ፍልፈሉ ቀበሮና ቁማር የተጫወተባቸው በጎች! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ጉድጉዳድ ሲምስ የኖረ ቀበሮ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጉድጓድ ሲቆፍር የበለዘውን ፊቱን ቅባት ተቀብቶ፤ አይኑን  ተኳኩሎና የበግ ለምድ ለብሶ ኢትዮጵያ የሚባል አሞሌ ጨው ይዞ ብቅ አለ፡፡  ኢትዮጵያ የሚለውን አሞሌ ጨው ያዩ የኢትዮጵያ በጎችም ጉረኖ ተመታሰርና ተመታረድ የሚያድን የበግ ነፃ አውጪ መጣ ብለው እንኳን በምድር  የሚራመዱ በሰማይ የሚበሩ ፍጥረታትም ጉድ እስቲሉ ፈነደቁ፡፡ ድምጣቸውን አጥፍተው መስካቸውን ሲግጡና የት እንደነበሩ የማይታወቁት ከርሳም በጎች ሳይቀር ተጠራርተው የበግ ለመድ የለበሰውን ቀበሮ ከበው ፌስታ አደረጕ፤ ጸሎትም አደረሱ፡፡ እነዚህ በጎች “ከባችሁ የምትጨፍሩለት ፍጥረት ጉድጓድ ሲምስ የኖረና ቁማር ሊጫወት የመጣ የበግ ለምድ የለበሰ ቀበሮ ነው”  ቢባሉም “ያለ አዋቂ ወሬ ነው፤ ጆሯችን አይሰማም፤ መሰሚያችን ጥጥ ነው” አሉና የሚመክራቸውን ፍጡር ሁሉ አጣጣሉ፤ ገላመጡ፡፡

የቁማሩ መሳካት የልብ ልብ የሰጠው የበግ ለምድ የለበሰው ቀበሮም ፈገግ ብሎ  “ኢት… ብኣ!” ሲል በጉረኖ ውስጥም በውጪም ያሉት የበግ መንጋዎችም ሜዳውን ሞልተው ተከትለው ያለማቋረጥ “ብኣ! ብኣ! ብኣ” እያሉ ዓለም ጉድ እስቲል ጪፈራውን አስነኩ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ሳንባቸውም፣ ልባቸውም፣ እስትፋሳቸውም አሞሌ ጨው የያዘው የበግ ለምድ የለበሰው ቀበሮ እንደሆነ ጮክ ብለው ያለ ሐፍረት በአደባባይ ተናገሩ፡፡ በተለይ ተውጪ ያሉት በጎች በሁለት እጅ የማይነሳ የለመለመ ላታቸውን እንደ ጋሊሊዮ ፔንዱለም እያወዛወዙ የፈረንጁንም የኢትዮጵያውንም በግ ጭፈራ ለወራት አስነኩ፡፡

ፀጉርን እንደ አለላ በቀለም ዘፍዝፎ ማደር ሽበትን ደብቆት እንደማይቀር ሁሉ መቀባባትና መኳኳልም እውነተኛ መልክን ወይም ተፈጥሮን ለዘላለም ደብቆት አይቀርም፡፡ ይህም በመሆኑ የቁማርተኛው ቀበሮ የበግ ለምድ እየሳሳና እንደ አሮጌ አቡጀዲ እየተቀደደ መጣ፤ ኩሉ እንደ ኮሸሽላ ቅጠል ረገፈ፤ ቅባቱም እንደ ግራር ቅርፊት ተቀረፋ፡፡ ይኸንን ጉድ የተመለከቱ ከበው ሲደንሱ ከነበሩት ዘልዛላ በጎች አንዳንዶቹ የቁማርተኛውን ቀበሮ እውነትኛ መልክ ማየት ሲጀምሩ መብረቅ እንደመታው ዛፍ ክው ብለው ደርቀው ቀሩ፡፡ አብዛኞቹ ግን ቁማርተኛው ቀበሮ የሚላቸውን እንጅ ዓይናቸውን ስለማያምኑ “ብ ኣ ኣ ኣ!” እያሉ አሁንም ቀበሮውን እንደ ጅራት ይከተላሉ፡፡ የተቀሩት ደሞ “ቀበሮ የበግ ለምድ ለብሶ ተበግ መሐል ይገኛል ብለን አልመንም ቃዥተንም አናውቅ ነበር” እያሉ የብሶት ድምጣቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   አቶ ዮሐንስን የምትወቅሱ፤  የየሱስና የጳውሎስን ታሪክ አትርሱ 

በግ ከተፈጠረበት ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ “ደጋግሜ ተሳስቻለሁ!” ብሎ ስተቱን አምኖና ከስህተቱ ተምሮ የራሱንም ሆነ የትውልዱን ኑሮ አሻሽሎ ስለማያውቅ እነዚህ በጎችም የእነሱን የማስተዋል ድህነትና ዘልዛላት ለመሸፋፈን ቀበሮ የተፈጠረበትና የተካነበትን ሙያ ስለሰራ ቀበሮን ኮንነው ራሳቸውን ቅዱስ አድርገው ቁጪ አሉ፡፡

ዳሩ ግን እነዚህ ተሳስተናልን የማያውቁ ቀበሮን ኮናኝ በጎች የሚኮንኑት ቀበሮ ተኳኩሎና አዲስ የበግ ለምድ ለብሶ “እኛ በጎች በቅዱሱ መጽሐፍ 69 ጊዜ ተጠቅሰናል” እያለ ነገ ቢመጣ ተውስጥም ተውጪም እንደገና ተጠራርተውና ሜዳውን ሞልተው ምድር ቁና እንስተምትሆን ይደልቃሉ፡፡

በግ የቀበሮን ቅድመ ታሪክ ተረድቶና አንጎሉን በሚቅበዘበዘው ዓይኑና በሚያነፈንፈው የአፍንጫው ቀዳዳ ውስጥ ተመልክቶ ምን የሸር ድሪቶ እንደሚደርትና ምን ዓይነት ቁማር እንደሚቆምር አስቀድሞ ማንበብ እስካልቻለ ድረስ እግሮቹን በጉረኖ ሲታሰርና አንድ በአንድ እየተነጠለ ሲሰዋ መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ የፍልፈል ቀበሮና የዘልዛላ በጎች ታሪክ ጥንት እንዲህ ነበር፤ ዛሬም እንደዚህ ነው፤ ወደፊትም እንደዚሁ የሚቀጥል ነው፡፡

 

መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አራት  ዓ..

 

ንጉሥ ሆይ ፋኖን ማሣደድ ያቁሙ ዕዳው ለርሥዎ ነዉ


—————————–

ሾልኮ የወጣ የጠሚ አብይና የነብይት ብርቱካን የፀሎት የትንቢትና የምክር ድምፅ ቅጂን THM ለቆታል:: ቅጂው ጠሚ አብይ ሴኩላር ሀገርን ለመምራት


ሾልኮ የወጣ የጠሚ አብይና የነብይት ብርቱካን የፀሎት የትንቢትና የምክር ድምፅ ቅጂን THM ለቆታል:: ቅጂው ጠሚ አብይ ሴኩላር ሀገርን ለመምራት
———————————-

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share