February 23, 2022
56 mins read

ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያ የትግራይ አካል ሆኖ አያውቅም

-------ፍትሃዊ መፍትሄ ስንል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው----

አክሎግ ቢራራ (/ ር)

በመጨረሻ እኛ የምናስታውሰው የጠላቶቻችን ቃላቶች ሳይሆን ድምጻቸውን ያጠፉትን የወዳጆቻችን ቸልተኛነት ነው

ዶር ማርቲን ሉዘር ኪንግ

ይህን በጥናትና በምርምር የተደገፈ ትንተና የጻፍኩት የዛሬ ሶስት ዓመት ነው። የጻፍኩበት ዋና ምክንያት ሸንጎ በተባለው ድርጅት ውስጥ በነበርኩበት ወቅት የጦፈ ውይይት ሲደረግ ቸልተኛነት ስመለከት ካየሁ በኋላ አቋሜን ለመግለጽ ነበር። በጉዳዩ ያልተስማሙ ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። አሁንም ሁንኔታው ቢቀየርና ስማቸውን ቢቀይሩም እንኳን እንደማይሳማሙ እገምታለሁ።

ቁም ነገሩ፤ የአማራው ምሁራን፤ የፖለቲካ ልሂቃን፤ አክቲቪስቶችና ሌሎች በእንድነት ቆመው መብታቸውን ካስተጋቡ ማንም ኃይል ስብአዊ መብታቸውን፤ ዜግነታቸውን፤ ክብራቸውን፤ በተለይ ህልውናቸውን ሊገፋቸው አይችልም። ቸልተኞች ቸላ የሚሉበት የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፤ ህወሓት ቢፈራርስም የህወሓት ተተኪዎችና አጃቢዎቻቸው የአማራውን መብት አሁንም በሚገባ የተረዱት አይመስለኝም።

በዚህ ፈታኝ ወቅት በጉዳዩ ግልጽና ሃቀኛ አቋም የያዘው ምሁር መምህር ታየ ቦጋለ ታህሳስ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ስለ ጉዳዩ የጻፈውን ሳነብ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። የጻፍኩትን ተመልሸ እንድመለከተው የቀሰቀሰኝ የሱ ጽሁፍ ነው። እኔ በወቅቱ የጻፍኩትና እሱ ዛሬ የጻፈው ተመሳሳይ መሆኑ አልገረመኝም። ታሪክን ሳያዛቡ ለማየት ችሎታ ያላቸው ተመራማሪዎች ለኢትዮጵያ የሚያበረክቱት ያልተዛባ አቀራረብ በዘላቂነት ሲታይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት መንፈስ ይጠቅማል። በህወሓት ዘረኛ ቡድን ለሞቱት፤ ለቆሰሉት፤ ለታሰሩት፤ ለተዋረዱት፤ ከቀያቸው ለተፈናቀሉት፤ ሰብአዊ መብታቸውን ለተገፈፉት ወገኖቻችን ፍትሃዊ መፍትሄ እንዲጎናጸፉ ያግዛል የሚል እምነት አለኝ።

ትህነግ (TPLF) መሳሪያ ተጠቅሞ፤ ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተባብሮ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እልቂት አካሂዷል። ይህ አካባቢው “ነፃ” ከወጣ በኋላ በጉግል ካርታ የሚታዩ ወደ ዘጠኝ የሚገመቱ የጅምላ መቃብሮች (ከፅሁፉ መጨረሻ አባሪ የሆነውን ይመልከቱ) ያረጋገጠው፤ የትህነግ መሪዎችና ግድያ የፈጸሙ አባላት ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ነው።

መምህር ታየ የጻፋቸውን አስኳል ጉዳዮች ባጭሩ ልጥቀስና ታዳሚዎች፤ የውሳኔ ባለሥልጣናት፤ በተለይ የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና የራያ ወገኖቸ የመምህር ታየንና የእኔን ዘገባዎችና ምክሮት እንዲጠቀሙባቸው አሳስባለሁ። እኔ የአሁኑ ታሪካዊ ሁኔታ ከመከሰቱ ከሶስት ዓመታት በፊት የጻፍኩትን ሰነድ በሙሉ እንድታነቡት አደራ እላለሁ። መምህር ታየ እንዲህ ብሏል።

“እውነት አንድ፤ ወልቃይት እና ጠለምት በዘመናት ታሪክ ውስጥ የዐማራ ማንነት ናቸው፤

እውነት ሁለት፤ ሕገመንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት ትህነግ በጠመንጃ ወስዷቸዋል፤ የሕገገመንግሥት ጥያቄ አይነሳባቸውም፤

እውነት ሶስት፤ ለ30 ዓመታት በወልቃይት፤ ራያና ጠለምት አማራ ነኝ ማለትና አማርኛ መናገር ያስገድል ነበር። አማራዎች በቋንቋቸው እንዲማሩ፤ እንዲዳኙና እንዲተዳደሩ አይፈቀድም ነበር። በአንጻሩ መራራ እውነት፤ አገው፤ ቅማንት፤ ኦሮሞ፤ አርጎባ አማራ ክልል ውስጥ በራሳቸው ይዳኛሉ።

እውነት አራት፤ ክ500,000 በላይ አማሮች በግፍ ከወልቃይት፤ራያና ጠለምት ተፈናቅለዋል። የእርሻ መሬቶቻቸው ተነጥቀው ለወያኔዎች ቤተሰቦች ተከፋፍለዋል።

እውነት አምስት፤ በአስር ሽህዎች አማራዎች በማንነታቸው ተጨፍጭፈዋል:: በማይካድራ ከሽህ በላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል። በሁመራ፤ የአማራ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል። ገና ሽህዎች እውነቶች ይወጣሉ።

እውነት ስድስት፤ የትግራይን ክልል ይመራ የነበረው የመንደር ጁንታ በቅርቡ በመከላከያ እና በአማራው ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። በሲኖ ትራክ ጨፍልቋቸዋል። ራቁታቸውን ልኳቸዋል። ገና ያልተገለጹና የሚገለጹ ግፎች ፈጽሟል። ይህንን ብልጽግና ነግሮናል። በማስረጃም አይተናል።”

 

ተያያዥ እውነቶችንም አቅርቧል። ለምሳሌ፤ የትግራይ ክልል “ልዩ ኃይል፤ ሚሊሽያና ፖሊስ የፌደራል ወታደሮችን፤ ፖሊሶችንና አማራዎችን” መጨፍጨፋቸው፤ “የጠለምት፤ የወልቃይትንና የራያ የአማራ ተወላጆችን” ያለምንም ማቅማማት ልክ በሩዋንዳ “እንተርሃምዌ” ተብሎ የሚታወቀው የጭፍጨፋ ቡድን እንዳደረገው ሁሉ፤ ህወሓት የራሱን የትግራይን ወጣቶች “ሳምራ” በሚል ስም አደራጅቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ፤ ከኢትዮጵያዊያን ባህልና ልምድ ውጭ በሆነ በሚዘገንን ደረጃ ንጹህ አማራዎችን አስጨፍጭፏል። “ትግሬ ባል አማራ ሚስቱን ገድሏል። ትግሬ ሚስት አማራ ባሏን ገድላለች።”

 

ከዚህ ላይ አንድ የአማራውን ሰብእነት ከሰው በታች የሚያደርግ ስም በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምቻለሁ። “አህያ” የሚል። ትህነግና ሳምራ “ይህን አህያ፤ ይህችን አህያ ግደል” እያሉ በሰው ሬሳ ላይ ይፎክሩ ነበር። ይህ ስያሜ በሩዋንዳ ቱትሲዎችን “ኮክሮች (Cockroach)” የሚል ስያሜ ከሰጡት ጋር ተመሳሳይ ነው። “አህያንና ኮክሮችን” መግደል ሃጢያት ሊሆን አይችልም ማለታቸው ነው።

 

እኔ ዘገባየን በጻፍኩበት ወቅት፤ በትግራይ ሕዝብ ስም የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳስጠነቀቁኝ ሁሉ፤ “የትግራይ ብልጽግናም ሆነ ህጋዊ የሚባሉ የትግራይ ፓርቲዎች ያለልዩነት ወልቃይት፤ ጠለምትና ራያን በተመለከተ የያዙት አቋም ከትህነግ (TPLF) አንድና ያው ነው”፤ በሚል በትክክል አስቀምጦታል። የሚቀጥለው ችግር የሚከሰተው በዚህ ምክንያት ነው።

 

እነዚህ ፓርቲዎች አሁንም ያልተዋጠላቸው ሃቅ ህወሓት በመሳሪያ ኃይል፤ ነዋሪዎቹን እየጨፈጨፈ፤ እያሰረ፤ እያቆሰለ፤ ከቀያቸው እያፈናቀለ ህወሓት የነጠቃቸው መሬቶች የትግራይ አካል እንጅ የአማራ አይደሉም የሚል በመረጃና በታሪክ ያልተደገፈ ኢ-ፍትሃዊ አቋም ይዘው ይሟገታሉ። ችግሩ የመሬት ነጠቃው ብቻ አይደለም። የማንነትና የሰብአዊ መብት መገፈፍ ጭምር ነው። ቋንቋህ፤ ባህልህ፤ ልምድህ፤ ማንነትህ ወዘተ “ትግሬ እንጅ አማራ አይደለም” የሚል እብሪተኛነት የተሞላበት ትርክት ነው።

 

የኢትዮጵያን ባለሥልጣናት እንዲያስቡበት የምመክራቸው፤ ጉዳዩ የመሬት ባለቤትነትነት ብቻ አለመሆኑን ነው።

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ያደረገው የተቀደሰና ፍትሃዊ ተግባር (“የማይካድ እውነት 7” እንዳለ ሆኖ፤ መምህር ታየ ቦጋለ “በመራራ 8” ያቀረበው ማስጠንቀቂያ ትክክልና በመሬት ላይ የሚታይ ነው። “በትግራይ ብልፅግና ውስጥ ያለው የትህነግ (TPLF) መዋቅርና የሌጋሲው አስቀጣይ፤ በኦሮምያ ብልፅግና ውስጥ ያለው የኦነግ ሴል ተጃምሎ ጅምላ ጭፍጨፋውን በረቀቀ መንገድ ለማስቀጠል አስቻይ ሁኔታ (enabling environment) የመፍጠር አቋም መያዙን አማራው ጠንቅቆ ተረድቷል።” ትክክል ነው። ህወሓትና የኦነግ ሴል የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ሆነው የአማራውን ህዝብ የሚጨፈጭፉ መሆናቸውን፤ ጭፍጨፋው በባሰ ደረጃ እንዲካሄድ መዶለታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። የምጨምረው አስኳል ጉዳይ ቢኖር፤ እነዚህን አጥፊ ኃይሎች ከጀርባ ሆኖ የሚደግፋቸው ደግሞ የግብፅ መንግሥት መሆኑ ነው።

 

በአማራው ሕዝብ ላይ ለ41 ዓመታት የተካሄደውና የሚካሄደው ግፍ፤ በደል፤ ጭካኔ የተሞላበት ግድያና ማሳደድ አሁንም አላቆመም። የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያና ሌሎች ተዛማጅ አካባቢዎች ቀደምት ነዋሪዎች ግፍና በደል ሲመረመር በዓለም የዜጎች እልቂት ፍርድ ቤት (International Criminal Court/ICC) የሚያስከስሱ መረጃዎች አሉ። ከብዙ መስዋእት በኋላ ፍትሃዊ መፍትሄ ስኬታማ ሆኗል ለማለት የምችለው የቀደምት ነዋሪዎቹ ሁሉን አቀፍ መብት በሕግ ሲከበርና ባለቤትነታቸው ዘላቂ ሲሆን ነው።

 

 

