April 26, 2022
255 mins read

ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ባላቸውና በአረመኔዎች የሚመራ ምስኪን ህዝብና አገር! – ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

I am …. a mortal enemy to arbitrary government and unlimited power. I am naturally very jealous for the rights and liberties of my country; and the least appearance of an encroachment on those invaluable privileges is apt to make my blood boil exceedingly. I have likewise a natural inclination to observe and reprove the faults of others., at which I have an excellent faculty” (Benjamin Franklin)

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

  ሚያዚያ  26 2022

a4563d48188bbbe950f69cc7f8cb4b94 1መግቢያ

የዛሬ አራት ዓመት ገደማ የወያኔ አገዛዝ ተወግዶ አዲስ አመራር ስልጣንን ሲይዝ ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። አንዳንዱም በደስታ ብዛት ያላለቀስ አልነበረም። ምክንያቱም ወያኔ ስልጣን ላይ ሆኖ 27 ዓመታት ያህል አገራችንና ህዝባችንን ረግጦ ሲገዛ የአገራችንን ህልውና ለማዳከምና፣ ከረጅም ጊዜ አንፃር ደግሞ ልትበታተን የምትችልበትን ሁኔታ ያልፈነቀለው ዲንጋይና ያላመቻቸው ሁኔታ አልነበረም። ጎሳን ከጎሳና፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር በማጋጨት ህዝባዊ ቅራኔ እንዲፈጠር አድርጓል። ለፈጠራና ለስራ የሚያመች ባህል ከማዳበር ይልቅ በሃይማኖት ስም የሚነግዱ እንደ አሸን እንዲፈልቁ በማድረግና የበልግና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት የስነ-ልቦና ውድቀትን አስከትሏል። በወያኔ ዘመን መጻህፍት-ቤቶችንና የጥበብ ማዕከሎችን መክፈት ሳይሆን እንደ ባህል የተወሰደው፣ ቡናቤቶችንና የምሽትቤቶችን፣ እንዲሁም የሚያሸበራርቁ ሆቴል ቤቶችንና ሞልስ በመባል የሚታወቅ ከ1990ዎቹ ዓ.. ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፉና ከአሜሪካን የተኮረጀ ትላልቅ የገበያ አዳራሾችን መክፈት ነው። እነዚህ ሁሉ በመደራረብ በተለይም የወጣቱን ስነ-ልቦና ማዳከማቸው ብቻ ሳይሆን ለዕውቀት ያለው ፍላጎት ደብዛው እንዲጠፋ  ተደርጓል። መጽሀፍ ክማንበብና አዕምሮውን እንዲያድስ ከማድረግ ይልቅ በየጨአት ቤቱና በየሻይቤቱ እየዋለ ትክክለኛ ዕውቀት ሊቀስምበት የሚችለውን አፍላ ዕድሜውን እንዲያጠፋ ተገዷል።

ሁላችንም እንደምናውቀው ወያኔ ለከፋፍለህ ግዛው እንዲያመቸው በአሜሪካንና በእንግሊዝ በመመከርና በመደገፍ የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚባለውን አገራችንን የሚያዳክምና በህዝባችን ዘንድ መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግና በጋራ ተነሳስቶ አገር እንዲገነባ የሚያግድ ፖሊሲ የሚሉት ነገር ተግባራዊ አደረገ። ይህ ዐይነቱ ፌዴራሊዝም ደግሞ ከዕውነተኛው የሪፑብሊክ አስተሳሰብና ከግለሰብአዊ ነፃነት ጋር የሚቃረን ብቻ ሳይሆን፣ ተሰባስቦና ተስማምቶ ይኖር የነበረውን ህዝብ እርስ በርሱ እንዳይተማመን መንገዱን ያመቻቸ ነው። በተጨማሪም ለካፒታልና ለስራ-ጉልበት እንቅስቃሴ መንገዱን የዘጋና የጎጠኝነት ስሜትን ያዳበረ ለመሆን የበቃ ነው። ይህን ዐይነቱን የጎሳ ፖለቲካም ተግባራዊ ለማድረግ የፈለገው  ከረጅም ጊዜ አንፃር ሲታይ ታላቋን ትግራይ ለመገንባትና፣ ሌሎች ክልሎችን ደግሞ የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት ውጤቶች አቅራቢ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። ይህም ማለት፣ ትግራይ ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ሲገነቡና አዳዲስ ከተማዎች ሲመሰረቱ ሌላው የኢትዮጵያ ግዛት ኋላ-ቀር መሆን አለበት ከሚለው ስሌት የተነሳ ነው። የአውሮፓ የቅኝ-ገዢዎች የአፍሪካን አገሮች በማስገደድ በፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ በማድረግ ዕድገታቸውንም እንዳዛቡባቸው ሁሉ ወያኔም ይህንን ዘዴ በመከተል ከትግሬ በስተቀር ሌሎች ክልሎች ጥሬ-ሀብትን በማውጣትና ፍራፍሬዎችን በመትከል ላይ ብቻ ማትኮር አለባቸው። በዚህ ዐይነቱ የሴንተር-ፔሪፈሪ ግኑኝነት(Center-Periphery Relations) ሌላውን የኢትዮጵያ ግዛት መበዝበዝና ማዳከም ብቻ ሳይሆን የበላይነቱንም ለረጅም ጊዜ ይቆያል የሚል ዕምነት ነበረው።  ለዚህ ደግሞ በየአካባቢው ራሳቸውን ሊያደልቡ የሚችሉና የዎር-ሎርድ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ይሁንና ደግሞ ለወያኔ አገልጋይ የሚሆኑ ኃይሎች መመልመል ነበረባቸው።

ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ ተግባራዊ ያደረገው ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፖለቲካ በመሰረቱ የታሪክን ሂደትና የአገራችንን ኢቮሉሺነራዊ ዕድገት የቀለበሰ ነው ማለት ይቻላል። አፄ ምኒልክም ሆነ የኋላ ኋላ አፄ ኃይለስላሴ ተግባራዊ ያደረጉትን የዘመናዊነት ፖሊሲና፣ ህዝባችንን ያሰባሰውንና፣ እየተሰባሰበ በመጣ ቁጥር ውስጣዊ ኃይል ያገኘበትንና፣ በብዙ መልኮች የሚገለጹ ለዕድገትና ለአንድነት መሰረት የሚሆኑ የባህል አብዮቶችን ለመቀልበስ የሚያስችል አካሄድ ነበር። እስካሁን ድረስ በታሪክ እንደተረጋገጠው በነፃነት ስም በውጭ ኃይሎች በመተጋዝ አንድ ወጥ የሆነን አገዛዝና፣ ከሞላ ጎደል ተስማምቶ የሚኖርን ህዝብ በዚህ መልክ የከፋፈለና አገሩን ያዳከመ የሌላ አገር አገዛዝ በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥም አልታየም። ይሁንና ወያኔና ሌሎች የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ያልተረዱት ነገር እንደዚህ በጎሳዎች የተከፋፈለች አገር በቀላሉ በውጭ ኃይሎች ልትጠቃ እንደምትችልና፣ ከውስጥ ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ(Home Market) ለመገንባት እንደማትችል ነው። ሌላው ግንዛቤ ውስጥ መግባት የሚገባውና እነ መለስ ዜናዊ በደንብ ያላጤኑት ነገር እነሱ ያመረቱትን የኢንዱስትሪ ምርት ለመሸጥ በሌሎች ክልሎችም ውስጥ ዕድገት መኖር አለበት፤ በማሺን ላይ በተመሰረተ ኢንዱስትሪ ብቻ ነው ሰራተኛውና የተቀረው በአገልግሎት መስክ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ህዝብ ቀስ በቀስ ይሁንና ደግሞ አስተማማኝ በሆነ መንገድ የመግዛት ኃይሉ(Buying Power) ሊያድግ የሚችለው:: የእነ መለሰ ዜናዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ጠቅላላው አስተሳሰባቸው የኢኮኖሚ ዕድገትን ህግና ሎጂክን የሚጥስ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ግለሰብም የተሟላ ነፃነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው። በዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ አስተሳሰብም የትግሬ ብሄረሰብም የሚጎዳ ነው።

በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ እንደታየው በፕላንቴሽን ኢኮኖሚና በጥሬ-ህብት ማውጣት ላይ ብቻ የሚሰማሩና ዋና የገቢ ምንጫቸውንም በእነዚህ መስኮች ላይ ያደረጉ አገሮች በምንም ዐይነት ህዝቦቻቸውን ከድህነትና ከረሃብ ማላቃቅ እንደማይችሉ ነው። አንድ አገር በተሟላ መልክ ልታድግና በቁጥር እየጨመረ የሚህድን ህዝብ ልትመግብና በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዲኖር ለማድረግ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማካሄድ አለባት። በማሽን ኢንዱስትሪ  የተደገፉ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉና ሲዳብሩ ብቻ ነው በቂ የስራ መስክ ለመክፈት የሚቻለው። በእነዚህ መስኮች በመታገዝ ብቻ ነው ህዝባዊ ሀብት መፍጠር የሚቻለውና ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድ ህዝብ አስተሳሰብ መዳበር የሚችለውና የመፍጠር ኃይሉም የሚያድገው ሳይንስንና ቴኮኖሎጂን መሰረት ያደረገ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሲስፋፋ ብቻ ነው። በዚህም አማካይነት ብቻ ነው ጠንካራና ተወዳዳሪ የህብረተሰብ ክፍል ማፍራት የሚቻለው። የወያኔዎች የኢኮኖሚ ፖሊሲና ጠቅላላው አስተሳሰባቸው በሙሉ ይህንን ዐይነቱን ተራ ኮመን ሴንስ የኢኮኖሚ ዕድገት ሎጂክን የሚፃረር ነው።

ህወሃት 27 ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ ላይ በተጠቀሰውና ተግባራዊ ባደረገው የነፃ ገበያ ብለው በሚጠሩት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ከፍተኛ የባህል ቀውስ እንዲከሰት ለማድረግ በቅቷል። ተግባራዊ ባደረገው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት እንደተነገረን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ያደገ ሳይሆን የብዝበዛ ስርዓትና ድህነት ነው የተስፋፉት። የውጭው ገበያ ክፍት በመሆኑም ምክንያት የተነሳ የውጭው ንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ መዛባቱ ብቻ ሳይሆን፣ አገራችንንም በቀላሉ መልሳ ልትከፍለው የማትችለው ዕዳ ተሸካሚ ለመሆን  በቅታለች። አዲስ በተፈጠረውም የፍጆታ አጠቃቀምም የተነሳና ገበያውም ክፍት ስለሆነ ካለምንም ቁጥጥር ከውጭ የሚመጡ ቆሻሻ መኪናዎችና ልዩ ልዩ የአረጁ መርዛማነት ያላቸው የኢሌክትሮኒክስ አካሎች በየቦታው ሜዳ ላይ በመጣላቸው አካባቢዎችን መመረዝና ወደ ውስጥ ደግሞ በመሬት ውስጥ ያለውን ውሃ ማበላሸት ጀመሩ። በወያኔ አገዛዝ ዘመን ነው ቁጥራቸው የማይታወቁ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች እንደ አሸን መፍለቅ የጀመሩትና፣ በኑሮ ውድነት የሚሰቃየው ወገናችን ከቆሻሻ መጣያ ቦታዎች ምግብ እየፈለገ መብላት የተገደደው። በወያኔ አገዛዝ ዘመን ነው በየቦታው ወጣት ሴቶች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ አካላቸውን እንዲሸጡ የተገደዱት። በወያኔ አገዛዝ ዘመን ነው ግብረ-ሰዶማዊነት የተስፋፋውና የራሳቸው መደነሻ ቦታ እንዲኖራቸው የተደረገው። በዚህ መልክ አዲስ የሆነና መንፈሱ ደካማ የሆነ ወደ ሴተኛ አዳሪነት የተለወጠ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት በመፈጠሩ ለታዳጊው ትውልድ መጥፎ ምሳሌ ሊሆን በቅቷል። መለሰ ዜናዊና ግብረ-አበሮቹ ናቸው የኢትዮጵያን ወጣት ሴቶች ለቤት ስራ በሚል ወደ አረብ አገሮች እንዲሄዱ የተስማሙት። በስምምነቱ መሰረት በየዓመቱ ወደ አርባ ሺህ የሚቆጠሩ የቤት ሰራተኞች ለመላክ ነበር። ይህ ዐይነቱ ዘመናዊ የባርያ ንግድ ብዙ ወጣት ሴቶችን ከገጠር ውስጥ እንዲመለመሉ በማድረግና በመገፋፋት፣ በማያውቁት አገርና በማይችሉት ቋንቋ ለጥቃት እንዲዳረጉ አብቅቷቸዋል። እናቴንና አባቴን እረዳለሁ በማለት ተጫውተው ሳይጠግቡና የመማር ዕድል ሳያገኙ በዚህ ዐይነቱ የባርያ ስራ ህይወታቸው እንዳለ እንዲጨልም ተደርጓል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሴት ልጆች ህይወታቸው እንዲያልፍ ተደርጓል። አገራችንም የውርደት ውርደትን ተከናንባለች። መለስና ግብረ-አበሮቹ ባላቸው የጥላቻ መንፈስ በመታወር የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነት በዚህ መልክ አዋርደዋል። እኛ ኢትዮጵያኖችም በዓለም ህዝብ ዘንድ እንድንናቅ ተደርገናል።

ወያኔ ይህንን ሁሉ እርኩስ ተግባር ከፈጸመና ከውስጥ ደግሞ የህዝባችንን ስልነ-ልቦና በከፍተኛ ደረጃ ከአዳከመ በኋላ በዚያ የጥፋት ሂደቱ ሊቀጥል አልቻለም። ማንኛውም ነገር የራሱ የሆነ ገደብ አለው። አንድ አገዛዝ በተለመደው የአገዛዝ ስልቱ ሊቀጥል አይችልም። የሚራብ ህዝብ፣ ዲሞክራሲ የጠማው፣ የስራ-መስክ የሚፈልግ ወጣትና ሌሎችም አዳዲስና ብሩህ ዕይታን የሚፈልጉ ሲበዛባቸው ማመፅ ይጀምራሉ። አንድ አገዛዝ ከጊዜው ሁኔታ ጋር የማይሄድና በኋላ-ቀር አስተሳሰብ እገዛለሁ ብሎ የሚንገዳገድ ከሆነና አመጽን በአመጽ እገታዋለሁ የሚል ከሆነ የግዴታ መውደቁ የማይቀር ጉዳይ ነው። በብዙ አገሮችም እየተደጋገመ የታየ ሃቅ ነው። የመጨረሻ መጨረሻም ራሱን የማይጠይቅና ለመሻሻልም የማይችል ኃይል እንደ ቆሽሻ ዕቃ የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቦታ መጣሉ የማይቀር የተፈጥሮ ህግ የሚመስል ጉዳይ ነው። የፈለገውን ያህል ቢመጻደቅና ኃይል አለኝ ብሎም ህዝብን ቢያስፈራራም ራሱ በፈጠረው ውጥንቅጥ ነገሮች መጠራረጉ የማይቀር የታሪክ ግዴታ ነው። ዛሬ እንደምናየው የውርደት ውርደት በመከናነብ ፋሺስታዊ በሆነ መልክ ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸመና፣ እወክለዋለሁ የሚለውን ጎሳም የመቶና የሁለት መቶ ዓመት ዕድሜ የሚሆን የቤት ስራ ሰጥትታል። እንደ ሰው እንዳያስብና ከሌላው ጋር ሃሳብ ለሃሳብ እየተለዋወጠና እየተጋገዘ እንዳይኖር አድርጎታል። መንፈሱን እንዳለ በድን አድርጎታል። ማንኛውንም የሰው ልጅ ሊኖረው የሚችለውን ሰብአዊ ባህርዮችና የመፍጠር ችሎታ እንዳለ ተሟጦ ከጭንቅላቱ እንዲወገድ ለማድረግ በቅቷል። አብዛኛው ህዝባችን ትግሬ በሚባለው እንደኛው ባለው ወገናችን ላይ አመኔታ እንዳይኖርበት ለማድረግ አብቅቶታል። አመኔታ የማይጣልበት የህብረተሰብ አካል ወይም ጎሳ ደግሞ በአገር ጉዳይ ውስጥ ምንም ዐይነት ተሳትፎ ሊኖረው አይችልም። ከማህበራዊ ኑሮ ጎሰኝነትን የሚያስቀድም ከሆነ፣ በሆነው ባልሆነው አሻጥር የሚሰራ ከሆነ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ለፈጠራ ስራና ለምርታማነት ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሁሉም አቅጣጫ የተስተካከለ ዕድገትና ባህላዊ ዕምርታ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው። በዚህ መልክ የትግሬ ብሄረሰብ ተወላጅ አሁን ደግሞ ኦሮሞዎች ከማህበራዊ ስሜት ይልቅ ጎሳዊ ስሜት እንዲያይልባቸውና የኑሮን ትርጉም እንዳይረዱት ለመደረግ በቅተዋል። ፈሪ፣ ጠብ ጫሪ፣ በራሱ የማይተማመንና በሁሉም አቅጣጫ ለማሰብ የማይችል ወጣት ትውልድ እንዲፈጠርና፣ መንፈሱ ሁሉ በጥላቻና ሌላውን በመናቅ እንዲቀረጽ ተደርጓል። በአጭሩ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብን እንዳያዳብር ለዝንተ-ዓለም አዕምሮውን እንዳለ ዘግቶበታል፤ በጨለማ ዓለም እንዲኖር ተፈርዶበታል ማለት ነው።

“በዶ/ር” አቢይ አህመድ የሚመራው “አዲሱ  የለውጥ ኃይል”  እየተባለ የሚጠራው ስልጣንን ሲጨብጥ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ምን ምን ዐይነት እርኩስ ስራዎችን ይሰራ እንደነበር የተገነዘበ መስሎን ነበር። በህዝባችን ላይ የፈጸማቸውን ጉዶች በሙሉና፣ በተለይም ደግሞ አገራችንን ያዳከመውን የጎሳ ፖለቲካ በመቀልበስ ወደ ተሻለና ወደ ስልጣኔ ጎዳና ያመራናል የሚል ዕምነት ነበርን። አለባበሱንና መልኩን ብቻ የተመለከተው ኢትዮጵያዊ በመፈንደቅ አዲስና ብሩህ የሆነ፣ እንዲሁም ደግሞ በአስተሳሰቡ ሊበራል የሆነ መሪ ስልጣንን ተቀዳጀ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። አንዳንዶች እጅግ በሚያሳፍርና በሚያሳዝን መልክ በማልቀስ የአቢይን ጫማ እስከመሳም የደረሱ ነበሩ። ይሁንና ሊበራል መስሎ የታየው፣ አሻግራችኋለሁ ብሎ የማለውና የተገዘተው፣ የኪነት ሰዎችን ሁሉ በመጋበዝ ስለኪነት አስፈላጊነት የተናገረው፣ አዛኝ መስሎ የቀረበውና ፈገግም እያለ የህዝብን ልብ የገዛው አዲሱ መሪያችን ይኸው እንደምናየው ሊበራልና ዲሞክራት ሳይሆን እጅግ አደገኛ እየሆነ የመጣ መሆኑን አስመስክሯል። “ምኑን ታዩታላችሁ ገና ብዙ ሰው ይሞታል” እያለ ርህራሄ የሌለው  መሆኑን አረጋግጧል። አስተሳሰቡና ድርጊቱ ከፋሺስቶች የማያንስ መሆኑን አስመስክሯል። ብሄራዊ ባህርይ የሌለው፣ አብዛኛውን  ህዝባችንን የሚንቅና፣ በተቃራኒው ደግሞ ለትግሬ ብሄረሰብ የሚቆረቆርና ወያኔን ናፋቂ መሆኑ በሚሰራው ስራ አረጋግጧል። ህዝባችንና አገራችን እዚያው በዚያው በጦርነትና በረሃብ፣ እንዲሁም በመፈናቀል ፍዳቸውን እንዲያዩ የሚያደርግ አዲስና ወጣት መሪ ነው ያጋጠመን። ከዚህም በላይ ደግሞ አገራችንን ለአረብ ቱጃሮችና ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በመቸብቸብ ላይ ይገኛል። የነፃነቱንና የብልጽግናውን መንገድ ውስብስብ እያደረገውና፣ ህዝባችንም ለዝንተ-ዓለም በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ሁሉንም ነገር በማመቻቸት ላይ የሚገኝ ነው።  ስርዓት ያለውና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባ፣ እንዲሁም የሊበራልና የመቻቻል ባህል እንዳይዳብር መንገዱን ሁሉ በማበላሸት ላይ የሚገኝ ነው። አዕምሮው በትክክለኛ ዕውቀት፣ በሀቀኝነትና በዲስፕሊን የታነፀ ኤሊት በአጠገቡ ከመሰብስብ ይልቅ አታላዮችንና አድርባዮችን፣ እንዲሁም ቂም- በቀልተኞችን በማስጠጋት የአጭበርባሪነት ባህል እንዲስፋፋ በማድረግ ላይ ነው።  ባይ ባይ ኢትዮጵያ ብለን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ ሊኖርብን ነው ማለት ነው።

ይህንን ኋላ-ቀር አስተሳሰብ፣ ከፍልስፍናና ከሳይንስ ጋር የሚጋጨውን የወያኔንም ሆነ፣ በተለይም ደግሞ የአቢይን አካሄድና ድርጊቱን ጠጋ ብሎ ለመመርመር የግዴታ መሰረታዊ ጉዳዮችን መመልከትና ማብራራት ያስፈልጋል፤ እንዲሁም በጭንቅላት ውስጥ መቋጠር ያስፈልጋል። ባለፉት 30 ዓመታትም ሆነ ቀደም ብለው የተፈጸሙት ፖለቲካዊ ስህተቶችና ወንጀሎች በሙሉ ካለምክንያት የተፈጠሩ ስላልሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን እያነሳን እስካልተወያየን ድረስ የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች በቀላሉ መፍትሄ የሚገኝላቸው አይደሉም። ችግሩም እየተባባሰና፣ ሌላ ኃይልም ስልጣንን ቢይዝ እንኳ ያለው ችግር ጥልቀትን በማግኘት የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ተከታታዩም ትውልድ፣ ምናልባትም ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ የህዝባችን ዕጣ ረሃብ፣ ድህነት፣ ጦርነትና መፈናቀል፣ እንዲሁም አቅጣጫን አጥቶ እዚህና እዚያ መንቀዋለል ይሆናል። ስለሆነም መሬዎቻችንም ሆነ ተማረ የሚባለው ኤሊት የአገራችንን ጥልቀት ያለው ችግር ለምን ለመረዳት አይችሉም? ለምንስ በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር በመመርመር ከተወሳሰበው ችግር ለመውጣት የሚያስችል መፍትሄ አይፈልጉም? ምን የሚያግዳቸውስ ነገር አለ? ለሚሉትና ለሌሎችም ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ እንሞክር። ይህንን ለመረዳት ጭንቅላት ለመዳበር፣ በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ለማንበብ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ለምን ችግሮች ይፈጠራሉ? ምክንያቶቻቸውስ ምንድ ነው? እንደኛ ባለውስ አገር ለምን ረሃብና ድህነት፤ እንዲሁም ደግሞ እልክ የሚያስጨርስ ጦርነት ይካሄዳል? ለምንስ እነዚህ ነገሮች መለያችን ሊሆኑ ቻሉ? በጎሳና በሃይማኖት መለያየት ይህን ያህል ያጨካክናል ወይ? ጦርነትስ ያማዝዛል ወይ? አንዱን ጎሳ ካለጠፋሁ በሰላም አልኖርም ብሎ አጠቃላይ ጦርነት ማውጀና አገርን ለማፈራረስ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምክንያቱስ ምንድነው? ወዴትስ ነው የሚወስደን? የመጨረሻ መጨረሻስ ማን ነው የሚጠቀመው? ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ከእነሱ ዕርዳታ በማግኘት ታሪክንና ባህልን ለማውደም መራወጥ ምን  የሚሉት ፈሊጥ ነው? እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለመረዳት ጭንቅላት ወይም አዕምሮ በታሪክ ሂደት ውስጥ ለመዳበር እንዴት እንደቻለና፣ የእኛ ህብረተሰብ ከሌላው በተለይም ከግሪኩም ሆነ ቀደም ብለው ከነበሩት ስልጣኔዎች ጋር፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ለካፒታሊዝም ዕድገት ምክንያቶች የሆኑትን የተፈጥሮ ሳይንስና የፍልስፍና ጉዳዮችን በማንሳት የሚለይበትን ለመመርመር እሞክራለሁ።

 

እግረመንገዳችንንየጭንቅላት መዳበርና የስልጣኔ ጉዳይ!

