመንግሥት በሕዝቡና ለሕዝቡ  ጥቅም  ይዋል፣ ከመንግሥትና ከድርጅት በላይ መሆኑ ይታወቅ፣

መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ እንጂ እንዳሻው የሚፈነጭ አዛዥና ፈላጭ ቆራጭ አይሁን፣

የሕዝቡ እኩልነት ይከበር፣የጾታ፣የሃይማኖትና የጎሳ  ልዩነት አይኑር፣

ሕዝብ የአገሩ ባለቤት፣የተፈጥሮ ሃብቱና ንብረቱ ጌታ መሆኑ ይከበር፣ በፈለገውና በመረጠው ቦታ ሄዶ ሰርቶ የመኖር መብቱ ይታወቅ፣

የጎሳ ፖለቲካና የጎሰኞች ሥርዓት ይወገድ፣

አገር እንደ ቀድሞው በተሻሻለ መልክ በክፍለሃገር ደረጃ ይዋቀር፣ የክልል ጎሰኛ አስተዳደር ይፍረስ፣

የኢትዮጵያ አንድነትና ዳር ድንበር ይከበር፣

መከላከያ የአገር ዳር ድንበር አስከባሪ፣  እንጂ የድርጅትና የግለሰብ ዘበኛ አይሁን፣

በአገርና በሕዝብ ላይ ወንጀል የፈጸሙ ለሕግ ይቅረቡ፣

እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ሰላምና እድገት ለተራበችው አገራችን የሚረዱ የዴሞክራሲ ምግቦች ናቸው እላለሁ።ለእነዚህም ዴሞክራሲያዊ ያገር ምግቦች አያሌ ወጣቶች የህይወት ዋጋ ከፍለውበታል።, በምክክር ኮሚቴው ማድቤት ውስጥ ተሸክነው ለፍጆታ ቢቀርቡ ኢትዮጵያ ልጆቿን እዬበላች ከመኖር ድና እያበላች ለማኖር ትችላለች ብዬ አምናለሁ።የሕዝቡ ጥያቄ እነዚህ እንጂ እንደ አውሬ አንዱ ሌላውን ለመብላት አሁን እንደሚታዬው በጎሳ ተከፋፍሎ የመገዳደልና  በጠላትነት መተያዬት አይደለም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።ሕዝቡ ከስርዓቱ ጋር እንጂ የእርስ በርስ ጥላቻና ግጭት አልነበረውም ፣አሁንም የለውም።ጎሳና ሃይማኖት ሳይለዬው በአንድ አገር ዜግነት ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ ሕዝብ ነው።እዬኖረም ነው።ክፍለሃገር ጠፍቶ በጎሳ አጥር ውስጥ ብቻዬን  በክልል በረት ውስጥ ልኑር ብሎም የጠዬቀበት አንድም ወቅት የለም።የሚለያዩት ክፉዎች ከጠፉለት  ለወደፊቱም በአንድነትና በሰላም  ለመኖር አያዳግተውም።እንዳይኖር የሚያደርጉት እራስ ወዳዶችና  በደካማ ጎኑ እዬገቡ በመቀስቀስ አንድነቱ እንዲላላና ለሃገሩ እንዳይቆም በማድረግ  አገራችንን ለባዕዳን አሳልፈው ለመስጠት የተሰለፉ ባንዳዎች ናቸው።

