ወሰኔ ይፍሩ [ፕሮፌሰር].
ክፍል አንድ
በመጀመሪያ ይህ ደብዳቤ ወደፊት በሕዝብ እና የሕግ የበላይነት የምትተዳደር ነፃ የሆነች አገር እንዴት እንደምትመሰረት እና በምን ዓይነት ሕገ መንግሥት እንደምንትዳደር ተወያይተን፣ሃሳብና መላ ምቶች ተንሽራሽረው አገራችን የሚያስፈልጓትን ለዉጦች በቅደም ተከተል እንዲደረጉ ለማሳሰብ ለውይይት ይጠቅም ዘንድ ታስቦ የቀረበ የውውይት ሰነድ ነው። ኢትዮጵያ ነጻ አገር ልትባል የምትችለው የዜጎች ሰብዓዊ እና ሕገመንግስታዊ መብት የሚረጋገጥባት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ ፍርድ ቤቶች፣ ምርጫ ቦርድን እና ሌሎችንም የሕዝብ ተቋማት ነፃ የሆኑባት እና በሕዝብ መልካም ፈቃድ የተመረጠ እዉነተኛ የሕዝብ መንግሥት ሲኖራት መሆኑ ግልጽ ነው:: ይህ ደግሞ ተግባራዊ እንዲሆን የሕዝብ ዉይይትና ምክክር ይጠይቃል:: ይህ ሰነድ እጅግ በጣም ሳይሰፋ ደግሞም ሳይጠብ በአገራችን እየተካሄደ ባለው “ለዉጥ” ዙሪያ ለአገራችን ይበጃል በምላቸው አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንድንሰጥ የሚያሳስብ ሲሆን በውይይት የሚሻሻል ነው:: ይህ የመወያያ ሰነድ/ደብዳቤ ብዙ ክፍሎችን የሚይዝ ይሆናል።
ክፍል አንድ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሶስት ትውልደ ዘመናት የተደረጉትን የመንግሥት ለውጦች እና “ታሪካዌ ሂደቱን” ትውልዱ ያደረጋቸዉን ታሪካዊ ስህተቾችን በዝርዝር ይተነትናል። በክፍል ሁለት ላይ ዓለም አቀፍ በሆነው “ዲሞክራሲና” ስለ ሕገ መንግሥት ታሪካዌ ሂደት ሰፋ ያለ ሃሳብ ይቀርባል። በክፍል ሶስት ከላይ በቀረቡት ሃሳቦች ላይ የሚሰጡትን ገንቢ አስተያየቶች ከግንዛቤ በማስገባት በሚያስማሙ አሳቦች ላይ ተመርኩዘን አንድ የስምምነት ውል ወይም ሰነድ ይኖረናል የሚል ተስፋ በማድረግ ነው።
በቅድሚያ ለለዉጥ ራሳችንን ከአዘጋጀን ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ሕገወጥ ስራዎች ዳግመኛ እንዳይደገሙ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እልባት ማግኘት እንዳለባቸው መስማማት ይኖርብናል:: በአለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ከሕግ ውጭ የተሰሩትን ሕገ ወጥ ስራዎች፣ ወንጀሎች እንደዘር ማጥፋት፤ የአንድ አናሳ ጎሳን የበላይነት ጌዜው በአለፈበት ሥርዓትና በአፈታሪክ ወሬ ሕዝብን አስገድዶ እንዲቀበል ማድረግ፤ ሕዝብን ከሚኖርበት ማፈናቀል፤ የአገር ንብረትን ለዉጭ ሃይል መሸጥ መለወጥ፤ የአገርን ገንዘብ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ውጭ ማውጣት፤ የብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ሕገ ወጥ በሆነ ብድር በመዉሰድና “የተበላሸ ብድር” እያሉ ወደ ግል ባንክ ማስገባት፤ የግል ንብረቶችን እየነጠቁ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መውሰድ፤ የተለያዩ የኢኮኖሚ ተቋማትን እና የሕዝብ/የመንግሥት ድርጅቶችን በአድሏዊነት ለአንድ ጎሳ ብቻ መስጠት፤ ቅጥ ያጣ ዝርፊያ ሌብነት የመሳሰሉት በሃገሪቷ እና በአለምአቀፍ ሕግ መሰረት ፍትሐዊ እልባት ማግኘት ያለባቸው መሆናቸው የማይካድ ሃቅ ነው:: በተጨማሪም በስምምነት የተመረጠዉን ጠቅላይ ሚኒስተርና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረበዉን ታሪካዊ የለውጥ ሂደት ከግቡ እንዳይደርስ ጽንፈኞችንና ተላላኪ ቅጥረኞችን በገንዘብ እየገዙ በአገር ውስጥ ሽብርን በመፍጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ በደሙ ያመጣዉን ለውጥ ለማስቆምና ወደ ነበሩበት ሥልጣን ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎች ሕገ ወጥ ስራቸውን ለዓለም ሕዝብ ማሳወቅና ከአሸባሪነታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በውጭ አገሮች የአስቀመጡትን በሕግ እንዲመልሱ ማድረግ፤ በአሜሪካ የሕዝብ ምክር ቤት የተጀመረዉን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዕቀባ ሕጋዊነት አግኝቶ በስራ ላይ እንዲውል ማድረግ፤ አንዳንድ በአሜሪካ የሚኖሩ ግለሰቦች በሰላም ስም ወደ አገር በመግባት የሚያካሂዱትን ሽብርተኝነት በአሜሪካ ሕግ መሰረት እንዲያቆሙ ማድረግ እና እነኝህን የሚመስሉ ሕገ ወጥ ስራዎች ሁሉ ዓለም አቀፍ በሆነው ሕግ መሰረት እንዲዳኙ በማድረግ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ከሽብርተኝነትና ወንጀል የጸዳች እንድትሆን ስምምነት ላይ መድረስ ይጠበቅብናል::
ጥያቄው አንድ መንግሥት ከላይ እስከ ታች ድረስ በአንድ ጎሳ የበላይነት ሙሉ በሙሉ ተይዞ በምን አይነት “ሁኔታ” የአስተዳደሩ ስርዓት ሊለወጥ ይችላል? ነው። ለ27 ዓመታት ያደረገው ትግል መራራና አስከፊ ከመሆኑም በላይ ቁጥሩ ይህ ነው የማይባል ሕዝብ አልቆ፤ አገሩ ለውጭ ሀብታሞች ተሸንሽኖ ተሽጦ፤ ንበረቱ ተዘርፎ፤ የአገሩ ጠቅላላ ገንዘብ ወደ ውጭ አገር ባንክ በግለሰቦች ስም ተዛውሮ፤ የአገሪቷ የመከላኪያ ጦር፤ የመንግሥት እና የግል የሆኑ የንግድ ተቋሞች በአንድ ጎሳ ቁጥጥር ሆኖ እንዴት ለውጥ ሊመጣ ይችላል ነው ጥያቄው? እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ሁለት ዓበይት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ በምን አይነት “ሁኔታ” ነው የትግራይ ነፃ አውጭ ነኝ የሚል የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊቆጣጠር የቻለው? ነው። በብሔር ነፃነት ስም የአገር መከፋፈል “ሁኔታ” ስለተፈጠረ ወያኔ ተለጣፊ ድርጅቶችን በሽግግር መንግሥት ስም ሰይሞ የይስሙላ የሕዝብ ምክር ቤት አባላትን በተለጣፊ ድርጅቶቹ አስመርጦ የመሰረተው በእርሱ የበላይነትና ጠቅላይ ሚንስተርነት ያዋቀረው መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም፣ ሕገመንግስቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከረበት አይደለም:: ይህ ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ 27 ዓመታት ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የተዋጋው ሕገ ወጥ መንግሥት ነው። እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ወያኔ ያዋቀረው መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ሞዴል መሆኑን ነው። ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካን የተለያዩ ጎሳዎችን በመከፋፈልና የክልል መንግሥት በመመስረት እርስ በርሳቸው እንዳይነጋገሩና አንድነት እንዳይፈጥሩ በማድረግ የአፓራታይድ ስርዓት ፈጥሮ ነበር። ይህንንም እዉን ስለአደረገ ለብዙ ዘመናት የአፍሪካን ሕዝብ በመጨቆን ሊገዛ ችሏል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው “ሁኔታ” ይህ ስለሆነ በቀላሉ ሊስተካከል አይችልም። ስለዚህ ይህንን “ሁኔታ” ከግንዛቤ አስገብቶ ሕዝብ በተረጋጋ መንፈስ ተወያይቶ የአገር ለዑላዊነትን የሚያመጣ “ሁኔታን” ፈጥሮ በውይይትና በዲሞክራሴ ያለውን ችግር መፍታት ታሪካዌ ግዴታ ነው። ኢትዮጵያ በክልል ተከፋፍላ በባህል በቋንቋ የማይተዋወቅ ሕዝብ ስለተደረገ ማንነቱን የሚገልጽበትን “ኢትዮጵያ” የምትባለዋን አገር ምን እንደሆነ እንደገና ማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው። “ኢትዮጵያ” የሁሉም መታወቂያ መጠሪያ ስሙ ነው። አድዋ ላይ የተዋደቀው ሕዝብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ክብር ሆኖ ሕያውነቱን አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንክሮ መመልክት ያለበት ሁለተኛው አብይ ጉዳይ ደግሞ ሕዝቡ ከጠቅላይ ሚንስተሩ ጋር ያደረገዉን ስምምነት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው “ሁኔታ” የተፈጠረው በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ነው:: የወያኔ መንግሥት ተገዶ አዲስ ጠቅላይ ሚንስተር መርጦ “በሁለት” ዓመት ግዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስረክባለሁ በማለት የተዋዋለዉን ውል መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለለውጡ ሂደት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር መደራደር አለበት፤ የታሰበው ለውጥ የሚከናወነው በሕዝብ የተመረጠና ለሕዝብ የሚሰራ መንግሥት ስልጣኑን ሲረከብ ነው። ከዚህ አጀንዳ ውጭ ሌላ ጉዳይ መኖር የለበትም። ለውጥ ማለት ወያኔን ስልጣን ላይ ማቆየት ወይም ያለፈዉን መጠገን ወይም ማሻሻል አይደለም።
ለውጥ ማለት
- ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ጽፎና ተወያያቶ ሲያጸድቅ፤
- ነፃ የሆነ ፍርድ ቤትን አዋቅሮ በስራ ላይ ሲውል፤
- ነፃ የሆነ የአስመራጭ ቦርድን አስተካክሎ በአገሪቷ የሚደረጉት ምርጫዎች ያለምንም ችግር ሲከናወኑ ነው።
ይህ ነው ለውጥ ማለት። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፖለቲካ ተኝታኞችና ጋዜጠኞች ከሕዝብ ጋር የመወያየት ግዴታ አለባቸው። አሁን ግን የሚደረገው በእርቅና በሰላም መንግሥት ለሕዝብ ይተላለፋል የተባለውን ውል ሙሉ በሙሉ የጣሰ ይመስላል፤ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ዋና ሃላፊነት ፀጥታን ማስከበርና የሚደረገው ለውጥ በሰላም እንዲሆን ከማድረግ ሌላ ስልጣን አልተሰጣቸውም፤ ሕዝብ በደስታ እልል ብሎ የተቀበላቸው አሸባሪው መንግሥት ተወግዶ ሕዝብ ለመረጠው መንግሥት እንዲያስረክቡ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለ27 ዓመታት ሲያሽብር የነበረው ኃይል እንደገና ወደስልጣን ለመመለስ በማሰብ የኛ መንግስት “የሽግግር መንግሥት” ነው ያሉትን ጠቅላይ ሚንስተር በግድም ሆነ በውድ አስገድዶ ለዉጡ እንዳይሳካ የሚያደርገው ጥረት የሚያመጣው ጥፋት ታላቅ መሆኑን የትግራይም ሕዝብ አስቦ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ታሪካዊ ግዴታው ነው። ይህ ካልሆነ መለስ ዜናዊ ሲመኘው የነበረው “የሩዋንዳ ዓይነት እልቂት” በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማምጣት እንዳይሆን የሁላችንም ሃላፊነት ነው። ወያኔ ካልገዛ አገር ትበጣጠሳለች ማለት ቅዠት ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበጣጠስም፤ ለብዙ ዘመን አብሮ በሰላም በፍቅር የኖረ ጨዋ ሕዝብ ነው።
