“የአፍሪቃ ችግር ቅኝ መገዛቷ ሳይሆን ነጻ መውጣቷ ነው” (ቦሪስ ጆንሰን፣ ያሁኑ የእንግሊዝ ጠሚ) (Africa’s problems is not that we were once in charge, but that we are not in charge anymore) Boris Johnson, Current Prime minister of UK
መንደርደርያ
- የእንግሊዝ መንግስትበሕቡእ እየከፈላቸው ወደ ዮክሬን የሚዘምቱትን ባብዛኛው ሥራአጥ የሆኑትን የእንግሊዝ ቦዘኔወች፣ ጀግኖች እያለ የሚያወድሰው የምዕራባውያን ቀንደኛ የቱልቀዳ (propaganda) መሣርያ የሆነው የእንግሊዙ ቢቢሲ (BBC)፣ ወደ ሩሲያ ለመዝመት የሚፈልጉትን ጦቢያውያን ደግሞ የሚልሱት የሚቀምሱት ስለሌላቸው ቀትላደር (በቀትል፣ በመዋጋት፣ በጦርነት የሚተዳደር፣ mercenary) ለመሆን የተገደዱ ምስኪኖች እያለ ሊሳለቅባቸው ይሞክራል፡፡
- የዩክሬኑ ዜሌንስኪ(Zelensky) ከሴኔጋልና ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ቀትላደሮችን (mercenaries) እንዲቀጥር ከፍተኛ ገንዘብ የመደበለት የእንግሊዙ ቅኝናፋቂ (neocolonialist) ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson)፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ ሩሲያን በቀትላደር ቀጣሪነት ለመወንጀል ይጣጣራል፡፡ እንግሊዛዊ ቀትልአደሮች በሩሲያውያን ሲማረኩ ደግሞ የሹም ዶሮ ናቸው እሽ አትበሏቸው ይላል፡፡
- የአማራ ሕዝብ የህልውና ጠላቶች የሆኑት ወያኔወችና ኦነጋውያንደግሞ ከቢቢሲ እና ከቦሪስ ጆንሰን ጋር ተቀናጅተው ወደ ሩሲያ ለመዝመት የሚፈልጉትን ጦቢያውያን አንገት ለማስደፋት ያሌ የሌለ የስድብ መዓት ያወርዱባቸዋል፡ምክኒያታቸውን ለመረዳት ደግሞ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ ርዕስ የጦመርኩትን ጦማር በድጋሚ ማንበብ ይበቃል፡፡ ከመጠነኛ ለውጥ ጋር በድጋሚ እነሆ፡፡
የፋኖ ሻለቃ ሩሲያ ይዝመት
ያገራትንና ግንኙነት በተመለከተ፣ ‹‹ቋሚ ጥቅም እንጅ ቋሚ ወዳጅ ወይም ቋሚ ጠላት የለም›› (There are no permanent enemies, and no permanent friends, only permanent interests) የሚል አባባል አለ፡፡ ባለመታደል ግን ይህ አባባል ለኢትዮጵያ አይሠራም፡፡ ኢትዮጵያ መሠረታዊና ዘላለሚዊ የሆነች ጠላች አለቻት፡፡ ይህችም ጠላት ገብጽ፣ ወይም አሜሪቃ፣ ወይም ፈረንሳይ ወይም ጣልያን አይደለችም፡፡ ስኮተትላንድም፣ ሰሜን አይርላንድም፣ ዌልስም አይደለችም፡፡ ይህች የኢትዮጵያ መሠረታዊና ዘላለማዊ ጠላት፣ እንግሊዝ የምትባል መሠሪ አገር ናት፡፡
ኢትዮጵያን በተመለከተ የእንግሊዝ መቸም የማይለወጥ ቋሚ ወጀም (ፖሊሲ፣ policy)፣ በርስበርስ ጦርነትና በመሳሰሉት ምክኒያቶች መቸም የማያልፍላት ዘላለማዊ ቆርቋዛ እንድትሆን ማድረግና፣ ለዚህ የተዳረገችው እንደነ ኬንያ ቅኝ ባለመገዛቷ መሆኑን በቀጥታና በተዛዋሪ በመስበክ፣ አፍሪቃ ቅኝ በመገዛቷ ተጠቀመች እንጅ ምንም አልተጎዳችም የሚል እሳቤ መፍጠር ነው፡፡ ቀንደኛው ቅኝናፋቂ (neocolonialist) ያሁኑ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson) “የአፍሪቃ ችግር ቅኝ መገዛቷ ሳይሆን ነጻ መውጣቷ ነው” (Africa’s problems is not that we were once in charge, but that we are not in charge anymore) እስከማለት የደረሰው በዚህ እሳቤ መሠረት ነው፡፡
