January 22, 2022
58 mins read

በችግሮች የተሞላውን የነስብሃት ነጋ አፈታት በተመለከተ፣ ክፍል 1 ከሰይጣን ጋር እስክስታ/ዳንስ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

ሰሞኑን የነስብሃት ነጋን መፈታት አስመልክቶ ውሳኔው ተገቢ አለመሆኑን አስተያየቴን በአደባባይ ገልጫለሁ። ተገቢ አይደለም ያልኩበት ምክንያት ግን እንደብዙሃኑ በስሜትና በቁጭት ላይ ብቻ የተመሰረተ አልነበረም። በቁጭትና በስሜት የተቃወሙትም በቂ ምክንያት እንዳላቸው እነስብሃትን ፈቶ የለቀቀው መንግስት ሊያውቅላቸው ይገባል።

Sibhat Negaሰለ እነስብሃት እንነጋገር ከተባለ፣ እኩይነት ስጋና አጥንት ተላብሶ በሃገራችን ምድር የተከሰተው በስብሃት ነጋ መሆኑን አውቃለሁ። ከወያኔ ወደ ትግራይ ህዝብ እንዲስፋፋ የተደረገው ጸረ አማራ እና ጸረ ኢትዮጵያ አመለካከት ዋናው አራማጅ ስብሃት ነጋ ነው። በአማራ ህዝብ ላይ ሂሳብ ማወራረድ የሚለውና የአማራን ህዝብ የዘር ማጥፋት ጥቃት ሰለባ ሲያደርገው የኖረው የወያኔ እቅድ የስብሃት ነጋ ነው። የትግራይ ወራሪ ሃይል በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸማቸው የግፍና የሰቆቃ አይነቶች በስብሃት የታሰበባቸው ናቸው።

በአንድ ወቅት “እንዴት የአማራን ህዝብ እንደህዝብ ትጠላለህ በሁሉም ብሄር ውስጥ መጥፎም ጥሩም ሰዎች ይኖራሉ” ለሚለው የጓደኛው አስተያየት ስብሃት የሰጠው ምላሽ “የአማራ ጥሩ የለውም። ጥሩ አማራ የሞተ አማራ ብቻ ነው የሚል” ነበር። አማራን መግደል፣ መቀጥቀጥ፣ መዝረፍ፣ ሴቶቹን በመድፈር፣ ማዋረድ በጥቃት መሳሪያነት ታስቦባቸው የትግራይ ወራሪ ሃይል ስልጠና የወሰደባቸውና ተግባራዊ ያደረጋቸው ጉዳዮች እንዲሆኑ ያደረገው ስብሃት ለመሆኑ ልንጠራጠር አይገባም። ከትግራይ አልፎ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በአማራው ላይ በጽንፈኛ ብሄረተኞች የሚወሰዱ አሰቃቂ ግድያዎች፣ ዘረፋዎችና መፈናቀሎች መነሻው በወያኔ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲስፋፋ የተደረገው የስብሃት ነጋ የአማራና የኢትዮጵያ ጥላቻ ነው።

ከአማራው አልፈን በአፋር ህዝብ ላይ የቆየው የወያኔ ጥላቻ ምንጩ የስብሃት ነጋና የቡችሎቹ የነመለስ ዜናዊ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ነው። የአፋሮች “እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ያውቁታል” የሚለው አባባላቸው እነዚህን ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ሁሌም ሲያሳምም የኖረ እንደሆነ አውቃለሁ። ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥዎች ለመከላከል አፋሮች የራሳቸው የታሪክና የጀግንነት አሻራ ያሳረፉ፤ በዚህም የሚኮሩና በኢትዮጵያ ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸው የወያኔን ጥላቻ እንዲያተርፉ አድርጓቸዋል።

በቅርቡም በአሸባሪው የወያኔ ወረራ በከፍተኛ ጭካኔ እንዲጨፈጨፉ፣ እንዲዘረፉና በእምነታቸው ላይ ሳይቀር ነውር እንዲፈጸምባቸው ያደረጋቸው፤ ይህ የኢትዮጵያዊነት ኩራታቸው ነው። ስለዚህ እንዲህ አይነቱ በቀጥታ በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ለተከሰተው ከፍተኛ የሰው እልቂት፣ የንብረት ውድመት፣ የስብእና ውርደት ተጠያቂ የሆነ ሰው ለማናችንም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በነጻ ከእስር ሲለቀቅ ኢትዮጵያውያን ቢናደዱና ቢቆጩ የሚገርም አይሆንም። “ስብሃት ነጋ በተንቤን ዋሻ በመከላከያ በተያዘበት ወቅት በሲቪል ሆነ በወታደራዊ አመራር ስልጣን አልነበረውም።

ስለዚህ በህግ ፊት ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም” የሚለው አባባል አጥጋቢ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በነጻነት የሚታዩበት የፍትህ ስርአት ያለ አድርጎ የሚያቀርብ ስለሆነ አስቂኝም ጭምር ነው። የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የምደግፈው ወደ ተስተካከለ የፍትህ ስርአት ሊወስደን ይችል እንደሆነ ተስፋ በማድረግ እንጂ ነጻና ገለልተኛ የፍትህ ስርአት ተገንብቷል ብዬ ስለማምን አይደለም። ማንም ኢትዮጵያዊ አያምንም።

በበኩሌ በነስብሃት መፈታት ተቃውሞየን ያቀረብኩት ከዚህ በላይ ከጠቀስኳቸው ከወገኖቼ ጋር በምጋራው የቁጭትና የንዴት ስሜት አይደለም። በቀል ፈላጊ ስለሆንኩም አይደለም። የኔ አይነት ሰው በመወያየት፣ በሰላምና በእርቅ ችግሮችን መፍታት የተማረው በአካዳሚ ተቋማት ወይም ቂም በሆዳቸው ይዘው ስለይቅርታ ከሚሰብኩ የእምነት ሰዎች አይደለም። መወያየት ባለመቻላችን፣ ለስላምና ለእርቅ ቦታ ባለመስጠታችን በሽዎች የሚቆጠሩ ውድና ብርቅ የሃገሪቱን ልጆች ህይወት ገብረን፤ አያቶቻችንን፣ አባቶቻችንን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በጅምላ መቃብር እንዲቀበሩና በሚሊዮኖች እንዲሰደዱ አድርገን ኢትዮጵያን ዛሬ ላለችበት የአካልና የመንፈስ ምስቅልቅል በመዳረጋችን ተሸክመነው ከምንኖረው ዘመን የማይሽረው ቁስላችን ነው።

