April 2, 2022
25 mins read

የጭንቀላት ሥጋ መብሰሉ ለማይቀረው እንጨት ይፈጃል – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

እንኳን ለሰባተኛው ንጉሥ 4ኛ በዓለ ሲመት እያንገጫገጨም ቢሆን እንደነገሩ አደረሳችሁ፡፡ ዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓመተ ፍዳ ነው፡፡ እውነቱን እየተረዳሁ “ዓመተ ምሕረት” ማለቱ በቃላት መቀለድ ነውና አልልም፡፡ አንዳንዴ በነባር ይትበሃሎች ላይ ማመጽ በጭፍኑ መወገዝ የለበትም፡፡

የዛሬ አራት ዓመት ልክ በዛሬዋ ቀን ሰባተኛው ዘንዶ ከሲዖል ወረደ፤ በሚያማልል የፊት ገጽታና ብዙዎችን በሚያነሆልል ማራኪ የቅጥፈት ንግግር ባዶ የነበረውን ወንበር ያዘ፡፡ የኢትዮጵያ ስም በጥሩ ጎኑ ተነስቶበት በማያውቀው ፓርላማ ውስጥ “ኢትዮጵያየ፣ ኢትዮጵያየ” የሚል ቃና ሲሰማ ብዙ ሰው በሰው አምሳል ወንበሩን ለያዘው ዘንዶ ፍቅሩንና ውዴታውን ቸረው፡፡ ብዙ ሳይቆይ ግን ዘንዶው እውነተኛ ተልእኮውን መደበቅ ስላቃተው የጭቃ ጅራፉን ማንጓት ጀመረ፡፡ የ“መግደል መሸነፍ ነው” ትርክቱንም ጣለና በነአሣምነው ጽጌ ምሥጢራዊ ህልፈት የደም ምጣድ ሙሽቱን በባለሟሎቹ አስጋግሮ በይፋ በማስመረቅ የኦስሽትዊዝ መንገዱን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ይሄውና ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያንን ተራ በተራ እየሰለቀጠ አራት ዓመቱን ደፈነ፡፡ ሀገሪቱም የለየላት ሲዖል ሆነች፡፡

የመጻፍ ፍላጎት የለኝም፡፡ ጨርሻለሁ፡፡ ብዙ ተናገርኩ፡፡ ሁሉም ሆኖ አንዱ ብቻ ይቀራል፡፡ ያም ይሆናል፡፡ … አሁን ጊዜው የአዝመራ መሰብሰቢያ እንጂ የመናገሪያ አይደለም፡፡ ብትናገር ባትናገር ደግሞ ማንም ግድ የለውም፤ በብዙ ነገር ተወጥሯል፡፡ ዘንዶው ቀላል አይደለም፡፡ የፖለቲካውን ቼስ አሳምሮ እየተጫወተው ነው፡፡ በዚህ ሂደት ጅሎች ይስቃሉ፤ ብልኆች ያለቅሳሉ፤ ሆዳሞች በ“ያባትህ አገር ሲወረር አብረህ ውረር” ፈሊጥ ከዘንዶው ጋር ተባብረው አገርን ያጠፋሉ – ግን እነሱም ይጠፋሉ፡፡ ብዙ የቤት ሥራ ስለተሰጠን በያቅጣጫው መፈናፈኛ አጥተን ሩጫ ላይ ነን፡፡ ይሁንና እኛ ጭንቀት ጥበታችን ከምድር አሸዋ የበዛ ይምሰል እንጂ ከኛ ይበልጥ ዘንዶው ተጨንቋል፡፡ ምክንያቱም ሰዓቱ ደርሳለችና፡፡ የዘንዶው ጊዜ እየተገባደደ ነው፤ ዘመኑ አልቋል፤ የንግርቱ ፍጻሜ ቀርቧል፤ ይህንን እርሱ ራሱም ያውቃል – የታዘዘውን ነው እየፈጸመ ያለው፡፡ ይህን በተመለከተም ስንጮህበት ባጅተናል፡፡ ብዙ የተባለለት የትንሣኤ ዘመን ከደጅ አለ፡፡ ግን ግን በነጻ አይገኝም!! ብዙ ነገር አለ ….

