ባሳለፍነው ሳምንት ዐርብ እለት በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ፣ ራስ መኮንን አዳራሽ፤ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር፣ በፕ/ር አሉላ ፓንክረስትና ባልደረቦች አስተባባሪነት “ናፍቆት” በሚል ርእስ በእስራኤላዊቷ አንትሮፖሎጂስት በ ፕሮፌሰር ማልካ ሻበቴይ የተዘጋጀ አንድ ጥናታዊ/ዘጋቢ/ፊልም ቀርቦ ነበር፡፡ የዚህ ፊልም አዘጋጅ የሆኑት ዶ/ር ሻበቴይ ኢትዮጵያን ለ40 ዓመታት ያህል እንደሚያውቋትና በኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤሎች ላይም ለበርካታ ዓመታት ጥናት እንዳደረጉ፤ ይኸው ፊልማቸውም የዚህ ጥናትና ምርምራቸው ውጤት መሆኑን ነበር የነገሩን፡፡
ፕ/ር ሻበቴይ “ናፍቆት” የሚለው ዘጋቢ ፊልም አካል የሆነ “the Hidden Jews of Ethiopia: the Beta Israel of Kechene and North Shawa” በሚል የረጅም ዓመታት የምርምር ሥራቸው ውጤት የሆነ መጽሐፍም በዚሁ ዓመት ለሕትመት አብቅተዋል፡ ከቀጨኔ ሰፈር ተነስቶ ሰሜን ሸዋ ባሉ ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤላውያን ባቋቋሟቸው ጥንታዊ ገዳማቶቻቸውንና የመኖሪያ መንደራቸውን መሠረት አድርጎ የተሠራው ይኸው ጥናታዊ ፊልም ስለ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤላውያን በጣሙን አስገራሚ፣ አስደናቂም አሳዛኝም የሆኑ ታሪኮችን የያዘ ነው፡፡
በሰሜን ሸዋ፣ በተራራ በተከበቡና የተፈጥሮ ውብታቸው ትንግርት በሆኑ ሸለቆዎች ውስጥ ማንነታቸውንና ታሪካቸውን ጠብቀው፤ ጥንታዊውን የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮ እየፈጸሙ የኖሩት እነዚህ ማኅበረሰቦች፤ “ሰቃልያነ ክርስቶስ፣ የተረገሙ ሕዝቦች፣ ጠይቦች፣ ካይላዎች፣ ሰውን የሚበሉ/ቡዳዎች… ወዘተ” የሚል የውርደት፣ የሃፍረት ስም ተሰጥቷቸው ለዘመናት ኑረዋል፡፡
“ናፍቆት” በሚል ርእስ የቀረበው ዘጋቢ ፊልምም፤ ኢትዮጵያውያኑ ቤተ እስራኤላውያን በተለያዩ ዘመናት የደረሰባቸውን ከመርግ የከበደ መከራቸውንና ሰቆቃቸውን፤ ብሶታቸውንና ናፍቆታቸውን፣ የቀደሙ አባቶቻቸውን ተስፋና የፍቅራቸውን ውል ኪዳን ነው የሚተርከው፡፡
በዚህ ፊልም ሥራ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የኢትዮጵያውያኑ ቤተ እስራኤላውያን፤ የእነርሱንና የሕዝባቸውን የዘመናት ሰቆቃቸውንና መከራቸውን፤ ብሶታቸውንና ናፍቆታቸውን ብቻ አይደለም በፊልሙ ውስጥ የሚተርኩት፤ የሚያወሱት፡፡ በሚያስደንቅ መልኩ የትውልድ ሀገራቸውን፣ ኢትዮጵያን ከእስራኤል ጋር ያስተሳሰረውን የሺሕ ዓመታት የታሪክ ድርና ማግ፤ የሃይማኖት፣ የባህልና የትውፊት መወራረስንም ጭምር የሚዘክር፣ የሚያስታውስ ነው፤ ና-ፍ-ቆ-ት ዘጋቢ ፊልም!!