ትህነግ፤ ኦነግ ሸኔና ጅሃዲስቶች በአማራው ሕዝብ ላይ ያካሄዱትና አሁንም በልዩ ልዩ ቦታዎች፤ በተለይ በቤኒ=ሻንጉል ጉሙዝ የሚያካሂዱት የአማራ ሕዝብ እልቂት ባስቸኳይ መቆም አለበት። መለስ ዜናዊ መተከልን ወደ ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ያጠቃለለበት ዋና ምክንያት ለዜጎች ደህንነት አስቦ አይደለም። ከትግራይ የመስፋፋትና አማራውን ከማዳከም እቅዱ ጋር የተያያዘ ስልት ነው። ይህን ሴራ ግብፅም እየተጠቀመችበት ነው። ይህ ክፍተት ሊዘጋ የሚችለው የአማራው ሕዝብ በአንድ ድምፅ ለመናገርና አቋም ለመውሰድ ሲችል ነው። ቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ተተኪ የእልቂት ምሽግ መሆን የለበትም። በትግራይ የተካሄደው ዘመቻ በዚህ ክልልም መካሄድ አለበት።

 

በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ግፉን፤ በደሉን፤ ታሪኩን በቀላሉ አያያቸውም የሚል ግምት አለኝ። እነዚህ አካባቢዎች ከህወሓት መንጋጋ ነጻ ወጥተዋል የሚል እምነት ካለን የማንነት ጥያቄ የህልውና ጥያቄ መሆኑን መቀበል አለብን። ጫና ማድረግ ያስፈልጋል።

 

በዚህም ምክንያት፤ የፌደራሉ መንግሥትና የአማራው ክልል አመራር ህወሓትን ለመደምሰስ ያደረጉት እየተናበቡ የመስራት ልምድ በወደፊት የፀጥታ አመራርም ወሳኝ ሚና አለው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ለአማራው ህይወትና ደህንነት ስኬት የአማራው ፋኖ፤ የአማራው ልዩ ኃይል፤ የአማራው ሚሊሽያና የአማራው ገበሬ ከፌደራሉ ፖሊስና መከላከያ ኃይል ጋር በመናበብ እንዲሰሩ ማድረግ ነው። የእነዚህን ከተራው ሕዝብ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ስብስቦች አቅማቸውን ማጠናከር ግድ ይላል። አማራውን ከእልቂት ለማዳን የሚቻለው መምህር ታየ በቁጥር 9 (1) እንደመከረው “ጸጥታው በፌደራል ፖሊስና ገዳይ ባልሆነው የአማራ ፀጥታ መዋቅር” ቢመራ ነው የሚለው አግባባ አለው። ይህንን ጉዳይ የአማራው ክልልንና የፌደራል ባለሥልጣናት እንዲያስቡበት አደራ እላለሁ። ተጨማሪ ጥቅም አለው። ግብፅና ሌሎች የውጭ ኃይሎች የሚያካሂዱትን የውክልና ጦርነት ኢትዮጵያ ለመቋቋም የምትችለው ተራው አገር ወዳድ ዜጋ አቅም ሲኖረው ነው። አማራው ለኢትዮጵያ ያሳየውና ወደፊትም የሚያሳየው ታማኝነት ስለማያጠራጥር፤ አቅሙን ማጠናከር ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ነው።

 

መምህር ታየ በቁጥር 9 (2፤ 3 እና 4) ያቀረባቸውን ምክሮች እኔም እጋራቸዋለሁ። “በጠለምት፤ ራያ እና ወልቃይት የሚኖሩ በወንጀል ድርሻ የሌላቸው የትግራይ ተወላጆች በቋንቋቸው የሚማሩበት፤ የሚዳኙበት፤ የሚገለገሉበት፤ አመች አሰራር ይፈጠራል። መብታቸው ሳይሸራረፍ መከበር አለበት።” ይህን የማይጋራ አማራ የለም። ግን፤ የትግራይ ተወላጆች ሃላፊነትም አብሮ መቅረብ አለበት። ይኼውም በጁንታው መሪነትና ትጥቅ ጭፍጨፋ ያካሄዱትን ግለሰቦች፤ ለምስሌ የሳምራ አባላትንና ሌሎች ነፍሰ ገዳዮችን የማጋለጥ ግዴታ አለባቸው። ከአሁን በኋላ የትግራይ ሕዝብ የነፈሰ ገዳዮች ምሽግ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም።

 

ተጨማሪ የፖሊሲ እድል አለ። ይኸውም፤ በኦሮሞያና በሌሎች ክልሎች የሚኖሩት በብዙ ሚሊየን የሚገመቱ አማራዎች በያሉበት መብታቸው ተከብሮ ራሳቸውን ሊያስተዳድሩ ይገባል። በአማራው ክልል የሚደረገው የኦሮሞና የሌሎች መብት ስኬት ለምን ለአማራው ይነፈገዋል? አልየ፤ ትህነግ የሚናገረው “አማራው አህያ ነው” የሚለውን የሚዘገንን ብሂል ሌሎችም የዘውግ ፓርቲዎች ይጋሩታል ማለት ነው። የብልፅግና አፓርቲ ይህንን “የከፋፍለህ ግዛው” ፖለቲካ ባህል መቃወምና ማወገዝ አለበት።

 

“ከ1983 እስከ 2013 ከመኖሪያ ቀየአቸው የተፈናቀሉና በሱዳንና በአማራ ክልል የተሰደዱ አማራዎች ባስቸኳይ መመለስ አለባቸው። በትግራይ ኩላኮች የተወሰዱባቸው የእርሻ መሬቶች ሊመለሱላቸው ይገባል።” ከዚህ ላይ የምጨምራቸው የፖሊሲ ምክሮች አሉ። ትህንግ ሲመሰረት ጀምሮ የነጠቀው መሬት ብቻ አይደለም። ትራክተሮችና ሌሎች መሳሪያዎችን ወርሷል። ባካባቢ የሚገኙ የወርቅና ሌሎች መአድኖችን ወርሷል። በወረሳቸው መሬቶች ላይ ሰሊጥ አምርቶ በየዓመቱ $121 ሚሊየን ለውጭ ገበያ ልኳል። የቀንድ ከብቶችን አድልቦ ለውጭ ገበያ ልኳል። በአማራው መቃብር ላይ ከብሯል ማለት ነው። ስለሆነም፤ ህወሓት የወረሰው ኃብት ተሽጦ ለመለሶ ማቋቋም ስራ እንዲውል እመክራለሁ። በተጨማሪ፤ የፌደራሉ መንግሥት በድህነት የወደቀውን አካባቢ መልሶ ህይወት እንዲዘራበት ለማድረግ ልዩ የባጀት ምደባ የማድረግ ግዴታ አለበት።