በእኛ በኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር የእኛን አገር የህብረተሰብ አወቃቀር በተነፃፃሪ የምርምር ጥናት(Comparative Studies) ዘዴ ለመመርመር አለመቻል ነው። ከዚህም በላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሚዋቀሩ በምድር ላይ በሚታዩ ሁኔታዎች፣ በደንብ በስርዓት የተዋቀረ የከተማ አገነባብ መኖርና አለመኖር፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የባህል ዕድገት መዳበርና አለመዳበር ጉዳይ፣ የስራ-ክፍፍል መኖርና አለመኖር፣ በዚህ ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት መፈጠርና አለመፈጠር ጉዳይ …ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ነገሮች  አንድ ላይ በመያያዝ በጭንቅላት መዳበርና አለመዳበር ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ በደንብ ለመመርመርና ለማጥናት ዝግጁ አለመሆን ወይም ደግሞ በፍጹም ፍላጎት አለመኖር ነው። በተለይም ጭንቅላት፣ አዕምሮ ወይም መንፈስና ትክክለኛ ዕውቀት በህብረተሰብ ዕድገት ላይ የሚኖራቸውን ሚና በቅጡ አለመገንዘብ በመሀከላችን ትልቅ አለመግባባት እንዲፈጠር አድርጓል። በተሳሳተና በትክክለኛ ዕውቀት ያለውን ልዩነት ለመረዳት አለመፈለግና ሸምጠጥ ብሎ መጓዝ በመሀከላችን ያለውን አለመግባባት አስፍቶታል ብል የምሳሳት አይመስለኝም። እንደሚታወቀው በምሁራን ዘንድ መግባባት ሊኖር የሚችለው ዕውቀት የሚባለው ነገር በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለምና የፍልስፍና መሰረት ላይ ተመስርቶ የተዋቀረ ለመሆኑ ግንዛቤ ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በዕውቀት ዙሪያ በአጠቃላይና፣ በተናጠል አንዳንድ ለትምህርት የሚሰጡ ለምሳሌ እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉ ነገሮችን ወስዶ እነዚሀን የመሳሰሉ በየትምህርት ቤቱ የሚሰጡ ትምህርቶች ከምን አንፃርና በምንስ የፍልስፍና መሰረት ላይ በመመርኮዝ እንደተዋቀሩ ክርክር እስካልተካሄደ ድረስ አልፈው አልፈው የሚቀርቡ ትችታዊ አተናተኖች ከፍተኛ አለመግባባትን ይፈጥራሉ። ከዚህ ስንነሳ አንድን ነገር በጥቁርና በነጭ እየሳሉ ንግግር በሚካሄድበትና በሚጻፍበት፣ ወይም ደግሞ ካለበቂ ጥናትና ምርምር በጭፍኑ አቋም በሚወሰድበት አገር ውስጥ መግባባት በፍጹም ሊኖር አይችልም። መግባባት ከሌለ ደግሞ አፍጠው አግጠው ለሚታዩ የህዝብ ችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ አይቻልም። የሳይንስንና የቴክኖሎጂን፣ እንዲሁም አጠቃላዩን የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ስንመለከት ካለትችትና ካለትችታዊ አመለካከት ሳይንስና ቴክኖሎጂ መዳበር ባልቻሉ ነበር። ስለሆነም ትችታዊ አመለካከትና ትችት ባልተለመደበት ህብረተሰብ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈና የተመሰረተ ህብረተሰብ መገንባት በፍጹም አይቻልም። በስነ-ጽሁፍ፣ በሙዚቃና በጠቅላላው አርትስ ብለን የምንጠራቸው ለማንኛውም ህብረተሰብ አስፈላጊና ህዝብን የሚያስተሳስሩ ነገሮችም በሙሉ ሊዳብሩና የሰውም ልጅ ጭንቅላት ሊፍታታና ችግሮቹን በሙሉ በሰላምና በክርክር ሊፈታ የሚችለው ትችታዊ አመለካከት(Critical Thought) ሲዳብርና ተቀባይነትም ሲያገኝ ብቻ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የንቃተ-ህሊና መዳበር፣ የአንድን ህብረተሰብ ሁለ-ገብ በሆነ መልክ መገንዘብና በተለይም ደግሞ የማያቋርጥ ግጭት ለምን እንደሚፈጠርና፣ በሰላም ለመኖር የሚፈልግን ተራ ህዝብ በዘለዓለማዊ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገባና ምክንያቱስ ምን እንደሆነ በደንብ ማጥናት ባለመቻሉ በህብረተሰባችን ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን፣ በተለይም ደግሞ ፖለቲከኛ ነን ባዮችን ባህርያቸውንና ድርጊታቸውን በደንብ ለመገንዘብ አልተቻለም። ባለፉት ሃምሳና አርባ ዓመታት በመጽሄቶችም ሆነ በጋዜጣዎች ላይ የሚወጡትን ጽሁፎች፣ ወይም ደግሞ በመጽሀፍ መልክ የሚቀርቡ ሀተታዎችን፣ አሁን ደግሞ በእንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ በድረ-ገጾች ላይ የሚለጠፉትን ጽሁፎችን ለተመለከተ ወይም ላነበበ ጽሁፎቹ በሙሉ ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር የተያያዙ አይደሉም። የአገራችንን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ችግሮች እያነሱ ለማወያየት የሚሞክሩና ጥያቄ እንድናቀርብ የሚጋብዙ አይደሉም። አንድ አገር፣ የአንድ አገር መንግስታዊ አወቃቀርና ፖለቲካው በምን ዐይነት ፍልስፍና ላይ መመስረት እንዳለበትና ሁለ-ገብ ዕድገትስ እንዴት ሊመጣ ይችላል?  በሚለው ዙሪያ ውይይትና ጥናትም ተካሂዶ አያውቅም። በአጭሩ በጭፍኑ ዝም ብለን የምንጓዝና የምንኖር ነን ማለት ነው።  ስለሆነም በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ከፍተኛ ግራ መጋባት መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፣  ለምን ዐይነት ህብረተሰብ እንደምንታገልና እንደምንጨቃጨቅም በፍጹም ግልጽ አይደለም። የሚጽፍም ካለ በሊበራሊዝም፣ በብዝሃዊነትና በነፃ ገበያ ዙሪያ ብቻ ነው። ይህም ቢሆን በደንብ የተጠና አይደለም። ሳይንሳዊ ግንዛቤ የጎደለውና አንዳች ዐይነት ቲዎሪንና የአሰራር ስልትን የተከተለ አይደለም። በዚህም አማካይነት ህዝባችን ከድህነት ተላቆ አስተማማኝ የሆነ ሁለ-ገብ ዕድገትን ይቀዳጅ አይቀዳጅ እንደሆን የሚጠቁም የለም። ባጭሩ በተዳፈነ፣ ጥያቄ በማያስነሳ፣ ለክርክር በማያመችና ተከታታይነት ኖሮት፣ በተለይም ለታዳጊው ትውልድ ትምህርታዊ የሆነን ነገር የሚያስጨብጥ ትምህርት አይደለም አብዛኛውን ጊዜ የሚጻፈው‹፤ ወይም ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚቀርበው። ሌላው ደግሞና በጣም አስፈላጊው ነገር፣ በመሀከላችን ያለው ትልቁ ችግር ዛሬ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጸው ዓለም፣ በአውሮፕላን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓዝ፣ ሰከንድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ መረጃን መለዋወጥ፣ ልዩ ልዩ የባህልና የስነ-ጥበብ ዕድገቶችና የስነ-ጽሁፍ ማበብና፣ ሌሎችም የዕድገት መለኪያዎች የሆኑ ነገሮች ሁሉ እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት ሊደርሱ ቻሉ? አነሰም በዛም ሁላችንም እንዴትስ ለመጠቀም ቻልን? ዛሬ የሚታዩት የስልጣኔ መግለጫዎች በሙሉ ሰው ሰራሽ? ወይስ በተዓምር የተፈጠሩ? ወይ ደግሞ ሌላ የውጭ አካል የሚባሉ ከላይ እያመጡ ምድር ላይ ያስቀመጧቸው? ወይስ ደግሞ በምርምርና ጭንቅላትን በማስጨነቅና ብዙ ውጣ ውረዶችን በማለፍ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ? ለመሆኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎችን ማን ፈጠራቸው? ታቅደውስ የተፈጠሩ? ወይም ደግሞ በሙከራና በልምድ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ነው የደረሱት? ከዚህ ጋር የሚያያዘው አንዳንድ ማህበረሰቦች በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ የዕድገት ደረጃ ላይ ሲደርሱና ስርዓት ያለው ማህበረሰብና ተቋማት ሲገነቡ እኛንስ ለምን ተሳነን? ኢንተለጀንስ የሚባለው ነገር ስለሌለን? ወይስ ደግሞ ካለን እሱን ለመጠቀም ባለመቻላችን? ከፈጠራና ከስራ፤ እንዲሁም ስርዓት ያለው ህብረተሰብ ከመመስረት ይልቅ ለምን ጦርነትን የህብረተሰባችን ችግር መፍቻ ለማድረግ በቃን? ከዚህም በላይ ዛሬ እንደሚታየውና ተቀባይነትን ለማግኘት የቻለው የተሳሳተ ትረካና ፖለቲካን ወደ ተንኮል መለወጥ ወይም የሴራ ፖለቲካ፣ እነዚህ ነገሮች እንዴትና ለምን በተለይም የመንግስትና የፖለቲከኛ ነን ባዮች የፖለቲካ ስልቶች ለመሆን በቁ? በዚህ ዐይነቱ የሴራ ፖለቲካስ- በመሰረቱ የሴራ ፖለቲካ ብሎ ነገር የለም- እየተወሳሰበ የመጣውን የአገራችንና የህዝባችንን ችግሮች መፍታት ይቻላል ወይ? ፖለቲካ በዚህ መልክ የሚመዘን? ወይስ ፖለቲካ የሚባለው ነገር ሳይንስና ከዚህም በመነሳት ጥያቄን የሚያነሳና ለችግሮች መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል መሳሪያ? እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ጥያቄዎችን ለመረዳት ከንቃተ-ህሊና መዳበር አንፃር ጠጋ ብለን ለመመርምር እንሞክር። የእኛን የህብረተሰብ አወቃቀርና፣ በተለይም ደግሞ የአዕምሮ አቀራረጽንና ብስለትን ወይም መዳበርን ከማየታችን በፊት በመጀመሪያ ደረጃ በተወሰኑ አካባቢዎች ለዛሬው የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት የሆኑ ስልጣኔዎች እንዴት ሊዳብሩ እንደቻሉ በመጠኑም ቢሆን እንመልከት።

የስልጣኔን ታሪክ ከሜሴፖታሚያ እስከግብጽ ድረስና ግሪክ፣ እስከ ህንድና ቻይና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ቀስ በቀስ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለመገለጽ የቻለውን የአውሮፓውን ስልጣኔ ስንመለከት በእነዚህ አካባቢዎችና አገሮች ውስጥ በማንኛውም ጊዜና ታሪክ በጊዜው በህንጻ ስራ፣ በዕደ-ጥበብና በንግድ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በማቲማቲክስና በፍልስፍና የሚገለጸው ስልጣኔ ሊፈጠር የቻለው በአንድ ጎሳ አማካይነት ብቻ አይደለም። አብዛዎቹ ስልጣኔዎች በአነሳሳቸው በወንዝ አካባቢና ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎች በንግድ አማካይነት በመገናኘትና እዚያ በመስፈር፣ በመጋባትና በመዋለድ የተወሰነ ሂራርኪያል የአገዛዝ መዋቅር በመመስረት የፈጠሩ እንጂ በምንም ዐይነት አንድ ጎሳ እንዳልፈጠረው ነው። ይህ ዐይነቱ ግኑኝነት መፈጠር፣ ከሌላ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ልምዳቸውንና ስልጣኔዎቻቸውን ከነበረው ጋር ሲያገናኙና ሲያዋህዱ በዚህ መልክ ልዩ ዕምርታን የያዘ ስልጣኔ መታየት ቻለ። ከሌላ አካባቢ የመጣው ከአገሬው ህዝብ ጋር ለመጋባትና ለመዋለድ በመቻሉ በዚያው መጠንም አዳዲስ የሚወለደው ህፃን ጭንቅላቱ በተሻለ መልክ ተቀርጾ የመውጣት ዕድል አጋጠመው። በዚህ መልክ የተፈጠረው ግኑኝነትና ክንዋኔ ለሚሶፖታሚያው ስልጣኔ መንገዱን ከፈተ። በማይታበል መልክ ይህ ዐይነቱ ዲያሌክቲካዊ ክንዋኔ(Thesis, Ant-thesis, Synthesis) ጭንቅላቱ ክፍት የሆነ፣ በረቀቀ መልክ የሚያስብና ቀስ በቀስ የተፈጥሮን ህግንና ትርጉም በመረዳት ማንኛውንም ለስልጣኔ የሚሆኑ ነገሮች በጭንቅላት አማካይነት መፍጠር እንደሚቻልና፣ ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ለስልጣኔ የሚሆኑ ነገሮች በተፈጥሮ ውስጥ እንደሚገኙ መረዳት አስቻለው። እንደ አልጀብራ የመሳሰሉት የሂሳብ ዐይነቶች  በሜሶፖታሚያ የተፈጠሩና፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ፈላስፋዎችና ሳይንቶስቶች ባግዳድ የኢራቁ ዋና ከተማ በመሰባሰብና ሃሳብ ለሃሳብ በመለዋወጥ ለማቲማቲክስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ  እንዳበረከቱ የማይታበል ሃቅ ነው።

ቀደም ብሎም ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ማበብ የጀመረውና፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ክፍለ-ዘመን ከፍተኛ ዕድገትን ያሳየው የግሪኩ ስልጣኔ አይዎናውያን ደሴቶች በሚባሉ ከግብጽና ከሩቅ ምስራቅ የመጡ ፈላስፋዎችና ነጋዴዎች አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩና ለፍልስፍናም መፈጠር አመቺ ሁኔታን እንዳነጠፉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዘመኑ  በአይዎናውያን ደሴቶች መታየት የጀመረው የንግድ እንቅስቃሴና የዕደ-ጥበብ ስራ ማበብ በጊዜው ብቅ ላሉት የተፈጥሮ ፈላስፋ ተመራማሪዎች እንደነታለስ ለመሳሰሉት የኮስሞስንና የተፈጥሮን ጉዳይ በጥልቀት እንዲመራመሩና ጥያቄም እንዲጠይቁ አስቻላቸው። ይህ ዐይነቱ የመጀመሪያው ምርምርና ኮስሞስንና ተፈጥሮን መቃኘት አዳዲስ ደቀ-መዝሙሮች እንደ አሸን እንዲፈልቁ አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። የኋላ ኋላ ደግሞ ሁኔታው እየተወሳሰበና በአንዳንድ አካባቢዎች ጎሳን ተገን ያደረገ ጦርነት ሲካሄድ በጊዜው ብቅ ያሉት እንደነ ሶክራተስና ፕሌቶ የመሳሰሉት ፈላስፋዎች የምርምራቸው ዋናው መነሻ ከኮስሞስና ከተፈጥሮ ባሻገር የሰውን ጭንቅላትና ባህርዩን መመርመር ነበር። ጥያቄውም በተለይም ስልጣን የጨበጡ ኃይሎችን ምን ነገር ነው ወደ ጦርነት የሚገፋፋቸው? ምክንያቱስ ምንድነው? ብለው መጠየቅና መልስ ለማግኘት መጣር ነበር። መልሳቸውም የማንኛውም ሰው አስተሳሰብ በአርቆ-አሳቢነትና አለማሰብ ስለሚዋልል፣ በተለይም ደግሞ ሰለዕውቀት ይህን ያህልም ግንዛቤ የሌላቸው ጠለቅ ብለው ስለማያስቡ ስልጣንና ስግብግብነትን(Power & Greed) ያስቀድማሉ። በዚህ መልክ የሚካሄድ የስልጣን ሽኩቻና ስግብግብነት መቅደም ፍትሃዊ የሚባለው ነገር እንዲደመሰስ ይደርጋል፤ ወይም ደግሞ ፍትሃዊ የሚባለውና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚባሉ ነገሮች ቀስ በቀስ እንዳይዳብሩ መንገዱን ሁሉ ይዘጋሉ። ፍትሃዊነትና ዲሞክራሲያዊ  ስርዓቶች በሌሉበት አገርና ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ገዚዎች ሁሉንም ነገር በዘፈቀደ ያደርጋሉ። የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚጥስ ስራ በመስራትና ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር የማይጣጣም ማንኛውንም ዐይነት “ፖሊሲ” ተግባራዊ በማድራግ አንድ ህዝብ ሁሉ ነገር ተዘበራርቆበትና ጨልሞበት እንዲኖር ለማድረግ ይችላሉ። የሚሰራውን የማያውቅ ትውልድ በማፍራት ህብረተሰብአዊ ትርምስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ከዚህ ዐይነቱ ስግብግብ ባህርይና ከማያቋርጥ ጦርነት ለመላቀቅ የግዴታ ፈላስፋዎች ስልጣንን መያዝ አለባቸው፤ አሊያም ደግሞ ፖለቲከኞች በፈላስፋዎች መመከር አለባቸው ይለናል ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶ። ፈለሳፋዎች ስልጣንን ሲይዙ ወይም ደግሞ ፖለቲከኞች በፈላስፋዎች ሲመከሩ የግዴታ ዋናው ተግባራቸው የሰለጠነ ስራ መስራት ይሆናል። በአንድ ማህብረሰብ ውስጥ የግዴታ የስራ-ክፍፍልና ንግድ፣ እንዲሁም ለጭንቅላት መዳበር የሚጠቅሙ ጥበባዊ ነገሮች ተግባራዊ ለመሆን ይችላሉ። በእርግጥም ሶሎን የሚባለው ታላቅ መሪና ፈላስፋ፣ ከአሪስቶክራሲው መደብ የተወለደው ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣንን ሲጨብጥ መሰረታዊ የጥገና ለውጥ በማድረግ በግሪክ ምድር ዐይነተኛ ለውጥ እንዲታይ ለማድረግ በቅቷል። ለሁለ-ገብ ዕድገት በሩን በመክፈት ፍልስፍና ዋናው የመከራከሪያና የመመራመሪያ መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። የተፈጥሮ ሳይንስና ጥበባዊ ዕውቀትንና ድራማ ሊያብቡ ችለዋል።

በጊዜው በግሪክ ስልጣኔ ዘመን ወጣቶች በልጅነታቸው ዘመን የሚማሩት ለጭንቅላት መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚኖራቸው፣ እንደ ቋንቋ፣ ጂኦሜትሪና ጂይምናስቲክ፣ እንዲሁም ሬሂቶሪክስ ወይንም ዲያሌክቲካዊ የክርክር ዘዴ፣ የመጠየቅና መልስ ለማግኘት የመጣር ዘዴዎችና ትምህርቶች ናቸው። ይህ ዐይነቱ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ የሰብአዊነት ትምህርት(Humanistic Thought or School) በመባል ይታወቃል። በዚህም መሰረትና በእነ ፕሌቶ ዕምነት ዕውቀት የሚባለው ነገር በሙሉ በጭንቅላት አማካይነትና ከጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠር ነው። ይህም ማለት ዕውቀት ከውጭ ከምናያቸው ነገሮች ወደ ጭንቅላታችን ውስጥ የሚገባ ሳይሆን፣ ጭንቅላትን በማስጨነቅ፣ ጥያቄ በመጠየቅና መልሶ መላልሶ ጥያቄ በማቅረብ መልስ ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ ነው። ይህ ዐይነቱ የዕውቀት ዘዴ ለሞራል፣ ለስነ.ምግባርና ለኤስቴቲክስ መሰረት በመጣል፣ ቀስ በቀስም ለሂሳብና ለተፈጥሮ ሳይንስ ምርምር አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። ይሁንና ይህ የእነ ፕሌቶ አካሄድ ሶፊስቶች በሚባሉ፣ በተለይም የዕውቀትን አፈጣጣርና የስልጣንን ጉዳይ ለየት አድርገው በሚተረጉሙ ተቃውሞ ደረሰው። በእነዚህ ፈላስፋዎች ዕምነትም ዕውቀት ከውስጥ በጭንቅላታችን አማካይነት የሚፈልቅ ሳይሆን፣ ዕውቀትን ከውጭ ነው የምናገኝው፤ የምናየው ነገር ጭንቅላታችን ውስጥ ሲገባና እሱን ስናብላላ ዕውቀት የሚባለው ነገር ይፈጠራል የሚል ነው። የፍትሃዊነትንም ጉዳይ በተመለከተ ሶፊስቶች ከእነ ፕሌቶ የተለየ አስተሳሰብ ሲኖራቸው፣ ማንኛውም ስልጣን ላይ ያለ ኃይል ራሱ በፈለገው መልክ ነው ፍትሃዊ የሚባለውን ነገር ሊተረጉመውና ሊሰጥ የሚችለው። የሶፊስቶችም አስተሳሰብ ወደ ጭንቅላት ያላተኮረ በመሆኑና ስለፍትሃዊነት ያላቸው አስተሳሰብ ለየት ያለ በመሆኑ በኋላ ለተነሱት የግሪክ መሪዎች እንደነ ፕረክሊን ለመሳሰሉት የፖለቲካ ፍልስፍና መሰረት በመሆን ፍትሃዊነትን የሚያዛባና ጭቆናን የሚያስቀድም፣ ከዲሞክራሲያዊና ከፍትሃዊነት ስርዓት  ይልቅ ዝናን የሚያስቀድም፣ ከስምምነት ይልቅ ጦርነትን የሚያስቀድም፣ የህዝብን ጥቅም ከሚያስቀድም ይልቅ የበላይነትን የሚያሰፍን፣ በዛሬው አጠራር ኢምፔሪያሊስታዊ አስተሳሰብ እንዲዳብርና፣ በገዢዎችም ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ቻለ። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ነው ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋ የቻለውና ለጦርነት ዋናው ምክንያት ለመሆን የበቃው። በ1945 ዓ.ም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንግሊዝን ሲተካ ዓለምን ለመግዛት የተከተለው መንገድ የእነ ፕረክሊንን ኢምፔሪያሊስታዊ አስተሳሰብ መነሻ በማድረግ ወይም በመቅዳት ነው። ስለሆነም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነትን ከተቀዳጀ ጀምሮ ይህንን ኢምፔሪያሊስታዊ አስተሳሰብ መመሪያ በማድረግና በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ ያልተመሰረተ፣ ለስልጣኔና ለሁለ-ገብ ዕድገት የማያመች ዕውቀት የሚመስል ነገር እንዲስፋፋ በማድረግ በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ ተከታዮችንና የዕድገት እንቅፋት ኃይሎችን ለመኮትኮት የቻለው። በዚህም መሰረት ከመንግስት መኪና ጀምሮ የኢኮኖሚውን መስክና የትምህርት ዘርፉን በመቆጣጠር አጠቃላይ ጭቆናና ድህነት እንዲሰፍኑ ለማድረግ በቅቷል። መንግስት የሚባለውም ነገር ወደ ተራ በዝባዥነትና ጨቋኝ መሳሪያነት ለመለወጥ የቻለው በዚህ ዐይነቱ ሶፊስታዊ ወይም ኢምፔሪሲስታዊ አስተሳሰብ በመመራትና የወጣቱን ጭንቅላት በማጨለም ነው።

እንደገና ወደ ግሪኩ ስልጣኔ ስንመለስ ታላቁ አሌክሳንደር ሲነሳ ዋና ዓላማው ከግሪክ ምድር አልፎ በአካባቢውና በሌሎች አገሮችም ስልጣኔን ማስፋፋት ነበር። ለዚህም ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በግብጽ ምድር አሌክሳንደሪያ የተባለው ከተማ ሲመሰረት እዚያ ከግሪክና ከሌላ ቦታዎች የተውጣጡ አዋቂዎች በመሳበሰብና ምርምር በማድረግ ነው ለስልጣኔ ዕድገት ከፍተኛ ዕምርታን የሰጡት። ታላቁ አሌክሳንደርም ለመጀመሪያ ጊዜ ለምርምር የሚያገለግል በጊዜው ሰባት መቶ ሺህ መጻህፎችን የሚይዝ ቤተ-መጻህፍት ያቋቁማል። ይህ ዐይነቱ የምርምር  ተቋም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ዕምርታን ይሰጣል። እነ አርቺሜዲስ የመሳሰሉት ታላላቅ የማቲማቲክስና የቴክኖሎጂ ሰዎች በዚህ ዐይነቱ የምርምር መስክ ውስጥ ገብተው ለመራመር በመቻላቸው ነው በጊዜው የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊታይ የቻለው። ግሪኮችም በሮማውያን ይደረግባቸው የነበረውን ወረራ ወይም ጦርነት ለመቋቋም የቻሉት እነ አርቺሜዲስ በሰሩት አዲስ የጦር መሳሪያ አማካይነት ነው። እዚህ ላይ ዋናው ቁም ነገር ፍልስፍና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ከተለያዩ ቦታዎች በመጡ ምሁራኖች የሚፈልቁና ልዩ ዐይነት ዕምርታን የሚያገኙ መሆናቸውን ለማሳየት ነው። ጭንቅላትም ሰፋና በተሻለ መልክ ሊያስብ የሚችለው ከሌላ አካባቢ ከመጡ ሰዎች ጋር ግኑኝነት ሲመሰረትና ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥ ሲኖር ብቻ ነው። በዚህ መልክ ብቻ ነው ዕውነተኛ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው። ይህ ዐይነቱ ሂደት ጤናማውና ለስልጣኔ ማበብ ከፍተኛ ዕምርታን የሰጠ ሲሆን፣ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ግን ጤናማ የሆነ ዕድገትን ወይም ስልጣኔን በፍጹም ማምጣት አይቻልም። ምክንያቱም ከሁለት መቶ ዓመት ጀምሮ፣ በተለይም ከ1945 ዓ.ም በኋላ የተከሰተው ልዩ ዐይነት የኃይል አሰላለፍና የተሳሳተ ዕውቀት መሰራጨት ሁለ-ገብና ሚዛናዊነት ያለውንና ለመንፈስ መዳበር የሚያመቸውን ስልጣኔ ስላጣመመው ነው። ስለሆነም የካፒታሊዝም ማየል፣ ወይም በተዛባ ንግድ፣ በዕዳ፣ በተሳሳተ የኢኮኖሚ ወይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ፣ ብሄራዊ ሀብትን ሊፈጥር በማይችል የሚካሄድ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ(Direkt Investment) የሚገለጸው ግሎባላይዜሽን ዕውነተኛ ዕድገትንና ስልጣኔን የሚያመጣ ሳይሆን ብዝበዛንና ጭቆናን የሚያሰፍን በመሆኑ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ከካፒታሊዝም ጋር የተያያዘውና ለካፒታሊዝም መሰረት የሆነው ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ መካሄድ የጀመረው የባርያ ንግድ፣ በአስረዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የቅኝ-አገዛዝ መስፈንና ጥቁር አፍሪቃን ተበዝባዥ ማድረግ፣እነዚህ ነገሮች በሙሉ ጤናማውን የስልጣኔ፣ የተሟላ ዕድገትንና የሰውንም ልጅ የማሰብ ኃይል ያኮላሹና ለማያልቅ ጦርነት የዳረጉት ናቸው። ለዚህም ነው ካፒታሊዝም በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ታላላቅ ጦርነቶች ሊከሰቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፉ የቻሉት። ስለሆነም የዛሬው ዘመን ግሎባላይዜሽን የብጥብጥና የመፈናቀል ምንጭ፣ እያንዳንዱ አገርና ህዝብ በሰላም እፎይ ብሎ እንዳይ‹ኖርና ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በስነ-ስርዓት እንዳይጠቀም የሚያደርግ ነው። በሌላ አነጋገር፣  በተለይም የሶስተኛ ዓለም ተብለው በሚጠሩትና በአገራችንም የሚታየው ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም በጎሳና በሃይማኖት ስም ተሳበው የሚካሄዱት ጦርነቶች በሙሉ ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። የሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች መንግስታትና ገዢዎች፣ እንዲሁም የእኛም አገር መንግስትትና አገዛዝ የህዝቦቻቸው ተጠሪዎች ሳይሆኑ በቀጥታ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ለትላልቅ ኩባንያዎች የሚሰሩና ድህነት እንዲፈለፈልና ሰፊውም ህዝብ ሰላም እንዳይኖረው የሚያደርጉ ናቸው።

የግሪኩ ስልጣኔ ከወደመና ሮማውያን ቦታውን ሲተኩ ከፍልስፍና ይልቅ ፕራክቲካል ወደሆኑ ነገሮች ላይ ነው ማተኮር የጀመሩት። በሮማውያን ወረራ የተነሳ የግሪኩ ስልጣኔ እንዳለ ባይወድምም በዚህ ዐይነቱ ኢምፔሪያሊስታዊ መስፋፋት ነው የኋላ ኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የጨለማው ዘመን ሊነግስና፣ የአውሮፓ ህዝብም በውዥንብር ዓለም ውስጥ እንዲኖር የተገደደው። የግሪኩ ስልጣኔ መዳበርና መስፋፋት በመቋረጡም ምክንያት የተነሳ ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ጦርነትና ረሃብ፣ እንዲሁም በሽታ ሊስፋፉ የቻሉት።  ይህ የጨለማ ዘመን ከስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ አስራ-አራተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የዘለቀና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት እንቅፋት የሆነ፣ ቀኖናዊ አስተሳሰብ የተስፋፋበትና ግለ-ሰብአዊ ነፃነት የታፈነበት ነበር። ይሁንና ግን ከአስራአራተኛውና ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ሬናሳንስ የሚባለው በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለጸው የመንፈስ ተሃድሶ ለመስፋፋት በመቻሉና በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮችም ተቀባይነትን ማግኘት በመቻሉ ለብዙ መቶ ዐመታት ሰፍኖ የነበረውን የተጣመመና ፀረ-ዕድገት አስተሳሰብ በዚያው መልኩ እንዲቀጥል አላስቻለውም። በአንዳንድ ቦታዎችም የዕደ-ጥበብ ሙያና ንግድ ሲስፋፉ፣ እንዲሁም ከተማዎችና ቤቶች ውብ በሆነ መልክ ሲገነቡ ይህ ዐይነቱ አዲስ ሁኔታ ለሳይንቲስቶች ብቅ ማለት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ብቅ ብቅ ያሉት ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች ደግሞ በጊዜው ተንሰራፍቶ የነበረውን የሃይማኖት ቀኖናዊ አስተሳሰብ ለመጋፈጥ በመቻላቸው አዲሱ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለሌችም አስተሳሰቦች አመቺ ሁኔታን በመፍጠር የህብረተሰብ ዕድገት ከብዙ አንፃሮች አኳያ መታየት እንደሚችል ለማረጋገጥ ተቻለ። ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለመዳበር በመቻሉም ያንቀላፋ የነበረው የአውሮፓው ህዝብ ጭንቅላት ቀስ በቀስ መንቃት ይጀምራል፤ ሰው መሆኑንም ይገነዘባል። የሳይንቲስቶችና የፈላስፋዎችም ዋናው ተግባር ሰፍኖ ከነበረውና የስውን አስተሳሰብ ጨምድዶ ከያዘው ቀኖናዊ አስተሳሰብ ጋር በመጋፈጥ ህዝባቸው ስልጣኔን እንዲጎናጸፍ ማድረግ ይሆናል። ዘመኑም በጨለማ ዓለም ውስጥ መኖርና በጭፍን አስተሳሰብ ከመጓዝ ይልቅ የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት ተፈጥሮን መቃኘትና የኋላ ኋላ ደግሞ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን በማዳበር ሁለ-ገብ ዕድገትን ተግባራዊ ማድረግ ይሆናል።

የምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበርና መስፋፋት የግዴታ በየጊዜው እየተወሳሰበ የመጣውን የህብረተሰብ አወቃቀር፣ የኃይል አሰላለፍና በቁጥር እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር የሚያስተናግዱና እንዲሁም በየጊዜው ሊለዋወጡ የሚችሉ የሰውን ልጅ ባህርዮች፣ የሀብት ክፍፍልና እንዲሁም ሌሎች ነገሮች መመርመሪያ ዘዴዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉ ዕውቀቶች ከመዳበራቸው በፊት ዋናው የምርምር መሰረቶች ፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ ነበሩ። የኋላ ኋላ ደግሞ በጊዜው የነበረውን ግትር አስተሳሰብ ለመዋጋት የሚያስችል የፖለቲካ ቲዎሪ ሊዳብር ቻለ። አንድን አገርና ህብረተሰብ በዲስፖታዊ አገዛዛ ማስተዳደር አለመቻሉን የተገነዘቡና፣ ይህም ዐይነቱ አካሄድ ለሳይንስና ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ በመሆኑ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ሊዳብር ቻለ። የሊበራሊዝም አስተሳሰብ መዳበርና የፖለቲካ መድረኩ ክፍት መሆን ለአዳዲስ አስተሳሰቦች መፍለቅ አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። የኢኮኖሚ ቲዎሪም መዳበር ቻለ። በሌላ ወገን ደግሞ በጊዜው የኢንዱስትሪ አብዮት ሲካሄድ ብዙ ምስቅልቅል ሁኔታዎች በመፈጠራቸውና ድህነትም እየተስፋፋ በመምጣቱ ይህንን ሁኔታ ለመገንዘብ የሚያስችሉ ትችታዊ አመለካከት ያላቸው የሊትሬቸር ጽሁፎችና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የሶስዮሎጂና የህሊና-ሳይንስ ጽሁፎች እንደ አሸን መፍለቅ ጀመሩ። ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ እንቅስቃሴና በተለያዩ ምሁራኖች መሀከል ይደረግ የነበረው ክርክር የግዴታ በፖለቲካው መድረክና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ማሳደር ተቻለ። ስለሆነም አንድን ህብረተሰብ ለማስተዳደርና ስርዓት ለማሲያዝ የግዴታ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ተቻለ። ማንም እየተነሳ በፖለቲካ ስም ህዝብን የሚያሳስትበትና አገርን የሚያፈራርስበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እየዳበረና ጥልቀትን እያገኘ የመጣው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለማንም መፈናፈኛ የማይሰጥ ለመሆን በቃ።

ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ጥልቀትንና ስፋትን እየያዘ ቢመጣም የአውሮፓው ዕድገት ቀጥተኛ መንገድን ይዞ የተጓዘ ነበር ማለት አይደለም። ከገዢው መደብ ጋር የተቆላለፉ ባለሀብታሞችና አንዳንድ ያልተገለጸላቸው ኃይሎች  የበላይነታቸውን ላለማጣት ሲሉ የግዴታ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን ነበረባቸው። በ19ኛው ክፍለ-ዘመንና እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በአውሮፓ ምድር ድህነት የተስፋፋበት ዘመን ነበር። የህብረተሰብን ዕድገት ህግ በተጣመመ መልክ የሚተረጉሙ አንዳንድ ምሁራንም በተለይም በማደግ ላይ የነበረውን የከበርቴ መደብ የበላይነቱን እንዳያጣ ኢኮኖሚ ቲዎሪን በተጣመመና ግልጽ በማይሆን መልክ መጻፍ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም በኢኮኖሚ ቲዎሪና በሶስዮሎጂ ዙሪያ የጦፈ ክርክር መካሄድ ጀመረ። ዕውነተኛ ዕውቀትን በሚያራምዱ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የህብረተሰብ ዕድገትን በተጣመመ መልክ በሚተረጉሙ ምሁራን መሀከል ክርክር መካሄድ ጀመረ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ሳይንሳዊ ዕውቀትና የሰብአዊው መንገድ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ለመውደቅ ቻሉ። ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመዳበር ቢችሉም የመጨረሻ መጨረሻ በአሸናፊነት ለመውጣት የቻለው የከበርቴው መደብ ነው። የመንግስት መኪናም አዲስ የተፈጠረውንና በአሸናፊነት የወጣውን የከበርቴ መደብ ለማንፀባረቅ በሚችል መንገድ ተዋቀረ።  ስለሆነም መንግስት ራሱ የኢ-ፍትሃዊነትና ያልተስተካከለ የሀብት ስርጭት ምክንያት ለመሆን በቃ። ወደ ውጭ ደግሞ ጦርነትን የሚያካሂድና ደካማ አገሮችን ለመውረር የሚችል ለመሆን በቃ። በሌላ አነጋገር ቀደም ብሎ የቅኝ-ግዛት አስተሳሰብ መስፋፋትና ደካማ አገሮችን  በቁጥጥር ስር ማድረግ፣ በቀላሉ አንገዛም ያሉትን አገሮች ደግሞ ጦርነት በማወጅ በኃይል ለመያዝ መሞከር በቀጥታ ከህብረ-ብሄር ግንባታና ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው ማለት ይቻላል። ወደ ውስጥ ደግሞ ብዝበዛን ማስፋፋት፣ ገበሬውን ከመሬቱ ማፈናቀልና ወደ ከተማዎች እንዲሰደድ በማረግ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ከካፒታሊዝም ዕድገትና መስፋፋት ጋር በቀጥታ የሚያያዙ ናቸው። ይህንን ዐይነት በአንድ በኩል የሀብት ክምችት መዳበርና በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር መውደቅ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የድህነትን መስፋፋት የተመለከቱ አንዳንድ የተገለጸላቸው ከከበርቴው መደብ የተወለዱ ምሁራን ነገሩን ክሪቲካል በሆነ መልክ ማየት ነበረባቸው። ስለሆነም የነፃ ገበያ ወይም ካፒታሊዝም በራሱ የተስተካከለ ዕድገትንና ሚዛናዊነት ያለው የሀብት ስርጭትን ማምጣት እንደማይችል ለማመልከት ሞከሩ። የማርክስና የኤንግልስ ስራዎች፣ በተለይም የዳስ ካፒታል መጻፍ ከጊዜው ሁኔታ የፈለቁና የጊዜውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት አንድ ህብረተሰብና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተለያዩ ምሁራን ዘንድ በተለያየ መልክ ለመተርጎም እንደሚችሉ ነው መረዳት የሚቻለው። በተለይም የካፒታሊዝም ማደግና ማበጥ ሙሉ በሙሉ ህዝባዊ ነፃነትን አላጎናፀፈም። ገና ኋላ-ቀር ከሆነ አስተሳሰብ ያልተላቀቀውና በማደግ ላይ የሚገኘው የከበርቴው መደብ ወዛደሩን በከፍተኛ ደረጃ ከመብዝበዝ ባሻገር የኑሮውን ሁኔታ ሊያሻሻልለት አልቻለም። ስለሆነም ወዛደሩ የራሱን መብት ለማስጠበቅ፣ የስራው ጫና እንዲቀንስለትና በቀን ከስምንት ሰዓት በላይ እንዳይሰራና፣ በአጠቃላይ በሚሰራበት ቦታ መብቱ እንዲከበርለትና ለስራውም ተመጣጣኝ ደሞዝ እንዲከፈለው ራሱን በሙያ ማህበር አማካይነት ማደራጀት ነበረበት።  በሌላ ወገን ደግሞ በጊዜው በተለይም በፖለቲካው መድረክ ላይ የሚወጡ ኃይሎችን ከአመጸኛና ከግትርነት ባህርያቸው ለማላቀቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ከፍተኛ ጥረትን ቢያደርጉም ካፒታሊዝም በውስጣዊው ቅራኔ በሚፈጥራቸው ክስተቶች የተነሳና፣ በተለይም ፍትሃዊነትንና እኩልነትን በሚጠሉ ኃይሎች የተነሳ እንደ ፋሺዝም የመሳሰሉትና በኮንሰርቫቲዝም ስም የሚነግዱ ኃይሎች ብቅ በማለት ለጦርነት ዋናው ምክንያት ለመሆን በቁ። የካፒታሊዝምም ዋናው ዓላማም ከትርፍ አንፃር ማምረትና በጉልበት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ስልተ-ምርትም እንደመሆኑ መጠን ጦርነት በራሱ የካፒታሊዝም ዋናው አካል በመሆን ትርፍን ማካበቺያ መንገድ ለመሆን በቃ። ስለሆነም ካፒታሊዝም እንደ ስልተ-ምርት ብቅ ካለበት ጊዜና ከፍተኛውን ደረጃ ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በአህጉር ደረጃና በዓለም አቀፍ ደረጃም ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል። የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች በመባል የሚታወቁት የዓለም ስምን ቢይዙም በመሰረቱ በአውሮፓውያን መሀከልና በአውሮፓ ምድር የተካሄዱ ጦርነቶች ናቸው። የጦርነቱም ዋና ምክንያት የበላይነትን ለማንገስና፣ በተለይም ደግሞ በመነሳት ላይ የነበረቺውን  ራሺያን የኋላ ኋላ ደሞ ሶቭየት ህብረት በመባል የምትታወቀውን ለመቆጣጠርና ሀብቷን ለመዝረፍ ነበር። ስለሆነም ከጀርመን ምድር የተጠነሰሱትና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መሞት ተጠያቂ የሁኑት ጦርነቶች በሙሉ በቀጥታ ከካፒታሊዝም ጋር የሚያያዙ ናቸው። ይህም ማለት በአንድ በኩል ሳይንስና ቴኮኖሎጂ ከፍተኛውን የዕድገት ደረጃ ሊይዙ ቢችሉም፣ በሌላ ወገን ግን ደግሞ ሳይንስና ቴኮኖሎጂን በመጠቀም ጦርነትን በሚያካሄዱ ኃይሎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የንቃተ-ህሊና አለመዳበር ክፍተት እንዳለ ነው ሁኔታው የሚያረጋግጠው። በሌላ አነጋገር፣ የአውሮፓው መንግስታትና የገዢው መደብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ መዳበር የተነሳ የግዴታ የሞራል ብቃትነትንና ሰብአዊነትን ለመጎናጸፍ አልቻሉም። በተለይም ስልጣንን የጨበጡ፣ በሚሊታሪ ውስጥ የሚሰሩና የእኮኖሚና የፖለቲካ ኤሊቶችን ጭንቅላት ርህሩህና አርቆ-አሳቢ በፍጹም አላደረጓቸውም። ዛሬም ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ ይህ ነው። በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ጭምር የሚካሄደው ጦርነት፣ አሁን ደግሞ ራሺያን ለማዳከምና የመጨረሻ መጨረሻ ለመበታተን ዩክሬይንን መሳሪያ በማድረግ የሚካሄደው ጦርነት በቀጥታ ከካፒታሊዝም ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ከመፈለግና፣ በሌሎች አገሮች ደግሞ የተስተካከለ ዕድገት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲአዊ ስርዓት እንዳይፈጠርና እንዳይመሰረት ለማድረግ ከመሞከር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ሁሉኑም ነገር እኛ ነን የምናውቀው፣ የእኛውም እሴት ነው ትክክለኛው፣ ስለሆነም ማንኛውም አገር እኛ የምንለውን መቀበል አለበት ከሚለው ግብዝ አስተሳሰብ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። ከዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ነፃነትን አፋኝ አስተሳሰብ ስንነሳ በአውሮፓ ምድርም ሆነ በአሜሪካ በአንድ በኩል እየመነመነ በመጣው ይሁንና ደግሞ በየጊዜው ምርምር በሚያደርገው የፍልስፍናና የሳይንስ፣ እንዲሁም የስነ-ጽሁፍ ኮሙኒቲው፣ በሌላ ወገን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ከምሁራዊ አስተሳሰብ በራቀው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚክስና የሚሊተሪ ኤሊት መሀከል ከፍተኛ የአስተሳሰብ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።  የፖለቲካው መድረክ እንዳለ በሚሊታሪ-ኢንዱስትሪና የኢኮኖሚክስ ኤሊት፣ እንዲሁም በቴክኖክራቶችና በቢሮክራቶች ቁጥጥር ስር የወደቀ በመሆኑ ለጦርነትና ላልተሰተካከለ የሀብትና የገቢ ስርጭት ዋናው ምክንያት ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል። በምዕራብ አውሮፓም ሆነ በአሜሪካ በየአራት ዓመቱ የሚካሄዱት ምርጫዎችና የተለያየ ስም ያላቸው ፓርቲዎች ስልጣንን ቢፈራረቁም በመሰረቱ ጦርነትን ለማስወገድ አልቻሉም፤ የተዛባ ሀብት ክፍፍልም እንዳይኖር መሰረታዊ ለውጦችን ማድረግ አልቻሉም። የሚወጡትና ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚና የቀረጥ ፖሊሲዎች በሙሉ ሀብት ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ከፍተኛው እንዲሄድ የሚያደርጉ ናቸው። ያለውን የሀብት ክፍፍልና የገቢ ልዩነት እንዲሰፉ የሚያደርጉ የኢኮኖሚና የቀረጥ ፖሊሲዎች ናቸው የሚወጡትና ተግባራዊ የሚሆንት ማለት ነው። አንዳንድ ፈላስፋዎች እንደሚሉት ከሆነ በአብዛኛዎቹ ካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ኒዎ-ፊዩዳሊዝም(Neo-Feudalism) ዐይነት ስርዓት  ሰፍኗል።

ለማንኛውም ቀደም ብሎም ሆነ የኋላ ኋላ የስልጣኔ ዕድገትንና ሰፋ ያለውን ምሁራዊ እንቅስቃሴ ታሪክ ስንመረምር እነዚህ  ነገሮች ሁሉ ሊፈጠሩ የቻሉት በአገራችን ምድር እንደተለመደው ተጨቁኜ ነበር፣ ተበድዬ ነበር፣ ተንቄ ነበር…ውዘተ. በማለት ሳይሆን ራስን ከተፈጥሮ ጋር በማገናኘትና ሳያቋርጡ ምርምር በማድረግና ከሌላው የተሻለ ሰርቶ ለመገኘት በመሞከር  ብቻ ነው። ለምሳሌ በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ እንደይሁዲዎችና ጥቁር አሜሪካኖች ከፍተኛ በደል የደረሰበት ያለ ህዝብ የለም። ይሁዲዎች በአውሮፓ ውስጥ እንደልዩ ፍጡሮች የሚታዩና፣ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በየጊዜው ለሚከሰቱት የወረርሽኝ በሽታዎች እንደ ዋና ምክንያት ሆነው የሚቆጠሩ ነበሩ። ስለሆነም የዕደ-ጥበብ  ሙያ የመሳሰሉ ውስጥ የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም። ያላቸው ዕድል በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ነበር። በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ የንግድ ስራ እንደዝቅተኛ ሙያ የሚቆጠር ነበር። ገንዘብም ማበደርና የወለድ ወለድ መጠየቅ ክልክል ነበር። ታዲያ ይሁዲዎች በዚህ እንደዝቅተኛ በሚታየው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍና በተዘዋዋሪ የዕደ-ጥበብ ሙያውን በመቆጣጠር ሀብት ማካበት ይጀምራሉ። ልጆቻቸውንም በማስተማር አንዳንዶቹ የወጣላቸው ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፣ የህግ ሰዎችና ትላልቅ ባንኮችን ለመቆጣጠር የቻሉ ይሆናሉ። ከዚህም አልፈው ፈጣሪ በመሆን ለጀርመን ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የሰው ልጅ የሚሆን ዕውቀት ያዳብራሉ። ጥቁር አሜሪካኖችም እንደዚሁ ከመሸጥና ከመለወጥ፣ እንዲሁም የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ውስጥ የግዴታ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ ዕድል አልነበራቸውም። የኋላ ኋላ ግን አንዳንድ የተገለጸላቸው ነጭ ምሁራን እንደ ቤንጃሚን ፍራንክሊን የመሳሰሉት ለጥቁሮች የሚሆን ትምህርት ቤት በመክፈት እንዲማሩ ዕድል ይሰጧቸዋል። በእንደዚህ ዐይነት ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተው የመማር ዕድል ያገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ልጆች ከነጮቹ በምንም እንደማያንሱ ለማረጋገጥ ይችላሉ። በዚህ መልክ ዕድል ያገኙት ጥቁር አሜሪካውያን የኋላ ኋላ የማቲማቲክስ፣ የአስትሮኖሚክስ ሰዎች፣ የሙዚቃና የሌሎችም ዕውቀት አፍላቂዎች በመሆን ተወዳዳሪነትቻውን ለማሳየት ይችላሉ። ይኸው እንደምናየው በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ የተወለዱት ጥቁር አሜሪካውያን በተለያዩ ከፍተኛ ሙያ ውስጥ፣ በተለይም በሆሊውድና በሙዚቃው፣ እንዲሁም በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ብቃትነታቸውን ለማሳየትና ለመወዳደርም እንደሚችሉ ያረጋግጣሉ። ሙያቸውም ከአሜሪካ አልፎ የዓለም ህዝብ በሙሉ የሚደሰትበት ነው። በታሪካቸው ውስጥ ይሁዲዎችም ሆኑ ጥቁር አሜሪካውያን የደረሰባቸውን የግፍ ግፍ እንደ ቂም በቀል በመቁጠር በነጩ ህዝብ ላይ ጦርነት አላወጁም። ለማረጋገጥ የቻሉት ያለውን ዕድል ሁሉ በመጠቀም ፈጣሪና ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚችሉ ብቻ ነው። እንደኛ ያሉ ደንቆሮ የብሄረሰብ አቀንቃኝ ኃይሎች ከዚህ በፊት ይበድለን ነበር፣ ይንቀን ነበር የሚሉትን በማሳዳድ አይደለም ሰው መሆናቸውንና ከሌላውም እንደማያንሱ ለማረጋገጥ የቻሉት።

ስልጣኔ በታየባቸውና የኋላ ኋላ ደግሞ በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የቴክኖሎጂ ዕድገት ሊታይ የቻለው የአገራቸውን ኋላ-ቀርነት በተመለከቱና ለህዝቦቻቸው የተሻለን ኑሮ ለማምጣት በታገሉና አርቀው በሚያስቡ ጥቂት ኃይሎች አማካይነት ብቻ ነው። ለምሳሌ ጀርመንን ብንወሰድ ጀርመን እንደ ህብረ-ብሄር ልትገነባ የቻለችው በጥቂት ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶችና የማቲማቲክስ ሰዎች፣ ሁለ-ገብ አስተሳሰብ ባላቸው የአርቴክቸርና የሶስዮሎጂ፣ እንዲሁም የስነ-ጽህፍ ምሁራን አማካይነት ብቻ ነው።  ከግሪክ የስልጣኔ ጊዜ ጀምሮ የዳበረውንና የተስፋፋውን ዕውቀት ስንመለከት ከህብረተሰብ ክንዋኔ ውጭ ያሉ አጉል ትረካዎችና ሊረጋገጡ የማይችሉ በጭቆና መልክ የሚሳበቡ ጒዳዮች ቦታ እንዴሌላቸው ነው። ጭቆናዎች ካሉና ዕድገት የማይታይ ከሆነ ይህ ጉዳይ በአንድ ብሄረሰብ ላይ የሚሳበብ ሳይሆን በጌዜው የሰፈነውን የተሳሳተ ዕውቀት፣ የስነ-ልቦና አወቃቀርንና የንቃተ-ህሊናን ጉዳይ ማዕከላዊ ቦታ በመስጠትና እነዚህ ነገሮችን እንደዋና ምክንያት ብቻ በመቁጠር ነው ጭቆናንም ሆነ ለዕድገት ጠንቅ የሆኑ ምክንያቶችን መረዳትና ማስወገድ የሚቻለው። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ሰው ወይም ብሄረሰብ በአፈጣጠሩ ጨቋኝና ሌላውን የሚንቅ ሆኖ አይፈጠርም። በሰው ጭንቅላት ውስጥ የሚቀረጹ መጥፎም ሆነ ጥሩ አስተሳሰቦች፣ አርቆ ማሰብም ሆነ አራቆ አለማሰብ በምድር ላይ ከሚታዩ የማቴሪያልና የሰው በሰው ግኑኝነት አማካይነት የሚፈጠሩ ናቸው። ስለሆነም ለአንድ አገር ዕድገት ጠንቅ መሆንና ጭቆና መስፈን ዋናው ተጠያቂ አንድ ጎሳ ሳይሆን፣ አንድ አገዛዝ የሚመራበትን መመሪያ በመመርመር ብቻ ነው መልስ ለማግኘት የሚቻለው። በሌላው ወገን ደግሞ እጅግ ወደ ኋላ በቀረ ስርዓት ውስጥ አንድ የገዢ መደብ በአንዳች ፍልስፍና አይመራም። የፖለቲካ አስተሳሰብም ያልዳበረ በመሆኑ ስልጣን ራሱ ለአንድ የተወሰነ የገዢ መደብ ብቻ በአምላክ ፈቃድ  የተሰጠ ተደርጎ ነው ግንዛቤ ውስጥ የሚገባው። ይህም ማለት የፖለቲካ ስልጣንና የገዢውም መደብ ሊተነተኑ የሚችሉት ከፖለቲካና ከሶስይሎጂ ቲዎሪ አንፃር ብቻ ነው። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ከአንድ ጎሳ የተውጣጣ የገዢ መደብ ለብዙ መቶ ዓመታት ስልጣንን ይዞ የአንድን አገር ዕድል የወሰነበት ጊዜ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። የሰው ልጅ ተንቀሳቃሽ እንደመሆኑና አንደኛው ጎሳ ከሌላው ጋር የመጋባቱ ጉዳይ የህብረተሰብ ታሪክ ግዴታ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ አንድ ጎሳ ብቻ ስልጣንን ይዞ የተቀመጠበት ታሪክ የለም።  በአገራችን የተለመደው አጉል አነጋገርና ከአንድ ጎሳ ብቻ የተውጣጣ የገዢ መደብ ለብዙ መቶ ዓመታት ስልጣንን ይዞ የቆየ ነው የሚለው የተሳሳተ ትረካ በመስፋፋቱ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ተቀናቃኝ የሆነ አስተሳሰብ እንዲዳብርና በአንዳንድ ብሄረሰብ ኤሊቶች ጭንቅላት ውስጥ እንዲቀረጽ ለመደረግ በቅቷል።  ስለሆነም  በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላቱ የተቀረፀ ወይም ፕሮግራምድ የሆነ ትውልድ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ለማየት በመቻሉ አንድን አገር እንዳለ የሚያናጋ ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እየፈጠረ ነው። በሚያራግበው አጉል ትረካ ጠቅላላው ህዝብ የስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን መንገዱን ሁሉ ለመዝጋት በቅቷል። በዚያው መጠንም ታዳጊው ትውልድ ጭንቅላቱ ቀጭጮ እንዲቀር ለማድረግ ችሏል። ጭንቅላቱ በተሳሳተ ትረካ የተያዘ ወይም ፕሮግራምድ የሆነ በመሆኑ ተግባሩ ሁሉ ተንኮል፣ ሰላም መንሳት፣ ጦርነትን መቀስቀስና የአብዛኛው ህዝብ አስተሳሰብ በዚህ እንዲወጠር በማድረግ ረሃብና ድህነት እንዳይወገዱ ለማድረግ በቅቷል። ግለሰብአዊ ነፃነት እንዳይኖር፣ ሰላም እንዳይሰፍንና በህዝብ መሀከል ጤናማ ግኑኝነት እንዳይፈጠር በማድረግ አገራችን በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንድትወድቅ አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። አገራችን ታሪክ የሚሰራባት ሳትሆን የብልግና ኢንዱስትሪ የሚስፋፋባትና ህዝቡም ብዥ ብሎበት እንዲኖር ሳያውቀው አደገኛ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በቅቷል።  ስለሆነም ነው በአገራችን ምድር ባለፉት አርባ ዐመታት ችግር ሊፈጠርና አገራችንም ወደ ጦርነት ቀጠናነት ለመለወጥ የቻለችው። ስለሆነም ነው ቀደም ብሎ በተማሪው እንቅስቃሴ ዘመን አላስፈላጊ ድርጊቶች ሊታዩ የቻሉትና፣ እስከዛሬም ድረስ ከዚህ ዐይነቱ ትርምስና ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ለመላቀቅ ያልቻልነው። ስለሆነም ነው የኋላ ኋላ የብሄረሰብን አርማ ይዘው የተነሱ ከዚህና ከዚያ የተውጣጡ ኤሊቶች ጠቅላላውን ህዝባችንን ፍዳ የሚያሳዩትና የስልጣኔን ብርሃን እንዳያይ ለማድረግ የበቁት።

 

 

 

 

የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር በቅጡ ለመረዳት ያለመቻል ችግር!

Not in Space and time you should search for your dignity, but in ordering your own Idea. All our dignity emanates from our ideas. Therefore, our pride must emanate not from space and time, which we cannot fill them. We should therefore try to think properly. That is the main principle of true moral. (Immanuel Kant)

በአገራችን ምድር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲጀመር የህብረተሰብአችንን አወቃቀር፣ የህዝባችንን የንቃተ-ህሊና ጉዳይ፣ በተለይም ደግሞ በየጊዜው ስልጣንን የጨበጡትን አገዛዞች የንቃተ-ህሊና ሁኔታ መመርመር ሳይሆን ህብረተሰባችንን በጨቋኝና በተጨቋኝ መሀከል መክፈል ነው። ይህ ዐይነቱ ጭፍን አስተሳሰብና በዚህ መመራት፣ በተለይም ደግሞ ጨቋኝ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ሲወገድ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚያብብና ፍትሃዊነት እንደሚነግስ አድርጎ ማቅረብ ወደ ውስጥ ገባ ብለን የህበረተሰብአችንን የማቴሪያል ሁኔታ፣ የአመራረት ስልትና ይህ ዐይነቱ በስራ-ክፍፍል ያልዳበረና በንግድ እንቅስቃሴ የማይገለጽ ማህበረሰብ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በቅጡ ለመመርመር ያለመቻል ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ጥሎናል። አርቀንና ረቀቅ ባለ መልክ እንዳናስብና እንዳንመራመር ሊያግደን በቅቷል። ቁጭ ብሎ ሳይንሳዊና ኢምፔሪካል ጥናት ከማድረግና፣ በየኤፖኩ የሚፈጠሩ በምድር ላይ የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ከማንበብ ይልቅ በሰዎች ላይ ወይም በአንድ ጎሳ ላይ ብቻ ያተከረ በሳይንሳዊ የትግል ታሪክ ውስጥ ያልታየ  የትግል ስልት በመከተላችን የግዴታ ነፃነትንና ዕድገትን አፋኝ ለመሆን በቅተናል። ጭንቅላታችንም በትክክለኛ ዕውቀት ለመቀረጽ ባለመቻሉ የተነሳ ፖለቲካ የሚባለው ሳይንሳዊ ዕውቀትና ችግር ፈቺ መሳሪያን ወደ ተንኮልና ወደ ሽወዳ መሳሪያነት ለመለወጥ በቅተናል። ስለሆነም ተንኮልንና ጉልበትን በማገናኘት ህብረተሰብአዊ ዕድገት እንዳይመጣ ብቻ ሳይሆን  በህዝባችን መሀከል ስምምነት እንዳይኖር ለማድረግ በቅተናል።

እንደሚታወቀው የአንድ ህብረተሰብ ታሪክ የግዴታ ከዕድገት ጋር የተያያዘ ነው። በዕደ-ጥበብ መዳበር፣ በንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት፣ በከማዎችና በመንደር መገንባት፣ በስነ-ጽሁፍ መዳበር የማይገለጽ ማህበረሰብ ታሪክ አለው ብሎ ለመናገር ያዳጋታል። በተወሰኑ ነገሮች የሚታይን እንቅስቃሴ ወስዶ በዚያ ላይ በመመርኮዝ ታሪክን ለመጻፍ መሞከር የሃሳብ መንሸራሸር እንዳይኖር ያግዳል። ጥያቄዎች  እንዳናነሳ፣ ምርምር እንዳናደርግ፣ በተለያዩ ነገሮች የሚገለጽ ዕድገት የማይታይ ከሆነ ደግሞ ለምን የሉም ብለን እንዳንጠይቅ እንገደዳለን። አስተሳሰባችን ሁሉ ውስንና እዚያው በዚያው የሚሽከረከርና፣ የሚታዩ ነገሮችን ለማየት እንዳንችል፣ በረቀቀ መልክ እንዳናስብና አዳዲስ ነገሮችን እንዳንፈጥር እንገደባለን ማለት ነው። ስለሆነም ስራችን ሁሉ የተስተካከለና ስርዓት ያለው ነገር ከመፍጠር ይልቅ ዝብርቅርቅ ነገሮችና ችግርን ፈጣሪ እንሆናለን። ካንት የሚባለው ፈላስፋ እንደሚለው በአንድ አገር ውስጥ ዝብርቅርቅ ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ለመፈጠሩ ምክንያቱን መፈለግ ያለብህ በጊዜና በሰዓት(Space and Time) ውስጥ ሳይሆን በጭንቅላትህ ውስጥ ነው ይላል። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችና የፖለቲካ ውዝግቦች የሚፈጠሩት ጭንቅላት በትክክል ያልተቀረፀ እንደሆነ ብቻ ነው። የሰው ልጅ ጭንቅላት ቀኖናዊ በሆነና በተሳሳተ ትረካ የሚወጠር ወይም የሚቀረጽ ከሆነ የግዴታ ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ሀብቶችን በደንብ ለመጠቅም አይቻልም። ኢ-ፍትሃዊነትና በዝባዥ ስርዓትን በመፍጠር የአንድ ህዝብ ዕጣ ለዝንተ-ዓለም በጭንቀትና በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ይሆናል። በመሀከላችን ያለው ትልቁ ችግር ይህ ነው። ከተወሰኑ ነገሮች ባሻገር እንዳናስብ የተፈረደብን። ለምድን ነው ይህ ሁኔታ የተፈጠረው? ብለን ለማውጣትና ለማውረድ ባለመቻላችን የህዝባችንን ኑሮ አስቸጋሪ እንዲሆን ለማድረግ በቅተናል።

ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት ስልጣኔዎች በሙሉ የዳብሩት ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎች ሲጋቡ፣ ልምዳቸውንና ስልጣኔያቸውን ማስፋፋት ሲችሉና፣ ይህም ተቀባይነት ኖሮት አገር ውስጥ ካለው ጋር ሲዋሃድ፣ ከዚህ ዐይነቱ ግኑኝነት ተጨፍልቆ የሚወጣው ለአዲስ ስልጣኔ መሰረት ይሆናል። በዚያው መጠንም የአስተሳሰብ አድማስ ይሰፋል። በረቀቀ መልክ ማሰብ ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ የአገራችንን የህብረተሰብ ታሪክ ስንመረመር፣ እስከተወሰነ ደረጃ እስካልሆነ ድረስ ከተለያዩ ቦታዎች ከመጡ ዕውቀቶች ጋር ያልተጋጨና ለመታደስም ያልቻለ በመሆኑ ሰፋ ያለ በተለያዩ ነገሮች የሚገለጽ ስራ ሊሰራ አልተቻለም። ሊታይ በሚቻልበት ቦታ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ሃይማኖትን ወይም ጎሳን  መሰረት ያደረጉ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በኦሮሞዎች ወረራ አማካይነት የነበሩት ቅሪቶች እንዳሉ ሊወድሙ ችለዋል ማለት ይቻላል።  በአስረኛው ክፍለ-ዘመን በዮዲት አማካይነት የአክሱሙ ስልጣኔ ከወደመ በኋላ ለመንስራራት ዕድል ያገኘው በአስራ-ህለተኛው ክፍለ-ዘመን ነው። ይህ ደግሞ ከውጭው ዓለም ተገልሎ የተደረገ እንቅስቃሴ በመሆኑ ከፍተኛ እምርታን ሊያገኝ በፍጹም አልቻለም። ይሁንና ቀስ በቀስ መታየት የቻለው በፊዩዳሉ ስርዓት ላይ የተመሰረተውና ሃይማኖትን እንደ ርዕዮተ-ዓለም የወሰደው ስርዓት በግራኝ መሀመድ ወረራ እንዳለ ይወድማል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ በቤተክርስቲያን አካባቢ የነበረው የተወሰነ እንቅስቃሴ ሊዳከመና ቤተክርስቲያናትም ሊፈራርሱ ችለዋል። የዮዲትም ሆነ የግራኝ መሀመድ አካሄድ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የኦሮሞዎች መስፋፋት ስልጣኔን ከማስፋፋት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ያለውን ከማፈራረስ ጋር በጥብቅ የተያያዘና፣ ካፈረሱም በኋላ በአዲስ መልክ ለመተካት የተደረገ ሙከራ አልነበረም። ይህም የሆነበት ምክንያት እነዚህ ከውስጥ የተነሱ ወራሪ ኃይሎች በሙሉ በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ ዕውቀት የሌላቸው በመሆናቸውና ጭንቅላታቸውም የዳበረ ባለመሆኑ ነው። ኑሮአቸውም በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረት የምርት ክንዋኔ ስላልነበር አስተሳሰባቸው በጣም ውስን ነበር።  ይህ ጉዳይ በአሁኑ በ21ኛው ክፍለ-ዘመንም የሚታይና ልክ እንደ ነቀርሳ በሽታ ከሰውነታችን ጋር የተዋሃደና አልላቀቅም ያለን ነው። ስለሆነም በተለይም ከአስረኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ ስንመረመር አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ሰፋ ባለ፣ በከተማዎችና በመንደሮች በስነስርዓት መገንባት፣ በዕደ-ጥበብ መዳበርና በንግድ እንቅስቃሴ የሚገለጽ ማህብረሰብ አልነበረም። በገጠርና በከተማ መሀከል ልዩነት አልነበረም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የአኗኗር ስልት ለፍልስፍናና ለሳይንስ ዕድገት የሚያመች አልነበረም።

በመጀመሪያ ደረጃ በፊዩዳሉ ስርዓት ላይ የተመሰረተው የአመራረት ስልት ሰፋ ላለ የስራ-ክፍፍል በሩን ክፍት አላደረገም። ለምሳሌ የአውሮፓውን የህብረተሰብ ታሪክ ላጠና፣ 1ኛ) የአውሮፓ ህብረተሰብ ከፊዩዳሉ ስርዓትና ከአንድ ጭፍን ሃይማኖት ሊላቀቅ የቻለው የግሪኩ ስልጣኔ መግባትና መስፋፋት ከቻለ በኋላ ነው። 2ኛ) የሩቅ-ንግድ የሚባለው የንግድ እንቅስቃሴ የፊዩዳሉን ስርዓት እንዲሰረሰር ወይም እንዲዳከም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማድረግ ችሏል። በዚህም አማካይነት ቀስ በቀስ መዳበር የቻለው የዕደ-ጥበብ እንቅስቃሴ ከንግዱ ጋር ሲያያዝና፣ በንግዱ ዘርፍ የተሰማራው አዲስ የፍጆታን አጠቃቀም ሲያስፋፋ በዚህ አማካይነት የፊዩዳሉ መደብ ሳይወድ በግድ አዲስ የፍጆታ አጠቃቀምን ይለምዳል። የፊዩዳሉ መደብም በገንዘብ የሚተመን ሀብት ስላልነበረው እየተስፋፋ የመጣውን አዲስ የፍጆታና ከሌላ አካባቢዎች የሚመጡ እንደ ቅመማ ቅመም የመሳሰሉና ከሀር የተሰሩ ልብሶችን ለመግዛትና ለመጠቀም ሲል የግዴታ ከነጋዴው መደብ ገንዘብን እንዲበደር ይገደዳል። ይህ ዐይነቱ ብድር ቀስ በቀስም የፊዩዳሉኑንም ሆነ የአሪስቶክራሲው መደብ በፖለቲካ መድረክ ላይ ያላቸውን የበላይነት ሊያዳክመው በቃ። በቁጥር አንድና ሁለት የተገለጹት ነገሮች አንድ ላይ ሲገናኙ ቀስ በቀስ የከተማዎች ዕድገት መታየት ቻሉ።  እንደነ ጋሊሊዬ ለመሳሰሉት ሳይንቲስቶች ለመመራመርና ለመፍጠር አመቺ ሁኔታዎችን ያገኛሉ። ይህ ዐይነቱ የምሁራዊ እንቅስቃሴ በመቀጣጠል ወደ ተሻለ ደረጃ ያድጋል። ተቀባይነትን በማግኘት አዳዲስ ደቀ-መዝሙሮች ይፈልቃሉ። እነዚህ ደግሞ ከተንቆራጠጠውና ለዕድገትና ለስልጣኔ እንቅፋት ከሆነው ስርዓት ጋር ይጋጫሉ። 3ኛ) በአውሮፓ የህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከአስራአምስተኛውና ከአስራስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት የተለመደ ባህል ነበር። በተለይም በ15ኛው ክፍለ-ዘመን የመጽሀፍ ማተሚያ መሳሪያ ጉተንበርግ በተባለው ጀርመናዊ ፈጣሪ ከተሰራ በኋላ መጽሀፎችን እየተረጎሙና እያባዙ ማስፋፋት የተለመደ ነበር። ስለሆነም ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ ማንኛውንም ለጭንቅላት መዳበር፣ ለምርምርና ለፈጠራ የሚያገለግሉ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መጽሀፎች እንደልብ ያገኙ ነበር። ኋላ ኋላ ላይ ትላልቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም የኢኮኖሚክስና የሶስይሎጂ ምሁራኖች የተማሩትን እንዳለ ቃል በቃል የሚሸመድዱ ሳይሆኑ የሚመራመሩ፣ ትክክል መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚጥሩና፣ አሻሽለውና አስፋፍተው የሚያቀርቡ ነበሩ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊዳብርና አዳዲስ ዕውቀቶችም ሊፈልቁ የቻሉት። ታሪክና የህብረተሰብ ዕድገትም ከሳይንስና ክፍልስፈና አንፃር የሚተረጎሙ እንጂ በጭፍኑ በጥቁርና በነጭ የሚጻፉ ወይም በጨቋኝና በተጨቋኝ እያሉ የሚተረጎሙ አልነበሩም። ይህ እያደና እየሰፋ የመጣው ምሁራዊ እንቅስቃሴ አንድን ህብረተሰብ በዘልማዳዊ ወይም ኋላ-ቀር በሆነ አገዛዝ ማስተዳደር እንደማይቻል ተገነዘበ። ስለሆነም የግዴታ በሁሉም አቅጣጫ ለውጥ መምጣት እንዳለበት በማመን ከነበረውና ለዕድገትና ለስልጣኔ እንቅፋት ከሆነው ኋላ-ቀር ስርዓት ጋር መጋጨት ጀመረ። ለውጥን የማይፈልገው የገዢ መደብና የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ ፈላስፋዎችንና ሳይንቲስቶችን ማሳደድና ማስር፤ እንዲሁም ደግሞ አንዳንዶችን እስከነህይወታቸው እንዲቃጠሉ እስከማድረግ ደረሱ። ይህም የሚያረጋግጠውና አንዳንዶችም ለማሳመን እንደሚሞክሩት የካፒታሊዝም ዕድገት በመፈቃቀድና በስምምነት ላይ ተመስርቶ የተገነባ ሳይሆን፣ የግጭትና የመገዳደል፣ የመጨረሻ መጨረሻም የማሰብ ኃይል የበላይነትን ሲይዝ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ለመሆን የቻለ ስልተ-ምርት ነው ማለት ነው። ከዚህ ውጭ የሚሰበኩ ሰበካዎች የተረት ተረቶች ናቸው።

ወደ አገራችን ስንመጣ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ድረስ በከተማዎች ዕድገት የሚገለጽ፣ በዕደ-ጥበብ መዳበር የሚታይ፣ በንግድ እንቅስቃሴ የሚገናኝ ህብረተሰብ፣ በስነ-ጽሁፍ መዳበር፣ ትችታዊ አመለካከት ባለውና ዕድገትን በሚፈልግ የሚገለጽ ማህበረሰብና አገዛዝ አልነበረም የሰፈነው። በሌላ አነጋገር፣ በሁሉም ዛሬ ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው ግዛት ውስጥ ቀደም ብለው የነበሩ በጎሳ መልክ ይኖሩ የነበሩትም ለአንድ ህብረ-ብሄር መመስረት የሚያመች የዕድገት እንቅስቃሴና መሰረት አልነበራቸውም። ይህ ዐይነቱ በተለያዩ ነገሮች ሊገለጽ የሚችል ዕድገት ለመኖር አለመቻሉና ባለመታወቁም የተነሳ በሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ ብሄረሰቦች በረቀቀ መልክ ለማሰብና በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የተሻለ ማህበረሰብ ለመገንባት አይችሉም ነበር ማለት ነው ። በተለይም ይኸኛው ወይም ያኛው ብሄረሰብ ተፈጥሮንና ኮስሞስን ሊቃኝ የሚችልበት እንደዚህ ዐይነት ፍልስፍና ነበረው ብሎ ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። ለምሳሌ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም በደቡቡ ክፍል የሚኖሩት ህዝቦች “ኦቡንቱ “ የሚባል ፍልስፍና ነበራቸው። በዚህም ፍልስፍና መሰረት ተፈጥሮንና ኮስሞስን ለመቃኘት ይችሉ ነበር። በአብዛኛዎችም ዘንድ በዕደ-ጥበብ ስራ የሚገለጽ ዕድገት ይታይ ነበር።  ይህ ኢቮሉሺነራዊ አካሄድ ግን በባርያ ንግድና የኋላ ኋላ ደግሞ በቅኝ-ግዛት አማካይነት እንዳለ ይወድማል። አፍሪካን ለመግዛት የመጡ የውጭ ኃይሎች ስልጣኔን ይዘው የመጡ ሳይሆን ያለውን ያወደሙና ተከታታይነትም እንዳይኖረው ያደረጉ ናቸው። የሌሎችን አፍሪካ አገሮችን ስልጣኔዎች ከእኛው ጋር ስናወዳድረው በተሻለ ደረጃ የሚገኙ ነበሩ ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው ከውጭ ከሚተበተብ ሴራ በስተቀር በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ሃይማኖትንና ጎሳን ተገን ያደረገ አገርንና ታሪክን አፍራሽ እንቅስቃሴ የማይታየው። በሌላ አነጋገር፣ በዛሬው ሁኔታም አብዛኛው የአፍሪካ ምሁር፣ ምሁር ነኝ ከሚለው ኢትዮጵያዊ በብዙ ነገሮች  በብዙ መቶ እጥፍ ይበልጣል። ስለሆነም ስነ-ጽሁፍም ሆነ ፍልስፍና ከእኛው አገር ጋር ሲወዳደር በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተሻለ መልክ የዳበረ ነው ማለት ይቻላል። ከአንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ጋር ሃሳብ ለሃሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ ከአንድ አፍሪካዊ ምሁር ጋር ተቀምጦ ለመከራከር በጣም ቀላል ነው። ሌላው አፍሪካዊ ምሁር ጥያቄ ለመጠየቅ የሚቃጣ ሲሆን፣ የእኛው ምሁር ደግሞ ጥያቄን ለመጠየቅም ሆነ ለመተቸት ዝግጁ አይደለም። እናውቀዋለን ብሎ የሚሸመጥጥና ሌሎች ለየት ያሉ አስተሳሰቦችን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ ነው። ስለሆነም በዕውቀትና በዕውቀት መሀከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት የማይፈልግ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የአገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ ስንመለከት  እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ምንም ዐይነት ዩኒቨርሲቲና ቤተ-መጻህፍትም አይታወቁም ነበር። በተለይም ተፈጥሮን ለመቃኘትና የኑሮን ትርጉም ለመረዳት የሚያስችል ዕውቀት አልነበረም ማለት ይቻላል።  በአንዳንድ አውሮፓ አገሮች ውስጥ ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ነው ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች መገንባትና ዕውቀትም መስፋፋት የጀመረው። በአገራችን ደግሞ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ  የተቋቋመው በ1950ዎቹ ዓመታት ውስጥ ሲሆን፣  በአውሮፓ ምድር ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙ ከአምስት መቶ ዓመት በኋላ ነው ማለት ነው። በመሀከላችን የ500 ዓመት ልዩነት አለ ማለት ነው። ይህ ልዩነት በራሱ ብዙ ነገሮችን ይነግረናል።

ለማንኛውም  በተለይም አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ከተመለሱ በኋላ የተቋቋሙት መሰረተ-ትምህርትቤቶች፣ መለስተኛ ትምህርትቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲስፋፉ እነዚህ ሁሉ የቱን ያህል ለዕድገትና ሰፋ ላለ ስልጣኔ ያመቻሉ ተብለው በምርምር የተቋቋሙ ሳይሆን በአቦ ሰጡኝ ነው የተቋቋሙት ማለት ይቻላል። በዩኒቨርሲቲ ደረጃም የሚሰጠው ትምህርት፣ ለምሳሌ በኢኮኖሚክስ፣ በሶስዮሎጂና በፖለቲካ ሳይንስ ዴፓርትሜንት ትችታዊ(Critical Thought) በሆነ መልክና በንፅፅር የሚሰጥ አይደለም። በኢኮኖሚክስም ሆነ በሶስዮሎጂ ዴፓርትሜንት ተማሪዎች የሚማሩት ትምህርት አንድ ወጥ ነው። የገበያ ኢኮኖሚ በአቅራቢና-በጠያቄ ህግ እንዴት እንደሚሰራ ከመማር በስተቀር ካፒታሊዝም እንዴት ለማደግ እንደቻለና፣ በምንስ ውስጣዊ ህግ እንደሚሰራና እንደሚንቀሳቀስ፣ ምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ እንደሚታየው ለምን ደግሞ በእኛ አገር በማሽን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የኢኮኖሚ ስርዓት ሊዳብር አልቻለም? ብለው ትችታዊ በሆነና ጥያቄን በሚያስነሳ መልክ አይማሩም። ለትችታዊ አመለካከት መዳበር የሚጠቅሙ በብዙ ምሁራን የተጻፉ የኢኮኖሚክስ ስራዎችና፣ እንዲሁም በማርክስ የተጻፈውና, በኤንግልስ የተጠናቀረውና የታከለበት በጣም አስፈላጊ ስራ ዳስ ካፒታል (Capital) በመባል የሚታወቀው ትልቅ ስራና እስካሁንም ድረስ ጊዜያዊነቱን ያላጣው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ አይሰጥም። ለምሳሌ በቶማስ ፒኬቲ(Thomas Piketty) በ2014 ዓ.ም ካፒታል በ21ኛው ክፍለ-ዘመን(Capital in the Tewnty-First Century) ተብሎ የተደረሰው ግሩም ስራ የሚያረጋግጥጠው የማርክስ መጽሀፍ አሁንም ቢሆን ጊዜያዊነቱን ያላጣ መሆኑን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዘመናዊነት የሚባለው ነገር በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአገራችን ምድር ሲገባ የፈጠረውን አዲስ የህብረተሰብ ግኑኘነትና አወቃቀር ከሶስዮሎጂ አንፃር ምርምር በማድረግ ተማሪዎች እንዲረዱት በትምህርት ደረጃ አይሰጥም። ስለሆነም በአገራችን ምድር የማህበረሰብ ምርምር(Social Research) የሚባል ነገር አይታወቅም። ታዲያ በእንደዚህ ዐይነት የተበላሸ የትምህርት አሰጣጥ የተማረ ተማሪ እንዴት ክሪቲካል በሆነ መልክ ሊያስብና ኤንተለጀንሱም ሊዳብር ይችላል? ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ስለኢንተለጀንስ መውደቅ የሚጽፉ አንዳንድ ምሁራን ለማየትና ለመመርመር የማይችሏቸው አያሌ ነገሮች አሉ ማለት ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን የየትምህርትቤቶችንም አሰራር ለተመለከተ ጥበባዊ በሆነ መልክ የተሰሩና የሚሰሩ አይደሉም። የታዳጊውን ትውልድ ጭንቅላት ለመሰብሰብና በረቀቀ መልክ እንዲያስብና ትዝታም እንዲሰማው ሆነው የሚሰሩ አይደሉም።  ከዚህም ባሻገር እስከአሁንም ድረስ የታዳጊውን ትውልድ መንፈስ ወይም አዕምሮ የሚቀርጽ አንድም ቤተ-መጻህፍት በየክፍለ-ሀገራት ዋና ከተማዎችና በየወረዳዎች ውስጥ አልነበረም፣ የለምም። ታዲያ በእንደዚህ ዐይነት እጅግ ወደ ኋላ በቀረ የትምህርት ስርዓት ውስጥና የማንበብ ልምድ ባልዳበረበት አገር  እንዴት አርቆ አሳቢና ፈጣሪ ትውልድ ማፍራት ይቻላል? አገር ወዳድና ለስልጣኔ ተቆርቋሪ የሆነን ትውልድስ መፍጠር ይቻላል ወይ? እንደሚታወቀው ሰብአዊነትና ብሄራዊ ስሜት ሊዳብሩ የሚችሉት አንድ ልጅ ከልጅነቱ ጀምሮ ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት የተኮተኮተ እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ጉዳይ በአውሮፓ ምድር ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተረጋገጠ ነገር ነው። ለማንኛውም በአገራችን ውስጥ ሰፋ ያለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት አለመታየቱ፣ ድህነት መስፋፋቱና የኋላ ኋላ አብዮት የሚባለው ነገር መከሰቱ ለብዙ መቶ ዓመታት ተንሰራፍቶ ከነበረው  ስርዓተ-ማህበር፣ የአመራረት ስልትና እጅግ ወደ ኋላ የቀረ የትምህርት ስርዓት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ጉዳይ‹ ነው። ስለሆነም በተለይም ከአብዮቱ መፈንዳት በኋላ የተፈጠሩት አስቸጋሪ ሁኔታዎችና እርስ በእርስ መገዳደሎች በቀጥታ ሊያያዙ የሚችሉት ከዕውቀት አለመስፋፋት፣ ወይም ደግሞ ከጭንቅላት አለመዳበርና ዞር ብሎ ለማየት ካለመቻል ጋር ነው። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው የተፈጠረውን ሁኔታ እንዳለ በጭፍኑ በተማሪው እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ማላከክ ወይም በማርክሲዝም ሌኒንዝም ላይ ማሳበብ ተገቢ አይደለም።

ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ምሁር ነኝ በሚለውና በፖለቲካ ውስጥ የተሳተፈውንና የሚሳተፈውን፣ በተለይም የብሄረሰብን አርማ ይዘው የሚያራግቡትን ጭንቅላት አስመልክቶ ከአባቶቻችን ጋር ሲወዳደሩ የእነዚህ ኤሊቶች ኢንተለጀንስ የቱን ያህል የወደቀ ለመሆኑ፣ ወይም ደግሞ የማሰብ ኃይላቸው በጣም ደካማ እንደሆነ የስነ-ልቦና ወይም የህሊና ሳይንስ ትምህርት በተማሩ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ችግሩን ለመረዳት ተሞኩሯል። በዚህ ዙሪያ የሚደረገው ምርምር አስፈላጊና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ጥሩ ቢሆንም፣ በሌሎቻችን ዘንድ የቱን ያህል ግንዛቤ ተሰጥቶት በጥልቀት ለመራመር ዕድል አግኝተን እንደሆን ወይም ፍላጎት ያለን ለመሆኑ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደሚታወቀው የጭንቅላትን ማደግ፣ ወይም ደግሞ የኢንተለጀንስ ማደግና የምሁራዊ አስተሳሰብን መዳበር አስመልክቶ በእዚህ ዙሪያ የተጠና ምርምር በአገራችን ምድር የለም። እስካሁን ድረስ ለጭንቅላት መዳበር አስፈላጊነትና ዕውቀትስ ማለት ምን ማለት ነው? በሚሉት ዙሪያ ይህን ያህልም ጥናትና ምርምር አልተደረገም። የአንድ አገር ዕድገት፣ የህዝቡም በሰላምና በደስታ መኖር የግዴታ ከአዕምሮ መዳበርና ከአርቆ-አሳቢነት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ዙሪያ አትኩሮ እስካልተሰጠ ድረስ በአገራችን ምድር መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት በፍጹም አይቻልም። አንድ አገርና ህዝብም የግዴታ የሚመሩበት ፍልስፍና ያስፈልጓቸዋል። ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አቅጣጫ የሚሰጠው መመሪያ ማዳበርና ታዳጊውንም ትውልድ ማስተማር የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

ለማንኛውም ቢያንስ ያለፉትን አርባ ዓመታት ያስቆጠረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታሪክ ለተመለከተ አብዛኛዎቻችን በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንሳተፋለን የምንል የምናካሂደው ትግል ከዕውቀት ጋር የተያያዘ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ፍልስፍናዊ መሰረቱ ምን እንደሆነ በፍጹም አይታወቅም። በአብዛኛዎቻችንም ዕምነት ፖለቲካ የሚባለው የአንድን ህብረተሰብ ዕድል የሚወሰን ትልቅ ነገር የግዴታ ከዕውቀት ጋር መያያዝ እንደሌለበት ነው። ይህንን ትተን በአገራችን ውስጥ ያለውን በምሁሩ ዘንድ የተከሰተውንና የሚታየውን የኢንተለጀንስ መውደቅ የሚጽፉ ምሁራን እንደተከታተልኩት ከሆነ በኢንተለጀንስና በምሁራዊ ዕድገት(Intellectual Development) መሀከል ያለውን ልዩነት በሚገባ አያሳዩም። ለምሳሌ አንድ ሰው በተወሰነ ነገር ላይ ኢንተለጀንት ሊሆን ይችላል። ይሁንና በየጊዜው የማያነብና ጭንቅላቱን ለልዩ ልዩ ዕውቀቶች ክፍት የማያደርግ ከሆነ የማሰብ ኃይሉ ሊጠብ ይችላል። ስለዚህም ኢንተለጀንስ በደንብ ሊቀረጽና የማሰብ ኃይልም ሊዳብር የሚችለው የዕውቀትን ምንነት መረዳት ሲቻልና፣ የአንድ ሰው ወይም የብዙ ሰዎች ጭንቅላት በትክክለኛው ዕውቀት ሲኮተኮት ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን በምሁሮች ዘንድ የሚታየውን የኢንተለጀንስ መውደቅ አስታከው የሚጽፉ አንዳንድ ምሁራን በግሪኩ ስልጣኔም ሆነ በኋላ ላይ በአውሮፓ ምድር ፍስልፍና ቀስ በቀስ እያለ መዳበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በፍልስፍናና በአጠቃላይ ዕውቀት ዙሪያ ይካሄድ የነበረውን ክርክር ያካተተ አይደለም። በተለይም ዕውቀት ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው የሚገኘው? በሚለው ዙሪያ በሶክራተስና በፕሌቶ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሶፊስቶች መሀከልና፣ በኋላ ላይ ኤምፕሪሲዝም ወይም ፖዘቲቭ ሳይንስ የሚባለውን የዕውቀት ዘርፍና፣ ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ምድር፣ በተለይም በእንግሊዝ አገር የተስፋፋውንና ይደረግ የነበረውን ክርክር ያካተተ አይደለም። ከዚያም ባሻገር በነገሮች መሀክል መያያዝ እንዳለና፣ በሌላ ወገን ደግሞ አንድን ነገር ነጥለው በመውሰድ ያንን መነሻ በማድረግ የሚሰጥ ሀተታ መሀከል ይደረግ የነበረውንና፣ አሁንም የሚደረገውን ክርክር በደንብ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም። ስለሆነም በኖርማቲቭና በራሽናል ሳይንስ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በኤምፕሪሲስት ወይም በፖዘቲቭ ሳይንስ መሀከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ሙከራ አይደረግም። በአሁኑ ዘመንም ኳንተም ፊዚክስ በመባል የሚታወቀውንና፣ ማንኛውም ነገር ከጥቃቅን ነገሮች የሚሰራና፣ አንደኛው በሌላው ላይ ተፅዕኖ እንዳለውና፣ በተለይም የአዕምሮን ወይም የመንፈስን የበላይነት የሚያሳየውን የዕውቀት ዘርፍ በደንብ ለማመልከት ጥረት አይደረግም። ሌላውና በደንብ ግንዛቤ ውስጥ ያልገባው ነገር ደግሞ፣ እነዚህ ተንታኞች በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ውጭ ባለው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ስለሚታየው  የኢንተለጀንስ መውደቅ ጉዳይ በሚጽፉበት ጊዜ የኢንተለጀንስ መዳበርና መውደቅ ከማቴሪያል ሁኔታዎች፣ በአንድ አካባቢ ከሰፈኑ የአሰራር ስልቶችና የሰው በሰው ግኑኝነቶች፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እያያዙ የኢንተለጀንስን ማደግና መውደቅ ለማሳየት በፍጹም አይጥሩም። በተጨማሪም የእያንዳንዱ ግለሰብ ጥረት ማድረግና ለማድረግ አለመሞከር ለጭንቅላት መዳበርና ሰፋ ባለ መልክ ለማሰብም ሆነ ለማሰብ አለመቻል ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት በግልጽ አይቀመጥም። በህሊና-ሳይንስም ሆነ በፍልስፍና እንደተረጋገጠው የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል በሙሉ በአንድ አገር ውስጥ በሰፈኑ የማቴሪያል ሁኔታዎች፣ የዕውቀት ጉዳይ፣ እያንዳዱ ታዳጊ ትውልድ ያደገበት ቤተሰብና የማቴሪያልና የዕውቀት ደረጃ፣ በአሁኑ ዘመን ደግሞ የሚዲያ ሁኔታ፣ እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ በመደመር የሰውን ኢንተለጀንስ በመቅረጽና ምሁራዊ አስተሳሰብን በማዳበር የየራሳቸውን ድርሻ ይጫወታሉ። ከዚህም በላይ ከልጅነቱ ጊዜ ጀምሮ የመጽሀፍ ማንበብን ልምድ ካላዳበረው፣ ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ቤተመጻህፍት በማይገኝበት ያደገና፣ የለጋ ዕድሜውን ባልባሌ ነገሮች ላይ ያሳለፈ ወጣት በአንድ ነገር ላይ ኢንተለጀንት ቢሆንም፣ ወይም አንድን ነገር የመቀበል ኃይሉ ከፍ ያለ ቢሆንም ያ ዕውቀት እንዴት እንደፈለቀና በነገሮች መሀከል መተሳሰርና አንደኛው በሌላኛው ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመረዳት የማይችል ከሆነ እንደዚህ ዐይነቱ ወጣት ከፍተኛ ምሁራዊ ግንዛቤ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችን ምድርና ውጭ በሚኖረውም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ለኢንተለጀንስ መውደቅና ለምሁራዊ ዕድገት አለመዳበር ዋናው ምክንያት አሁንም ቢሆን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትራዲሽናል በሆነ መልክ የሚያስብ ነው። ከሚኖርበት አካባቢና አብሮ ከሚውላቸው ጓደኞቹ ወጣ በማለትና ከሌላው ጋር በመገናኘት አዳዲስ ነገሮችን ለመማር በፍጹም አይፈልግም። አብዛኛውም በየሰሚናሮች ውስጥ አይሳተፍም፤ ፍላጎትም የለውም። አብዛኛዎቻችን ዘመናዊ የሚባሉ ነገሮችን እየተጠቀምን አስተሳሰባችን ከምንጠቀምባቸው ዘመናዊ ከሚባሉ ነገሮች ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም። ስለሆነም ኑሮአችንና አስተሳሰባችን እዚያው በዚያው የሚሽከረከሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

የኢንተለጀንስን መውደቅ በእኛ አገር ብቻ የሚታይ ሳይሆን በራሳቸው አደጉ ወይም ሰለጠኑ በሚባሉ የካፒታሊስት አገሮችም አፍጦ አግጦ የሚታይ ነገር ነው። ስታትስቲክሶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በኢንዱስትሪ ወይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የሰው የማሰብ ኃይል ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ25% ቀንሷል። ለዚህ ምክንያት የሚሰጡት ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ ከመጽሀፍ ማንበብ ጋር ያለው ግኑኝነት መቀነሱ፣ በከፍተኛ ደረጃ አሰልቺ በሆኑ ስራዎች በመጠመዱና ለማንበብ ጊዜ አለማግኘት፣ አብዛኛው ወደ ፍጆታ አጠቃቀም ነገሮች ላይ ማድላቱ፣ ይህንን ሁኔታ የሚያበረታቱ ትላልቅ የገበያ አዳራሾች በየቦታው መስፋፋታቸው፣ እንደ ሶሻል ሚዲያ የመሳሰሉት መስፋፋትና፣ አብዛኛውም ከስማርትፎን ጋር ፍቅረኛ መሆኑና፣ እንደ ፋስት ፉድ የመሳሰሉ ለጭንቅላት መዳበር የማያመቹ አመጋገቦች መስፋፋትና ሌሎችም እንደ ዋና ምክንያቶች የሚወሰዱ ናቸው። የኢንተለጀንስ መቀነስ ደግሞ በአመጽ መስፋፋት የሚገለጽ፣ የቀኝ አስተሳሰብ ስር መስደድ፣ አብዛኛው ህዝብ በትክክለኛው አነጋገርና በተሳሳተ ትረካ መሀክል ያለውን ልዩነት አለመረዳት፣ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያደላ ቀኖናዊ አስተሳሰብ የሚመስል መስፋፋትና ለሌሎች አመለካከቶች ራስን ክፍት አለማድረግ፣ የእኛው ብቻ ትክክል ነው ማለት፣ የሌሎች አገሮችን ታሪክ በተነፃፃሪ ጥናት ለመመርመር አለመሞከር፣ የራስንም የካፒታሊዝምን የውጣ ውረድ ዕድገትና ለዕድገት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ለመረዳት አለመቻል፣ በተለይም በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጥንታዊ ዕውቀቶችንና ለስልጣኔ መሰረት የሆኑ፣ አሁንም ቢሆን በጣም አስፈላጊና ዘለዓለማዊነት ያላቸው ዕውቀቶች  በተለይም ታዳጊው ትውልድ እንዳይማራቸው ማድረግ…ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለኢንተለጀንስ መውደቅና ለምሁራዊነት አለመዳበር ከፍተኛ ሚና ያላቸው ነገሮች ናቸው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ አምባገነናዊ አገዛዞች መስፋፋታቸውና ጭቆና መብዛቱ፣ ህዝቦቹም እንዲፈናቀሉ መደረጋቸው፣ በአገሮች መሀከል ያለውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በጦርነት ለመፍታት መሞከር፣ ለዚህ ሲባል ደግሞ የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን መስራትና የዓለምን ህዝብ ማስፈራራት፣ እነዚህ ሁሉ ከኢንተለጀንስ መውደቅ ጋር የሚያያዙ ናቸው። የካፒታሊዝም ዕድገት በቀጥታ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጭንቅላት ምርምር ውጤቶች ቢሆንም ቴክኖሎጂን የሚቆጣጠሩ ኃይሎችና መንግስታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭቆናን እያስፋፉና በየአገሮች ውስጥም ሰፋ ያለ ምሁራዊ አስተሳሰብ እንዳይዳብር እንቅፋት እየሆኑ መምጣታቸውን እንመልከታለን። በሌላ አነጋገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የግሎባል ካፒታሊዝም መስፋፋት የግዴታ ለአምባገነናዊና ፈሺሽታዊ ስርዓቶች መነሳት ምክንያት የሆነና፣ ይህንንም የሚደግፍ ነው። ምክንያቱም ፋሺሽታዊ አገዛዞችን ተገን በማድረግ ነው በሶስተኛው ዓለም አገሮች ያሉ የጥሬ-ሀብቶችን ለመቀራመት የሚችለው። ሰለሆነም ግሎባል ካፒታሊዝም በተለይም በሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የነቃና የአወቀ፣ እንዲሁም የተገለጸለት የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳብር በፍጹም አይፈልግም።

ወደ አገራችን ስንመጣ የኢንተለጀንስ ጉዳይ መውደቅ ወይም በደንብ አለመዳበር ቀደም ብዬ በተነተንኩት መሰረት የሚገለጽ ሲሆን፣ በተለይም ከአብዮቱ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የሚታዩት ዘግናኝ ነገሮችና በንዑስ ከበርቴው የሚፈጸሙት ፋሺስታዊ ድርጊቶች በሙሉ ዋናው ምክንያቶቻቸው ጭንቅላት አስፈላጊውን ዴየት ወይም ጭንቅላትን የሚያዳብርና ሰብዓዊ የሚያደርግ ዕውቀት ለመስፋፋት ያለመቻሉ ነው።  የ1950ዎቹ ጀምሮ በዘመናዊነት ስም ተግባራዊ የሆኑትን ነገሮች ለተከታተለና የአሁኑንም ሁኔታ ላጠና አብዛኛው መጥፎ ድርጊቶች በሙሉ የተፈጸሙትና የሚፈጸሙት ካልተማረውና ፊዩዳል እየተባለ ከሚወነጀለው የህብረተሰብ ክፍል ሳይሆን በተራ አካዴሚክስ ዕውቀት በሰለጠነው፣ ከኢኮኖሚክስ አንስቶ እስከ ሚሊተሪውና እስከ ፀጥታና ፖሊስ በመሳሰሉ ኃይሎች አማካይነት ነው። ስልጣንንም የሚጨብጡ፣ ወይም የጠቅላይ ሚኒሰተርነትን ደረጃ የደረሱ ግለሰቦችና ሚኒስተሮች ከታች ወደ ላይ መንደሮችን በመገንባት፣ የስራ-ክፍፍል በማዳበርና፣ ስራቸውንና ዕውቀታቸውን እያረጋገጡ የመጡ ሳይሆን ከጫካ ትግል በኋላ ሰተት ብለው ወደ ቤተ-መንግስት በገቡና እብዛኛውን ዕድሜያቸውን ሰውን በመግደልና ተንኮል በመስራት ያሳለፉ ናቸው። ስለሆነም ከእነዚህ ሰዎች ፍትሃዊነትንና ዲሞክራሲያዊ አገር ግንባታን መጠበቅ አላዋቂነት ነው። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ሃያና ሰላሳ ዓመታት ያህል የተለማመዱትንና ተግባራዊ ያደርጉ የነበሩ መጥፎ ስራዎችን ወይም ተንኮሎችን በሙሉ ነው ወደ ፖለቲካ ለመተርጎም የሚሞክሩት። ስለሆነም ሰለ ሰው ልጅ ምንነትና ታሪክ ሰሪነት፣ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስና በምን ዘዴ ነው ቀስ በቀስ ከታች ወደላይ ሊገነባ የሚችለው? የትኛውስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ሰፋ ላለ የምርት እንቅስቃሴ የሚያገለግለው? ሳይንስና ቴክኖሎጂስ በኢኮኖሚና በህብረተሰብ ዕድገት ውስጥ ያላቸው ወይም የሚኖራቸው ሚና እንዴት ይታያል? እያሉ የሚጠይቁና፣ አንድ አገርና ህብረተሰብ በፀና መሰረት ላይ ሊቆሙ ወይም ሊገነቡ የሚችሉበትን ሁኔታዎች የማመቻች ኃይልና ዕውቀት በፍጹም ያላቸው አይደሉም። ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ነገር በእነዚህ ዐይነት መሪዎች ጭንቅላት ውስጥ አይታወቅም። ፖለቲካን የሚረዱት ተራ የተንኮል መስሪያ መሳሪያና አገርን ማከረባበቻ አድርገው ነው። በዚህ መልክ የሚካሄድ ፖለቲካ ደግሞ ፖለቲካ አይደለም። ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን ችግርን ፈጣሪ ሳይሆን ችግርን ፈቺ ነው። ፖለቲካን ወደ ሴራነት ወይም ወደ ተንኮል የሚለውጡ  ሰዎች በመሰረቱ ጭንቅላታቸው የታመመና በፖለቲካው መድረክ ውስጥ መሳተፍ የሌላባቸውና የኃላፊነት ቦታ የሚሰጣቸው መሆን አይገባም። ፖለቲካ ዕውቀትን፣ ንጹህነትን፣ ዲሲፕሊንና ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት መቀበልንና የሞራል ብቃትነትን የሚጠይቅና የሚያካትት እንደመሆኑ መጠን፣ እነዚህንና ሌሎች የሞራልና የስነ-ምግባር ጉዳዮችን ሊያሟላ የማይችልና ራሱን እንደ አገልጋይ ሳይሆን እንደ ባለስልጣን የሚቆጥር በፖለቲካ ዙሪያ ዝር ማለት የለበትም። ባጭሩ በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ጭንቅላት በሚገባ አለመኮትኮቱና በትክክለኛው ዕውቀት ያለመቀረጹ ነው።

ይህንን ጉዳይ ትተን ኢትዮጵያን እንደ ህብረ-ብሄር( Nation-State) አድርጎ ለመገንባት የተወሰደውን እርምጃ ስንመለከት በመሰረቱ ይህ ሂደት ሊጠናቀቅ ያልቻለው ከላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት በተለይም የሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት በምሁራዊ እንቅስቃሴና በስራ-ክፍፍል ለመዳበር አለመቻሉና፣ ከአካባቢው ባሻገር አርቆ የሚያስብና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተንቀሳቀስ በመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ውስጥ ሊሳተፍ የሚችል የተገለጸለት የከበርቴ መደብ ሊፈጠር  ባለመቻሉ ነው። በሌላ አነጋገር፣ እስከ 1950ዎቹ መግቢያ ድረስ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ የከበርቴ መደብ ያልተፈጠረበትና ምንም ዐይነት ምህራዊ ወይም ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ እንቅስቃሴ ያልነበረበት አካባቢ ነበር ብሎ አፍን ሞልት መናገር ይቻላል። ወደ ሌሎች ግዛቶችም ስንመጣ ዛሬ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ይኖሩ የነበሩ ነገስታትና ህዝቦች እንደዚሁ በደንብ የተደራጀ ማህበረሰብ አልነበራቸውም። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የኋላ ኋላ እየተስፋፋ የመጣው የኦሮሞ ጎሳ በከፍተኛ ደረጃ በዝቅተኛ የአኗኗር ስልት የሚገለጽ፣ ምንም ዐይነት ምሁራዊ መሰረት የሌለውና፣ በምንም ዐይነት የስራ ክፍፍል የሚገለጽ ስላልነበር ሂደቱ በሙሉ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ ውድመትን ነበር። ሌሎችን እየጠራረገና እያባረረ፣ አሊያም ደግሞ እየጨፈለቀ የሚኖር ነበር ማለት ይቻላል። ከእንደዚህ ዐይነቱ ጎሳ የወጡ የኦሮሞ ኤሊቶች በመባል የሚታወቁ የኋላ ኋላ ከአስኳላ ትምህርት ጋር ሲጋጩ ቀድሞውኑ ጭንቅላታቸውን የሚያዳብር ዕውቀት ስላልቀመሱ በጥራዝ-ነጠቅነት መንፈስ በመወጠር አስቸጋሪ ሁኔታን ወደ መፍጠር ነው ያመሩት። በተለይም ከፕሮቴስታንት ሃይማኖት ጋር፣ ይህንን ተገን አድርገው በተለይም ከጀርመን የሄዱ የሃይማኖት ሰዎች ጋር በመተዋወቃቸው ልዩ ዐይነት ስነ-ልቦና ወይም ፀረ-ኢትዮጵያ ስሜት፣ በመሰረቱ ፀረ-ህዝብና ፀረ ስልጣኔ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የሆነ ፀረ-ጥቁር ስሜትን በጭንቅላታቸው ውስጥ ሊቀርጹ ችለዋል። የውጭ ኃይሎችም ዋና ዓላማ እንደነዚህ ዐይነት ጨቅላ አስተሳሰብ ያላቸውን የጎሳ ኤሊቶች በመመልመልና እነሱን ይጠቅሙ ይመስል በመስበክ ወይም ማኒፑሌት በማድረግ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያስተናግድ የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚና አገር እንዳይገነባ ለማድረግ ነው። በጥራዝ-ነጠቅ አስተሳሰብ መንፈሳቸው የተቀረጸው የኦሮሞ ኤሊቶችና ይህንን ዐይነቱን የፈረንጆችን ሴራ ለመረዳት የማይፈልጉና የማይገባቸውም ትክክለኛ ዕውቀትን መገንባት ሳይሆን የያዙት ፈሊጥ የፈረንጆች መጫወቻ በመሆን የተሳሳተ ትረካን ማራገብ ነው። ይህ ዐይነት መጃጃልና የፈረንጆች መጫወቻ በመሆን አንድን አገር ከውስጥ ለማዳከም መጣር በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም። ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ እነዚህ ኢሊት ነን የሚሉ የኦሮሞ ተወላጆች ማንኛውም ሰው ሊኖረው የሚገባውን ባህርይ በጭንቅላታቸው ውስጥ ለማዳበር በፍጹም አልቻሉም። አንድ የተማረም ሆነ ያልተማረ ሰው ሊኖረው የሚገባው ባህርዮች፣ ለምሳሌ አርቆ-አሳቢነት፣ ማስተዋል፣ ወደ ኋላ መለስ ብሎ የታሪክን ሂደት መመርመር፣ መጸጸት፣ ለሌላ ሰው ማሰብ፣ መሳቅና ማልቀስ እንዲሁም ልዩ ልዩ የሰው ልጅ ባህርዮች ከጭንቅላታቸው ውስጥ ያልተቀረጹና በልባቸውም ውስጥ የሌሉ ናቸው። ለዚህ ነው በተሳሳተ ወይም በአጉል ትረካ፣ አሊያም በህብረተሰብ ሳይንስ ሊረጋግጥ በማይችል ትረካ የሰውን ልብ የሚያደርቁትና ወርቃማ ጊዜን የሚያባክኑት። ለዚህም ነው አረመኔዎች ለመሆን የበቁትና በኋላ-ቀር አስተሳሰብ በመጠመድ ኢትዮጵያን እንዳለች ለማውደም የሚቅበዘበዙት። በሌላ ወገን ደግሞ በእነሱ አስተሳሰብ ሌላውን በተለይም አማራውን እንዳለ በመጠራረግ ወይም በመግደል ተደላድለው ኦሮሚያ የምትባል አገርን  ለመመስረት የሚችሉ መስሏቸዋል። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸውም የሚያረጋግጠው የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ ያልተረዱ መሆናቸውን ነው። ተፈጥሮም ሆነ ማንኛውም ህብረተሰብ ሊኖሩ የሚችሉት በአንድ ወጥ ነገርና በአንድ ወጥ አስተሳሰብ ብቻ አይደለም። ተፈጥሮንና ህብረተሰብ ቆንጆ ናቸው የሚያሰኛቸው የልዩ ልዩ ነገሮች ውጤቶች በመሆናቸው ነው።

ወደ ትግሬም ስንመጣ ያለው ችግር ከዚህ የባሰ ነው። ትግሬ የሚባለው ክልል ቀድሞ የስልጣኔ ምንጭ ለመሆኑ ይታወቃል። ይሁንና በታሪክ ሂደት ውስጥና በተፈጥሮ አቀማመጥ የተነሳና፣ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ለመዋሃድ ባለመቻሉ ልዩ ዐይነት የሆነ በጣም አደገኛ ስነ-ልቦና ያዳበረ ነው። ይህ ዐይነቱ ስነ-ልቦና የግሪክ ፈላስፎች እንደሚሉት በበላይነት ስሜትና በድንቁርና የሚገለጽ ሲሆን፣ ከተሳሳተ ዕውቀት ጋር ሲጋጭ አንድን ህብረተሰብ እንዳለ የሚያናጋና ለስልጣኔም እንቅፋት የሚሆን ነው። ወያኔ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት የተወሰነውን የትግሬ ኤሊትና ታዳጊውን ትውልድ በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላቱን በመበወዙ የተነሳ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ አገሪቱን እንዳለ ወደ ብልግና ኢንዱስትሪ የቀየረና የፈረንጆችም መጫወቻ ያደረገ ነው። በአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ያሰማራቸው የትግሬ ተወላጆች አስተሳሰባቸው የተጨናገፈ በመሆኑ ዋና ዓላማቸው ራስን ማደለብና በማቴሪያል ሁኔታ ከሌላው ሻል ብሎ መገኘት ነው። ካድሬዎችም እንደሚሉት የተቀረውን የኢትዮጵያ ግዛት የሚፈልጉት ለመበዝበዝና ትርፍ ለማካበት ብቻ ስለሆነ በየቦታው ያሉ ስትራቴጂክ የጥሬ-ሀብቶችን መቆጣጠርና በአጭር ጊዜ ውስጥ መክበር ነው። በሌላ አነጋገር፣ የሰለጠነ፣ የተማረና አገርንና ህዝብን የሚያስከብር የህብረተሰብ ክፍል እንዳይዳብርና ተከታታይነት ያለው ስራ እንዳይሰራ መንገዱን ሁሉ መዝጋት ነው ዋና ዓላማቸው። ከዚህ ዐይነቱ ሰንካላ አስተሳሰብ ስንነሳ ወያኔና ተከታዮቹ በተለይም ፀረ-አማራ ስሜት ማዳበራቸውና ፋሺስታዊ ድርጊቶችን መፈጸማቸው የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ስንትና ስንት ወንጀሎች እንደፈጸመ ይታወቃል። ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላም ስንትና ስንት አሻጥር እንደሰራና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ  በተለይም በአማራውና በአፋሩ ወገናችን ላይ አጠቃላይ ጦርነት እንዳወጀና፣ ለብዙ ሺሆች ወገኖቻችን ማለቅ ተጠያቂ ለመሆን በቅቷል። ለጭንቅላት የሚዘገንኑ፣ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን መደረግ የለባችውም የሚባሉ አሳዛኝ ድርጊቶችን በሙሉ ፈጽሟል። በዚህ ዐይነት ድርጊቱም አነሰም በዛም ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የትግሬ ኤሊትና ህዝብ ተባባሪው ነው። የወያኔን ዘግናኝ ድርጊት በግልጽ ያወገዘ በጣት የሚቆጠር ነው፤ ወይም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ታዲያ በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ከእንደዚህ ዐይነቱ አስችጋሪ ብሄረሰብና ኢሌት፣ እንዲሁም ለስልጣኔና ተስማምቶ ለመኖር ከማይችል ጎሳ ጋር አብሮ መኖር ይቻላል? ይህ ጉዳይ የግዴታ በቂ ምርምር የሚያስፈልገው ነው። ዝም ብሎ በይሉኝታ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። አንድ ኤሊትና ህዝብ በበላይነት ስሜት የሚወጠርና አስቸጋሪ እስከሆነ ድረስ፣ በተለይም ደግሞ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ወይም የእነሱ ተላላኪ በመሆን ጦርነትን የሚያውጅ እስከሆነ ድረስ ከእንደዚህ ዐይነት እልክ አስጨራሽና ጠማማ ጭንቅላት ካለው ኤሊት ጋር  ምንም ነገር መስራት አይቻልም። ስለሆነም የትግራይ ክልል በሚሊታሪ መፈታትና፣ ከተፈታም በኋላ ወደ መገንጠል ማምራት ያለበት ጉዳይ ነው። ከአመጸኛና ከገዳይ ጋር አንድ ላይ በመሆን ምንም ዐይነት ታሪካዊ ስራ መስራት በፍጹም አይቻልም።  አንድን አገር መገንባት የሚቻለው ከሰለጠነ ሰው ጋር፣ ትችትን ከሚቀበልና በክርክር ከሚያምን ጋር ብቻ ነው። ምንም ዐይነት ዕውቀት ሳይኖረው አውቃለሁ፣ ስልጣን ይገባኛል ከሚል ደንቆሮ ኃይል ጋር ሰለህብረተሰብ ግንባታ ማሰብ በፍጹም አይቻልም።

 

የአቢይ አገዛዝ በዘመናዊ ፖለቲካ መነፅር ሲመረመር!

    

በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ዘመናዊነትን(Modernization) አስመልክቶ የተደረገ ጥናትና ክርክር በፍጹም ያለመኖሩ ነው። የኢትዮጵያን አጠቃላዩን የህብረተሰብ አወቃቀርና የህዝባችንንም አኗኗር ሁኔታ ስንመለከት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ የሚሆኑት ነገሮች በሙሉ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት የሚሰሩት ከተማዎችና መንደሮች፣ እንዲሁም ቤቶች በሙሉ የተወሰኑ የጄኦሜትሪ ቅርጾችን ተከትለው፣ የሰውንም የማሰብ ኃይል ለማሳደግ እንዲችሉ ሆነውና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንዲያስተናግዱ ተብለው የሚሰሩ አይደሉም። የመንገዶችም አሰራር በእግራቸው ለሚጓዙና በዕድሜያቸው ገፋ ላሉ ሰዎችና ልጆች ለአደጋ ሳይጋለጡ ሊንቅሳቀሱ  እንዲችሉ ሆነው የሚሰሩ አይደሉም። በየቦታው እዚህና እዚያ የሚከፈቱት ቡና ቤቶችና ሻይቤቶችም በተለይም የታዳጊውን ልጅ አዕምሮ ለመሰብሰብና አትኩሮውንም ለማሳደግ ተብለው የሚሰሩ አይደሉም። ስለሆነም የከተማዎችና የመንገዶች አሰራር የሰውን መንፈስ የመረበሽ ኃይላቸው ከፍ ያለ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ ዘመናዊነት የሚባለው ነገር ወደ አገራችን ሰተት ብሎ ሲገባ በአቦ ሰጡኝ የገባ እንጂ ተጠንቶና ተብላልቶ ያልገባ መሆኑን ነው የሚያመለከተው።

በአውሮፓ ምድር ውስጥ ዘመናዊነትን አስመልክቶ ብዙ ጥናቶች ተካሂደዋል። በአጠቃላይ ሲታይ ዘመናዊነትን አስመልክቶ ከአዎንታዊና ከአሉታዊ ጎኑ አንፃር አያሌ መጽሀፎችም ተጽፈዋል። እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ በዘመናዊነት ስም የሚካሄዱት ክንዋኔዎች በሙሉ አብዛኛውን ጊዜ በጠቅላላው ህዝብ የሚወሰኑ ስላልሆኑና፣ በኃይል አሰላለፍም የሚደነገጉ በመሆናቸው በየጊዜው ብቅ ብቅ ያሉ ምሁራንና ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው የዘመናዊነትን ትርጉም፣ በግለሰቦች ባህርይና በጠቅላላው በአንድ ህዝብ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመመርመርና ለማጥናት ተገደዋል። ይህም የሚያረጋግጠው በአውሮፓ የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑት ነገሮች በሙሉ ዝምብለው በአቦሰጡኝ ሳይሆን ከብዙ አኳያ በመመርመር ነው። ከዚህ ስንነሳ የዘመናዊነት ትርጉም አያሌ ነገሮችን ያካተተ ነው። ይህም ማለት አንድን ህብረተሰብ የሚመለከቱ ነገሮች በሙሉ የሚያካትት ነው ማለት ይቻላል።

የዘመናዊነት አስተሳሰብ በቀጥታ ከመንፈስ ተሃድሶ፣ ወይም ኮስሞስንና ተፈጥሮን ከመቃኘት ጋር፣ እንዲሁም የሰው ልጅ በምድር ላይ ሊኖረው የሚችለውን ሚና፣ እንዲሁም ከየት እንደመጣ፣ ለምን በዚህች ዓለም ላይ እንደሚኖርና፣ ምንስ ማድረግ አንዳለበትና ወዴትስ እንደሚጓዝ ከሚለው ፍልስፍናዊ አስተሳሰብና ጥያቄዎች ጋር በመያያዝ በጭንቅላት ክንዋኔ የተፈጠረ አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ ጭንቅላትን ማዕከላዊ ያላደረገ፣ ከሳይንስና ከፍልስፍና ምርምር ጋር ያልተያያዘ ህብረተሰብአዊ መሻሻል ወይም ዘመናዊነት ሊኖር አይችልም ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ በፍልስፍና አስተሳሰብ ዘመናዊነት መንፈሳዊና የማቴሪያል ሁኔታዎችን የሚያካትትና ሚዛኑን ጠብቆ መጓዝ ያለበት ነው ማለት ነው።

ዘመናዊነት በጤናማ መልኩና ተስተካክሎ ተግባራዊ እንዲሆን ከተፈለገ የግዴታ የፖለቲካ ሞደርናይዜሽን ያስፈልጋል። የፖለቲካ ዘመናዊነት ደግሞ ከመንግስት መኪና አወቃቀር፣ ከተቋማት ግንባታ ጋርና በጥብቅ የሚያያዝና፣ የመንግስትን መኪና የሚጨብጡ ሰዎችን የሞራልና የዕውቀት ብቃት የሚመለከት ነው። በሌላ አነጋገር፣ መንፈሳቸው ሳይታደስ፣ በጥሩ ዕውቀት ጭንቅላታቸው ሳይኮተኮት፣ አርቆ-የማሰብ ኃይላቸው በደንብ ሳይዳብር ዝም ብለው ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የግዴታ ጭቆናንና ብዝበዛን ነው የሚያመጡት። ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮችም ሚዛናዊነታቸውን ያልጠበቁና በስርዓትም የማይገነቡ ስለሚሆኑ አንድን ህብረተሰብ ግራ የማጋባት ኃይላቸው ከፍ ይላል ማለት ነው። ስለዚህ ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ የፖለቲካን ቲዎሪ አስመልክቶ ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ እስከ 18ኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያም በኋላ ከፍተኛ ምርምር የተደረገውና፣ ሁለ-ገብ ስልጣኔን በሚፈልጉና፣ በሌላ ወገን ደግሞ የያዙትን ቦታ ላለማጣት በሚፈልጉት ኃይሎች መሀከል ከፍተኛ ትግል ብቻ ሳይሆን ወደ ጦርነትም ያመራ ትግል የተካሄደው። ይህም ማለት ለአንድ አገር የተሟላ ዕድገት የግዴታ የፖለቲካው መስክ መስተካከል አለበት፤ በነቁና በተማሩ፣ እንዲሁም በተገለጸላቸውና የስልጣኔን ትርጉም በተረዱ ሰዎች መያዝ አለበት። ከዚህ በመነሳት ግልጽ የሆኑና ዲሞክራሲያዊ ይዘት ያላቸው፣ ለህዝብ የሚያገለግሉና ህዝብንም ሊያሳትፉ የሚችሉ ተቋማት በየቦታው መተከል አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እያለ እየተያያዘና እየተሻሻለ ሊመጣና የህዝብን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ሁለ-ገብ ዕድገት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው። ሰፊውም ህዝብ የፖለቲካውን ሂደትና ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን ይገነዘበ ዘንድ የግዴታ መማርና ማወቅ አለበት። በየቦታውም ሰፊውን ህዝብ መጻፍና ማንበብ ሊያስተምሩ የሚችሉ ተቋማት መገንባትና ግልጋሎት መስጠት የዘመናዊነት ዋናው መሰረት ነው። ሰፊው ህዝብ ባልተማረበትና ባልነቃበት አገር ውስጥ ጤናማ የሆነ ዘመናዊ ፖለቲካ ማካሄድ አይቻልም። ስለሆነም ፖለቲካ የሚባለው ነገር ከህዝብ ጋር በቀጥታ የሚያያዝና የህዝብንም ችግር መፍቻ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን አንድ ህዝብ እስካልተማረና እስካልነቃ ድረስ በየጊዜውና በተለያዩ መስኮች ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን መቆጣጠር አይችልም። በሌላ አነጋገር፣ ፖለቲካ የሚባለው ነገር ፖለቲከኛ ነን፣ ህዝብን እንወክላለን፣ ከዚህም በመነሳት የተመረጥን ስለሆን የፈልግነውን ነገር ለማድረግ እንችላለን ለሚሉ የሚጣል መሆን የለበትም። ይህም ማለት ህዝባዊ ተሳትፎ የሌለው አገዛዝና መንግስት ዘመናዊነት የጎደለው ነው ማለት ነው።

ላይ ከተተነተነው መሰረተ-ሃሳብ ስንነሳ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘመናዊነት(Economic and Social Modernizatiion) ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገትና ተቻችሎ መኖር አስፈላጊና እንደመሰረታዊ ጉዳዮችም መታየት ያለባቸው ነገሮች ናቸው። ይህ ደግሞ ሰፋ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ መደገፍ ያለበትና፣ በመጀመሪያ ደረጃ የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ያለበት ጉዳይ ነው። ለኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ኑሮ መሻሻል የግዴታ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በጣም አስፈላጊዎች መሆናቸውንም መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። በንግድ እንቅስቃሴ ብቻ የሚገለጽ ወይም በብልጭልጭ ነገሮች ብቻ የሚገለጽ በራሱ የዕድገት መለኪያ ስለማይሆን ትክክለኛና ሁለ-ገብነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የግዴታ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሲደገፍ ብቻ ነው። ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ደግሞ የግዴታ መሰረታዊ የምርምር ተቋማት መገንባት አለባቸው። ከዚህም በላይ ወጣቱ በተለያዩ ሙያዎች ሊሰለጥን የሚችልበት ተቋማት መገንባት አለባቸው። ይህ ብቻ ሲሆን የህዝብን የቀን ተቀን፣ የማዕከለኛና የረጅም ጊዜ ፍላጎቶች በየደረጃው መመለስ ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የባህል ዘመናዊነት(Cultural Modernization) የሚባል ነገር አለ። የባህል ዘመናዊነትም በቀጥታ ከመንፈስ ተሃድሶ ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ መጠን፣ ጠቅላላው የሰው ልጅ ዕድገትና መሻሻል፣ የአኗኗር ስልቱና፣ በአጠቃላይም አርትስ በሚባሉ ነገሮች የሚገለጸው ባህላዊ ዘመናዊነት ይባላል።

ባጠቃላይ ሲታይ ዘመናዊነትን አስመልክቶ በአገራችን ያለው መምታታት በጥንታዊው ወይም በክላሲካል፣ ወይም ደግሞ መንፈሳዊነትን ባስቀደመውና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በካፒታሊዝም የሚገለጸው ዘመናዊነት በአንድ በኩልና፣ በሌላው ወገን ደግም ከቅ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተግባራዊ የሆነውን በተለይም ከአሜሪካን የመጣውን “የዘመናዊነት አስተሳሰብ” መሀከል ያለውን ትልቅ ልዩነት የመረዳት ችግር አለ። ይህ አንደኛው ችግር ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአብዛኛዎቻቸን ዕምነት በነፃ ገበያ የሚገለጸው የካፒታሊዝም ዘመናዊነት ካለምንም ህብረተሰብአዊ ግጭትና ማፈናቀል፣ እንዲሁም ጭቆናና ብዝበዛ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ነው። ከፊዩዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም የተደረገውን መሸጋገርና ህብረተሰብአዊ ለውጥ(Transformation Debate) አስመልክቶ እዚህ አውሮፓ ውስጥም ሆነ አሜሪካን በ1960ዎችና በ1970ዎቹ ዓመታት የጦፈና ትምህርታዊ ክርክር ተካሂዷል። እነዚህ ነገሮችና በጠቅላላው የሰውን ልጅ ዕድገት የሚመለከቱ ነገሮች በአገራችን የምሁር እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ ስለማይታወቁ በመሀከላችን ከፍተኛ አለመግባባት አለ። አለመግባባት ባለበት አገር ውስጥ ጥላቻና መናናቅ የስውን ጭንቅላት በመወጠር ለስራ ወይም ለለውጥ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ለማንኛውም በእነዚህ ነገሮች ላይ ግልጽ አስተሳሰብ ሲኖረን ብቻ ነው በአገራችን ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑትን ነገሮች በሙሉ በዘመናዊነት መነጽር ለመመርመር የምንችለው። ዘመናዊነት የሚለው ጽንሰ–ሃሳብ ግልጽ እስካለሆነ ድረስ ደግሞ ማንም እየተነሳ አገርን ማተረማመስና ህዝብን ግራ ማጋባት ይጀምራል።

ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት አቢይ ስልጣንን ሲጨብጥ ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። አንዳንዱም እንዳለ ጭልጥ ብሎ በመግባት አድርባይ ባህርዩን ለማሳየት ነው የሞከረው። ይሁንና አቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ አገራችንና ህዝባችን አንዳችም ጊዜ እረፍት አግኝተው አያውቁም።  ህዝቡን ለማረጋጋት የሚያመች ፖለቲካ ከማካሄድ ይልቅ ጠባብ አስተሳሰብና አገር አፍራሽ የኦሮሞ ጎጠኞችን በመንግስት መኪና ውስጥ በመሰግሰግ የፖለቲካ መድረኩን እንዲቆጣጠሩት በማድረግ  ነው ሰፊው ህዝባችን በፍርሃት እንዲዋጥ ለማድረግ የበቃው። አጠቃላዩን የፖለቲካውን አካሄድ ስንመለከት አቢይና ግብረ-አበሮቹ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆን የገባቸው ስላልሆኑ ሰፊውን ህዝብ የማንቃት፣ የማደራጀትና፣ በተለይም ከጎሳ ባሻገር በመመልከት እንደሰው እንዲያስብና በጋራ በመነሳት አገሩን እንዲገነባ የወሰዱት አንዳችም ፖለቲካዊ ስራ የለም። አቢይ ፖለቲካን የተረዳው ህዝብን ማደራጃ፣ ማንቂያና አገርን የማስከበሪያ መሳሪያ ሳይሆን አንድ ሰው ብቻ ተዋናይ ሆኖ የሚታይበት መሳሪያ አድርጎ  ነው የተገነዘበው። ስለሆነም ሰፊውን ህዝብ በመናቅ የፖለቲካውን መድረክ እንዳለ በመቆጣጠር ከሳይንስ፣ ከሎጂክና ከፍልስፍና ውጭ የሆኑ ነገሮችን በመናገር አዋቂ መስሎ በመቅረብ ህዝብን በማደናገር ላይ ይገኛል። በሚቆጣጠረው መድረክ ላይ እንደፈለገው ሲናገርና ሰውን ሲሰድብ ተው የሚለው አካል ስለጠፋ ሰፊው ህዝባችን ግራ የተጋባበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ባለፉት አራት ዐመታት በፖለቲካ ስም የሚካሄደውን ድርጊት ስንመለከት የአቢይና የግብረአበሮቹ ፖለቲካ ህዝባዊ ቅራኔን ከማጥበብ ይልቅ የሚያስፋ፣ ሰላምን ከማስፍን ይልቅ ብጥብጥን የሚጋብዝ፣ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች በፍርሃት ተውጠው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው። እንደተነገረን ከሆነ አቢይ ዶክትሬቱን የሰራው ሰላምና እርቅ((Peace and Reconciliation) በሚለው ዙሪያ ነው። ይህም ማለት በአገራችን ምድር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍንና ይቅር በመባባል በአንድነት ለስራ እንዲነሳሳ ማድረግ ማለት ነው። የአቢይን የዶክትሬት ስራ ሳላበነው ከየትኛው ፍልስፍና አንፃርና፣ በምን ዐይነት ሳይንስና ቲዎሪ ተደግፎ፣ እንዲሁም የህብረተሰብአችንን ታሪክ በማጥናት አንድ ዐይንት ድምደማ ላይ ይደረስ አይድረስ ፍርድ ለመስጠት በጣም ያስቸግራል። ይሁንና ከአርዕስቱ ብቻ ተነስተን ያለፈውን አራት ዐመት የአገዛዝ ድርጊቱን ስንመረምር የዶክትሬት ስራው በአገራችን ምድር አራት ዐመት ያህል ከተፈጸሙት ዘግናኝ ድርጊቶች ጋር በፍጹም የሚጣጣሙ አይደሉም። በመሰረቱ የዶክትሬት ስራ ሙሉ ጊዜን የሚጠይቅና አምስት ዐመት ያህልም የሚፈጅና፣ በየጊዜውም ፔፐርስ ማቅረብ ስለሚያስፈልግ የላይ ላዩን ብቻ ስንመለከት አቢይ በስም እንጂ በዚህ አርዕስት ዙሪያ በተከታታይ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ እንዲሁም በየጊዜው የጥናት ጽሁፎች በማቅረብ የዶክትሬት ስራውን እንዳልሰራ ለመገንዘብ እንችላለን። ሌላው ደግሞ አምስት ዐመት በአንድ አርዕስት ላይ የዶክትሬት ስራውን ለመስራት የሚፈልግ ሰው ዝም ብሎ የሚነሳ  ሳይሆን፣ ቀደም ብሉ ከተማረው ጋር በጥብቅ የሚያያዝ መሆን አለበት። ለምሳሌ አንድ ኢኮኖሚክስ የተማረ ሰው፣ ከቢኤ ጀምሮ እስከ ማስትሬት ድረስ የሰራ ዶክትሬቱን ለመስራት ከፈለገ በዚያ ትምህርትና አንድን አርዕስት በመምረጥ ብቻ እንጂ፣ በፍልስፍና ወይም በፊዚክስ ዶክትሬቴን ለመስራት እፈልጋለሁ ሊል አይችልም፤ ተቀባይነትም አይኖረውም። ሌላው በጣም አስቸጋሪ የሚሆነው ነገር አንድ ሰው ዶክትሬቱን ለመስራት ሲነሳ ከዚህ ቀደም በማንም ያልተደረሰበት ወይም በደንብ ያልተብላላ ነገር ካለ አዲስ ትንታኔ ለመስጠት ወይም አንድን ነገር ግልጽ ለማድረግ ነው። የአቢይን የዶክትሬት አርዕስት አስቸጋሪ የሚያደርገው፣ አርዕስቱ በደንብ ከታሰበበት የግዴታ ከፍልስፍናና ከህብረተሰብ ዕድገትና በተለያዩ አገሮች ጋር ከተከሰቱት ግጭቶች ጋር መያያዝ ያለበት መሆን አለበት። ይህም ማለት የአምስት ዓመት ስራና ከአምስት መቶ በላይ ገጾችን የሚይዝ ሀተታ መሆን አለበት። በየኢፖኩ የተመሰረቱትን የመንግስት አወቃቀሮች፣ የአገዛዞችን የንቃተ-ህሊና ጉዳይና፣ በምድር ላይ የሚታየውን የማቴሪያል ሁኔታ ያካተተ መሆን አለበት።  ከዚህ አጭር ገለጻ ስንነሳ የአቢይ የዶክትሬት ዲግሬ በጣም አጠራጣሪ ነው ማለት ነው። ስለሆነም  የአቢይ አረመኔያዊ ተግባርና፣ በተለይም ደግሞ ሃይማኖትንና ዘርን ያተኮረ ከፍተኛ ወንጀል ሊገርመን አይገባም። ምክንያቱም አንድ ዶክትሬቱን በከፍተኛ ምርምር የሰራ ሰው በሂደት ውስጥ ጭንቅላቱም ስለሚበስል የግዴታ አረመኔያዊ ተግባር ሊፈጽም አይችልም፤ የሚፈጽምም ካለ ባስቸኳይ እርምጃ መውሰድና ችግሩን መሰረታዊ በሆነ መንገድ መፍታት የሚችል ይሆናል። የአቢይን የአራት ዓመት አገዛዝ ስንመለከት እንዲያውም ሰው በሞተ ቁጥር የሚደሰትና፣ ገና ምኑን አይታችሁት እያለ ነው ሰፊውን ህዝብ ሞትን እንዲለምደውና እንደተራ ነገር አድርጎ እንዲቆጥረው ለማድረግ የሚሞክረው። ለማንኛውም የዶክትሬት ስራ ቀደም ብለው ከተማሩት ነገሮች ጋር የሚያያዝና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የአስር ዓመት ዝግጅት የሚያስፈልገው ወይም የአስር ዓመት የስራ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አንድ ተማሪ ቢኤውን ለማግኘት የግዴታ አራት ዓመት ያስፈልገዋል። በጣም ጥሩ ውጤት ካገኘ ብቻ  ነው ማስትሬት ዲግሪውን መስራት የሚችለው። የማስትሬት ስራም ቢያንስ ሶስት ዓመት ይፈጃል። የማስትሬት ቴሲሱንም መጻፍ አለበት። በማስትሬት ትምህርቱና ቴሲሱ በጣም ጥሩ ውጤት ካገኘ ብቻ ነው የዶክትሬት ዲግሪ ሊሰራ የሚችለው። ለምስሌ በፊዚክስ ዶክትሬቱን ለመስራት የሚፈልግ  ሰው እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት ማምጣት አለበት። ከኢኮኖሚክስ ጋር የሚገናኝ አንድ አርዕስት መርጦ ዶክትሬቱን የሚሰራ ከሆነ ደግሞ በጣም ጥሩ ውጤት ማምጣት አለበት። የዶክትሬት ስራውንም ለመስራት ሁለት ፕሮፌሰሮች ያስፈልጉታል። የዶክትሬትም ሆነ የማስትሬት ስራና ትምህርት በርቀት የሚካሄድ ትምህርት ሳይሆን የተቀን ተቀን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመገኘትና ላይብረሪ ውስጥ መጻፍ በማንበብና ጠቃሚ ነገሮችን በመልቀም የሚጻፍ ነው። አንድ ሰው የዶክትሬት ዲግሪውንም ካገኘ በኋላ አልፎ አልፎ የግዴታ ሳይንሳዊ ጽሁፎችን መጻፍ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ካጉል ትረካና ከግብዝነት ሊድን የሚችለው። በዚህም አማካይነት ብቻ ነው በተቃቃራቢ አነሰም በዛም ጥሩ ዕውቀት ለመቅሰም የሚቻለው።  ባጭሩ የአገራችንን የፖለቲካ ትርምስና መዘላበድ ስንመለከት አዲሱ የገዢ መደብና ሚኒስተሮቹ በሙሉ ከሳይንስ ዓለም የራቁና ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ግንዛቤ እንደሌላቸው መገንዘብ እንችላለን።

ከዚህ ዐይነቱ ዕውቀተ ወይም ሳይንሰ-አልባ ሁኔታ ስንነሳ በፖለቲካው መድረክ ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይልቅ ዲስፖታዊ አገዛዝ የሰፈነበትን መሆኑን እንመለከታለን። እንደሚታወቀው ለዲሞክራሲያዊ ተሳትፎና ስርዓት መስፈን የግዴታ በመንግስቱ መኪናና ስልጣንን በተቆናጠጠው የገዢ መደብ መሀከል መቆላለፍ መኖር የለበትም። በሌላ አነጋገር፣ የመንግስቱ መኪና የገዢው መደብ የግል ሀብትና የመጨቆኛ መሳሪያ መሆን የለበትም። ይህ አንደኛውና መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ ራሱ የገዢ መደብ የሚባለው ለህግ ተገዢ መሆን ያለበትና፣ በህግ-የበላይነት ማመንና መቀበል ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ስንነሳ አጠቃላዩ የፖለቲካ መድረክ በኤክሲኩቲቩ፣ በህግ አውጭውና ህግን በሚያስፈጽመው መሀከል ግልጽ የስራ ክፍፍል መኖር አለበት። ይህም ማለት ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጀምሮ እስከ ሌሎች ሚኒስተሮች ድረስ በሙሉ በፓርላሜንት ወይም በህግ አውጭው ቁጥጥር ስር ያሉና የአገዛዙን ስራ በሚቆጣጠሩት ፓርሊሜንታሪ ኮሚሽን ተጠያቂ የመሆን ግዴታ ያለባቸው ናቸው። ይህም ማለት ራሱ ጠቅላይ ሚኒስተሩና ሌሎች ሚኒስተሮችም ከህግ አውጭው ቁጥጥር ስር አልፈው በመሄድ የራሳቸውን አጀንዳ መከተል አይችሉም ወይም ተግባራዊ የማድረግ መብት የላቸውም ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነት አምባገነናዊ አካሄድ ካለ የግዴታ ህገ-መንግስቱን በሚቆጣጠረው ፍርድቤት(Constitutional Court) የመከሰሰና የመጠየቅ ግዴታ አለባቸው ማለት ነው። በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ግን ፓርሊያሜንቱ ራሱ ትክክለኛ ፓርሊያሜንት ያልሆነና፣ የተለያዩ የህብረተሰብን ክፍሎች የሚውክሉ ፓርቲዎች የማይሳተፉበትና፣ ያሉትም በትክክለኛና ህብረተሰብን በሚጠቅሙ ዕውቀቶች ያልታነጹ ናቸው። በተለያዩ ፊልድ የሰለጠኑንና በየጊዜው የህብረተሰብ ችግሮችን በማንሳትና በመጻፍ፣ እንዲሁም በተለያዩ ዕውቀቶች የሰለጠኑ ሰዎች ተሳትፎ የሌለው ፓርሊያሜንት በመሰረቱ የአድርባዮች መሰብሰቢያ መሆኑ የማይቀር ነው። አገዛዙን ለመቆጣጠር የማይችል ፓርሊያሜንት ደግሞ የግዴታ ለአምባገነናዊ አገዛዝ አመቺ መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ለማንኛውም ያለፈውን አራት ዓመት የአገራችንን ፖለቲካ ስንመለከት ዋናው ተዋናይ አቢይ ነው። ሁሉንም አድራጊና አስፈጻሚ ራሱ ነው። ዕቅድ አውጪና አስፈጻሚም ራሱ ነው። ማንኛውም ተግባራዊ የሚደረግ ነገር በሙሉ በሱ ቁጥጥር ስር ያለና፣ ከሱ ቁጥጥር ስር ውጭ የሚካሄድ ነገር ካለ መሰናክል የሚፈጥር ነው። ሰሞኑን የምናየውና የምንሰማው ይህንን ሀቅ ነው። በደብረ እንቁ ልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚሰራው የመስቀል ፕሮጀክተንና አምስት ዓመት ጥናትና ዕቅድን የፈጀ፣ ከሁለት ዓመት ጀምሮ በመሰራት ላይ የሚገኘውን ትልቅና ለህዝብ፣ በተለይም ለወጣቱ መገልገያ ሊሆን የሚችል ፕሮጀክት በአቢይ ቀጭን ትዕዛዝ እንዲቆም ተደርጓል። የአቢይ ዋና ዓላማም በተለይም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን መዋጋትና አማራ የሚባለውን ብሄረሰብ ማውደም ነው። በዚህ ዐይነት አካሄዱም አቢይ ለማረጋገጥ የቻለው የእነ መለስ ዜናዊንና የስብሃት ነጋን ዋና ዓላማ ነው ማለት ይቻላል። ያለፈው አራት ዐመት የአቢይ ፖለቲካም የአነጣጠረው በአማራውና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ነው። በሌላ ወገን ደግም አቢይ እንደሚነግረን ከሆነ በየቀኑ መጽሀፍ ቅዱስን እንደሚያነብና ሃይማኖተኛም እንደሆነ ነው። ይሁንና ግን እሱ ሌላ ዐይነት መጽሀፍ ቅዱስ ካላነበበ በስተቀር እኛ በምናውቀው መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ በተለይም ጥንታዊ በሆነና የመጀመሪያው የአርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ጦርነት አውጅ የሚል ነገር አልተጻፈም። ቢጻፍም እንኳ አንድ ፖለቲከኛ ነኝ የሚልና 115 ሚሊዮንን ህዝብ የሚያስተዳድር ሰው ማካሄድ ያለበት ፖለቲካ ከሃይማኖት ጋር መገናኘት የሌለበት ጉዳይ ነው። አንድ አገዛዝና ጠቅላይ ሚኒስተር ወይም የከተማ አስተዳደር በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ህዝባዊ ቅራኔ የመፍጠር መብት የላቸውም። እንደዚህ ዐይነቱንም አደገኛ ተግባር የሚፈጽሙ ከሆነ በፖለቲካ ስልጣን ላይ የመቆየት መብት የላቸውም።

ባጠቃላይ ሲታይ በፖለቲካ ቲዎሪ የውስጥና የውጭ ፖለቲካ የሚባል ነገር። የውስጥ ፖለቲካ ከጸጥታና ከሰላም አንስቶ፣ እስከማህበራዊ ጉዳዮች፣ የጤና መስክ፣ የትምህርት ጉዳይ፣ ለህዝብ መጠለያ የሚሆን የቤት ስራ፣ የከተማ ግንባታ፣ የትናንሽና የማዕከለኛ ኢንዱስትሪ ተከላ፣ የስራ መስክ መፍጠር፣ ባጭሩ ሚዛናዊነት ያለው ዕድገት ማካሄድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስተሩ አጠቃላዩን ስራ የሚቆጣጠር ሲሆን፣ እያንዳንዱ ሚኒሰተርም ለተቀመጠበትና ኃላፊነት ለተሰጠው ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ነው ማለት ነው። ለምሳሌ የኢኮኖሚክስ ሚኒስተር ዋናው ተግባር የግዴታ በአገር ውስጥ በማሽን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የአገር ውስጥ ገበያ የሚገነባበትን ሁኔታ ሳይታክቱ መስራት ነው። ለዚህ ደግሞ የግዴታ የኢኮኖሚክስ ታሪክ፣ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና የተለያዩ ፖሊስዎች ዕውቀት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ሌሎችም በተሰጣቸው ኃላፊነት ሳይታክቱ ህዝብን ማገልገል አለባቸው። በዚህ መንፈስ የማይሰራ እንደ መንግስትና አገዛዝ ሊቆጠር በፍጹም አይችልም።

ሌላው ደግሞ የውጭ ፖለቲካ ነው። የውጭው ፖለቲካ የግዴታ ከአገር ጥንካሬና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የውጭው ፖለቲካ ዋና ዓላማም ብሄራዊ ነፃነትን ማስጠበቅና የዜጎችችን መብት ማረጋገጥ ይሆናል። በሌላ አነጋገር አንድ አገዛዝ የአንድ የውጭ ኃያላን መንግስት ተላላኪና ትዕዛዝ ተቀባይ አይደለም። በሌላ አነጋገር ወደ ውጭ ለመከበርና ላለመደፈር፣ በእኩል ደረጃ ለመደራደር ወይም ለመከራከር የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ የቤት ስራ መስራት ያስፈልጋል። በአራት ዓመት ፖለቲካው አቢይ ይህንን ያረጋገጠ አይደለም። በአንፃሩ ብሄራዊ ነፃነታችን እንዲደፈር፣ ማንም ኃይል እንዲበታትነን አመቺ ሁኔታዎችን የፈጠረ ነው። በአገራችን ምድር ለውጭ ኃይሎች የሚሰራ አገዛዝ ነው ያለው ማለት ይቻላል። ለዚህ ዐይነቱ የትዕዛዝ ተቀባይና ብሄራዊ ነፃነት መደፈር አስቸጋሪው ጉዳይ በአገራችን ምድር የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ያለውና ለብሄራዊ ነፃነት የሚቆረቆር የህብረተሰብ ኃይል ለመኖር አለመቻሉ ነው። በሁሉም አቅጣጫ የበሰለ፣ ለህዝብና ለአገር ዕድገት የሚቆረቆር ኃይል ባለመኖሩ አገራችንና ህዝባችን ለአደጋ ተጋልጠዋል ማለት ይቻላል።

ከፖለቲካ ቀጥሎ ደግሞ የግዴታ የኢኮኖሚ ዘመናዊነት ወይም ሞደርናይዜሽን የሚባል ነገር አለ። ትክክለኛው የኢኮኖሚ ዘመናዊነት የሚጀምረው የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ከማሟላት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ እዚያው በዚያው ሁለ-ገብ የሆነ ዕድገት ማካሄድ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል ያስፈልጋል። የአውሮፓውን የካፒታሊዝም ዕድገት ስንመለከት አካሄዳቸው የአገር ውስጥ ገበያን መገንባት፣ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችንና መንደሮችን በመገንባት በመንገድ፣ ቀጥሎ ደግሞ በባቡር ሃዲድ ማያያዝ ነበር። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና እንቅስቃሴ በጊዜና በቦታ ብቻ ስለሚካሄዱ። ስለሆነም በአውሮፓ የአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከተማዎችን በተቀነባበርና ለሰው ልጅ መኖሪያና መንቀሳቀሺያ እንዲሆኑ አድርጎ መስራት የተለመደ ነበር። ለዚህ ዐይነቱ የአገር ግንባታ የተከተሉትም መርካንትሊዝም የሚባል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲሆን፣ ይህም ፖሊሲ በአንድ በኩል በማሽን ኢንዱስትሪ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማደግ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ከውጭ በሚመጡ ምርቶች እንዳይፈራርሱ የሚከላከል ፖሊሲ ነበር። በዚህም አማካይነትና ዕውቅ በሆነ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ነው በአውሮፓ ውስጥ ካፒታሊዝም ሊያድግና ሊስፋፋ የቻለው። ይህም ማለት አንድ አገር በነፃ ገበያ ፖሊሲ አማካይነት የተሟላና የተስተካከለ ዕድገት ማየት አትችልም ማለት ነው።

የአቢይን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት እሱም ሆነ በአካባቢው ያሉት ሰዎች ስለትክክለኛው የኢኮኖሚ ፖሊስ የማያውቁ ብቻ ሳይሆኑ የህዝባችንን መሰረታዊ ችግሮች ለመረዳት የማይችሉ ናቸው። በምድር ላይ የሚታየውና ህዝባችንን የሚያስቸግረውን፣ በብዙ መልኮች የሚገለጸውን ድህነትና ዝርክርክነት የሚታያቸው አይደለም። የግሪክ ፈላስፎች እንደሚሉት ጭንቅላት ማየት የማይችል ከሆነ ዐይንም ማየት ስለማይችል በምድር ላይ የሚታዩ አስቀያሚ ነገሮች በሙሉ ለአዲሶቹ የገዢው መደብ አካል ለሆኑ ሰዎች እንደተራ ነገር ነው የሚታያቸው። በትክክልም ጭንቅላት ሲያይ ብቻ ነው ዐይንም በደንብ ማየት የሚችለው። አቢይ በረሃብ የሚሰቃየውንና መጠለያ ያጣውን ህዝባችንን ቅጠል ቀቅላችሁ ጨው ጨምራችሁ በመብላት ነው ከረሃብ ልትፈወሱ የምትችሉት እያለ  ነው አዲስ ቲዎሪ የሚያስተምርን። ስንዴ ብቻ በአገራችን ይመረት ይመስል ስንዴ አምርተን ወደ ውጭ መላክ አለብን እያለ በህዝባችን ላይ ይቀልዳል። ለምግብ የሚሆን ነገር ስንዴ ብቻ ሳይሆን፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዘንጋዳ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ጤፍ፣ ድንች፣ ልዩ ልዩ በመሬት ውስጥ የሚበቅሉ እንደ ወጭኖና ጎደሬ የመሳሰሉ ፍሬዎች፣ አተር፣ ሽምብራ፣ ባቄላና ሌሎችም ለዘይት የሚያገለግሎ አያሌ ጥራጥሬዎችና ዘሮች አሉ። ከዚህም ባሻገር አትክልቶችን በስነ-ስርዓትና በበቂው ማምረት ይቻላል። ታዲያ የተለያዩ የሰብል ዐይነቶች ማምረት በሚቻልበት አገር ውስጥ ለምንድነው በስንዴ ላይ ብቻ ማትኮር የተገደደው? ለምንስ የቅድሚያ ቅድሚያ ለውጭ ገብያ ተብሎ የሚመረተው? የትኛው የኢኮኖሚ ቲዎሪስ ነው የሚያስተምረን?  የአቢይ የተዛባ አስተሳሰብ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም።  እንደጦጣ ዛፍም ላይ ማደር ይቻላል፤ ጫካ ውስጥም መኖር ይቻላል እያለ ነው የሚነግረን።  በ21ኛው ክፍለ-ዘመን አገራችንና ህዝባችንን ወደ ዲንጋይ-ዘመን ለመመለስ የሚጥር መሪ ማግኛታችን በጣም የሚያሳዝን ነው። እሱ ከእነቤተሰቡ ጭምር ቤተመንግስት ውስጥ እየተንፈላሰሰ፣ ሌሎች ባለስልጣናት ተብዬዎች ደግሞ በቪላ ቤት ውስጥ እየተንደላቀቁ እየኖሩ ህዝባችን ሜዳ ላይ ተጥሎ፣ ጎጆ ቤት ያለው ደግሞ ዝናብ እየፈሰሰበት ሲኖር ዝም ብለው የሚመለከቱ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያለቸው ሰዎች ናቸው አገራችንን የሚያስተዳድሩት። ታሪካዊ፣ ባህላዊና ብሄራዊ ንቃተ-ህሊና የሌላቸው ሰዎች ናቸው በስልጣን ላይ ቁጥጥ ብለው በህዝባችን ላይ የሚቀልዱት። ለማንኛውም አቢይና ግብረ-አበሮቹ በሚከተሉት በእነ ዓለም ባንክና/(WB) በዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) በሚደነገግ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር ልታድግና ህዝቦቿም ከድህነት በፍጹም ሊላቀቁ አይችሉም። በትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር በመገናኘት በሚታቀድ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው አንድ አገር በጸና መሰረት ላይ ልትገነባ የምትችለው። አቢይና ግብረ-አበሮቹ ይህንን የማድረግ ብቃት የላቸውም።

ይህንን ትተን ወደ ሌሎች እንደጦርነት የመሳሰሉት ነገሮች ስንመጣ በተለይም በሰሜኑ ክፍል የሚካሄድውን ጦርነት አስመልክቶ በመጀመሪያው ጦርነት ወያኔ ከተበታተነና ኃይሉም ከተዳከመ በኋላ እንደገና እንዲንሰራራ በማድረግ በተለይም በአማራውና በአፋሩ ህዝባችን ላይ ጦርነት እንዲታወጅ ያደረገ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ወያኔ እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ አማራውና አፋሩ ወገናችን በጦርነት እንዲጠመዱ ያደረገና ለብዙ ሺሆች ወገኖቻችን መገደል ምክንያት የሆነ ሰው ነው ማለት ይቻላል። አቢይና ግብረ-አበሮች እንደዚህ ዐይነቱን ወንጀል በተደጋጋሚ ሲሰሩ የሚያስቆማቸውም ኃይል በፍጹም አልተገኘም። ምሁራዊ ብቃትነት የሌላቸው የወታደሮቹ መሪዎች ከአቢይ ቀጭን ትዕዛዝ በመቀበል የሚያጎበድዱና ህዝብን የሚያስጨፈጭፉ ለመሆን በቅተዋል። ምሁራዊ ብቃትነት የሌላቸው የወታደሩ አዛዦቹ ብሄራዊና ህዝባዊ  ስሜት ስሌላቸው በቀላሉ በእንደዚህ ዐይነቱ በራሱ ምንም ዐይነት ምሁራዊ ብቃት በሌለው አንድ ጠቅላይ ሚኒስተር በመታዘዝ አገር እንዲፈራርሱ ለማድረግ በቅተዋል። በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በዚህ መልክ ህዝብን ማስጨፍጨፍና ማፈናቀል ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።

በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችን ምድር የሚካሄደውን ጦርነት ለተመለከተ ሰው፣ አቢይና ግብረ-አበሮች የያዙት ፈሊጥ ጦርነትን አገር አቀፋዊ በማድረግ ሰፊው ህዛብችን በጭንቀትና በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ነው።  ከጦርነት በስተቀር ሌላ ነገር እንዳያስብ እያደረጉት ነው። መንፈሱን ሰበብ በማድረግና በሰላም በመኖር አገር እንዳይገነባ የህዝብን መንፈስ የሚረብሽ ማንኛውንም ነገር እያደረጉ ነው። በዚህም ተግባራቸው የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችንና እንደ ቢልጌት የመሳሰሉትን የህዝብ ቅነሳ ፖሊሲ የሚያራምዱትን አደገኛ ኃይሎች ተግባር እነ አቢይም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ናቸው። ስለሆነም ለወያኔ በተደጋጋሚ ወረራ እንዲፈጽም አመቺ ሁኔታዎች ከመፍጠር ባሻገርና በሱዳንም በኩል በአየርም ሆነ በምድር በኩል የጦር መሳሪያዎች እንዲገቡለት በማድረግ አማራውንና አፋሩ ወገናችን ዘለዓለማቸውን በጦርነት እንዲወጠሩ ማድረግ መግቢያ መውጫ እያሳጧቸው ነው። በወለጋና በሰሜን ሸዋ በኦነግ ሸኔ የሚካሄደውን ጦርነት ስንመለከት ደግሞ ዋናው ትዕዛዝ ሰጪዎች እነ አቢይና ሺመልስ አብዲሳ ናቸው። ሰሞኑን የወጣው ዘገባም እንደሚያረጋግጠው የፀጥታው ኃላፊ ተመስገን ጥሩነህና ምክትሉ በቀጥታ ለኦነግ ሸኔ ትዕዛዝ እንደሚሰጡና ህዝብም እየፈራ እንዲኖርና ሌላው ደግሞ እንዲገደል ማድረግ ነው። ይህን ዐይነቱን አስተሳሰብና ድርጊት ፖለቲካ ብለን ልንጠራው እንችላለን ወይ? በሌሎች አገሮች ውስጥስ በቀጥታ በመንግስት የተደገፈ ጦርነት በህዝብ ላይ ይካሄዳል ወይ? ይህ ዐይነቱ አረመኔያዊና ኋላ-ቀር አስተሳሰብስ ከየት ሊመጣ ቻለ? ምክንያቱስ ምንድነው? የእነ አቢይና የእነሺመልስ አብዲሳስ ዋናው የመጨረሻው ዓላማቸው ምንድነው? በዚህ ዐይነቱ አገርን የማተረማመስ ፖለቲካቸው ስልጣን ላይ ለመቆየት ይችላሉ ወይ? አንድ አገዛዝ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ሊቆይ የሚችለው ለህዝብና ለአገሩ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ሲሰራ ብቻ ነው። በታሪክ ውስጥ ህዝብን በማሰቃየት፣ በማስፈራራትና በማሳደድ ለረጅም ዐመታት ስልጣን ላይ የቆየ አመራር የለም። በአጭሩ የአራት ዓመቱን የፖለቲካ ዘይቤያቸውንና ድርጊታቸው ስንመለከት እነዚህ ሰዎች ይህንን ትልቅ አገርና በቁጥር እየጨመረ የሚሄድን ህዝብ ካለአቅማቸው ነው የሚመሩት። ምንም ዐይነት ዕውቀትና አገርን በስነ-ስርዓት የማስተዳደር ችሎታ ሳይኖራቸው ነው በአጋጣሚ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ማለት የቻሉት። ስለሆነም የታሪክና የባህል ንቃተ-ህሊና የሌላቸውና በሰው መሞት የሚደሰቱ ሰዎች ስልጣንም ላይ የመቆየት መብት በፍጹም የላቸውም። በዚህ ከቀጠሉ አገራችንን እንዳለ ነው የሚያፈራርሱት።

በአጠቃላይ ሲታይ የአቢይንና የግብረአበሮችን ፖለቲካ ስንመለከትና ስንመረምር እነዚህ ሰዎች አስተሳሰባቸው በሙሉ ኋላ-ቀርና መንፈሳቸውም አረመኒያዊ ነው ማለት ይቻላል። ድርጊታቸው በሙሉ ከሳይንስ፣ ከፍልስፍናና ከሰብአዊነት ፖለቲካ ጋር የሚጣጣም አይደለም። በጆን ሚልተን አጠራር(The Paradise Lost) በሚለው መጽህፉ ውስጥ እንደ ተቀመጠው ሰይጣናዊ ባህርይ ያላቸው፣ የህዝብን ደህንነት የማይፈልጉና፣ የአገራችንን የተሟላ ዕድገት የሚጠሉና፣ በህዝብም ዘንድ ስምምነት እንዳይኖር ቀን ከሌት የሚሰሩ እጅግ አደገኛና ኋላ-ቀር አስተሳስብ ያላቸው ኃይሎች ናቸው ማለት ይቻላል። ስለሆነም፣ የጥበብ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ፣ የፍልስፍናና የባህል ዕድገት፣ የተስተካከለና የሁለ-ገብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጠንቆች ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው ሰፊው ህዝባችን እንዳይነቃና እንዳይማር፣ እንዲሁም እንዳይደራጅ መንገዱን ሁሉ ሊዘጉ የበቁት። በደንብ ያልተማረ ሰፊ ህዝብና በጥልቀትና በተወሳሰበ መልክ የሚያስብ ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር ደግሞ አንድ አገር ለውጭ ኃይሎች ሴራ መጋለጧ የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይም ከኢኮኖሚክስ አንስቶ እሰከሶስዮሎጂና ፍልስፍና፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ጥልቅ ዕውቀት ያለው ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር የውጭ ኃይሎች በኤክስፐርት ስም እየመጡ ብዙ ነገሮችን ማበላሸት ይችላሉ። ከተማዎች በዕቅድና ለሰፊው ህዝብ በሚስማማ መልክ እንዳይሰሩ በአንዳንድ ትላልቅ ፎቅ ቤቶችና በሆቴል ቤቶች ላይ በመሰማራት የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። የምናየውም ሀቅ ይህንን ነው።

በአጭሩ አቢይና አማካሪዎች፣ እንዲሁም የካቢኔት ሚኒስተሮች ምን እንደሚሰሩ የሚያውቁት ነገር የለም። አንድን ህብረተሰብ እንደሚያስተዳድሩና፣ ህብረተሰብም በሰዎችና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚገለጹና፣ ሰው እንደመሆናቸውም መጠን ቢያንስ መሰረታዊ ፍላጎታቸው(Basic Needs) መሟላት እንዳለባቸው  የተረዱ አይመስሉም። እነሱ የተንደላቀቀ ኑሮ ሲኖሩና፣ በቀን ከሶስት ጊዜ በላይ ምህብ እያመራረጡ ሲበሉ ሰፊው ህዝብ የሚቀምሰው እንደሌለው ወይም ደግሞ በዋጋ ግሽበት እንደሚሰቃይ በፍጹም አይታያቸውም። ስለሆነም በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እንደሚመሩና ህዝባችንንም በምን ዐይነት ፍልስፍና  እንደሚመሩ በፍጹም የሚያውቁት ነገር የለም። ምንም ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም የሌለው አገዛዝ ደግሞ ለምን ስልጣን ላይ እንተቀመጠ በፍጹም ሊገነዘብ አይችልም። ከዚህ ስንነሳ መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ታዲያ አቢይን በምን የፖለቲካ መነፅር ነው መመልከት ያለብንና ፍርድስ መስጠት የምንችለው? እንደኛ ባሉ አገሮች  ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የሚሰራው ስህተት  ስልጣን ላይ ያሉትም ሆነ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች ምን ዐይነት ርዕየተ-ዓለም እንዳላቸው አለማወቃቸው ነው። ስለሆነም ተግባራዊ የሚያደርጉት አጠቃላዩ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከህብረተሰብ፣ ከባህል አንፃር፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ፣ ከስነ-ልቦና አንፃር. ከአካባቢ ሁኔታ አኳያ፣ በህብረተሰብ ውስጥ እርስ በእርስ በሚኖረው ግኑኝነት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖና ውጤት አለማወቃቸው ነው። ስለሆነም የታሪክ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የአካባቢና የስነ-ልቦና ግንዛቤ የሌላቸውና፣ ታሪክም እንዴት እንደሚሰራ የማያውቁ ናቸው። ይህን ሁሉ ከመረምርኩ በኋላ የምደርስበት ድምዳሜ ዛሬ በአገራችን ምድር በስልጣን ላይ ያለው በአንድ ግለሰብ የሚመራው አገዛዝ ፋሺሽታዊ ብዬ ነው የምደመድመው።  ፋሺስታዊ የሚያስብለውም በአንድ ብሄረሰብና በሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ዘር-ተኮር ጥቃት ማድረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ባለፉት ስምንት መቶ ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ለተፈጸሙት “መጥፎ ነገሮች” በሙሉ አንድን ጎሳ በጅምላው ተጠያቂ ማድረጉ ነው።  በዚህም አካሄዱ በተለይም የአማራው ብሄረሰብ ለልዩ ልዩ ባህላዊ ዕድገቶች ያበረከታቸውን አዎንታዊ ወይም ጤናማ አስተዋፅዖች እንደመጥፎ ነገር ወይም የሌሎችን ብሄረሰቦች ባህልና ዕድገት እንደተቀናቀነ ወይም እንዳወደመ አድርጎ መውሰዱ ነው። ስለሆነም  የጀርመን ናዚዎች በጀርመን ምድር ለተከሰቱት መጥፎ ነገሮች በሙሉ ይሁዲዎችን በውሸት በመወንጀል ተጠያቂ እንዳደረጓቸው ሁሉ በአቢይና በሺመልስ አብዲሳ የሚመራውም የኦሮሞ ፋሺሽታዊ ቡድን በውሸት የአማራውን ብሄረሰብ በመወንጀል በጅምላ እየጨፈጨፈውና በዕውቅ መንደሮችንና ከተማዎችን እንዳፈራረሰበትና እያፈራረስበትም እንደሆነ ይታወቃል። ይህንን ተግባር የሚፈጽም በአንድ በኩል በወታደሩ ውስጥ የተደራጀ ቡድን ሲኖር፣ በውጭ ደግሞ ኦነግ ሸኔ የሚባለው ፋሺሽታዊ ቡድን በቀጥታ ከአቢይና ከሺመልስ አብዲሳ ትዕዛዝን በመቀበል በአማራው ብሄረሰብ ላይ የሚያደርገው የጅምላ ጭፍጨፋ በቂ ማረጋገጫ ነው። ከዚህም በላይ አቢይና ሺመልስ አብዲሳ ፋሺሽቱን የወያኔን ቡድን መልሶ እንዲያንሰራራ በማድረግና በአማራውና በአፋሩ ወገናችን ላይ ዘግናኝ ድርጊት እንዲፈጽም ሁኔታውን ማመቻቸት፣ ስንትና ስንት አሰቃቂ ግፍ ከፈጸመ በኋላ ደግሞ ከዚህ ፋሺሽታዊ ቡድን ጋር የዕርቅ ድርድር ለማድረግ ቀና ደፋ ማለት፣ እነዚህና በተለይም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አማራውን እንዳያንሰራራ በተለይም በፋኖዎችና በአማራ ልዩ ኃይል ላይ የሚያደረገው የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻና ክትትል በሙሉ ፋሺሽታዊ የሚያስብሉት ናቸው። ከዕውነተኛ ነፃነትና የዲሞክራሲ ትግል አንፃርም እንደዚህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊና አገር በታኝ ቡድን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ከስልጣን ላይ መወገድ ያለበት ነው። ወያኔና ሌሎች በኦሮሞ ብሄረሰብ የሚነግዱ እንደነጃዋር የመሳሰሉ ፋሺሽታዊ ቡድኖችና ሌሎችም ኋላ-ቀር ኃይሎች በስልጣን ዙሪያ ዝር ማለት ያለባቸው ኃይሎች አይደሉም። የስልጣኔ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የተሟላ ዕድገት ፀሮችና ለሰላምም ጠንቆች በመሆናቸው በስልጣን አካባቢ መድረስ የለባቸውም።  በአንፃሩ ለፍርድ የሚቀርቡና ህዝብን ከህዝብ በማጣላት፣ አገር እንዳይገነባ መሰናክል በመፍጠር፣ ህዝባችን ከድህነትና ከረሃብ እንዳይላቀቅ ለውጭ ኃይሎች አጎብድዶ የእነሱን አገር አጥፊ ድርጊት ተግባራዊ በማድረግ፣ እነዚህ ነገሮች በሙሉ በህግ የሚያስጠይቋቸው ናቸው።

በየአስተዳደር ውስጥ የተሰማሩትን ሰራተኞችም ስንመለከት ከገጠር እየመጡ እንዲሰገሰጉ የተደረጉ ናቸው። ድሮ ተራው የሌሎች ነበር፤ አሁን ደግሞ የእኛ ነው በማለት ስለአስተዳደር ችሎታ የሌላቸውና በደንብ ያልሰለጡኑ ኦሮሞዎችን በማሰማራት ህዝቡን በጭንቀትና በፍርሃት ውስጥ እንዲኖር አድርገውታል። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሰው በማንኛውም የአድሚኒስትሬሽን ስራ ውስጥ ከመሰማራቱ ወይም ከመቀጠሩ በፊት የአስራሁለተኛን ክፍል ያጠናቀቀ መሆን አለበት። በሁለተኛ ደረጃ፣ ችሎታ ባለው ሙያ ወይም የአስተዳደር ክፍል ከሶስት እስከ አራት ዓመት ድረስ በቲዎሪና በተግባር መስልጠን  አለበት። በመጨረሻም ፈተናውን በበቂ ውጤት ካለፈ በኋላ በሚፈልገው የስራ-መስክ መቀጠር ይችላል። ከዚህ ስንነሳ ማንኛውም በሙያ የሚሰለጥንና ወደ ስራ መስክ የሚሰማራ ሰው  በጎሳ መነጽር የሚታይ መሆን የለበትም። ለአንድ ህዝብ ግልጋሎት የሚሰጥ ሰው ከጎሳ አስተሳሰብ ንጹህ የሆነና ደሞዝ ለሚከፍለው ህዝብ አስፈላጊውን ግልጋሎት መስጠት የሚችል መሆን አለበት። ይህ ነው ትክክለኛውና የሰለጠነው የአሰራር መንገድ። አቢይ አህመድና  አበበች አዳኔ መቅጠር የሚፈልጉትን ሰዎች የሚመለከቱት በዕውቀት ወይም በችሎታ መነጽር አይደለም። የሚመለከቱት በጎሳ መነጽርና ኮታ ለማሟላት ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና አካሄድም ፀረ ዕድገትና ፀረ ሰላም ነው። ባስቸኳይ መቆም ያለበት ነገር ነው። ሙስናንና የተበላሸን አሰራር የሚያስፋፋ ነው። በዚህ ዐይነቱ አካሄድም አንድን አገር ከገባችበት የተወሳሰበ ችግር በፍጹም ማላቀቅ አይቻልም። የድህነትንና የፀረ-ሰላም ዘመኑን ከማራዘም በስተቀር የሰፊውን ህዝብ የተቀን ተቀንና የረጅም ጊዜ ፍላጎትና ጥያቄ መመለስ አይቻልም።

 

በእኛ መሀከል የሚታየው ትልቁና ዋናው ችግር!

Do you please yourself with the fancy that you are doing a good job? You are mistaken.    

 Half the lives you save are not worth saving, as being useless; and almost the other half   

 out not to be saved, as being mischievous.”(Benjamin Franklin to his friend to the

  medical doctor)

በአገራችንም ሆነ ከውጭ ሆኖ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚደረገውን ትግል ለተመለከተ አብዛኛዎቻችን ለምን ዓላማ እንደምንታገል በፍጹም አለማወቃችን ብቻ ሳይሆን የምንመራበት ፍልስፍናና ሳይንስ ምን እንደሆኑ በፍጹም አለመታወቃቸው ነው። ለአገርና ለህዝብ የሚደረግ ትግል ደግሞ የግዴታ አንዳች ዐይነት ፍልስፍናና ሳይንሳዊ መመሪያ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ካለሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መመሪያ የሚደረግ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ጥፋት ብቻ ነው የሚያመራን። እንደሚታወቀው አንዳች ዐይነት ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መመሪያ የሌለው ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ግለሰብም ሆነ ድርጅት በፕሪንስፕል የሚመራ አይደለም። በፕሪንስፕል የማይመራ ገለሰብም ሆነ ፖለቲከኛ ደግሞ የሞራል ብቃት ሊኖረው በፍጹም አይችልም።

ሌላው በመሀከላችን ያለው ትልቁ ችግር በአንድ በኩል ለአገራችን እንታገላለን እያልን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ግለሰብአዊ ነፃነትንና አስተሳሰብን ለማዳበር ያልቻልን ነን። አብዛኛዎቻችን በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የማንሳተፍና ያላለፍንም ስለሆነ የተሟላ መንፈሳዊ ነፃነትን ማዳበር አልቻልንም። ስለሆነም አብዛኛዎቻችን ይህንን ወይም ያኛውን ግለሰብ፣ ወይም ደግሞ ይህንን ወይንም ያኛውን ድርጅት በጭፍን አምነን የምንከተልና ለትችታዊ አመለካከት ጭንቅላታችንን ክፍት ያላደረግን ነን። እንደሚታወቀው እንደዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ነው በተለይም በአብዮቱ ወቅት የታየውና እርስ በእርስ ለመገዳደል ምክንያት ሊሆን የቻለው። ምክንያቱም በድርጅቶች ውስጥ መሪዎች ከሚባሉት በስተቀር ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥና መከራከር ያልተለመደና የማይፈቀድም በመሆን አንድን ድርጅት በጭፍኑ የማመንና የመከትል ባህል ሊዳብር ቻለ። በመሰረቱ እንደዚህ ዐይነቱ አሰራርና ጭፍን ዕምነት ለፋሺዝም መሰረት የሚሆን ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ነው በአብዮቱ ወቅት የማርክሲዝምን ካባ በመልብስ የንዑስ ከበርቴው ፋሺዝም ሊስፋፋ የቻለውና መረን የለቀቀ የእርስ በርስ ግድያ ሊፈጸም የቻለው። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላና፣ በተለይም ደግሞ ከምርጫ 1997 ዓ. በኋላ አንድን ግለሰብና አንድን ድርጅት ማመን ዋናው ፈሊጥ ለመሆን በቃ። ማንኛውንም ነገር አንድ ግለሰብ እንደሚችልና እንደሚሰራ አድርጎ በማቅረብ ጥናትና ምሁራዊ ክርክር እንዳይዳብሩ መንገዱ ተዘጋ። ታዋቂ ግለሰቦችን ወይም አንድን ድርጅት በማምለክ በየቦታው የሚሯሯጡ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች አንዳንዴም እስከመሳደብና እስከመደባደብ የደረሱበት ጊዜ ነበር። ይህ ዐይነቱ ከምሁራዊ ብስለት የጎደለ አመለካከትና አንድን ግለሰብ ማምለክ በመሰረቱ የማንኛውንም ፍልስፍና መሰረተ-ሃሳብ የሚፃረርና ለተሟላ ዕድገትም እንቅፋት የሚሆን ነው።

ከዚህ ስንነሳ ሌላው በመሀከላችን ያለው ትልዩ ችግር አብዛኛዎቻችን ከዕውቀት ርቀን የምንገኝና፣ የተለያዩ ጋዜጣዎንና መጽሀፎችን ለማንበብ ጊዜ የሌለን ነው። ለዕውቀትም ኢንቬስት ለማድረግ በፍጹም አንፈልግም። አንዳንዶቻችን እንደምንም ብለን መጽሀፎች ጽፈን ለሺያጭ በምናቀርብበት ጊዜ ቢያንስ 50 € አውጥቶ ገዝቶ ለማንበብ የሚፈልግ የለም። እንደሚታወቀው ስለአገርና ስለዕድገት በምናወራበት ጊዜ ከዕውቀት ውጭ ምንም ነገር ለመስራት አንችልም። ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን ሰፋ ባለ ዕውቀት መሰረት ብቻ ነው አንድን አገር በተሟላ መልክ ለመገንባት የምንችለው። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድን አገር ለመገንባት በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ያስፈልጉናል። አንድ አገር ካለሳይንቲስቶች፣ ካለፈላስፋዎች፣ ካለኢንጂነሮችና የቴክኖሎጂ ሰዎችና ሌሎችም ዕውቀቶች በፍጹም ልትገነባ አትችልም። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ኢንቬስት ማድረግ፣ ማጥናትና መከራከር በጣም አስፈላጊ ነው። ምናልባት አንዳንዶቻችን ተገንዝበን እንደሆን ይህች ዓለም በመፈቃቀድና በመከባበር፣ አንደኛው ሌላውን በማገዝ የተገነባች አይደለችም። በአገሮች መሀከል ከፍተኛ ውድድር ያለና፣ በተለይም ደግሞ እንደኛ ያሉ አገሮች ባሉበት ቀጭጨው እንዲቀሩ ከፍተኛ አሻጥር ስለሚሰራ ይህንን ዐይነቱን አሻጥርና የሰላም ጠንቅ አካሄድ ለመታገልና ለመቋቋም የምንችለው በተወሳሰበ ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው።

ሌላውና ትልቁ ችግራችን ክሪቲካል አስተሳሰብ ምን እንደሆን አለማወቃችን ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ ሰዎች ክሪቲካል ሃሳብ በሚያቀርቡበት ወይም አንድን ነገር ከሌላ አንፃር ለማየት በሚፈልጉበት ጊዜና ትችትም ሲሰዘነዝሩ ይህ ዐይነቱ አቀራረብ እንደመጥፎ አካሄድ መታየቱ ነው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ሰፋ ባለ መልክ ለመተንተን እንደሞከርኩት ዛሬ የምንኖርበት ዓለምና፣ የምንጠቀምባቸው ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች በስንትና ስንት ትግል፣ ምርምርና ክርክር እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ እንደደረሱ ነው። ስለሆነም አንድ አገርና ህብረተሰብ እንዲያድጉና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆኑ ከተፈለገ የግዴታ መከራከር፣ የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን ዝም ብሎ አለመቀበል፤ ጥያቄ መጠየቅና መልስም ለማግኘት ጥረት ማድረግ ለተሟላ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ከዚህ አጭር ትንተና ስነሳ በተለይም በአለፉት ሃያ ዐመታት ብቻ እንደተከታተልኩት በየሚዲያው የሚቀርቡና በኤክስፐርት ስም ስለአንዳንድ ነገሮች አስተያየት እንዲሰጡ የሚጋበዙ የሚሰነዝሯቸው አስተሳሰቦች በተለያም የወጣቱን መንፈስ የሚበርዙና የማሰብ ኃይሉንም የሚያበላሹ ናቸው። አብዛኛዎች ጋዜጠኞችም ምሁራዊ ብስለት ወይም መሰረት የሌላቸው በመሆናቸው ለክሪቲካል አስተሳሰብ ክፍት የሆኑና የሚጠይቋቸውም ጥያቄዎች ከሳይንስ ጋር የሚገናኙ አይደሉም።  በተለይም የዩቱቭ ቻናል መክፍት ቀላል በሆነበት ዓለም ውስጥ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል የዩቱብ ቻናሎች በመክፈት ይህንን ወይም ያንን ሰው እየጋበዙ ህዝብን ማደናገር የተለመደ በመሆኑ ጥራት ያለው ሃሳብ እንዳይንሸራሸር ለመደረግ በቅቷል። ዩቱቭ ቻናሎችም የውሸታሞች፣ የኮንፒራሲ ዜናዎች ማሰራጫዎች፣ አልፎ አልፎ ደግሞ እጅግ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እየተጋበዙ እንደፈለጋቸው የሚዘባርቁባቸው መድረኮች ለመሆን በቅተዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ጋዜጠኛ ነን ባዮች አንድ ሰው ስንትና ስንት ወንጀል ከሰራ በኋላና ወንጀሉም እየታወቀ አገዛዙን ብቻ ስለተቃወሙ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችን እንደፖለቲከኞችና ለለውጥም እንደሚታገሉ አድርጎ ማቅረብ በጣም አደገኛ አሰራር ነው። ለምሳሌ ታምራት ላይኔና ልደቱ አያሌውን፣ እንዲሁም  ከአሜሪካን ጋር እጅና ጓንቲ ሆነው የሚሰሩና፣ ስልጣን ላይ ቢወጡም የአሜሪካንን እርኩስ ስራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉ አንዳንድ ግለሰቦችን እየጋበዙ “ገለጻ” እንዲሰጡ ማድረግ ከጋዜጠኛ ስነ-ምግባር ጋር የሚሄድ አይደለም። ስለሆነም ጋዜጠኞች ነን የሚሉና በዚህ ሙያ ተሰማርተው የሚሰሩ በቂ የፖለቲካ ቲዎሪ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የሚዲያ ባለቤቶች በውስጣቸው ውስጥ የስራ-ክፍፍል በማድረግ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ በሚፈልገውና በሚቀለው ሙያ መስለጠን አለበት። አንድ ጋዜጠኛ ስለአንድ ነገር በቂ ግንዛቤ ሲኖረው ብቻ ነው ክሪቲካል ጥያቄዎችን ለማቅረብ የሚችለው። ስለዚህ በአገራችን ምድር ለውጥ እንዲመጣ፣ ሰላም እንዲሰፍንና ህዝባችንም እፎይ ብሎ እንዲኖር የምንፈልግ ከሆነ የግዴታ እያሰብንና እያጠናን መስራቱ በጣም አስፈላጊ ነው። እንደዚህ ዐይነቱን ጽሁፍና በዚህ ግለሰብ የተዘጋጀውን ድረ-ገጽና የዩቱቭ ቻናል መደገፍና ማበረታታት ያስፈልጋል። እንደነዚህ ዐይነት ጽሁፎች ዝም ብለው የሚጻፉ ሳይሆን የብዙ ዐመታት የስራ ውጤቶችና አንድንም ጽሁፍ ለመጻፍ ሁለትና ሶስት ሳምንት መቀመጥ ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ብቻ ነው ለህዝብና ለአገር ትግል ማድረግ የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ!!

                                                   [email protected]

www.fekadubekele.com

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop