መስኩና ተራራው ወንዙም እንደሚያውቀው፣
በግ እየነጠለ ቀበሮ እሚበላው፣
ልግመኛና ሰነፍ ሲሆን ነው እረኛው፡፡
እረኞች ታታሪ በሆኑበት ዘመን፣
እንኳን በጋቸውን የሚጠብቁትን፣
ተሞት አትርፈዋል አሳማ ውሻውን!
ሰላሳ ዓመት ወዲህ ቀኖናው ተሽሮ፣
ቀበሮው ተኩላው እረኛ ተቀጥሮ፣
በጎችን አስፈጀ ለአውሬ በሩን ከፍቶ፡፡
እንኳንስ ለማየት ለመስማት ከባድ ነው፣
ጠቦት ለቀበሮ ገብሮ ያስበላው፣
ተዝካር ፍታት ብሎ ይዝቃል እረኛው፡፡
የተቀቡ እረኞች እግዜር የላካቸው፣
ቀበሮን ተጋፍጠው ተበግ በፊት አልቀው፣
ጠቦት የሚገብር አውደልዳይ ተካቸው፡፡
እረኛ አሰልጣኙ ማር ይስሐቅ የበቃው፣
ብሎ እንዳልነገራቸው መከራ ፀጋ ነው፣
በጎቹን አስፈጁ ተዓለም ፉንቃ ይዘው፡፡
በዚህ በጉድ ዓለም በተመሳቀለው፣
በጉ ተአውሬ ገጥሞ እረኛን ጠበቀው፡፡
እረኛው ልግመኛ ጅል መሆኑን አይተው፣
ሰልለው ሰልለው አጥርህን ነቅንቀው፣
በተራ በተራ እየጨረሱህ ነው፡፡
ሳጥናኤል ዳግመኛ መላክ እንደማይሆን፣
ቀበሮም በምልጃ አይተው በግ መብላትን፡፡
ስለዚህ በጉ ሆይ ይኸን ተገንዝበህ፣
ቀበሮው የጅብ አፍ እንዳለው ተረድተህ፣
ራስህን ወደ አንበሳ ወደ ነብር ቀይረህ፣
እንደ ድር አብረህ እንደ ተርብ ተናድፈህ፣
ሰይጣን የላከውን እንድትመልስ ይርዳህ፡፡
በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
ጥር ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.