ለተከበራቹህ ወገኖች ያገረሸው ወረርሽኝ
የኮሮና ልምድ ከጀርመን – ፈጣኑ አራተኛው ማዕበል እና የክትባት ግዴታ 16.12.2021
ካለፈው በመቀጠል አራተኛው ማዕበል ጀርመንን እያጥለቀለቃት ይገኛል። ይህንንም አስመልክቶ አዳዲስ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። በጀርመን እና በጎረቤት አገሮች የሚመዘገበው በወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። በአለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል የተገኘው ኢንፌክሽን በአማካይ እንደገና በመጨመር ከ340 በላይ አሻቅቧል። ይህም በአለፈው ጽሁፌ ላይ መስከረም ውስጥ 263 ነበር። በአንዳንድ ወረዳዎችም ከሺ በላይም ደርሷል። የሚያዙትም በቀን በሰኔ እና በሐምሌ ከመቶዎች፣ በመስከረም ወደ 15ሺዎች ጨምሮ የነበረው በህዳር መጨረሻ ላይ እስከ 70ሺዎች በላይ በሪኮርድ ሲወጣ አሁን ውደ 50ሺዎቹ ወርዷል። ለምሳሌ በ24 ሰዓት ውስጥ 522 ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉ ተመዝግቧል። ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በጀርመን ከ6,670,407 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 5,618,600 የሚሆኑ አገግመዋል። ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 107,202 ሺ ደርሷል። በክሊኒኮች/ሆስፒታሎች ላይ ያለው ውጥረትም አልረገበም።
- ማህበርዊ ግንኙነት
ቁጥራቸው ከበዛ ሰዎች ጋር ከቤት ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር ከመገናኘት በፊት በኮሮና ቫይረስ ኢንፌክሽን አለመኖሩን ለማረጋገጥ ሙሉ በሙሉ መከተብ ወይም ማገገም መስፈርቱ ነው። ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል የተገኘው ኢንፌክሽን ከ350 ከበለጠ የሚከተሉት ገደቦች ወጥተዋል፥ አየር በሚያስተላልፉ በቤት ውስጥ አዳራሾች ውስጥ ለሁሉም ክስተቶች የተከተቡ እና ያገገሙ የሚለው ደንብ የጸና ነወ። በቤት ውስጥ የሚፈቀደው ቢበዛ 50 ሰዎች ሲሆኑ ይህም ሙሉ በሙሉ ለተከተቡ ወይም ላገገሙ ብቻ ነው የሚፈቀደው። ከቤት ውጭ የግል ስብሰባዎች በአጠቃላይ የተሳታፊዎች ቁጥሩ ከ200 በላይ ማለፍ የለበትም ይህም ከሆነ ሙሉ በሙሉ ለተከተቡ ወይም ላገገሙ ብቻ ነው የሚፈቀደው።
- የተከተቡ ወይም ያገገሙ የ2„ጂ“ ደንብ
በብዙ ከተማዎች፣ ወረዳዎች የተከተቡ ወይም ያገገሙ የ2ጂ (Geimpfte und Genesene / Vaccinated and Recovered) ደንብ የጸና ነው። ይህ ማለት ምግብ ቤቶች፣ የቲያትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ሙዚየሞች፣ የመዋኛ ቦታዎች፣ የአካል ብቃት ማዕከላት፣ የውስጥ ክፍሎች፣ የተወሰኑ የመዝናኛ ቦታዎችን ወዘተ መግባት የሚፈቀድላቸው ክትባቱን የወሰዱ እና ያገገሙ ብቻ ነው። በክሊኒኮች፣ በሆስፒታሎች በቤተ አረጋውያን እና የመሳሰሉት ቦታዎች የሚሰሩት ከክትባት በተጨማሪም በየጊዜው መመርመር ይኖርባቸዋል። በህክምና ወይም በጤንነት ምክንያቶች በተረጋገጠ መስፈርት መከተብ ያልቻሉ ሰዎች 2G በሚተገበርበት ቦታ ላይ ዕለታዊ አሉታዊ የናሙና ምርመራ ውጤት ማቅረብ ያስፈልጋቸዋል። የዕለት ዕለት ችርቻሮ ዘርፉን የ2ጂ ደንብ እስካሁን ድረስ አይመለከተቸውም። በህዝብ ማመላለሻዎች ለመገልገል የሚችሉት የተከተቡ ወይም ያገገሙ ወይም የቀን ምርመራ ውጤት ያቀረቡ ናቸው።
- የክትባት ግዴታ