 

ለማይካድራ ወገኖቻችን መታሰቢያ መሰረተ ልማት እንስራ።

 

ሰቲት ሁመራ፤ ወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ የትግራይ ክፍለ ሃገር ወይንም ክልል አካል የሆነው በኃይልና በወረራ ብቻ ነው። ወረራውን (Annexation) ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ ነዋሪውን ሕዝብ በሚዘገንን ደረጃ መጨፍጨፍና ከንብረቱና ከመሬቱ ማስወገድ አስፈላጊ ነበር። የአማራው ክልል መንግሥት፤ የፌደራሉ መንግሥት ባለሥልጥናት እና በኢትዮጵያዊነታችን የምናምን አገር ወዳዶች ሁሉ ያለብን ግዴታ መጀመሪያ የአማራ ነዋሪዎች እልቂት መካሄዱን መቀበል ነው። ወንጀለኛው ማን እንደሆነ ሊካድ አይችልም። እልቂት ያካሄዱት ኃይሎች፤ የትህነግ እና የሳምሪ መሪዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።

 

በተጨማሪ፤ ነዋሪዎቹ ባለፉት አርባ አንድ ዓመታት የተካሄደባቸው የንብረት ውድመት፤ የንጹህ ዜጎች እልቂት፤ አካለ ስንኩልነት፤ የስነ ልቦና ጫናና በሽታ፤ ከቀዮቻቸው መባረር ወዘተ ካሳ መከፈል አለበት። ከመሬታቸው ተፈናቅለው በመላው ዓለም የተሰደዱት አማራዎች ወደ ቀየዎቻቸው ተመልሰው መቋቋም አለባቸው። ይህን የመልሶ ማቋቋም ወጭ ሊሸፍን መገደድ ያለበት ትህነግ/ህወሓትና “ወራሽ ነኝ” የሚለው ክፍል ነው።

 

ትህነግ/ህወሓት በመፍረስ ላይ መሆኑን እየተቀበልኩ፤ ልዩ ልዩ በትግራይ ሕዝብ ስም የተመሰረቱት የማህበረሰብና የፖለቲካ ድርጅቶች ግን በወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ “ባለቤትነት” ጉዳይ ላይ የወሰዱት አቋም ተመሳሳይ መሆኑ ያሳዝናል። ተቀባይነት የለውም። በዚህ ጥናት እንዳሳየሁት፤ የትግራይ ወሰን ተከዜ ነው። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሰቲት ሁመራና በሌሎች ለም መሬቶች ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች ሲመሰረቱ የማስታውሰው መረጃ ከኤርትራና ከትግራይ ብዙ ሽህ ትግርኛ ተናጋሪዎች ወደ አካባቢው ይመጡ እንደ ነበረ ነው። ብዙዎቹ ባሉበት ኑሯቸውን መስርተዋል።

 

ትህንነግ በመታገል ላይ በነበረበትና የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ከያዘ በኋላ የሚከተሉትን አጠናክሯል፤

 

  1. ስልታዊ በሆነ ደረጃ የአካባቢውን የአማራ ነዋሪ ሕዝብ ጨፍጭፏል፤ አስሯል፤ አቁስሏል፤ እንዲሰደድ አድርጓል፤ ብዙ ማይካድራዎች እንዲፈፀሙ አመቻችቷል;

 

  1. መሬቶቹን ወደ ትግራይ ክልል አጠቃሏል፤

 

  1. የነዋሪውን ሕዝብ የዘውግ ስርጭት ቀይሯል፤

 

  1. የቦታዎችን፤ መንገዶችን፤ ወንዞችን ስሞችና ቋንቋውን ቀይሯል፤

 

  1. በዓለም ደረጃ የአስተሳሰብና የትርክት ለውጥ እንዲካሄድ ዘመቻዎችን በተቀነባበረ ሁኔታ አካሂዷል።

 

በየትኛውም ዓለም ቢሆን አንድ ኃይል መሳሪያ ተጠቅሞ፤ ጥንታዊ ነዋሪዎችን (Indigenous population) ከጨፈጨፈ እና ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ ካደረገ በወንጀለኛነት ይጠየቃል። ትህነግን/ህወሓትን የተኩት ኃይሎችና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ማጤን ያለባቸው በዓለም ሁሉት አይነት የህግና የፍትህ መርሆዎች ሊኖሩ እንደማይችሉ ነው። አንዱ የአማራውን ሕዝብ ብሶትና ጭንቀት ዝቅ የሚያደርግ፤ ሌላው ችግሩን የፈጠረው ኃይል ወገን ተበድሏል የሚል ትርክታዊ ብሂል። ይህ አቋም ፍትሃዊና ሚዛናዊ ሊሆን አይችልም።

በተጨማሪ እኛ ለአካባቢው ሕዝብ ህይወትና ደህንነት እናስባለን የምንል ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሆነን በማይካድራ ለተጨፈጨፉት ወገኖቻችን ልጆችና ቤተሰቦች ተመጣጣኝ፤ በግልፅ የሚታይ፤ ለማህበረሰቡ ተፈላጊ አገልግሎት የሚሰጥ (Flagship) ፕሮጀክት እንድንሰራ አደራ እላለሁ። ዛፎች ከመትከል በተጨማሪ ማለቴ ነው። ከማስታወሻ ኃውልት በተጨማሪ ማለቴ ነው።

 

መምህር ታየ በተራ ቁጥር 10 ያቀረበው ትንተናና ምክር ግልጽ ስላልሆነልኝ ለመገምገም አልችልም። ሆኖም፤ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አነሳለሁ። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የብልፅግና አባላት፤ የትግራይን ጨምሮ፤ “ሬፈረንደም” ይላሉ። ነዋሪዎችን ጨፍጭፎና እንዲፈናቀሉ አድርጎ “ድምጽ ይሰጥበት” የሚል አቋም ለምን?

