ኤርትራ በኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ ውክልና ከአምባሳደር ወደ ጉዳይ አስፈጻሚ ዝቅ አደረገች

ኤርትራ በኢትዮጵያ ላላት ኢምባሲ በኢምባሲው ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ዲፕሎማትነት ያገለገሉትን ቢንያም በርሄን ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጋ መሾሟን ይፋ አድርጋለች።

ጉዳይ አስፈጻሚ ቢኒያም የሹመት ደብዳቤያቸውን በዚህ ሳምንት ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያቀረቡ ሲሆን፣ ለአፍሪካ ኅብረት ጭምር የኤርትራ ቋሚ ተወካይ ሆነው እንደሚያገለግሉ ተገልጧል።

ኤርትራ ላለፉት ሦስት ዓመታት አምባሳደር ሠመረ ርዕሶምን በባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ወክላ የቆየች ሲሆን፣ በተያዘው ወር መግቢያ ግድም ግን አምባሳደር ሠመረ የሥራ ዘመናቸውን አጠናቀዋል ተብለው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

ኤርትራ የዲፕሎማቲክ ውክልናዋን ለምን ከአምባሳደር ወደ ጉዳይ አስፈጻሚ ደረጃ ዝቅ እንዳደረገች ወይም የጉዳይ አስፈጻሚው ሹመት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ የኤርትራ መንግሥት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው ነገር የለም።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ አዲሱ የኤርትራ ጉዳይ አስፈጻሚ የሹመት ደብዳቤያቸውን ከማቅረባቸው ትንሽ ቀደም ብላ ለአሥመራ አዲስ አምባሳደር መሾሟን አስታውቃ ነበር። አዲሱ ተሿሚ አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ሲሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በግብርናና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በሃላፊነት ሰርተዋል። ሁለቱ አገሮች ከሦስት ዓመት በፊት እንደገና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ካደሱ ወዲህ ባሉት ጊዜያት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ዘሪሁን መገርሳ በአሥመራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

ኤርትራ የዲፕሎማሲ ውክልናዋን ወደ ጉዳይ አስፈጻሚ ዝቅ ማድረጓን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ርምጃ ትወስድ እንደሆነ የጠየቅናቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ምንጮች በጉዳዩ ላይ አስካሁን ውሳኔ እንዳልተላለፈ ነግረውናል። በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግን አንድ አገር የዲፕሎማሲ ውክልና ደረጃውን ዝቅ ሲያደርግ፣ ሌላኛው አገር ተመሳሳይ ርምጃ መውሰዱ የተለመደ ነው።

ኤርትራ ለኢትዮጵያ በጉዳይ አስፈጻሚነት የሾመቻቸው ቢንያም በርሄ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደሉም። በ1980ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ የያኔው ወጣቱ ቢንያም የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራዊያን ተማሪዎች በሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል የኤርትራ መንግሥት ልኳቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበሩ ናቸው። ሆኖም ግንቦት 1990 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ፣ ቢንያም ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ከሌሎች ነጻ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ከነበሩ ኤርትራዊያን ተማሪዎች ጋር በመንግሥት ውሳኔ ወዱያውኑ ከኢትዮጵያ ተባረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጎንደር አዘዞ! "ዙ 23 ተማርኳል- ደብረታቦር፥ ደብረማርቆስ ፋኖዎች ገብተዋል

በኋላ ግን ቢንያም አገራቸው ኤርትራ አዲስ አበባ በሚገኘው አፍሪካ ኅብረት ባላት የዲፕሎማቲክ ውክልና ውስጥ መድባቸው ከአስር ዓመታት በላይ በፖለቲካ ኦፊሰርነት፣ በምክትል ቋሚ መልዕክተኛነት እና በጉዳይ አስፈጻሚነት ለዓመታት አገልግለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]

2 Comments

  1. ፓለቲካና ፓለቲከኞች በሁለት ነገሮች ይመሰላሉ። አንደኛው በቆሻሻ ክምር ላይ በሚተራመሱ ውሾች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀለሟን እንደ ምትለዋውጠው እስስት ነው። ላስረዳ። ውሾች መራኮታቸው፤ መናከሳቸው፤ አንድ አንድን ማጥቃቱ የሚበላ ፍለጋ ነው። ቆይተው የውሾች ፓክ መስርተው ሌላውን አዲስ መጥ በጋራ ያጠቃሉ። አልፎ ተርፎም እርስ በእርሳቸው እንደ መጀመሪያው ሲናከሱ በዚህም በዚያም እየቆሳሰሉ ይሞታሉ። የእስስቷ ግልጽ ነውና ማብራሪያ አያስፈልገውም። ጣሊያን ዳግመኛ ኢትዮጵያን ወራ ከሊቢያ፤ ከኤርትራ፤ ከሱማሊያና ከሌሎችም ሃገሮች ሰዎችን አሰባስባና አስታጥቃ ሂድና ግደሉ በማለት ስታስማራቸው ከእነዚህ የጣሊያን ቅጥረኞች መካከል አንድ ቢሞት እንዲቀበር እንኳን አይፈቅድም ነበር። ነጩ ዓለም ጥቁሩን አለም አሻንጉሊት ካረገው ዘመን ተቆጥሯል አሁን በቻይናና በቀድሞዎቹ ቅኝ ገዥዎች እጅ የቀጥታና የተዘዋዋሪ ተንኮል እየተገዳደልን እንገኛለን። ስለሆነም የአብይና የኢሳያስ የጫጉላ ቤት ፍቅር መቀዝቀዙ አስገራሚ አይሆንም። ቆይተው ደግሞ በአንድም በሌላም አሳበው ይገዳደላሉ። ጀግና የምንለው ወንድምና እህቱን የገደለውን አሻንጉሊት አይደል? ሌላ ማን ከባህር ማዶ መጣና።
    በመሰረቱ የኤርትራና የኢትዮጵያ የሽርጉድ የሶስት ዓመት እንዘጥ እንዘጥ ለሁለቱ ህዝቦች ያተረፈው አንድም ነገር የለም። ወሬ፤ ፉከራ፤ የጠላቴ ጠላት ጠላቴ ነው በማለት ወያኔ መውጋት ወዘተ ካልሆነ በስተቀር የኤርትራ ህዝብ ዛሬም ቢሆን በእድሜ ልኩ መሪ እየተመራ ይገኛል። የዶ/ር አብይ መንግስትም በኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ሃተፍ ተፍ ይላል። ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም ይሉሃል ይሄ ነው። በዘሩ፤ በጎሳው፤ በክልሉ፤ በጎጡ እንዳሻው ሰንደቅ እየሰቀለ የሚያቅራራውና አንተ ከእኛ ወገን አይደለህም በማለት ሰውን ከቀየው የሚያባርረው፤ ሰውን ከእነ ህይወቱ የሚያቃጥለው የእብድ ጥርቅም ክርስቲያን ነኝ አለ እሰላም ሆነ አውሬነቱ አለቀቀውም። ለዚያ ነው አሁን አሁን ትሻልን ትቼ ትብስን በማለት ሰው የሚያማርረው። ደርግን ወያኔ ሲተካው ያኔ እሰየው ያሉና ከበሮ ይዘው የተቀበሏቸው ዛሬ ላይ ሃገሪቱ ያለችበትን የመፍረክረክ አዝማሚያ ሲያዪ ምን ይሉን ይሆን? በሾኬ ጠለፋ ወያኔን የተካው የብልጽግናው መንግስት ሽብርና ድህነትን ሲያላብስን አይናችን እያየ እግዚኦ እንዲህም አለ እያለን ደንዝዘን ቆመናል። ባጭሩ የሃበሻ ፓለቲካ ዝንተ ዓለም መገዳደል እንጂ ትርፍ ለመከረኛው ህዝብ አስገኝቶ አያውቅም። የገደለውን ሌላ ገዳይ ይገለዋል። ያሰረውን ሌላ አሳሪ ያስረዋል። ሲገላበጡ መኖር ነው።
