ምክንያተ ጽሕፈት- በብዙ የማከብራትና የማደንቃት አንዲት ወዳጄ የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በዓልን ምክንያት በማድረግ፤ “ዋጋችን ስንት ነው? ልካችንስ ምን ድረስ ነው?!” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ አካፈለችኝ። እናም ይህ የወዳጄ ጥልቅ መንፈሳዊ ሐሳብን ያዘለ መጣጥፍ ይህን ጹሑፍ አዋልዷል… ወዳጄ ልቤ ምስጋናዬ ካለሽበት ይድረስሽ ብያለኹ።
ዋጋችን/ልካችን ምን ድረስ ነው? ምን ያህልስ ነው? ልካችንን/ዋጋችንን በቅጡ ያለማወቅ የሚፈጥረው የማንነት ዝብርቅርቆሽና የሕይወት ስንክሳር የት/እምን ድረስ ነው? የሚለው ጥያቄ ከፍጥረት ማግሥት ጀምሮ በርካታ ሊቃውንትን፣ ፈላስፎችን በብርቱ ያነጋገረ፣ ያመራመረ ሰፊ ርእሰ ጉዳይ ነው። ወደእነዛ የጠቢባንና የፈላስፋዎቹ ሰፊ ሐሳብ/ትንታኔ ለመግባት ገጹም ጊዜውም አይፈቀድም። በአጭር ቃል፤ ሰው በመንፈሳዊውም ሆነ በሳይንሱ እውቀት ትንታኔ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ፣ የፍጥረት አለቃ፣ ምርጥ/የተመረጠ ነው። ይህ ሰው የተባለ ፍጥረት ደግሞ በፈጣሪው እጅግ የተወደደ፣ የተከበረ ነው።
በቤተክርስቲያናችን ሠለስቱ ምዕት/፫፻፲፰ ሊቃውንት በቅዳሴያቸው ስለዚህ በፈጣሪው ስለተወደደው ሰው ስለተባለው ፍጥረት ሲያመሰጥሩ፤ “አዳምን/ሰውን እግዚአብሔር ከምድር አፈር በውብ እጆቹ አበጃጀው፤ የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውን እጅግ ወደደው፤ ሳመውም።” ይሉናል።
እንዲሁም እንግሊዛዊው ተወዳጅና እውቁ ደራሲ ሼክስፒር “ሐምሌት” በተባለው ድንቅ የተውኔት ሥራው፤ “ሰው ከመላእክት ይልቅ የከበረ፣ የአምላኩ የፍቅር ማኅተም የታተመበት እንዴት ውብ፣ ድንቅ ፍጥረት ነው፣ ሐሳቡስ ምንኛ ምጡቅ፣ ረቂቅ ነው…፤” በማለት ይገልጸዋል።
ይህ በአምላኩ እጅጉን የተወደደ ፍጥረት ሰው በዓመፃና በኃጢአቱ ምክንያት ከክብሩ በተዋረደና ለሞት ፍርሃት ለሲኦል ባርነት ተላልፎ በተሰጠ ጊዜ እንኳን አምላክ ፈጽሞ አልተወውም። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ሊያድነው ሊቤዠው ወደደ፤ ፈቀደ እንጂ። እናም አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ!! ይህን ከሰው አእምሮ በላይ የሆነና ከማስተዋልም የሚያልፍ እግዚአብሔር ለሰው የገለጸውን ፍቅር የሰማይ ሰራዊት፣ መላእክቱ፤
“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ ሃሌሉያ!” ሲሉ ይህን ፍቅር እጅጉን ተደነቁበት፣ በአዲስ ዜማ፣ በአዲስ ሰማያዊ ቅኔም አወደሱት። ሰማይ ሰማያት፣ ምድርና ሞላዋም በዚህ ታላቅ ፍ-ቅ-ር እጅጉን ተደመሙ፤ ተገረሙበት።