በመሆኑም ውሳኔውን የተቃወምኩት ቂም ሳልቋጥር፣ በቀልን ሳልናፍቅ፣ ቁጭትና ስሜቴን ወደ ጎን አስቀምጬ እንደበረዶ በቀዘቀዘ የተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሁኜ ነው። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ብቻ አንስቼ ነው። ያነሳሁት “የእነዚህ እርኩስ ወንጀለኞች መፈታት ለህዝብና ለሃገር ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል” የሚል ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ መስሎ ቢታየኝ የመንግስትን ጥረት በሙሉ ከልቤ ከመደገፍ ወደኋላ አልልም ነበር። ይህ አይነቱ ባህልና ስብእና እንዳለኝ የተቃወምኳቸው ብቻ ሳይሆኑ የወያኔ መሪዎችም ጭምር ያውቁታል። ውሳኔው ትክክል አይደለም ያልኩት ከሃገራዊና ህዝባዊ ጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ ጎልቶ ስለታየኝ ነው።

sibhat nega

እስካሁን ድረስ መንግስት ለምን እነስብሃት ነጋን እንደፈታቸው የሰጣቸው ምክንያቶች እርስበርሳቸው የሚጣረሱ፣ ማንንም ማሳመን ያልቻሉ ናቸው። “ለሰላም ሲባል ነው፤ ፍርድ ቤቱ የጀመረውን ክስ ቢቀጥል ማስረጃ ሊያቀርብባቸው የማይችል ጉዳይ ስለሆነ ነው፤ ሰዎቹ በእድሜ የገፉ በሽተኞች በመሆናቸው እስር ቤት ከሚሞቱና የበለጠ የበቀል አዙሪት ከሚጦዝ ቢለቀቁ ጉዳት አያመጣም ብለን ነው፤ ለብሄራዊ ውይይትና እርቅ መጀመር አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡” የሚሉ ምክንያቶች በተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ተሰጥተውናል። የበለጠ ግራ መጋባትን እንጂ ሰዎቹን መንግስት ለምን እንደፈታ የተጨበጠ ነገር አላገኘንም።

ከፍችው ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍችው ሃሳብ ለእኛም አስደንጋጭ ነበር ማለቱ የበለጠ ግራ አጋብቶን ነበር። ከዛ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዳያስፖራ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ያደረገው ንግግር ከተጋባዦቹ ብዙ ጭብጨባ ቢለገሰውም የሃገሪቱን ፖለቲካ ከምር ለምንከታተለው ስዎች ከሁሉም ንግግሮች በባሰ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ያሳየ ሆኖ አግኝተነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛን አስደንግጧል በሚል የሰጠው ማብራሪያ እኔን አስደንግጧል። “ዶ/ር ጌዲዮንና ጓደኞቹ እንደ አስማተኛ የተፈችዎችን የስም ዝርዝር ማንም አስቀድሞ ሳያውቅ በነጻነትና ገለልተኛነት አቀረቡት።”ተብለናል።

ከፍችው ማግስት ዶ/ር ጌዲዮን በጉዳዩ ላይ በሚድያ ማብራሪያ ለመስጠት በመጣበት ወቅት በአንደበቱና በፊቱ ላይ ትልቅ ጭንቀት አይተናል። ያንን የመሰለ በአልጀዚራና በቢቢሲ ሃርድ ቶክ ላይ ኢትዮጵያን በሚያኮራ ደረጃ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከማንም የመንግስት ባለስልጣን በላይ መንግስትን ወክሎ በአንደበተ ርቱእነት የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳት የቻለ ሰው፤ በአማርኛ ቋንቋ ስለፍችው ማብራሪያ መስጠት አቅቶት አንደበቱ ተሳስሮ አይተነዋል። ይህን ተመልክተን የአቃቤ ህግ መስሪያ ቤት የተፈችዎችን የስም ዝርዝር በስልጣኑ አቀረበ የተባለውን መግለጫ ለማመን እንዲከብደን አድርጎታል።

ሌሎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያዎች እጅግ አሳሳቢ ሆኖ አግኝቻቸዋለሁ። ‘የመከላከያ አዛዦች ሹመት እንደጠየቁኝ፣ ተፈናቃዮችና ሌሎችም የራሳቸው ጥያቄ እንደጠየቁኝ ሁሉ ለድል ያበቃኝ ፈጣሪ በይቅርታና በምህረት መንገድ እንድሄድ ጠይቆኛል” ብሎናል። የዚህን አባባል አሳሳቢነት በቦታው እንመለስበታለን። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪዎች፣ አፈቀላጤዎች፣ የመንግስት የኮሚኒኬሽን ባለስልጣናት፣ የፍትህ አካላት የሰጡን አስተያየቶች በቅርጽም በይዘትም አስገራሚ ሆነው አግኝተናቸዋል።

አንዳንዶች በቅኔ በተረት መልኩ ሊያስረዱን ሲሞክሩ፣ ሌሎቹ “እመኑን አትቸኩሉ ወደፊት ታዩታላችሁ ብዙ ጥቅም የሚኖረው ውሳኔ ነው” እያሉን ነው። ይህ አባባል የራሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ነው። እነዚህ ሁሉ ተደምረው ጉዳዩን የበለጠ አወሳሰቡት እንጂ ሌላ የፈየዱት ነገር የለም።

ይህ እንዳለ ሆኖ የፍችው ምክንያት ምን እንደሆነ ባልጠራበት ሁኔታ የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች በመሰላቸው መንገድ የውሳኔውን ሚስጥር በመተርጎም አስተያየቶቻቸውን ለመስጠት ሲሞክሩ ታይተዋል። እነዚህ አስተያየቶች ከአራት አቅጣጫዎች የተሰነዘሩ ናቸው።

