ዶሮው ለ3ኛ ጊዜ ጮኽ! – ከወንድሙ መኰንን፣ እንግላንድ

“እውነት፡ እልኻለኹ፥ በዚች፡ ሌሊት፡ ዶሮ፡ ሳይጮኽ፡ ሦስት፡ ጊዜ፡ ትክደኛለኽ።”
ማቴዎስ 26 ቁጥር 34

ከወንድሙ መኰንን፣ እንግላንድ 11 January 2022

መግቢያ

ጥቅምት 24 ቀን 2013 በውድቅት ሌሊት በትዕቢት የተወጠሩ የጦርነት ከበሮ ደላቂ የሕወሀት ባለሥልጣናት፥ ለዘመናት በገነቡት የጦር ኃይላቸው የትግራይን ሕዝብ ደሙንና አጥንቱን መስዋዕት እየከፈለ ሲጠብቃቸው የነበረውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን፥ የጭካኔ ጥግ በሚሆን አኳኋን፥ በተኙበት ጦራቸውን አምዘግዝገው ወጉት፥ ሳንጃቸውን ወድረው አረዱት። የሞቱትንም ሬሳቸውን ታይቶ በማይታወቅ ሆኔታ ልብሳቸውን ገፈው እርቃናቸውን ሜዳ ላይ ደርድረው የትግራይን ህዝብ አስጨፈሩት። በሕይወት የተያዙትን ፥ ጥይት ላለማባከን በማለት አስተኝተው ሲኖ ትራክ ነዱበት።

ይኸ በወገናችን ላይ የደረሰው ግፍ አንገሽግሾን፣ በመንግሥት ላይ የየራሳችንን ቁርሾ፣ ለምሳሌ አማራው ላይ በአጣዬ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በወለጋ፣ በጋሞው ላይ በቡራዩ፣ ኦሮሞ ባልሆነው ሕብረተሰብ ላይ በሻሻማኔ፣ በዘዋይ፣ በአርሲ የተፈጸመውን ግፍ በማየት፣ ለህዛባችን የመኖር ዋስትና ላልሰጠ መንግሥት ላይ ጥርሳችንን ነክሰንበት የነበረው ሁሉ ለጊዜው ልዩነታችንን ወደጎን ገፍተን ከመንግሥት ጎን ተሰለፍን። የሕወሀት ጭካኔ ያንን አስጥሎን በአንድ ላይ አቆሞን ነበር። በየጊዜው ከመንግሥት በኩል የሚደረጉት አንዳንድ አስደንጋጭ ውሳኔዎች ግን ይኸንን አንደነታችንን እይሸረሸረ መሄዱ አልቀረም። በየጊዜው ለሚፈጠረው ቅሬታ መንግሥት ብቻ ነው ተጠያቂው!

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣ

ወራሪውና ጨፍጫፊው የትግራይ አሸባሪ ቡድን ይኸን አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙት ለ27 ዓመታት ዓይን ባወጣ ዘረፋ፥ በታጠቁት የጦር መሣሪያ፥ በዘረኝነት ጠበል አጥምቀው፣ ከሰውነት ወደ አውሬነት በቀየሯእው የትግራይ ተዋጊና ባካበቱት ኃብት ተማምነው ነበር “ጦር አውርድልን” እያሉ መሬቱን ሲገርፉት የነበሩት። ዓላማቸውንም ለማሳካት የያንን የመሰለ እኵይ የጦር ወንጀል ከፈጸሙ በኋል፣ ወደ አዲስ አበባ ገስግሰው ገብተው መንግሥት ገልብጠው ኢትዮጵያን በመበታተንና ታላቋን ትግራይን የመመሥረት ዓላማቸውን አንግበው ፎክረው ዘመቻቸውን ጀመሩ። ነግር ግን በመንገዳቸው ላይ ለ27 ዓመታት ረግጠው የገዙት፣ መሬቱን ቀምተው፥ መብቱን ገፈው፥ ሀብቱን ዘርፈው የጨቆኑት የአማራ ሕዝብ በጀግንነት በልዩ ኃይል ሚሊሺያውና በፋኖው ተደራጅቶ ከፊታቸው ተጋረጠባቸው። አዲስ አበባ ለመግባት ይኽን ልበ ሙሉ ጀግና ሕዝብ፥ ዳሽቆ ማለፍ ቀላል አልሆነላቸውም።

በጭካኔና ከዱር አውሬነት በባሰ ወንጀል የተደፈረው የኢትዮጵያ ህዝብም ተቆጣ። ከዳር እስከዳር ከወንድሙ የአማራው ሕዝብ ጎን ለመቆም ሆ ብሎ ወጣ።። በየቦታው ተሠማርቶ የነበረ የመከላከያ ሠራዊትም ከያለበት ተሰበሰበ። ሕይወቱን አትርፎ አምልጦ ወደ ኤርትራ ተሻግሮ የነበረውም የመከላከያ ሠራዊት ተደራጅቶ ተመለሰ። የአማራው ሕዝብ ገትሮ የያዘለትን አውሬ ለመምታት፣ ደረሰለት። የአማራው ልዩ ኃይልና ፋኖው አላሳልፍ ከማለቱም ባሻጋር ገስግሶ ከጎንደር የተቀማውን ርስቱን ተዋግቶ ወልቃይትንና ሁመራን ነጻ አወጣቸው። የወያኔ ገዳይ ቡድን መሸነፉን ሲያውቅ በማይካድራ 1,100 ንጹህ ምስኪን አማሮችን ጥቅምት 29 ቀን ላይ ጨፍጭፎ ወደ ሱዳን ፈረጠጠ። በሂደት ራያም ነጻ ወጣች። የአማራን ምድር ረግጦ ማለፍ ቀረበትና በሦስት ሳምንት ውስጥ ዕብሪተኛው የሕወሀት አመራር የጥጋብ ፊኛው ተነፈሰ። የራሱን ህዝብ እንደጅል ቆጥሮ፥ “ባጫ ደበሌን ማረኩልህ ደስ ይበልህ፥ አበባው ታደሰን ገደልኩልህ እልል በል፥ 180,000 ጦር ደመሰስክልህ” እያለው “ደቂሴ ንሬን” አንከስ እያለ አስጨፈረው። የማታ የማታ ዕውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ሆነና፥ ዋና ከተማውን ጥሎ ወደ ተንቤን ተራራ እግሬ አውጩኝ አለ። “አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣ ታላቅ ቾሎታ ነው” አለ ዘፋኙ! ተዋጊዎቹም ልብሳቸውንና መለዮአቸውን አውልቀው ከሲቪሉ ከሕዝብ ተቀላቅለው ተመሳሰሉ። ኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰነቀረባትን የሕወሀት እሾህን ነቅላ ከስቃይ የምትገላገልበት ቀን የደረሰላት መሰላት። ህዝቡ ደስ አለው። የአንድነት ጡሩምባ ከዳር እስከ ዳር ተነፋ። አኩርፎ የነበረው ውጪ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት ቆመ። የኢትዮጵያ ትንሳኤ የደረሱላት መሰለው። መከላከያው፣ ልዩ ኃይሉ፣ አመራሩን እያሳደደ የገባበት ግብቶ፥ ከተቻለ ከነሕይወቱ ይዞ፥ እምቢ ያለውን እስከወዲያኛው ሸኝቶ ሕወሀትን ታሪክ ለማድረግ ተጋድሎውን ተያያዘው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምጧ የተራዘመባት- ኢትዮጵያ! – ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ

ጉድና ጀራት ከወደ ኋላ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፥ ልዩ ኃይሉና የአማራው ወዶ ዘማች ፋኖው፥ እንዲሁም በወያኔ ርኬት ድብደባ ተጋብዘው ወደ ውጊያው የተቀላቅሉ ኤርትራውያን ተዋጊዎች ፥ በአየር ኃይሉ ተዋጊ ጄቶችና ሰው አልባ በራሪዎች (ድሮናች) በታጀበው ውጊያ የተንቤን ተራራ ጋየች። በዚያ እልህ አስጨራሽ ውጊያ 15 ገደማ የሚሆኑ፥ ስብሀት ነጋን ጨምሮ ከዋሻ እየተጎተቱ ወጡ። ወደ ዘብጥያም ወረዱ። እነ ሥዩም መስፍንና ዐባይ ጸሀይ የተባሉት የወያኔ አመራሮች ግን እጅ አንስጥም ብለው ወደማይቀርላቸው ሲኦል ተሸኙ። የኢትዮጵያ ህዝብ በከፊልም ቢሆን አንጀቱ ራሰ። የውጭ ጠላቶቻችን ቢጮሁ፥ ቢያላዝኑ፥ ኢትዮጵያ ፍንክች አላለችም። የተቀሩትን የሕወሀት አመራሮችን ማደኑ ቀጠለ። እነደብረጽዮን፥ ጻድቃን፥ ታደሰ ወረደ፥ … የመሳሰሉት በየጢሻው እየተሽሎከሎኩ እስከ ሰኔ ድረስ ከመያዝ አመለጡ።

የዓለም አቀፉ ጫና ቢበዛ፥ የምዕራቡ ዓለም ጋዜጦች፥ ቴሌቪዥኖች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የውሸት መረጃዎችን ቢለቁም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቁመው መከቱት። የአባቶቻችን የጀግንነት ወኔ የተመለሰ መሰለ። እኛም የመንግሥት ቃል አቀባዮች በጊዜው እየወጡ፣ ይኸን ያህል ተደመሰሰ፣ ይኸን ያህል ተማረከ እያሉ ሲያስረዱን፣ በኩራት ተዝናንተን፣ የቀሩትን አመራሮች የሚያዙበትን ወይም የሚወገዱብትን ዜና ስንጥብቅ በድንገት ወሽመጣችን ተቆረጠ።

