ተባሿል – አስቻለው ከበደ አበበ

ይህን ጽሑፍ ለመፃፍ ስዘገጃጅ፣ እወንበሬ ላይ እንደተቀመጥኩ አንቀላፋኝና ትንሽ አቃዠኝ፡፡ ነገሩ እንደዚህ ነው፡፡ አንዲት የሃበሻ ቀሚስ የለበሰች መልከመልካም ሴት በቀኜ በኩል ከኔ ቀደም ብላ ትሄዳለች፣ የአየር መንገድ አስተናጋጂም ትመስላለች፣ ተከተልኳት፡፡

አካሄዷ ግን ለየት ያለ ነው፡፡ እንደው ሰፈፍ ሰፈፍ ትላለች፡፡ በሞል ውስጥ በትልልቅ ንግድ ቦታዎች ውስጥ ትጓዛለች፡፡ እንዲህ እያለ ሌላ ድንቡሸቡሽ ያለ ፊት ያላት፣ ፊቷ ላይ ካለው ከነማዲያትቷ  የምተምር፣ ነገር ግን የጎዳና ላይ  የጉሊት ቸርቻሪ የምትመስል ሴት መጥታ ምነው እኔን የማታየኝ አለችኝ፡፡

ድንቡሼ ቆንጆን ተከትዬ ወደ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ የሚኒባሱ ወንበሮች ልክ እንደ ውይይት ወንበሮች ፊት ለፊት ተሳፋሪውን የሚያተያዩ ናቸው፡፡ ድንቡሼን ከቀኜ ሌላ ወጣት ልጅ ደግሞ ከግራዬ ተቀምጦ ጉዞ ጀመርን፡፡

በግራ በኩል የተቀመጠው ወጣት፣  የግራ ኪሴ ውስጥ ያለውን ቦርሳ ለመውስድ የተለያዩ የስርቆት ቴክኒኮችን ይጠቀማል፣ እኔም በልቤ አሁን እኮ ዲያሰፖራ ነው ብሎ ገንዘብ ፍለጋ ነው የሚለፋው አልኩ፡፡ በዲያስፖራው ኪስ የሚገኘው ክሬዲት ካርድ እኮ፣ የሰቱደንት ሎን፣ሞረጌጅ እዳ፣ አረ ምኑ ቅጡ ያለበት ነው፡፡ ከዚያም ተው አልኩት፣ ነቄ እንዳልኩ ሲያውቅ “ተባሿል ነገሩ” ብሎ ቀኝ እጁን ለግጭ ዘረጋልኝ እኔም በግራዬ መለስኩለት፡፡ ከገባሁበት የሰመመን ህልም ያነቃኝ አንድ ጎላ ብሎ የሚሰማ የወለዬዎች አባባል ነበር፡፡

ከአንቺ ያለብሽ መርሃባ  ኪታቡ ያለው ከኛ ጋራ፡፡     አይ ህልም እልም ከማያደርሰን ቦታ የለም፡፡ እኔም ከእንቅልፌ እንደነቃሁ፣ ደግሞ የጠ/ሚ አብይ የትውልድ ስፍራ፣ በሻሻ፣ በህልሜ ምን ልትሰሪ መጣሽ አልኩ፡፡ የአራዳ ቋንቋ አንድን ቃል ይዞ በዚያ ላይ እንደሚራባው፣ ለምሳሌ ባነነ ለሚለው ተባኗል(ታውቋል) እንደሚለው፣ ህልም አይጠየቄው ከበሻሻ ተባሿለን አመጣልኛ፡፡

ትውልዴና እድገቴ መርካቶ አካባቢ ስለሆነ፣ አንድ ሰው ሊያደርገው የሚፈልገው ነገር ሲነቃበት፣ በአራዳ ቋንቋ ተባኗል ነው የሚባለው፡፡ እንዴ ተባኗል በተባሿል ተቀየረ እንዴ ብዬ እራሴን ጠየቅሁ፡፡ ከዚያም ከአቶቡስ ተራ እስከ በረንዳ አማኑኤል፣ ከተክለሓይማኖት- ልደታ እስከ ዮሃንስ-ራስ ደስታ የነበረኝ የልጅነት ትዝታዬ ተቀሰቀሰ፡፡

መቼም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባ ላይ  ግብይቱን ይፈጽምበት የነበረው ቦታ በእነዚህ በጠቀስኳቸው ቦታዎች የታቀፈ ነበር፡፡ እንዲሁም አብዛኛው ነጋዴ አውቶቢስ ተራን ሳይረግጣት አያልፍም ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ላይ የሃገሪቱ ህዝቦች የሚያደርጉት ፍሰት ታላቅ ስለነበር ነጣቂ ወመኔዎች በብዛት እዚያ ነበር የሚሰማሩት፡፡

እኔ ወጣት በነበረኩበት ግዜ ለነዚህ ወመኔና ሌቦች የተለያ ስም እንሰጣቸው ነበር፡፡ እከሌ የመንገድ ትራነሰፖርት ወይም የካርታ ስራ ድርጅት ተቀጣሪ ነው ከተባለ የስራ ድርሻው ይታወቃል፡፡ የአውቶብስ ላይ ሌባ ነው ወይም ቀዩን ያየ ጥቁሩን ያየ የካርታ ቁማርተኛ ሌባ ነው ማለት ነው፡፡

የአውቶቡስ ተራ ወመኔዎች የክፍለሃገር ነጋዴዎችን ለይተው ያውቋቸዋል፡፡ የዚያን ግዜ ገንዘብ እንደ አሁኑ በባንክ ቼክ ማንቀሳቀስ የተለመደ ስላልነበር በኪሳቸው ይዘው የሚመጡ ቡዙዎች ነበሩ፡፡ ታዲያ ገንዘብ የያዘውን ነጋዴ ከመቅጽበት ይለዩትና በሽምግልና ወይንስ በአስተንፋሹ በኩል ለመቅረብ ይወስናሉ ፡፡ የራሳቸው የሆነ መግባቢ ቋንቋ አላቸው፡፡

አስተንፋሽ ማለት ወደ ነጋዴው ከፊት በኩል ቀርቦ ያለማቋረጥ በፈጣን ቦክስ ሆዱ ላይ ይተከትከዋል፣ ነጋዴው ትንፋሽ እንደ እንዳጠረው ሌሎች ጀሌዎቹ ደግሞ ነጋዴው ብሽሽቱ ውስጥ አሊያም የትም ስፍራ የደበቀውን ገንዘቡን አውልቀው ይወስዱለታል፡፡ ነገሩን ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ሊያከናውኑት ይችላሉ፡፡

ሰውዬውን በሽምግልና የሚቀርቡት ከሆነ፣ ሁለት ህጻናት ልጆች እየተጣሉ እግሩ ስር ይወድቃሉ፡፡ እውነተኛ ፀብ ነው የሚመስለው፤ ከፍ ያለው ልጅ ትንሹን በደንብ ነው የሚመታው፡፡ ይሄኔ ትንሹ ልጅ ሄዶ ነጋዴው እግር ላይ ተጠምጥሞ አድኑኝ ይላል፡፡ የዋሁ ነጋዴ ተው ተው ሲል ሌሎቹ አባሪዎቻቸው ከውስጥ በኩል በሚስጥር ኪሱ ሰፍቶ የደበቀውን ገንዘቡን በንፋስ እጃቸው ገብተው ያወልቁለታል፡፡

የኦሮሚያው ብልጽግና አሰተንፋሽ እንዳለው አሁን አሁን ነው መገለጡ የመጣልኘ፡፡ እሱም ኦቦ ሽመልስ ነው፡፡ እየተዟዟረ አማራውን፣ ሱማለሌውን፣ አፋሩን፣ ደቡቡን…በፈጣን ኮንፊውዝና ኮነቪስ እጆቹ ሆዳቸውን ይነርታል እናም አብይም የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድህን ሆኖ ይገለጣል፡፡ ዜጋው በእንደዚህ ሁኔታ መብቱና ነፃነቱን ሲወሰድበት እያየን ይኸው አራት አመት አለፈ፡፡ እዚህ ላይ ምን ብለን እንጥራቸው? ሃቱ ወይስ ቡቱ? ሌባ ወይስ ዘራፊ?