ወደድክም ጠላህም ሁለቱ በሬዎች ተያይዘው ይወድቃሉ፤ አንደኛው በሬ – አበያው በሬ – በቅርብ ይነሳል፤ ግራ ሲያጋቡት ከርመው አሁን አሁን እበረቱ ድረስ ዘልቀው – ሊያውም ቀሪውን ዓለም ሣይቀር በሚያስገርም ልዩ ዕብሪትና ንቀት ተወጥረው – ስሊውን ስለያዙት ለኅልውናው ሲል ያስቀመጠውን ያነሳል – ጸሎትም ጦር ነው፤ ሱባኤም ጦር ነው፤ ዕንባና የሕይወት ውጣ ውረድ የሚፈጥረው ሰቆቃም ጦር ነው፤ መፈናቀልና አንገትን በሜንጫ መቀላትም ትልቅ ጦር ነው፤ መሰደብና መንገላታትም “ያንተ አይደለም” በሚል ከሥራና ከመኖሪያ ቤት መነቀልም ጦር ነው፤ ያስቀመጠውና አሁን ተገዶ የሚያነሣው እንግዲህ ጠበንጃ ብቻ እንዳይመስልህ፡፡ የውጊያው አውድማ ተለቅልቋል፡፡ የሚቀረው ፊሽካው ብቻ ነው – የላይኛው ፊሽካ፡፡ በፍቅር ስለፍቅር እንደሞተላቸው በእልህ ይነሳና የጋራ ቤቱን ከቃጠሎና ከውድመት ይታደጋል፡፡ ያኔ ክልፍልፍ በሬዎች የማያውቁትን ጦርነት ገጥመው ከኢትዮጵያ የታሪክ ገጽ እስከወዲያኛው ይጠፋሉ፤ ሕዝቡ ግን የትም አይሄድም፤ አብሮነቱንም ይቀጥላል፡፡ በዚያን ጊዜ በጥጋብ የታወሩ ዘረኞችና በሕዝብ ዕልቂት የሚደሰቱ ጭራቆች ከአውስትራሊያም ሆነ ከሚኖሶታ ወይንም ከቤተ መንግሥትና ከደምቢዶሎ ሆነው የሚከረፋ የዘረኝነት ቅርሻታቸውን ማሰማት ያቆማሉ፡፡ ጣቢያዎቻቸው ሁሉ no signal ወይም bad signal ለማለት ይገደዳሉ፡፡ ራሳቸውንና ልጆቻቸውን በአማርኛ ቋንቋ እያሰለጠኑ ሌሎችን ግን አደንቁረው ከማንም ጋር እንዳይግባቡ የሚያደርጉ የኦነግ ፕሮፓጋንዳ ሰለባዎች ያኔ ሥፍራ የላቸውም፡፡ ብደርስ ደስ ባለኝ!!

በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ልንገርህ፡፡

ፈጣሪ መላእክቱን ሊፈትን ወደደና ከመንበሩ ተነስቶ ተሰወረባቸው፡፡ የፈጣሪ ወንበር ባዶ መሆኑን ያጤነው በፈጣሪው ሲቀና የነበረው ሊቀ መልአኩ ሣጥናኤል ሄዶ ተቀመጠበት፡፡ መላእክት ተሸበሩ፤ ተወናበዱ፡፡ “ማን ነው የፈጠረን?” በማለትም እርስ በርስ መጠያየቅ ጀመሩ፡፡ ያኔ ሊቀ ሣጥናኤል “እኔ ነኝ የፈጠርኳችሁ” አላቸው፡፡ ገሚሶቹ አላመኑትም፡፡ አንዳንዶቹ ግን አመኑትና ሰገዱለት፡፡ ያመኑት በአንድ ወገን ያላመኑት በሌላ ወገን ሆነው ተፋጠጡ፡፡ ከሊቃነ መላእክቱ አንዱ “አምላካችንን እስክናገኝ በያለንበት ጸንተን እንቁም!” የሚል መልእክት አስተላለፈ፡፡ ሣጥናኤል በማይመጥነው ወንበር፣ ባልተፈቀደለት ሥልጣን፣ በማይችለው ቦታ ራሱን በራሱ ሾሞ በመገኘቱ ምኞታዊ የምናብ ልዕልና ሊከተለው ያልቻለ ፈተና ገጠመው፤ (አዎ – ድንቄም መፈክር! “ከፈተና ወደ ልዕልና!” ተባለልን በዚያን ሰሞን፡፡ ሀፍረትን ከሸጡ አይቀር እንዲህ ነው)፡፡ ለማንኛውም ፈጣሪያቸውን በብልጭልጩ የሣጥናኤል ጊዜያዊ ሹመት ያልለወጡ መላእክትና በሣጥናኤል መፈንቅለ መንግሥት ያመኑ መላእክት ታላቅ ጦርነት ውስጥ ገቡ፡፡ ሣጥናኤል ኃይል ተሰጥቶት ነበርና የጻድቃን መላእክትን ክንፍ እየነጨና እየሰባበረ ጉድ ሊሠራቸው ተቃረበ፡፡ አስፈሪ ጦርነት እየተካሄደ ሳለ ፈጣሪ ደረሰ፡፡ ጦርነቱም ቆመ፡፡ በዚያ ጦርነት ውጤት መሠረት ሣጥናኤል ከክብሩ ወርዶ ሲዖልን ወረሰ፡፡ በእምነታቸው የቆሙ ቅዱሣን መላእክትም ይሄውና እስከዛሬዋ መዓልት የልዑል እግዚአብሔርን ዙፋን እንዳጀቡ በይባቤና በፀጋ ከአብና ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር በክብር ይኖራሉ፡፡ ልብ አድርግ – የሣጥናኤል ወገን ይታወቃል፤ የእግዚአብሔር ወገንም ከሌላው ይለያል፡፡ እየገዛን ያለውን ዕወቅ፡፡

የኢትዮጵያም ወቅታዊ ሁኔታ ያንን የመላእክትና የአጋንንት ጦርነት የሚመስል ነው፡፡ አጋንንት ኃይል የላቸውም አንበል፤ በደምብ አላቸው፡፡ ግን ኃይላቸው የሚፀናው የእግዚአብሔር ፀጋና በረከት ያለው ሰው እስኪመጣ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ለንፋስ የተሰጠ ዱቄት ናቸው፡፡ በንነው ይጠፋሉ፡፡

ልብ አድርግ፡፡ እንደአፄ ኃይለ ሥላሤ ተንኮለኛ፣ እንደመንግሥቱ ኃ/ማርያም ገዳይ ጉልበተኛ፣ እንደመለስ ዜናዊ መሠሪ ሸረኛና ሀገር በታኝ ካለ ንገረኝ፡፡ አሁን የት አሉ ብዬ አልጠይቅህም፡፡ ምክንያቱም ዕድሜም በሽታም ሊወስዳቸው ይችላልና፡፡ ነገር ግን የመንግሥታቸውን መጨረሻ እናስታውስ፡፡ የነሱን ብቻ ሣይሆን የቀደምት ጨካኝ መንግሥታትን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ እናስብ፡፡ ሁሉም ተዋርደው አይደለምን ሥልጣናቸውን ያጡት? ታዲያ ማን ነው በሀገርና በሕዝብ ላይ ሸንቶና ቀዝኖ በሰላም የኖረና ልጅም ወጥቶለት ዘር የተካ? ንገረኛ! እርግጥ ነው – ከክፉም ሻል ያለው ክፉ ይመረጣልና የልቡን ቀና ኢትዮጵያዊነት ፈጣሪ አይቶ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን በልጅ ባርኮታል፡፡