በመጨረሻ ሃሳብ ሳልሰጥበት ማለፍ የማልችለው ስለለውጡ የሚደረገውን ውይይት ነው፤ የጥናት ተመራማሪዎች ስለሚያደርጉት ጥናት መልሰው መላልሰው ሲናግሩ “ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ” ነው ይላሉ [ወይም ደግሞ በተለምዶ አነጋገር “The Paralysis of Analysis” ይላሉ]። ስለዚህ ወገኖቼን ማሳሰብ የምፈልገው ከጠቅላይ ሚንስተሩ ጋር የተደረገው ስምምነት በሁለት ዓመት ግዜ ውስጥ ኢትዮጵያን ሲያሸብር የነበረው አሸባሪ መንግሥት ለሕዝብ እንዲያስረክብ ነው። ግዜ አነሰኝ ከአለ አስፈላጌው ግዜ ተጨምሮሎት በሰላም እንዲያስረክብ ከማድረግ በስተቀር ሊላ ውይይት “ውሀ መውቀጥ ይሆናል”። ሆኖም ስለ ዲሞክራሴ፤ ስለ ሕገ መንግሥት፤ ስለ ሕግ በላይነት፤ ስለ ነፃ ፍርድ ቤት፤ ስለ ምርጫ ቦርድና ስለ ሕዝብ ባለቤትነት ከሌሎች አገር ታሪካዌ ሂደት አስፈላጊነት መወያየት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። እነዚህን በተመለከተ በቅደም ተከተል በተከታታይ ውይይታችን ላይ ይቀርባሉ። ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ላይ እንደተጠቀሰው፣ በክፍል ሁለት ላይ የሚቀርበው በተከታታይ ያለፉት ሶስት ትውልደ ዘመናት ያደረጉትን ታሪካዊ ፖለቲካ ለውጥ ነው። ይህም በጊዜ ብዛት 90 ዓመታት የፖለቲካ ሂደት ይሆናል። ሂደቱም ሙሉ በሙሉ ስለተጠናቀቀ እንደ ታሪክ መወሰድ ይቻላል። ጊዜውም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1930 እስከ 2020 ያለው የፖሊቲካ ሂደት ይሆናል። እንግዲህ ውድ ወገኖቼ ይህንን የፖለቲካ ሂደት በምን አይነት “ሁኔታ” ላይ ሆነን ነው መወያየት የምንችለው? ለውይይቱስ ምን አይነት ቅድመ “ሁኔታ” ያስፈልጋል? በማለት ነው። በአጭሩ የሚያስፈልገው ቅድመ “ሁኔታ” የመናገር፣ የመጻፍ፣ በአጠቃላይ ፍጹም ነፃ የሆነ የብዙሐን መገናኛ፣ ከምንም ነገር ገለልተኛ የሆኑ ጋዜጠኞች ተደራጅተው [institutionalized] ሲገኙ ነው። ጋዜጠኞች ከፖለቲካ፣ ከጎሳ፣ ከሃይማኖትና ከግል ጥቅም ጋር የተያያዘ ነገር ሁሉ ፍጹም ነፃ መሆን ግዴታቸው ነው። የጋዜጠኛ ዋናው ተግባሩ የአገርን ጉዳይ በተመለከት ሁለ ገብ በሆነ መንገድ ተመልክቶ ለሕዝብ ማሳወቅና ጥቅሙንና ጉዳቱን ለይቶ ማመልከት ነው። ከሁሉ በላይ የሕገ መንግሥቱን መከበር፣ የሕግ በላይነትን አስፈላጊነት፣ የግለ ሰቡን ሰብአዊ መብት መከበሩን፣ የፍትሕ ሥርዓት መጠበቁንና መንግሥት በሕዝብ ስም የሚሰራውን በጥብቅ እየተከታተለ ማሳውቅ ነው።
በተጨማሪ ጋዜጠኛ የውጭ አገርን ግንኙነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለዉን የፖለቲካ ሂደትንና “ሁኔታ” እየተነተነ ለሕዝብ ማሳወቅ ዋነኛ ከሚባሉት ተግባራት አንዱ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የመልካም አስተዳደር “ቅድመ ሁኔታ” እንዴት መፈጠር እንዲሚችሉ መላ ለመምታት ነው። ምክንያቱም ይህ “ሁኔታ” ካልተፈጠረ መልካም አስተዳደር በራሱ ወይም በተአምር ሊፈጠር የሚችል ርዕተ ዓለም አይደለም። ዶክተር አቢይ የኢሀደግን አሽባሪነትና የሰራቸውን ወንጀል ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቀው ይቅርታ ጠይቀው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝብ ለሚመርጠው መንግሥትን እናስረክባለን ብለው ቃል ሲገቡ የነፃነት “ሁኔታ” ተፈጠረ ብለን ነበር። እዚህ ላይ በጥንቃቄ ማስተዋል ያለብን ጠቅላይ ሚንስተሩ ያሉበትን “ሁኔታ” ነው። ለለውጥ ተዘጋጁ ብሎ መልዕክቱን ከማድረስ በላይ ሌላ ስልጣን የላቸውም። የጠቅላይ ሚኒስተሩም ስራ ከዚህ ሊያልፍ አይችልም። ሆኖም አሸጋግራለህ ባሉት መሰረት የአገሩን ሰላምና የሕዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ ግዴታ ነው። ወገኖቼ እዚህ ላይ በቅጡ ማስተዋል ያለብን ተፈጠረ የተባለው “ሁኔታ” በአንድ ሰው ችሮታ የተሰጠ አይደለም፤ ብዙ ሰው በአደረገው ከፍተኛ መስዋዕትነት ነው። እኛ ግን ልክ እንዳለፈው ትውልድ ሳንጠቀምበት ከእጃችን ሊያመለጠን ነው። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለውጥ ሊያመጡልን ነው ብሎ መጠበቅ ቀበሮዋን መሆን ነው፤ ቀበሮዋ በሬ ስታይ ብልቱ ዱብ ብሎ የምትበላው እየመሰላት ትከተላላች ይባላል። ጠቅላይ ሚኒስተሩ የኢሃደግ ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው። ተጠሪነታቸውም ለድርጅቱ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። እኛም በሕዝብ ደም የተገኝዉን “ሁኔታ” ካልተጠቀምንበት ጠቅላይ ሚንስተሩ በደስታ ኢሃደግን በድል አድራጊነት መልሶ ስልጣን እንዲወጣ ለማድረግ መሆኑን ማወቅ ይገባናል። ይህም ሊሆን የሚችለው ከአለፈው ጥፋት ስላልተማርን ነው። ስለዚህ ምናልባት ትምህርት እንዲሆን በማለት ያለፈውን ትውልድ የፖለቲካ ሂደት አጠር ባለ መልኩ ይቀርባል። መልካም ንባብ።
ያለፈው ትውልድ ያደረጋቸው የፖለቲካ ለውጥና ታሪካዊ ሂደት የሚጀምረው በንግርት መልክ ተጽፎ እንደ ምሳሌ ሆኖ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ግብረገብ እንዲማሩበት በግዕዝ ብራና ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ነው። ይህ ጸሐፊ ደብረ ሲና በሚገኝው አብዮ ትምህርት ቤት በሚባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ በግብረገብ ክፍል በቂስ ታደሰ እየተተረጎመ የተማረው ትምህርት ነው። አስተማሪያችን እንደነገሩን ከሆነ ደራሲው መሪጌታ አጥናፍ ሰገድ ዋቄ ይባላሉ። እሳቸውም የዶባው ባላባት የአቦ ዋቄ ልጅ እንደሆኑና አሉ ከሚባሉት የዋዜማ ሊቃውንት አንዱ እንደነበሩ ይነገርላችዋል። በተጨማሪ መሪጌታ አጥናፍ ሰገድ ዋቄ ተጉለት በሚገኝው አጃና ሚካኤል በሚባለው ደብር የዋዜማ መምሕር እንደነበሩ አስተማሪያችን ይነግሩን ነበር። ተጉለትም በዋዜማ ታዋቂ እንደሆነ ይታወቃል። የሳቸዉንም ጽሁፍ በምንማረበት ጊዜ እሳቸዉን በሃላፊ ጊዜያት ስለሚጠራቸው በዚያን ጊዜ በሕይወት እንደሌሉ ያስታውቃል። የግብረ ገብ መምሕራችን ድምጻዊ ስለነበሩ ግዕዙን ወደ አማርኛ እየተረጎሙ ጣዕም በሚሰጥ ዋዜማ ሲያነቡልን ተመስጠን ነበር የምናዳምጥው። ምንም እንኳ ከ60 ዓመት በፊት ቢሆነውም የመሪጌታውን ትንቢት በሚገባ ላስታውሰው እችል ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። ምናልባት ቋንቋው እንደሊቃኑ ላይሆን ይችላል። ታላቁ ሊቅ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንዳለው የአማርኛ ቃንቋ እጅግ የላቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ስለሆነ ታላቅ ሊቅ ሲጽፈው ጣዕሙ የተለየ ይሆናል፤ ለማንበብም ሆነ ለመስማት የሚያስቸግር በከፍተኛ ደረጃ የዳበረ ቋንቋ ነው ይላል። ስለዚህ እዚህ በትውስታ የሚቀርበው ቋንቋ እንደ ዋዜማው መምህር ሊሆን አይችልም። ሆኖም በተቻለ መጠን የመመህሩን አጻጻፍ ችሎታ ለማንጸባረቅ እምክራለሁ። ጽሑፉ በነጠላ ዓረፍተ ነገር፣ በመስተዋድድ፣ በአንቀፅና በንዑስ አንቀጽ ታጅቦ ተጽፏል፤ የመሪጌታው ትንቢት እንዲህ ይላል፤
የደጉ እምዬ ምኒልክና የደጓ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ሲያበቃ ኢትዮጵያ ለሶስት ትውልድ በመከራና በስቃይ ውስጥ ታልፋለች፤ ከቀዳማዊ ምኒልክ እስክ ዳግማዊ ምኒልክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የነገሥታት ዘመን እዚህ ላይ ያበቃል። በመጨረሻው ዙፋን ላይ የሚቀመጠውም ንጉሥ ራሱን ወዳድ አገሩን አሳልፎ ለባዕድ የሚስጥ፤ ሃብትና ንብረት በቃኝ የማይል ንፉግ፤ ስለስሙ ታላቅነት ሌት ተቀን ሳይታክት የሚሰራ በግለሰባዊነት መንፈስ የተሞላ ሰው ይሆናል። ሰውነቱንም እንደሰው ሳይሆን እንደ ጣኦት እንዲመለክ አድርጎ ለግዛት ዘመኑ ዘለዓለም እንዲሆን የሚመኝ ጣኦት አምላኪ ይሆናል። በግዛት ዘመኑም ረሃብ፤ ድርቀት፤ ጎርፍ፤ ማዕበል፤ ሰብሉን ጠራርጎ የሚበላ አንበጣ ይመጣበታል፤ በውጭ ጦርም ተሽነፎ ይሰደዳል። እንደገናም ተመልሶ አገሩን ይገዛል፤ የግዛት ዘመኑም 44 ዓመት ይሆናል፤ በዘመኑም አገሪቷ የምትታወቀው በረሃብና በችግር ይሆናል። ከሱ በኋላ የዘውድ አገዛዝ ስርዓት በጉግ ማንጉግ ስርዓት ይተካል፤ የጉግ ማንጉግ ትውልድ ሁሉን አውቃለህ የሚል ይሆናል፤ ሁሉም አዋቂ፤ ሁሉም መሪ ሆኖ እኔ በልጥ እኔ በልጥ በማለት ይገዳደላል፤ እሱ ያለው ከአልሆነ አባቱን፤ እናቱን፤ ወንድሙን፤ እህቱን የሚገድል ትውልድ ነውና፤ መግደልም ጀግንነት ስለሚመስለው ይመጻደቃል፤ መጎደኛም ስለሆነ ግብረ ገብነት የለውም፤ ከጥፋቱም መማር አይፈልግም፤ ስህተትን ስለማያቅ ምንጊዜም ቢሆን የሚሳሳት አይመስለውም፤ ፍጹም አዋቂ ነኝ ብሎ ያምናል፤ አዋቂነቱንም በግድ እንዲታወቅለት ያደርጋል፤ ራሱን ማወደስ ትልቀኛው ተግባሩ ይሆናል። ግን በራሱ ኃይል እንደ ንፋስ ብን ብሎ ይጠፋል። ከሱም ቀጥሎ የወንበዴ መንግሥት ይመጣል። ውንብድናውም በአገሩ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ይሆናል፤ ሴትን ልጅ እባልዋ ፊት ይደፍራል፤ ልጅም እናዳታፈራ መካን ያደርጋታል። የሰውን ንብረት ያለምንም ሃፍረት ይቀማል፤ ይሉኝታ የሚል ቃል በቋንቋው ውስጥ ያለ አይመስልም፤ አገሩን ለውጭ ሃብታሞች ይሽጣል፤ የአገሩን ሃብት ወደ ውጭ አገር ያሸሻል፤ የኢትዮጵያን የተለያዩ ጎሳዎች ለያይቶና በድንበር ከልሎ ነፃ ብሔረሰቦች ናችሁ በማለት ራሱን የብሔር በሔረሰቦች የበላይ ጠባቂ በማድረግ በሚቃወሙት ላይ የዘር ማጥፋት ያካሂዳል። የብሔር ብሔረሰቦች ጽንፈኞችን አሰልጥኖ እሳትና መርዝ አጉርሶ እርስ በእርሳቸው እንዲፋጁ ያደርጋል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር አልነበረችም እያለ ሕዝቡን እንዳይግባቡ ያደርጋል። ይህም ፍጅትና መከራ የበዛበት ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ይነሳበታል፤ አናሳም ስለሆነ መግቢያ ቀዳዳ ያጣል፤ ያም መከራና ፍጅት የበዛበት መልካሙን ትውልድ ይወልዳል፤ መልካሙ ትውልድ መላ ኢትዮጵያን ይሞላታል፤ ሆኖም ወንበዴው ተኩላ ሆኖ የበግ ለምድ ለብሶ መልካሙን ትውልድ ሊበላ ይመጣል፤ ግን በመከራ የተፈተነው መልካሙ ትውልድ እራሱን አሳልፎ ለተኩላዎቹ አልሰጥም በማለት በአሽናፊነት አገሩን ኢትዮጵያን ያድናል:: በመጨረሻም መልካሙ ትውልድ ጥንታዊት የሆነዉን የኢትዮጵያን ክብርና ግርማ ሞገስ ይመልሳል፤ የጎሳ እኩልነት፤ የማያልቅ ፀጋ፤ ማርና ወተት እንደ ውሀ የሚፈስበት አገር ትሆናለች፤ እንደገና ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘለዓለም ተክብራ ትኖራለች።
የመሪጌታው ንግርት አፈ ታሪክ ነው ተብሎ መወሰድ አይኖርበትም፤ ንግርት የሌለው ሕብረተሰብ የለም፤ በሁሉም ባሕል አለ። ንግርቱም እንደ ትንቢት ተወስዶ ከሃይማኖት ጋር ከተያያዘ የሕብረተስብ ችግር ሊፈታ አይችልም፤ በአገራችን በየጊዜው ባሕታውያን እንደዚህም የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች “ሁኔታን” አይተው የሚያስከትለውን በማስታዋል ይናገራሉ። መሪጌታው የሁለቱን ነገሥታት “ሁኔታ” በአንክሮ ተመልክተው በቀጣዩ ሶስት ትውልድ የሚመጣውን መከራ በትክክል ሊያውቁ ችለዋል፤ የመጥፎ “ሁኔታ” ውጤት ጥሩ ሊሆን አይችልም፤ ሌላ ጥሩ “ሁኔታ” ካልተፈጠረ ታሪካዊ ሂደቱ በተከታታይ መጥፎ ስለሚሆን፤ ስለዚህ የትንቢት ጉዳይ ሳይሆን “ሁኔታ” እየተከሰት የሚያመጣው መከራ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት የመሪጌታውን ንግርት መተንተን ይሆናል።
የመጀመሪያው “ሁኔታ” የተፈጠረው በኢጣልያን ፋሺስት ጦርነት ምክንያት ንጉሡ ወደ እንግሊዝ አገር ተሰደው ለአምስት ዓመት ኖረዋል፤ በዚህ አጋጣሚ የእንግሊዘን አገር የአስተዳደር ስርዓትና የንጉሠ ነገሥቱን በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ያለውን ተግባር ሳይመለከቱ ከግንዛቤ ያስገቡት የንጉሠ ነገሥቱን ኑሮውንና ክብሩን ብቻ ነበር። የእንግሊዝ ንጉሥ በማግና ካርታ [Magana Carta-Liberation] 1215 የነፃነት ሰነድ ላይ በተፈረመው ውል መሰረት ንጉሡ እንደማንኛውም ሰው የሕግ በላይነትን ተቀብሎ በአገሩ ሕገ መንግሥት ደንብ ለመተዳደር የተስማማመብት ነው። በሕዝብ ምክር ቤትና በጠቅላይ ሚንስተር የሚመራ መንግሥት መመስረቱንና ንጉሠ ነገሥቱ ምንም ዓይነት
ስልጣን እንደሌለው አስተውለው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ተመሳሳይ “ሁኔታን” ፈጥረው ሕዝባቸዉን ነፃ ሊያወጡ ሲችሉ ስለአልተጠቀሙበት ሕያዉነት የሚያስገኝላቸውን እድል አልፈው ለጥፋት ተዳርገዋል። ታሪካዊ “ሁኔታን” ያለመገንዘብ የሚያስከትለው ጥፋት ከባድ ነው። ንጉሡ ከስልጣን ሲወርዱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተከሰትዉን “ሁኔታ” ተመልክተው አገሩን መሪጌታው እንዳሉት ከጉግ ማንጉግ ስር እንዳትወድቅ ማዳን ሲችሉ በቸልተኛነት አገሩን ጥፋት ላይ እንድትወቅ አድርገዋል። ጉግ ማንጉግ በኖ ሲጠፋ የተፈጠረው “ሁኔታ” አገርን መከፋፈልና እንዳልነበረ ማድረግ ስለነበር ለወንበዴዎቹ ጥሩ “ሁኔታ” ስለሆነ ዛሬ አገራችንና ሕዝቡን በክልል የተከለለ የ80 ብሔረሰቦች አገር ሆኖ አክራሪ ጽንፈኞች እያሽበሩ በስርዓት አልባነት የምትገኝ አገር ሆናለች።
በእርግጥ አንድ ሰው “ሁኔታን” ፈጥሮ አምባገነንነትን ሊያመጣ ይችላል። ምክንያቱም የአምባገነንት ባለቤት ምንም ጊዜ ቢሆን አንድ ሰው ነው። የእንግሊዙ ንጉሠ ነገሥት በማግና ካርታ ላይ የሕዝቡን ነፃነት የተቀበለው ተገዶ ነው፤ በኢትዮጵያ ያ “ሁኔታ” ስላልነበረ ነገሠ ነገሥቱ በፈቃደኝነት ለሕዝብ ስልጣንን መሰጠት ፈቃደኛ አልነበሩም። አሁንም ቢሆን ለሕዝብ አምባገነኖች ስልጣንን አይሰጡም። ዲሞክራሲን የሚያመጣ ሕዝብ እንጂ ጠቅላይ ሚንስተሩ አይደለም፤ ዲሞክራሲ በአንድ ሰው ፈቃድ የሚከሰት አይደለም፤ ይህንንም በክፍል ሶስት በዝርዝር ይጻፋል፤ ከዚህ ሌላ ውድ ወገኖቼ በጥንቃቄ መመልከት ያለብን እውጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን በእነዚህ የለውጦች ዘመናት ምን አይነት ሚና እንደተጫውትን ነው። የምንፈልገዉን ዲሞክራሲ ማምጣት የምንችለው አንድ ሆነን በውውይት ነው፤ የሃሳብም ልዩነት ቢኖር የሚፈታው ዲሞክራሳዌ በሆነ ውይይት ነው። የንጉሠ ነገሥት አገዛዝ አበቃ ሲባል ተሰባስበን ወደ አገር የገባነው ለመወያየትና አገራችንን በዲሞክራሲ እንድትመራ ለማድረግ ሳይሆን እያንዳዳችን ስልጣን ለማግኝት ስለሆነ “ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር” ብለን ተላለቅን፤ ይህ መሪጌታ እንዳሉት “የጉግ ማንጉግ ዘመን ሆነ።” በወንበዴዎቹ ዘመን ደግሞ ተሰባስበው የገቡት “ካሬ ሜትር ቦታ ተመርተው” ኢትዮጵያን ሊከፋፍል ለመጣ ጠላት ሃይል ድጋፍ በመስጠት የጥፋቱ ተካፋይ ሆነዋል። ይህ መጻፍ አለበት፤ ስለዚህ ይህ ጸሐፊ የዚያ “አጥፍቶ ለጠፋው ትውልድ” ወገን ስለሆነ ያደረግነውን ስህተት ለመጭው ትውልድ መጠቆም አስፈላጊ መስሎ ስለታየው ነው። እንግዲህ “እኔን ያየህ ተቀጣ” ብሎ የሚቀጥለው ትውልድ የቀድሞው ትውልድ የሰራዉን ጥፋት አርሞ ደሙንና አጥንቱን ከስክሶ ለመጣው “መልካም ትውልድ” ማስረከብ ታሪካዊ ግዴታ ነው።
ክፍል ሁለትን ለማጠቃለል ያህል አሁን የተፈጠርውን “ሁኔታ” በአጭሩ መግልጽ አፈላጊ ነው። ኢሕድግ በጠቅላይ ሚንስተሩ አማካይነት በሁለት ዓመት ውስጥ ሕዝብ ለመረጠው መንግሥት ሥልጣን አስረክባለሁ ያለው ተገዶ ነው። ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ በክልል ለከፋፈለን፣ ለአሰረን፣ ለገደለን፣ ከመኖሪያችን ለአፈናቀለን፣ ዘርን ላጠፋ፣ አገርን ሽንሽኖ ለውጭ ሃይል ለሽጠ መንግሥት ሁለተኛ አንገዛም ብሎ ነው። ይህንን ለውጥ እዉን ለማደረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ መነጋገር ያለበት በለውጡ ሂደት መሆን አለበት እንጂ ጠቅላይ ሚንስተሩ ስለሚሾመውና ስለሚሽረው፤ ኢሕድግ ለ27 ዓመታት አደርኩት ብሎ ስለሚሰራው ድራማ፤ ቤተመንግሥት ዉስጥ ወታደሮች ስለአደረጉት ጨዋታ አይደለም። የኢሕድግ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዩ መሆን የለበትም። ነፃ የሆኑና ገለልተኛ የሆኑ ጋዜጠኞች ካሉ ውይይታቸው ስለሚጻፈው ሕገ መንግሥት፤ ስለ ነፃ ምርጫ ቦርድ፤ ስለ ነፃ ፍርድ ቤት፤ ለኢትዮጵያ ምን አይነት ሕገ መንግሥት ያስፈልግታል፤ ሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ ተብሎ ለሚመሰርተው መንግሥት የሚያስፈልገው አመራር ምን አይነት ቢሆን ጥሩ ነው? በፕሬዝዳንትና በጠቅላይ ሚንስትር ያለዉን ልዩነት፤ የፖለቲካ ፓርቲ በምን አይነት መደራጀት እንዳለበት? በጎሳና በብሔር ያለዉን ልዩነት? ታሪካዌ አመጣጡንና ሂደቱን፤ በሕገ መንግሥቱ እንዴት መካተት እንደሚችል? እነዚህ ሁሉ በአዋቂዎች አስተባባሪነት ከሕዝቡ ጋር መወያየት አስፈላጊ ነው።
ከሁሉ በላይ ለውጡን ምክንያት በማድረግ የገቡት ኢትዮጵያን ከአለፈው ትውልድ ምን መማር እንዳለባቸው ከግንዛቤ አስገብቶ ምን አይነት ሚና እንደሚጫወቱ በዝርዝር መታወቅ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ከአለፈው ጥፋት መማር ስለማይቻል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። እስከ አሁን ድረስ ለለውጡ ሂደት የፖለቲካ ፕሮግራም አዘጋጅተው ለሕዝቡ ያቀረቡት ነገር የለም፤ ጥቂት አክራሪ የጎሳ ጽንፈኞች በቁርስና በምሳ ተገዝተው በሕዝቡ ላይ ሽብር እየፈጠሩ ነው። አንዳዶቹም ድርጎ እየተቀበሉ በምርጫ ጊዜ ሽብር ለመፍጠር መዘጋጀታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። አንድ መቶ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የተለያዩ የጎስ ድርጅቶች የየራሳቻውን ፕሮግራም በማውጣት ተደራጅተዋል። በጎሳ ተደራጅተው የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ ተገቤ ነው። ግን በሃይማኖትና በዘር የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት የሚያመጣው የኢሕድግን ክልል መንግሥት ስለሆነ ይህንን ከግንዛቤ አስገብተው ከሕዝባቸው ጋር ተነጋግረው የሕዝብ መንግሥት የሚመሰርበትን “ሁኔታ” መፍጠር ታሪካዊ ግዴታቸው ነው። መልካሙ ትውልድ ደሙን አፍሶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣዉን ነፃነት ማደናቀፍ መሆኑን ተረድተው ያለዉን ልዩነት በውይይትና በዲሞክራሲ አጥብቦ የሕዝብ መንግሥት የሚመጣብትን “ሁኔታ” መፍጠር ታሪካዌ ግዴታ ነው። ይህ ካልሆነ ተመልሶ ያለፈው ትውልድ ያጠፋዉን መድገም ይሆናል። በክፍል ሶስት ላይ “ዲሞክራሲ እንዴት እንደተመሰረተ ከዓለም አቀፍ ታሪካዊ ሂደት ጋር እያመሳከርን እንማማራለን።
ክፍል ሶስት
በሶስተኛው ክፍል የሚደረገው ውይይት እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ መከራ ፈትኖ ለወለደው “መልካሙ ትውልድ” ለሚመሰረተው መንግሥት ምሶሶና ግድግዳ ሆኖ አዲስቷን ኢትዮጵያ በምን ዓይነት “ሥርዓትና” “ሁኔታ” ሊሰራ ይችላል ብለን በተረጋጋ መንፈስ ሆነን የምንወያይበት መድረክ ይሆናል። ውይይቱ በበለጠ እንዲዳብር በማለት ሕዝብ ለሚመሰርተው መንግሥት አስፈላጊ ናቸው በምንላቸው ዝክረ ነገሮች ላይ እናተኩራለን። ከዚህ ውጪ ኢሃዴግ በአወጣው አጀንዳ ላይ ሆነን መዋለል አስፈላጊ ያለመሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ግዴታው ነው። በብዙሃን መገናኛና በአብዛኛው ድህረ ገጾች ላይ የሚደረገው ውይይት ኢሃዴግ በአወጣው አጀንዳ ስለሆነ የለውጡን ሂደት ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ማለት ይቻላል። ስለዚህ እዚህ ላይ የሚቀርቡት ውይይቶች ስለ ዓለም አቀፍ “ዲሞክራሲ” ስለ “ሕገ መንግሥት” ስለ “ነፃ ፍርድ ቤት” ስለ “ነፃ ምርጫ ቦርድ” ስለ “ሕዝብ መንግሥት አወቃቀር” ይሆንና በተጨማሪ አገራችን ውስጥ ለብዙ ጊዜ ሲያወዛግብ የነበረዉን “ሁኔታ” የሚገልጽ እንደ “ብሔር” “ብሔር ብሔረሰቦች” እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን “ጎሳዎች” “በአብዮታዌ ዲሞክራሲ” ስም እንዴት ወደ “ብሔር ብሔረሰቦች” ተለውጠው እንደተከፋፈሉ በሰፊው መወያየት አስፈላጊ ነው። ለውይይታችን ግልጽ እንዲሆን በማለት የእነዚህን “ቃላት” አመጣጥ፣ ትርጉምና አጠቃላይ ይዘታቸውን እንመለከታለን። ለምሳሌ “ዲሞክራሲ” ምን ማለት እንደሆነ እንዴትስ እንደመጣ፣ “ብሔር” ወይም “የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት” እንዴት እንደመጣ ከእነ ትርጉሙ፣ “ጎሳ” ምን ማለት ነው? “በጎሳና” “በብሔር ብሔረሰቦች” ያለውን ልዩነት ዓለም አቀፍ በተስማማበት ትርጉም መሰረት እንወያያለን። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት ለመልካም አስተዳደር “ዲሞክራሲ” በዋናነት “ቅድመ ሁኔታ” ሆኖ ሲቀርብ ደግሞ በአንጻሩ “ብሔር ብሔረሰቦች” “ጎሳ” “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚባሉት ዝክረ ነገሮች በአንድ አገር ፖለቲካ ሂደት ላይ ምን አይነት ሚና እንደሚጫወቱ በዝርዝር ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል። በክፍል ሁለት ላይ በዝርዝር እንደቀረበው “ዲሞከራሲ” ሊመሰረት የሚችለው ከዚህ የሚከተሉት “ቅድመ ሁኔታዎች” ሲቀነባበሩ ነው [ቅድመ ሁኔታዎችን ክፍል ሶወስት ይመልከቱ]።
እነዚህ “ቅድመ ሁኔታዎች” የሉም። እነዚህ “ቅደመ ሁኔታዎች” ከሌሉ መልካም አስተዳደር ሊኖር አይችልም። በአለፉት ሶስት ትውልደ ዘመናት እነዚህ “ቅድመ ሁኔታዎች” አልነበሩም። አሁንም የሉም። “ቅድመ ሁኔታ” በተአምር የሚከሰት ርዕዮተ ዓለም አይደለም። በታሪካዌ ሂደት ቀስ በቀስ የሚዳብርና እንደልምድ ሆኖ [norm] በስራ ላይ የሚዉል ያልተደነገገ ሕግ ነው። ማለትም ሕዝብ በዘልማድ የሚገለገልበት ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል የልጆችን ጨዋታዎች ብንመለከት ለጨዋታቸው ሁሉ ያልተደነገገ [ያልተጻፈ] ሕግ አሉት። ያን ሕግ የሚያከብር ልጅ ከጨዋታ ውጭ ይሆናል፤ “አፋራም ተብሎ” ማንም ልጅ ከሱ ጋር አይጫወትም፤ ከባድ ቅጣት ነው። ደግሞ ወደ ተደነገገ ሕግ ስንመጣ ቀስ በቀስ በዓለም አቀፍ አዋቂዎች የዳበረ ነው። “ሕግ” ፍጥረትንና የሰዉን ልጅ ባሕርያት አጥንተው ለሰው ልጅ መተዳደሪያ ይሆናል ተብሎ በውውይትና በስምምነት የተደነገገ የሰው ልጅ መተዳደሪያ ደንብ ነው። እንግዲህ ከልጆች ጨዋታዎች ሕግ ወደ “ሕብረተሰብ መተዳደሪያ ሕግ” ተሻግረን እንወያያለን።
የአእምሮቻንን ጅማት ለማጠንቀርና የሕሊና ንቃታችን ከፍ እንዲል በማለት ይህንን ውይይት የምንጀምረው አገር በቀል በሆነው ዘርዓ ያዕቆብ በተባለው ፈላስፋ ላይ ይሆናል። ዘርዓ ያዕቆብ የንቧን ስራ በትኩረት ተመልክቶ እንዲህ ይላል፦
ንብ ስራዋ እፅብ ድንቅ ነው። የማትቀስመው ዕፅዋት የለም። ከእነዚህ ሁሉ ዕፅዋት የቀሰመችዉን ሰብስባ እጅግ ጣፋጭ የሆነዉን ማር ትሰራለች። ማሩም ለመጠጥ የሚሆን ጠጅ ይወጣዋል። የጠጁም ቅሪት ጧፍ ሆኖ በጭለማ ጊዜ ብርሃንን ይሰጣል። ዕውቀት በተለያየ ስፍራ ይገኛል። የሰውም ልጅ እንደንቧ ሆኖ የተለያዩ ቦታ የሚገኝዉን ዕውቅት ቢቀስም ብዙ ዕውቀቶችን ይሰበስባል። እንደ ንቧም ባለሙያ ይሆናል። ግን አንድ ሰው ሁሉን አውቃለሁ ካለ ምንም ነገር የማያውቅ መሃይም ሆኖ ይቀራል። ለመሃይምነቱም ፍጹም ተወዳዳሪ አይኖረውም። ግብዝና ሞጎደኛም ስለሆነ ሂደቱም ታሪካዊ አይሆንም። ስርዓት አልባም ስለሆነ ኑሮው ሁሉ በመከራ ይሆናል። ስህተቱን መልሶ መላልሶ ስለሚሰራው ከመከራው ምንም ጊዜ ቢሆን አይወጣም። መከራም አይመክረዉም። [ዘርዓ ያዕቆብ]
እንግዲህ እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ትኩረት ሰጥተን ከተመለከትን “ሕግ” እንደማሩ ከተለያዩ ሃሳቦች የመነጨ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ዲሞክራሲ እንደወርቅ ተፈልቅቆ የወጣው እንደማር ተሰርቶ በወጣው “ሕግ” ነው። “ሕግን” አንድ ግለሰብ አንድ ቀን ተነስቶ ያወጣው ነገር አይደለም። ወይም የአንድ ግለሰብ ስራ አይደለም። እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ፍጥረትን በትኩረት ከተመለከቱ ግለሰቦች ተሰባስቦ ነው “ሕግ” የሆነው። ዲሞክራሲም በአንድ ግለሰብ በጎ ፈቃድ የተሰጠ የመልካም አስተዳደር “ሁኔታ” አይደለም። ግለሰብ “ያዘው” “እሰረው” “ግረፈው” “ግደለው” የሚል ባሕርይ ስለአለው ብቻዉን የሚያመጣው “አምባገነንነት” እንጂ ዲሞክራሲን አይደለም። በታሪክ ውስጥ ዲሞክራሲ በግለሰብ ችሮታ ወይም “በአብዮታዌ ዲሞክራሲ” መጥቶ አያቅም። “የአብዮታዌ ዲሞክራሲ” ዋና ስራው የግለሰቡን አምባገነንት መብት ማስጠበቅ ነው። በአብዮታዌ ዲሞክራሲ ጎሳውን ብሔር ነው፤ብሔሩን ክልል ነው፤ ክልሉን መንግሥት ነው፤ እያለ “ብሔር ብሔረሰቦች” ብሎ የፈጠራቸውን ማዋጋት፣ ማፋጀት፣ በቋንቋ እንዳይግባቡ ማገት፣ ማሰር፣ ያልተባበሩትን መግደል፣ መዝረፍ፣ መሰረቅ ነው። አብዮታዌ ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ መልካም አስተዳደር አላመጣም። ያመጣው ፍጅትና ከሚኖርበት መፈናቀል ነው። አሁን ያለው “ሁኔታ” በቂ ምስክር ነው።
ይህንን “የሕግ” አመጣጥ ከግንዛቤ አስገብተን “ሕግና” “ሕገ መንግሥት” እንዴት ሊዳብሩ እንደቻሉ እንመለከታለን። ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ እንዳለው “ሕግና” “ሕገ መንግሥት” የዳበሩት በየቦታው ከሚገኙ ፈላስፋዎች ነው። እዚህ ላይ ሳልል የማላልፈው አንድ ግንዛቤ አለኝ። ይኸውም አገር በቀል የሆነዉን ብቸኛ ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብን እንደ ፈላስፋ አንመለከተዉም። በተለይ ምሁር ነን የምንለዉ ዘርዓ ያዕቆብን የምናየው እንደ ተራ “ደብተራ” ነው፤ የደብተራ ትርጉሙንም ምን እንደሆነ አናውቀውም። በዚህ ጸሐፊ እይታ እኛ ኢትዮጵያኖች ያለመጠን “ጥገኛነት” እንደሚያጠቃን ነው። ራሳችንን ችለን እንዳንመራመር ታላቅ የሆነ ተጽኖና እገታ አለብን። እንግዲህ ስለ ዘርዓ ያዕቆብ የተባለዉን በአትኩረት እንመልከት።
“ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ፈላስፋ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ከሌሎች ሰምቶ የጻፈው እንጂ እሱ ይህንን የመሰለ ፍልስፍና ሊጽፍ አይችልም።” በማለት እናጣጥለዋለን። ይህም ማለት ፍጡራዊ የሆነዉን ችሎታችንን ትኩረት ሰጥተን ዘርዓ ያዕቆብ የተመለከተዉን ፍጡራዊ ንብ ማየት አለመቻላችን ነው። ጥራት የሌለው ፍልስፍናችንም ጎጠኛ፣ ዘውገኛ፣ ጽንፈኛ፣ ጎሰኛ አድርጎናል። ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳዝነው የቤተክርስቲያንችን ሊቃውንት እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ፍጥረትንና የሰው ልጅ “ሁኔታ” ማየት ስላልቻሉ ዘርዓ ያቆዕብን ሃይማኖተ ቢስ እያሉ እነሱ የአምባገነን “አወዳሽ” ሆነው ቀርተዋል። ስለዚህ የተወለደው መልካሙ ትውልድ ያለፈዉን ትውልድ ስህተት ተመልክቶ አገሩን ኢትዮጵያን በመልካም አስተዳደር እንዲመሰርታት ተስፋ እናደርጋለን።
የሕግና ዲሞክራሲ ታሪካዊ ሂደት
ብላቴን ጌታ ሲራክ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ “ራሴ ላስ” ተብሎ በእንግሊዛዊ ደራሴ በሳሙኢል ጆንሰን የተጻፈዉን መጽሐፍ ሲተረጉሙ እንዲህ ይላሉ፤ “መጽሐፉ ስለ ስነ ፍጥረት ሲመራመር ወደር የለዉም። ከፍጥረት ሁሉ የሰው ልጅ ፈጽሞ እርካታ የሌለው ፍጥረት ነው።” ይሉና ትንተናቸዉን ይጀምራሉ፦
ራሴ ላስ የተባለው አልጋ ወራሽ [መስፍን] በዚያ በተራራ በተከበበችው ሸለቆ ዉስጥ ሲኖር ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ተደራጅቶ የአባቱ ዙፋን ላይ ዘውዱን ጭኖ እንዲቀመጥ እስኪጠራ ድረስ ይጠብቃል። ግን ጊዜው እስኪደርስ ድረስ በልዑላን ቤተሰቦች ታጅቦ፤ በእምቢልታ፣ በመለከት፣ በበገና፣ በተለያዩ ሙዚቃ እየተደሰተ ማርና ወተት እንደዉሀ እየፈሰሰለት ይኖራል። ግን እነዚህ ደስታ ይሰጡታል የተባሉ ነገሮች ሁሉ እያሉ ምንም ነገር ያስደሰተው የለም። በመጨረሻም በሸሎቆው ያሉትን እንስሳት ተመልክቶ መስፍኑ እንዲህ አለ ይባላል። “እነዚህ ሁሉ እንስሳት እንደእኔ እርቧቸው ይበላሉ። ዉሀ ጠምቷቸው ይጠጣሉ፤ እኔም እንደነሱ እበላለሁ፤ እጠጣለሁ፤ ግን እንደነሱ እርካታ አድርጌ አላርፍም፤ ለፍላጎቴ መጠን የለውም፤ ስለዚህ ከዚህ ሸለቆ ውስጥ ወጥቼ የምፈልገዉን ነገር ማግኝት አለብኝ።” ብሎ ከእህቱና ከጠባቂው ጋር ወደ ግብፅ አገር ሄደ። እዚያም ሲደርስ የፈለገዉንና እርካታ የሚሰጠዉን ነገር ስላላገኘ ወደ አገሩ ተመለሰ። የአልጋ ወራሹም ፍላጎት ፍጻሜ የሌለው ፍጻሜ ሆነ። ከፍጡራን ሁሉ የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለውም። [ራሴ ላስ]
የሕግና ዲሞክራሲ አመጣጥ የሚጀምረው ታላላቅ ናቸው ከሚባሉት “ታሪክ” አምድ ላይ ነው። ከላይ የተጠቀሰው “ራሴ ላስ” ልብ ወለድ ስለሆነ “ታሪክ” ነው ብለን አንወስደዉም። ግን ሥነ ጽሑፉ ላይ ስለ ሰው ልጅ በምሳሌ የተነገረው እውነት ነው። ሰውንና እንስሳትን አነጻጽሮ አንዱ ፍጡራዊ በሆነ ገደብ እርካታ ሲያገኝ ሌላኛው ደግሞ ፍጡራዊ በሆነ ገደብ የለሽ ፍላጎት ይኖራል። እንግዲህ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብለን ብንመለከት እንስሳና ሰው የተለያየ ባሕርይ እንዳላቸው ያሳየናል። የሰው ልጅ እንስሳትን በተለያየ ዘዴ እንደሚቆጣጠረው ሁሉ ራሱንም ገደብ አስይዞ መቆጣጠር ችሏል። ለምሳሌ የኢንግሊዝና የአሜሪካን ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ እንዴት እንደተመሰረተ ብንመለከት የመልካም አስተዳደር “ታሪካዊ” ሂደትን በሚገባ ልናውቅ እንችላለን። ይህም ማለት አምባገነን በየጊዜው እየመጣ የራሱን ፍላጎት ሊጭንብን አይችልም። እኛም እንደከብት መንጋ ለውጥ ሳይኖር ሊመጣልህ ነው እየተባልን በወሬ አንነዳም። ለውጥ ታሪካዊ ሂደት አለው። ይህውም የኢንግሊዝ ሕዝብ የንጉሠ ነገሥቱን ገደብ የለሽ ስልጣን “እምቢ ብሎ” በ 1215 በማግና ካርታ [Magna Carta] ላይ በተፈረመው ስምምነት መሰረት የንጉሡን ስልጣን ገድቧል። ይህም ማለት ንጉሠ ነገሥቱ ምንም ዓይነት ስልጣን ሳይኖረው በዙፋኑ ላይ እንዳለ ሆኖ የመልካም አስተዳደር የበላይ ጠባቂ ሆኗል። ከዚህም በላይ “ታሪካዊ” ሆኖ በዓለም ሕዝብ የሚታወቀው “የእንግሊዝ ሕዝብ ሰብአዊ መብት” [English Bill of Rights, 1689] ተብሎ የሚታወቀውና ለብዙ አገሮች ተምሳሊት የሆነው “የሕዝብ ሰብአዊ መበት” ነው። ይህም መብት የሕዝብን “የመናገር” “የመጻፍ” “የመሰብሰብ” “የመምረጥ” “ራሱን ለመከላከል መሳሪያ የመያዝና” “ያለሕዝብ ፈቃድ መንግሥት ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል” የተደነገገበት የሕዝብ መተዳደሪያ ደንብ ነው። እንግዲህ በአትኩረት መመልከት ያለብን “ዲሞክራሲ” የሚመሰረተው በሕግ የበላይነት ነው እንጂ “በአብዮታዊ ግርግር” አይደለም፤ ዲሞክራሲ የሚመሰረተው በሕዝብ ነው። የመለሰ ዜናዊ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሕዝብን ለመዝረፍ የተደረገ ግርግር ነው።” “ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንደተባለው ከብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ከሕዝብ ተዘርፏል፤ የትግሬ ወያኔ “አብዮታዊ ዲሞከራሲ” ማለት ይህ ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ ጫካ እንገባለን ስለሚሉና ጫካ የሽፍታ መኖሪያ ስለሆነ ይህንን ውንብድናቸውን የሚያስቆም ኃይል ማሰማራት አያስፈልግም። ከጫካ ውጭ ሆነው እንደሰው መኖር ስለማይችሉ እርካታቸውን የሚያገኙት ጫካ ውስጥ ስለሆነ ይህ መብታቸው መጠበቅ ይኖርበታል።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ ምንጭ
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት “አባቶች” እየተባሉ የሚታወቁት ሕግ አርቃቂዎች ሕገ መንግሥታቸዉን ያረቀቁት ከተለያዩ አገሮች በተሰባሰቡ ስነ ፍጥረትን በአትኩረት ከሚያጠኑ የፍልስፍና ተመራማሪዎች ነው። የሴኔጋሊስ ስነ ፍጥረትና ታሪክ ምሁር ሼክ አንታ ዲዮፕ በጥናት እንደደረሰበት ፍልስፍናን ፍልስፍና የሚያደርጉት ሁለት ባሕርይ ሲኖሩት ነው ይላል። አንደኛው ተፈላሳፊው “እሱ ራሱን መሆኑን ሲያቅ፣” ሁለተኛው ደግሞ ተፈላሳፊው “እውነት የሆነውንና እውነት ያልሆነውን ለይቶ ሲያቅ” ነው ይላል። እንስሳትና ሰው የሚለዩት በዚህ መስፈርት ነው። እንስሳት ራሳቸውን ያውቃሉ ግን “እውነትንና እውነት ያልሆነዉን” ነገር ያውቃሉ ማለት ያስቸግራል:: “እውነትንና እውነት ያልሆነዉን” ለይቶ ማወቅ ትኩረትን ይጠይቃል:: ስለዚህ ሰው ስለሆነ ብቻ ትኩረት ይኖረዋል ማለት አይቻልም። ትኩረት ከሌለ “እውነትንና እውነት ያልሆነዉን ነገር ማወቅ ያስቸግራል።” ስለ ፍልስፍና ጥራት ሁለት “ሐተታዎችን” የጻፈ የምዕራብ አፍሪቃው አሞ የሚባል ፈላስፋ ደግሞ [Amo, West African Philosopher 1703/1759] “ፍልስፍና ጥራት ሊኖረው የሚችለው ተፈላሳፊው ቅን በሆነ ልቦና እና ትክክል የሆነ የስነ ፍጥረትን መመርመሪያ ሲከተል ነው” ይላል። እንግዲህ እዚህ ላይ በአትኩረት መመልከት ያለብን የአሜሪካ ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ በምን አይነት “ሁኔታ” እንደተፈጠረ ነው። የሕገ መንግሥታቸዉን መግቢያ እንመልከት፦
Preamble
We the People of the United States, in Order to form a more perfect Union, establish Justice, insure domestic tranquility, provide for the common defense, promote the general welfare, and secure the Blessings of Liberty to ourselves and our posterity, do ordain and establish this Constitution for the United States of America.
እንግዲህ ይህንን የሕግ መግቢያ ስንመለከተው የሚያሳየው የሕዝቡን አንድነት ነው። “እኛ በአሜሪካ ውስጥ የምንኖር ሕዝብ ሕብረታችን ከምንጊዜም በፊት እንዲዳብር፣ ፍትህና ሰላም እንዲኖረን፣ ዳር ድንበራችን እንዲጠበቅ፣ ለሁላችንም መልካም አስተዳደር እንዲኖረን፣ ተባርኮ የተሰጠነን ነፃነት ለእኛና ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ በማሰብ ይህንን ሕገ መንግሥት ለተባበረችው አሜሪካ የመተዳደሪያ ደንብ እንዲሆን አጽድቀናል።” ይህ ከተባለ በኋላ ለአገራቸውና መለያ ለሆነው ባንዲራቸው ያላችውን ክብርና እምነት ለመጠበቅ ቃል ኪዳን ይገባሉ። “ I pledge allegiance to the Flag of the United States of America and to the Republic for which it stands, one nation, indivisible, with liberty and justice for all.”
እዚህ በአትኩረት የምንመረምረው በመግቢያው ላይ የተጻፈበትን ቃላት ነው፤ “የአገር ሰላም” “የአገር መከላኪያ ጦር” “የአገር መልካም አስተዳደር” “ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፈው ነፃነት” ሲሆን “ጎሳ” “ብሔር” “የብሔር ብሔር እኩልነት” “አብዮታዌ ዲሞክራሲ” የሚል ነገር የለበትም። ቃል ኪዳናቸውም ለባንዲራቸው፣ ለማይከፋፈለው ሕዝብ፣ ለነፃነታቸውና በፍትሕ ለተመሰረተችው ለተባበረችው አሜሪካ መቆማቸዉን ያስታውቃሉ። መንግሥታቸውም የተዋቀረው “መንግሥት በሕዝብ ለሕዝብ” በሚለው ወሳኝ በሆነው መርሐ ግብር ነው። መንግሥትን የሚያቋቁመው ሕዝብ ነው።
የአሜሪካ ሕዝብ ከመላ ዓለም የተሰባሰበ ነው። የሌለ አይነት ጎሳ የለም። ምንአልባትም ከማንም አገር የበለጠ የጎሳ ዓይነት ያለበት አገር ነው ማለት ይቻላል። ግን ልዕላዊነትን መርጦ አንድ ሕዝብ በመሆን የማይከፋፈል አገር በሕገ መንግሥቱና በዲሞክራሲ የሚመራ ስርዓት መስርተዋል። ሕጉም የተረቀቀው ከተለያዩ ፈላስፋዎች በተወሰደ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ለምሳሌ የአንድ አገርን መንግሥት አስተዳደር ለሶስት ከፍሎ የጻፈውን የፖለቲካ ስርዓት ተመራማሪዉን ፍልስፍና የወሰዱት ሞንቴስኪው [Montesquieu 1689/1755] ከሚባለው የፈረንሳይ ፈላስፋ ላይ ነው። በሶስት የተከፈሉት የአስተዳደር ስልጣን ክፍሎች ሚዛናዊ ስለሆኑ በእኩልነት የአገሩን ዲሞክራሲ ይጠብቃሉ። ሕዝብ ወኪሉን ይመርጣል[ምክር ቢቱን] የሕዝብ ምክር ቤት ሕጉን ያወጣል፤ ፍርድ ቤቱ ሕጉን ይተረጉማል፤ የአገሩ መሪ ሕጉን ያስከብራል፤ አንዱ ከአንዱ አይበልጥም። ሶስቱም መንግሥት በእኩልነት እየተጠባበቁ ሕዝቡን በዲሞክራሲ እንዲተዳደር በአንድነት ሆነው ይመራሉ። ያለመግባባት ሲፈጠር በዲሞክራሲ ይፈታል። የአገሩ መሪ ሕግን ሲተላለፍ ፍርድ ቤቱ ያግተዋል። የሕግ በላይነትን አልቀበልም ሲል ደግሞ የሕዝብ ምክር ቤቱ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በመተባበር ከአመራር ስራው ላይ ያነሰዋል።
የአሜሪካንን ሕገ መንግሥት ታሪካዊ ከአደረጋቸው አንዱ የሰብአዊ መብት ነው። [The Bill of Rights] ይህም ጽንሰ ሃሳብ የመጣው ከእንግሊዛዊ ፈላስፋ ጆን ስተዋርት ሚል [John Stuart Mill 1806/73] ነው። የግለሰብ መብት ሊታገት የሚችለው የሕብረተሰቡን መብት ሲነካ ብቻ ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ የግለሰቡ መብት መነካት የለበትም። ብዙኃኑ የአናሳዉን መብት እንደራሱ አድርጎ መጠብቅ አለበት ይላል። የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አጥብቆ የግለሰቡን መብት ከሁሉ አብልጦ ያስከብራል። ቮልተየር [Voltaire 1694/1778] የሚባለው የፈረንሳይ ፈላስፋ ሃይማኖትና መንግሥት መለያየት አለባቸው ይላል። መንግሥት ሃይማኖት ስራ ውስጥ፤ ሃይማኖት መንግሥት ስራ ውስጥ መግባት የለበትም። ግለሰብም የፈለገዉን ሃይማኖት መከተል መብቱ ነው። መንግሥትም እግለሰቡ ሃይማኖት ውስጥ መግባት የለብትም። የመናገር፣ የማመልክ፣ የመነገድ መብት መነካት የለበትም ይላል። የአሜሪካ ሕገ መንግሥት እነዚህን መብቶች በጥንቃቄ ይጠብቃል። በተጨማሪ ሕግ አርቃቂዎቹ የበርካታ ፈላስፋዎችን ጽንሰ ሃሳብ በመውሰድ የተጻፈ ሰነድ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻላል። በ 225 ዘመን ውስጥ ለ27 ጊዜ ተሻሽላል።
እንግዲህ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የተወለደው በርከት ካሉ ስነ ፍጥረትን ከሚመራመሩ ፈላስፋዎች በተወሰደ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ሰነዱ የሰዉን ልጅ ባሕርይ በሚገባ ሊቆጣጠር የሚችል ልጓም ነው። ይህም ሆኖ የሕገ መንግሥቱ ታሪካዊ ሂደት ብዙ ውጣ ውረድ ነበረበት። ሕገ መንግሥቱ በፈጠረው “ዲሞክራሲ” የተባበረችው አሜሪካ “አንድ ሕዝብ” “አንድ የማይከፋፈል አገር” “የገለሰብ መብት የሚጠበቅበት ሕብረተሰብ” “በአንድ ባንዲራ” ስር ሆኖ በስምምነት ለመኖር ቃል ገብቶ አገሩን የመሰረተበት “ሁኔታ” ነው። ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንን ቃል ኪዳን የሚያፈርስ ኃይል ተነስቶ ነበር። እንግዲህ ትኩረታችንን ከፍ አደረገን ማየት ያለብን እንደገና “ራሴ ላስ” ላይ የተጻፈዉን ፍጡራዊ የሆነዉን ታሪካዊ ሂደት ነው። ይኸውም በእንስሳና በሰው ልጅ ያለውን ፍጡራዊ የሆነዉን ገደብና ገደብ የሌሽን እርካታ ነው። የሕግ በላይነትን አንቀበልም ብለው ገደብ የሌሽን ፍላጎታቸዉን ለሟሟላት የፈለጉ ግለሰቦች ችግር በመፍጠር አዲስ የተፈጠረውን ዲሞክራሲ ሊያፈርሱ በተለያዩ ጊዜ ሞክረው ነበር። ነገር ግን የሕግ በላይነትን ተቀብለው አገራቸዉን በዲሞክራሲ እንድትመራ የፈለጉ ዜጋዎች ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ የአሜሪካንን ዲሞክራሲና የግለስቡን “ሰብአዊ መብት” አሰከብረዋል፤ በተለይ የጥቁርን ሕዝብ በታችነትና የተለየ “ጎሳን” በላይነት “ሁኔታ” ለመፍጠር በተደረገ ሙከራ የአሜሪካ ሕዝብ በታላቅ ጀግንነት አንድነትንና እኩልነትን በዲሞክራሲ መስርቷል:: የአሜሪካንን ዲሞክራሲ በስራ ላይ ለማዋል ብዙ አገሮች ሞከረው ነበር። ላቲን አሜሪካኖች የአሜርካንን ሕገ መንግሥት ለመከተል ሙከራ አድረገዋል። ግን በስራ ላይ ሊውል አልቻለም። አውሮፓውያንም በተለያየ ጊዜ ሙከራ አድርገዋል። የፊሊፕንስ መንግሥት ቃል በቃል ሕገ መንግሥቱን ወስዶ ነበር ግን በአምባ ገነን ተወግዶ ስራ ላይ ሳይውል ቀርታል። ዲሞክራሲ በስራ