ይህን አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ የሆነበትን የማዳን ፍቅሩን- ምሥራቃውያኑ ኦርቶዶክሳውያን የሥነ-መለኮት ምሁራንና የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት እንዲህ ሲሉ በአድናቆት ይገልጹታል፤ “እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ (ፍቅሩ) ይበልጣል፣ እጅጉንም ይልቃል።” ወዳጆቼ ይህን ምሥጢር በደንብ ለመረዳት ከቤተልሔም የከብቶች ግርግም እስከ ቀራኒዮ ጎልጎታ ድረስ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ ሰውን በመውደዱ የፈጸመውን የፍቅሩን፣ የማዳኑን ሥራ መመልከት፣ ማስተዋል ያስፈልገናል።
እግዚአብሔር ወልድ ከ፺፱ኙ በጎች ይልቅ የባዘነውን፣ የጠፋውን አንዱ በግ/የሰው ልጅ በዛው እንደጠፋ ይቀር ዘንድ ፍቅሩ አላስቻለውምና ሰውን ሊፈልገው ከሰማይ መጣ። የቤተክርስቲያናችን ሊቅ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው፤ “ኃያል እግዚአብሔርን ፍቅር ከመንበሩ ሳበው እስከሞትም አደረሰው፤” በማለት የዳንበት፣ የተመረጥንበት፣ የተወደድንበት አምላካዊ ፍቅር ምን ያህል ዘላለማዊ፣ ሕያው፣ ታላቅ፣ ዕፁብ እና ድንቅ… መሆኑን ያስረዳናል። በእውነትም እግዚአብሔር እኛን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ እኛን የወደደበት ፍቅር፣ ሰውን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል፣ ይደንቃልም።
በገዳማውያ አባቶች ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሰውን የወደደበትን ይህን አምላካዊ፣ አባታዊ ፍቅር የሚያዘክር አንድ ታሪክ አለ። አንድ መነኩሴ የሆኑ መናኝ አባት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማረውን፤ “አባታችን ሆይ!” የሚለውን ጸሎት በአንቃድዎ ሕሊና፣ በተመስጦ ሆነው ለረጅም ደቂቃዎች አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ በማለት ሲጸልዩ የሰማ አንድ ወጣኒ መናኝ፤ “አባታችን ጸሎቱን ይዝለቁት እንጂ “አባታችን ሆይ!” ብቻ እያሉ ቀሩ እኮ ሲል በመገረም ይጠይቃቸዋል።
እኚህ አባትም ሲመልሱለት፤ “ልጄ እንደ እኔ ያለውን ደካማና ኃጢአተኛ ባሪያውን የወደደበትን፣ ያፈቀረበትን የአምላኬን፣ የጌታዬን- የጌትነቱን ቸርነት፣ የአባትነት ፍቅሩን መቼ ተናግሬው፣ መቼ አሰላስዬው በቅቶኝ ወደሌላው ጸሎት ልዝለቅ ብለህ ነው። ልጄ ይህ ከአእምሮ፣ ከስማተዋልም በላይ የሚያልፍ እኔን፣ ሰውን ሁሉ ያዳነበት የአምላኬ፣ የአባቴ ፍቅሩ ሁሌም አዲስ ሆኖ ቢመስጠኝ፣ ቢያስገርመኝ ይኸው ዘወትር አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ፣ አባታችን ሆይ ስለው እውላለኹ…
ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር እኛን የወደደበት፣ ያዳነበት ፍቅር ልክም፣ ወደርም የለውምና በዚህ ፍቅር ውስጥ ሆኜ ይህን ታላቅ፣ ቸር አባት ሁሌም አባታችን ሆይ እለዋለኹ …።” ሲሉ መለሱለት።
“ከተፈጠርንበት ጥበብ ይልቅ የዳንበት ፍቅር/ጥበብ ይበልጣል…!!”
መልካም የትንሣኤ በዓል!
ሰላም!!