 

በወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ እና ራያ ህወሓት ቀደምት ነዋሪዎችን (indigenous Amhara) ጨፍጭፏል፤ በልዩ ጉድጓዶች ቀብሯል፤ አቁስሏል፤ አስሯል፤ አባሯል። በምትካቸው የትግራይ ተወላጆችን አስፍሯል። የሕዝቡን ስርጭት ስር ነቀል በሆነ ደረጃ ቀይሮታል። “ሬፈረንደም” ይካሄድ የሚለው ስሌት በአማራው ላይ ከግፍ ላይ ግፍ መጨመር ነው።

 

የአማራው ሕዝብ በአንድነት ይህንን የገደፈ ፖሊሲና ጥሪ መቃወም አለበት። እኔ የምፈራውና መወገድ ያለበት ፖሊሲ አማራውን ወደ ሌላ የባሰ ጦርነት እንዳይሄድ ስልታዊ መንገድ መከተልና ፍትሃዊ መፍትሄ መስጠት ነው። ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያ በታሪካችን የትግራይ ሆኖ አያውቅም። በመሳሪያ ኃይል የተነጠቀ መሬትና በግፍ የተጨፈጨፈ ሕዝብ መሆኑን መገንዘብ አደጋውን ይገታዋል።

 

በመጨረሻ፤ መምህር ታየ እንዲህ በሚል ደምድሟል። “ይህንን መራራ እውነት ክደህ፤ የኦነግ፤ የቢኒ ሻንጉል ጉሙዝ እና የትህነግ ገዳይ አስገዳዮች የሚፈልጉትን ውሸት ብትፅፍላቸው በከፍተኛ በሽህዎች ላይኮች (Likes) ያጅቡሃል። በአንፃሩ ውሸትና ጥላቻ በገነነበት ምድር ይህንን የማይካድ እውነት ስትፅፍ ለእውነት የቆሙ ኢትዮጵያዊያን ብቻ በLike ያጅቡህና Silent majority ለእውነትህ በውስጡ በማይታይ ፈገግታ ይከተልሃል። እውነቱ ይኸው ነው።” ህወሓት፤ ተተኪዎቹና የኦነግ ሴል በመላው ዓለም የዘረጉት የሕዝብ ግንኙነት፤ የመገናኛ ብዙሃን እና የዲፕሎማሲ መረብ የሚያስተጋባው የመጀመሪያውን ነው።

 

ፈረንጆች ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ። “ይዞታ ሶስት አራተኛ መስፈርት ነው።” የአማራው ሕዝብ ታግሎና ብዙ መስዋእት ከፍሎ የተነጠቀውን መሬቱን አስመልሷል። በኃይል የተከለከለውን ሰብአዊ መብቱንና የማንነት ክብሩን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ይህ ስኬት የፖለቲካ ንግድ እንዲካሄድበት አይፈቅድም የሚለውን ስሌት ማጤን ይበጃል።

 

አብዛኛው አገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ መከላከያውን ጨምሮ የሚታገለው ለእውነቱ ስለሆነ መምህር ታየ እንዳለው የሚያሸንፈው ሁለተኛው፤ እውነቱን መቀበል የሚለው ክፍል ነው። የዛሬ ዓመት ህወሓት እንደ እምቧይ ካብ ይፍረከረካል የሚል ግምት የለኝም ነበር። ተፍረክርኮ ዋሻ ለዋሻ እንደ ቀበሮ ይሮጣል። ሆኖም፤ የዘረጋው መዋቅርና ከኢትዮያ ድሃ ሕዝብ የዘረፈውና ከአገር ያሸሸው ግዙፍ የውጭ ምንዛሬ አስጊ ነው የሚል ግምት አለኝ። ለዚህ የሚበጀው መፍትሄ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥትና በውጭ የምንኖር አገር ወዳዶች በመናበብ የተዘረፈውና ከአገር የሸሸው የውጭ ምንዛሬ ክትትል እንዲደረግበትና ለባለቤቱ ለኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ልማት እንዲውል ማድረግ ነው። ዓለም ባንክ ስለጉዳዩ የሚከታተል ክፍል እንዳለው አውቃለሁ። ሰፊ ጥናትና ምርምር አካሂዶ “የተዘረፈ ኃብት የማስመለስ” ዘዴዎችን አባል መንግሥታት እንዲጠቀሙበት ጠቁሟል (Asset Recovery Handbook, the World Bank, 2020).

 

ይህ በአንድ በኩል ሲታይ ስጋት፤ በሌላ በኩል ደግሞ እድል እንዳለ ሆኖ፤ የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠልምትና ራያ ጉዳይ ፍትሃዊ ውሳኔ እንደሚያገኝ አልጠራጠርም። ለዚህ ወሳኙ የአማራው ክልል አመራርና የመላው አማራና ሕዝብ ቆራጥነት ነው።

 

ፍትሃዊ የምልበትን በመረጃ የተደገፈ ትንተና ከዚህ ጋር የተያያዘውን ሰፊ ዘገባ እንድታዩት አሳስባለሁ። በተለይ፤ የአማራ ክልል እና የፌደራል ባለሥልጣናት ጥናቱን ተመልከተው ፍትሃዊ እርምጃ እንደሚወስዱ እገምታለሁ። መምህር ታየ ቦጋለን ለእውነት ስለቆመ ከመቀመጫየ ተነስቸ “ይባርክህ” እላለሁ።

ኢትዮጵያን ለማፈራረስና ሕዝቧን ለእርስ በርስ እልቂት የአመቻቸው የህወሓት ኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርአት የፈጠረውን መሰረታዊ ችግር አሁንም ገዢው ፓርቲ አግባብ ባለው ሁኔታ አላየውም፤ ቢያየውም ችግሩን ንቆ ትቶታል። ይህ የጥፋት ክስተት እንዳለ ሆኖ “ተቃዋሚ ነን” የምንለው ግለሰቦችና ስብስቦች በአበይት ብሄራዊ ችግሮች ላይ ምን አይነት አቋም እንወስዳለን? ጥፋቶችን እያየን ለምን ዝም እንላለን? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥባቸው እጠይቃለሁ። የእኔ መከራከሪያ ነጥብ እንዲህ የሚል ነው። አማራው፤ ኦሮሞው፤ ጉራጌው፤ አፋሩ፤ አኟኩ፤ ሲዳማው፤ ትግራዩና ሌላው በደሙ

