March 21, 2022
5 mins read

የአሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑካን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተነጋገሩ

David Satterfield Olusegun obasanjo 768x518 1

David Satterfield Olusegun obasanjo 768x518 1የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና የአሜሪካ አቻቸው ዴቪድ ሳተርፊልድ ትላንት ሰኞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሁለቱ ልዩ ልዑካን በአዲስ አበባ የተገናኙት፤ አምባሳደር ሳተርፊልድ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጣቸውን የአፍሪካ ቀንድ የልዩ ልዑክ ኃላፊነት ባለፈው ታህሳስ ወር የተረከቡት ሳተርፊልድ አዲስ አበባ የገቡት ትላንት ሰኞ መጋቢት 12፤ 2014 ነው። ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የሚቆዩት ልዩ ልዑኩ፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሹማምንት እና ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

አምባሳደር ሳተርፊልድ በትላንት የአዲስ አበባ ቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ከሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እና የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዎዬ ጋር ተነጋግረዋል። ልዩ ልዩ ልዑኩ ከሁለቱ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ጋር፤ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታዎችን ጨምሮ በቀጠናው ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቢያስታውቅም ዝርዝሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል።

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዩ ልዑክን ትላንት ያገኙት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዎዬ፤ ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት በዋሽንግተን ዲሲ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር። በዚህ ውይይት፤ የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳንን ጨምሮ የጸጥታ እና የፖለቲካ ችግሮች ያሉባቸው የአፍሪካ ሀገራት ጉዳዮች ትኩረት አግኝተው ነበር።

በወቅቱ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት እንዲሁም ከህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር ጋር የተገናኙት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ኢትዮጵያ የተመለከቱ ጉዳዮች አንስተዋል። ሳምንታ ፓወር በዚሁ ውይይታቸው “በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ ነው” ያሉት “ቀውስ” የፈጠረባቸው ስጋት ላይ መነጋገራቸውን አስታውቀው ነበር።

ሳማንታ ፓወር፤ የኢትዮጵያ “መንግስት የእርዳታ ስርጭት ማስተጓጎሉን ቀጥሏል” የሚል ክስም በወቅቱ አቅርበዋል። የአፍሪካ ህብረት ሹማምንት፤ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቪክቶሪያ ኑላንድ ጋር በተገናኙበት ወቅትም ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንዱ እንደነበር ተገልጿል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ግጭት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለበረታበት የአፍሪካ ቀንድ አዲስ ልዩ ልዑክ የመደበችው ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ነው። በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሳተርፊልድ፤ የልዩ ልዑክነት ኃላፊነቱን ከጄፍሪ ፌልትማን ተረክበው ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

277005920 662094348336531 2721623907625901316 n
Previous Story

የ”ቅዱስ” አባታችን ፣ የኢትዮጵያ ወይስ የትግራይ ፓትርያርክ ለሌላው ሕዝብ ሌላ የሚቾህለት ፓትርያርክ ሳያስፈልግ አልቀረም

Next Story

ፍልፈሉ ቀበሮና ቁማር የተጫወተባቸው በጎች! – በላይነህ አባተ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop