አዎ! የዛሬው ወለጋ ኦሮሞ ኢትዮጵያን ከመውረሩ በፊት የጥንት ስሙ ቢዛሞ ይባል ነበር! – አቻምየለህ ታምሩ

ከሰሞኑ በሰጠሁት አንድ ቃለ ምልልስ ላይ «ወለጋ ከኦሮሞ ወረራ በፊት የጥንት ስሙ ቢዛሞ ይባል ነበር» በማለት የተናገርሁትን አንድ ወዳጄ «ይህ የደብተራ ታሪክ ነው፤ ማስረጃ ልታቀርብ አትችልም» የሚል ትችት ሰንዝሮ ነበር። «ማስረጃ ልታቀርብ አትችልም» ብሎ ማስረጃ እንደመዝ የገፋፋኝን ወዳጄን ስለትችቱ እያመሰገንሁ ማስረጃዬን እነሆ ብያለሁ።
ወለጋ ከኦሮሞ ወረራ በፊት የጥንት ስሙ ቢዛሞ ይባል እንደነበር የጻፉት ትምህርት የላቸው ተብለው ባላዋቂዎች የሚሰደቡት «ደብተራ» የታሪክ ጸሐፊዎች ሳይሆኑ የሎንዶን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ምሩቅ ኦሮሞው አቶ ይልማ ደሬሳ ናቸው። አቶ ይልማ ደሬሳ ከጥሊያን ወረራ በፊት ከሎንዶን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በዲግሪ የተመረቁ ሲሆኑ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለብዙ ዓመታት የገንዘብ ሚኒስትር ነበሩ።
አቶ ይልማ የወለጋው ባላባት የደጃዝማች በከሬ ጎዳና ኦሞ ፋሮ ሲኒካ ኘአ ዶሮ የልጅ ልጅ ናቸው። የአቶ ይልማ አያት ደጃዝማች አመንቴ በከሬ ይባላሉ። የደጃዝማች አመንቴ በከሬ ልጅ ደግሞ የአቶ ይልማ ደሬሳ አባት ብላታ ደሬሳ አመንቴ ናቸው።
አቶ ይልማ ደሬሳ በ1959 ዓ.ም. «የኢትዮጵያ ታሪክ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን» በሚል ባሳተሙት የታሪክ ጥናታቸው የዛሬው ወለጋ በ17ኛው መቶ ክፍለ በኦሮሞ ተወርቶ ስሙ ወደ ወለጋ ከመቀየሩ በፊት ጥንተ ስሙ ቢዛሞ ይባል ነበር። በግዛቱም አማራ፣ ጋፋትና እናርያ የሚባሉ ነገዶች ይኖሩበት ነበር። የቢዛሞ ግዛት ከዐፄ ዐምደ ጽዮን ጀምሮ የኢትዮጵያ አካል እንደነበር በዐፄ ዐምደ ጽዮን ታሪከ ነገሥትተ መዝግቦ ይገኛል።
ኦሮሞ በተለይም የሜጫ ኦሮሞ አካባቢውን ወርሮ ከያዘው በኋላ ግን ነባር ነገዶች ጠፍተውና ማንነታቸው በኦሮሞ ተቀይሮ ታሪካዊው የቢዛሞ ግዛት የስም ለውጥ አድርጎ ወለጋ ለመሆን በቅቷል። ( ምንጭ፡ ይልማ ደሬሳ (1959)፥ የኢትዮጵያ ታሪክ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን፥ገጽ 17)
በአቶ ይልማ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ሙሉ ታሪክ እነሆ!
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ ችግር የመሪነት ደረጃ ላይ የደረሰ መሪ አለመኖሩ ነው

3 Comments

  1. አቻምየለህ ደጋግሞ የሚጽፈውን ስመለከት ነበር። ሥራ ፈት ይመስላል። ነጋ ጠባ ኦሮሞ እንዲህ አለ፣ ሆነ፣ ሊሆን ነው ይላል። ያልዋለበትን ጦር ሜዳ መዳኘት ይቃጣዋል፤ ባልቻ አባ ነፍሶን አሳንሶ አማራ ወገኑን ማግነን ይሻል፤ ካራማራ ላይ ጀግና ማነው ቢባል በዚያ የነበሩ እና አገር ያወቃቸው ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ እና አሊ በርኪ ናቸው። አቻምየለህ ግ ን ጀግ ና ከእርሱና ከቢጤዎቹ ሌላ ያልሰማቸው ወገኑን ይጠራልናል። የሚያሳዝነው፣ ጀግ ኖቻችን አንዳቸውም ዘራቸውን ያልጠሩ ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ያኮራቸው ነበሩ፣ ናቸው። አቻምየለህ የባለውለታውን የህወሓትን ሥራ እየሠራለት ነው!

    ደጋግሞ የሚያቀርበው መረጃ አባ ባህርይ የተባሉ ደብተራ የጻፉትን ነው። ደብተራው በወቅቱ ስላዩት ነገር ጽፈዋል ብንልም፣ የጻፉት በገባቸው እና ዓለምን በሚያዩበት በኦርቶዶክስ አማራ መነጽር ነው። ይህን ስል ወቀሳ አይደለም፤ ኦሮሞም ትግሬም አሜሪካኑም የሚያዩት እንደ አስተዳደጋቸው ነውና! ሌላ ማመሳከሪያ አለ? ሲባል፤ ሌላ ፈረንጅ መንገደኛ፣ ቋንቋና ባህሉን የማያውቅ ከጻፈው ውስጥ የሚፈልጋትን መራርጦ ያቀርብልናል። ከላይ ይልማ ዴሬሳ የጻፉትን መርጦ ሊለው ላሰበው የሚደግፈውን ብቻ ቆርጦ ነው። ይልማ ዴሬሳ ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ መማራቸውን ያነሳው ለምንድነው? “ደብተራው” ኋላ ቀር ናቸው ካላችሁ፣ ዘመናዊው ኦሮሞ ራሳቸውን ኮንነው እኔን ደግፈው ደብተራውን ደግፈው ጽፈዋል ለማለት ነው። ይልማ ዴሬሳ የጻፉት ግን ሲነበብ አቻምየለህ ወይም ቢጤው ደብተራ ከተናገሩት እና ካሰበው ጋር ጨርሶ አይስማማም። “ታሪክ ተማራማሪ” ብሎ ራሱን በሰየመ ግለሰብ ይህን አኳኋን ማየት አሳፋሪና አቅሙ ያነሰ የመንደር ወሬኛ ያደርገዋል።

    አቻምየለህ በዚህ ዘመን ያለ አቅማቸው ለመሆን ከሚንጠራሩ መሓል ይመደባል። ህወሓት ወደ ኖርዌይ ስኮላርሺፕ ሰጥቶት ስለ ትግራይ ማይክሮክሬዲት ጥናት ቢጤ እንዲያካሄድ አሰማርቶት ረድቶት ነበር። ያኔ አማራነቱን በጨርቅ ቋጥሮ ደብቆ ነበር። ህወሓት ሸሽቶ ጫካ ሲገባ፣ የቋጠራትን አውጥቶ አማራ፣ አማራ ኦሮሞ ኦሮሞ ማለት ጀመረ። ይኸ ነው የአማራ ምሑር ነኝ ባይ! አማራን አላወቀውም ወይም ንቆታል። ፊት ለፊት ህወሓትን የተጋተሩ እነ ፕሮፌሰር አስራትን ምን ያርጋቸው? የአቻምየለህ ሾልኮ “ታሪክ ተማራማሪ” መሆን አሳፋሪ ነው። ተመራማሪ አንዲት ብጣሽ የደብተራ ያልተመሳከረች ማስታወሻ አንጠልጥሎ መሮጥ አይደለም። ጥላቻን በምርምር ስም መዘርገፍ አይደለም። ተመራማሪ ምግባሩ ጭለማን በመግፈፍ ስላለንበት ዓለም አዲስ እውቀት መፈንጠቅ ነው። አቻምየለህ የተሠማራው ጭለማን ለማብዛት ነው። ጋላ ጋላ ኦሮሙማ ወለጋ ማለት ለርሱና ለቢጤዎቹ እንደ ጀብድ ነው።

    አቻምየለህ ለማስትሬቱ የጻፈውን ሰነድ ስመለከት ነበር። በእንግሊዝኛ አጻጻፉን። እንዲህና እንዲያ ለማለት ቦታው አይደለም። አንድ ነገር ግ ን ግልጽ ነው። አቻምየለህ የ “ተማራማሪነትን መስፈርት የሚያውቅ አይመስልም፤ “ተመራማሪ” ሳይሆን “ተጠራጣሪ” “አጭበርባሪ” ነው። ይልቅ ምክር ልስጥህ፦ እንደ ተማራማሪ ሳይሆን እንደ አስተያየት ሰጭ ራስክን አቅርብ። “አክራሪ” ትባል ይሆናል እንጂ “ተመራማሪ” ይበዛብሃል።

  2. እንግዲህ ቅስሙን ሰበርኩ ብለህ የተተናኮልከው የኔ ከምትለው ማስረጃ መዞልሃል የደናቁርት እንካ ስላንትያ ከምትዘግብ ትምህርቱን ወስደህ ተጠቀምበት

    • ቢረጋ፣ አልፎ አልፎ ምላሽ መስጠት ሞክር እንጂ በደፈናው ቅስም መስበር መተናኮል ደናቁርት ማለት ምላሽ ሊሆን አይችልም። አለም ከጻፈችው ወይም ከጻፈው ከየቱ ጋር አልተስማማህም? አለም ስለ አማራ (ፕሮ አሥራት) ጥሩ አስተያይት መሰለኝ፤ “የኔ ከምትለው” ምን ማለትህ ነው? ከዚህ ቀደም ባለው ጽሑፉ ላይ አቶ አቻም ኦሮሞ ወራር ነው ብሎ ደጋግሞ ጠቅሷል። ይኸ አባባሉ ታዲያ አያጋጭም ትላለህ?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share