እጅግ አድርባይ የሆኑ ሁሌም ስልጣን ላይ ለወጣ ሃይል ሁሉ በጭፍኑ የማደግደግ ባህል ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ከተለመደው የማደግደግ ባህላቸው ተነስተው የመንግስት ውሳኔ ለማንም ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ ውሳኔውን ሲደግፉ ታይተዋል። በደንብ ቢጠየቁ ምኑን እንደደገፉ ራሳቸውም የሚያውቁት አይሆንም። እንደዚህ አይነቶቹ ግለሰቦች ጥቂት ቢሆኑም ድምጻቸውን አጋኖ የሚያስተጋባላቸው አጋር የመንግስት ሚድያ አላቸው። እንዲህ አይነት ሰዎች በሃገር ውስጥም በዳያስፖራውም እንዳሉ ይታያል።

ከመጀመሪያዎቹ ቀጥሎ፤ ከኢህአደጋዊው የጥርናፌ ባህል ያልተላቀቁት የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ በብልጽግና ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ስራ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት፣ እንዲሁም ለብልጽግና ፓርቲ ማደሩ ይጠቅማል ያሉ ሌሎች አካላት፣ ለውሳኔው በቂ ምክንያት ሳያቀረቡ የተለመደውን በመንግስት ውግንና የተሞላውን ፕሮፓጋንዳ ሲያካሂዱ እያየናቸው ነው። ከእነዚህ ውጭ በተለይ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በበጎ አይን የሚያዩና ተቀራርበው እየሰሩ ያሉ ሃይሎች የውሳኔው ምክንያት ግልጽ ባይሆንላቸውም ኢትዮጵያ ያለችበትን አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሃላፊነት በተሞላው መንፈስ “ይህ ውሳኔ የተጀመረውን በጋራ ሃገር እና ህዝብን የመታደግ አዲስ ባህል በመጉዳት ለሃገሪቱ ጠላቶች ቀዳዳ የሚከፍት እድል ስላለው፣ ቀዳዳ እንዳይከፈት” አበክረው ተማጽነዋል።

በአራተኛ ረድፍ ላይ የቆመው ሁሌም ማናቸውንም የመንግስት ውሳኔ መልካም ይሁን መጥፎ በመቃወም የግልና የቡድን ጥቅም በሃገርና በህዝብ ኪስራ ለማስጠበቅ ቆርጦ የተነሳው ወገን ነው። ለዚህ ሃይል ይህ ግልጽነት የሌለው ውሳኔ የሰርግና ምላሽ ሁኔታ ፈጥሮለታል። በዩትዩብና በማህበራዊ ሚድያ ገንዘብ የመሰብሰብ፣ በመንግስትና በህዝብ መሃከል መቃቃር እንዲፈጠር፣ ሀገር እንዲፈራርስ ያለውን ህልም ማሳኪያ አድርጎ እየሰራበት ይገኛል። እኔም ይህን ወሳኔ ስቃወም ውሳኔውን ለምን እንደተወሰነ የተለየ መረጃ ኖሮኝ አይደለም። ሆኖም የሃገራችንን የፖለቲካ ሂደት በቅርበት እንደሚከታተል ሰው ለዚህ ውሳኔ ምክንያቶች ይሆናሉ ብዬ የገመትኳቸውን ነጥቦች በሙሉ መዘርዘርና ጥቅምና ጉዳታቸውን ማጤን ከባድ ስራ ነው ብዬ አላምንም። እነስብሃት ነጋን ለመፍታት መንግስት ለምን እንደወሰነ በውል አናውቅም ማለት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን ነጥቦች አንድ በአንድ መዘርዘር አንችልም ማለት አይደለም።

የውሳኔውን ምክንያቶች ከመዘርዘሬ በፊት በሁለት ነጥቦችን ላይ ያለኝን እይታ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። የመጀመሪያው ነጥብ የውሳኔውን አላማ (motive) የተመለከተ ነው። በበኩሌ ይህን ውሳኔ የተቃወምኩት ውሳኔው ቀና ካልሆነ፣ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለመጉዳት በማሰብ የተደረገ ውሳኔ ይሆናል ከሚል ጥርጣሬ በመነሳት አይደለም። ጦርነቱ በፍጥነት አልቆ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ተረጋጋ የፖለቲካና መንግስታዊ ስርአት ግንባታ እንድታዞር፣ በተለይ ከሁሉም ነገር በላይ የኢትዮጵያና የህዝቧ የዘመናት ማድያት የሆነውን ሃገራዊ ድህነት የመቅረፍ ስራ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ መሆኑን እና ጦርነቱ በዚህ ቀና ህልም ፊት የቆመ ደንቃራ እንደሆነ አድርጎ በተለይ ዶ/ር አቢይ እንደሚያየው አውቃለሁ።

ችግሩ ያለው ውሳኔው፣ እውን እንደወሳኞቹ በጎ ምኞት የጦርነቶችን እድሜ በኢትዮጵያ ያሳጥራል ወይ? እውን የተረጋጋ ፖለቲካዊና መንግስታዊ ስርአት ለመገንባት የተሻለ እድል ይፈጥርልናል ወይ? እውን ሁለመናችን ወደ ልማት እና ብልጽግና በማዞር የኢትዮጵያን ህዝብ ለስቃይ የዳረገውን፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የሞራልና የስብእና መቃወስ ምንጭ የሆነውን ድህነትን እንድንቀንስ እድል ይሰጠናል ወይ? ነው። በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእራት ግብዣው ላይ ውሳኔው ያስከብራል ያላቸውን ሶስት ነጥቦች መጨመር እንችላለን። እውን ውሳኔው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቅ ይሆናል ወይ? እንዳውም እነዚህ ሶስት ነጥቦች የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈተሹ የሚገባቸው ናቸው። ሚድያው እንደ ገደል ማሚቱ እየደጋገመ እያስተጋባቸው ስለሆነ።

ሁለተኛው ነጥብ “መንግስት ለምን በውል ውሳኔውን እንደወሰነ ሳታውቁ ትቃወማላችሁ” በሚለው ጉዳይ ነው። ሲጀመር በቂ ማብራሪያ ያልሰጠውና አብዛኛውን ሰው በጉዳዩ ላይ እንዲጠነቁል ያደረገው መንግስት ነው። መጠየቅ ካለበት ለህዝብ በቂ መግለጫ መስጠት የተሳነው መንግስት እንጂ የራሳቸውን መላ በመምታት የሚቃወሙት መሆን የለባቸውም። “በቂ ማብራሪያ መንግስት እስከሚሰጥ ጠብቁ” ለሚሉት ውሳኔው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚቀር ቢሆን ኖሮ ምክራቸውን መቀበል ቀላል ይሆን ነበር። ችግሩ መንግስት በቂ ማብራሪያ ሳይሰጥ ውሳኔውን ተግባራዊ እያደረገው ነው። አንዴ ውሳኔው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በተለይ ውሳኔው አንዳንዶቻችን እንደሰጋነው በሃገርና በህዝብ ላይ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ ውሳኔ ሆኖ ከተገኘ መዘዙ የከፋ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ “ወሳኔው ወደ ከፋ ጥፋት ሊወስደን ይችላል” የሚል ጥርጣሬ ያላቸው አካላት የውሳኔው መዘዝ ይሆናል ያሉትን እያቀረቡ መንግስትን ቢቃወሙ፣ ቢሞግቱ፣ መንግስትን ቢያስጠነቅቁ፣ ቢያሳስቡ ወይም ቢማጸኑ “ትክክል ናቸው” ማለት እንችላለን። እኔም ይህን በማመኔ ነው የመንግስትን እርምጃ አጥብቄ የተቃወምኩት። ቀጥሎ የምሸጋገረው ለመንግስት ውሳኔ ምክንያቶች ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ወሳኝ ነጥቦች ወደ መዘርዘሩ ነው። ነጥቦቹን በወቅቱ ክብደት ሰጥቼ ባስቀመጥኩበት ቅደም ተከተል በተራ ቁጥር አስቀምጣቸዋለሁ። በእራት ግብዣው ላይ ዶ/ር አብይ ያደረገው ንግግር ትንሽም ቢሆን ስራችንን ቀለል አድርጎልናል ብዬ አምናለሁ።

የውሳኔ ምክንያቶች፤

1) ውሳኔው ከውጭ መንግስታት በተለይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የተፈጠረ አዲስ ግንኙነት፣

2) “ጦርነቱ ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ መቋጫ ያስፈልገዋል” ከሚል እምነት ለፖለቲካ መቋጫው የእርቅ፣ የድርድርና የውይይት መንገድ ለመክፈት፤

3) በወያኔ ካምፕ ውስጥ ልዩነቶች በመቀስቀስና ክፍፍል በመፍጠር ጦር ሰባቂውን ወገን ለማዳከም፣

4) ከእምነት ጋር የተያያዘ የእርቅና የምህረት ቀኖና ለማስፈጸም የተወሰደ ውሳኔ፣

ውሳኔውን በግራም ሆነ በቀኝ ብናገላብጠው የውሳኔው ምክንያቶች ከዚህ ውጭ ሊወጡ አይችሉም። እስካሁን የተሰጡት ማብራሪያዋች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው።

የገና እለት ከምሽቱ አራት ሰአት በኋላ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ሰበር ዜና” በሚል ርእስ መደበኛ ፕሮግራሙን ሲያቋርጥ እኔ የጠበቅኩት መንግስት በትግራይ አሸባሪ ቡድን መሪዎች ላይ የተቀዳጃቸውን የድል ዜና ሊያበስር ይሆናል የሚል ነበር። ሌላው የጠበቅኩት ዜና ትልቅ የእልቂት ወይም ከባድ የሃዘን ዜና ነበር። እነዚህ ሁለት የጠበቅኋቸው ዜናዎች ሳይሆኑ ቀርቶ ከወያኔ ደጋፊዎች ውጭ አድማጭን ያስደነገጠ ዜና ተደጋግሞ ተነበበ።

እነ ጀዋር እና እነ እስክንድር ለብሄራዊ ውይይቱ ተአማኒነት ሲባል ይፈታሉ የሚል ግምት ቢኖረኝም እነስብሃት ነጋ ግን እንዲፈቱ የሚያደርግ ምድራዊ ምክንያት ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። በተለይ እንዲህ አይነቱ ዜና በበአል ቀን እንዳውም ከመሸ በኋላ እንዲነገር የተፈለገበት ምክንያት ብዙ ጥያቄዎች እንዳነሳ አደረገኝ። የነጀዋርና የእነእስክንድር ከነስብሃት ጋር ተደባልቆ መፈታት ሰበር ዜናው እነስብሃትን ከመፍታት ጋር እንጂ ከነጀዋርና እስክንድር መፈታት ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ እንዳስብ አድርጎኛል። እንዲያውም “እነእስክንድርና ጀዋር በዛ ቀን እንዲፈቱ የተደረገው በነስብሃት መፈታት በህዝቡ ውስጥ የሚነሳውን ድንጋጤና ቁጣ ለማደብዘዝ ካልሆነ ሌላ ምክንያት አይኖረውም” የሚል ድምዳሜ ላይ አደረሰኝ።

የዜናው ተቻኩሎ የመለቀቅ ጉዳይ፣ በተለይ የእለቱን በአልነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንግስት ፍቺውን በተመለከተ ቃል የገባለት አካል ሊኖር እንደሚችልና ቃሉን ለመጠበቅ ሲል የገናን እለት እንኳን ማለፍ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንደገባ ነው የገባኝ። “ይህን ማድረግ የሚችሉ አሜሪካኖች ብቻ ናቸው” ብዬ በማሰቤ ነው ለነስብሃት መፈታት ዋናው ምክንያት አሜሪካ ትሆናለች በማለት የደመደምኩት። ሌሎችንም ከላይ ያስቀመጥኳቸውን ምክንያቶች ብዘረዝርም ዋናው ምክንያት ይሆናል ያልኩትን ጉዳይ በጥልቀት መመልከት ጀመረኩ።