    በ Swiss town of Montreux አንድ ቤተሰብ ከሰባተኛው ፎቅ ላይ በመዝለል አራቱ የአንድ ቤተሰብ ሰዎች ማረፋቸውን ፓሊስ በነገረን በቀናት የወያኔ ቱልቱላ ነፊዎችና ደጋፊዎች በስዊዝ አደባባይ ለተቃውሞ በመውጣት ሰው ሲቃጠል አሳይተዋል። እየመረጡ ማልቀስ ይሉሃል ይሄ ነው። እልፍ አማሮች በኦሮሞና በትግራይ ወራሪ ሃይልች ሲጨፈጨፉና ሲቃጠሉ ማን ድምጽ አሰማ? እስከ መቼ ድረስ ነው በዘር ተሰላፊዎችና መርጦ አልቃሾች ሆነን እድሜአችን የምንገፋው? በጠራ ቀን በናይሮቢ ታፍኖ ስለተወሰደው ኢትዮጵያዊ ባለሃብት ሳሙኤል ተክለሚካኤል ማን ድምጽ ያሰማ? እኔ በወያኔ ደጋፊዎች ድራማና ተቃሞ ችግር የለብኝም። ችግሬ ሰውን በሰውነቱ አይተን መቼ ነው የምናለቅሰው፤ የምናስተዛዝነው? ይኼ ከትግራይ ነው ያ ከኤርትራ ያ ከአማራ እያልን ቱልቱላ ከመንፋት የምንቆጠበው?
    ነገሬን ከታሪክ ጋር አያይዤ የፓለቲካንና የፓለቲከኞችን ከንቱነት በማሳየት ልቋጭ። ጊዜው ኢትዪጵያ በጣሊያን ተወራ ግራዚያኒ በአዲስ አበባ በነጭ ፈረስ ላይ ሆኖ የሚታይበት ወቅት ነበር። ንጉሱ በስደት እንግሊዝ ሃገር ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ወደ እየሩሳሌም ተጉዘዋል። የእንግሊዝን ብርድና ዝናብ ንግስቲቱ አልቻሉትም። በዚህ መካከል ንጉሱና ረዳቶቻቸው ለፈረንሳይ ለእንግሊዝ መንግስት አቤት ቢሉም የጣሊያኑን ፋሽሽት ሞሶሎኒን ለማስደስት ሲባል መንግስታቱ ዝምታን መረጠው ነበር። ሳይታሰብ ሂትለር ተነሳና አንድም ጥይት ሳያጮህ ፓሪስን ሲቆጣጠር ነገር ሁሉ ተቀየረ። ጣሊያን እጣዋን ከናዚ ጋር አደረገች። ያ የፓለቲካ አሰላለፍ የኢትዮጵያንም የነጻነት ቀን አፋጠነ። ጣሊያኖች ከሃገራችን ወጡ። ጀርመንም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በህዋላ አሜሪካ፤ ራሺያ፤ ፈረንሳይ፤ በእንግሊዞች ተቀራመቷት። በህዋላ ሁለቱ ሃይላን መንግስታ አሜሪካና ራሺያ ፈነጠዙባት። የምስራቁ ካምፕ ፈርሶ ጀርመን አንድ እስከሆነችበት ዘመን ድረስ ነገርየው እንዲያ ቆየ። ለዚህ ለዚያም ነው ፓለቲካ የቆሻሻ ክምር ነው የምለው። ምንም እሳት ቢያጋየውም ነዶና ጢሶ አያበቃም። እየቆየ መጤሱ አይቀርም። አፍሪቃ በተለይም ምስራቅ አፍሪቃ በትኩረት ደግሞ የሃበሻዋ ምድር የቦብ ማርሊን Redemption song በማንጎራጎር ለሁሉም የሰው ልጆች እኩልነት መቆም እስካልተቻለ ድረስ በቋንቋና በሃይማኖት፤ በዘርና በጎሳ ወይም ሌላ ጊዜው ባበቀለው አራሙቻ መፋተጉ ዋጋ የለውም። ኢትዪጵያዊው ከያኔ ምኒሊክ ወሰናቸው ” የደም ጎዳና” በሚለው ላይ እንደሚለን ዛሬም ደም ነገም ደም ነው። ይብቃን!

  2. ይህን ዜና ብሎ ያሠራጨ አዲስ ስታንዳርድ ነው። በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መሓል አንድ ችግር እንደ ተፈጠረ ለማስመሰል ነው። እውነቱ ግን እንዲህ አይደለም። በአምባሳደር ደረጃ ወይም ዝቅ ብሎ ግንኙነት በአገራት መሓል የተለመደ ነው። አዲስ ስታንዳርድ ወይ ይህን አያውቅም ወይም እንደ ለመደው የትህነጎችን ምግባር ለማባዛት በፕሮፓጋንዳ ተሠማርቶ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share