ሰኔ 21 ቀን ደረሰ። የኢትዮጵያ መንግሥት ጆሮ ጭው የሚያደርግ መርዶ ተነገረን። ማንም ያልጠበቀ በጣም የከፋ ዋጋ የሚያስከፍል፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምነቱን የጣለበት የሚሸረሽር: መንግሥት  እርምጃ ወሰደ። የያዘውን ይዞ፥ የቀረውን ታንኩን፥ መድፉን፥ ዲሽቃውን፥ ብሬሉን ጥሎላቸው፥ ከትግራይ ከወጣ በኋላ ልክ ወያኔዎች እንደሚያደርጉት፣ “አሸንፌ ተመለኩ፥ ደስ ይበላችሁ ብሎ” ሊያስጨፍረን ሞከረ። “ሕወሀት ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን የሚያሰጋ ደረጃ ላይ እንደሌለች አውጆ አርፋችሁ ተኙ ተባልን። ክው አልን። ባለንበት ኩምሽሽ አልን። መንግሥት “የምንፈልገውን እያሳየን ወደበረሀ ወስዶን እዚያው ጥሎን ተመለሰ” ጉድና ጅራት ድሮም ከወደ ኋላ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ዶሮ ጮኸ።

የወሎው፥ የሰሜን ሸዋና የአፋሩ ሕዝብ ከነከብቶቹ እልቂትና መፈናቀል የማን ስህተት ነው?
ይኸን መጠየቅ ጊዜው አሁን አይደለም ልትሉኝ ትችላላችው። ለመሿሿምና ለመሸላለም ጊዜው ካመቸ፣ ዋጋ የሚይስከፍሉ ስህተቶችማ ሲሠሩ ዝም ማለት አድር ባይነት ነው። እንዳይደገም! እንዲህ ዓይነት ጥቆማ መንግሥትን ቢጠቅመው እንጂ አይጎዳውምና፣ ካድሬዎች አደብ ግዙ። ጃንሆይንም መግሥቱንም ገደል የከተታችሁት የእናንተ ዓይነቶቹ ናችሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ሊነገራቸው ይገባል።

መከላከያችን መቀሌን በድንገት ጥሎላቸው ሲወጣ፣ ባይሆን ደጀኑ የሆነውን የአማራና የአፋር ድንበር ላይ እንደመቆየት ዕድላችሁ ያውጣችሁ ብሎ ሁለቱን ሕዝብ አጋፍጦ ዞር ማለት ምን ይባላል! በዚህ ላይ አማራው እንዳይታጠቅ ላለፉት 30 ዓመታት ተፈርዶበታል። ቆይ እንጂ! ልክ አሜሪካና እንግሊዝ ናዚ ጀርመኒና ኮሙዩኒስት ራሺያ ሲተላለቁ በራሳቸው እስከሚመጣ ድረስ ዝም እንዳሉት መንግሥታችን አማራውና ትግሬው እንዲተላለቅለት አውቆ የተዋቸው አስመስሎበታል። የሕወሀት አመመራሮች በወርቅ መሶብ የቀረበላቸውን ድል ሳያስቡት ተቀብለው፣ መቀሌን በከበሮ ድለቃ ቀውጡት።  እግዚአብሔር ዘፈን ሲያምረው ማንን ነበር ያጠግባል የተባለው? ረሳሁት። የሕወሀት አመራሮች ከተሸሸጉበት ጎሬ ወጥተው፥ መሣሪያቸውን ከደበቀቡት ጉድጓድ ቆፍረው አውጥተው፥ መከላከያውም ትቶላቸው የወጣውን ዘመናዊ መሣሪያ “እናመሰግናለን” ብለው ተቀብለው፥ እንደ እባብ አፈር ልሰው ነፍስ ዘርተው፣ ወደ የዕዝ ማዕከላቸው ተመለሰሱ። የምዕራቡ ዓለም አደነቋቸው። የጦር ታክቲክና ስትራተጂአቸውንም ዕጹብ-ድንቅ አሉላቸው። የጻድቃን የጦር አመራር ብቃት በአፍሪካ ታይቶ የማይታውቅ ተብሎ ተጨበጨበለት። እነ ጌታቸው ረዳ የምዕራቢያውያን ሜዲያ ኮከብ ሁነው የጋዜጦቹን ገጽ ሞሉት። የቴሌቪዥኑንና የሬዲዮውን ሜዲያ ተቆጣጠሩት። በዚያ አላበቁም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አራት” በሁለት ሺህ አስራ አራቷ ኢትዮጵያ እይታ ሲገመገም፣

“ከአማራው ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን” በማለት፥ ሕወሀቶች አማራው ላይ ዘመቱ! ጎንደርን በከፊል፥ ወሎን መሉ በሙሉ፥ ሰሜን ሸዋ ተቆጣጥረው የደም መሬት አደረጉት። ወንዶቹ ታረዱ፥ ሴቶቹ፥ ሕጻናቱና አሮጊቶች ሳይቀሩ በተፈራራቂ የሕወህት መንጋ ተደፈሩ። ከመንግሥት ተቋም እስከ የግለሰብ ንብረት ዘረፉ፥ የቀረውን አወደሙት። ከብቶቹም ተረሸኑ። የአማራው ሚሊሺያና ፋኖ አንዳንንዴ ብቻውን ሌላ ጊዜም በመከላከያው እየታገዘ ቢዋጋም እንድ በአንድ የወሎን ትላልቅ ከተሞች፥ ላሊበላ፥ ደሴና ኮምቤልቻ ሳይቀሩ በሕወህት ቁጥጥር ሥር ወደቁ። ወያኔዎች ሸዋም ዘለቁ። ተሰምቶ የማይታወቅ ግፍና ጭፍጨፋ አደረሱ። የአንድ ቀን መዘዝ በዘጠኝ ወር ይመዘዝ ይሉሀል ይኸ ነው። ይኸ ጉድ ተሸፋፍኖ መታለፍ የሌለበት ግፍ ነው። ተመዝግቦ ይቀመጥ። የስህተቱ ምንጭ ከመቀሌ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ደጀኑንም ለቆ ማፈግፈግ፣ አማራና አፋርን ዋጋ አስከፍሏል።

ሚሌ የምትባለዋን መተላለፊያ ዘግተው የኢትዮጵያን ጉሮሮ እንዘጋለን ብለው ዝተው ማንንም አስቀይሞ በማያውቀው አፋር ህዝብ ላይ ዘመቱበት። አፋሮች ተጨፈጨፉ። ሕዝባቸው አለቀ፥ ንብረታቸው ወደመ። ጭፍራ የምትባለው ከተማቸው ወደመች። አፋሮች ግን ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነት ሚሌን ላለማስነካት በታላቅ ጀብዱ ታሪክ ሠሩ። ሕወሀቶች ሚሌን ለመያዝ እንደቋመጡ ዓላማቸው በአፋር አናብስት ከሸፈባቸው። ኪሳራ!

በወሎ ግንባር ግን ታሪኩ ሌላ ነበር። ደሴንና ኮምቦልቻን በብዙ መስዋትነት ከጨበጡ በኋላ፥ ሕወህቶች ደብረሲና ደረሱ። አዲስ አበባን ለመያዝ ቀናት ሲቀራቸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የምር ሰይፉን መዘዘ። በራሱ ደረሰአ! ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ ከተኙበት ባነኑ። ልክ ናዚ ጀርመኒ ፖላንድን መውረራቸው ሳያንስ ፓሪስን ተቆጣጥረው የእንግሊዝ ወደቦችና ከተሞችን መደብደብ ሲጀምሩ እንግሊዝ እንደባነነችው ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እራሳቸው  ታጥቀው ጦሩን ሊመሩ እንደቀድሞዎቹ መሪዎች ግንባር ገቡ። በራሳቸው መምጣቱ በጀ ልበል?! ቢዘገይም የሚደነቅ እርምጃ ነበር። የሰው ወኔው ተመለሰ። ሕዝቡ እንደገና ሆ ብሎ ወጣ። መከላከያው፥ ልዩ ኃይሉ፥ ፋኖውና አፋሩ ልዩ ኃይልና ሕዝብ በተቀናጀ መልኩ በጀግንነት፥ በቆራጥነትና በወሳኝነት፥ ወራሪ፥ ጨፍጫፊ እና ዘራፊ የወያኔ፥ ሪፍራፍ ተዋጊን መክቶ፥ ለአራት ወራት ሙሉ  እየገደሉም እየሞቱም፣ ተንፏቅቀው ተንፏቅቀው ደብረሲና የደረሱትን ጉዶች፥ በሁለት ሳምንት ከሰሜን ሸዋና ወሎ ጠራርገው፥ እንዲፈረጥጡና ሬሳቸውን እንኳን ሳያነሱ ኮረም እንዲገቡ አደረጓቸው። አፋርም ሙሉ በሙሉ ተለቀቀ። ይኸ ምንድነው የሚያሳየው? ቀድሞውኑ መንግሥት ችላ በማለት የውሎ፥ የሰሜን ሸዋና የአፋር ምድርን እንዲይዙ ዕድል ሰጥቷቸው ነው እንጂ፣ የነዚህን መሬቶች የመርገጥ አቅም ወያኔዎች ባልነበራቸው ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግባቸውን በከፊል ፈጽመው በኋላ ወደ አዲስ አዲስ አበባው ቢሮዋቸው ተመለሱ።