የነዚህን አጠፋፍ ደግሞ በቅርብ ታያለህ፡፡ አሁን የሚይዙትንና የሚለቁትን አጥተው እንደኔው እያበዱ ነው – የኔው በብስጭት መሆኑን ታዲያ አትርሳብኝ፡፡ እነዚህ ወንበር ብርቁ ኬኛዎች ሁሉንም ለኔ ከማለታቸው የተነሣ ከምድር አልፈው ሰማዩንም መቆጣጠር እየሞከሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አልበቃቸው ብላ የፈጣሪን ቦታ በመተካት የወቅቱን ዝናብ “እኛ አዘነብንላችሁ” እስከማለት ደርሰው ፈጣሪንና ተፈጥሮን ክፉኛ ተዳፍረዋል፡፡ ይህ ብቻውን የሚያመጣባቸውን መቅሰፍት ጠብቅ፡፡

በዱሮ ዘመን “የዛሬውስ ጥጋበኛ ሽንት ቤትም አያስኬድ” የሚል ምሣሌያዊ አባባል እሰማ ነበር፡፡ ይገርመኛል አሁን ላይ ሆኜ ያን ተረት ሳስታውሰው፡፡ እንዴት እንደተረቱት ሳስብ ደግሞ ግርም ይለኛል፡፡ እውነት ነው፡፡ ችግሩ ግን አንዱ ባጠፋው ሌላው መኮነኑ ነው፡፡ ጥጋበኛ ሰው የተፈጥሮ ጥሪህን እንኳን በአግባቡ ሳትመልስ እንድትነሳ ያጣድፍሃል፡፡ ምን እያልኩ እንደሆነ አንዳንዴ ለራሴም ስለማይገባኝ ይቅር በሉኝ፡፡ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ያሳበደ አገዛዝ ለኔስ መች ሊመለስ! ግን አይዞን – አንድዬ ይገላግለናል፡፡ የትግሉን ወጪ ከግማሽ በላይ የሚሸፍነው ከራሳቸው ጥጋብና ዕብሪት የሚወጣው የበደልና የግፍ ደለል ነው፡፡ እኛ ያለብን ወደፈጣሪ መመለስ ብቻ ነው፡፡ በቶሎ እንመለስ፡፡

“ዳቦ በሙዝ ብሉ፣ እንጀራና ወጥን ለባለጊዜዎች ስጡ” ተብለሃልና ደግሞ ዐይንህ እንጀራ ላይ እንዳያማትር፡፡ ግን ግን ሙዙም እኮ በኪሎ 30 እና 40 ብር ነው፤ በዚያም ላይ አንድ ጉርሻ የማይሆን ዳቦ 6 ብር ነው፡፡ እሱስ እንዴት ይቻላል ነው ጥያቄው፡፡ ዱሮ ቆሎ ቆርጥሜ የገዛኋት ምናምን ትል ነበር፡፡ የዛሬ ቆሎ እኮ ከዱሮ ፊሪዳ ዋጋ በለጠ፡፡ የ20 ብር ቆሎ ለሕጻንም ራት አይሆን፡፡ የት ነው ያለነው ግን? ደግሞስ ለሀሰት ንግግሩ ለከት ቢያበጅለት ምን ነበረበት? ወይ የሰው ዐመል!

ወገኔ ቻለው እንግዲህ፡፡ በዘርና በነገድ፣ በሃይማኖትና ባገር ልጅነት መለያየትህ ለዚህ አብቅቶሃል፡፡ ሞትህም እንዳያምር አድርጎሃል፡፡ ጥሩ ሞት ሲያምርህ ይቀራል፡፡ ሩቅ የነበረው ቆንጨራ ደግሞ በየደጅህ – በአዲስ አበባም – በአዋሳም – በደሴም – በከሚሴም – …. መጥቶልሃል፤ በየከተማው ያለህ ወንድም እህቴ ግዴለህም ዝም ብለህ ጨፍር፤ ዳንኪራህን እርገጥ፤ የሚያዋጣህ እሱ ነውና አደራህን እንዳታቋርጥ፡፡ የኦሮሙማ ሆድ እስኪጠግብ ኢትዮጵያ ለይቶላት መውደሟ እውነት መሆኑ ያልተገለጠላቸው ወገኖች አሁንም ከዘንዶው ገር መሞዳሞዳቸውን እንደቀጡሉ ናቸው፡፡ ሆዳቸው አይጉደል፣ ቪኤይታቸውንም አይቀሙ እንጂ ለሀገርና ለወገን ምን ደንታ አላቸው? ግን የርሱን ጽዋ አብረው ይጎነጫሉ፡፡ ጊዜው ቀርቧልና ይህን ሁሉም ይወቀው፡፡ መስመሩንም ይለይ፡፡

የጠፉ ነገሮችን መመለስ ስለሚቸግር በዐውሬው መንደር ውስጥ መልካም አስተሳሰብ ያላችሁ አንዳንድ ወገኖች ብትኖሩ እባካችሁን የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ፡፡ ለምሣሌ ያሬድ ሙዚቃ ቤት በኦሮምያ ፍርድ ቤት ሊጠቀለል ነው ይባላል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ ታሪካዊ ሥፍራዎች ሆን ተብሎ እንዲወድሙ እየተደረገ ነው፡፡ ሌላ ሌላው ወደነበረበት ሊመለስ ይችላል፤ የወደመ ታሪክን መመለስ ግን ይከብዳል፡፡ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ የቱዋሬግ አማጽያን የቲምቡክቱውን እስላማዊ ቅርስ በዶማና በግሬደር አወደሙት፤ አሁን አነሱም ቅርሱም የሉም፡፡ ብቻ እነዚህ የሀገራችን ቱዋሬጎችና አልቃኢዳዎች ብዙ ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት ጥንቃቄ ይወሰድ፡፡ የነጋበት ጅብ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህ “ሰዎች” ብዙ ጠባሳ እንዳያሳርፉ በየአካባቢው ሕዝቡ በተቻለው ይረባረብ፡፡ ትልቁን ጦርነት የሚያካሂደው ግን ሌላ ኃይል አለና ለዚያ አትጨነቁ፡፡ ጊዜ ያነሳል፤ ጊዜ ይጥላል፡፡ የወደቀ እሚመስል ሲነሳ የተነሣ እሚመስል ይወድቃል፡፡ አልወድቅ ብሎ ያስቸገረን ትዕቢትና ዕብሪት ነው፡፡ እናም እንጸልይ፡፡ ጸሎት ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ያመጣል፡፡

እግዚአብሔር ወይንም ሁሉን በሚያስማማ ዘመነኛ አጣራር “ፈጣሪ” አንድን ሕዝብ ሊቀጣው ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥ እንደሚያነግሥ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ እግዚአብሔር አይቀጣም የሚሉ አሉ በርግጥ፡፡ ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች የተወሰኑት “የገዛ ኃጢኣታችን ነው የሚቀጣን” ይላሉ፡፡ በዚህም አለ በዚያ የቅጣቱ መንስኤም ሆነ ቀጪው ምንም ይሁን ማን የዓለም ሕዝብ በተለይ በአሁኑ ወቅት ክፉኛ እየተቀጣ ነው፡፡ የእኛ የኢትዮጵያውያን ቅጣት ግን እጅጉን የተለዬና ታይቶና ተሰምቶም የማያውቅ ነው፡፡ ሌሎች የሚቀጡት በውጭ ኃይል ሲሆን የኛው ቅጣት ግን የራሳችን ናቸው በምንላቸው ነገር ግን ራሳቸውንና ሀገራቸውን በካዱ ዐረመኔዎች ነው፡፡ የውጪዎቹ ቅጣት ይበልጡን ከኅሊናዊና አእምሯዊ ሁኔታዎች ጋር የተገናኘ ሲሆን የኛ ግን ከአካላዊና ነፍስና ሥጋን ከሚያሟግት የኑሮ ስቃይ ጭምር ነው፡፡ ጠግቦ መዋጋትና ተርቦ መዋጋት ለየቅል ናቸው፡፡ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ጋር ተቆራርጦ ከአውሮፓ ውሻ ያነሰ ኑሮ መኖር በርግጥም መረገም ነው፡፡