ቻንስለር አንጄላ ሜርክልን በመተካት ባለፈው ሳምንት አዲሱ መራሂ መንግስት የሆኑት እና ከሶሻል ዴሞክራቶች፣ ከአረንጓዴ እና ሊበራሎች ጋር በመሆን የሶስትዩሽ የጥምር መንግስት ያቋቋሙት ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝም ሆነ አጋሮቻቸው ከምርጫ በፊት „የክትባት ግዴታ የለም፣ ሎክዳውንም ተመልሶ አይመጣም“ ብለው የነበሩ ሲሆን አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ የክትባት ግዴታን በመወሰናቸው ፈታኝ ሆኖባቸዋል። የጀርመን ፓርላም የኢንፌክሽን ህግን በማሻሻል ታካሚዎች እና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን ከኮቪድ 19 ኢንፌክሽን በተሻለ ለመከላከል በማለት በጤና እና እንክብካቤ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሰራተኞች እና እንደየስራው ባህሪይ የሚመለከታቸው የመከተብ ግዴታ እንዳለባቸው ወስኗል። ይህ በልዩ ጤንነት ምክንያት መከተብ የማይችሉትን አይመለከትም።
- ኮሮና፣ ቴሌግራም እና ወንጀል
አዲስ የተሾሙት የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሯ እንደገለጹት በሀሰት መርጃ ላይ በተመረኮዘ፣ ፀረ-ኮሮና እና የቀኝ አክራሪዎችን እንቅስቃሴ ያያዙ ከ100ሺ በላይ ተከታዮች ያለው የተለያዩ ግሩፖችን የያዘውን ቴሌግራም የሚሰኘው የመልዕእክት ማስተላለፊያ ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጽዋል። በተጨማሪም ከኮሮና ክትባት ጋር በተያያዘ መልኩ በቅርቡ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ግለሰቦች የማስፈራራት ደብዳቤ የደረሳቸው ሲሆን የጀርመን ፖሊስም ይህንን መከታተል ጀምሯል። የኮሮና ክትባት ሳይወስዱ ግን እንደተከተቡ አድርጎ የሚያሳይ የሀሰት መታወቂያ የሚይዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል። በዚህም የተነሳ ሳይከተቡ እንደተከትቡ አድርገው የተጭበረበረ የኮሮና ክትባት መታወቂያ ካርድን ለሚጠቀሙ እስከ 5 አመት በእስራት እንዲቀጡ ህግ እየረቀቀ ነው።
- ኮሮና እና የመኪና አደጋ
ዓመታዊው የትራፊክ አደጋ አሀዝ መመዝግብ ከጀመረበት 65 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው የትራፊክ ሞት በዚህ ዓመት ተመዝግቧል። በጀርመን 2021 በመንገድ አደጋዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመቀነስ ወደ 2450 ወርዷል። ለዚህ ምክንያቱ በዋነኛነት በኮሮና ቫይረስ እና በተደረገው የሎክዳውን እርምጃ የእንቅስቃሴ መገደብ ነው።
- የሌላ አገር ልምዶች
በኦስትሪያ ላልተከተቡት ከወራት በፊት የነበረ የሎክዳውን ገደብ ተመልሶ ተጥሎባቸዋል። ያልተከተቡ ሰዎች የራሳቸውን የመኖሪያ አካባቢ እንዲለቁ የሚፈቀድላቸው ለተወሰኑ ቦታዎች (ሥራ፣ ትምህርት፣ የዕለት ተለት ፍጆታ ዕቃዎችን ለመግዛት፣ ወዘተ) ብቻ ነው። ከመሸም የሰዓት እላፊ ገደብ ይመለከታቸዋል። ታላቋ ብሪታንያ የማጠናከሪያ ክትባት ዘመቻዋን እያፋጠነች ነው። በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ የክትባት ማዕከሎች እና ክሊኒኮች ፊት ለፊት ከፍተኛ ወረፋዎች ነበሩ።
- ራስን ለይቶ መቀመጥ (ኳራንቲን) የሚያስገቡ ሀገሮች
