ጂአይ ጄን ታዋቂዋ የፊልም ተዋናይት ዴሚ ሙር የልዩ ኃይል ወታደር ሆና የምትተውንበት ፊልም ነው፡፡ ሁልጊዜም ለየት ማለት የምትወደዋና ራሷን የወጣላት ምሁርም አድርጋ የመቁጠር ዝንባሌ የሚታይባት የዊል ስሚዝ ሚስት ጃዳ ፒንከት ደሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፀጉሯን እልም አድርጋ በመላጨት የጥንታዊ አፍሪካውያን ሴት ነገሥታትና ጣዖቶችን ከመሰለች ቆየች፡፡ በሚዲያ አፐሌሺያ የተሰኘ ፀጉሯን የሚያረግፍ ህመም ተጠቂ መሆኗም ሲነገርላት ቆይቷል፡፡
ኮሜዲያኑ ክሪስ ራክ ታዲያ በኦስካሩ ሽልማት ሥነሥርዓት ላይ ይቺን በእውነትም የዴሚ ሙርን ጂአይ ጄን የመሰለችውን ጃዳ ፒንከት – ፀጉርሽ ጂአይ ጄንን አስመስሎሻል፣ ይመችሽ፣ ከልብ እወዳችኋለሁ ብሎ ሲናገር፣ ንፅፅሩ ሳቅን የሚያጭር በመሆኑ ሁሉም ሲስቅ ነበር፡፡
በሚስቱ የአዕምሮ ቁጥጥር ሥር እንደዋለ ለብዙ ጊዜ ሲነገርበት የቆየው ጅሉ ዊል ስሚዝ ታዲያ በቀልዱ አብሮ ሲስቅ ከቆየ በኋላ የሚስቱን ፊት መለዋወጥ ሲመለከት – ከተቀመጠበት ተነስቶ በመድረክ ላይ የነበረውን የብዙ ዓመት የሙያ አጋሩን ክሪስ ራክን በዓለም በቀጥታ ለሚሊዮኖች በሚተላለፍ መድረክ ላይ በጥፊ አጩሎታል፡፡
ብዙዎቹ ‹‹ሴት የላከው…›› ብቻ አድርገው ወስደውታል፡፡ ብዙዎች ቀልድ እየተተወነም መስሎን ነበር፡፡ የሆነው ግን በጣም የሚገርምም፣ የሚያሳዝንም፣ ለማመን የሚከብድም ጋጠወጥነት ነው፡፡ ከስነምግባሮች ሁሉ የወጣ አስፀያፊ ተግባርን በአደባባይ የፈጸመውን ሰው ደግሞ፣ በዚያው መድረክ እያጨበጨቡ ኦስካር ሸለሙት፡፡ የባለጌዎች ጉባዔ ይህን ይመስላል፡፡ ዓለማችን ምን ዓይነት የሞራል ልሽቀት ደረጃ ላይ እንዳለከች ከዚህ የበለጠ ማሳያ ያለ አይመስለኝም፡፡
ልክ ዊል ስሚዝ ቀልደኛውን ክሪስ ራክ ተነስቶ በጥፊ ሲመታ የታየኝ፣ ሌላ ሰው፣ ሌላ ነጭ ሰው፣ ቢሆን ዊል ስሚዝ ይህንን ዓይነት ፀያፍ ድርጊት ይፈፅም ነበር? ብዬ ነው ራሴን የጠየቅኩት፡፡ በፍጹም አያደርገውም! የዊል ስሚዝን ጋጠወጥ ድርጊት ስመለከት የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ ናቸው ትዝ ያሉኝ፡፡
የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ‹‹ከሀገራችን ውጡልን!›› ብለው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡ ጥቁሮችን በላያቸው ላይ የመኪና ጎማ አጥልቀው፣ ቤንዚን አርከፍክፈው ከነነፍሳቸው ሲያቃጥሉ ሲመለከቱ፣ ሙጋቤ በጣም ተበሳጭተው የተናገሩት ንግግር ነው የመጣብኝ፡-
‹‹እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን እኮ እንግሊዞች መቶ ዓመት ቀጥቅጠው ሲገዟቸው፣ እንኳን ካገራችን ውጡ ብለው ነጭን ሊያቃጥሉ ይቅርና፣ ቀና ብለው ለማየት ሲንቀጠቀጡ ነው የኖሩት፣ ዛሬ አንድን ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ ጠርተህ፣ እንኳን በህይወት ያለ ነጭ ሰው ይቅርና፣ የሞተን የነጭ ኃውልት ምታ ብትለው ሀሞቱ የለውም፣ ጥቁሮችን ግን ከነነፍሳቸው በቁማቸው ሲያቃጥል ታየዋለህ፣ ይሄ የመጨረሻው ወራዳ የባርነት አመል ነው፣ እንጂ ከሀገር ፍቅር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም!››
ዊል ስሚዝ፣ ክሪስ ራክን በዓለም ፊት በጥፊ በመምታት ራሱን ነው ያዋረደው፡፡ ጋጠወጥነቱን ነው ያስመሰከረው፡፡ ሚዲያ ያገነናቸው ያልበሰሉ ሰብዕናዎችን ጉድ ነው ለዓለም አውጥቶ ያሰጣው፡፡ አሳፋሪ ብልግና ነው፡፡ ግን ብልግናው – ተራ ብልግናም ብቻ አይደለም፡፡ ሙጋቤ እንዳሉት – የባርነት መንፈስ የወለደው ብልግናም ጭምር ነው፡፡
Hats off to Chris Rock!
ጋጠወጥ አስጠላኝ!