 

የተማረከ ስርዓት

ይህ ስርዓት የሚያገለግለው ህወሓትንና ታማኞቹን ብቻ ሆኗል። ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመራመር፤ የኢትዮጵያን ነጻነትና ክብር ስኬታማ ያደረገው አንድ ብሄር አይደለም። ኢትዮጵያ በአንድ ብሄር ተገዝታ አታውቅም። እንዳለመሆኑ መጠን አሁንም አገሪቱን ከጥፋትና ከውርደት የሚንከባከባት አንድ ብሄር አይሆንም። ኢትዮጵያ የሁሉም ብሄረሰቦችና ኃይማኖቶች አገር ናት። በብሄር ተቃርኖ ስልጣን የሚሸምተውና የሚነግደው ህወሓት፤ በብሄረሰቦች እኩለነት አመካኝቶ፤ ሕዝቡን ከፋፍሎ የአንድን አናሳ ብሄር የበላይነት ተቋማዊ አድርጓል። ለምሳሌ፤ የጋምቤላን ለም መሬት ከነዋሪዎቹ ነጥቆ፤ ለፈረንጆችና ለተመረጡ የትግራይ ተወላጆች አስተላልፎ “እድገት” አካሂዳለሁ ይላል። ይህ እድገት ሳይሆን ውርደት መሆኑን ታዛቢዎች ገምግመውታል። ህወሓት ይህ “ውርደት ነው! አፈና ነው! ኢሰብአዊ መርህ ነው! የባስ ድህነት ነው! ብሎ ትችት የሚያቀርበውን ሁሉ እያደነ ያስራል፤ ይገድላል፤ እንዲሰወር ያደርጋል። የእድገት ትርጉም የተለየ ካልሆነ በስተቀር፤ በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው እድገት ለሌቦች፤ ለሙሰኞች፤ በተለይ ለህወሓቶት አመች ሆኖ ቆይቷል። ባለሥልጣናት ችግሩን አይክዱም፤ “ኪራይ ሰብሳቢነት አገር ያጠፋል” ይላሉ። ሌብነት ለማለት ግን አይችሉም፤ አይፈልጉም። “ኪራይ ሰብሳቢነት” እንደ ተራ ነገር ሁሉን አቀፍ የሆነ አባባል ሆኖ ትርጉመ ቢስ ሆኗል። ልክ እንደ “ተሃድሶ” ማለት ነው። እያሰሩና እየሰረቁ “ተሃድሶ” ምን ትርጉም አለው።

 

ተሃድሶ ማንን አደሰ፤ ማንን አደኸየ?

ቁም ነገሩ ግን፤ አንበሳውን የእድገት ውጤት ማርኮ ራሱን ሃብታም ያደረገው ህወሓት ነው። አዲስ አበባን ተረክቦ ለትግራይ ተወላጆት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ፤ የከተማ መሬትና ሌላ ግዙፍ ኃብት ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ ያስተላለፈው ህወሓት ነው። በአዲስ አበባ ቦሌ “መቀሌ” ተብሎ የሚጠራው አካባቢ የዚህ የመሬት ነጠቃ፤ የሰፈራና የኢኮኖሚ የበላይነት ውጤት ነው። መሬቱ ከማንና እንዴት እንድተነጠቀ የሚያሳዩ ብዙ መጻጽፍት፤ ምርሞሮችና መጻህፍት ስላሉ አንባቢ ሊከታተላቸው ይገባል። ችግሩ የመረጃ እጥረት አይደለም። በተለይ፤ አስተማማኝ መረጃ ያለው፤ የዱሮው የኢህአዴግ የመገናኛ ባለሥልጣን የነበረው አቶ ኤርምያስ ለገሰ ያሳተመው የመለስ ልቃቂት የተባለው መጽሃፍ የህወሓትን ሙሰኛነት፤ ሌብነት፤ ባለጌነት፤ ጠባብ ዘረኛነት፤ ግፍ፤ በደል፤ ኢ-ሰብአዊነት፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊነት፤ ጸረ-ሕዝብነት፤ ጸረ-ፍትህነት ወዘተርፈ ጥልቀት፤ ስፋትና አደጋ ቁልጭ አድርጎ አቅርቦታል። ሀወሓት ከሕግ ውጭ የሰበሰበውን ግዙፍ ሃብት አካብቶም፤ እኔ የበላይነቱን ይዠ ካልቆየሁና አሁንም ድርጅታዊ ምዝበራ ለማካሄድ ካልቻልኩ አገሪቱ “ትፈራርሳለች” ይለናል። አዲሱ በብሄር ልዩነቶች ላይ የተመሰረተው የፌደራል ስርዓት የቆየውን የሕዝብ ትሥስር አጥፍቶና ልዩነቶችን አጠናክሮ፤ ለአንድ በብሄርህ ለተዋቀረ ድርጅት የበላይነት መሳሪያ ሆኖታል፤ “ለአዲስ የስልጣን ከበርቴዎች” ዋና መሰረት ሆኖ ቆይቷል። ለማጠናከር የምፈልገው ጉዳይ በፖሊሲና በድርጊት ሲታይ፤ ህወሓት የበላይነቱን እስካልያዘ ድረስ ኢትዮጵያ ብትፈራርስና ሕዝቧ እርስ በርሱ ቢተላለቅ ደንታ እንደሌለው ማወቅ የዜግነት ግዴታችን ነው። ይህን መሰረታዊ አስተያየት ለማጠናከር እፈልጋለሁ። የህወሓት ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ህወሓት የተመሰረተውና ስኬታማ ለማድረግ የወሰነው፤ የትግራይን ሕዝብ ለማገልገል ክልሉን “ከኢትዮጵያ ነጻ ማውጣት ነበር።

 

ምን ተይዞ?