የኮሮና ስርጭት ያልተገደበባቸው እና የልውጡ ተህዋሲ ከተስፋፋባቸው ሀገሮች የሚመጣ ወይም ጎብኝቶ የሚመለስ ሰው እስከ 10 ቀን የሚደርስ ኳራንቲን አሁንም ቢሆን ይገባል። የልውጡ ከፍተኛ ተላላፊ ተህዋሲ ኦሜክሮን(Omicron) አለባቸው የተባሉት አገሮች ላይ እንደ ቦትስዋና፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሶቶ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ ሲጠብቅ በደቡብ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ላይ ግድበት ተደርጓል። ከታች በተጠቀሱት ከፍተኛ ተጋላጭ በሆነ አካባቢ የቆዩ ያልተከተቡ ሰዎች ጀርመን ከደረሱ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ቤታቸው በመሄድ እና ለአሥር ቀናት በቤት ውስጥ ራስን ለይተው መቆየት አለባቸው። የክትባት ማረጋገጫ ወይም አሉታዊ የምርመራ ውጤት ያቀረበ ሰው በቤት ውስጥ ያለውን ገለልተኛነት አይመለከተውም ወይም አስቀድሞ ያለጊዜው ሊጨርስ ይችላል። እነዚህ ሀገሮች ኢትዮጵያን አካትቷል፣ ሀገሮቹም ፦
ግብፅ፣ አልባኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ባርባዶስ፣ ቤላሩስ፣ ቤልጂየም፣ ቤሊዝ፣ ቦስኒያ እና ሄርዞጎቪና፣ ቡልጋሪያ፣ ቡሩንዲ፣ ዶሚኒካ፣ ኢስቶኒያ፣ ጆርጂያ፣ ግሪክ፣ ሃይቲ፣ አየርላንድ፣ የመን፣ ዮርዳኖስ፣ ካሜሩን፣ ኮንጎ፣ ኮሪያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ክሮኤሺያ፣ ላኦስ፣ ላቲቪያ፣ ሊቢያ፣ ሊችተንስታይን፣ ሊቱዌኒያ፣ ማሌዥያ፣ ሞሪሸስ፣ ሜክሲኮ፣ ሞልዶቫ፣ ሞንቴኔግሮ ሪፐብሊክ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሰሜን መቄዶኒያ፣ ኦስትሪያ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ፖላንድ፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ስዊዘርላንድ፣ ሰርቢያ፣ ሲሼልስ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬንያ፣ ሱዳን፣ ሶሪያ አረብ ሪፐብሊክ፣ ታጂኪስታን፣ ታንዛኒያ፣ ትሪንዳድ እና ቶቤጎ፣ ቼክ ሪፖብሊክ፣ ቱርክ፣ ቱርክሜኒስታን፣ ዩክሬን፣ ሃንጋሪ፣ ቬንዙዌላ፣ ቦሊቫሪያን ሪፐብሊክ፣ ዩናይትድ ኪንግደም የታላቋ ብሪታንያ እና የሰሜን አየርላንድ፣ ቬትናም
- የክትባት ይዘት
3,63 ቢሊዮን (46,6 %) የአለማችን ህዝብ ሲከተብ፣ አፍሪካ እስካሁን ከ10% በታች ብቻ ሰው ነው ሁለት ጊዜ የተከተበው። ለቁጥር ያህል ጀርመን 58.2 ሚሊዮን (69.9%)፣ ቻይና ወደ 1.16 ቢሊየን (82%)፣ ሕንድ 530 ሚሊዮን (38.8%) ፣ ዩናይትድ ስቴትስ 201 ሚሊዮን (61.1%)፣ ብራዚል 141 ሚሊዮን (66.3%)፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ 9.02 ሚሊዮን (91.2%) ሲከትቡ ከአፍሪካ ለመጥቀስ ሞሮኮ 22,9 ሚሊዮን (62%) ደቡብ አፍሪካ 15.5 ሚሊዮን (26.1%)፣ ኢትዮጵያ 10,5 ሚሊዮን ክትባቶች በማቅረብ 1,45 ሚሊዮን ሰዎች (1.3%) ሁለት ጊዜ ደግመው ተከትበዋል።
ጀርመንን ጨምሮ በብዙ አገሮች ሁለት ጊዜ ተከትበው ስድስት ወር ላለፋቸው ሶስተኛ የማጠናከሪያ ክትባት መስጠት COVID booster shots የሚወስዱት እኔንም ጨምሮ እየተበራከተ መጥቷል። የጀርመን የክትባት ኮሚሽን STIKO ሁለተኛውን ክትባትን ወስደው 5 ወር የሆናቸው በሙሉ ማጠናከሪያ እንዲወስዱ የሚመክረ ማሻሻያ አውጥቷል።
- የወረርሽኙ ማገርሸት
ለወረርሽኙ ማገርሸት ምክንያት የሚጠቀሱት በቁጥር 18 የጠቀስኩ ሲሆን አዲስ የመጣው ኦሜክሮን የተሰኘው ልውጥ ለወረርሽኙ የተሰጠውን ክትባት ሊቋቋም ይችላል በሚለው ስጋት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰሙ እና ምርምሮች እየተደረጉ ነው።
ከመልካም የጤንነት እና የሰላም ምኞት!
“አንድ ሰው ሊያገኘው የሚችለው የሚያምር ሐውልት በተግባሩ በሚወዱት ሰዎች ልብ ውስጥ ነው”
– አልበርት ሽዌይዘር
ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)