እስራኤላውያን በአምልኮ ቀርሽ ፍቅር ከሚወዱትና ከሚያከብሩት ነጻ አውጪያቸው ከሊቀ ነቢያት ሙሴና ኢትዮጵያዊ ባለቤቱ ሲፓራ ጀምሮ- በጥበብ ፍቅር ነፍሷ ተንድፎ ኢየሩሳሌም ድረስ በተጓዘችው በኢትዮጵያዊቷ የንግሥተ ሳባና በአይሁዳዊው ንጉሥ ሰለሞን ፍቅር ድረስ በዘለቀው ግንኙነት ውስጥ፤ የሁለቱ ሀገራት፣ የሁለቱ ሕዝቦች የኢትዮጵያውያንና የእስራኤላውያን ዘመናትን ያስረጀ አስደናቂ የሆነ የታሪክ ትስስር፣ የፍቅር ውል ኪዳንና ሕያው የተስፋ ቃል፤ በፕሮፌሰር ሻበቴይ “ናፍቆት” ጥናታዊ ፊልም ውስጥ በሚገባ ተንጸባርቋል፡፡
ከአዲስ አበባ፣ ቀጨኔ ሰፈር እስከ ሰሜን ሸዋ ባሉ የቤተ እስራኤላውያኑ ኢትዮጵያውያን ጥንታውያን ገዳማት ድረስ የተዘረጋው “የናፍቆት” ፊልም ዐፅመ ታሪክ ነፍስና ሥጋ ድረስ ዘልቆ አጥንትና ጅማትን ለይቶ እስከሚወጋ ድረስ የኢትዮጵያውያኑን ቤተ-እስራኤላውያን- የዘመናት ብሶታቸውንና ትዝታቸውን፣ ብርቱ ናፍቆታቸውንና፣ ከብረትም የጠነከረ የመንፈስ ጽናታቸውን፣ ከመርግ የከበደ የመከራቸውንና የሰቆቃቸውን ድንበር ተሻገሮ- ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን፣ የአባቶቻቸውን ሕያው የተስፋ ቃል እና የፍቅራቸውን ዘላለማዊ ውል/ኪዳን የተሸከመና ከፍ ያደረገ ነው፡፡
“በናፍቆት” ፊልም ላይ ያየናቸው ኢትዮጵያውያኑ ቤተእስራኤላውያን የዕድሜ ባለጸጋ አባቶችና እናቶች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ልጆቻቸው፣ ለረጅም ዓመታት በምንኩስና ሕይወት ተወስነው ፈጣሪያቸውን በማገልግል የሚኖሩ አረጋውያን ሁሉም በአንድነት- የአባቶቻቸውን የተስፋ ምድር የሆነችውን፣ የዳዊትን ከተማ ኢሩሳሌምን በዓይነ ሕሊናቸው በሩቅ አሻግረው እየተመለከቱ ማንነታቸው እንዳይጠፋ፣ ታሪካቸው እንዳይበረዝ በጸሎት፣ በመንፈስ የሚጋደሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አረጋውያን አባቶችና እናቶች ቤተ-እስራኤላውያኑ አዲሱ፣ ወጣቱ ትውልድ ማንነቱን የዘነጋ፣ ከታሪኩ የተፋታ፣ የቀደሙ አባቶቹን የተስፋ ቃል የረሳ ብኩን፣ ፈሪ ትውልድ እንዳይሆንም የአባቶቻቸውን ውርስ- የፍቅር፣ የተስፋ ቃል ኪዳን ዘወትር ደግመው ደጋግመው ያሳስቧቸዋል፤ ያስታውሷቸዋልም፡፡
በዚህ ፊልም ውስጥ የሚታዩት የቀጨኔ ሰፈር ቤተ እስራኤላውያን ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸውም ለረጅም ዓመታት ከማኅበረሰቡ ተገለውና ተንቀው የቆዩበትን ደካማና ስሑት እሳቤ ለመሻር ብዙ ደክመዋል፡፡ ማንነታቸው፣ ታሪካቸው ታውቆ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅርና በሰላም ለመኖር ያደረጉት ጥረታቸው፣ ድካማቸው በጥቂቱም ቢሆን ፍሬ ያፈራ ይመስላል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ኢትዮጵውያኑ ቤተ-እስራኤላውያን ተሳክቶላቸው ወደ አባቶቻቸው ተስፋ ምድር ወደ ኢየሩሳሌም በሚሻገሩበት ጊዜ እንኳን ኢትዮጵያን በልባቸው ጽላት ተሸክመዋት የሚጓዙ፣ የቃል ኪዳን ታቦታቸው፣ የሁልጊዜም ናፍቆታቸውና ትዝታቸው እንደሆነች ነው ደጋግመው የሚናገሩት፡፡
“በናፍቆት” ፊልም ምረቃ ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አቶ አለልኝ አድማሱም ይህንን እውነታ በእንዲህ መልኩ ነበር ከፍ ያደረጉት፡፡ ክቡር አምባሳደሩ በንግግራቸው፤ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ስላለው ዘመናትን ያስረጀ ታሪካዊ ግንኙነት፣ ጥብቅ ስለሆነው የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የሃይማኖት፣ የባህልና የትውፊት ውርርስን አስመልክተው ሲናገሩም፤