በምን የተፈጥሮ ኃብት? የሚለውን ጥያቄ ብናነሳ መልሱ ግልጽ ይሆናል። ከሌሎች የብሄር ስብስቦች ጋር ተመካክሮ ኢህአዴግ የተባለውን ጥምረት የፈጠረበት ዋና ምክንያት ያላሰበውን ኢትዮጵያን በሙሉ ለመግዛት እንዲያመቸው፤ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ለመሰብሰብ እንዲያስችለው፤ መሬቶችን ነጥቆ ለማጠቃለልና የመጨረሻ ግቡን ስኬታማ ለማድረግና ለማመቻቸት እንዲያስችለው ነው። የትግራይ ክልል ገና ባይገነጠልም፤ ይህ ህወሓት ሲመሰረት የጸነሰው የመሬት ነጠቃና የመስፋፋት እቅድ ተሳክቶለታል። በአገር ደረጃ ሲታይ፤ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሚገመተው ህገ ወጥ “ኪራይ” የተሰበሰበው ከትግራይ ክልል ውጭ ነው። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ፤ ከኦሮሞያ፤ ከደቡብ፤ ከአማራ። ለም መሬቶቹና ወንዞቹ የተነጠቁት የሌላው ሕዝብ የተፈጥሮ ኃብት ነው። የፖለቲካ የበላይነቱ ለህወሓትና ለደጋፊዎቹ የጠቀመው ለዚህ “ኪራይ ሰብሳቤነትና” የግልና የቡድን ኃብት አካባችነት ሆኗል። ግዙፍ ስልጣን! ግዙፍ ኃብት! አስገኝቷል። ሌሎቻችን ይህን የፖለቲካ ስልጣን የበላይነት ከኢኮኖሚና ከተፈጥሮ ኃብት የበላይነት ጋር ማያያዝ አለብን የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም፤ በክልሎች የሚካሄደው ግፍ፤ በደልና ድርጅታዊ ምዝበራ በአገር አቀፍ ከሚካሄደው እምብዛም አይለይም። የሚዘረፍበትን ቦታ የሚወሰነው የሚሰጠው ጥቅም ነው።

ለነጻነት፤ ለፍትህ-ርትእ፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ለሕግ የበላይነትና ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የቆምን ገለሰቦችና ስብስቦች ያለን አማራጭ አንድ ብቻ ነው። የህወሓትን ጨካኝነት፤ ጠባብ ዘረኛነት፤ ጎጠኛነት፤ ከፋፋይነት፤ “ኪራይ ሰብሳቢነት”፤ መሬት ነጣቂነትና ተስፋፊነት ጉዳትና አደጋዎች አይተን፤ ተባብረን፤ ተማምነን፤ ኃይላችን ሰብስበን፤ ይህን ጨካኝ ቡድን ከስልጣን ማውረድ ነው። ይህን ካላደረግን ግን በታሪክ ተጠያቂዎች እኛው ነን። ህወሓት የሚሰራውን ያውቃል:: የተካነበትን ከፋፍለህ ግዛውን ከመቸውም በበለጠ ደረጃ ይቀጥልበታል። ህወሓት ለተከታታይ ትውልድ ደህንነት ደንታ የለውም፤ ከራሱ ጥቅምና ስልጣን በላይ አያስብም። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ጥላቻን፤ ግጭትን አያስብም። ይህ በትግራይ አካባቢ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ተስፋፍቷል፤ ጥልቀት ይዟል። ለምሳሌ፤ የኦጋዴን ኢትዮጵያ ሕዝብ በድርቅ ረሃብ እየተሰቃየ፤ ህወሓት አሜሪካኖችን ለመማጸን ብቻ በወር $250,000 ወጭ ያደርጋል። በውጭ የሚኖሩ ዲሞክራት ኢትዮጵያዊያንን ይከሳል። ይህ ጨካኝ ቡድን ነው ለብሄረሰቦች ፍትህ እቆረቆራለሁ የሚለን!!

 

እንደገና፤ ወደ ኋላ ዘወር ብለን ብናይ፤ ዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ከመመስረቷ በፊት ተራው ሕዝብ ተመካክሮና ተባብሮ የምንኮራባትን ኢትዮጵያን በነጻነት ጠብቋታል። ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ ደግሞ፤ ከሁሉም ብሄሮችና ኃይማኖቶች የተወጣጣው ብሄራዊ የመከላከያ ኃይሏ የአለምን ሕዝብ ባስደነቀ ደረጃ ነጻነቷን አስከብሮላታል። በኮሪያና በኮንጎ የፈጸመው ጀብዱ ለሁላችንም ኩራት ነው። ኢትዮጵያ ካላት ትንሽ ገቢ ተጠቅማ በቅኝ ገዢዎች ይሰቃዩ የነበሩትን የአፍሪካ አገሮች ነጻነት ደግፋለች። የአፍሪካን አንድነት ድርጅት መስርታለች። ዛሬ ለዚህች ሃገር የቆሙላት እንዲገለሉ፤ ከቀያቸው እንዲባረሩ፤ እንዲሰደዱ፤ እንዲምበረከኩ እየተደረገ ነው። ታሪካችን ካልካድን በስተቀር አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለዚህች ታሪክ ላላት አገር በደማቸው ያልከፈሉት መስዋእት የለም።

 

የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ የህብረት ትግል ውጤት ነው። ይህ የመተባበር ብሄራዊ እሴት እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ። ከተባበርንና ከተቻቻልን እምቅ ኃይላችን ከህወሓቶች በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ችግሩ የህወሓት ጥንክርናና ኃይል አይደለም። የኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚዎች መበታተን፤ መከፋፈል፤ መጠላለፍ ነው።

 

የብሄር ፌደራሊዝም ከፈጠራቸው ክስተቶች መካከል ከፋፍለህ ግዛው ዋናው መሳሪያ ነው። ስርአቱ የህወሓት የበላይነት መሳሪያ ሆኗል። ለምሳሌ፤ የፌደራል ምክር ቤት የሚባለው የህወሓት መሳሪያ ነው። የምርጫ ቦርድ፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የደህንነትና የመከላከያ ተቋማት፤ መገናኛ፤ ብሄራዊ ባንክ፤ ጉምሩክና ሊሎች ቁልፍ ተቋሞች የህወሓት መሳሪያዎች ናቸው። ህወሓት የማይቆጣጠረው መስሪያ ቤትና ባለሥልጣን ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም። በሃያ አንደኛው ምእተ አመት፤ እንደዚህ ያለ የአንድ ብሄር የበላይነት የአገዛዝ ሁኔታ፤ የትም አገር ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም።

