ተመዝኖ የቀለለ፣ በትንሹ ያልታመነ፣ ለትልቁ አይሾምም – የዘ-ሐበሻ ሳምንታዊ ርእስ አንቀጽ

ከሁለት መቶ አመታት በፊት የነበሩ፣ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት፣ ቶማስ ጀፈርሰን፣ ከተናገሯቸው በርካታ የሚጠቀሱ ንግግሮች መካከል አንዱ፣ ስለ መንግስት ሃላፊነት የተናገሩት ንግግር ነው። ” የአንድ መንግስት ሃላፊነት የሚመራዉን አገርና ህዝብ ደህንነትና ደስታ ማስጠበቅ ነው። መንግስት የሚኖረው ለዜጎች ጥቅም እንጂ ለገዢዎች ጥቅም አይደለም” ነበር ያሉት።

“ኢትዮጵያ መንግስት አላት” ነው የሚባለው። “የመንግስት ሃላፊዎች ምን ያህል ዋና ሃላፊነቶቻቸውን እየተወጡ ነው ?” ለሚለው ጥያቄ ግን፣ እየሰሩ ያሉትን በማየት መመዘኑ አስቸጋሪ አይደለም የሚሆነው።

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስቱ ቁንጮ የሆኑት፣ ዶር አብይ አህመድ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው። በትረ ስልጣን ከጨበጡ አራት አመት ሆኗቸዋል። በርሳቸው ዘመን፣ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊያና ማህበረሰባዊ ቀውሶች ውስጥ የተዘፈቁበት፣ በሕይወት የመኖር ዋስታ ያጡበትና ደህነንታቸው ትልቅ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ዘመን ነው የሆነው። ምንም እንኳን “ለውጥ” የተባለው መምጣቱ ትልቅ ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ጭሮ የነበረ ቢሆንም፣ በሕወሃት/ኢሕአዴግ ጊዜ ከነበረው ሁኔታዎች የከፋ እየሆኑ ነው። ከዳጡ ወደ ማጡ፣ ከእሳት ወደ ረመጥ እየተሸጋገርን ነው።

በትግራይ፣ በቤኔሻንጉል፣ በሰሜን ወሎ፣ በራያ፣ በጠለምት፣ በስሜን ጎንደር፣ በዋገመራ፣ በአፋር፣ በወለጋ፣ በጉጂ፣ በምእራብና ሰሜን ሸዋ ጦርነቶች ወይም አለመረጋጋቶች አሉ። በሶማሌ ክልልና በደቡብ ባሌና ቦረና ዞኖች ድርቅ ገብቷል። በዜጎች ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው። ከተሞች ወድመዋል። በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የኑሮ ውድነት ከመክበድ አልፎ ወገብ እየሰበረ፣ ብዙዎችን መሬት ላይ እየጣለ ነው። በኢትዮጵያዉያን መካከል የዘር መካረሩ እጅግ በጣም አስፈሪ በሆነ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት፣ በፈተናዎች ስርቆትና፣ በአራሚዎች በርካታ ስህተቶች ምክንያት ችግሮች ተፈጥረዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ተስፋ የሚያጨለም፣ ትውልድ የሚገድል ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህም ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ውዝግቦች እየተነሱ ነው። ንጹሃን ዜጎች በተለይም በአዲስ አበባ በግፍና በጅምላ እየታሰሩ ነው። ባለስልጣናት እንደፈለጉ ህዝብንና አገርን እየሰደቡ፣ እኛን ለምን ተቃወማችሁ፣ “እኛ ተሰደብን” በሚል ከሕግ በላይ ሆነው ዜጎችን እያሰቃዩ ነው። በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያዉያን በስጋትና በፍርሃት ውስጥ እየኖሩ ነው። በአገራቸውም በቅያቸው ሁሉ ነገር ጨለማ እየሆነባቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በትህነግ የጦርነት ክተት አዋጂ  “ወራሪ እና ተስፋፊ ” ማን ነበር ? - ማላጅ

እነዚህን መሰረታዊ የሕዝብ ችግር የመፍታት፣ የመቅረፍና፣ ለሕዝብ ተስፋ የመስጠት ሃላፊነት የመንግስት ነበር። ግን የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት እንኳን ችግሮችን ሊፈታ የችግሮቹ አካል እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው። መንግስት ሕዝብ እያለቀ ጨዋታ ነው የያዘው።

ብዙ በዜጎች ሕይወትና ደህንነት ዙሪያ የተገናኙ አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉ፣ የብልጽግና መንግስት አጀንዳዎቹ አድርጎ እየተንቀሳቀሰባቸው ያሉ ጉዳዮችን ስንመለከት “አራት ኪሎ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ? ወይስ የቡርኪና ፋሶ ? “፣ እንድንል የሚገፋፋ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድ፣ በዚህ ሳምንት፣ አስፈላጊና አንገብጋቢ ናቸው ብለው፣ ሄደው ከጎበኟቸው ቦታዎች መካከል፣ የጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት፣ በአዳማ ያለ የቆርቆሮ ፋብሪካ፣ ለጤና ባለሞያዎች የተደረገ ሽልማትና ድግስ፣ የገበታ ለአገር በሚል በጎርጎራ ያለ ፓርክ ይገኙበታል። በሰቆጣ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በዱብቲ፣ በነቀምቴ፣ በደብረ ብርሃን፣ በቆቦ ፣ በምንጃር … ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ካምፖችን፣ አንዳቸው ጋር ሄደው፣ ለመግብኘት፣ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አልሞከሩም። የፈረንሳይዋ ንግስት ማሪ አንቷኔት ፣ ህዝቡ ተርቦ ዳቦ ብሎ ሲጠይቅ፣ “ኬክ ለምን አትሰጧቸውም” እንዳለችው፣ “ዘይት ተወደደ፣ ኑሮ ተወደደ” ሲባሉ፣ ቅጠል አሳይተው፣ “ዘይት ሳትጨምሩ፣ ጨው ብቻ አድርጋችሁ ለምን አትበሉም ?” የሚል የስላቅና የንቀት ምላሽ ነበር የሰጡት።

የኢትዮጵያ ችግር የተፈጥሮ ሃብት ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር በሕዝብና በሕዝብ መካከል ያለ ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር ለሕዝብና ለአገር የሚያሰብ መሪ አለመኖሩ ነው።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የዶር አብይ አህመድ መንግስት ለገዢዎች ጥቅም የቆመ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ አይደለም። ቅድመ ሁኔታዎቹ የግለሰቦችን ተክለ ሰውነት መገንባት፣ ድግስና ሽብረቃ ማብዛት እንጂ፣ ታች ወርዶ ኢትዮጵያዊያንን ቀና ማድረግ ላይ አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማርኛን የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ የማድረግ ግዴታነትና ተገቢነት (በራህማቱ ኪየታ)

ለሕዝብ ያልቆመ መንግስት እስከቀጠለ ድረስ የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎቶች አይከበሩም። የሕዝብ መከራና ስቃይ እየተባዛና እየጨመረ ይሄዳል ። አገርም ትፈርሳለች።

“በትንሹ ያልታመነ በትልቁ አይሾምም” ይላል ታላቁ መጽሃፍ። ላለፉት አራት አመት አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻግር ያልቻለ ወደፊትም ሊታመን አይችልም። የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት እንዲለወጥ ካልተደረገ ፣ በበፊቱ አሰራር፣ በበፊት ስርዓት፣ በበፊት የጎሳ ሕግ መግስትና የጎሳ አወቃቀር ፣ በበፊቱ ሰዎች አገር እየተመራች፣ የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር አይመጣም።

ለውጥ የተባለው ሙሉ እንደተቀለበሰና የባሰ አገዛዝ እንደመጣ በመረዳት፣ ከአራት አመታት በፊት ሕወሃት/ኢሕአዴግን ለማስወገድ ይደረግ ከነበረ ትግል በተጠናከረ ሁኔታ ኦህዴድ/ብልጽግና ለመታገል ፣ ዜጎች ዘር፣ ኃይማኖት ሳይለያቸው መረባረብ አለባቸው የሚል እምነት አለን።

አዎን ዜጎች ምርጫ አለን። ዝምታን መርጠን ጥቂቶች አገርን ሲያፈርሱና ህዝቡን ለመከራ ሲዳርጉ ማየት፣ ወይንም የድርሻችንን በመወጣት አገራችን፣ ሕዝባችንን፣ ከተሞቻችንን፣ ቅያችን፣ ቤተሰቦቻችን ማዳን፣ ለልጆቻችንም ደግሞ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ ማድረግ። ምርጫው የኛው ነው።

 

4 Comments

  1. “ከሶስት መቶ አመታት በፊት የነበሩ፣ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት፣ ቶማስ ጀፈርሰን፣”

    OOPS! ውይ! የዚህ ርዕሰ አንቀጽ ፀሓፊ አሜሪካ መቼ እንደተፈጠረችና ቶማስ ጀፈርሰን መቼ ፕሬዝዳንትዋ እንደሆኑ በደምብ ጠንቅቆ ያዉቃል።