1) ውሳኔው ከውጭ መንግስታት በተለይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የተፈጠረ አዲስ ግንኙነት፣

የተለያዩ የአሜሪካ የጥናትና የምርምር ቡድኖች፣ የታወቁ የውጭ ጉዳይ ተንታኝ የህትመት ድርጅቶች፣ የውጭ ጉዳይ ሙያተኞችና ፖለቲከኞች፣ የአሜሪካ መንግስት በምስራቅ አፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአሜሪካንን ብሄራዊና መሰረታዊ ጂኦ ፖለቲካል ጥቅም ክፉኛ የሚጎዳ እንደሆነና መስተካከል እንደሚገባው መወትወት ከጀመሩ ቆይተዋል። ሆኖም የአሜሪካ መንግስት የውጭ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ እንደነ ሱዛን ራይስ፣ ጌል ስሚዝና ሳማንታ ፓወር የመሳሰሉ የወያኔ ወዳጆችና ቅጥረኞች በአስተዳደሩ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን መያዛቸውና ወያኔ በወታደራዊ ጉልበቱ አሜሪካኖች የጠሉትን የአብይን መንግስት የመጣል እድሉ ገዝፎ በሚታይበት ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘቸውን በሃገራችን ኪሳራ ጥቅሟን የሚያስከብር አቋም ለማስተካከል ፈቃደኛ አልነበረችም። ሆኖም ግን በፖለቲካ 24 ሰአት ረጅም ነው እንደተባለው አሜሪካ አቋሟን የማስተካከል እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድትወስድ የሚያስገድዱ ኩነቶች ተበራከቱ።

ዋናው ኩነት የአሜሪካ ፈረስ ሆኖ አዲስ አበባ ይገባል የተባለው ወያኔ በጥቂት ሳምንታት በኢትዮጵያ መከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት ተቀጥቆጦ ከሞላ ጎደል ከአፋርና ከአማራ ክልል ተጠራርጎ መውጣቱ ነው። በወታደራዊ ጉልበት የአብይ መንግስትን መጣል የማይቻል መሆኑ ግልጽ ሲሆን አሜሪካ ጥቅሟን የምታስከብርበት ሌላ አማራጭ ወደ ማሰብ መሄዷ የግድ ነበር። በዚህ ላይ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መጀመሪያ ኢትዮጵያን ቀጥሎ ኤርትራን በዚህ የጦርነት ወቅት መጎብኘቱ፣ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ እንመድባለን ማለቱ፣ ቻይና ከ300 ቢሊዬን ዶላር በላይ ከአፍሪካ ጋር ላላት የንግድ ትስስር መመደቧ፣ ሌሎችም እንደ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቱርክና ኢራንን የመሳሰሉ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያሳዩት መቀራረብ ኢትዮጵያ ያለአሜሪካ ትብብር ህልውናዋን እና ጥቅሟን አስከብራ የምትሄድ አሜሪካንን የማትፈልግ ሃገር እየሆነች መሄዷ፣ አሜሪካንን እያሳሰባት እንዲመጣ አድርጓታል።

በዚህ ላይ አሜሪካ በወሰደችው አይን ያወጣ ኢትዮጵያን የማጥቃት አቋም የተነሳ በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውና፣ በሃገር ውስጥ ወደ ሰፊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲያድግ በመንግስት ያልተፈለገው፣ (ከብልጽግና ፓርቲ ቁጥጥር ውጭ ይወጣል በሚል ስጋት) ሆኖም ግን ወደ ውጭ የተዛመተው “ኢትዮጵያን አትንኩ” (hands off Ethiopia) እንቅስቃሴ እራሱን አጠናክሮ ወደ አለም አቀፉ በቃ (Nomore) ጸረ አዲሱ ቅኝ አገዛዝና ጸረ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንቅስቃሴ ማደጉ ሌላ የአሜሪካን ራስ ምታት እየሆነ መጥቷል። ይህ እንቅስቃሴ በፍጥነት በአፍሪካና በካሬቢያን ሃገሮች ብቻ ሳይሆን በላቲን አሜሪካ፣ በኢራንና በቻይና እየተዛመተ ያለ እንቅስቃሴ መሆኑ ከአሜሪካኖች የተሰወረ አይደለም።

አሜሪካኖች የበቃ እንቅስቃሴ ምን ያህል እንዳሳሰባቸው ማስረጃው “በአሜሪካን ሃገር ውስጥ በትውልደ ኢትዮጵያውያን መሃል ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች እነማን ናቸው?” የሚል ጥናት እንዲያጠና ለአንድ የግል ኩባንያ ገንዘብ ከፍለው ስራ ማስጀመራቸውን ነው። የዚህ ጥናት አላማ መደለል ያለባቸውን ተጽእኖ አሳዳሪዎች መደለል፣ ማስፈራራት የሚገባቸውን ለማስፈራራትና በበቃ ንቅናቄ መሪዎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ነው።የእነዚህ የተደራረቡ ኩነቶች ድምር አሜሪካ በፍጥነት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት መርምራ ኢትዮጵያ የያዛቸውን ከአሜሪካ የመራቅና አሜሪካንን የማሳጣት ስራ ማስቆም ቀዳሚ ስራዋ አድርጋ የምትንቀሳቀስበት ሁኔታ ውስጥ እንደምትገባ መተንበይ ከባድ አልነበረም።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማድረግ ሁኔታውን ለመቀልበስ የምትሞክርባቸው አማራጮች ሁለት ነበሩ። አንዱ ወያኔ ጥቅም ባይኖረውም፣ ለወያኔ ድጋፍ እየሰጡ ማቆየት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትን፣ የእርዳታ አቅርቦት ችግርን ሰበብ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና ቀጥተኛ ባልሆነ ወታደራዊ መንገድ ተጽእኖ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው አማራጭ አሜሪካ አይኗን በጨው ታጥባ “ድሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ወዳጆች ነን፣ ወያኔ ያደረሰውን ጥፋት ተመልክተናል፣ በትግራይ ይሁን በሌላው የሃገሪቱ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ መፍትሄ መስጠት የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት እኛን ከሃፍረት ሊያድነን የሚያስችሉ (for face saving purposes) እርምጃዎች ቢወስድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም ወዳጅነታችንን ማጠናከር እንፈልጋለን” የሚል አማራጭ መውሰድ ነው። በገና እለት በተጣደፈ መንገድ የእነስብሃት መፈታታ ሲታወጅ በኔ አእምሮ የመጣው “አሜሪካ ሁለተኛውን አቋም በመውስድ ወያኔን ለጥቅሟ ስትል ለመክዳት ወስናለች” የሚል ነበር። አሜሪካ በማስፈራራት ተጽእኖ እንዳላመጣችብን ገምቼ ነበር።

