ጨው ኮርማን ጠለፈው!

በእባብ ሰባኪነት ሔዋንን ተገዛው፣
ተበለሱ ፍሬ አዳም ተገመጠው፣
ዋንጫ ተቀብሎ አንካር አሞሌ ጨው፣
ቀልቡን አሽመድምዶ ኮርማውን ጠለፈው፣
አራጅ ለማታለል በምላስ ሲያልሰው፡፡

አንበሳና ነብር ጎሽ የሚፈራውን፣
ሻኛውን ቦጅሮ እምቡእ ሲል ሲጀነን፣
“እንክክ” ብለው ሰጥተው አልሰው አሞሌን፣
ጠልፈው ተምድር ጣሉት እንደ አዳም ሚስት ሔዋን፡፡

ሲያገሳ እንደ አንበሳ እምቡኡ የሚለውን፣
መጥለፊያ መጫኛ ቦጫጭቆ ሐጂውን፣
በጨው ቀልቡን ገዝተው አረዱት ኮርማውን፡፡

እንደ ወንጅ ስኳር ጨውን እያላሱ፣
ሐሳዊ ሰባኪያን ልብ እየሰረቁ፣
ስንቱን ኮርማ በሬ አርድው ጠብሰው በሉ፡፡

“ለበሬ ሳር እንጅ አይታይ ገደሉ፣”
የሚለውን ተረት እየተረተሩ፣
ስንቱን ኮርማ ሰንጋ አሞሌ እያላሱ፣
አራጆች ተምድር ደም እንዳፈሰሱ፣
ትናንት ነበሩ ዛሬም ይኸው አሉ፡፡

ኮርማ ሆይ ልብ ግዛ ተአዳም ሔዋን ተማር፣
ጨው በለስ አልሰው አይጣሉህ ተምድር!

ኮርማ ሆይ ተመከር ይግባህ ያለም ምስጢር፣
ሰማይ ዝቅ ብሎ ምድር ከፍ ብትል፣
አራጅ ንሳ ገብቶ ካራን ስለማይጥል፣
ሻኛህን መድፍ ሰርተህ ቀንድህን ምኒሽር፣
አራጅህን መክት እርድን ተከላከል፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከንቱ ሆይ! - በላይነህ አባተ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share