ጦሩ በሽሽት ላይ ያሉትን የወያኔ “እውር ድንብር” ተዋጊዎችን አባርሮ ኮሩም ደረሰ። የመቀሌ ባለሥልጣኖች ተደናብረው፣ ጓዝና ጉዝጓዛቸውን ቀርቅበው፣ ተስፋ በመቁረጥ፣ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ “አድኑን” እያሉ እየተማጸኑ፣ ወደተምቤን ተራሮች መጓጓዝ ሲጀምሩ እንደገና “ደጉ” መንግሥታቸው ነፍስ ዘራላቸው። የኢትዮጵያ ጦር አሳዶ የወያኔን አመራር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አከርካሪ ይሰብራል ብለን ስንጠብቅ፣ ወጃን እንደተቆጣጠሩ፣ አላማጣን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አንድ ቀን ሲቀራቸው፣ “ባለህበት እርጋ” የሚል ትዕዛዝ መንግሥት አስተላለፈ። እንደገና ወሽመጣችን ተቆረጠ። ወያኔ እንዳትጠፋ አልተፈለገም ማለት ነው? አውላላ ሜዳ ላይ እንደገና ተጣልን! ዶሮው ለሁለተኛ ጊዜ ጮኸ!
ሦስኛው ዶሮ!
ለሁለተኛ ጊዜ የመኖር ዕድል የተሰጣቸው የወያኔ ተዋጊዎች፥ መፈርጠጣቸውን አቁሙው አፈሙዛቸውን ወደኋላ አዞሩ። በወልቃይት ጠገዴ በኩልም ያለ የሌለውን ጦራቸው ሰብቀው ውጊያ ጀምሩ። እስካሁን አዲ አርቃይን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተቆጣጥረው፣ ጎንደሬ አማራውን እያፈናቀሉት ነው። በአፋር በኩል የአባላ ከተማን በመድፍ አያወደሙት ነው። በአላማጣ በኩል ውጊያቸውን አጧጡፈው  ዋጃና፥ ጥሙጋ የተባሉትን ከተሞች ተቆጣጥረው ወደቆቦ የምድር ክላስተር ቦምብ እይተኮሱ እየገሰገሱ ነው። ቆቦን በመድፍ ከርቀት ማጋየታቸውን ቀጥልዋል። ምስኪኑ ህዝብ፣ ከዋጃ ወደ ቆቦ ተፈናቀለ። ቆቦም መደብደብ ሲጀምር፥ ከቆቦ ወደወልዲያ እየተመሙ ነው። ከወልቃይት ጠገዴም አማራው እንደገና ተክዷል እየተባለ ሽብር እየተነዛ ነው፥ መካላከያም፥ ልዩ ኃይሉም፥ ፋኖውም ይውጣ የሚባል መመሪያ እንደተሰጠ ሹክሹታው ቀጥላል። ጭስ ካለ እሳት አለ። ከዚህ በፊት የተንሾከሾከው በሙሉ ዕውን ሁኖ የእለ? የኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የቁጣ ንግግርም ይኸንኑ አመላካች ይመስላል። አማራው እንደገና በጎንደር ቅስሙ እስኪሰበር ከተተወ ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው እንደሚባለው ለመንግሥትም ጦስ ይዞ ይመጣል። አለባበሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ይባል የለ? የሱዳን ኮሪዶር ሕወሀቶች ማስከፈት ከቻሉና እንደገና መታጠቅ ከቻሉ፣ መንግሥትንም የመግልበጥ ሕልማቸው ሊሳካ ይችላል። ጦር መሣሪያቸው አልቆ ያልጨረስናቸው፣ ሌላ አውዳሚ መሣሪያማ ከታጠቁ  ሕዝባችንን ይጭርሱና ኢትዮጵያን ወደመበታተናቸው ሁለተኛ ደረጃ እቅዳቸው ይራምደሉ። ለኃጢአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል ይባላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የ“ዓለም አቀፍ አማራ ተራድኦ ድርጅት” ምሥረታ አስፈላጊነትን በሚመለከት – ለውይይት የቀረበ

ጦርነቱ ገና አላላቀም። የምን አሸሻ ገዳሜ ነው? መንግሥት ሆይ! የጦር አማራሮቹን ጠርተህ ከምትሾምና ከምትሸልም ይልቅ፣ መጀመሪያ ጦርነቱን በድል ፈጽም! ለመሆኑ፣ መቼና ለማን ነው የማርሻልነት ማዕረግ የሚሰጠው? ጦርነቱ እስኪጠናቀቅ ፌሽታው መቆየት አይችልም ነበር? የልጅ ነገር አደረጋችሁት። የምታቦኩት ሁሉ ለራት አልበቃም!

ውጪ ኗሪው ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራው) ተጋብዞ በገፍ ወደ አገር ገብቷል። ለምን ጋበዛችሁት? በስሜት የተዘጋጀለትን ሁሉ እየጎበኘ በደስታና በጉጉት አገሩን እንዴት እንደሚረዳ፥ የወደሙትን መልሶ እንዴት አድርጎ እንደምያቋቋምለት በታላቅ ተነሳሽነት እየተመካከረበት ባለበት በዚህ ጊዜ ሌላ ዱብ ዕዳ ለምን አወረዳችሁበት? ብዙዎቻችሁን ሕወሀት ለዚህ ደረጃ አሰልጥና አሳድጋ እንዳደረሰቻችሁ እናውቃለን። ለምን ከዚያ አስተሳስብ ሰብራችሁ አትወጡም? ለምን አገራችንን ዋጋ ታስከፍሏታላችሁ? ለኢትዮጵያ እንደምታወሩት ከቆማችሁ ብሰሉ እንጂ! ከጎናችሁ የምንቆመው ስንተማመንባችሁ ነው። ስንት ጊዜ በእናንተ ላይ ያለንን እምነት ትሸረሽራላችሁ? የምነፍልገውን እያሳያችሁን ወስዳችሁ በረሀ የምትጥሉን ደነዞች አድርጋችሁ አትቁጠሩን።

እኛ የቀሩትንም የሕዋህት ባለሥልጣናት የተከፈለው መስዋዕትነት ተክፈሎ ተይዘው ለፍርድ ይቅርባሉ ብላን ስንጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዕለተ ዓርብ፣ ያውም በጌታችን የመድኃኒታችን የእየሱስን ክርስቶስ በአለ ልደት በሚከበርበት ቀን፥ ተስፋችንን አጨለሟት። በስንት መስዋዕትነት የተያዙት የወያኔ ቁንጮ መሪዎችን፣ አቶ ስብሀት ነጋን፥ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋን፥ አቶ አባይ ወልዱን፥ እቶ አባዲ ዘሙን፥ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርን እና አቶ ኪሮስ ሀጎስን በይቅርታ ፈትቼአቸዋልሁ፥ ብለውን እርፍ! ምን? ይኸን ሲያውጁ፣ ለ3ኛ ጊዜ ዶሮው ጮኸ! በደም የተበከለችው፣ በጣዕር በስቃይ ላይ ያለችው ምስኪኗ እናት ኢትዮጵያም ዕንባ ባቀረሩ ዓይኖቿ ጠቅላይ ሚኒስትሯን አየች።

10 Comments

  1. እንጨት ቁጭ ብሎ ሰው እየነደደ
    ሕግ አዋቂው ቆሞ ሌባ እየፈረደ
    አንበሳ በጅቦች እየተሳደደ
    ሰው እየተጋዘ አውሬ እየነገሰ
    ቀሳውስት ተወግዘው ሌባ እየቀደሰ
    ይሕ ሁሉ ሲሰራ መላው ጠፍቶን እኛ
    እረ ወዴት ገባህ የሰማዩ ዳኛ!!!!!!

    ገጣሚ ህሊና ደሳለ

  2. ህሊና ደሳለ በግጥም ያለቸው/ያለው እንዴት ነገርን ሁሉ ያሳያል? ይገርማል። የእኛ ሃገር የሌቦች ሃገር ናት። ለሃገራቸው ሲሉ በየበረሃው የተፋለሙ በከተማ ጩልሌዎችና የዘር ፓለቲከኞች ተጠልፈው ሲወድቁና ለወገን ለሃገር በማለት ቤትና ቤተሰብ በመተው ግፈኞችን የተፋለሙትን ወደ ጎን አድርጋ ልምጭ ይዘው ሰው ሲያሰቃዪ የነበሩት ን የምትሾም ምድር ናት። እውነት የሌለበት ምድር መሆኗ እልፍ ማሳያ ነገር ቢኖርም የታምራት ነገራና የመዓዛ መሃመድ መታገት አንድ ነው። ስብሃት ነጋንና የዘመናት ደም አፍሳሾችን በአሜሪካ ትዕዛዝ የፈታው የጠ/ሚ አብይ መንግስት ድምጽ ለሌላቸው፤ ዝንተ ዓለም በፍርድ ቤት ምልልስ ቤተሰብና እስረኛ በስቃይ ውስጥ ላሉት ማን ጠበቃ ይሁንላቸው? በኢትዮጵያ ጉዳይ አንገቴን እሰጣለሁ ያለው ጠ/ሚር በአሜሪካ ተሸውዶ አሁን ወያኔና ኦነግን እደራደራለሁ ማለቱ የሽንፈቱን ከፍታ ያሳያል። ፍጻሜ ባላገኘ ጦርነት በአዲስ አበባ አደባባይ የሚሿሿሙት እነዚህ ሰዎች ለቀጣይ ፍትጊያ እቅድና ዝግጅት ያላቸው አይመስልም። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስወግዶ በወያኔ ባንዲራ ራሱን የጠቀለለው ወያኔ እገነጠላለሁ ብሎ በዚህም በዚያም ሰው እያማታ በመሆኑ በአውሮፓ፤ በእስያ፤ በአውስትራሊያ፤ በአረብ ሃገራትና በሰሜን አሜሪካ ትግሬዎች ራሳቸውን ነጥለው ቅዳሴውን በትግርኛ፤ ስብከቱን በትግርኛ በማድረግ ልክ እንደ ሻቢያ ሃገር ነን በማለት ደፋ ቀና ይላሉ። አይ ጥቁር ህዝብ አንድ ሁን አትበለው እንጂ ለመቀጣቀጥ እማ ማን ብሎን። የተንኮላችን ማለቂያ የለውም። ሲጀመር ነገራችን ሁሉ ዲስኩር የበዛበት በመሆኑ ትላንት ያልነውን ለዛሬ አናስታውስም። መለፍለፍ ብቻ። ከእርቅ ይልቅ ጠብ፤ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፤ አብሮ ከመኖር ይልቅ በዘርና በቋንቋ ዙሪያ መዳከር እድሜ ለወያኔ መለያችን ሆኗል። የዶሮው መጮህ እንኳን ዝም ብሎ ነው። ዶሮው ሁሉ ታርዶ አልቆ የሚጮህ የለም። ሰው በሥጋ የተለከፈ ይመስል ያለ ሥጋ ምግብ ያለ የማይመስልበት ምድር ማለት ኢትዮጵያ ናት። አለኝ ያለውም የሌለውም ሥጋ ሥጋ ይላል። በዚያች ምድር ላይ ስቃይ የሚያየው ሰው ብቻ ሳይሆን የሰማይ አዕዋፍና የምድር ላይ ተርመስማሽ ጭምር ነው። ለሰው ልጅ ማዘን የሚጀምረው ተፈጥሮን በማፍቀር ነበር። ያ ግን የለም የትም እረጂው ስጋውን አምጭው ሆኗል ተረቱ ሁሉ ተለውጦ።
    በምንም አይነት ሂሳብ ቢሆን ወያኔ ሰላምን ተቀብሎ በህግ ጥላ ስር ይኖራል የሚሉ ሁሉ ሙታኖች ናቸው። ወያኔ የእድሜው መርዘም የሚታየው የሰው ደም ሲፈስ ብቻ ነው። ለዚህ ምስክሩ በጨለማ በወሎና በጎንደር፤ በሽዋ በአፋር ወስዶ የደፋቸው የትግራይ ህጻናት ልጆች ናቸው። ለትግራይ ህዝብ ጭራሽ አይገደውም። ሰላም የሚኖረው ወያኔ ከመሰረቱ ሲነቀልና የትግራይ ህዝብ በራሱ መርጫ የሚሆነውን ሲወስን ነው። ይህ የወያኔ ካድሬዎች እያሉ የማይታሰብ ነገር ነው። ጠ/ሚሩ ተሸውዷል። የሾኬ ጠለፋው አሁን ካልገባው ቆይቶ ይገባዋል። በዚህ ሁሉ አሻጥር ግን የአማራ ህዝብ ዋጋ ከፋይ መሆኑ እጅግ ይዘገንናል። በምህረት ከሥር የተፈቱት እልፍ የወያኔ ሰዎችም ጉድጓድ ከመቆፈርና ፈንጂ ከመቅበር አይገቱም። የሚያሳዝነው የተቀበረውን ፈንጂ እንኳን ለማምከን የምትረዳው አይጥ በስምንት አመቷ ማረፏን ዛሬ ሰማሁ። ሃይለኛ አነፍናፊ ነበረች። ከወያኔ ጋር እርቅ እሳት ታቅፎ እንደመተኛት ይቆጠራል። ወያኔ እያለ እርቅ ከማድረግ ትግራይን ይዘው የብቻ ሃገር ቢሆኑ ይመረጣል። በምንም ሂሳብ ለሰው ልጆች ሰላም አይሰጡም። አውሬዎች ናቸው። የአሜሪካም ድጋፍ ራሷ የአውሬ ባህሪ ስላላት ተላላኪዎቿን ትወዳለች። ሌላ ሚስጢር የለውም። በቃኝ!