የሕዝቡን የዓላማና የፍላጎት ትስስር የሚያሳዬን የታሪክ ምስክር  ከላይ የዘረዘርኳቸው የዬካቲቱ 1966 አገር አቀፍ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የቀረቡትና አሁንም በመቅረብ ላይ ያሉ  ጥያቄዎች ናቸው። እኔም በተሳተፍኩበት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋናቸው ፊት ቀርበን የተነበበውና የተሰጣቸው በእኔ የተጻፈ  11 ጥያቄዎችን የያዘ ደብዳቤ እነዚህኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ያካተተ ነበር። የሰነዱም ኮፒ በእጄ ይገኛል።ላለፉት አርባ ስምንት ዓመቶች አብሮኝ ሲንከራተት የኖረው ይህ ሰነድ የሕዝቡ እውነተኛ ጥያቄ ምን  እንደነበር  ያረጋግጣል፤ለአሁኑም መፍትሔ ፍለጋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ።ለታሪክ ትምህርትም ይረዳል እላለሁ።ፊትም ሆነ አሁን የሕዝቡ ጥያቄዎች አንድ አይነት ናቸው፤መልስ ይፈልጋሉ።የተጨመረው ቢኖር ከሰላሳ ዓመት ወዲህ የሰፈነውን የጎሰኞች ስርዓት የሚመለከተው ጥያቄ ብቻ ነው።ጥያቄዎቹ መልስ ካላገኙ በተያዘው የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ጉዞ ስንኳትን ከኖርን፣አጥፍቶ በመጥፋትና በመበላላት አባዜ ውስጥ እንደተነከርን እንኖራለን። አገራችንም የደስታ ኑሮ የሚኖሩባት ሳትሆን በግፍ የሚገደሉትን፣በርሃብና ቸነፈር የሚያልቁትን ልጆቿን እዬዋጠች የማትጠግብ የብዙዎች ከርሰመቃብር ሆና ትቀጥላለች።

አገራችንን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት እንተባበር፣የዬካቲቱን መንፈስ እንላበስ!

ጎሰኝነትና የጎሳ ስርዓት ይወገድ፤ሕዝባዊ ና ፍትሃዊ ሥርዓት ይስፈን!!

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!

አገሬ አዲስ

 

 

1 Comment

  1. ችግራችን ሥር ሰደድና ትውልድ ተሻጋሪ ነው። በየጊዜው ጠበንጃን አስቀድመውና በዘራቸውና በቋንቋቸው ተደግፈው ሃገር ከሚያተራምሱት በፊትም ሥራና ተግባራችን ድርቡሻዊ እንደነበር መለስ ብሎ ከእሳት የተረፈውን ታሪክ ማገላበጥ በቂ ይሆናል። ከደርግ እስከ ብልጽግና (ድህነት) ያለው ጉዞ ደግሞ መመዘኛ ያጣ የግፍ ዘመን ነው። ታዲያ በዚህ ሁሉ ስርግብ ብዙዎች ተሰውተዋል። ለሃገር ለወገን ብለው ደማቸውን አፍሰዋል። የሃገሪቱ የፓለቲካ ሚዛን ሁልጊዜ ገዳዳ በመሆኑ አወዳደቃችን የአህያ ውድቆሽ እየሆነ የቆመውንና የወደቀውን ለይተን ማወቅ ከተሳነን ቆይተናል። አንዴ አሞካሽተን የሸለምነውን መልሰን ስናዋርድ፤ ትላንት በግፈኞች በትር የተቀጠቀጠውን ስንገድልና ድጋሚ ስናሰር፤ አልፎ ተርፎም የመናገር የመጻፍ ነጻነት አለ እያልን በዙፋኑ ላይ በጊዜው የተቀመጡት የፓለቲካ ወስላቶች ሁሉ እኔን ካልመሰላችሁ አይናችሁን ላፈር በማለት የሃገሪቱን ምርጥ ልጆች ለእስራት፤ ለስደት፤ ከባሰም አፈር ተመልሶባቸዋል። ባጭሩ የሃገሪቱ የፓለቲካ ሂደት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጀምሮ እስከ ገዢው መደብ ጠንጋራና ሸፋፋ አካሄድን ነው የሚከተሉት። አንድ ላይ ጀመሮ አለመጨረስ፤ የፓለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች መከፋፈል እና ባልተግባቡበት ነገር መፏከት ሁሉ የሚያሳየን ሃበሻ በየወንዙ የሚማማል የማይተማመን መሆኑን ነው። በቀትር ጥላው ከሚደነግጥ መንገደኛ ጋር ብዙ መጓዝ አይቻልም። ቢዘፈን፤ ቢሸለል፤ ታሪካችን የ 3ሺ ወይም የመቶ ብናረገው ምንም ፋይዳ የለው።
    በቅርቡ አቶ ጀዋር መሃመድ በሰጡት የቃል ምልልስ ያረኩት ጠባብ የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደ መሶሎኒ ዘቅዝቀው ቢሰቅሉት ደስታቸው ነው። ውጊያቸውን ከሰውዬውን ስብዕና ጋር አገናኝተውታል። ኦሮሞ ኦሮሞ አላለም ይሉናል። ግን ሸኔ እልፍ ስፍራዎችን ሲያቃጥልና ሲዘርፍ የሚሉት አንድም ነገር የለም። የእብድ ፓለቲካ ይህ ነው። በመሰረቱ አቶ ጀዋር በስጋውም አምሮበት በእይታውም ተሽሎት ብቅ ማለቱ እሰየው ያሰኛል እንጂ ቡራ ከረዬ አያሰኝም። ቃለ መጠየቁ ሁሉን ያካተተ፤ የሃገሪቱን ውስብስብ ፓለቲካ ለይቶ ያወቀ ይመስላል። የምድሪቱ ችግር እኛው ነን የምለውም ደጋግሜ ለዚህ ነው። ባንጻሩ አቶ አንድዓለም አራጌ በጭላንጭልም ቢሆን ከፕ/ብርሃኑ ነጋ ጋር የሃሳብ ፊልሚያ መግጠሙን አመላክቷል። ይህ ያለፈው ታሪክን አያሳይም? እየጀመሩ መናድ፤ እያፈረሱ መገንባት፤ አድሮ ደግሞ በዚህም በዚያም ስም እየለወጡና በሃሳብ ሽኩቻ እየተፋለሙ ሌላ ጎጆ መቀለስ ይህ የሃገራችን የፓለቲከኞች ተግባር መሆኑ አሳፋሪ ነው። መንግስት ነኝ ባዪ ደግሞ ጸሃፊና ጋዜጠኞችን እንዲሁም ወታደራዊ መኮነኖችን አልፎ ተርፎም ፋኖን እያፈነና እያሳደደ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቢል የገደል ማሚቶ ጭኾት ብቻ ነው የሚሆነው። ይህ ሲባል በፋኖ ስም ሃገር የሚያምሱ፤ የሚዘርፉ አልፎ ተርፎም ግብር እስከ መሰብሰብ የደረሱ የጊዜው የጭቃ ሹሞች የሉም ማለት አይደለም። መታረም እና መመከር ያለበትን እንደማስተካከል ከሰራዊቱ ጋር አብሮ ተሰልፎ ዋጋ የከፈለ ወገን ላይ ሰራዊት ማሰማራት ነገርን ማክረርና ሆን ተብሎ አንገት ለማስደፋት የተደረገ ድርጊት ነው። ሊቆም ይገባዋል!