ከላይም ይሁን ከታች የታዘዘብን ቅጣት ሲፈተሽ አስገራሚ ነው፡፡ ኦነግ-ሸኔ የተባለ ዐውሬ የኦሮሙማ ፍልስፍና አራማጅ ቤተ መንግሥቱን ከተቆጣጠረ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መቅኖ አጥተው እየባዘኑ ይገኛሉ፡፡ ከወያኔ የቀጠለውና በወያኔ የታወጀው አማራን ከኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን ከመላዋ ዓለም የማጥፋት ክፍለ ዘመናዊ ምዕራብ-ሠራሽ ታላቅ ሤራ ግዘፍ ነስቶ በእግሩ መራመድ የጀመረው ኦነግ-ሸኔ ቤተ መንግሥት ከገባ ከ201ዐ ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ ይህ ሀፍረትና ይሉኝታ የማያውቅ የወያኔ ግርፍ ኦነግ-ሸኔ ማዘዣ ጣቢያውን አራት ኪሎ ከሚገኘው የሀገራችን ቤተ መንግሥት አድርጎ ያሻውን እያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የሕዝብ ዕልቂትንና መፈናቀልን፣ የአማራ ውድመትንና የትግራይንና የአማራን ነገዶች ማጨራረስን እንደአገዛዝ ሥልት የሚጠቀም የኦነገ-ሸኔ ቡድን ቤተ መንግሥት ቁጭ ብሎ እያለ የኢትዮጵያን ትንሣኤ መጠበቅ ከሞኝነቶች ሁሉ የከፋ ነፈዝነት ነው፡፡ በአዲስ አበባና በመላዋ ሀገራችን ውስጥ እየሆነ ያለውን ኦሮሙማዊ የዘረኝነት ዐይን ያወጣ ድርጊት ማየት የማይችል ሰው ቢኖር ኅሊናው የታወረ ነው፡፡ የይስሙላና የተወላገደም ቢሆን ኢትዮጵያ ህገ መንግሥት እያላት ያንን ህገ መንግሥት ተብዬ በጠራራ ፀሐይ የሚሽርና የ86 ጎሣና ነገድ ዋና ከተማ አዲስ አበባን በጉልበት ወደኦሮምያ የሚጠቀልል ወምበዴ “ፌዴራል መንግሥት” ነው ያለን፡፡ አዲስ አበባን የያዙ የኦሮሙማ የሥራ ኃላፊዎች በህገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሀገሪቱን የሥራ ቋንቋ ካለማወቃቸውም በተጨማሪ የልደት ሠርቲፊኬት ሲጠየቁ የሞት የሚሰጡ ማይማን ናቸው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ደም እያለቀሰ ነው፡፡ ሙስናው እግር ከወርች አስሮ አላላውስ ማለቱ ሳያንስ በቋንቋ መግባባት አቅቶን ባቢሎን ሆነናል፡፡ የመኪናው ታርጋ ሁሉ ኦሮ ነው፤ ሁሉም ኦሮ! ቢሮው ሁሉ ኦሮ፣ ባንኩ ኦሮ፣ የሚቀጠረው ሠራተኛ ኦሮ፣ አየር መንገዱ ኦሮ፣ ሚኒስትር መ/ቤቱ ሁሉ ኦሮ፣ ትምህርት ቤቶች ኦሮ፣ ባንዲራውና የባንዲራ መስቀያው ዘፈን ማለቴ መዝሙር አማራ-ጠሉ የኦሮ ክልላዊ መዝሙር፣ … ምን አለፋህ – ፊንፊኔ በርግጥም “ፊን” እያለች ነው፡፡

ቋንቋም ቁም ነገር ሆኖ እነዚህ ዕብሪተኞች ኦሮምኛ ካልተናገራችሁ አዲስ አበባን ልቀቁ እያሉን ነው፡፡ ቋንቋ ማለት ከሸሚዝና ከካናቴራ ያልዘለለ ዋጋ እንዳለው አልተረዱም፡፡ ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ ለአምልኮት የሚበቃ ጣዖት እንዳልሆነ አልገባቸውም፡፡ እነሱም ያሳዝናሉ እኮ፡፡ ወደው መሰለህ? ከተደፈነ ጭንቅላት ይሠውርህ ወንድሜ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop