በኦሮምያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ኅዳር በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ በተፈፀመው ጥቃትና ግድያ ውስጥ “የፀጥታ ኃይሎች እጅ አለበት” የሚያስብል በቂ መሠረት አለ ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።
አዲስ አበባ — የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኦሮምያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት አርዳ ጅላ ላይ ኅዳር 22 / 2014 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት የሕይወትና የአካል ጉዳት ስለመድረሱ ጥቆማ እንደደረሰው አትቶ ከታኅሣሥ 7 እስከ ታኅሣሥ 12 / 2014 ዓ.ም. ቦታው ላይ መገኘቱን፣ ተጎጂዎችን፣ የዐይን እማኞችን፣ የሟች ቤተሰቦችንና የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት አነጋግሮ ምርመራ ማካሄዱን ገልጿል።
ኅዳር 21 / 2014 ዓ.ም. ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ወደ ተለያዩ ቀበሌዎች ለሥራ ወጥተው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አካባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ በነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ኢፍቱ በሚባል ቦታ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት አሥራ አንድ የፖሊስ አባላት መገደላቸውና ቢያንስ ሌሎች 17 የፖሊስ አባላት መቁሳለቸው መታወቁን የኮሚሽኑ መግለጫ አመልክቷል።
ይህንን ተከትሎ በማግሥቱ ኅዳር 22 / 2014 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሠፈር የደረሱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የዐይን እማኞች ማስረዳታቸውን መግለጫው ገልጿል።
ኮሚሽኑ ዛሬ፤ ጥር 25 / 2014 ዓ.ም. ያወጣው ይህ ሪፖርት በፀጥታ አባላቱ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል አሥራ ስድስቱ ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ መወሰዳቸውንና አሥራ አራቱ በጥይት ተመተው ስለተገደሉበት ሁኔታ ይናገራል።
የከረዩ አባ ገዳ ከዲር ሃዋስን ጨምሮ አሥራ አራቱ የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተመተው መገደላቸውንና ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ ጫካ ሮጠው ማምለጣቸውን ምስክሮች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱ ጠቁሟል።
አስከሬኖቹን ለማንሳት ግድያው ወደ ተፈፀመበት ቦታ የሄዱ ሰዎች በቦታው በነበሩ ፖሊሶች እንዳያነሱ በመከልከላቸው አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ መቆየታቸውንና የፈነዳዱና በከፊል በአራዊት የተበሉ ጭምር እንደነበሩ አስከሬኖቹን ያነሱና የቀበሩ ሰዎች መግለፃቸውን፤ እንዲሁም አስከሬኖቹ ከጀርባ በኩል ወገባቸውና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች የነበሩባቸው መሆኑን እንዳስረዱ ያብራራል።
በዕለቱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱት ሰላሣ ዘጠኝ የጅላ አባላት መካከል ሃያ ሦስቱ ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሁለት ሣምንታት በኋላ ጅሎ ቦረዩ የተባለ የጅላ አባል አስክሬን ሞጆ ከሚገኝ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ሠፈር ለቤተሰብ መሰጠቱን፤ ጭንቅላቱ ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስልና የድብደባ ምልክቶች እንደነበሩ አስክሬኑን የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት ለኮሚሽኑ መግለፃቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት አመልክቷል። አሥር ላይ የነበሩ የጅላ አባላት ከሣምንታት መለቀቃቸውንም አመልክቷል።
ኢሰመኮ በምርመራው ወቅት በሰበሰባቸውና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ኅዳር 22 / 2014 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ እንደተወሰዱ በመግለፅ የፀጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት የተገደሉ መሆኑንና ይህም ከሕግ አግባብ ውጭ የተፈፀመ ግድያ ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ እንዳገኘው አስታውቋል።
በኃይል ከተወሰዱት ሃያ ሦስት የጅላ አባላት መካከል አንድ ሰው ሞጆ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የኦሮምያ ልዩ ኃይል ሠፈር ውስጥ በቁጥጥር ሥር እያለ መሞቱንና ቤተሰቦቹ ያለምንም ምርመራ አስክሬኑን እንዲወስዱ መደረጋቸውን፣ አስከሬኑ እንዲቀበር መደረጉ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ከሕግ ውጭ የተፈፀመ ግድያ መኖሩን በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ማግኘቱን ኢሰመኮ ገልጿል።
“በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን ግድያ የፈፀሙና ያስፈፀሙ፤ የፖሊስ አባላቱን የገደሉና የአካል ጉዳት ያደረሱ ሰዎችን የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አስታውሰዋል” ብሏል።
ኮሚሽነሩ ስለጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለፅ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሠረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት እንዲመለስ ማድረግ እንደሚጠበቅ ማሳሰባቸውንም መግለጫው አመልክቷል።
ይህ ሁኔታ በተፈጠረ ሰሞን የአሜሪካ ድምፅ ባቀረበው ሪፖርት ላይ እማኝ ነን ያሉት ሰዎች ግድያው የተፈፀመበትን ሁኔታ ማስረዳታቸውንና የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር ኮምዩኒኬሽንስ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አንበሱ “አባ ገዳ ከዲር ሃዋስን የገደሉት የመንግሥት የፀጥታ አባላት ናቸው” መባሉን ማስተባበላቸው ተዘግቧል። ለግድያዎቹ ተጠያቂው ኦነግ ሽኔ ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂዎች መሆናቸውንም አመልክተው ነበር።
እራሳቸውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከሚሉት ታጣቂዎች ያኔም ሆነ ከዚያ በኋላ ምላሽ ያልተሰማ ሲሆን የዛሬው የኢሰመኮ ሪፖርት ከወጣ በኋላም የኮሚሽኑንና የኦሮምያን ባለሥልጣናት ለተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረናቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ። – VOA