ለቸኮለ! ሰኞ ጥር 16/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የአማጺው ሕወሃት ታጣቂዌች ዛሬ በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ ዞን መጋሌ እና አብአላ ወረዳዎችን መልሰው በኃይል እንደተቆጣጠሩ እና በበራህሌ ወረዳ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ከሕወሃት ታጣቂዎች ጋር በአብአላ እና መጋሌ ወረዳዎች ጦርነቱ እንደቀጠለ መሆኑን እና ሕወሃት በሰላማዊው ሕዝብ ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ እያካሄደ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

2፤ የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ቦርድ የኢትዮጵያ መንግሥት በድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም ላይ ያቀረበውን አቤቱታ ላለማየት መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል። ቦርዱ ዛሬ አልወያይበትም ብሎ ወደ ጎን የገፋው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዶ/ር ቴዎድሮስ የአማጺው ሕወሃት ደጋፊ እንደሆኑ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሐሰተኛ መረጃ እንደሚያሰራጩ ጠቅሶ የድርጅቱ የበላይ ቦርድ ምርመራ እንዲያደርግባቸው ያቀረበውን አቤቱታ ነው። ቦርዱ ይህን የወሰነው፣ በዶ/ር ቴዎድሮስ ሁለተኛ ዙር የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዕጩነት ላይ ለመወያየት ዛሬ በጀኔቫ ባደረገው ስብሰባ ላይ እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል። ጉዳዩ እጅግ ውስብስብ፣ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለውና ከቦርዱ አሠራር ውጭ እንደሆነ ኬንያዊው የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ ፓትሪክ አሞት ለቦርዱ የተናገሩ ሲሆን፣ ጉዳዩን ሌላ የሚመለከተው አካል ቢያየው ይሻላል በማለት ያቀረቡትን ሃሳብ ቦርዱ ተቀብሎታል።

3፤ የፌደራል ደኅንነት እና ጸጥታ ግብረ ኃይል የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን 5 ተማሪዎችን እና 1 ነጋዴን እንዳገቱ ማስታወቁን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ግለሰቦቹን ያገቷቸው፣ ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን በተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ ሳሉ ነው። ግብረ ኃይሉ ታጋቾቹን ከታጣቂዎች ለማስለቀቅ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ አክሎ ገልጧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢትዮጵያ የጤና ተቋማት በአሸባሪው ሕወሃት ሲወድሙ የዓለም ጤና ድርጅት ዝምታን መምረጡ የሚያሳዝን ነው

4፤ አማጺው ሕወሃት በአፋር ክልል አብአላ በኩል በከፈተው አዲስ ጦርነት ሳቢያ ብቸኛው የየብስ መስመር በመዘጋቱ መንግሥት ከዓለማቀፍ አጋሮቹ ጋር በመተባበር ለትግራይ ክልል አስቸኳይ መድሃኒቶችን ማጓጓዝ እንዳልቻለ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ባወጣው መግለጫ ገጹ አስታውቋል። መንግሥት በክልሉ ተከስቷል የተባለውን የመድሃኒት እጥረት ለመቅረፍ ከተመድ እና ከዓለማቀፍ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር አስፈላጊ መድሃኒቶችንና የሕክምና አቅርቦቶችን በካርጎ አውሮፕላን ወደ ክልሉ ለማጓጓዝ መወሰኑን ሚንስቴሩ ጠቁሟል። ጤና ሚንስቴርም በዓለማቀፍ አጋሮች እጅ የሌሉ መድሃኒቶችን እና የሕክምና አቅርቦቶችን በዚሁ የካርጎ አውሮፕላን በረራ አማካኝነት ለመላክ እንደተዘጋጀ ተገልጧል።

5፤ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) በቅርቡ ይጀመራል የተባለውን አገራዊ ምክክር በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ገለልተኛ አካል እንዲመራው በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በኩል በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ግንባሩ በአገራዊ ምክክር መድረኩ የሚሳተፈው 6 ዓለማቀፍ መስፈርቶች የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟላ ብቻ እንደሆነ የገለጠው መግለጫው፣ የምክክር ኮሚሽኑ ዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ አሰጣጥ ሂደት ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ በሁሉም ስምምነት የተቀረጹ መስፈርቶች መኖር አለባቸው ብሏል። አገራዊ ምክክሩ የሚካሄድ ከሆነ የሱማሌ ክልል ሕዝብ በቅድሚያ መክሮና ዘክሮ የጋራ አጀንዳዎቹን መቅረጽ እንዳለበት የግንባሩ መግለጫ አሳስቧል። ግንባሩ ጨምሮም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የደረሰበት የሰላም ስምምነት ባግባቡ እየተተገበረ እንዳልሆነ የጠቀሰ ሲሆን፣ የሱማሌ ሕዝብ ጥያቄዎች በጊዜ ካልተፈቱ ዘግይቶ የሚፈነዳ ቦምብ ይሆናሉ በማለት አስጠንቅቋል።

6፤ የሱማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያውን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ከአሸባሪነት መዝገብ እንደሰረዘ የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የቀድሞው የሱማሊያ መንግሥት ኦብነግን ከ4 ዓመት በፊት በአሸባሪኑት መፈረጁ ሕጋዊ እንዳልነበር የሀገሪቱ ሚንስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባሳለፈው ውሳኔ ገልጧል። ከ4 ዓመት በፊት የሱማሊያ መንግሥት ሁለቱ ሀገራት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ሳይኖራቸው አብዲከሪም ሼህ ሙሴ የተባሉትን የኦብነግ አመራር ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ መስጠቱም፣ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት የጣሰ ተግባር እንደነበር ምክር ቤቱ የገለጸ ሲሆን፣ አብዲከሪም ለደረሰባቸው የመብት ጥሰትም ይቅርታ ጠይቋል። ኦብነግ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት የሱማሊያን ውሳኔ አድንቋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አስቸኳይ ጥቆማ ለኢትዮጵያ መንግስትና ኢትዮ-ቴሌኮም (እውነቱ ቢሆን)

7፤ 20 ሀገር በቀል ሲቪክ ማኅበራት በቅርቡ ይቋቋማል የተባለውን አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሚመሩ ኮሚሽነሮች መካከል ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ በጋራ መጠየቃቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ዘግቧል። በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ረቂቅ ላይ ተነስቶ የነበረው የሴቶች ድርሻ በጸደቀው አዋጅ ሳይካተት መቅረቱን ማኅበራቱ ተችተዋል። ማኅበራቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዕጩ ኮሚሽነሮችን አመራረጥ መስፈርት እና ሂደት ግልጽ እና ተዓማኒ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች በምን መስፈርት እንደሚመርጥ እስካሁን ይፋ አላደረገም።

  1. በኢትዮጵያ የታኅሳስ ወር የዋጋ ንረት ከ35 በመቶ እንዳለፈ እና በኅዳር ወር ከነበረበት በ2.1 በመቶ እንደጨመረ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ከሁለት ሳምንት በላይ ዘግይቶ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። የምግብ ዋጋ ንረቱ በኅዳር ወር ከነበረበት 38.9 በመቶ ወደ 41.6 በመቶ ያሻቀበ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ደሞ ከ25.2 በመቶ ወደ 26.6 በመቶ አሻቅቧል። በታኅሳስ ወር የተመዘገበው የዋጋ ንረት በሀገሪቱ በ10 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ሲሆን፣ ዋና ምክንያቱ በዓላት እንደሆኑ መረጃው አመልክቷል። ባንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ያለው ዋጋ በ20 በመቶ እንደወረደ የዘገበው ደሞ ብሉምበርግ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share