    በትግራይ የትግራይን ልጆች ለሞትና ለረሃብ እየማገድ ለትግራይ ህዝብና ነጻነት ነው የቆምነው ሲሉን ወቸው ጉድ ምድሪቱ ሁሉ በእብዶች ተጠፍራ ተይዛለች ያሰኛል። ወያኔ ካደረገው አንድ ግፍ ላካፍላችሁ። ሰራዊቱ 20 ዓመት ሙሉ ትግራይ ውስጥ ሲቆይ ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፤ ባጭሩ ተጣምሯል። በዚህም መሰረት የሰራዊቱ ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት ነበራቸው። ታዲያ ሰራዊቱ ትግራይን ዳግም ከተቆጣጠረና ሳይታሰብ ጥሎ ሲወጣ ልጁን፤ ቤተሰቡን ጥለው ነው የወጡት። ወያኔ ዳግመኛ መቀሌን ሲቆጣጠር ያደረገው እነዚህ ቤተሰቦችን ከቤት ማስወጣትና ማባረር ነበር። አይ ጭካኔ። ወያኔ አረመኔ ነው ለራሱ ህዝብም አልሆነም አይሆንም የምንለው ለዚሁ ነበር። በዘር የሰከረው የሃበሻ ስብስብ ግን እውነትን ማየት አልቻለምና ዛሬም እንደ እንቁራሪት አንድ ሲንጫጫ አብሮ ይነጉዳል። እውነት በሃበሻው ምድር ሞታ ከተቀበረች ቆይታለች። በዚህ ላይ አወናባጅ የሶሻል ሚዲያና የምዕራባዊያንን ጫና ስናይ መከራችን ማቆሚያ ያለው አይመስልም።
    Ethiopia: The country that cut off its head : a diary of the revolution የተሰኘውን መጽሃፍ ላገላበጠ ያለፈውን እይታ በግልጽ ያሳያል። ኢትዮጵያዊው ባብሌ ቶላ ደግሞ To kill a generation: The Red Terror in Ethiopia ላይ ምን ያህል የሰው ልጅ ጨካኝ እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል። የወያኔ ክፋትና ጭካኔ በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ በመሆኑ ዛሬም ያልቆመው እርስ በእርስ ለጥፋት የተቆራኘው የመከራ አዝናቢነታቸው ገና አልተገታም። አልፎ ተርፈውም ትግራይን እንገነጥላለን ሲሉ አለማፈራቸው። ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ፤ ትግራይም ያለ ኢትዮጵያ ኑረው አያውቁም። ይህ በደመ ነፈስ የሚፎከረውና ቤ/ክ ሳይቀር ያሰለፈው ተንኮል ህዝባችን ለባሰ መከራ ይዳርጋል እንጂ የተገነጠሉት ያተረፉትን ትርፍ አላየንም። ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አርጋን እያሉ ሲለፉ ኑረው ዛሬ ዙረው ተመልሰው ንጽህ ዓየር የሚተነፍሱት ከነጻዋ ኤርትራ ነፍሴ አውጭ ብለው በተጠለሉበት ዓለምና በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህ የፓለቲካን ፎከታምነት በማይጨበጥ ነገር ላይ የሚያስጨፍረን። ግን ዛሬ ላይ ለምድረስ ስንቱን ገደል፤ ስንቱን አፈረስን፤ ስንት ሰቆቃና ሲቃ በህዝባችን ላይ አዘነብን። ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ የሚለውን መጽሃፍ ትውስ ያደርገኛል። ፓለቲካ የወስላቶች ክምችት ነው። ሃይማኖት የማታለያ ካባ ነው። ምድሪቱም ልጆቿን ያለማቋረጥ ስትሰለቅጥ ትኖራለች። ነጩ ዓለምም በእኛ ላይ በቅርብና በሩቅ ይስቃል። ዓረቡም ነጩን ተከትሎ ተንኮሉን ይጎነጉናል። ለምድሪቱ ደዌ መፍትሄው እኛው በእኛው ነን። በዚህዝ ስንኝ ልሰናበታችሁ።
    ሰው በሰው ተበልቶ አጥንቱን ይግጣል
    እሱም በወረፋው ሌላ የተራበ ይጎረድመዋል
    ሲበሉ ሲባሉ መሬት ተሽከርክራ
    ነግቷል አታስቡ ይላል ባለ ቀኑ
    ከመበላት ተርፎ ሌላውን ሊበላ ዛሬም አሰፍስፎ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Amhara 7
Previous Story

በዐማራ ሕዝብ ላይ ለሚደረገዉ አፈናዉና ወረራው ምላሽ – ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (ዐሕድ)

Andualem and christian
Next Story

የኢዜማው አንዷለም አራጌ እና የአብኑ ክርስቲያን ታደለ የእሮሮና የአቤቱታ ፖለቲካ – ጠገናው ጎሹ

Go toTop