የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ልዑክ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጉ ታውቋል።

” በህዝበ ውሳኔ አንስማማም፤ ህዝበ ውሳኔ እንደማናካሂድ መላው የአማራ ህዝብ ማወቅ ይገባዋል ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ማወቅ አለበት ” – ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት [በራሱ ፕሮግራም] ከተለያዩ ተቋማት እና ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውቋል።

ይህንንም አስመልክቶ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለኢትዮ 251 ሚዲያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮ/ሌ ደመቀ በማህበራዊ ሚዲያ ” ተጠርተው ነው የሄዱት ፣ ድርድር ሊደረግ ነው ” እየተባለ ሲሰራጭ የነበረው መረጃ ሀሰት መሆኑንም አመልክተዋል።

ኮሚቴው ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ምክንያት ሲያስረዱ አካባቢው ላይ ፦
– የመልሶ ማቋቋም ስራ አልተሰራም
– የበጀት ምደባ አልተደረገም
– የወሰን እና የማንነቱን ጉዳይ እውቅና አልሰጠም ፣ ምንም እንኳን ብልፅግና ፓርቲ / አካባቢው ለማስተዳደር ውክልና ቢሰጠንም / የአማራ ክልል ብፅግና ፓርቲም ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ማህበረሰቡ ተገቢ አገልግሎት እያገኘ አይደለም ስለዚህ ይህንና ተያያዥ ጉዳዮች መንግስት ከምን አደረሰው የሚለውን ለማጣራት እንዲሁም ለመጠየቅ ነው የመጣነው ብለዋል።

ኮሚቴው ፥ በአዲስ አበባ ቆይታው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ብልፅግና ፓርቲ እና ምክትል ጠ/ሚ ጋር መገናኘቱንና መወያየቱን ገልፀዋል።

” ፕሮግራም አስይዘን ካለመምጣታችን አኳያ ፣ በድንገት ብንመጣም መስሪያ ቤቶቹ በጥሩ ሁኔታ አስተናግደውናል፤ በአብዛኛው የተገኘው ሀሳብም ጥሩ ነበር ” ብለዋል።

” መሆን ስላለበት ጉዳይ ተነጋግረናል ” ያሉት ኮ/ሌ ደመቀ በተለይ የበጀቱ ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለገንዘብ ሚስቴር ቢፅፍም ሚኒስቴሩ መልስ ሰጥቶ ወደ ማህበረሰቡ ስላልደረሰ ይህን ጉዳይ ተነጋግረንበታል ብለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሠማዕታት ጥሪ (ኢሕአፓ))

ኮሚቴው በአ/አ ቆይታው ጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ አህመድን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ስራ ስለተደራረበባቸው ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ እና በቀጣይ ቀጥሮ እንገናኛለን ማለታቸውን ኮ/ሌ ደመቀ ተናግረዋል።

” የአካባቢውን ጉዳይ መንግስት ልዩ የሆነ ትኩረት ሰጥቶ ማየት አለበት ” የሚሉት ኮ/ሌ ደመቀ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩ መጨረሻው በህዝበ ውሳኔ እንደሚሆን ሀሳብ መስጠቱን ያነሱ ሲሆን በኮሚቴው በኩል ግን ” በህዝበ ውሳኔው ” አለመስማማቱን ተናግረዋል።

ኮ/ሌ ደመቀ ዘውዱ ፥ ” በህዝበ ውሳኔ እንደማናካሂድ መላው የአማራ ህዝብ ማወቅ ይገባዋል ፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ማወቅ አለበት ፤ ይሄን አካባቢ ወደ ህዝበ ውሳኔ የሚያስኬድ ምክንያታዊ ውሳኔ ስላልሆነ ያንን እንደ ኮሚቴ አንቀበለውም፤ እንደህዝብም አንቀበለውም። ” ብለዋል።

ምክንያቱን ሲያስረዱም ” በህገመንግስትም አልሄድንም ህግ ተጥሶ፣ የህዝብ መብት ተረግጦ ብዙ ባለአባቶች ተገለው ተሰውረው ያህንን አካባቢ ድርጅቱ TPLF ሆን ብሎ መሬት ፈልጎ አካባቢ ፈልጎ የወረረው አካባቢ ስለነበር አሁን የሚፈታው በህግ ነው የሚለው ምክንያታዊ ነው ብለን አናስብም። ብዙ የህግ ባለሞያዎችን አማክረናል ይሄ ጉዳይ በህግ እስካልሄደ በህግ አይደለም የሚመለሰው በፖለቲካ ውሳኔ ነው የመጨረሻ እልባት ማግኘት ያለበት የሚል ሀሳብ እየሰጡ ነው እውነት ነው ምክንያታዊም ነው የነሱ ሃስብ በሚል አጥጋቢ ምክንያት ስላገኘን በዚህ ምክንያት ህዝበ ውሳኔ ፌዴሬሽን ም/ቤት ብሎ የሚያስበው ትክክል አይደለም፤ በዛ ባይሆን የሚል ነው ” ብለዋል።

ኮሎኔል ደመቀ ፥ ” በገዛ በራሳችን መሬት፣ በገዛ በራሳችን ርስት የትግራይ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ወሳኞች ሆነው ሊመጡ ይገባል ብለን አናምንም ፤ እንደኢትዮጵያውያን አብረን በጉርብትና መኖር እንችላለን ፣ ይሄን አካባቢ ግን በህዝበ ውሳኔ ለጨረታ ወጥቶ ምንደራደርበት ጉዳይ እንዳልሆነ ግን መላው ህዝብ ሊያውቀው ይገባል። ይሄን ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልፀናል። ሌሎችም የሚመለከታቸው የመንግስት አመራሮችም ይሄን ጉዳይ በትክክል አይተው ሊፈቱት ይገባል እኛ ወደ አካባቢው መጥተናል ተመልሷል እውቅና ግን ማግኘት አለበት ” ሲሉ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሜሪካ አመረረች አብይ እጅ ላይ ካቴና | አዲስ የተመረቀው ልዩ ኃይል ፈረሰ | ፋኖን የተቀላቀለው ኮለኔል ሌላ ያልተሰሙ የሰራዊቱን ሚስጥሮችን አወጣ | በሸዋ ኮማንዶ ተማርኳል በርካታ ሰራዊት ተደምስሷል ፋኖ ማርሸት

አካባቢው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጀት ሊመደብለት ይገባል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ፥ መድሃኒት የለም፣ ታማሚዎች አይታከሙም ፣ወላዶች እየታከሙ አይደሉም ፣ ህፃናቶችም እየሞቱ ነው ፣ ውሃ የለም ፣መብራት የለም ፣ እዛ የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞችም ሞያተኖች መብታቸው እየተጠበቀ አይደለም ፤ ስለዚህ መንግስት በአፋጣኝ የዚህን ህዝብ ችግር አይቶት ሊፈታው እና መፍትሄም ሊሰጠው ህዝቡም ከችግር የሚወጣበትን ነገር ሊፈጥር ይገባል ብለዋል።

 

ምንሊክ ሳልሳዊ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share