በሰባዎቹ መጨረሺያ ላይ የጄኔራል ዊንጌት ት/ቤ ተማሪ ሳለሁ ወደ ት/ቤ ለመሄድ ኮልፌ- ሰፈረ ሰላም ያለውን ታይዋን ተብሎ የሚጠራውን የገበያ ስፍራ አቋርጬ መሄድ ነበረብኝ፡፡ በግዜው እዚያ አካባቢ የተለመደ ቀዩን ያየ ጥቁሩን ያየ ጨዋታ ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ ሁለት የውስጥ ገጻቸው ጥቁር የሆኑና አንዱ ደግሞ ቀይ የሆነ ምልክት ያላቸው ካርታዎች ወደ ላይ ገልብጠው፣ ሁለት ሶስት ግዜ ያሳዩና ከዚያ ካርታውን ገልብጠው፣ ወደጎን ወደ ጎን ይቀያይሩታል፡፡ በዚህን ግዜ የካርታው ጀርባ አንድ አይነት ቀለም ስላለው ተጨዋቹ ከስር ቀይ ቀለም ያለውን ካርታ መከተል ነው ያለበት፡፡

አጫዋቹ ከስር ቀይ ምልክት ያለበት ካርታ የቱ ነው ይላል? ከዚያም መነሺያ ይቆርጣል፡፡ በሃያ ብር ይባላል፡፡ ተጨዋቹ ያወቀ የመሰለው ግዜ የተባለውን ብር ያክል ያስቀምጣል፡፡ ሰውዬው በትክክል ቦታ ላይ ካሰቀመጠ እና ሌሎቹ የአጫዋቹ አጇኳሚ ጓደኞቹ የተጨዋቹን ቁመናና ኪስ ከመዘኑ በኋላ፣ እንዲያሸንፍ ያደርጉታል፡፡

ሰውዬው ማለቴም ተጨዋቹ የበላ ሲመስለው፣ ሁለት መቶ ሶስት መቶ… እየመደቡ ይሄዳሉ፡፡ በእውነት አይኑ የሰላ ከሆነ፣ ቀዩ ላይ በመቶዎች የሚቆጠር ብር ሲያስቀምጥ፣ አጇካሚዎች ደርበው ገንዘብ ያስቀምጣሉ፡፡ ጨዋታው ይፈርሳል፡፡ እንዲህ እያደረጉ ተጨዋቹን ማለትም ነጋዴ ሊሆን ይችላል ወይም ገበያተኛውን ባዶ ኪሱን ያስቀራሉ፡፡ እጁ ላይ የቀረ ሰዐት ካለው እንኳን በእጅ ሰዓት የሚጫወት አጇካሚ አለ፡፡ አጇካሚዎቹ የማይጠበቁ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ኮፊታ የደፋ ሞስሊም የሚመስል ሽማግሌ፣ ባልቴቶች፣ ጋቢ የለበሱ ባለ ጥላ ከዘራ ያዥ ጎለማሶች…

እንግዲህ ኦቦ ሽመልስ ፖለቲካ ቁማር ነው ካሉንና ይህን ድምጹን ከሰማንው ስንት ግዜ አለፈን? የቁማሩንም ጨዋታ ለማካሄድ ስንት ግዜ ባህርዳር እንደ ተመላለሱ ባአንደበቱ ሲናገር ሰምተንዋል፡፡ የከተማ የህዝብ ቁጥርን መቀየርና ኦሮሚኛ ተናጋሪውን በየክልሉ ማብዛት የኦሮሚያ ብልፅግና ፖለተካዊ ግቡን የሚመታበታ ስትራተጂው ነው፡፡እንግዲህ እዚህ ላይ ጥያቄው የሚነሳው፣ አጫዋቹ ማን ነው? አጇካሚውስ?

መንገድ ትራንስፖርት የሚሰሩ ሌቦች፣ በተሳፈራችሁበት ሁሉ አብረዋችሁ የሚጓዙ ናቸው፡፡ አውቶብስ ላይ ከሆነ፣ ትፍግፍግ ግፊያ ሲበዛ ምላጭ ይዘው የውስጥ የኮት ኪስ ይሰነጥቃሉ፡፡ ጉዞው አውሮፐላን ላይ ኮሆነ፣ ለምሳሌ  የቅዱሳን እምነት ነው ብለው በሐይማኖት አሳበው አደንዛዥ እጽ ከማሸከም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ አረ ስንቱ? እንደየ መጓጓዣው አይነት ይለያያል… የነ አብይ የፖለቲካ ንስሃ አባት የሆነው፣ አባ ዱላ ገመዳ፣ ጡረታ ወጣ መሰለኝ፣ በኢህአዲግ ግዜ ወርቅ በአየር መንገድ ተጭኖ ሊወጣ ሲል፣ ለአስቆመ ፖሊስ ጥቁር መነጽሩን ወረድ አድርጎ በምን አገባህ አተያይ እንዳየው በግዜው መረጃው ነበረን፡፡

አሁን ደግሞ ሌላኛ መጫወቻ ካርድ ብቅ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ የአብርሐም ልጆች ሐይማኖቶች መፍለቂያ ቦታ ባትሆንም፣ ሁሉም አብርሓማዊ እምነቶች ውስጥ ጉልህ ሰፍራ የያዘችበት መግነጢሳዊ ኃይል የሚገርም ነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን መውጫው ላይ ጀምሮ ፣ ከነብይት ቡርቱካን  እስከ ሼህ ጂብርል ድረስ የተናገሩለት ነው እየተባልን በየመሐበራዊ ሚዲያው ተሰበክን፡፡ ይህን ተከትሎም ብዙ የፐሮቴሰታነት ነብያቶችች ተግተለተሉ፡፡ የስልጣን ዘመኑ በአስር፣ አስራ አምስትና ሰላሳ አመት እንደሆነ ከፈጣሪ ሰምተናል ብለውም ተናገሩ፡፡ አንዱ እግዚአብሔር ሶስት አፍ ይኖረው እንደሆን እባካችሁ ጠይቁልኝ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢትዮጵያ የማዕድን ሙስናን ለመሸፋፈን የሚደረገው ዘበት

አሁን ሰሞነኛው የሆነው ደግሞ፣ የጠ/ሚ ባለቤት የዝናሽ ሃገር ጎንደር በእስልምናና ክርሰቲያን መካከል ለመስራት በተሞከረ ግጭት ታመሰች፡፡ የአብይ ሃገር ሰዎች ጂማ ላይ፣ ሞስሊም ጎንደሬወን ሊከላከሉ ሰልፍ ወጥተው  ፋኖን አሸባሪ ነው ብለው ፈርጀው አወገዙ፡፡

አይገርምም? ጎንደሬ ክርስቲያኑ እኮ፣ “እስላም ካበለ፣ ቀን ዘነበለ፡፡” ብሎ የሚተርት ነበር፡፡ ዘመናዊ ባንክ አፄ ምኒልክ እስቲያስተዋውቁ ድረስ፣ በአማራው ሀገር ያለ ክርሰቲያን ገንዘብ የሚያሰቀምጠው  ሞስሊሙ ቤት ነበር፡፡ አረ ምን ይህ ብቻ? በአማራ ስላለ “ግራ ጥሁፍ” ስለሚባል ነገር ልንገራችሁ፡፡ ይህ ከሸዋ እስከ ጎንደር ይታወቃል፡፡ እንደ ቤተ እስራኤሉ አሸንክታብ(ቴፊሊን) በአንገት የሚንጠለጠል ነው፡፡ ብዙ የአማራ ክርስቲያኖች ይህን በአረብኛ የተከተበ ህቡእ ስም ለመፍተሄ አጋንንታዊ ደዌዎች ከሼኮቹ ጋር ሄደው ያሰሩ ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ይሰራበታል፡፡ የሰው ልጅ ሲቸግረው፣ በአመነበት እምነት መፍተሄ ሲያጣ ወደ ቅርብ ጎረቤቱ ጠጋ ማለቱ በታሪክ የተለመደም አይደል፡፡

ይህ ሁሉ በእንዲህ እንዳለ፣ እሰቲ አንድ ነገር እናስታውስ፡፡ ጠ/ሚ ስለሮሞዳን ፆም አንድ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሞስሊሞች  የሉም ሰለሚሉን ሮሞዳንን…” ከዚያ በኋላ እየሆነው ያለውን ተመልከቱት፡፡ ለምን ስለ ቁጥር ማውራት እንዳስፈለጋቸው አልገባኝም፡፡ ኦሮሞ ስልሳ ሚሊዮን ነው የሚል ትርክት አለ፡፡ ሰባ አምስት በመቶው ኦሮሞ ደግሞ ሞስሊም ነው ሲል አሃዝ ያቀብላል፡፡

1996 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ ሞስሊም ሪፓብሊክ የሚል ህቡእ ድርጅት ተነስቶ ነበር፡፡ ይህ ድርጅት የሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሞስሊሞች ቁጥር ከስልሳ በመቶ በላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉ ብሔረሰቦች ኦሮሞ ከሃምሳ ፐርሰንት በላይ ነው ይልና፣ ከመቶ ኦሮሞዎች ሰማኒያውን ያክል ሞስሊሞች ናቸው ይላል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵው ጠ/ሚ ሞስሊም መሆን አለበት ሲል መደምደሚያ ያቀርባል፡፡ ፓርላማውም ከግማሽ በላይ በሞስሊሞች ሞሞላት አለበት ይል ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ 2000 ዓ.ም ጅማ ጉማ ላይ ለኢትዮጵያ መእከላዊ መንግስት አንገብርም የሚል አልቃይዳን መሰል ቡድን  ተመሰረተ፡፡ ከጂማ እስከ ወለጋ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ቤ/ክርስቲያናት ተቀጠሉ፡፡ አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት ቤ/ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ካልተሳሳትኩ የተቃጠሉት የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያናት ቁጥር ከአስር አይበልጥም፡፡ ዶ/ር አብይ የፒ.ኤች.ዲ ጽሑፋቸውን የሰሩት በጂማ ባለ የሐይማኖት ግጭቶች አፈታት ላይ እንደሆነ አምብቤአለሁ፡፡

ከአስር አመት በፊት የወያኔ የደህንነት ሹም ከኢ.ቲ.ቪ. ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ሁለት ኋይሎች ኢትዮጵያ ላይ እየተዋጉ ነው ብሎን ነበር፡፡ አንደኛው ከአረብ ሃገራት የሚመጣው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ይነሳል፣ የፔንጤውን ኋይል ማለቱ ነው፡፡

በወያኔ የመጨረሻ አስር አመቶች፣ በአዲስ አበባ የቦኮ ሃራምን አሰተምሮ የሚከተል  ዊንጌት ት/ቤ አካባቢ አቡደርዳር የሚባል ሰፈር ተፈጠረ፡፡ አቡደርዳሮች ልጆቻቸውን ት/ቤ አይልኩም፡፡ ከእነሱ የተለዩ አሰተምህሮ ያላቸው የመንግስት(ወያኔ) የስልጣን መዋቅር ውስጥ ስልጣን መያዝ አለብን ብለው የተሰማሩም ፖለቲካዊ ሞስሊሞችም ተፈጥረው እንደነበር ይነገራል፡፡

ያን ግዜ አንድ የወለጋ ተወላጅ የሆነ የሞያ አጋሬ መምህር የነበረ የገነት ቤ/ክ ፓስተር ነበር፡፡ ፓሰተሩ ወደጄ ለእዚህ ጽንፋዊ እንቅስቃሴዎች በፕሮትሰታነት ዘንድ ማርከሻ የፖለቲካ ንቅናቄ እንደነበር አጫውቶኛል፡፡ ለዚህም ኦረቶዶክሱን ለመያዝ እንደሚፈልጉም ገልፆልኝ ነበር፡፡

አይ. ኤስ.አይ.ኤስ የካሊፌት ግዛት ባለበት ካርታው ኢትዮጵያን ያጠቃለለ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትውሰታ ነው፡፡ የወያኔ(ማሌሊት) ኃይሎች ደግሞ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ አህባሽ የተባለውን የእስልምና ዘርፍ ኢትዮጵያውያን ሞስሊሞች እንዲከተሉ በሴሚናር ሊያስገድዱ ሞከሩ፡፡ ወያኔ (ማሌሊት) ክርስቲያኑንም ሆነ ሞስሊሙን በየቤተ እምነቱ እንደቀጠቀጠ ነበር ዘመኑን የጨረሰው፡፡

አሁን፣ አሁን ጠ/ሚ አብይ አንድ ነገር ከተናገሩ በኋላ ለምን መዓት እንደሚመጣ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አብይ ቤንሻንጉል ጉምዝ ሄደው እኛ የምናወራው  ጫካ ውስጥ ስላለው ዘጠና ሺህ ጉሙዝ ነው፡፡ እነሱ ፌስ ቡክ ስለሌላቸው የሚጮህላቸው  የለም አሉን፡፡  ያን ተከትሎ ስንት አማራ፣ አገውና ኦሮሞ… በቀስት ተገደለ፡፡ ቀብራቸውም በኤክሰካቫተር ተካሄደ፡፡ እዛ ጋር ነው  የዲፐሎማሲው ከፍታ ዝቅዝቅ የወረደው፡፡ የደምቢዶሎው የአማራ ተማሪዎች ጠለፋ ማረጋገጫ የሌለው ውሸት ነገር ነው ሊሉንም ሞክረዋል፡፡

አሁን ደግሞ ጨዋታ ጨዋታቸውን ላውጋ፡፡ የወሎው ሱፊ ሞስሊም ሼህ ሁሴን ጅብሪል ስለ ጠ/ሚ እንደተናገሩ ተደርጎ በጀሌዎቻቸው ሲነገር እንሰማለን፡፡ እውነት ነው የሞስሊምና የክርስቲያን ልጅ የሆነ ደግ ሰው ለኢትዮጵያ በክፉ ዘመን ይደርስላት የሚል ትንቢት ተናግረዋል ተብሎ ስለ እሳቸው በተጻፈ መጽሐፍ ላይ አንብቤለሁ፡፡ በፍጹም ከጂማ የሚል ነገር ግን የለም፡፡ ስለ እሳቸው ግጥሞች በሃምቡርግ ዩንቨርሰቲ የቀረበ(1996 ዓ.ም.) ጽሑፍ ቁ. 162

 

አስመራና ትግሬ ስትል ሺህ ገዳይ                                                      እባብ ከተፍ ይላል መምጪያው ሳይታ፡፡       ሸዋ የዚያን ግዜ ይላል ዋይ! ዋይ! ዋይ!        ጀርባውን መጅ መታው ወደ ትግሬ ሲያይ፡፡

እሳቸው የወዲፊቱን ተናግረዋል ከተባለ፣ ሸዋ ኢትዮጵያዊነትን የሚወክል ፖለቲካን አመለካች ሆኖ ነው የተገለጸው፡፡ ሸዋ ጀርባውን የተመታው ከዚህ ዘመን ውጭ መቼ ነው? ወያኔ ወደ አራት ኪሎ ሲመጣ በግልጽ በጦረነት ነው፡፡ እንደ እባብ መምጪያው ሳይታወቅ አይደለም፡፡ ሸዋ ወደ ሰሜን አቅንቶ ሲያይ ከጀረባው የተነሳው ኃይል፣ ከአብይ መንግስት ሌላ ማን ሊሆን ይችላል?

ስለሚመጣው የመልካሙ ግዜ ጥሩው ንጉስ፣ተናገሩ የሚባለውም

በአባቱ ገ/ ህይወት በእናቱ ፋጡማ        ይመጣል በጧት ጠሐይ ድምጹ ሳይሰማ፡፡                                                          በስተ ጠሐይ መውጫ ይመጣል ያሉት                                                   እኔን ይመስለኛል ከመሐመዶች ቤት፡፡

እንግዲህ ጂማ በሻሻ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ካርታ በምስራቅ በኩል ነው የሚል ካለ የዞረበት ብቻ ነው፡፡ ወገን ግጥሙን እዚህ ላይ ያዝ፡፡ ሁለቱም፣ ማለትም አብይና ጀዋር ለምን ይመስላችኋል በእናቴ፣ በአባቴ፣ በባለቤቴ ኦርቶዶክስ፣ ሞስሊም ና ፐሮቴስታንት ነኝ እያሉ የሚነግሩን? ኦሮሙማ አዲስ የኤቲስት ብያኔ እንዳለው ባላውቅም ጀዋር ወላጅ አባቱ ኤቲስት እንደነበረ ነግሮናል፡፡

የበሻሻው አራዳ አብይ ግን የአፄ ቴውድሮስ ሀገር ተወላጇን እመቤት ዝናሽን በጥናት በትዳር በመጣመር ጀዋርን ቦንሰውታል፡፡ ጀዋርስ ቢሆን ወለጋ ዘልቋል እኮ፡፡ መቼም አብይ አህመድ ሩዋንደ በነበሩበት ግዜ አንዲት ፈረንሳዊት ይዤህ ሊህድ ስትለኝ፣ እኔ ወደፊት ንጉስ የምሆን ሰውዬ እምቢ አልኳት አሉን፡፡ ዱሮ ከወታደር ጓደኞቻቸውም ጋር ፎቶ እንደማይነሱ ነግረውናል፡፡ ለምን? ወደ ፊት ንጉስ ሲሆኑ በኋላ እያሳዩ…ወቼ ጉድ እንዲህ ነው መስመራዊ ጓድነት፡፡ ይህ በዩትዩብ ላይ ስለሚገኝ መመልከት ይቻላል፡፡

ማንም ይምዘዘው ማን፣ በአውራው የኦዲፓ(ኦሕዴድ) ብልጽግና ዘመነ፣ ስለ ስልጣን ሲባል የሐይማኖት ካርድ ተመዟል፡፡ ጎጋውን ሞስሊሙንም በሰሜት ሊነዳ አቅዶ እየንተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ግን አንድ ጥያቄ እዚህ ላይ መጠየቅ እፈልጋለሁ? በኢህአዲግ ግዜ ለኢትዮጵያውያን ሞስሊሞች፣ ኩማ ደመቅሳ አህባሽን ሲያስተዋውቅ የስለላ መረቡን በበላይነት ሲመሩ የነበሩ አለቆች ሚናቸው ምን ነበር? መቼም የኦነጉን ለሱኒው ኢትዮጵያውያን ሞስሊሞች ሊሰብክ ሲሞክር፣ ለገሰ ወጊን ላድን ሞክሬ ነበር እና ለግንቦት ሰባትም መረጃ አቀባይ ነበርኩ እንዳሉት፣ ኩማ ደመቅሳ የለማ መገርሳ ግዛት የነበረው ኮተቤ ላይ ተሰፊር ሊያደርግ ሲሞክር ተው ብዬው ነበር እንዳይሉን፡፡ መቼም ወያኔ የሃገሩን በሬ በሃገሩ ሰርዶ የሚለውን ቢህል ተጠቃሚ ስለነበር አስተያየትዎን ለማወቅ ፈልጌ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቅዱስ ፓትርያርኩና የማኅበረ ቅዱሳን ልዩነት ወደ ሃይማኖት አደገ

የደርጉ ኮሚኒስት ግዜ  የክርስተያኑም ዘርፎች እንዲሁም የሞስሊሙም እምነት ተከታዮች የነበሩ ካድሬዎች ነበሩ፡፡ አንድ የሞስሊም ሼክ  ነኝ የሚሉ ካድሬ ወደ አንድ ቤት ጎራ ይሉና ይለምናሉ፡፡ እንደኛው የቆሎ ተማሪዎች ማለት ነው፡፡ ስራቸው ግን በየጓዳው እየገቡ የህዝብን የልብ ትርታ መሰለል ነበር፡፡

በዘመዶቼ ወለዬዎች ዘንድ ሴት እንዳያዩ ፊታቸውን የሚሸፍኑ ሼሆች ነበሩ፡፡ እሳቸውም እንዲህ ያደርጉ ነበር፡፡ ለቆንጂት አይናማዋ ሃውለት፣ ፊታቸውን እንደጋረዱ ከበርሽ ቆሜአለሁ አሏት፡፡ ምግብ አውጥታ ልትሰጣቸው ስትል፣ አይነ እርግባቸውን  አንስተው እጭኗ መሃል  እያዩ አምጪ አሏት፡፡

“ምን ነው እነ ሼሁ?” አለች፡፡

“ካንቺ ያለብሽ መረሃባ፣ ኪታቡ ያለው ከኛ ጋራ፡፡” ሆነ መልሳቸው፡፡ አጃይብ በል ወሎ! አጃይብ በል ጎንደር! በጻፍኩልህ መጽሐፍ ተሰፈር፣ በቀደድኩልህ ቦይ ና ውረድ ግዜ ላይ ደረስን እኮ፡፡

ጀዋር እሱ በተወለደበት አካባቢ ክርሰቲያኖች አንገታቸውን ቀና ቢያደረጉ በሜንጫ ነው የምንላቸው ያለ ግዜ፣ የን ለምን እንደዛ እንዳለ መብራሪያ ሲሰጥ ጎንደሬ ሞስሊም ጓደኛው በጎንደር ሞሰሊሞች ላይ የሚደርሰባቸውን በደል በነገረው ግዜ ወገንተኝነቱን ለማሳየት መሆኑን ገልጾል፡፡ አክሎም ኦሮሞ ተደረጅቶ እራሱን ነፃ ካወጣ ለትግራዩና ጎንደሬው ሞስሊም ይደርስለታል አለ፡፡ የሚገርመው ግጥምጥሞሽ ደግሞ ጀዋር ከእስር ተፈቶ ከሀገር ከወጣ በኋላ የጎንደር ሞስሊሞች ላይ ይህ ጥቃት መድረሱ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚለውን አባባል ብናነሳው ተገቢ አይሆንም ትላላችሁ? አንዱ ወፍ ፋኖ ነው፡፡ ሌላኛውን ደግሞ እናንተ ገምቱ፡፡

የሆነ ሆኖ ጀዋር ያን ንግግር በሚያደርግበት ግዜ  ያስብ የነበረው፣ ለኦሮሞ ሁሉ  መንፈሳዊ ግቡ መዳረሻው እስልምና እንደሆነ ነው፡፡ ታዲያ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? አለው እኮ፡፡ እዚያው እሱ ይህን የተናገረበት መድረክ ላይ  ሰማኒያ በመቶ ኦሮሞ ሞስሊም እንደሆነ ይነገር ነበር፡፡

የኦሮሞ ፖለቲከኞች የመጨረሻ ግብ ግራ ያጋባል፡፡ ለግል ስልጣንና ጥቅም ሐይማኖትንም ቢሆን እስከ መጠቀም መሄድ ነው? ወይስ ኦሮሞን “ነፃ አውጥቶ” ፍትህና እኩልነት አስፍኖ ማስተዳደር ነው? ኦሮሞን በግድም ይሁን በውድ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ማንገስ ነው? መቼም ሟቹ ጠ/ሚ መለስ የተናገረውን ሰምታችሁ እንዳይሆን ይህን ያህል የምትንቦጃቦጁት፡፡

ኦሮሞን ከፈለገ ማን ያቆመዋል? ምስራቅ አፍሪካን ከፈለገ ይጠቀልላል አይነት ንግግሩን ማለቴ ነው፡፡ መቼም መለስ በዘረኝነት ይታማል እንጂ በአንጻራዊነት ሲታይ ከእውቀት ማነስ ነፃ ነው፡፡ ስለ ኦሮሞው ማህበረሰብ እንዲያ ብሎ የተናገረው ያው ”ዶሮን ሲያታልሏት፣ በመጫኛ ጣሏት“ የሚለውን አባባል ይዞ ነው፡፡

1993 ዓ.ም. ከወያኔ ክፍፍል በኋላ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ መምህራን፣ ወያኔ በክረምት መርሐ ግብር ለተከታታይ ሳምንታት ፖለቲካው ሲግተን ነበር፡፡ እኔም የአዲስአበባ ከንቲባ የነበሩት አቶ አሊ አብዶ የሚያሰለጥኑበት ስብሰባ ታዳሚ ነበርኩ፡፡

አሊ አብዶ ስልጠናው ላይ “ዱቤ የሚለው ስማችንን ዱባለ በሚል እንድንቀይር የነፍጠኛው ስርአት አስገድዶን ነበር…” አሉ፡፡ የጥያቄ ሰዓት ሲደርስ እጄን አውጥቼ “የቀደሙት የፊውዳል ኢትዮጵያ ነገስታት ስም ማሰቀየርን አጀንዳቸው አድርገው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ጃጋ ማኬሎ ጀነራል ደረጃ የደረሱት ስማቸውን ሳይቀይሩ ነው፡፡ እነ ገረሱ ዱኬስ ቢሆኑ…እንደሚመስለኝ ሰዎች ስማቸውን ከራሳቸው እምነትና አመለካከት ተነስተው ሊቀይሩ ይችላሉ፡፡

“ክርስቲያኖች ለምሳሌ ከሐይማኖታቸው የተነሳ የመ/ቅ የአይሁድ ስሞችን ወስደው ይሰየሙባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የእርሰዎ ስም ኦሮሚኛ አይደለም እንደሚመስለኝ በሐይማኖት ተጽኖ የአረብኛ ስም ይዘዋል…አንድ ብሔረሰብ የአጎራባቹን ብሔር ስም ለልጁ ቢሰይም እንደምን ነቀፌት ሊሆን ይችላል?” ብዬ ጠየቅኩ፡፡

የአሊ አብዶ ምላሽ ሌሎች የተናገርኳቸውን ፖለቲካዊ አስተያየቶችን አባሪ አድርገው በማቅረብ  “እኔ እዚህ የመጣሁት አንተ ኢህአዲግ እንድትለኝ፡፡ እኔ ደግሞ መአህድ እንድልህ አይደለም…” ብለው በፍረጃ አፌን ለማዘጋት ሞከሩ፡፡ አንድ የኢህአዲግ አባል የነበረ ወዳጄ የሒሳብ መምህር በበነጋታው ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ወደ እኔ ጠጋ ብሎ፣ ማታ ከስብሰባ በኋላ እለቱን ስንገመግም ስለ አንተ ተነሳና የፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳልሆንክ ግን የቀዳማዊ ኃ/ ስላሴ አፍቃሪ መሆንህ ላይ ተወያየን አለኝ፡፡ ከውጭ ሃገራት ባህላዊ ማዕከሎች ጋር ጠጋ ጠጋ የምትለውን ነገርንም ተነጋግረንበታል አለኝ፡፡ የአዱ ገነት ልጅ ባለህበት ይመችህ፡፡

አሊ አብዶ ስብሰባው እንደተጀመረ፣ አንዳንድ የውጭ ሀገራት ተልእኮ ይዘው ስብሰባችንን ከመስመር አቅጣጫ ውጭ ሊያደርጉ የሚሞክሩ አሉ ሲሉ አፌን በወያኔ ጌታቸው እጅ ሊሸብቡ ሞከሩ፡፡ይህ ነው አሁንም ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እውነታ፡፡

መንግስትን የማይመች አንድ ነገር ተናገር ስም ይለጠፍልህና ለምት ያዘጋጁሃል፡፡ እንዴት በዚህ ግዜ ይህን ትናገራለህ ይሉሃል፡፡  በጦርነት ስም የፖለቲካ ቁማራቸውን የሚያሰሉበትን ግዜ፣ ከአካይስቱ ጌታቸው አሰፋ የወያኔ ትምህርት ቤት ትዝታቸው እራሳቸውን የሚያሰመርቁበት ግዜ፣ ኮምፓሷና ማህለቋ እንደ ጠፋባት መርከብ ኢትዮጵያን በማረፊያ አልባ ወጀብ የመቱበትን ግዜ፣ አቦ ተውና፡፡

ከተነሳ ላይቀር እስቲ ስለ ስም ትንሽን እንበል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የኔን ስም የሚያወጣ፣ አልገቤው ባላገር የሚሉት ነፍሱን የሚያዳምጥ ካልሆነ ማን አለ? መቻል እኮ የውሻ ስም ነው ብለው የሚቀልዱብኝ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ ከተሜነት ሲቀለድብህ አብረህ መሳቅና በእራስ ላይ መቀለድም አይደል?

የኦሮሚያ ባለስልጣናት አድሮ ቃሪያ መሆናቸው ስለምንድን ነው?  ለምን ስሜ ኃይለእየሱስ( ኃይሉ ጎንፋ) መባል ተጀመረም መጥቷል፡፡ ያውም የኦሮሚያ የፀጥታ አማካሪው ጀነራሉ፡፡  ምን ችግር አለው? እዚህ የምኖርበት ካናዳ፣ በብርቲሽ ኮሎምቢያ ውስጥ የህዝቡ ቁጥርን ካሰብነው ኤሲያው ይበልጣል፡፡

ነገር ግን፣ ቻይናዎቹ ሁለተኛ ስም አላቸው፣ የውም በፍቃደኝነት፡፡ ምክነያቱም አንድ የቢዝነዝ ሰው ስራው እንዲሳለጥለት፣ ለኮሚኒኬሽን ሲባል ቀላል ስም ያወጣል፡፡ ብዙዎቹ በሚታወቅ የአውሮፓውያን ስም እራሳቸውን ይጠራሉ፡፡ ሀበሸውም እንዲሁ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ እነ ተመስጌን ቶም ተብለዋል፡፡ አለማየሁ፣ አሌክስ፣ ቶሎሳ ደግሞ ቴላስ፣ እኔም አስቻለው፣ አሹ፡፡

ይሄ ለኮምኒኬሽን ስሉጥነት ሲባል የተደረገ ነው፡፡ ካንቶኒስና መንደሪን ተናጋሪው ለራሱ ቢዝነስ ሲል ያደርገዋል፡፡ በየ መስሪያ ቤቱ ሲቀጠሩ ማን ተብለህ ልትጠራ ትፈልጋለህ የሚል ጥያቄ ቅፁ ላይ ይሞላል፡፡

ኃይሉ የሚለውን ስማቸውን የተጠየፉት ሰውን አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ፡፡ ለምን የኦሮሞ ስሞች የአረብ ስሞች ሆኑ ብለው አይናገሩም? እሰቲ መሐመድ ጨቋኝ ነበር ይበሉን፣ እየሱስ የሚለው ስማቸውን ፖለቲካሊ እንደተጠየፉት ፡፡ ወይም አህመድንም እንደዛው፡፡  ከዚያ ጂማ መሄድ አያስፈልግዎትም አሪሲ ላይ ይጠናቀቃሉ፡፡

መቼም ስምን መልአክ ያወጠዋል ብዬ አልዘባበትም፡፡ አንድ በቀድሞው የኢትዮጵያ ደርግ ዘመን የተነገረ  ቀልድ ላጋራችሁ፡፡ አብዛኞቹ አንጋፋ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከአብዮቱ መባቻ ጀምረዉ በመደባዊ ትግል ውስጥ ያለፉ ናቸውና፣ መኢሶን፣ኢጫት፣ ኢሰፓ… ስለዚህ ውስጠዘው ይገባቸዋል ባይ ነኘ፡፡ በደርግ ግዜ መደባዊ ስሞች ለሰዎች መጠሪያነት ይውሉ ነበር፡፡ ታገል፣ አብዮት፣ ሰፊው ህዝብ፣ እናት ሀገር…