አሜሪካኖች አንድ ወሳኔ ሲወስኑ በበዙ አቅጣጫ ነገሮችን አጢነው ነው። ከሚያጤኑት ጉዳይ መሃከል ግለሰቦችን ጭምር ነው። አብይን በኢኮኖሚ ማእቀብ፣ በወታደራዊ ፉከራ፣ በዲፕሎማሲ ጦርነት አስፈራርተው ነው እነስብሃትን እንዲፈታ ያደረጉት የሚለውን የአንዳንድ ጓደኞቼን ትንተና ያልተቀበልኩት አሜሪካኖች አብይን በማስፈራራት ቢቀርቡት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ወስዶ የበለጠ ጸረ አሜሪካ የሆነ ስሜት በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት እንደሚፈጥር፣ በማስፈራሪያ ሊያስጎነብሱት የሚችሉት ሰው እንዳልሆነ ስለሚያውቁ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የእራት ግብዣ ንግግር ግልጽ ሆኖ የወጣው ጉዳይ አሜሪካ የማስፈራራት ተጽእኖ እንዳላደረገች ነው። አሜሪካ የኢትዮጵያን አቋም በደንብ ተረድተው መስመራቸውን ለማስተካከል ከተዘጋጁት መሃል አንዷ እንደሆነች ፍንጭ ሰጥቶናል። ዝርዝሩን ማወቅ ስለማንችል አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግስት ለመሸንገል እስከምን ርቀት ልትጓዝ እንደወሰነች መናገር አልችልም። ሆኖም ለኢትዮጵያ መንግስት በፍንጭ ደረጃ ቃል የገባቻቸው በርካታ ነገሮች ይኖራሉ የሚል እምነት አለኝ። አንዱ ወደ አግዋ ኢትዮጵያን መመለስ፣ ሌላው የወደሙትን ክልሎች ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ሰፊ ድጋፍ ማድረግ፣ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ሰፊ እርዳታ መለገስ፣ የወያኔ መሪዎች ከሰላም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው በመንገር ተጽእኖ ማድረግ፣ የአለም የፋይናንስ ተቋማት በራቸውን ለኢትዮጵያ ክፍት እንዲያደርጉ ማድረግ፣ በአሜሪካን ባንኮች ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ ያደረጉትን ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ መፍቀድና ሌሎችንም ነጥቦች ሊያካትት ይችላል የሚል ግምት አለኝ።

በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ከወያኔ ጋር በጥቅም ከተቆራኙት የጌል ስሚዝ ጋንግ በስተቀር የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ለወያኔ መሪዎች የተለየ ፍቅር እንደሌላቸው ገልጫለሁ። አሜሪካ ለወያኔ የምታሳየው ውግንና ወያኔ የአሜሪካን ጥቅምና ፍላጎት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፈጸም የተመቻቸ መሳሪያ ነው ብላ ከማመን እንደሆነ በተደጋጋሚ አስረድቻለሁ። አሜሪካ ቁርባን የምትገባው ሃገር፣ ድርጅትና ግለሰብ የለም። ወያኔ በመሳሪያነት ጠቀሜታ እንደሌለው በውል የተረዳ የአሜሪካ መንግስት ወያኔን አገልግሎቱ እንዳበቃለት መሳሪያ አውልቆ ቢጥለው የሚገርም አይደለም። አሜሪካ ከወያኔም ጋር ይሁን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቋሚ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሊኖራት የማትችል ሃገር ናት። ቋሚ ጥቅሟን የማያስከብሩ እስከሆነ ድረስ ሁለቱን ለመክዳትና ለማጥቃት ወደ ኋላ አትልም።

ግምታዊ በሆነ መንገድ የምንወያይ ቢሆንም አሜሪካ እንዲወገድ ስትፏችር ወደነበረው የአብይ መንግስት ፈገግታ የተሞላ ፊቷን ስታዞር “ምን አገኛለሁ ብላ ነው?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው ። በዚህ የተለሳለሰና ዱላ የሚባል ነገር የሌለው በከረሜላ ብቻ በተሞላ አቀራረባቸው አሜሪካኖች ኢትዮጵያን የተጠጉት ምን ማከናወን ፈልገው ነው? የኢትዮጵያ መንግስት ስሟን ባይጠቅስም፣ የአሜሪካንን አዲስ አቀራረብ በድል መልኩ አቅርቦታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኛ ሸብረክ አላልንም ያሉት ሌሎች ናቸው ሲለን ስለነማን እየነገረን እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዛም አልፎ እነስብሃትን መልቀቅ ጥቅም የሚያስገኝ እንደሆነ በቅኔ እና በተረት እየተነገረን ነው። ስለጥቅም እየነገሩን ያሉት ግለሰቦች “ይህን የአሜሪካ አዲስ አቋም ከነሙሉ ትርጉሙና መዘዙ ተረድተውት ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ ጠላት ብላ የፈረጀቻቸው አገሮች የሉም ብሎ ነግሮናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲፕሎማት መሆን ስላለበት እነዚህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መናገር አይችልም። በአደባባይ አገሮችን እየዘረዘረ ወዳጅና ጠላት ሃገራት እያለ እየፈረጀ የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ ሰነድ ጽፎ በማሳተም የበተነውን መለስ ዜናዊ አውግዤ፤ ዶ/ር አብይን ጠላትና ወዳጅ እያልክ መንግስታትን በአደባባይ ዘርዝርልን ማለት አልችልም። ይህን ብዬም የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ጠላት ብላ የፈረጀቻቸው ሃገራት የሉም” የሚል አባባሉ ከዲፕሎማሲ ቋንቋ ዘሎ ግን የእውነተኛ እምነት መገለጫ ከሆነ ሃገራችን ትልቅ ችግር ውስጥ ነች።

በተለይ አሜሪካና የምእራብ መንግስታት ለረጅም ዘመናት፣ እሰከ ትናንትና ድረስ ኢትዮጵያን በማጥቃት የፈጸሟቸውን እኩይ ተግባራት ብዙ እንደሆኑ እናውቃለን። ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን ራሷን በኢኮኖሚ የቻለች፣ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የነጻነት ምድር ሆና፣ በአፍሪካዊ አርአያነቷ ገና እንድትወጣ አሜሪካና የምእራብ መንግስታት ከቶውኑ አይፈልጉም። አሜሪካና ሸሪኮቿ የምእራብ ሃገራት ሁሌም ማየት የሚፈልጉት በነጮች ቀጭን ክር ታስረው የሚንቀሳቀሱ የአፍሪካ አገሮችን ነው። አፍሪካን በነጮች ምክር፣ ትእዛዝና ድጋፍ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ማድረግ ከስትራተጂ ጥቅማቸው ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። እነዚህ ሃገራት የአፍሪካ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ብልጽግና ሰላም እና አንድነት ጸሮች ናቸው።

አሜሪካ ወያኔን በመደገፍ የሸረበችው ሴራ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ ከራሱ ፣ ከቅርብ ጎረቤቶቹና ከአፍሪካ፣ በአሜሪካና በምእራባውያን ተመሳሳይ በደል ከደረሰባቸው ሃገሮችና ህዝቦች በስተቀር፣ አጋር እንደሌለው ለማየት የቻለበት እድል ስጥቶታል። የአሜሪካና የምእራባውያንን የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጠበቃነት ጭምብል ወልቆ ለማየት ችሏል። እነዚህ ሃገራት ስለዲሞክራሲና ስብአዊ መብት የሚያወሩት ጥቅማቸው እስከተከበረ እንጂ ጥቅማቸው የማይከበር ሆኖ ካገኙት ሃገር ከማፍረስና ህዝብ ከማጥፋት የማይመለሱ እንደሆነ መረዳት ችሏል። መራባውያን እንደወያኔ አይነቶቹን ሃገር አፍራሽና ህዝብ ጨራሽ ሃይሎች ለመደገፍ ወደኋላ እንደማይሉ ሁላችንም የሃገራችን ደሃ ገበሬ ሳይቀር በአይናችን ያየነው ጉዳይ ነው። ከዚህ ቀደም በርእዮእተ አለም ደረጃ ሲገለጽ የነበረው የምእራባውያን እኩይነት ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው በአሜሪካኖችና በምእራባውያን ድጋፍ ወያኔ በሃገራችን እና በህዝባችን ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ሰቆቃና ውድመት ግልጽ ሆኗል። ይህ የህዝብ እውቀት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ትንሳኤ መሰረት ነው።

በዚህ የታሪክ መጋጠሚያ የደረሰብን ሰቆቃና ውድመት ይዞት የመጣው አንድ ትልቅ እድል አለ። በቀላሉ የማይገኝ እድል። ራሳችንን እንድንፈትሽ፣ እውነተኛ ወዳጅ ጠላታችንን እንድንለይ አስችሎናል። ወያኔ በዘር ሰነጣጥሮ ሲያባላው የነበረ ህዝብ የአንድነትን ትርጉምና ሃያልነት የተማረበት እድል ሰጥቶታል። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ድክመት የአንድነት አለመኖር መሆኑን አሳይቶናል። ከምንም ነገር በላይ በሰላም ለመኖር የውስጥ ችግራችንን ማቃለል፣ ከጎረቤቶቻችንን ጋር በሰላምና በመልካም ጉርብትና መኖር፣ የመላውን የአፍሪካ ህዝብ ወንድማዊና እህታዊ አጋርነት የሚያስፈልገን እንደሆነ አሳይቶናል። የአሜሪካን እርጥባንና በዴሞክራሲና በሰብአዊ መብት ስም የሚፈስ የአዞ እንባ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የባርነት ቀንበር የሚያጠብቅ እንጂ ነጻነት እንደማያመጣ አስረድቶናል። “እኛ የአድዋ እንጂ የአገዋ ልጆች አይደለንም” የሚል ትልቅ ትርጉም ያለው አባባል በምድራችን እንዲሰማ አድርጓል።

አሜሪካኖች በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን የተጀመረው በቃ እንቅስቃሴ በሁለቱ ሃገሮች ድንበር ታጥሮ እንደማይቀር አውቀውታል። ጉዳዩ የኢትዮጵያን መንግስት ከአሜሪካ ጫና ማላቀቅ ሳይሆን የአፍሪካን ህዝብ የአህጉሩ ባለቤት የሚያደርግ ስር ነቀል እንቅስቃሴ እንደሆነ ገብቷቸዋል። የኢትዮጵያ ጥንካሬ ከጎረቤቶቿ ከኤርትራና ከሶማሌያ ጋር ያላት ወገናዊ ትስስር እንደሆነ ያውቃሉ። ኢትዮጵያ ከምእራባውያን የሎሌነት ቀንበር ነጻ የምትሆነው፣ ክብሯ፣ ሉአላዊነቷንና ጥቅሟን ማስከበር የምትችለው የአሜሪካኖችን ተጽእኖ ተቋቁማ በምትገነባው ሃገር በቀል ኢኮኖሚ፣ በምርጫዋ ላይ ተመስርታ በምትገባባቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች፣ በራሷ ጥረት በምትገነባው ለሁሉም ዜጎቿ የሚመች ጤነኛ የፖለቲካ ስርአት እንደሆነ ያውቁታል። የብሄራዊ ጥቅሟና ደህንነቷ ምንጭ የህዝቧ አንድነት ጀግንነትና አይበገሬነት እንደሆነ አስቀደመው ያውቁታል።

ዛሬ አሜሪካኖች በፈገግታ የተሞላ ፊታቸውን ወደ ዶ/ር አብይ መንግስት ሲያዞሩ፣ ከዱላ ነጻ የሆኑ ብዙ ከረሜላዎችን ውሰዱ ሲሉ ግባቸው ኢትዮጵያን መልሰው የአሜሪካ ጥገኛ ማድረግ ነው። አድዋን በአግዋ መቀየር፣ ኢትዮጵያ ከቻይና ከሩሲያና ከሌሎች በፈቃዷ ከመሰረተቻቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ራሷን እንድታርቅ ነው። በተለይ ደግሞ ለአሜሪካ አልገብርም ካለው፣ የኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር አጥብቃ የያዘችውን ወዳጅነት ኢትዮጵያ እንድታላላ ለማድረግ ነው። በእርዳታ ፣ በዲፕሎማሲ ድጋፍ ፣ በወታደር ስልጠና እና በመሳሪያ አቅራቢነት ፣ የእናንተም ጠላት የኔም ጠላት ነው በሚል ሃፍረት የለሽ እወጃ ስም፣ አሜሪካ ማግኘት የምትፈልገው የአሜሪካ ተላላኪ የሆነች በጎረቤቶቿ በአፍሪካውያን በሌሎችም የአለም መንግስታት አይን በጥርጣሬ የምትታይ ኢትዮጵያን ነው።

የአሜሪካ ፍላጎት ለኢትዮጵያ ክብር ሲል በተጀመረውና የአፍሪካን ክብር ለማስመለስ ወደ ትልቅ እንቅስቃሴ እያደገ ባለው የበቃ እንቅስቃሴ ላይ የኢትዮጵያ መሪዎች ውሃ እንዲቸልሱበት ነው። በእራት ግብዣው ላይ ዶ/ር አብይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የደያስፖራውን እንቅስቃሴ የእሱን መንግስትና ኢትዮጵያን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ እንደተፈጠረ አድርጎ በማቅረብና ንቅናቄው ፊቱን ወደሌሎች ጉዳዮች እንዲያዞር የሰጠው ምክር የአሜሪካኖችን ልብ የሚያሞቅ እንደሆነ መታወቅ አለበት። የበቃ እንቅስቃሴ እንዲበተን ትኩረቱን ወደ ጥቃቅን ነገሮች እንዲያዞር አሜሪካኖች ይፈልጋሉ። የነስብሃት መፈታት ያስነሳው አቧራ የበቃ እንቅስቃሴን ለማናጋት በቅቷል። ኢትዮጵያ የበቃን አለም አቀፍ እንቅስቃሴ በመምራት የፓን አፍሪካን መሪነቱን መረከብ ሲገባት ንቅናቄውን የሚያዳክም ወሳኔዎች በመወሰን ልትጎዳው አይገባም።

በራሱ ህዝብ አቅምና ጥረት ላይ ኢኮኖሚውን፣ ወታደራዊ ጉልበቱን፣ ፖለቲካዊ ጤንነቱን ያልገነባ፤ ከአካባቢው ሃገራት ጋር በመልካም ጉርብትና የማይኖር የአንድ ሃገር መንግስት የአሜሪካ ቁራኛ ሆኖ እንደሚያርፈው አሜሪካኖች ጠንቅቀው ያውቁታል። እንዲህ አይነቱ መንግስት የገዛ ሃገሩንና ህዝቡን ጥቅም ማስከበር አይችልም። አሜሪካኖች እንዲህ አይነቱ መንግስት ከህዝብ የተገነጠለ፣ በህዝብ የተጠላ በመሆኑ ህልውናውን ለማስጠበቅ ከአሜሪካኖች በጎ ፈቃድና ድጋፍ ውጭ መኖር እንደማይችል፤ በብዙ ሃገሮች ላይ ከፈጸሙት ደባ ተነስተው የሚያውቁት ሃቅ ነው። እንዲህ አይነት ከህዝቡ ጋር የተኳረፈ መንግስት፣ ህዝብን በአሜሪካ ጠመንጃና የስለላ ቴክኖሎጂ እየቀጠቀጠና እያፈነ ከመኖር ውጭ አማራጭ አይኖረውም።

የእነ ስብሃት መፈታት ከአሜሪካ በኩል ከመጣ የአቋም ለውጥ ከሆነ ዶ/ር አብይ በሰዎቹ መፈታት እናስጠብቃለን ያለውን፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፣ ሉአላዊነትና ብሄራዊ ደህንነት የሚያስጠብቅ አይሆንም። በዶ/ር አብይና በደጋፊዎቹ ዙሪያ የሚሰጡ መግለጫዎች ይህን ከሰይጣን ጋር የሚደረግ ዳንስና መዘዙን በሚገባ አጢነውታል ወይ የሚል ጥያቄ ጭሮብኛል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግስት የፈለገችውን መልካም ነገር ቃል ብትገባም ከአሜሪካ ለሚገኙ ድጋፎች በሚል እነስብሃትን ወደ መፍታት ተኪዶ ከሆነ ውጤቱ ዶ/አብይ የሚወደውን ተረት ልዋስና “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” ይሆናል። ከሰይጣን ጋር እስክስታ መጨረሻው ስቅስቅታ ይሆናል ባይ ነኝ።

Andy
አንዳርጋቸው ጽጌ

2) ጦርነቱ ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ መቋጫ ያስፈልገዋል ከሚል እምነት ለፖለቲካ መቋጫው የእርቅ፣ የድርድር፣ የውይይት መንገድ ለመክፈት፣

በሚቀጥለው ክፍል በዚህ ርእስ ዙሪያ ያለኝን እይታ ይዤ እቀርባለሁ። ይቀጥላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop