የጫነው ዲግሪ አይረዳ የደፋነው ቆብ አያስጥል!

May 28, 2022

Kidnaper Abiyእንደ ጥንት አባቶቻችን እምነትን በአለት ላይ ገንቡ ብንባል፣
እንደ እምቧይ ክምር በድቡሽት ላይ ስንክብ ስንቆልል፣
የቅጥፈት ስብከት ሲነዳን ነፋስ እንዳየው ባዶ ቅል፣
የጫነው ዲግሪ አይረዳን የደፋነው ቆብ አያስጥል፡፡

 

አይ እኛ!

 

ሰውን በሥራው መዝኑ የሚል ትዕዛዝን ቦጭቀን፣
ግብር የሌለው እምነትም የበሰበሰ ገለባ መሆኑን እረስተን፣
የዋሾ ስብከት እንደ አልኮል ጥንብዝ አድርጎ አስክሮን፣
ዓለም ጉድ እስቲል ተገዳዮች ጋር ዳንስና እስክስታ አወረድን፣
ለሰላሳ ዓመት የገደሏቸውን ሰማእት እምሽክ አድርገን ቆርጥመን፡፡

 

አይ እኛ!

 

ሕዝብ በዘር ቢላዋ ሲታረድ ጽንሱ ተማህጸን ሲውጣ፣
በቅል በገንዳ ተቀድቶ ደሙ እንደ እርጎ ወተት ሲጠጣ፣
የአስከሬን ክምር ተሻግረን የስልጣን እርከን ስንወጣ፣
በአድርባይነት ዝም ስንል ተዝንጀሮ አንሰን ተጦጣ፣
የሰማይ ንጉስ ምን ይለን መጨረሻው ቀን ሲመጣ?

 

አይ እኛ!

 

ተዘርተን በቅለን ላንቀር ላንኖር ማቱሳላ እድሜን፣
አዋጅ ሳይነግር ሊወስደን ደዌና አደጋ አንድ ቀን፣
ጥቅምና ስልጣን ሆዳችን እንደ ንድፍ ጥጥ አሳስቶን፣
ታራጆቹ ጋር ስንዝቅ የሰማእት አጥንት ማንኪያ አርገን፣
መለኮት በችሎት ደጃፍ ታሪክ በመዛግብቱ ምን ይለን?

 

አይ እኛ!

 

የቅደመ አያትን አደራ ጀግንነት ታሪክ ስንከዳ፣
ለመቅቡጥ ለስልጣን ብለን ተሕዝብ ሃይማኖት ስንወጣ፣
ሳጥናኤል እንደ ዛፍ እስስት መልኩን ቀይሮ ሲመጣ፣
በውሸት ተስፋ ወስውሶ ሊነጥቀን ተመላክ ተሕዝብ ጓዳ፣
የደፋነው ቆብ አያስጥል የጫነው ዲግሪ አይረዳ፡፡

 

አይ እኛ!

 

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ግንቦት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

284375734 10227326710984276 7097029380191254601 n
Previous Story

ኦህዴድ ዛሬ የያዘዉን ስልጣን ያገኘዉ እጅግ በርካታ ጀግኖች ወያኔን ታግለዉ በህዝባዊ ትግል አስወግደዉት ነዉ

Meaza Mohamed
Next Story

ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ በፌደራል ፖሊስ አባላት ተያዘች

Go toTop