ላይ እንዲውል ከተፈለገ ሕብረተሰቡ እንደ አይኑ ብሌን መጠበቅ አለበት፤ ይህ ካልሆነ አምባገነን ተነስቶ ገደብ የሌሽ የሆነዉን ፍላጎቱን ሕዝብ ላይ ስለሚጭን “ዲሞክራሲን” በታላቅ ጥንቃቄ መጠበቅ የዜጋዎች ሃላፊነት ነው። አምባገነንን አጥብቆ መዋጋት ለሰው ልጅ ነፃነቱና ክብሩ ነውና።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው “ሁኔታ” ተመሳሳይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ “የትግራይን በላይነት” አጥብቆ በመቃወም ኢሕድግን ማስወገድ አለበት። በዲሞክራሲ አሸናፊና ተሸናፊ የለም። አሁን የሚደረገው ጥረት ኢሕድግን መልሶ ስልጣን ላይ ለማድረግ ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥብቆ መከላከል አለበት። ወያኔ እርካታቢስ ስለሆነ አስሮም፣ ገድሎም፣ ሰርቆም፣ በልቶም አይጠግብም።
የጠቅላይ ሚንስተሩ ቢሮ ከውጭ አገር በሕግ የሰለጠኑ የሕግ አማካሪዎች ያስፈሉጉታል። ብዙ ሕግን ያልተከተሉ ስራዎች በአገር ውስጥ እየተሰሩ ነው። የወያኔ ምክር ቤት ተፈጸመው ለተባለው ወንጀል ሁሉ ማንንም ቢሆን በምህረት ሊያድን አይችለም። በዘር ማጥፋት ተጠያቂዎች አሉ። የመንግሥት አቋምዋትን እንደ አየር መንገድ፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሙንኬሽን የሕዝብ መንግሥት ሳይመሠረት ሊሽጥ አይገባም። ሲቆጣጠረው የነበረውን ፍርድ ቤቱንም ነፃ ሊያደርገው አይችልም። ለለውጥ ቃል በተገባው መሰረት ሕዝብ ለሚመርጠው ስልጣንን ከማሰረከብና የአገሩን ሰላም ከማስከበር ሌላ ስልጣን እንደሌለው የሕግ አዋቂዎች እንዲነግሩት ያስፈልጋል።
ክፍል ሶስትን ለማጠናቀቅ ያህል አጠር ያለ ውይይት ያስፈልጋል። በቅደም ተከተል ይቀርባል እንደተባለው ስለ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ስለ ጎሳ፣ ስለ የፖለቲካ ፓርቲ አመሰራረት፣ ስለ ነፃ ፍርድ ቤት በክፍል አራት ላይ በዝርዝር ይቀርባል። ሊላው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው የምንለው ነገር ቢኖር ምርጫው በምን አይነት “ሁኔታ” ይካሂዳል በሚለው ጉዳይ ላይ ነው። ይህንን በተመለከተ በመጨረሻው ውይይታችን ላይ በክፍል አራት ላይ በዝርዝር ይቀርባል፤ ይኸውም ዲያስፖራው ምን ሊረዳ እንደሚችል፤ የምርጫ ሳጥን [Eletronic Machine] ከተለያዩ አግሮች በእርዳታ የምናገኝበትን “ሁኔታ” ማመቻቸት፤ ሕዝብ የተስማማበት ከአራት የማይበልጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስምምነት የሚመሰረትበትን “ሁኔታ”፤ ለምሳሌ የገበሪዎች፤ የወጣቶች፤ የሴቶች፤ የሰራተኞች፤ ሕዝቡ በየቀበሌው፤ በየወረዳው፤ እንዴት ተደራጅቶ የምክር ቤቱን አባል እንዲት እንደሚመርጥ [A blue print and a road map for genuine democracy] እነዚህን ሁሉ ለማከናወን የሚወስደው ግዜ ተሰልቶ እንዲስተካከል ማሳሰብ፤ የምርጫው ቦርድ በምን አይነት “ሁኔታ” እንደሚመሰረት፤ ነፃ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግና ወንጀለኞች ወደ ፍርድ የሚቀርቡበት፣ የተዘረፉትና ወደ አንድ ክልል ቦታ ተወሰደው የተከማቹት የእንዱስትሪ ማምረቻዎች የሚመለሱበት “ሁኔታ” ማመቻቸት፤ በሕገ ወጥ መንገድ ተዘርፈው በውጭ አገር ባንኮች የተቀመጡ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አማካይነት የሚመለሱበትን “ሁኔታ” መወያየት አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሁሉ በቅጡ ተጠንቶ በክፍል አራት ላይ ይቀርባል።
ክፍል አራት
ስለ ኢትዮጵያ ነፃ ምርጫ ለውይይት የቀረበ አጀንዳ
ክፍል ሶስት ላይ እንደተጠቀሰው በቅደም ተከተል ይቀርባል እንደተባለው ስለ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ስለ ጎሳ፣ ስለ የፖለቲካ ፓርቲ አመሰራረት፣ ስለ ነፃ ፍርድ ቤት በዚህ ክፍል ላይ በዝርዝር ይቀርባል። ሌላው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው የምንለው ነገር ቢኖር ምርጫው በምን አይነት “ሁኔታ” ይካሄዳል በሚለው ጉዳይ ላይ ነው። ይህንን በተመለከተ በዚህ በመጨረሻው ውይይታችን ላይ በዝርዝር ይቀርባል፤ ይኸውም ዲያስፖራው ምን ሊረዳ እንደሚችል፤ የምርጫ ሳጥን [Eletronic Machine] ከተለያዩ አገሮች በእርዳታ የምናገኝበትን “ሁኔታ” ማመቻቸት፤ ሕዝብ የተስማማበት ከሶወስት ወይም ከአራት የማይበልጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስምምነት የሚመሰረትበትን “ሁኔታ”፤ ለምሳሌ የገበሪዎች፤ የወጣቶች፤ የሴቶች፤ የሰራተኞች፤ ሕዝቡ በየቀበሌው፤ በየወረዳው፤ እንዴት ተደራጅቶ የምክር ቤቱን አባል እንዴት እንደሚመርጥ [A blue print and a road map for genuine democracy] እነዚህን ሁሉ ለማከናወን የሚወስደው ግዜ ተሰልቶ እንዲስተካከል ማሳሰብ፤ የምርጫው ቦርድ በምን አይነት “ሁኔታ” እንደሚመሰረት፤ ነፃ ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግና ወንጀለኞች ወደ ፍርድ የሚቀርቡበት፣ የተዘረፉትና ወደ አንድ ክልል ቦታ ተወሰደው የተከማቹት የእንዱስትሪ ማምረቻዎች የሚመለሱበት “ሁኔታ” ማመቻቸት፤ በሕገ ወጥ መንገድ ተዘርፈው በውጭ አገር ባንኮች የተቀመጡ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አማካይነት የሚመለሱበትን “ሁኔታ” መወያየት አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሁሉ በቅጡ ተጠንቶ በዚህ ክፍል ላይ ይቀርባል። ግን እዚህ ላይ በጥንቃቄ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያለብን የለውጡን ሂደት ለማሰናከል ወይም ደግሞ በመደመር መልክ እንደገና የለውጡ ደጋፊዎች ነን በማለት ወደስልጣን ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አጥብቀን መከላከል ይኖርብናል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕደግ)ን ጠግነው ቢመለሱ የሚያመጣው የተለመድውን እልቂት እንጂ ለውጥን አይደለም። የ27 ዓመቱ አብዮትዌ ዲሞክራሲ፤ የብሔር ክልል መንግሥት፤ የብሔር ብሔ ረሰቦች እኩልነት ያመጣው አብዮታዌ ግርግርን ነው፤ የክልል ፌደራሊዝም ያመጣው ዘር ማጥፋትን፤ መፈናቀልንና ዝርፌያን ነው፤ ወያኔ አሁን የሚጮኸው በግርግር የሚሰርቀውንና የሚዘርፈውን ሃብት ስለቆመበት ነው። ሊያቀው የሚገባ ነገር ቢኖር ሁለተኛ የማሰር፤ የመግደል፤ ዘር የማጥፋት፤ በሕገ ወጥ መንገድ በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሃብት ወደ ውጭ ማሸሽ ያለመቻሉን ነው፤ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ይጠየቃል፤ [Money Laundering, Illicit funds and Stolen Money , according to US Department of Justice and FBI is illegal; public corruption, no matter where it occurs, is a threat to a fair and competitive global economy. The FBI is committed to working with foreign and domestic partners to identify and return these stolen assets to their legitimate owners]. በቻይና፤ በሲንጋፎር፤ በመካከለኛው ምስራቅ፤ በካናዳ ባንኮች ውስጥ የተቀመጡ ገንዘብና ንብረቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ማስመልሰ ግዲታ ስለሆነ አጥብቀን በስራ እንዲውል ማድረግ ነው። በተጨማሪ ወያኔ ለዉጡን ለማወናበድ ያልሆነ ታሪክ አለ እያለ የሚያወራዉን ፕሮፓጋንዳ ለሕዝብ ማሳወቅ ታሪካዌ ግዲታ ስለሆነ ጎሳ፤ ብሔር፤ የብሔር ብሔረሰብ እኩልነት፤ አብዮታዌ ዲምክራሲ፤ ዲሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነና ታሪካዌ ሂደታቸውን እያመሳከርን እንወያያለን፤ ነገር ግን የምርጫውን ሂደትና ሕገ መንግሥቱን ሕዝብ በየቀበሊው ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ወደ ምርጫ መሂድ ታጥቦ ጭቃ መሆኑን በቅድሚያ ማወቅ ይኖርብናል።
ውይይታችን በመረጃ እየተደገፈ እንዲዳብር በማለት ታሪካዌ ሂደቶችን እየጠቀስን በተረጋጋ መንፈስ ሆነን መወያየት አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ጥንታዌት አገር ነች ስንል ታሪክን ምስክርነት ይዘን ነው። በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያ የተፈጥረችው በምኒልክ ዘመን የዛሬ መቶ ዓመት ነው፤ ከዚያ በፊት “የበርካታ ብሔረ ሰቦች በነፃነት በብሔር ተደራጅተው” የሚኖርበት አካባቢ ነው [አገር እንዳይባል ኢትዮጵያ የሚባል የለም ተብላል] ሲባል አይን ያወጣ የባንዳዎች ፕሮፓጋንዳ ነው። ይህንን በተመለከተ በተረጋጋ መንፈስ ሆነን አጠር ያለ ውይይት እናድርግ።
ጎሳ ማለት ምን ማለት ነው? ስቲቭን ኦፕንሃመር [Stephen Oppenheimer, 2004] የሚባል የኦክስፎርድ ዩነቭርስቲ [Professor of Anthropology at Oxford University] የስነ ፍጥረት መምሕር ስለ ሰው ልጅ “ታሪካዌ” ሂደት ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤
የሰው ልጅ አመጣጡና እድገቱ አስገራሚ ነው። ከሁሉ በላይ እጅግ በጣም ያስገረመኝ ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ከአንድ አፍሪቃዌ እናትና አባት መምጣቱን ያለማወቁን ነው፤ በአንድ ወቅት አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ሆኜ የተገነዘብኩት ነገር ነው። ቺጋጎ አውሮፕላን ጣቢያ ትኪት ማስቆረጫ ላይ የተሰለፉትን ሰዎች ስመለከት አንዱ ከካሪያባን፤ አንዱ ደግሞ ከአውሮፓ፤ ሊላው ደግሞ ከአውስታራሊያ፤ ከኒው ግኔ፤ ከደቡብ አሚሪካ፤ ከሕንድ፤ ከቻይና ለስብሰባ ለመሂደት ትኬታቸውን ለማስቆረጥ በተሰለፉበት ወቅት አይን ለአይን አይተያዩም ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት ከተለያየ ዘር ነን ብለው ስለሚያምኑ መተያየቱን አስፈላጊ ሆኖ ስላ አላገኙት ነው። ነገር ግን እነዚህ ሰባት ሰዎች ከአንድ እናትና አባት የተወለዱ አፍሪቃውያን ናቸው [ Stephen Oppenheimer 2004].
ይህ ማለት እነዚህ ከተለያየ አገር የመጡ ሰዎች ጎሳችው ቢጠና ከአፍሪቃዋ እናትና ከአፍሪቃው አባት ነው። የሰው ልጅ ዘር አንድ ነው፤ እንደ እህል ዘር የተለያየ አይደለም፤ ጢፍንና ማሽላን ቀላቅለህ ብትዘራው የምታገኝው ሰብል “ማሽላና ጢፍን ነው፤ ማሽላው ጢፉን መስሎ አይበቅልም፤ ጢፉም ማሽላን መስሎ አይበቅልም። እንግዲህ “ጎሳ” በታሪክ ውስጥ እጅግ ጎልቶ የሚታየው በአስራ ሁለቱ ነገደ እስራኢላውያን ነው። ይህንን እንመልከት።
ብሔር ምን ማለት ነው? ከላይ ስለጎሳ የተሰጠዉን “ታሪካዌ” ሂደት በትኩረት ብንመለከት “የብሔርን” አመጣጥ ይነግረናል። ሕንድ፤ ቻይና፤ ኒው ግኒ፤ አውስታራሌያ ብሔር ናቸው፤ ማለትም አገር ወይም መንግሥት ማለት ነው። አስራ ሁለቱ የእስራኢል ጎሳዎች ደግሞ አንድ ነገድ ወይም ብሔር ናቸው እንጂ በሔሮች አይደሉም፤ “ብሔር” አይበዛም አንድ ነው። ደግሞ “ብሔረ ሰቦች” ሲባሉ የሚያመለክተው የተለያዩ አገሮችን እንጂ አንድ አገርን አይደለም፤ ለምሳሌ አሜሪካ የተለያዩ “ብሔረ ሰቦች” ያሉበት አገር ስለ ሆነች ሊለያይ የማይችል አንድ “ብሔር” ተብሎ ነው የሚጠራው። ጥንታዌት ኢትዮጵያ ከሰማንያ የሚበልጡ “ጎሳ” ያለባት አንድ “ብሔር” ነች። በረጅም ግዜ ታሪኳ የተለያዩ “ብሔረ ሰቦች “ ሆና አታውቅም፤ ማለትም ከሕንድ፤ ከቻይና፤ ወይም ራሱን ችሎ እንደ አገር ሆኖ የተደራጀ “ብሔረ ሰቦች” አልነበረችም። ዘመነ መሳፍንት “የብሔረ ብሔረሰቦች” አገዛዝ ሳይሆን “የጎሳ” ክፍፍል ነው። ምኒልክ “ጎጃምን” “ወሎን” “በጌምድርን”፤ “ኦሮሞን” “ደቡቡን” ቀጥ ቅጦ ነው አንድ ያደረገው ፤ በተለይም የኦሮሞን ሴት ጡት ቆርጣል የተባለው የባንዳ ልጆች ፕሮፓጋንዳ ነው፤ ሚኒልክ ጠብቶ ያሳደገውን ጡት አልቆረጠም፤ የምኒልክ እናት ወይዘሮ እጅጋየሁ የጫጫው ባላባት የአቦ“ዋቆዮ” የልጅ ልጅ ናቸው፤ የተቆረጠውንም ጡት የሚያሳየው ሐውልት ሕዝብን እርስ በርሱ ለማፋጀት የተደረገ ጥረት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅና ይህንን የጥላቻ መታሰብያ ማፈርስ “ታሪካዌ” ግዴታ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ንጉሠ ነገሥቱ ከአንድ የተለየ ብሔር ሆኖ አያውቅም፤ ቀዳማዌ ኃይለ ሥላሴ ከግማሽ በላይ ኦሮሞ ናቸው፤ ልጅ ኢያሱ የራስ አሊ [ንጉሥ ሚካኢል] የወሎ ኦሮሞ ባላባት ልጅ ናቸው፤ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የገዥው ክፍል ከሁሉም ጎሳ የተሰባሰበ ነው፤ መንግሥቱ ሃይለማርያም ኦሮሞ ነኝ ይላል፤ እንዲት ሆኖ ነው የአማራ ጎሳ ለነበረው “ሁኒታ” ሁሉ ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው? በኢትዮጵያ ታሪክ “የጎሳ” የበላይነት የተጀመረው በወያኔ ዘመነ መንግሥት ነው፤ የሂትለርን ትግል [ My Kempf or My Struggle] አንብቦ በስራ እንዲውል ያደረገው መለስ ዜናዌ ነው፤ የኤርያን ወይም የኖርዲክ ዘር [ Aryan or Nordic race] የሚለዉን የሂትለርን የጀርመን በላይነት ሃሳብ ተክትሎ ነው “እንደ ወርቅ ከጠራው ከትግሬ ሕዝብ መወለዴ ያኮራኛል” ያለው። ግብዝነቱ እንጂ የትግሬ ሕዝብ “ወርቅም” “ብርም” “መዳምም” አይደለም፤ እንደ ሊላው ወንድሞቹና እህቶቹ ሰው ነው፤ የትግሬ ክብርና ሞገሱ ጥንታዌት ኢትዮጵያ ነች፤ ከዚህ ውጭ የትግራይ ብሔር መንግሥት በታሪክ ኖሮም አያቅም፤ ይህንን የትግራይ ምሁራን ለትግራይ ሕዝብ ማሳወቅ ታሪካዌ ግዲታቸው ነው።
ጎሳን በተመለከተ አጠር ያለ ውይይት ያስፈልጋል፤ በተለይ በአማራና በኦሮሞ መካከል ያለው ግንኙነት ልዩ ነው፤ እንደነዚህ ሁለት ጎሳዎች የተደባለቀ የለም፤ በተለይ የሸዋው አማራና ኦሮም ሙሉ በሙሉ መለየት በማይቻልበት “ሁኔታ” ላይ ነው ያለው፤ ሸዋ ውስጥ ያለ ኦሮሞኛ ተናጋሪ አማራ ነው፤ ይህም በግራኝ መሐመድ ወረራ ግዜ የተካሂደ ታሪክ ነው። የአዲስ አበባ ሕዝብ ግማሹ አማርኛ ተናጋሪ ኦሮሞ ነው። ይህ በታሪክ ተደግፎ መጻፍ ይኖርብታል። ያለማወቅ ደፋር ያደርጋል እንደተባለው የወያኔ ካድሪዎች “አማራና ኦሮም እሳትና ጭድ ናቸው” እያሉ የሚያሶሩት ከፋፍሎ ለመግዛት ነው።
አብዮታዌ ዲሞክራሲ ማለት በክፍል ሶወስት ላይ በአጭሩ እንደተጠቀሰውና ሜጀር ጄነራል ባጫ ደበሌ እንዳሉት “የማፍያ ግርግርና የአሸባሪዎች” መዝረፊያ ዘዴ ነው። የአብዮታዌ ዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ተቆንጽሎ ይተወሰደው ከማርክሲዚምና ከሊንንዝም ርዕይተ ዓለም ነው [Marxsim/Leninsm]። የዚህን ጽንሰ ሃሳብ ጥራዝ ነጥቀው “በራሳቻው አመለካከት “ጎሳውን ብሔር” ነው፤ “ብሔሩን ክልል” ነው፤ “ክልሉን መንግሥት” ነው በማለት በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ዝርፊያና ገደብ የሊሽ ሌብነት የተካሂደበት፤ በዓለም ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የሰብአዌ መብት ጥሰት የተካሂደበት “ሁኔታ” ነው። ዝርፊያውና ሌቢነቱ ገደብ የሊሽ ነው። ኢትዮጵያን እርቃነ ስጋዋን አስቀርተው ምንም ነገር የለንም በማለት የካዱበት “ሁኔታ” ነው አሁን ያለው። ይህም ማለት “ያዘው” “ልቀቀው” የሚል “ሁኔታ” ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ፤ አንድ የሕግ ባለሙያ በአደረጉት ጥናት ላይ እንደዘገቡት ያለፉት ሶወስት መንግሥታት ከውጭ ያገኙት እርዳታ የዝርፊያውን ልክ በሚገባ ያሳያል። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በአርባ ዓመታት ውስጥ ከውጭ የተገኝው እርዳታ $ 4.5 ቢሊዮን ዶላር፤ የደርግ መንግሥት በአስራ ሰባት ዓመታት ግዜ ውስጥ ያገኝው $ 5.0 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የወያኔ መንግሥት በ27 ዓመታት ግዜ ውስጥ ከውጭ በእርዳታ $50 ቢሊዮን መሆኑን አሳውቀዋል። ከዚህ ሊላ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም $20 ቢሊዮን ከውጭ ተበድረዋል፤ በድምሩ $70 ቢሊዮን ዶላር የት እንዳለ ሊታወቅ አልቻለም ብለዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መለስ ዜናዌ ያወቀረው “የማፊያው አሸባሪ” መንግሥት ነው።
እንግዲህ በዋነኛነት የሚቀርበው ጥያቄ ከላይ የተጠቀሰዉን የሕዝብ ገንዘብ እንዲት ማስመለስ ይቻላላል? ወንጀሎኞች በምን አይነት ፡ሁኔታ” ፍርድ ሊቀርቡ ይችላል? ነው። ከዚህ በተጨማሬ አሽዋ ስካር ነው ተብሎ፤ የአገር መሬት በጅምላ ተሸጦ፤ የግል አየር መንገድ በግለሰብ ተደራጅቶ፤ የኢትዮጵያ መርክብ ኃይል በግለ ሰብ ተገዝቶ፤ አትራፊ የተባሉትን የመንግሥት ድርጅቶችን እንደ አየር መንገድ፤ መብራት ኃይል፤ ቴሊኮሙኒኬሽን ወደ ግል ንብረት እንዲዛወሩ ተመቻችቶ፤ የትግራይ ሕዝብ መረዳጃ፤ የሜቴክ ድርጅት፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አውታር በወያኔ ስር አድርጎ፤ በአገሩ ውስጥ አሉ የተባሉትን እንዱስትሪዎች በአጠቃላይ ወደ ትግራይ ክልል ተካቶ፤ በዓለም ላይ ታይቶና ተሰርቶ የሚያውቅ ስብአዌ መብት ተጥሶ፤ የሰውን ልጅ እራቁቱን ከአሪዌት ጋር እጫካ ውስጥ እንዲያድር ተደርጎ፤ የሰው ልጅ ከነነፍሱ መቃብር እንዲገባ ሆኖ፤ የአካሉ ቆዳ እንዲበጣጠስ ፤ የወንዱ ልጅ ብልት ተኮላሽቶ፤ ሴታን መካን አድርጎ፤ በቂም በቀል ዘር ጠፍቶ በአለበት “ሁኔታ” ለውጥን ማምጣት ያለበት ሕዝብ እንጂ እነዚህን ሁሉ አሰቃቂ ወንጀል የሰራ ኢሕደግ አይደለም። ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገቡት ቃል “በሁለት ዓመት ውስጥ በምርጫ ማስረከብ ነው እንጂ ኢሕደግን መልሶ ስልጣን ለማውጣት አይደለም። አሁን ያለው የለውጥ ሂደት የተገኝው በሕዝብ ታላቅ መስዋዕትነት ነው፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይቻኮል በተረጋጋ መንፈስ ሆኖ ከጠቅላይ ሚንስተሩ ጋር በተዋዋለው መሰረት “መንግሥት በሕዝብ ለሕዝብ” ብሎ በዲሞክራሲ ተወያይቶ አዲሲታን ኢትዮጵያን ይመሰርታል። ስለዚህ ከዚህ የሚከተሉትን መርሃ ግብር በቅደም ተከትል በስራ ላይ ማዋል ታሪካዊ ግዲታ ነው።
- ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው? እንዲትስ በስራ ላይ ሊውል ቻለ? በዚህ መርሃ ግብር ላይ በየቀቢለው ሰፋ ያለ ውይይት ያስፈልጋል። ለውይይቱ እንዲረዳ በማለት የአሚሪካንን ሕገ መንግሥትና ዲሞክርሲ በሶወስተኛው ክፍል ላይ ያለውን ይመልከቱ።
ለተከብሩ ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አቢይ አህመድ በተላከው ግልጽ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው [የተላከዉን ደብዳቤ ይመልከቱ] ለለውጡ በመጀመሪያ ደረጃ አስፈላጊ ናቸው ከተባሉት ውስጥ ሕገ መንግሥትና የሕግ በላይነት ነው። ይህንን በተመለከተ የሕግ አርቃቂ ኮሚሽነር በአስቸካይ እንዲሰየም ነበር። እስከአሁን ድረስ የተወሰደ እርምጃ የለም፤ ስለዚህ አስችካይ እርምጃ መወሰድ አስፈላጊ ነው። የሕግ ባለማዮዎች ሕገ መንግሥቱን ከአረቀቁ በሕዝብ ይጸድቃል። ይህ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምርጫ ቦርድ መምሪያ እስኪመጣ ድረስ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መውያየቱ ጠቃሚ ነው።
- ነጻ የሆነ የምርጫ ቦርድ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወይዘሮ ብርቱካን መደቅሳን ለምርጫ ቦርድ በሊቀ መንበርነት መምረጣቸው ትልቅ እርምጃ ነው። ሆኖም ነጻ ፍርድ ቢት ሳይኖር የሕግ በላይነት ሳይከበር ወይዘሮ ብርቱካን በተአምር የሚሰሩት ነገር አይኖርም፤ እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበትና ለውጥን ማየት ያለብን ከአስተሳሰባችንና ከባሕላችን ጋር ነው፤ ለውጥ በግለሰብ በጎ ፈቃድ የሚስጥና የሚመጣ ነገር አይደለም። የወይዘሮ ብርቱካን መደቅሳና የዶር አቢይ አህመድ በጎ አስተሳሰብ ቀና ነው፤ ግን እላይ እንደተጠቀሰው በዓለም ታሪክ ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ በግለሰብ ስጦታ አልመጣም፤ ሊመጣም አይችልም፤ ዲሞክራሲ የሚዋቀረው በስምምነት ነው። ለውጥ የየግለሰቡን አስተሳሰብና የፍላጎቱን ገደብ ሕግን ተቀብሎ መገደብ ይኖርበታል፤ የሕግ በላይነት ለምርጫ “ቅድመ ሁኒታ” ነው። ይህ ከአልሆነ ውጢቱ ያው የምናውቀው ነው፤ቢደመረም ቢቀነስም የሚያመጣው ለውጥ የለም።
- የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢበዛ ከሶወስት መብለጥ የለበትም፤ በአሁኑ ግዚ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊያካቱቱ የሚችል የሴቶች ድርጅቶች ነው፤ አንደኛ በድርጅት ደረጃ የኢትዮጵያ ሴቶች፤ የተከበሩ ወይዘሪት ብርቱካን መደቅሳ እናድሉት፤ “የነፃነት ሀውልት ነች” ስለዚህ የኢትዮጵያን ልዑላዌነትና ሰላም የማስጠበቅ የተለየ ችሎታ ስለአላቸው በማሕበር ተደራጅተው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ፓርቲዎች መምሪያ እየሰጡ ተመራጮችን ከሕዝብ ጋር ያዋያያሉ፤ “የኢትዮጵያ ሴቶች መልካም አስተዳደር፤ ሰብአዌ መብት፤ አንድነትና ሰላም ድርጅት” [Ethiopian League of Women for Democracy, Huaman Rights, Peace and Unity]
ተብሎ ቢሰየም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያስተባብሩና በአገር ውስጥ ሰላም ሊያመጡ ይችላሉ፤ እንደ ኢትዮጵያ እናቶች በኢሕደግ መንግሥት ያለቀስና የተሰቃየ የለም፤ ልጆቻቸው በጅምላ ተገድለዋል፤ ልጃ ሬሳ ላይ እንድትቀመጥ ተገዳለች፤ መካን እንዲሆኑ ተገድዋል፤ አባቶቻቸው፤ ባሎቻቸው ታስረዋል፤ ተገድለዋል፤ ከሴቶች ሊላ የኢትዮጵያን ሰላምና የሰውን ልጅ ሰብአዌ መብት የሚያስጠብቅ ሊላ ሰው አይኖርም፤ የኢትዮጵያን አንድነትና ነፃነት ያስክብራሉ፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተምስሊት ይሆናሉ።
- በፖለቲካ ፓርቲ ደረጃ አንደኛ፡ የወጣቱ ትውልድ [በመከራ ተፈትኖ የተወለደው መልካሙ ትውልድ] “የኢትዮጵያ ወጣቶች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ”[Ethiopian Youth Democratic Party] ተብሎ ሊጠራ ይችላል፤ አዲሱ ትውልድ ያሳለፈው መከራና ስቃይ ከፍተኛ ስለሆነ የአንድነትንና የሰላም አስፈላጊነት ጠንቅቆ ያውቃል፤ ሰብአዌ መብትንም ያከብራል፤ እሱ እንደተዋረደው ማንም እንዲዋረድ አይፈልግም። በዚህ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የወጣቱን የኢኮኖሚና ማሕብረሰባዊ ፍላጎት እንዲማላ እሰራለሁ የሚል ሁሉ አባል ሆኖ ለምርጫ መቅረብ ይሽላል።
- ሁለተኛ “የኢትዮጵያ ገበሪዎች አንድነት ፓርቲ”[Ethiopian Union Farmers Party] የገበሪውን ጥቅምና መበት አስከብራለሁ የሚል ገበሪዉን ወክሎ መመረጥ ይችላል [በኢትዮጵያ ታሪክ እንደገበሬው የተበደለ ክፍል የለም፤ ነፃ አውጭዎች ነን የሚሉ ሁሉ የገበሬውን ፖለቲካ መቀላቀል ግዲታ ነው]።
- ሶስተኛ “የኢትዮጵያ የተባበሩት ሰራተኞች ፖለቲካ ፓርቲ”[ Ethiopian United Labor Party] የሰራተኛዉን መብትና ጥቅሙን አስጠብቃለሁ የሚል አባል በመሆን መመረጥ ይችላል። የእነዚህ ሶወስት የፖለቲካ ድርጅቶች [ፓርቲዎች] ፍላጎት በሚገባ ተተንትኖ መጻፍ ይኖርበታል [party platform]፤ አሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች ነን የሚሉ ሁሉ በእነዚህ ክፍል ተካተው በአገር ደረጃ መንቀሳቀስ ይችላሉ፤ ከሶወስት አንዱን መርጠው ፕሮግራማቸዉን አስተካክለው የአገሩን የመኖሪያ ሕግ ተቀብለው መመረጥም መምረጥም የሚችሉበትን መንገድ ሊያስተከክሉ ይገባችዋል። ይህንን በተመለከተ የምርጫ ቦርድ ሰፋ ያለ መግለጫ ማዘጋጀት አለበት፤ ተወዳዳሪዎች ለሶወስቱም የመንግሥት ክፍል ሊወዳደሩ ይችላሉ፤ ይኸውም “የሕዝብ መምሪያ ምክር ቢት”፤ “የሕዝብ መወሰኛ ምክር ቢት” እና “የአገሩን መሪ” [ፕሪዚዳንት] ይሆናል። ለፕሪዚዳንነት ሁለት ከፍተኛ ድምጽ ያመጡ ተወዳዳሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ለምርጫ ይቀርባሉ። ለዚህ ሁሉ የምርጫው ቦርድ በዝርዝር መምሪያ ማዘጋጀት ይኖርበታል። በሕገ መንግሥቱ በዝርዝር ስለተመራጮና ስራና የስራ ግዲታ ይደነገጋል።
- በሕገ መንግሥቱ በጎሳና በሃይማኖት መደራጀት ክልክል መሆን ይኖርበታል።
- አሁን ያለው የክልል መንግሥት እንዲት እንደሚካለል ሕዝብ ተውያዮቶ መወሰን ይኖርበታል፤ በጎሳና በሃይማኖት የኢትዮጵያ መሪት እንዳይካለል በሕዝብ ውይይት ተወስኖ በሕገ መንግሥቱ የክልል መንግሥት ክልክል መሆን አለበት።
- የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሚሪካንን ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ በትኩረት ተመልክቶ በስራ ላይ የሚውልበትን ዘዴ መመካከር አስፈላጊ ነው፤ ከእንግሊዝ የተወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትር አመራር ለኢትዮጵያ አይሰራም፤ በሕዝብ የሚመመረጥ የሕዝብ ምክር ቢት፤ የፍርድ ቢት፤ በፕሪዝዳንት የሚመራ አመራር ለኢትዮጵያ መልካም አስተዳደር ሊያመጣ ይችላል። ይህንን በተመለከት ሰፋ ያለ ውይይት ያስፈልጋል።
- ለተመራጮች የግዚ ገደብ ማድረግ፤ ግዲታቸውንና ኃላፊነታቸውን በሕገ መንግሥቱ ማካተት ያስፈልጋል።
- በሶወስት ክፍል የተጠቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአካባቢው ሕዝብ አቅርቦ ማስተዋወቅና መወያየት፤ ሕዝብ ጥቅሚንና እነኒትን ያስክብራል የሚልዉን ድርጅት እንዲመርጥ መብቱን ማሳወቅ፤ ይህንን ድርጅት ወክለው ለመመረጥ የሚያስችላቸዉን ሕግ ማውጣት፤ በሚመረጡበት አካባቢ የንዋሪነት ዘመን መተመን። የእድሚና የስነ ምግባር መስፈረት በግልጽ ማስቀመጥ።
- የቀብሊያቸውን አስመራጭ ኮሚቲ ደንብና ስርዓት በግልጽ ማሳወቅ።
- የውጭና የአካባቢውን የምርጫ ታዛቢዎች ደንብና ስርዓት በግልጽ ማሳወቅ።
- በሕገ መንግሥቱ መሰረት የምርጫውን ቀን፤ ግዜና ስዓት በግልጽ ለሕዝብ ማሳወቅ።
- የምርጫ ምዝገባዉን ቀን፤ጊዜ ና ስዓት በግልጽ ማሳወቅ።
- ምርጫ በሚካሂድበት ግዜ መራጮች ተረጋግተው እንዲመርጡና ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ።
- በምርጫ ቀን ተመራጮች ምረጡኝ የሚል ምንም አይነት መልክት በየትኛውም ቦታ ማደረግ እንደማይችሉ ሕጉንና ስርዓቱን ለሁሉም ወገን ማሳወቅ።
- የቀበሊው አስመራጭ ኮሚቲ ሕዝቡን በነፃ ሆኖ የመምረጥ መብቱን ማስተማር።
- በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምርጫው እንደተከናወነ ለበላይ አካል ለሆነው ለብሕራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቅ።
- ምርጫው ከመደረጉ በፊት ብዙ “ቅድመ ሁኒታዎች” ያስፈሉጉታል፤ ነፃ የምርጫ ቦርድ፤ ነፃ ፍርድ ቢት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ የጸደቀ ሕገ መንግሥት፤ እነዚህን “ሁኒታዎች” ለመፈጠር ብዙ ግዜ ይጠይቃል፤ በተባለው ሁለት ዓመት ውስጥ ሊከናወን ስለማይችል ኢሕደግ በሰጠው ሁለት ዓመት ላይ 3 ዓመት ጨምሮ “ቅድመ ሁኒታዎችን” ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው። ሕዝብ ይህንን ጉዳይ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተነጋግሮ ጊዚውን ማረዘሙ ግዲታ ነው።
- እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚመጣው መምርያ በተጨማሪ እንዲረዳ ተብሎ ነው። የአስተዳደር ክፍሉ ከማዕከላዊ መንግሥት የተለየ ቀብሊዉን የሚያስተዳድርበት ሕግ መኖር አለበት፤ ለምሳሌ የቀበሊው ናሪ ለምክር ቢት አባልነት መወዳደር ቢፈልግ የቀበሊዉን ሕግ ማማላት ይኖርበታል፤ በስነ ምግባር ብቁነት፤ ቢያንስ ሰባት ዓመት[?] በቀበሊው የኖረ ሲሆን ሊላ የሰብአዊ መብቱ የማይጣስና በማዕከላዊ መንግሥት የተጠበቀ ይሆናል።
ይህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ሕዝብ በየአውራጃው፤ በየወረዳው፤ በየምስሊነው፤ በየቀቢለው መወያየት ያስፈልጋል፤ ይህንን ውይይት ለማካሂድ ሕዝቡ የማንንም ፈቃድ አያስፈልገውም፤ መግሥትን በሕዝብ ለሕዝብ የሚመሰርተው ሕዝብ ነው፤ የአገሩን ሕግ የሚደነግገው የሕዝብ ተወካይ ነው፤ ዲሞክሪሲን የሚመሰርተው ሕዝብ ነው፤ ለምሳሌ የአሚሪካ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያው ምዕራፍ የሚለውን እንመልከት፤ “የሕገ መንግሥቱን ሕግ የማውጣት ስልጣን ያለው ሕዝብ የመረጠው የምክር ቢቱ አባል ብቻ ነው” ይላል። ይህም ማለት መንግሥት የሚመሰረተው በሕዝብ ነው፤ ሕግ የሚወጣው በሕዝብ ነው። በሕግ በላይነት ወይም በሕዝብ በላይነት ዲሞክራሲ ይጠበቃል። ሕዝብን በማሰር፤ በመግደል፤ ከሚኖረበት በማፈናቀል፤ ዘር በማጥፋት፤ሃብት በመዝረፍ፤ 70 ቢሎዮን ዶላር ከአገር በማሽሽ ዲሞክራሲ አይመሰረትም። የወያኔ ዲሞክራሲ መስረቅና መዝረፍ ነው። ይህንን ለማስቆም መንግሥት በሕዝብ ለሕዝብ ብለህ ቆርጠህ መነሳት አለብህ፤ ከአንተ ሊላ ማንም ዲሞክራሲ ሊያመጣልህ አይችልም። ማንንም ማምለክ አይኖርብህም፤ አንድ ሰውን ማምለክን ስትጀምር መታሳር፤ መገደል፤ መፈናቀል፤ መናቅ፤ መሰደድ አብሮ ይጀመራል። ሕግን በባላይነት ስታይ፤ የወግንክን ስብአዊ መብት ስታከብር፤ ስታስከብር በነፃ መንፈስ ትሞላለህ፤ አገርህ ፍትህና የሚያልቅ ሰላም፤ ብልጽግና፤ ማርና ወተት እንደ ውሀ የሚፈስባት አገር ትፈጥራለህ፤ አይዞህ እንደምንም ብልህ ተነሳ፤ ሊላ ሰው እንዲያነሳህ አትተጠብቅ።
ክፍል አራትን ለማጠናቀቅ ያህል ስለ ጎሳ አጠር ያለ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፤ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ የአንድ ጎሳ በላይነት በዚህ አይነት “ሁኒታ” ተደርጎ አይታወቅም፤ ጎሳዎችን በብሔር ከልሎ ራሱን በፌደራል አስተዳደር ስም ሰይሞ የጎሳዎች አስተዳዳሪ በመሆን በዓለም ታሪክ ውስጥ ተፈጽሞ የማያውቅ ውንጅልና የፈጽመ ከሰው ያልተፈጠረ ይመስል በሰው ልጅ ይህ ነው ሊባል የማይችል ውንጅልና ፈጽማል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ወንጀል በአገራችን ላይ ሁለትኛ እንዳይፈጸም መፋረድ ታሪካዊ ግዲታው ነው፤ ይህ በይቅርታ ሊታለፍ አይገባውም፤ የተዘረፈዉን ገንዘብ፤ ንብረት፤ የተነጠቀውን የከተማ መሪቶች፤ ተዘርፈው የተወሰዱትን የእንድስትሪ ሃብቶች፤ በፍርድ ቢት ወደ ባለቤቱ እንዲመለስ ማደርግ፤ በሕዝብ ገንዘብ የተከማቸውን የትግራይ ልማት ድርጅትን $12 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን ሃብት ወደ መንግሥት እንዲገባ ማድረግ፤ ከዲያስፖራው ጋር በመተባበር እውጭ የተቀመጠውን ገንዘብ፤ በንብረትነት በተላያዩ ግለሰቦች የተያዙ ቤቶች፤ የንግድ አቃማት፤ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ማስመለስ፤ የሕዝብ መንግሥት ሳይመረጥ ምንም ዓይነት የሕዝብ ኢኮኖሚክ ተቃማዋት ወደ ግል ንብረትነት እንዳይዘዋወር ሕዝብ ማደረግ አለበት:: በመጨረሻም ወያኔ በጅምላ በማንነታቸው ለተገደሉት፤ አካለ ጎዶሎ ለተድረጉት፤ በያለበት ቦታ ለተፈናቀሉት፤ ማይካድራ ላይ ለተጨፈጨፉት፤ በአረመኔዎች ለትገደሉት ለኢትዮጵያ መከላካያ ሰሪዊት ካሳ $2.5 ቲሪሊዮን ዶላር ለቤተሰቦቻቸው እንዲከፈል ማድረግ ፍትሐዊ መፍትሄ ነው። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በክብር ትኑር።
Reference:
- Magna Carta, 1215
- English Bill of Rights
- Declaration Indepdence
- The United States Constituion
- Sirak Hiruy H. Sllasie: Rase Las: The Prince of Abysinia
- Philosophers who influenced the writing of the American Connstitution:
- Jean-Jacques Rousseau [1712-1778].
- Thomas Hobes [1588-1679]
- John Lock [1632 -1704]
- Voltaire [1694-1778]
- Montesquieu [1689-1755]
- Zer’a Ya’qob [see the Nile Valley civilization፡ A Historiographical Commentary on Ancient Africa,
- Stephen Oppenheimer [see the Nile Valley Civilization………….]
- Amo West African Philosopher [see the Nile Valley Civilization
- The Origin of the Script see Chapter 4 [The Nile Valley Civilization]