ባጭሩ ለመናገር የእንግሊዝ ዓላማ ጥቁሮች ነጭን ድል ባደረገችው በጦቢያ ከመኩራት ይልቅ እንዲያፍሩባትና የነጭን የበላይነት በጸጋ እንዲቀበሉ፣ ጦቢያን አሳፋሪ ለማድረግ፣ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የእንግሊዝ ሰፋሪወች የበላይ የሆኑባት አሜሪቃም፣ ነጮችን ድል ባደረገቸው በሄይቲ (Haiti) ላይ የምትከተለው ቋሚ ወጀም (ፖሊሲ፣ policy) ይህንኑ ነው፡፡ ምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች (neocolonialists) ዓለምን በበላይነት በመቆጣጠር ሁሉን በጃቸው በደጃቸው እስካደረጉ ድረስ፣ የጥቁሮች አሸናፊነት ተምሳሌቶች የሆኑት ኢትዮጵያና ሄይቲ በርስበርስ ጦርነት እየተተራመሱና በድህነት ወለል ላይ እየማቀቁ ጥቁሮችን ማሸማቀቂያ እንዲሆኑ ለማድረግ የማያደርጉት የለም፡፡
የጦቢያ ዐበይት ችግሮች (በተለይም ደግሞ ከጎጠኝነት የሚመነጩ ችግሮች) ክራቸው ቢመዘዝ፣ ሂደው፣ ሂደው ጫፋቸው የሚገኘው ከቁጥር አስር ዳውንኒግ መንገድ (Number 10 Downing Street) ነው፡፡ አሜሪቃን ጨምሮ ሁሉም ምዕራባውያን አገሮች የኢትዮጵያ ወጀማቸውን (ፖሊሲያቸውን) የሚወጅሙት (የሚያረቁት)፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ጠበብቶች ናቸው በሚባሉት በመሠሪወቹ በእንግሊዞች ምክር መሠረት ነው፡፡ ባሜሪቃና በሌሎች የምዕራባውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውስጥ የኢትዮጵያን ጉዳይ በበላይነት የሚቆጣጠሩት የአንግሊዝ ዘር ያላቸው ፀረጦቢያወች ወይም ደግሞ በነዚህ ፀረጦቢያወች የተመረዙ ባለስልጣኖች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሳይደግስ አይጣላምና፣ አገራችን ጦቢያ ዘላለማዊ ጠላት ብትኖራትም፣ በዚያው አንጻር ደግሞ ዘላለማዊ ወዳጅ የሆነች፣ በጭንቅ ቀን ሁልጊዜም የምትደርስላት አገር አለቻት፡፡ ይህችም የጦቢያ ዘላለማዊ ወዳጅ ሩሲያ ናት፡፡ ባድዋ ጦርነት ጊዜ የሩሲያ ቄሳር፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ እስታሊን፣ በሶማሌ ወረራ ጊዜ ብሬዥኔቭ፣ የጦቢያ ወዳጅነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ምዕራባውያን ኖቤል የሸለሙት ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ በምዕራባውያን እየታገዘ የጦቢያ ምሰሶ በሆኑት በአማራ ሕዝብና በተዋሕዶ ላይ የሚያወርደውን መቅጸፈት በጽኑ የሚቃወመው የሩሲያው የቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ነው፡፡
ሩሲያኖች ይህን ሁሉ ለጦቢያ የሚያደርጉት ደግሞ ከጦቢያ ምንም ሳይጠይቁና ሳያገኙ ነው፡፡ አሜሪቃ በጦቢያ ላይ የገነባችው አንድ ነገር ቢኖር ለስለላ የምትገለገልበትን ቃኘው ጣቢያን (Kagnew Station) ብቻ ነበር፡፡ በንጉስ ኃይለ ሥላሴ በምትደዳደረው ጦቢያ ውስጥ የሚገኘውን ብቸኛውን ነዳጅ ማጣሪያ አሰብ ላይ የገነቡት ግን ኮሚኒስቶቹ ሩሲያኖች ነበሩ፡፡ ባልቻ ሆስፒታልና ባህርዳር ፖሊቴክኒክም የሩሲያ ቱርፋቶች ናቸው፡፡
መውደድ አይምሯዊ ሳይሆን ልቦናዊ ስለሆነ ምክኒያት አልባ ነው፡፡ የሚወድህ ሰው አረክለትም አላረክለትም ይወድሃል፡፡ ሩሲያም የፑሽኪንን አገር ኢትዮጵያን የምትወዳት ስለምትወዳት ብቻ ነው፡፡ የሩሲያ አምባሳደር ጥርት ያለ አማረኛ የሚናገሩ መሆናቸው ብቻ፣ ሩሲያ ስለ ኢትዮጵያ ስላላት አመለካከት ብዙ ይናገራል፡፡ በሌላ በኩል ግን መኻል አዲሳባ ላይ ተንሰራፍቶ በጋሻ የሚለካ ርስት የያዘው የእንግሊዝ ኤምባሲ፣ የኤምባሲው ሠራተኞች ኣማረኛ እንዲናገሩ ማበረታታት ይቅርና፣ የእንግሊዘኛ ትምህርት ቤት ከፍቶ ንግዱን እያጧጧፈ፣ የኢትዮጵያን ልጆች አማረኛ መናገርና ዲንጋ መወርወር ያስቀጣል እያለ በማስተማር፣ ከገዛ ሕዝባችን በሚዘርፈው በገዛ ገንዘባችን እገዛ አገራችን ላይ ያዋርደናል፣ ይልቁንም ደግሞ እንዲያዋርደን እኛው ራሳችን ፈቅደንለታል፡፡
ያገራቸን የጦቢያ የጭንቅ ቀን ደራሽ ሩሲያ፣ አሁን ላይ ደግሞ እሷ ራሷ በተወሰነ ደረጃ ጭንቅ ላይ ትገኛለች፡፡ ምዕራባውያን ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው እሷ ላይ በመረባረብ ህልውናዋን ክፉኛ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም፣ ትንሽ፣ ትልቅ ሳይባል ማናቸውም ዓይነት እገዛ ያስፈልጋታል፡፡ የኢትዮጵያን ወዳጅ ሩሲያን በተቻለው አቅሙ ቢያግዛት የሚወደው ደግሞ ኢትዮጵያን የሚወደው የአማራ ሕዝብ ነው፡ የአማራ ሕዝብ ደግሞ ባሁኑ ጊዜ እሱ ራሱ ጭንቅ ላይ በመሆኑ፣ ሩሲያን እምብዛም ማገዝ ባይችልም፣ ያለውን እስከወረወረ ድረስ ፈሪ አይባልም፡፡
በተለይም ደግሞ አንድ ሻለቃ ወይም ከዚያ በላይ የአማራ ፋኖ ወደ ሩሲያ ቢዘምትና አስፈላጊው ሥልጠናና መሣርያ ተሰጥቶት ዩክሬን ላይ ቢሰማራ፣ አፍሪቃን ዳግም ቅኝ መግዛት አለብን ብሎ የፎከረው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson) በወዶ ዘማችነት ሽፋን የሚያሰማራቸውን የእንግሊዝ ወታደሮች እየገረፈ ልክ በማስገባት ለሩሲያ ከፍተኛ ውለታ ሊውልላት ይችላል፡፡ ይህ ውለታ ደግሞ የጦቢያንና የሩሲያን ወዳጅነት በደም ያስተሳስረዋል፡፡ ፋኖ ደግሞ ከሩሲያውያን የሚቀስመውን የመሣርያ አጠቃቀምና ወታደራዊ ጥበብ በመጠቀም፣ የአማራ (ስለሆነም የጦቢያ) ጠላት የሆኑትን ወያኔንና ኦነግን በቀላሉ አክስሞ የአማራን (ስለሆነም የጦቢያን) ቀጣይነት ማረጋገጥ ይችላል፡፡ የፋኖ ሩሲያ መዝመት፣ ጥቅሙ ለሩሲያ ብቻ ሳይሆን ራሱ ፋኖ ለቆመበት ዓላማም ጭምር ነው፡፡
ሰው ሁሉ እኩል ነው (all men are created equal) የሚል በወረቀት ላይ ብቻ የተወሰነ ሕገመንግሥት በመጻፋቸው የሚመጻደቁት ጆርጅ ዋሽንግተን (George Washington) እና ቶማስ ጀፈርሰን (Thomas Jefferson) ጥቁሮችን ጽፈት ለመማር ሞክራችኋል በማለት ጣቶቻቸውን በሚያስቆርጡበት ዘመን፣ የሩሲያው ቄሣር ታላቁ ጴጥሮስ (Peter the Great) ግን፣ ኦቶማን ቱርኮች በባርነት የሸጡለትን የታላቁን ቀያኔ (poet) የእስክንድር ፑሽኪንን (Alexander Pushking) አያት፣ ኢትዮጵያዊውን አብርሐም ጴጥሮስ ሃኒባል (Abram Petrovich Hannibal) የክርስትና ልጁ አድርጎ፣ ፈረንሳይ ድረስ ልኮ በመድፈኛነት አስተምሮ በማስመረቅ የሩሲያ ቄሣር ጦር ዋና ጀነራል (Imperial Russian Army general-in-chief) አድርጎት ነበር፡፡
ፋኖወች ዩክሬን ቢዘምቱ ደግሞ፣ በጦቢያዊ ጀግንነታቸው ሩሲያንም ጦቢያንም አኩርተው፣ የጦቢያን ዘላለማዊ ጠላት እንግሊዝን አሳፍረው፣ ጥቂቶቹ ፋኖወች አያታቸው አብርሐም ሃኒባል ከደረሰበት ከፍተኛ ወታደራዊ ደረጃ የማይደርሱበት ምንም ምክኒያት የለም፡፡
የዩክሬን ጦርነት ምዕራባውያን ከሩሲያ ጋር የሚያደርጉት የውክልና ጦርነት (proxy war) እንጅ ከዩክሬን ብሔራዊ ጥቅም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ የምዕራባውያን ዓላማ ዓለምን ሙሉ በሙሉ እንዳይቆጣጠሩ እንቅፋት የሆነችባቸውን ሩሲያን ክፉኛ በማሳፈር፣ ከቻሉም ደግሞ ድምጥማጧን በማጥፋት፣ ለሌኛዋ ተገዳዳሪያቸው ለቻይና ማስፈራሪያ ማድረግ ነው፡፡ ከሩሲያ ጋር እየተዋጉ፣ ትኩረታቸው ቻይና ላይ መሆኑ በግልጽ የሚመሰክረው፣ የዩክሬን ጦርነት በዩክሬን ስም ይሁን እንጅ ለዩክሬን ሲባል አለመሆኑን ነው፡፡ በለስ ቀንቷቸው ሩሲያንና ቻይናን ካሸነፉ ደግሞ በቀጥታ የሚያመሩት ወደ አፍሪቃ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ቦሪስ ጆንሰንም ዩክሬን ላይ የተቀሰቀሰውን እሳት ከማንም በላይ እየቆሰቆሰ የሚያራግበው፣ የረዥም ጊዜ ሕልሙን እውን ማድረጊያ ሁኖ ስላገኘው ብቻ ነው፡፡
ዩክሬን የተጎዳቸው ምዕራባውያን ሩሲያን ለመፋለሚያ የመረጧት ያልታደለች የጦር ሜዳ በመሆኗ ብቻ ነው፡፡ እንደ እንግሊዝና አሜሪቃ አያያዝ ከሆነ ደግሞ የኑክሌር አርማጌዶን ልትሆን የተቃረበች ትመስላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ዩክሬናውያን ከማንም በላይ መውቀስ ያለባቸው ዜሌንስኪ (Zelensky) የሚባለውን የራሳቸውን ቧልተኛ መሪ ነው፡፡ ይህ ሩሲያጠል (russophobic) ግለሰብ፣ የኑክሌር ትራጀዲን ከቲቪ ኮሜዲ መለየት የማይችል፣ በቤቱ ውስጥ ያለው ነጻነት ጎረቤቱን ለማስሸበር ቀርቶ ለመረበሽ መብት እንደማይሰጠው ያልተረዳ፣ ለኪውባ (Cuba) የሠራው ለዩክሬን መሥራት እንዳለበት የማያውቅ ወይም እንዲያውቅ ያልተደረገ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ምዕራባውያን እንደ ትልቅ ጀግና እየቆጠሩት፣ ዘረኛው ዊንሰተን ቸርችል (Winston Churchill) በየቦታው እየተዘዋወረ ቱልቱላውን ይነፋ እንደነበረው፣ እሱንም ቱልቱላውን እያስነፉት ከፍተኛ አድናቆት እስከቸሩት ድረስ፣ ዩክሬኖች ጨርሰው ቢያልቁ ግድ የሌለው አረመኔ ነው፡፡
ነገሮችን ሳሰላስላቸው የዩክሬኑ ዜሌንስኪ እና የጦቢያው ዐብይ አሕመድ በተወሰነ ደረጃ ይመሳሰሉብኛል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ሁለቱም አጭበርባሪ ተውነቴኞች ናቸው፡፡ የዜሌንሰኪ ዓላማ ለዩክሬን የቆመ መስሎ ዮክሬኖችን እና ሩሲያኖችን በማጨፋጨፍ ምድሩን ባድማ አድርጎ የስላቮችን አገር የምዕራባውያን የርሻ መሬት (lebensraum) በማድረግ የነ ሂትለርን ምኞት ማሳካት ነው፡፡ የኑክሌር ጦርነት እንዲቀሰቀስ የሚቋምጠውም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡ የዐብይ አሕመድ ዓላማ ደግሞ አንዴ ከትግሬ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአማራ ጋር የወገነ እየመሰለ፣ በአማራና በትግሬ መካከል እሳት እየለኮሰና እያቀጣጠለ፣ አማራና ትግሬን እርስ በርስ አጫርሶና አወዳድሞ፣ የአማራና የትግሬን ምድር ባድማ በማድረግ የኦሮሞን አጼጌ (Oromo Empire) በመላው ጦቢያ ላይ መመሥረት ነው፡፡
ዩክሬኖችን ከሩሲያኖች ጋር እንዲያጨፋጭፍ ዜሌንስኪን በገፍ የሚያስታጥቁት ምዕራባውያን፣ ዘወር ብለው ደግሞ ዩክሬኖች ላይ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጸመ በማለት የአዞ እንባ እያለቀሱ፣ የሩሲያ ጦር የበላይ አዛዥ የሆነውን ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ (war criminal) ብለው በይፋ ከሰውታል፡፡ በዚህ እሳቤያቸው መሠረት ትግራይ ላይ ተፈጽመዋል ብለው በሰፊው ለሚያስወሯቸው ወንጀሎች የመጀመርያው ተጠያቂ ማድረግ የነበረባቸው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆነውን ዐብይ አሕመድን ነበር፡፡ ዐብይ አሕመድ ግን መለስ ዜናዊን የተካ፣ መለስ ዜናዊን በሚያስንቅ ሁኔታ አማራን የሚነክስላቸው ውሻቸው ስለሆነ፣ ዝንቡን እሽ አይሉም፡፡
ምዕራባውያን ቅኝናፋቂወች (neocolonialists) በተለየም ደግሞ እንግሊዞች የአማራ ሕዝብ መሠረታዊና ዘላለማዊ ጠላቶች የመሆናቸውን ጉልህ ሐቅ የአማራ ሕዝብ እያነቀውም ቢሆን መዋጥ አለበት፡፡ እነዚህ ምዕራባውያን በአማራ ሕዝብ ላይ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ስለተፈጸሙት፣ በማስረጃ የተደገፉ፣ ሊካዱ የማይችሉ ጭፍጨፋወች ትንፍሽ ሳይሉ፣ ትግራይ ላይ ተፈጸሙ ስለተባሉ ማስረጃ ስለሌላቸው ወንጀሎች አለመጠን የሚጮኹት፣ ፋኖን በጦር ወንጀለኝነት ፈረጀው በማጥፋት፣ የአማራን ሕዝብ ለወያኔና ለኦነግ ጭራቆች አሳልፎ ለመስጠት ነው፡፡ ዋና መሠረቱ እንግሊዝ ላይ የሆነው (በሰበአዊ መብት ሰበብ የምዕራባውያን ቅኝናፋቂወችን አጀንዳወች ለማራመድ የተቋቋመው) አምንስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty Internatioal) የሚባለው የቅኝናፋቂወች ድርጅት በቅርብ ጊዜ በወልቃይት ላይ ያቀረበው ፀራማራ ዘገባም ሌላ ምንም ሳይሆን የዚህ ጉልህ ሐቅ ጉልህ ነጸብራቅ ነው፡፡
ስለዚህም ፋኖ ምዕራባውያን ቅኝናፋቂወችን ዩክሬይን ላይ መዋጋት ያለበት፣ ለሩሲያ ሲል ብቻ ሳይሆን፣ ለራሱም ሕልውና ጭምር ነው፡፡ ባጠቃላይ ደግሞ አፍሪቃውያን ቦሪስ ጆንሰን በግልጽ እንደዛተው የእንግሊዝ ጭራቅ ተመልሶ መጥቶ ቦጫጭቆ ሳይበላቸው በፊት፣ ዩክሬን ላይ የተፈጠረላቸውን መቸም የማይገኝ እድል በመጠቀም፣ ሳይቀደሙ ቀድመው፣ ጭራቁን እራሱ ጓሮ ሂደው ጨርቅ ማድረግ አለባቸው፡፡
መስፍን አረጋ
[email protected]