ከተወለዱባትና ካደጉባት ጎንደር የፋሲል ከተማ እስከ አገረ እስራኤል የታተመውን የማንነታቸውን ሕያው አሻራ፣ በሕዝባቸው አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክና ቅርስ፤ በቀደሙ አባቶቻቸው የተስፋ ቃል ኪዳን ውል መካከል… ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከአብርሃም እስከ መልከጸዴቅ፣ ከሙሴ እሰከ ኢትዮጵያዊ ሚስቱ ሲፓራ፣ ከንግሥተ ሳባ እስከ ንጉሥ ሰለሞን፣ ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ባኮስ እስከ ሐዋርያው ፊሊጶስ፣ ከሰለሞን ቤተመቅደስ እስከ ከዴር ሱልጣን ገዳምና የላሊበላ የዐለት ውቅር አብያተ ክርስትያናት… ወዘተ በሁለቱ ሕዝቦች (በእስራኤላውያንና በኢትዮጵያውያን) የታሪክ ሰንሰለት ውስጥ- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የደመቀና ያማረ፣ የከበረና የገዘፈ ታላቅ ማንነት እንደሆነ ነው ከታሪክ በማጣቀስ በታላቅ ክብርና ኩራት ያነሱት፤ ያወሱትም፡፡
በአጭር ቃልም፤ ኢትዮጵያውያኑ ቤተ-እስራኤላውያን የእነዚህ የሁለቱ አገራትና ሕዝቦች- የኢትዮጵያና የእስራኤል የታሪክ እውነት መሠረትና ድልድይ፤ ሕያው ምስክርና ቅርስ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት- ከአብርሃም እስከ መልከ ጸዴቅ፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ መሐመድ፣ ከግሪካውያኑ ጠቢባንና ፈላስፎች ከሔሮዱተስ እስከ ሆሜር… የአምላክ ስጦታ፣ የተፈጥሮ ውበት ምስጢር/ትንግርት፣ የእውነትና የፍትሕ ማንፀሪያ፤ ሚዛን፣ የሰውነት ክብር ትልቅ መገለጫ ነው!!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት- ከመተማ ጉርዓና ጉንደት፣ ከመቅደላ ዶጋሊና የዐድዋ ተራሮች አስገምግሞ ለመላው ዓለም የተሰማ፣ የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕቦች የነጻነት ብስራት ድል ነው፤ ኢትዮጵያዊነት- ከአፍሪካ እስከ ሰሜንና አሜሪካና ላቲን አሜሪካ፣ ጃሜይካና ካረቢያን፣ ጃፓንና ቻይና ድረስ የተተከለ የፍቅር፣ የሰው ልጅ ክቡር ማንነት ትእምርት /Symbol/ እና የባርነትን ድቅድቅ ጨለማ የገፈፈ የነጻነት የብርሃን ዓምድ ነው!!
የኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ- ከጆሞ ኬንያታ እስከ ጋናው የነጻነት አባት ክዋሜህ ንኩሩማ፣ ከደቡብ አፍሪካዊው የፀረ አፓርታይድ ታጋይና አርበኛ ኔልሰን ማንዴላ እስከ ታቦ እምቤኪ፣ ከሮዛ ፓርክ እስከ ዊኒ ማንዴላ፣ ከፓን አፍሪካኒስቶቹ ከማርከስ ጋርቬይ እስከ ዊልያም ዱ ቦይስ፣ ከኪንግ ማርቲን ሉተር እስከ ባራክ ኦባማ… ወዘተ ያበራ፣ የደመቀ የነጻነት ችቦ፣ የነታነጽ ቀንዲል ነው!!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት- ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓ እስከ ህንድና ቻይና፣ ከፋርስ እስከ ባቢሎን፣ ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ከሰለሞን ቤተመቅደስ እስከ ዴር ሱልጣን፣ ከሳውዲ ዐረቢያ/መካና መዲና እስከ አክሱምና አልነጃሺ መስጊድ የሰው ልጆች ታሪክና ሥልጣኔ ክቡር የመሠረት ድንጋይ፣ የሦስቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች የአይሁድ፣ የክርስትና እና የእስልምና ማደሪያ፣ ማረፊያ ክቡር ጽላት፣ ከፈጣሪ ዘንድ ለሰው የተቸረ የፍቅር ቃል ኪዳን ማሕተም፣ ሰው የመሆን ክብርና የመንፈስ ልእልና ክቡር መዝገብ፣ ቅዱስ ታቦት ነው!!
‘‘ኢትዮጵያ የምስጢር (የትንግርት) ምድር“/”Ethiopia፡– Land of Wonders and Mystery’’
ሰላም! ሻሎም!