  2. “ከሶስት መቶ አመታት በፊት የነበሩ፣ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት፣ ቶማስ ጀፈርሰን” ያልከውን አንብቤ ስስቅ ነበር። ችኲል ጅብ ቀንድ ይነክሳል ት ዝ አለኝ። የቤት ሥራህን ሳታገባድድ ለመወንጀል አትቻኮል። ጄፌርሰን ፕሬዚንደት የነበሩት ከ1801 እስከ 1809 ነው፤ እንደ ተወለዱ፣ በ1743 ተናግረው እንኳ ቢሆን 300 ዓመት አይሆንም! በቅድሚያ ግ ን ፕሮፓጋንዳና ርእሠ አንቀጽ ምን እንደ ሆኑ ለይ። ቻዎ

  3. ይድረስ በክፉውም በፈንጠዚያውም ቀናትና ወራት የምታስተነፍሱን የዘሃበሻ ባለቤቶች! ብሶት የወለደውን ምንባባችሁን አየሁትና አንዲት መሰረታዊ ነገር ብቻ እንድንማማርበት ለማቅረብ ፍቀዱልኝ። እንዲህም አላችሁ:

    “የኢትዮጵያ ችግር የተፈጥሮ ሃብት ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር በሕዝብና በሕዝብ መካከል ያለ ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር ለሕዝብና ለአገር የሚያሰብ መሪ አለመኖሩ ነው”

    አሁን ባለንበት ወቅት ማለትም ከዶር አቢይ አስተዳደር ጀምሮ – ፈረንጆቹ እንደሚሉት I respectfully disagree. የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር እራሱ ባለጉዳዩ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ ሁኔታ ተማርኩ ባዩ ነው። ይህ መሪ ከቶ እንዳልሆነ በፖይንት ላስረዳ – ከብዙ በጥቂቱ፣

    ፩) መሪውማ ታይቶ የማይታወቅ ዴሞክራሲ ፅልመቱን ከመላእክት አንድ ላይ ሰብስቦ ፣ተበታትኖ የተወጣጠረውን ሃይማኖት አንድ አድርጎ ኑ በሰፊው ገበታ ለአገር እንምከር ብሎ አላለም? አላደረገውም? ከዚህ በላይ የቀደምት መሪዎች አድርገዋል? ሌላው ቢቀር በትዊተርና ግልፅ ቪዲዮ ሲሞሸለቅ በፈገግታ ሥራ ገበታው አልተገኘም? ባለቤቱ ፣ መልካሟ ሰው ሳትቀር የቀደምት “ንግስቶች” ዱባይና ኒውዮርክ የሚሽቀረቀሩበትን ገንዘብ፣ ያውም ከባለቤቷ መፅሃፍ ችርቻሮ በተገኘ፣ በትርፍ ጊዜዋ በፀሎት፣ በሥራ ጊዜዋ ወያኔ እድሜውን ሲያፈርስ የኖረን ቤተእምነትና ት/ቤቶች በመስራት አልተጠመደችም? ከዚህ በላይ ለህዝብ ማሰብ ከቶ ዬት ይገኛል?
    ፪) ገና ለከርሞ የሚመጣውን መከራ በማሰብ ፣ በቅፈላ ያውም በዶርሲሣ ከሚገኝ ስንዴ ጦም ማደሬን እመርጣለሁ ብሎ የቆመን ፊታውራሪ መሪ ሲሆን እናበረታው ነበር እንደ ቆፍጣኔዎቹ ኤርትራውያን እንጅ በካቦ ይህን ሰውዬ አንጎትተውም ነበር። ዛሬን ያስወቀሰው ይህ ማሳ ላይ መገኘት – እመኑኝ – ወቅቱ ሲደርስ ለዳግማዊ ኖቤል እጩ እንደምናረገው አልጠራጠርም።
    ፫) የጠቀሳችሁት ሁሉ መከራና ችግር አዎ በዚህ ፬ አመታት ሆነዋል። ይሁንና የሆኑበት ምክንያቱ ግን ይህ ቅን ሰውዬ ሥራውን ባለመስራቱ ሳይሆን ከጀርባው ብዙ ሳቦታጅ ስላለና የንደሱ አይነቶች በቁጥር እጅግ አናሳ በመሆናቸው ብቻ ነው። በበኩሌ ጥራ ብባል ከአቢይ፣ ሙስጠፌ ሌላ አንዲት ስለ ሺህ የምትበቃ አዳነች አቤቤና በዝምታው ውስጥ ትሁትና የኢትዮጵያዊነት ጮራ ያፈነጠቀበት ታዬ ደንደአ ናቸው የሚታዩኝ ከሚሰሩት ሥራ በመነሳት። ይህ ሁሉ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሃገር፣ ለ አርባ አመታት በእግሯ እንዳትቆም በውስጥ ምቀኞች የተሸረበባት ምስኪን ሃገር ሲያደማት የኖረው ወያኔ ዞር አለ እንጅ መዋቅሩ መቼ ተነካና ነው ይህን ሰውዬ ነጥለን ለመፈረጅ የምንችለው? ሁላችንስ ብንሆን ስንቶቻችን ለዛች አገር እናስባለን?አለማሰባችንን በሚቀጥለው ፖይንት ልግለፅላችሁና ሃሳቤን ልቋጨው – ረዘመብኝ

    ፬) ስንቶቻችን እያወቅን እንኳ በአቢይ ብቻ በመናደድ HR6600ን የሚያክል መሰሪ ህገ ረቂቅ ድጋፍ ወጣን? ወያኔዎቹስ ከሊቅ እስከ ጳጳስ ኢትዮጵያን በቃል ኪዳን ለማፍረስ ተማምለዋልና በስጋም በመንፈስም አሜሪካ አስፋልት ዘልቀው ተንከባለው ሊያስበይኑብን ላይ ታች ሲሉ ወገን ተብዬው -አቢይን የጎዳ ይመስል- በናት አገሩ ላይ አድማ ሲያስመታ በኔ በኩል ለአገር አለማሰብ ማለት ይሄ ነው። የገዛ ታፋን በባዙቃ የመምታት ያህል ህሊና ማጣት። ለማወቅና መረዳት እንኳ አለመታደል። በስሜት መነዳት ነው አለማሰብ ለኢትዮጵያ!

    ማሳረጊያ!
    ህዝባችን ዖሮሞ ይሁን ትግሬ፣ አማራ ይሁን ሌሎች እያለቁ ነው፣ እየተሰደዱና እየተሰቃዩ ነው። በተለየ የዖሮሚያ ግዛት እየሆነ ያለው አዎ አሳፋሪ ነው። እኔ በበኩሌ ዴሞክራሲ ተብዬው ጊዜአዊነት ይዘነው ክብርት አዳነችን ለአስተዳዳሪነት ብትሾምና የሷን ከንቲባ ፅ/ቤት ሌለኛዋ አንበሲት ብርትኳን ሚ’ደቅሣ ብትረከብ ከፍተኛ ፅዳት ታመጣ ነበር። ይህ ካልሆነ ጊዜያዊ ወታደራዊ ካውንስል የሚመራው፣ ተጠሪነቱ ለ አቢቹ የሆነ በስሩ ሳተናዎቹን የሪፐብሊካን ጋርድን ያዋቀር ስፔሻል ፎርስ አሳይመንት ወስዶ ዖሮሚያን ካላፀዳልን ችግሩ ብሶ ሸገር ደጃፍ እንዳይደርስ ያሰጋኛል። እናም ችግሩ የመሪው ሳይሆን የተመሪው ቸልተኝነት ነው ባብላጫው።ሁሉም በየቤቱ መፍትሄ መውለድ አለበት። በዖሮሚያ ህዝቡም በስሙ ሸኔ እንዲህ ሲፈነጭበት ዝም ማለቱን አልወደድኩም። አንድ ድንቅ የጉጂ አባት ኦቦ ሺመልስን ድንቅ ጠይቀዋል። ያደኩበትና የተወለድኩባት ዖሮሚያ – የዛሬውን አያድርገውና – እንዲህ አይነቶቹ ከእውነት የሚላተሙ አባቶች በሽበሽ ነበሩ። እጅግ አዝናለሁ በሆነውና እየሆነ ባለው ባገራችን። ይቅርታ አበዛሁባችሁ። እንደምታወጡት ቅንጣት አልጠራጠርም። ልዩነትን በጨዋነት መሞገት እራሱ ፀጋ ነውና። ሰላም ሁኑ።

  4. ወንድማችን አባ ዊርቱ በርኦሮሚያ ውስጥ የ governance ችግር እንዳለ መግለፃቸው አንድ ትልቅ እመርታ ነው። ምክንያቱም ያለውን ችግር መረዳት በራሱ ለመፍትሄው 50%አስተዋፅዎ ማድረግ ነው።ጥያቄው መልሱ ምን መሆን አለበት በሚል ነው ላይ ነው።
    ትልቁ ስህተት ” በሬዬን የሰረቀን ፣አፋልገኝ “ብሎ መጠየቅ ነው።ውጤቱም በሬውም አይገኝ፣ ሌላም ካለ ይሰረቃል።ስለዚህ ለኢትዬጵያችን መፍትሄ ለማግኘት ወያኔ በሰራልን ሳጥን ውስጥ ሆነን ሳይሆን፣ ከሳጥኑ ወጥተን አድማሳችንን አስፍተን ማየት ስንችል ብቻ እና ብቻ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share