አንድ በአብዮቱ ካምፕ የሚኖር ቤተሰብ ነበር፡፡ አባት አብዬት ይባላል፡፡ እናት ደግሞ እናት ሀገር፡ ልጅን ምን ብለው የጠሩት ይመስላቹሃል? ሰፊው ህዝብ፡፡ አንድ ቀን ልጅ ሰፊው ህዝብ ቀኑን ሙሉ ት/ቤ ውሎ እንደራበው ተሲያት ላይ እቤት ሲመጣ፣ እናቱን መጣራት ጀመረ ግን መልስ የለም፡፡

በቤቱ ውስጥም ምንም ምግብ የለም፡፡ በተንገረበበው በር ወደ ጓዳ አዝልቆ ቢያይ፣ አባትና እናቱ አልጋውን ትተው መሬት ላይ መርፌና ክር ሆነው ይታገላሉ፡፡ ከዚያም ምን አለ መሰላችሁ“አብዮት እናት ሃገርን በጠራራ ፀሐይ እመሬት ላይ አስተኝቶ ይኮደኩዳል፣ ሰፊው ህዝብ ግን በርሃብ ያልቃል፡፡”

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ከሰው ያቀያይማል"??? - ጠገናው ጎሹ

ለወንድም አብይ አህመድ አንድ ነገርን ልል እፈልጋለሁ፡፡  በዘመንዎ ያለተፈጠሩ የፕሮትሰታንት የነብያት አይነት የሉም፡፡ ጡጡ ጣጣን የመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ ያደረገ ነብይ ባይ ነኝ የሚለውንም ሰምተንዋል፡፡ አንድን ህፃን ቻይነኛ ተነገር ብትለው፣ የሚለውን የህጻናት ጂብሪሽ አይነትም የመንፈስ ቅዱስ ልሳን ነው ተብሎ ጎጋው አማኝን ሃሌሉያ ሲያስብል በሚድያ ላይ ተመልክተናል፡፡

አብዛኞቹ አንድ አይነት ናቸው፣  ነብይነቴ በፕ/ት ትራምፕ ዘመን የተረጋገጠ ነው የምትለውንም ጨምሮ፣ ኮሮና አዋረዳት እንጂ፡፡ ስለእርስዎም የማይነገር የትንቢት አይነት የለም፡፡ ከብዛቱ እርስ በእረስ መጋጨቱ፡፡ እራሳቸውን ነብይ ብለው የሚጠሩት የህልምና ራእይ ትርጉም እንኳን በቅጡ ያለገባቸው ናቸው፡፡ መቼም ይሄ መንፈሳዊ ሿሿ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ሿሿውን የሚሰራው ግን  አጋንንት ይሆን ፖለቲካው መለየት እስኪያቅተን ድረስ ተቸግረናል፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ከእውቀት ማነስ የተነሳ ነው እንደዚያ የሚሆኑት፡፡ አንድ ጋሞ ውስጥ በደርግ ግዜ የነበረ  ተገለጠልኝ ያለ ፕሮቴሰታንት፣ ለተከታዬቹ እንደ ኤልያስ እንነጠቃለን ብሎ የበቆሎ ማሳ ውስጥ ይዟቸው ገባ፡፡ ኋላ ግን ተከታዬቹን ሁሉ የደርግ ጅራፍ ሲሳይ አደረጋቸው፡፡ ከዚያው ቦታ የመጣው፣ ጡጡ ጣጣ፣ ነብይ ነህ ብለውት ነግረውት ነጭ ሳር ፓርክ ውስጥ ገብቶ አምላኩን ለማግኘት እንደ ጸለየ በመሐበራዊ ሚዲያ አጫውቶናል፡፡

ግን እራበው፣ የሚበላው አጣ፡፡ ወደ አእምሮው የሚሄደው ኦክስጂን ተቋረጠ፡፡ ሆዳችን ሲጠግብ የደም ዝውውራችን ሁሉ ወደ ታች ስለሚወርድ ኦክሲጂን ወደ አእመሮ ክፍላችን ስለማይወጣ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ይለናል፤ያንጎላጂጀናል፡፡ እንደዚሁም ሲረበን ክስተቱ አንድ አይነት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ቢሆን ይህን እኮ ነው የሚለው “ከድካም የተነሳ ህልም ይታለማል …”

ሲረበኝ ይህ መ/ቅ ገጽ በገጽ በልቼለሁ የሚለው ወጣት፣ ምናልባት መሬት ላይ ይወድቃል ከዚያም የነጭ ሳር ጦጣዎች ይመጡበታል፡፡ ከዚያም አንቺ ጦጣ፣ አንተ ጦጣ እያለ ለመጣራት ይሞክራል፡፡ ከዚያ ምኑ ቅጡ…ጡጡ ጣጣ የመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ ሆኖ ሊገለጽለት ይችላል፡፡ ይህ ግን ለከተሜዎቹ ነቢያትም በተለያየ አግባብ ይሰራል፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው እራስክን ፈትሽ “ማንም የቆመ የሚመስለው ቢኖር…” ሃገርን በምረቃና መግዛትና ማስገዛት አይቻልም፡፡

የሳይኮ አናሌቲክስ ቀደምቶቹ እነ ካርል ዮንግ እንደሚሉት፣ ህልም ሲፈታ ድብቁንና የተሸረጠውን ንቃተ ኅሊና ውስጥ ያሉትን ነገሮች እንደ ግብዐት ይወስዷቸዋል፡፡ እኔም ይህን ይዤ ይህን ጽሁፍ ላዘጋጅ ስል የተገለጠልኝ የመሰለኝን የሰመመን ህልም በእራሴ ላይ ለመተንተን ሞከርኩ፡፡ ይገርማል!

ከአርት ት/ቤ ምሩቃን ጋር ታላቅ ወደጅነት ነበረኝ፡፡ የእስክንድር ቦጎሲያንና የሜተር አርቲስት የአለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አድናቂዎች መካከል ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ችያለሁ፡፡ ሁለቱ ጉምቱ ሰዓሊያን እናት ኢትዮጵያ ብለው የሳሏት ምስል አንድ አይነት አይደሉም፡፡ አንዱ በታሪክና ባላት እምቅ ኃይል ሊያስውባት ይችላል፣ ሌላኛው ደግሞ ባለው አሁናዊ ህልውናዋ ሊያኮሰምናት ይችላል፡፡ የሰአሊውን የእይታ ነፃነት እንቀበላለን፡፡

አሁን ወደ ህልሜ፡፡ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ እንደማንኛውም ሰላም ወዳድ ሰው ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ሰው ወደ ስልጣን መጣ አልኩ፡፡ በብዙ ወጀብ ውስጥ ያሉ ሰው ቢሆኑም መጨረሻ ላይ የመፍትሔው አካል መሆን ይችላሉ ብዬ አሰብኩ፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ እንደ አንድ ዜጋ የተሰማኘ ስሜት ነበር፡፡ በዜግነት መብት ደረጃ ከሆነ ደግሞ አንድ ኢትዮጵያዊ ከጠ/ሚሩ ጋር እኩል ነው፡፡

ነገር ግን፣ ነገሩ ሁሉ ውሎ ሲያድር ከኢትዮጵያ እኛ፣ ወደ ኦሮሙማው ኬኛ ተቀየረ፡፡ በዚያም አላበቃም ወደ ጠ/ሚ አኒሞ(እኔ) ተዳረሰ፡፡ እኔና መሰሎቼ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ አዲስ የተነሳን ሰው አብረን አናጣምም አልን፡፡ በቫንኮቨር ረዲዮ ጣቢያ ላይ ከሁለት አመት በፊት ቀርቤ ይህንኑ ተናግሬአለሁ፡፡ ጠ/ሚሩም ወደ ፊት እያዩ ወደ ኋላ  ስለ ሚደንሷትን የማይክል ጃክሰን ዳንስም አውግቼለሁ፡፡

አዲስ ከሚነሳና የህዝቡን ቀልብ ይስባል ከሚሉት የብሔርም ይሁን የህብረ ብሔር ሃሳብ ጋር ፊታቸውን በፈገግታ ሞልተው እየተያዩ፣ ወደ ኋላ  የተዉት ከሚመስለው ማጠንጠኛው አቋማቸው፣ በማይክል ጃክስን ዳንስ ሲጓዙ በተደጋጋሚ አስተውያለሁ፡፡

የእኚህ ሰው አገዛዝ በልዋጥህ ተደበልበሉ የእሳቸውና መሰሎቻቸው ርእዮት አለም  የሆነው ኦሮሙማ ላይ የተማከለ ነው፡፡ በብሔር ብሔረሰቦች ላይ ያላቸው አተያይ ከደብል ስታነዳርድ አልፉአል፡፡ በአይሁድ እምነት ባለው መሲህነትና በናዚ ጀርመን መሪ ፉረር መካከል በተቀረቀረ የመሪነት ዘይቤ ሲዳክሩ ይታያሉ፡፡ ለእሳቸው ንግስና ያለተንበረከከ ነፍስ ሁሉ ይጠፋል፡፡

ጡጡ ጣጣ፣ ቸሁንግ ቻን ሻይ…ፓፓራላላ ነመስቴ ትሪና ዳባሽ ነብያቶቻቸው ሁሉ ይሄንኑ ለምእመናኑ ይሰብኩላቸዋል፡፡ እሳቸውን ስመለከት ለእኔ ግን የሚታየኝ የፊውዳሉ መሪ መገለጫ የሆኑት የፍቅር እስከመቃብሩን ፊውታራሪ መሸሻ ናቸው፡፡

ፊውታራሪ መሸሻ በየአመቱ የሚዘክሩት ታቦት ሲቆጡ አብሮ የሚቆጣ ይመስላቸው ነበር፡፡ ግዜው ፊውዳሊስም ስለነበር፣ ቀለሙም ብዙ ስላልዘለቃቸው፣ ሰለዚያም እንረዳቸዋለን፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ት/ቤት ተምሬለሁ ያውም በ ፕ.ኤች.ዲ ደረጃ የሚል ሰውን ምን እንበለው?

እንግዲህ በዚህ ውዥንብር ውስጥ ሆኜ ነው ያን ህልም ያለምኩት፡፡ ለዚህም የእዚህ ሁሉ የሃሳብ ምዛኔና ቅንብሩ፣ የጠ/ሚ ተቀዋሚዎች የበሻሻ አራዳ ስያሜ ሰምቼ በውስጤ ቀን ላይ ሲነታረክብኝ የሚውለው ሃሳብ ሁሉ ተሰናስኖ፣ በህልሜ(unconscious)   ከሆነው የአእምሮዬ ድብቅ ክፍል ብቅ አለ፡፡ ይሄው ነው መገለጡ፡፡ ከጠ/ሚ ሃገርን በፓርኮች ማስዋብና በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ… በትሪሊዮን ብሮች የሚገመት ውድመት ስለ የትኛው ግድ እዲለኝ ይገባል?

አሁን በኢትዮጵያ ሰፍኖ ያለውንና በህዝቦች ጥፋት ላይ ግለሰቦችን ሃብታም የሚያደርገውን የብሔር ፖለቲካ ሳስብ ዱሮ እናቴ ከአርባ አመት በፊት ገዝታ የሰጠችኝ ድርሰነ ገብርኤል ላይ የተጻፈ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ታሪኩ ከቤተ ክርሰቲያን ግንባታ ጋር ይያያዛል፡፡ መጽሐፍስ እንደሚለው ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይደል፡፡

ዐውር የሚባል አንድ ቤ/ክ የሚገነባ ሰው ነበር፡፡ አውር ቤ/ክ ሲገነባ ሴይጣን በሽማግሌ አምሳል ወደ እሱ ጋር መጣ፡፡ በዚያም ተቀመጠ፡፡ እኔ በጌታ ቤት ቁጭ ብዬ መጦር አይገባኝምም አለ፡፡ ከዚያም ትንንሽ ጡብ ድንጋዬች በአቅሜ ላቀብል ብሎ ተቀላቀላቸው፡፡ ጎረምሳ ሰው የማይችለውን ታላቅ ድንጋይ እያነሳ፣ ከመሰላል በታች ያሉ ሰዎች አናት ላይ ይጭንባቸውና ይገድላቸው ጀመር፡፡ ሰራተኞች ቢያምጹ አውር ሴይጣኑን ውሃ አመላላሽ አደረገው፡፡

ያም ሴይጣን ውሃ በአህያ እየጫነ ከሩቅ ቦታ ያመጣል፡፡ ልክ ቤ/ክ ጋር ሲደርስ ውሃ የያዘውን ማድጋ ይሰብራል፡፡ እንዲህም ብሎ ያስባል፣ የውሃውን ምንጭ አደርቃለው፡፡ የአህዮቹንም ጉልበት አደክማለሁ፡፡ የቤ/ክ ስራም እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያን በድንጋይ እየወገራት ያለውና እዝቦቿን ለረሃብና ውሃ ጥም እየዳረገ ያለው  ምንድን ነው ብለን ብንጠይቅ፣ የዜግነት ክብርን የሚያሳጣው የብሔር ፖለቲካ ሆኖ እናገኛዋለን፡፡

ንቃ ወገኔ! በብሔር ልክ ተሰፍታ ፍተህን ለዜጎች የምታሰፍን ኢትዮጵያ የለችም፡፡ ወያኔ ለሃያ ሰባት አመት ሞክሮ አቆሳስሎን ሄዷል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ደግሞ የተጫነብንን የእንጨት ቀንበር አወረደልን ስንል የብረት ቀንበር እየጫነብን ይገኛል፡፡ ጣኦት የነበረውን ወያኔን ሰባብሮ ጥሎ ሰብረባሪውውን መልሶ አብኩቶ ሌላ ጣኦት መሆን ፈልጓል፡፡

ፍትህ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊና ሁሉም ዜጎቻን በእኩልነት የምትጠቅም ኢትዮጵያን ማየት የምንፈልግ ሁሉ ተረኝነትን፣ የግለሰቦች አምባገንንነትና የአውራ ብሔርተኝነት አስተሳሰብን በመዋጋት ትግላችንን አጠናክረን መቀጠል ይገባናል፡፡

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ

 

 

1 Comment

  1. መቸውንም ቢሆን እንደ ሃበሻ ያለ አስቸጋሪ ህዝብ በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም። ዝፈን ሲሉት የሚያለቅስ፤ አልቅስ ሲሉት የሚዘፍን፤ በምቀኝነትና በፈጠራ ወሬ የሰከረ፤ እርስ በእርሱ የማይተማመን አሁን ደግሞ ይባስ ተብሎ በክልል ፓለቲካ ዝብርቅርቁ የወጣ ለገዥም ለአስተዳዳሪም የማይመች ህዝብ ነው። ይህን ጉዳይ ለማረጋገጥ በእኔ ሃሳብ ላይ ድንጋይ ከማዝነብ ወደ ኋላ ታሪካችን መርምሮ ከአሁኑ ጋር ማገናዘብና እውነቱን መረዳት ይቻላል። ድሮም ቢሆን ከብት እረኛው፤ ገበሬው፤ ነጋዴው፤ ባጠቃላይ በምድሪቱ ያሉ ሁሉ መንግስትን በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የሚተነኩሱበት ነገር አያጡም ነበር። አሁን ደግሞ ጊዜው ሰልቶ በፈጠራም በቅመራም የሚቀርብለትን ወሬ እየተጋተ ስንቱ እንደ እንቁራሪት በነሲብ በጅምላ ሲንጫጫ መስማት እየተለመደ ሆኗል። የአሁን የዓለም ችግር የወሬ እጦት ሳይሆን እውነትና ውሸቱን ለይቶ ማየት አለመቻሉ ነው። Confuse and diffuse the News በሚል መርሆ ስንቱን እሳት እያስበሉት ይገኛሉ። ለዚህ ዋንኛ ማሳያው የራሽያና የዪክሬን ጦርነት ነው። ራሽያን ለማዳከም ዪክሬናዊያንን መገበር። ይቺ ናት ፓለቲካ!
    የኢትዮጵያ መሪዎች በጉልበትም ሆነ በስመ መርጫ የስልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ ቃላቸው ወለላ ነው። “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ያሉን 17 ዓመት ሙሉ አንድ ትውልድ መንጥረው አልፈዋል። ከዚያም እነርሱን ተክተው የከተማ አለቆች የሆኑት ሻብያና ወያኔ ሥራና ተግባራቸው ድርቡሻዊ ሆኖ እንሆ የደርግን ዘመን የሚያስናፍቅ ጊዜ ላይ ደርሰናል። በዚህ ሁሉ መካከል ወያኔ ስልጣኑ ከእጅ አፈተለከና ከዚያው ከወያኔ የክፋት ኮሮጆ አፍትልኮ የወጣው የዶ/ር አብይ መንግስት እየቆየ ወያኒያዊ ክፋቱ በአደባባይ በመታየት ላይ ይገኛል። ዜጎች ይታፈናሉ፤ ይገደላሉ፤ በዘርና በጎሳ በተሰመረ አሰራር አንድ ሌላውን ያራውጣል፤ ያስርባል፤ ይዘርፋል፤ ያባራል፤ ይገላል። ችግሩ የሁላችንም እንደመሆኑ መጠን መፍትሄውም የሚመነጨው ከእኛው ከራሳችን ነው። ሰውን በሰውነቱ የማይፈርጅ ኋላ ቀር የሆነ የጎሳ፤ የሃይማኖትና የክልል ፓለቲካ የሰው ልጅን አውሬ ያደርጋል እንጂ እይታውን ሃገር አቀፋዊ ወይም አለምን እንዲመለከት አይረዳውም። ከለለ ማለት ለእኔ ብቻ አለ ማለት ነው። ቋንቋ መግባቢያ ሆኖ እያለ በጥላቻ ተሞልቶ ሃገርን ለማፍረስ ከነጭና ከአረብ ሴራ ጋር ማበር የራስን ቤት እሳት ለኩሶ ድረሱልኝ እንደማለት ይቆጠራል። ቁጥራቸው ሰማይ ጠቀስ የሆነው የእድሜ ልክ የኦሮሞ ፓለቲከኞች ለኦሮሞ ህዝብ ያስገኙለት አንድም ጭብጥ ነገር የለም። ልክ ወያኔ በትግራይ ህዝብ ስም ቁማር እንደሚጫወተው ሁሉ እነርሱም በኦሮሞ ህዝብ ስም ይነግዳሉ። ትላንት የወያኔ ተለጣፊ አሁን ደግሞ የብልጽግና (የድህነት) ፓርቲ እንደ ፈለገ የሚዘውረው የአማራን ህዝብ እንወክላለን የሚለው ወገን ደግሞ የራሱን ህዝብ እያቆሰለና እያሰረ አልፎ ተርፎም እየገደለ ተነሱ ወያኔ ሊወራችሁ ነው ይላል። ጊዜና ወቅትን ያልጠበቀ ዝናብ ለገበሬ እንደማይጠቅም ሁሉ የአሁኑ የአማራ ባለስልጣኖች አፈናና ግድያ የህዝቡን መከራ ያባብሳል እንጂ የምፍትሄው አካል አይሆንም። እንዲህ ባለ ሂሳብ ተካረው አይደል እንዴ ባለፈውስ በጥይት የተጠዛጠዙት። አታድርስ ነው።
    ከነብይት ብርቱካን እስከ ሼህ ጂብርል ተነበዩለት የተባለው ብሎም ጭፍን የፕሮቴስታንት አማኞች ያሞካሹት የዶ/ር አብይ መንግስት ሥራው ሁሉ የሳጥናኤል እየሆነ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነው። ነብይት ብርቱካን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራንፕንም ታሸንፋለህ በማለት ጸሎት አርጋ ነበር ያ ግን አልሆነም። ሲጀመር ፓለቲካና ሃይማኖት አብረው አይሄድም። የወደፊቱንም የሚያውቅ የለም። ዝም ብሎ መዳከር ነው። ከዛሬ ዘመን ነብይ/ነብያት ነን ባዮች የሃገራችን ጠንቋዪችና ቃልቻዎች ይሻላሉ። ጠነቆለ አሳየ አመላከተ ማለት ስለሆነ የቡና ሲኒም ቢሆን አሳይተው የቅርቡን ኗሪ ሩቅ መንገድ ልትሄድ ነው ሲሉት ተስፋው ለምልሞ ለቀናት ደስ ብሎት ነገርየው ሳይሆን ሲቀር ይረሳዋልና!
    ምድሪቱ ሰላም እንድታገኝ ምን ብናረግ ይሻላል? በቅድሚያ ወያኔ መጥፋት አለበት። ወያኔ የክፋት ሁሉ ኮሮጆ ነው። በኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ውስጥ እንደ ወያኔ ያለ ዘረኛና ግፈኛ ተፈጥሮ አያውቅም። ሰውን ጉድጓድ ቆፍረው( ወይም ሟችን አስቆፍረው) ከእነነፍሱ የሚቀብሩ ጉዶች ናቸው። በትግራይ ምድር ወያኔ ያደረሰው ግፍ ሰው በዘር ስለሰከረና ስለሚፈራም አይነገርም እንጂ የጉድ ነው። ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች ደም አፍሳሽ ድርጅቶች ሁሉ ዋልታና ማገር ነው። ወያኔ ቢጠፋ ሌሎችም ይከስማሉ። የትግራይ ህዝብም የራሱን ውሳኔ አፈሙዝ ሳይደገንበት መምረጥ ይችላል። ሁለተኛ – የዶ/ር አብይ መንግስት በጊዜ የሰውን ሰቆቃ ሰምቶ ማስተካከል ካልቻለ አወዳደቁ የሮም ነው የሚሆነው። ውድቀቱን የሮም የሚያደርገው የመንግስቱ ግዝፈትና ጥንካሬ አይደለም። በምድሪቱ ላይ የሚከተለው መከራ ግን በወያኔ ጊዜ ሰዎች ደርግን እንደናፈቁ ሁሉ ወያኔን የሚያስናፍቅ ጊዜ ሊያስመኝ ይችላል። ሰው በማፈን፤ በማሰር፤ በመግደል በስልጣን ላይ መቆየት ቢቻልም ፍጻሜው የፍርስራሽ ክምር ነው። ልብ ላለው ያለፈው ታሪካችንም የሚያስተምረን ይህኑ ነው። እንደ ዝንብ የ 24 ሰአት እድሜ ላለው የፓለቲካ ስልጣን እንዴት ባለ ሂሳብ ነው ወገናችን የምንገለውና የምንገርፈው? አይበቃም ለቅሶና ዋይታ። አይበቃም ሰውን እያሰሩ ቤተሰብን ማሰቃየት? አይበቃም አንዴ የሾሙትንና የሸለሙትን በአፈና ቡድን ማፈንና ማዋረድ? እንዲህ ያለው የመንግስት ሥርዓት የማፊያ አሰራር እንጂ ህግና ደንብ ባለበት ምድር የሚተገበር ተግባር አይደለም። በሸህ ጅብሪል ግጥም ልሰናበታችሁ።
    በሮቼን አምጡልኝ አርጄ ልብላቸው
    ደግሞ እንደ መሬቱ ሳይካፈሏቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share