  3. ውድ ወንድሜ ወንድሙ፤
    ባለፉት ከዓምሳ ዓመታት በላይ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የታወቀ መለያችን፤ ስለ በደላችን በየቀኑ እየዘረዘርን መቀመጥ ነው። ይህ አሁን በቃ!
    አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፤ በያለንበት፤ በጣም ቀላል ግልጥና ሁላችንንም በሚያሰባስብ ዓላማ ዙሪያ ለአገራችን እንቁም። ሌላው ሁሉ ለሌላ ጊዜ ይተው!
    አሁን ጥያቄው፤ በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል ካልተገፋ፤ የፈለገ ብንጽፍና ብናላዝን አያዳምጠንም። ተሰባስበን ገፊ ኃይል ስንሆን ብቻ ነው ዋጋ የሚኖረን።
    አገራችንን ለዚህ ያበቃት የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መደምሰስ አለበት።
    ኢትዮጵያ በውጪ ምንግሥታት ፍላጎትና ዕቅድ አትተዳደርም።
    የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና ይህ ድርጅት በኢትዮጵያ ያስቀመጠው ሕገ-መንግሥትና የአስተዳደር ዘይቤ ከሥሩ መመንገል አለበት።
    በቦታው ሁሉን ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት እና በያንዳንዱ ግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብት የተመሠረተ ሕገ-መንግሥት እንዲተካ ማድረግ።
    ለዚህ፣ ለሕግ የበላይነትና ለአገራችን የምንቆም መሰባሰብና በኒህ ዙሪያ ብቻ የምንችለውን ማድረግ አለብን።
    ለዚህ እኔ ዝግጁ ነኝ። ባለነብት ተቀምጠን የምንፈልገው እንዲሆን መጠበቅ ያብቃ።
    እኛ ካልሆን ማን? ዛሬ ካልሆነ መቼ?
    አስከመቼ!
    ድረገጽ አዘጋጁ ከፈቀደ ይሄው ኢሜሌ
    eske.meche@yahoo.com

  4. የተከበሩ አንዷለም፤
    ችግሩን መረዳት ወደ መፍትሔ ይመራል። ከአድዋ ድል በኋላ፥ ጠላት ለበቀል ሲዘጋጅ፥ ወገን በሰገሌ የርስበርስ ውጊያ ተጠምዶ ነበር። ጠላት ዳግም ሲመጣ የኢትዮጵያን ልሂቃን ፈጅቶ፥ መሪ አልባ አድርጎን፥ ሥነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን ተክሎብን ሄደ። በዚህ ክፍተት ውስጥ፥ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ባሕሉን፣ ሀገሩን፣ እሴቶቹን የማያውቅ፥ የሚንቅ፣ የሚጠላ፥ ሀገሬ ሀገሬ እያለ ባዶ ጩኸት የሚጮኸ ወይም ጭራሽ ያለውን ደምስሶ አዲስ ሀገር ለመፍጠር፥ ለመገንጠል የሚባዝን ትውልድ ብቅ አለ።
    ሀገርን ለማዳን፥ አስቀድሞ እንዲህ መላ ቅጡ የጠፋበትን ትውልድ ወደ በጎ ሕሊናው፣ ወደ ቀደመ ማንነቱ፣ ወደ ቀልቡ፣ ወደ ፈሪሀ እግዚአብሔር፣ ወደ ቀደመቺዋ ሃይማኖት፣ ወደ ግብረገብ መመለስ ይገ’ባል። ሰዎቹ ሲድኑ ሀገሪቱም ትድናለች። ሰዎቹ ከቀና መንገድ ሲወጡና እርስበርስ ሲጠፋፉ ወይም በመለኮታዊ ፍርድ ሲጠፉ ደግሞ ሀገር ጠፋች ይባላል። ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ብሎ አምላካችን ከዚህ ይሰውረን፤ አሜን።

    • በመለኮታዊ ሃይል ሃገርን ከወያኔ ማዳን ቢቻል ኑሮ የወልቃይትና የራያ እንባ ከ 30 ዓመት በፊት በተገታ። ችግራችን በተሰጠን ጭንቅላት ነገርን ከማመዛዘን ይልቅ አማልክቶችን ስንጠራ ቀኑ ይመሻል። ፈጣሪ በሃበሻ ፓለቲካ ጭራሽ አይገባም። በርቀት እጅን አጣጥፎ እርስ በእርሳችን አዕምሮ እንደ ሌላው እንስሳ ስንተራረድ ያያል። ሌላው ሁሉ ዝም ብሎ ጊዜ ማባከን ነው፡ ሃገርን ለማዳን የሰው ልጆች ህብረትና አንድነት አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ ነው።

    • ኢትዮጵያዊ ካገርህ ከወጣህ ቆየህ መሰል ወጣቱ ያልከው የትግሬው ወጣት መለስ ዜናዊ እኔ እስካለሁ በርትተህ ዝረፍ በርትተህ ተማር ስላለው እንዴት አድርጌ የኢትዮጵያን አጥንት ልጋጥ እንጅ እንዴት አድርጌ ኢትዮጵያን ልጥቀም የሚል ሃሳብ የለውም ቄሮ የተባለው ጉድ ደግሞ ጁዋር መሀመድ አሰልጥኖ ያዝ ሲለው ሰው መግደል ንብረት ማውደም መለስና አርብ የሰጡትን ባንዲራ ይዞ መንገላወድ ነው። ዘረፋም ስለለመደ ስራና ትምህርት አለርጅኩ ነው።ቀሪው ደግሞ መለስ ዜናው ክ10 በላይ አትማር ስላለው የማሰቢያ ህሊናዉ ባለመጥናቱ የክፉ ልማድም ተጠቂ ሁኗል እግዜር በጥበቡ መላ ካልፈጠረ ቀሪው ዘምን ጨለማ ነው።

  5. የነበረውን ችግር አሁንም እየተካሄደ ያለውን በደል መላው ኢትዮጵያዊ/ዊት ሁሉ ያውቀዋል።አናሳ እና ደካማ የንግግር ዘይቤዎችን እየመነጠሩ በሥልጣን ላይ ያሉ ባለሥጣናትን በተናጠል ስም እየጠሩ በበዳይነት ዋሻ አጉሮ ማላዘን እና በተገኘው የዜና ማሰራጫ ድሪቶ እየደረቱ መጽፉ አዋጭ አይደለም።የሚበጀው እኔስ የድርሻየን ለሀገር እና ለወገን ምን አበረከትኩ? ምንስ ላበርከት ብለን ራሳችንን ጠይቀን “አንዱ አለም ተፈራ ” እንዳለው የቆየውን ወደኋላ በመተው ተገፊ ከመሆን ገፊ ለመሆን ሁሉን ለያሰባስብ የሚችል መሰረታዊ የመፍትሄ ሃሣቦች ቢሰነዘሩ አዋጭ መንገድ ነው እላለሁ።

    • አምባው በቀለ እንዳንተ ተመሳስሎ የሚጓዝን ቀበሮና ተኩላ ማጋለጥ ቀላል ስራ አድርገኸዋል

  6. የኦሆዴድ/ ብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ ተቃዋሚ ኢትዮፕያ ዉስጥ ሊኖር አይፈልግም። አማራ እና ትግሬ ድግሞ ለስልጣኑ መቀጠል የሚያሰጉት ናቸው። በአሁኑ ግዜ ያለፈው አልፈዋል አሁን ልብ ካልገዙ። ገና የከፋ እልቂት ይመጣል። የአብይ መንግስይ ወያኔ ሲያስቸግረው ከ አማራ ጎን ፡ አምራ ሲያስቸግረው ከወያኔ ጋር እየሆነ ፡ ሁለቱ እርስ በርስ ጥርስ ሲነካከሱ ፡ ስልጣኑ ያለ ጠንካራ ተቃዋሚ ይቀይላል። ለዚህ ነው አደርቃይ በወያኔ ተይዛ ዝም ብሎ ያለው። ውልቃይትም ነገ ከወያኔ ጋር ሲታረቅ ለቆ ይወጣል። የ አማራ ሃይል አልወጣም ካለ ለውያኔ አጋፍጦት ይወጣል ከዛ በሃላ የከፋ እልቂት ይመጣል።የኤረትራው ፕረዚደንት እንደተናገረው መንግስት መከላከያ ሲያስወጣ ለኤረትራው መንግስይ አላሳወቀም። አብይ ክህደቱ የምጀምረው ከዚህ ነው። በስንት የኤርትራ ወጣት መስዋት ቀልደዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share