ሕግ በማስከበር ሰበብ ህዝብን ማሸበር
በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል!!!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአምባገነኖች አገዛዝ ተላቅቃ ወደ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለመሸጋገር በርካታ ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡ የአያሌ ኢትዮጵያውያንን የማይተካ የሕይወት መስዋዕትነት የጠየቁት እነዚህ ሙከራዎች ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ያመጡ ናቸው ባይባልም ብዙ የተማርንባቸው መሆኑ ግን የአደባባይ እውነት ነው፡፡
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ ያስወገደው የሕወሓት አገዛዝ ሥርዓት በብልፅግና ተሸፍኖ ለዳግማዊ ጥፋት ተመልሶ እንዲመጣ ለአፍታም ቢሆን ልንፈቅድለት አይገባም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን በእልህ የታገለውና አሁንም እየታገለ ያለው በጉልበት የተጣለበትን አፈና በመፀየፉ እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ከህወሓት ውድቀት ያልተማረው የሕወሓት የመንፈስ ወራሽ የሆነው የብልፅግና ሥርዓት በአሁኑ ወቅት በአማራ ህዝብ እና የአማራ ተቆርቋሪ በሆኑ የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆች ላይ እየፈፀመ ያለውን አፈና ድርጅታችን መኢአድ በፅኑ ያወግዛል፡፡
የአማራ ህዝብ ከምድረ ገፅ እንዲጠፋ በህወሓት ተፈርዶበት ጦርነት በተከፈተበት ወቅት ሕዝባችንን ለሚገድሉ፣ ሀገራችንን ለሚያፈርሱ ጠላቶች ዕድል አንሰጥም ብለው፣ ከገዳዮች ፊት ቆመው የሕዝብን እልቂትና የሀገርን የመፍረስ አደጋ የተከላከሉ በዚያ ክፉ ጊዜ ለህዝብ ብለው ደረታቸውን ለጥይት አረር በመስጠት ሲታገሉ የነበሩ የጦር መሪዎችና ወንድሞቻችንን እንዲያፍኑ ልንፈቅድላቸው አይገባም፡፡
ችግሮች እንኳን ቢያጋጥሙ በሰለጠነ አካሄድ ተነጋግሮ ለችግሮቹ መፍትሔ መፈለግ እንጂ በዛ የጭንቅ ወቅት ያለምንም ማመንታት ኃላፊነትን ወስደው ሀገርን ለታደጉ የጦር መሪዎች ክብር መስጠት ሀገራዊ ግዴታ ሲሆን ማዋከብ ግን የነውር ጥግ ነው፡፡
ድርጅታችን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በሕዝባችን ላይ የሚፈፀመውን አፈና እና ወከባ አጥብቀን እያወገዝን፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድሞችና እህቶቻችን ላይ የሚፈፀም ጥቃት ቢኖር በእኛ ላይ እንደተፈፀመ የምንቆጥረውና የምናወግዘው ነው፡፡
በመሆኑም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሚከተሉትን አስቸኳይ ጥሪዎች ያቀርባል፡-
- በፋኖ ላይ የሚደረገው የአፈናና የእስር ዘመቻ ለአማራ ህዝብ የታሪክና የማህበራዊ ክብር ጉዳይ መሆኑን በመረዳት፤ የአማራ ህዝብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥቃቱን መመከትና ማክሸፍ ይኖርበታል፡፡
- የአማራ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ምሁራን ይሄን አስከፊ ጊዜ በየአካባቢያችሁ በመነጋገርና በመመካከር በጥበብና በብልሀት እንድታልፉት ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
- በሕግ ማስከበር ሰበብ የአማራ ክልል ከተሞችን የጦር አውድማ ማድረግ እና ንፁሀንን መግደል በአስቸኳይ ቆሞ ችግሩ በውይይትና በድድር እንዲፈታ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
- ለክልሉ መንግስት
- በዚያ የጭንቅ ጊዜ ለታደጋችሁ የአማራ ወጣት፣ ፋኖና ለታላቁ የአማራ ህዝብ ጥሩ ነገር ብትሰሩ ታተርፉበታላችሁ እንጂ አትጎዱም እና የጀመራችሁት የአፈናና የእስር ዘመቻ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል እና ቆም ብላችሁ እንድታጤኑት እንመክራለን፡፡
- በሲዳማና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ንፁሀን ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግስቱ በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆኑ ሌሎች አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በቸልተኝነት ማየቱን አቁሞ አፋጣኝ ርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ደህንነት እንዲያረጋግጥ ስንል አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
- በአዲስ አበባ ከተማ በጋዜጠኞች፣ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የሚፈፀመውን መንግስታዊ አፈናና እስር በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
- በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ት/ቤቶች የኦሮሚያን ባንዲራ በመስቀልና የኦሮሚያን መዝሙር ዘምሩ በሚል የኦሮሚያ ብልፅግና ጉዳይ አስፈፃሚ በሆኑ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ኃላፊዎች እየተሰራ ያለው አደገኛ እና አመፅ ቀስቃሽ ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡
- በአሁን ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን እየተጎሰመ ያለው የጦርነት ቅስቀሳ ሀገሪቱን ወደ ዳግም እልቂት የሚወስዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ራሱን ከዳግማዊ ጥቃት እንዲከላከልና ሀገሪቱንም ከመፍረስ እንዲታደግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