 

(The Core Problem)

ችግሩን በአጭሩ ላስቀምጠው። በአገር ደረጃ ሲመረመርና ሲገመገም ግልጽ መሆን ያለበት አበይቱ ጉዳይ ህወሓት የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ይዞ እስከቆየ ድረስ የኢትዮጵያ ዘላቂነት አስተማማኝ አይሆንም። የድርቅ ረሃብ አይቀረፍም። ዘላቂንትና ፍትሃዊነት ያለው፤ በራሱ ሊተማመን የሚችል (Reslient) እድገት ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም፤ የውጭ ድጋፍም ቢቀጥልም፤ አብዛኛው የእድገት ውጤት በህወሓቶች ይማረካል። ካፒታሉ ይባክናል። ኃብት ይሸሻል። አሁን ያለው የተዛባ የነፍስ ወከፍ ገቢና ሕዝብን መአከል ያላደረገና የተዛባ የክልሎች ልማት ይባባሳል። በተመሳሳይ፤ አብዛኛው ሕዝብ የማይሳተፍበት የእድገት ውጤት (የተማረከው ኢኮኖሚ) ሲቀጥል፤ የባሰ ግጭትን፤ ድህነትን፤ ረሃብን፤ ስደትን ይፈጥራል። የተዛባ ገቢና የክልሎች እድገት አለመረጋጋትን ያባብሰዋል። ሁኔታው እየተባባሰ ሲሄድ የሕዝብን አመጽ ያጠናክረዋል የሚል ግምት አለኝ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁለት አቅጣጫ እየተቀጣ፤ ህይወቱና ኑሮው እየተናጋ ነው። አንድ፤ የህወሓት የፖለቲካ የበላይነት መዘዞች የፖለቲካ ስልጣኑን የማረከው ህወሓት ከራሱ ጥቅም ባሻገር ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ መሻሻል ምንም ደንታ የለውም የምልበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና የተፈጥሮ ኃብት ምርኮኛ በማድረጉ ነው። ህወሓትና ደጋፊዎቹ የሚያካሂዱት አደገኛ የእድገት መርህ ድህነትን፤ በተለይ ረሃብን መቅረፍ አልቻለም፤ አይችልም። የሚያካሂዱት አይን ያወጣ በጠባብ ብሄርተኝነት የተበከለ ድርጅታዊ ምዝበራን ነው። የወላቃይት ጠገዴን የማንነትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ለማየት የሚቻለው ከዚህ ህወሓቶች ለትግራይ ሕዝብ ቃል ኪዳን ከገቡበት የመሬት ነጠቃና ተስፋፊነት አንጻር ብቻ ነው። ለህወሓቶች ነጠቃውና ክልል አንድን ማስፋፋቱ የእደገት መሰረት ሆኗል። የምግብ ዋስትና፤ የኢንዱስትሪ፤ በተለይ የእርሻ ግብዓቶች የሚያስፈልጋቸው ኢንዱስትሪዎች ስኬታማና ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በተነጠቁት ለም መሬቶች የበላይነትና በሚያመርቱት ውጤት ነው።

 

በተመሳሳይ መሬቱ ለተነጠቀው ነዋሪዎች የመሬት ነጠቃውና መስፋፋቱ የህልውና ጥያቄ ሆኗል። የመሬት ነጠቃና ተስፋፊነት የፖለቲካ ውሳኔ ነው። የፖለቲካ የበላይነት ለኪራይ ሰብሳቢነት አመች ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር “ድርጅታዊ ምዝበራ” በሚለው መጽሃፌ በመረጃ አሳይቻለሁ። አቶ ኤርምያስ ለገሰ በመጽሃፉ፤ “የመለስ ልቃቂት” ያሳየው ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ነው። ህወሓቶች የሚሉት ግዙፍ ኃብት ለመያዝ የቻሉት በራሳቸው ጥረት እንጅ በኪራይ ሰብሳቢነት አይደለም ነው። በጥረት፤ በውድድር፤ በግልጽነት፤ ያለ ምንም ጎሳዊ አድልዎ የተገኘ ኃብት ነው ለሚለው መከራከሪያ መረጃዎቹስ የት አሉ? ተብለው ቢጠይቁ መልስ ይኖራል የሚል ግምትና እምነት የለኝም። መረጃዎች በፋብሪካ የሚመረቱ ይመስላሉ።

 

ለምሳሌ፤ የፖለቲካ ስልጣን የያዙትና ስልጣኑ እንዲቀጥል ያደረጉት “ሕዝብ ስለመረጣቸውና ስለሚያፈቅራቸው” ነው ይሉናል። የእኔ መከራከሪያ ነጥብ ከዚህ የተለየ ነው። በፖለቲካው ሲታይ፤ ህወሓት የምርጫ ውድድሮችን አግቦ፤ ተቃዋሚዎችን አስሮ፤ የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት አፍኖ፤ የአስቸኳይ አዋጅ አውጆ ሕዝብ “መርጦኛል” ማለት ሕዝብን መናቅ ነው እላለሁ። ኢህአዴግ በሕዝብ የሚተማመን ከሆነ የሕዝብን ነጻነት ተቀብሎ፤ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ፈትቶ፤ የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት አክብሮ፤ የምርጫ ቦርድ፤ ፍርድ ቤቶች፤ የፌደራል ፖሊሲው፤ ደህንነት፤ መከላከያና ሌሎች ብሄራዊ ተቋሞች ከህወሓት መንጋጋ ነጻ እንዲሆኑና ብሄራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጎ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሊያደርግ ይችላል። ግን አያደርገውም። በሕዝብ እመነት የለውም። ሕዝብን አፍኖ “ሕዝብ መርጦኛል፤ ሕዝብ ያፈቅረኛል” የሚለው ብሂል ተቀባይነት እንደሌለው ሕዝቡ ወስኗል። ድምጹን አሰምቷል። ልጆቹን መስዋእት አድርጓል። ሕዝብ ገዢውን ፓርቲ ባይቃወም ኖሮ፤ የአስቸኳይ አዋጅ አያስፈልግም ነበር። ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ አያምንም!!!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop